የአንባብያን ጥያቄዎች
እንደ ደረቅ ፕላዝማ ያሉ የደም ተዋፅዖዎች በምግብ ውጤቶች ውስጥ ተጨምረው ሊሆን ይችላል የሚለው ስጋት ክርስቲያኖችን ምን ያህል ሊያሳስባቸው ይገባል?
የእንስሳት ደም (ወይም ተዋፅዖው) በአካባቢው በሚገኙት የምግብ ውጤቶች ውስጥ በእርግጥ እንደሚጨመሩ የሚያሳምን ተገቢ መሠረት ካለ ክርስቲያኖች አግባብ ያለው ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባቸዋል። ቢሆንም በጥርጣሬ ብቻ መሸበር ወይም መሠረት በሌለው ጭንቀት ውስጥ መኖር ጥበብ አይደለም።
በሰው ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ ፈጣሪያችን የሰው ልጆች ደም መብላት እንደማይገባቸው ሕግ አውጥቷል። (ዘፍጥረት 9:3, 4) ደም የእርሱ ስጦታ የሆነውን ሕይወትን እንደሚወክል ገልጿል። ከአንድ ፍጡር የወጣ ደም በመሠዊያው ላይ ለሚደረግ መሥዋዕት ብቻ ለመጠቀም ይቻላል። አለበለዚያ ከአንድ ፍጡር የወጣ ደም በመሬት ላይ ሊፈስስ ይገባዋል። ይህም ደሙን ለአምላክ እንደ መመለስ ያህል ነው። ሕዝቦቹ ደምን በመውሰድ ሕይወታቸውን ከማቆየት ሊቆጠቡ እንደሚገባቸው ገልጾላቸው ነበር። አምላክ “የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ” በማለት ደንግጎ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:11-14) ደም መብላትን የሚከለክለው የአምላክ ሕግ ለክርስቲያኖችም በድጋሚ ተነግሯቸዋል። (ሥራ 15:28, 29) ስለዚህ የጥንት ክርስቲያኖች ከታነቁ እንስሳት ሥጋ ወይም ደም ያለባቸውን ምግቦች ከመብላት መቆጠብ አስፈልጓቸው ነበር።
ሆኖም ተግባራዊ በሆነ አባባል ክርስቲያኖች ‘ከደም ለመራቅ’ ያላቸውን ቁርጥ ውሳኔ እንዴት ይሠሩበት ነበር? (ሥራ 21:25) “በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ” በሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ብቻ ይመሩ ነበርን?
አልነበረም። በ1 ቆሮንቶስ 10:25 ላይ የሚገኙት ቃላት የሚያመለክቱት በጣዖት ቤተ መቅደስ ተሠውቶ ሊሆን ስለሚችል የእንስሳ ሥጋ ነው። በዚያ ጊዜ ከጣዖት ቤተ መቅደስ የሚተራርፈውን ሥጋ ለነጋዴዎች በመሸጥ ያስወግዱት ነበር። እነሱም ለሽያጭ ከሚያቀርቡት በሉካንዳቸው ውስጥ ካለው ሌላ ሥጋ ጋር ይቀይጡት ይሆናል። የጳውሎስ ነጥብ ከጣዖቱ ቤተ መቅደስ የሚወጣው ሥጋ መጥፎ ወይም የተመረዘ እንዳልሆነ የሚገልጽ ነው። የእንስሳውን ደም ማፍሰስና ደሙን በጣዖቱ መሰዊያ ላይ ለመስዋዕት ማቅረብ የተለመደ ነገር ይመስላል። ስለዚህ ከተረፈው ሥጋ ጥቂቱ ከቤተ መቅደሱ ወይም ከአረመኔዎች የተሳሳተ እምነት ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ በገበያ ላይ ቢሸጥ ክርስቲያኖች ልክ ለሽያጭ እንደሚቀርብ ንጹሕና በተገቢው ሁኔታ ደሙ የፈሰሰለት ሥጋ አድርገው ሊገዙት ይችሉ ነበር።
ይሁን እንጂ እነዚያ ክርስቲያኖች በአካባቢው ካሉት ሉካንዳዎች በአንዱ ውስጥ የሚሸጠው ሥጋ ከታነቀ እንስሳ (ወይም በደም የተሠራ ምግብ) እንደሆነ የሚያውቁ ከሆነ ሁኔታው የተለየ ይሆናል። የሚገዙትን ሥጋ በመምረጥ በኩል ጥንቃቄ ያስፈልጋቸው ነበር። ደም የያዙት የሥጋ ውጤቶች የተለየ ቀለም ያላቸው ከሆነ እነዚህን ለመለየት ይችሉ ይሆናል። (በዛሬውም ጊዜ ከደም የተሠራ ምግብ የተለመደ በሆነባቸው አገሮች ብዙውን ጊዜ በቀለሙ ሊለይ ይችላል።) ወይም ክርስቲያኖች ጥሩ ስም ያለውን ሉካንዳ ቤት ወይም የሥጋ ነጋዴ ሊያጠያይቁ ይችሉ ይሆናል። አንድን ሥጋ ደም ይኖረዋል ብለው ለማመን የሚያስችላቸው ምንም ምክንያት ከሌለ በቀላሉ ገዝተው ሊበሉት ይችላሉ።
በተጨማሪም ጳውሎስ “ገርነታችሁ [ምክንያታዊነታችሁ አዓት] ለሰው ሁሉ ይታወቅ” በማለትም ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ይህ ምክር ሥጋ በመግዛትም ጉዳይ ላይ ሊሠራ ይችላል። የእስራኤላውያን ሕግም ሆነ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአስተዳደር አካል ድንጋጌ የአምላክ አገልጋዮች ስለ ሥጋ በማጠያየቅ ብዙ ጊዜና ሰዓት ማጥፋት እንዳለባቸው ወይም በሥጋው ውስጥ ደም ይኖር ይሆናል የሚል ትንሽ ጥርጣሬ ካላቸው አትክልትን ብቻ የሚመገቡ መሆን እንዳለባቸው አያመለክትም።
አንድን እንስሳ የገደለ እስራኤላዊ አዳኝ ደሙን ያፈስሰው ነበር። (ከዘዳግም 12:15, 16 ጋር አወዳድር።) ቤተሰቡ ሁሉንም ሥጋ መብላት ካልቻለ ጥቂቱን ይሸጠው ይሆናል። በትክክል ደሙ ፈስሶ የሞተ እንስሳ እንኳን ሥጋው ውስጥ ጥቂት ደም ይቀራል። ይሁን እንጂ ሥጋ የሚገዛ አይሁዳዊ እንስሳው ከሞተበት ደሙ እስከ ፈሰሰበት ጊዜ ድረስ ምን ያህል ደቂቃዎች እንደቆየ እና ደሙን እንዲፈስ ለማድረግ የትኛው ደም ቅዳ ወይም ደም መልስ እንደ ተቆረጠ እንዲሁም እንስሳው ተንጠልጥሎ የነበረው በእንዴት ዓይነት ሁኔታና ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እስከ መጠየቅ ድረስ መሄድ እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው ምንም ነገር የለም። ከዚህም በተጨማሪ የአስተዳደር አካሉ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ሥጋ ከመብላታቸው በፊት በዚህ በኩል በጣም ዝርዝር የሆኑና የማያጠራጥሩ መልሶች የሚያስፈልጓቸው ይመስል አስቀድመው የሚደረጉ ያልተለመዱ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ አልጻፈም።
በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ሕጉ፣ ልማዱ ወይም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሥጋ ውጤቶች (እምብዛም እንዳልተለመዱት ከደም እንደሚሠሩት ምግቦች ያሉ ካልሆኑ በስተቀር) በሚታረዱበት ጊዜ ደማቸው ከፈሰሰላቸው እንስሳት የሚገኙ ናቸው። ስለዚህ በእነዚያ አካባቢዎች የሚኖሩ ክርስቲያኖች በአስተራረዱ ወይም በምግቡ አሠራር ሂደት ላይ ከሚገባው በላይ መጨነቅ አያስፈልጋቸውም። ይህን አባባል ሰፋ በማድረግ ለሌሎች ጉዳዮችም ስንጠቀምበት ‘በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ . . . ሳይመራመሩ ሊበሉና’ ከደም እንደራቁ ተሰምቷቸው ንጹሕ ሕሊና ሊኖራቸው ይችላል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖችን እንዲረበሹ ያደረጉ ደምን በንግድ መጠቀምን የሚመለከቱ ቴክኒካል የሆኑ ዘገባዎች አሉ። በሥጋ ማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ የንግድ ሰዎች ከሚታረዱ እንስሳት የሚፈሰው በጣም ብዙ ደም ተጠራቅሞ እንደ ማዳበሪያና የእንስሳት ምግቦች ላሉ ትርፍና ጥቅም ለሚያስገኙ ነገሮች ሊውል እንደሚችል ይናገራሉ። ተመራማሪዎች ደም (ወይም የደም ተዋፅዖዎች) በታሸጉ ሥጋዎች ውስጥ ይጨመሩ ወይስ አይጨመሩ በሚለው ጥያቄ ላይ ምርምር አካሂደዋል። ጥቂት የንግድ ፋብሪካዎች እንደ ቋሊማ ላለ ወይም ለተፈጨ ሥጋ መተኪያ የሚሆን ጥቂት ፐርሰንት ፈሳሽ፣ በረዶ ውስጥ የቆየ ወይም ደርቆ ዱቄት የሆነ ፕላዝማ (ወይም ቀለም እንዳይኖረው የተደረገ የቀይ የደም ሴል አካልን) እንደሚጨምሩ ታውቋል። ሌሎች ጥናቶችም በተፈጨ ሥጋ፣ በዳቦ ውስጥ፣ ለማሟያነት ወይም ውኃንና ስብን ለማያያዝ ሲባል ወይም በሌሎች ምግቦች ወይም መጠጦች ውስጥ ፕሮቲን ወይም ብረት ለመጨመር ሲባል ዱቄት የሆኑ የደም ውጤቶችን እንደሚጠቀሙ ለይተው አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ምርምሮች ለአሥርተ ዓመታት ሲካሄዱ መቆየታቸው ትኩረት የሚያሰጠው ነው። ሆኖም እንዲህ ባሉት ምርቶች መጠቀም በብዙ አገሮች በጣም ውስን ወይም እንዲያውም የሌለ ነገር ነው። አንዳንድ ዘገባዎች ይህ ለምን እንደሆነ ለማሳየት ይረዳሉ፦
“ደም ለግንባታና ለሥራ ጠቃሚነት ያላቸው ፕሮቲኖች ምንጭ ነው። ይሁን እንጂ የቀንድ ከብቶች ደም በደማቅ ቀለሙና በተለየ ጣዕሙ የተነሣ በቀጥታ ለሰው ምግብነት ጥቅም ላይ የዋለው በተወሰነ መጠን ብቻ ነው።”—ጆርናል ኦፍ ፉድ ሳይንስ፣ ጥራዝ 55፣ ቁጥር 2፣ 1990
“የደም ፕላዝማ ፕሮቲን በኃይል እንደ መሟሟት፣ ስብን እንደ ማዋኃድ እና ውኃን እንደ ማስወገድ ያሉ ጠቃሚ ባሕርያት አሉት። . . . እነዚህም ምግብን በማሸግ ሂደት ውስጥ ትልቅ ጥቅም ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ ፕላዝማን በተለይም ውኃው ከወጣለት በኋላ የሚያጣራ ውጤታማ የሆነ ሥርዓት በጃፓን ውስጥ አልተቋቋመም።”—ጆርናል ኦፍ ፉድ ሳይንስ፣ ጥራዝ 56፣ ቁጥር 1፣ 1991
ብዙ መንግሥታት በታሸጉ ምግቦች ስም ላይ የተሠሩባቸው ቅመማ ቅመሞች በዝርዝር እንዲጻፉ ስለሚጠይቁ አንዳንድ ክርስቲያኖች አልፎ አልፎ በታሸጉ ምግቦች ላይ ያሉትን ጽሑፎች ያነባሉ። ደም ይኖራቸው ይሆናል ብለው ለመጠራጠር ምክንያት ካላቸው በእነዚህ ምግቦች ማሸጊያ ላይ ያለውን ጽሑፍ ለማንበብ ይመርጡ ይሆናል። ደም፣ የደም ፕላዝማ፣ ግሎቢን (ግሎቡሊን) ፕሮቲን ወይም የሂሞግሎቢን (ወይም የግሎቢን) ብረት እንዳለባቸው የተዘረዘረባቸውን የምግብ ውጤቶች ማስወገዱ ተገቢ ነው። ከአንድ የአውሮፓ ኩባንያ በዚህ መስክ የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸው፦ “ተጠቃሚው ምግቡ ስለተቀመመባቸው ነገሮች ወይም ስለ ይዘቱ እንዳይሳሳት ግሎቢንን እንደ ቅመም ተደርጎ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚመለከት መረጃ በምግቡ ማሸጊያ ላይ ሊገለጽ ይገባል።”
ይሁን እንጂ በእሽጉ ላይ ያሉትን ጽሑፎች በማንበቡ ወይም የሉካንዳዎችን ሁኔታ በማጠያየቁ ረገድ ምክንያታዊነት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን በታሸጉ ምግቦች ላይ የተጻፉትን ጽሑፎችና ቅመማ ቅመሞች ማጥናት መጀመር ወይም በምግብ ቤቶች ወይም በምግብ መሸጫ መደብሮች ያሉትን ሠራተኞች መጠየቅ ይገባዋል ማለት አይደለም። በመጀመሪያ አንድ ክርስቲያን ‘በዚህ አካባቢ ወይም አገር ውስጥ ደምና የደም ተዋፅዖዎች በማንኛውም የምግብ ውጤቶች ላይ እንደሚጨመሩ የሚያሳዩ የተረጋገጡ ማስረጃዎች አሉን?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበት ይሆናል። በብዙ ቦታዎች መልሱ የሉም ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች በግላቸው ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ በርቀት ያሉ ነገሮችን ለመመርመር ብዙ ጊዜና ትኩረት ላለማጥፋት ደምድመዋል። የዚህ ዓይነት ሁኔታ የማይሰማው አንድ ሰው በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና ኖሯቸው ነገሩ ምንም እንዳልሆነ በሚሰማቸው በሌሎች ላይ ሳይፈርድ ከሕሊናው ጋር የሚስማማ ነገር ሊያደርግ ይችላል።—ሮሜ 14:2-4, 12
ምንም እንኳን ደም የያዙ የምግብ ውጤቶች ሊመረቱ የሚችሉ ቢሆንም ይህ በወጪው፣ በሕግ ወይም በሌሎች ነገሮች ምክንያት በስፋት አይሠራበትም። ለምሳሌ ያህል ፉድ ፕሮሰሲንግ (መስከረም 1991) እንዲህ ብሏል፦ “ውኃው ከተለየለት የቀንድ ከብት ፕላዝማ (ካለቀለት የተፈጨ ሥጋ ውስጥ) 1% በታች ለመቀየጥ ችግር ላለባቸው ለብዙዎቹ ምግብ የሚያሽጉ ፋብሪካዎች ከአጓት የሚገኘውን የተከማቸ ፕሮቲን እንደ አማራጭ አድርገው በመቀየጥ ይተኩና በአይሁዳውያን ሕግ መሠረት ለመበላት የሚቻል ሥጋ ያደርጉታል።”
በብዙ አገሮች ያለው ሕግ፣ ልማድ ወይም ምርጫ እንስሳት ሲታረዱ ደማቸው እንዲፈስ የሚያዝ ሲሆን ደሙን ከሌሎች ምግቦች ጋር ቀላቅሎ መጠቀምን ይከለክላል። በአካባቢያችሁ ያለው ሁኔታ የተለየ እንደሆነ እንድታስቡ የሚያደርግ ወይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዐቢይ ለውጥ እንደተፈጸመ የሚያሳይ ምንም የተጨበጠ መሠረት ከሌለ ክርስቲያኖች ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ወይም በወሬ ከመረበሽ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ሆኖም ደም በምግብም ይሁን በሕክምና ውስጥ በስፋት እንደሚጠቀሙበት በእርግጠኝነት ከታወቀ ከደም እንድንርቅ ከአምላክ የተሰጠንን ትዕዛዝ ለመታዘዝ መቁረጥ ይኖርብናል።