የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 12/1 ገጽ 12-17
  • “አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ መምጣት
  • የማጥራት ሥራ
  • ቁርባኖችና አሥራቶች
  • ምንም እስከማይጎድል ድረስ መባረክ
  • የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሥራት ምን ይላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • የይሖዋን ውለታ እንዴት ልንመልስ እንችላለን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የሚልክያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 12/1 ገጽ 12-17

“አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ”

“የሰማይን መስኮት ባልከፍትላችሁ . . . በዚህ ፈትኑኝ።”—ሚልክያስ 3:10

1. (ሀ) በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ ለሕዝቡ ያቀረበው ምን ግብዣ ነበር? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ ለፍርድ መምጣቱ ምን ውጤት አስከተለ?

በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እሥራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ ሆነው አልተገኙም። አሥራትን ከመክፈል ትቆጥበውና እንከን ያለባቸውን እንስሳት ቁርባን አድርገው ያመጡ ነበር። ሆኖም አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ ካገቡ ምንም እስከማይጎድላቸው ድረስ በረከቱን እንደሚያዘንብላቸው ይሖዋ ቃል ገብቶ ነበር። (ሚልክያስ 3:8-10) 500 ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ ይሖዋ የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ በሆነው በኢየሱስ ወኪልነት በኢየሩሳሌም ወደነበረው ቤተ መቅደስ ለፍርድ መጣ። (ሚልክያስ 3:1) እሥራኤላውያን በሕዝብ ደረጃ ችግረኞች ሆነው ተገኙ፤ ወደ ይሖዋ የተመለሱት ግለሰቦች ግን በብዙ ተባርከው ነበር። (ሚልክያስ 3:7) የይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች፣ አዲስ ፍጥረት የሆኑ “የእግዚአብሔር እሥራኤል” ለመሆን ተቀቡ።—ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 3:25, 26

2. ሚልክያስ 3:1-10 ሁለተኛ ፍጻሜ ያገኘው መቼ ነበር? ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ምን እንድናደርግ ተጋብዘናል?

2 ከዚያ ወዲህ 1,900 ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ በ1914 ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ንጉሥ በመሆን በዙፋን ላይ ተቀመጠ። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የሚልክያስ 3:1-10 ቃላትም ሁለተኛ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ከዚህ አስደሳች ሁኔታ ጋር በተያያዘ መንገድ በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራው እንዲያገቡ ተጋብዘዋል። እኛም እንዲህ ብናደርግ ምንም እስከማይጎድለን ድረስ በረከቶችን እናገኛለን።

3. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን (ለ) ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በፊት በይሖዋ ፊት መንገድን ያስተካከለው መልእክተኛ ማን ነበር?

3 ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ መምጣቱን በተመለከተ “እነሆ፣ መልእክተኛዬን እልካለሁ፣ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል” ብሏል። (ሚልክያስ 3:1) የዚህ ትንቢት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜ በመሆን ዮሐንስ መጥምቁ ለኃጢአት ንስሐን እየሰበከ ወደ እሥራኤል መጥቶ ነበር። (ማርቆስ 1:2, 3) ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ ለሁለተኛ ጊዜ ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ አስቀድሞ የሚሠራ ሥራ ነበርን? አዎ። ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በፊት ከነበሩት አሥርተ ዓመታት አስቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ንጹሑን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርት እያስተማሩና እንደ ሥላሴና የሲኦል እሳት የመሳሰሉትን አምላክን የሚያዋርዱ ሐሰቶች እያጋለጡ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ አሉ። የአሕዛብ ዘመን በ1914 እንደሚያልቅም አስጠነቀቁ። ብዙ ሰዎችም ለእነዚህ የእውነት ብርሃን አብሪዎች አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ።—መዝሙር 43:3፤ ማቴዎስ 5:14, 16

4. በጌታ ቀን መልስ ማግኘት ያለበት ምን ጥያቄ ነበር?

4 1914 መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታ ቀን” ብሎ የሚጠራውን ዘመን ያስጀመረ ዓመት ሆነ። (ራእይ 1:10) በዚህ ዘመን የ“ታማኝና ልባም ባሪያ”ን ማንነት ለይቶ ማወቅንና የእርሱን ‘[በጌታው ንብረቶች ሁሉ ላይ] መሾሙን’ ጨምሮ ዓበይት ሁኔታዎች ሊፈጸሙ ቀርበው ነበር። (ማቴዎስ 24:45-47) ያኔ በ1914 በሺዎች የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቲያኖች ነን ይሉ ነበር። ታማኝና ልባም ባሪያ መሆኑ በጌታው በኢየሱስ ክርስቶስ ተቀባይነት የሚያገኝ የትኛው ቡድን ይሆን? ይህ ጥያቄ መልስ የሚያገኘው ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ ነበር።

ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ መምጣት

5, 6. (ሀ) ይሖዋ ለፍርድ የመጣው ወደ የትኛው ቤተ መቅደስ ነበር? (ለ) ሕዝበ ክርስትና ከይሖዋ የተቀበለችው ፍርድ ምንድን ነው?

5 ይሁንና ይሖዋ የመጣው ወደ የትኛው ቤተ መቅደስ ነበር? ቃል በቃል በኢየሩሳሌም ወደነበረው ቤተ መቅደስ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በኢየሩሳሌም ከተሠሩት ቤተ መቅደሶች የመጨረሻው በ70 እዘአ ተደምስሶ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ጥላ የሆነለት የበለጠ ቤተ መቅደስ አለው። ቅድስተ ቅዱሳኑ በሰማይ፣ አደባባዩ ደግሞ በምድር የሆነው ይህ ቤተ መቅደስ የቱን ያህል ታላቅ መሆኑን ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብራውያን 9:11, 12, 24፤ 10:19, 20) ይሖዋ ለፍርድ ሥራ የመጣው ወደዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነበር።—ከራእይ 11:1፤ 15:8 ጋር አወዳድር።

6 ይህ የሆነው መቼ ነበር? በተገኘው ተጨባጭ ማስረጃ መሠረት በ1918 ነበር።a ውጤቱስ ምን ነበር? ሕዝበ ክርስትናን በተመለከተ እጆቿ በደም የተነከሩ፣ ራሷን ለዚህ ዓለም አመንዝራ አድርጋ ያቀረበች ብልሹ ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ከሀብታሞች ጋር በመሻረክ ድሆችን የምትጨቁን፣ እውነተኛውን አምልኮ በመከተል ፈንታ አረማዊ መሠረተ ትምህርቶችን የምታስተምር ድርጅት ሆና ይሖዋ አግኝቷታል። (ያዕቆብ 1:27፤ 4:4) ይሖዋ በሚልክያስ በኩል “በመተተኞችና በአመንዝሮች፣ በሐሰትም በሚምሉ፣ የምንደኛውንም ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቲቱንና ድሃ አደጉን በሚያስጨንቁ፣ . . . ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ” በማለት አስጠንቅቋል። (ሚልክያስ 3:5) ሕዝበ ክርስትና ይህን ሁሉና ከዚህም የባሰ ነገር አድርጋለች። ታላቂቱ ባቢሎን ተብላ ከምትጠራው በመላው ዓለም የተንሰራፋችው የሐሰት ሃይማኖት ሥርዓት ክፍል ከሆኑት ከቀሩት ሃይማኖቶች ጋር እንድትጠፋ ይሖዋ የፈረደባት መሆኑ በ1919 ግልጽ ሆኖ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች “ሕዝቤ ሆይ፣ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” የሚለው ጥሪ በይፋ መነገር ጀመረ።—ራእይ 18:1, 4

7. ኢየሱስ ታማኝና ልባም ባሪያው እንደሆነ አድርጎ የተቀበለው ማንን ነው?

7 ታዲያ ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነበር? ታማኝና ልባሙ ባሪያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለመጥምቁ ዮሐንስና የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ለሆነው ለኢየሱስ የምስክርነት ሥራ ምላሽ በሰጠ አነስተኛ ቡድን ጀመረ። በእኛ መቶ ዘመን ደግሞ ታማኝና ልባም ባሪያ የሚባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ፊት ለሚጠብቃቸው ታላቅ ሥራ መሰናዶ በሚያደርጉባቸው እስከ 1914 በነበሩት ዓመታት ያቀረቡትን ጥሪ እሺ ብለው የተቀበሉ ጥቂት ሺህ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት አስቸጋሪ መከራዎች ቢደርስባቸውም በመጽናት ልባቸው ከይሖዋ ጋር መሆኑን አሳይተዋል።

የማጥራት ሥራ

8, 9. በ1918 ታማኝና ልባም ባሪያው መጥራት ያስፈለገው በምን መንገድ ነበር? ይሖዋስ በዚህ ረገድ ምን ተስፋ ሰጥቶ ነበር?

8 ይሁን እንጂ ይህ ቡድንም እንኳን መጥራት ወይም መጽዳት ያስፈልገው ነበር። ከእነርሱ ጋር ተጎዳኝተው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ተመልሰው የእምነት ጠላቶች በመሆናቸው መመንጠር ነበረባቸው። (ፊልጵስዩስ 3:18) ሌሎች ደግሞ ይሖዋን ከማገልገል ጋር የሚመጡትን ኃላፊነቶች ለመሸከም ፈቃደኞች ስላልነበሩ አፈገፈጉ። (ዕብራውያን 2:1) ከዚህም ሌላ መወገድ የሚያስፈልጋቸው ባቢሎናዊ ልማዶች ገና ቀርተው ነበር። በድርጅት ደረጃም ታማኝና ልባም ባሪያ መጽዳት ነበረበት። ይህን ዓለም በተመለከተ ተገቢ የሆነ የገለልተኝነት አቋም መያዝና በሥራ ላይ ማዋል ነበረበት። ዓለም እያደር ብልሹ እየሆነ በመጣ መጠን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ርኩስነት ከጉባኤው ለማስወገድ ከባድ ትግል ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር።—ከይሁዳ 3, 4 ጋር አወዳድር።

9 አዎን፣ ማጽዳት ያስፈልግ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ በዙፋን ላይ የተቀመጠውን ኢየሱስን በሚመለከት በፍቅሩ ተገፋፍቶ “እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፣ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፣ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ” በማለት ቃል ገብቷል። (ሚልክያስ 3:3) ከ1918 ጀምሮ ይሖዋ በቃል ኪዳኑ መልእክተኛ በኩል ተስፋውን በመፈጸም ሕዝቡን አጽድቷል።

10. የአምላክ ሕዝቦች ያመጡት ምን ዓይነት ቁርባን ነበር? ይሖዋስ ምን ግብዣ አቀረበላቸው?

10 የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞችና በኋላ በይሖዋ አገልግሎት የተባበሩአቸው እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋ እንደ ብር አንጣሪና አጥሪ ሆኖ በመሥራቱ ተጠቅመዋል። (ራእይ 7:9, 14, 15) እነርሱ በድርጅት ደረጃ በጽድቅ ቁርባንን ለማቅረብ መጥተዋል፣ አሁንም እየመጡ ነው። “እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቁርባን ደስ ይለዋል።” (ሚልክያስ 3:4) ይሖዋ በትንቢቱ “በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ በረከትንም አትረፍርፌ [ምንም እስከማይጎድላችሁ ድረስ አዓት] ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]” በማለት የጋበዛቸው እነዚህን ነው።—ሚልክያስ 3:10

ቁርባኖችና አሥራቶች

11. በአሁኑ ጊዜ በሙሴ ሕግ መሠረት ቁርባን ማቅረብ የማያስፈልገው ለምንድን ነው?

11 በሚልክያስ ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ‘እንደ እህል፣ ፍራፍሬና እንስሳት’ ያሉትን ቃል በቃል ቁርባንና አሥራት አድርገው ያመጡ ነበር። በኢየሱስ ዘመንም እንኳን ታማኝ እሥራኤላውያን በቤተ መቅደሱ ቁርባኖችን ያቀርቡ ነበር። ይሁን እንጂ ከኢየሱስ ሞት በኋላ ይህ ሁሉ ተለወጠ። ተለይተው የተወሰኑ ቁሳዊ ቁርባኖችንና አሥራቶችን ማቅረብን ጨምሮ ሕጉ ተሻረ። (ኤፌሶን 2:15) ኢየሱስ በሕጉ ሥር የነበሩትን ትንቢታዊ የቁርባን አምሳያዎች ፈጽሞአቸዋል። (ኤፌሶን 5:2፤ ዕብራውያን 10:1, 2, 10) ታዲያ ክርስቲያኖች ቁርባኖችንና አሥራቶችን ሊያቀርቡ የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

12. ክርስቲያኖች የሚያቀርቡት ምን ዓይነት መንፈሳዊ ቁርባኖችና መሥዋዕቶችን ነው?

12 ቁርባኖች ለክርስቲያኖች በላቀ ደረጃ በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚቀርቡ ናቸው። (ከፊልጵስዩስ 2:17​ና ከ2 ጢሞቴዎስ 4:6 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት” ባለ ጊዜ የስብከቱ ሥራ መሥዋዕት እንደሆነ ተናግሯል። “ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” በማለት አጥብቆ ባሳሰበ ጊዜ ስለ ሌላ ዓይነት መንፈሳዊ መሥዋዕት አመልክቷል። (ዕብራውያን 13:15, 16) ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ አቅኚነት አገልግሎት እንዲገቡ ሲያበረታቱአቸው ዮፍታሔ ሴት ልጁን ድል ላስገኘለት አምላክ “የሚቃጠል መሥዋዕት” አድርጎ እንዳቀረበው ዓይነት ለይሖዋ ቁርባን አድርገው አቀረቡአቸው ሊባል ይቻላል።—መሳፍንት 11:30, 31, 39

13. ክርስቲያኖች ቃል በቃል የገቢያቸውን አንድ አሥረኛ መስጠት የማይፈለግባቸው ለምንድን ነው?

13 ይሁንና ስለ አሥራቶችስ ምን ሊባል ይቻላል? በአንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያኖች እንደሚደረገው ክርስቲያኖች የቁሳዊ ገቢያቸውን አንድ አሥረኛ ለብቻው እያስቀመጡ ለይሖዋ ድርጅት የመስጠት ግዴታ አለባቸውን? እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ደንብ ለክርስቲያኖች እንደተደነገገ የሚገልጽ ጥቅስ የለም። ጳውሎስ በይሁዳ ለነበሩ ችግረኛ ክርስቲያኖች መዋጮ በሰበሰበ ጊዜ ከመቶ የተወሰነ እጅ መሰጠት እንዳለበት የተጠቀሰ ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ጳውሎስ በልዩ አገልግሎት ላይ ስላሉት ሲናገር አንዳንዶቹ በፈቃደኛነት መዋጮዎች መተዳደራቸው በጣም ተገቢ መሆኑንና እርሱ ግን ራሱን ለመርዳት ሲል ለመሥራት እንደተዘጋጀ ገልጿል። (ሥራ 18:3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 9:13-15) ለዚህ ዓላማ ተብሎ የተወሰኑ አሥራቶች አልነበሩም።

14. (ሀ) አሥራትን መስጠት ሁለንተናችንን ለይሖዋ መስጠትን የማያመለክተው ለምንድን ነው? (ለ) አሥራቱ የሚያመለክተው ምናችንን ነው?

14 በግልጽ እንደምናየው አሥራት ለክርስቲያኖች ምሳሌ የሚሆነው ወይም የሚያመለክተው ሌላ ነገርን ነው። አሥራት አንድ አሥረኛ ስለሆነና አሥር ቁጥር ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ለምድራዊ ነገሮች ምልአትን ስለሚያመለክት ሁለንተናችንን ለይሖዋ መስጠትን ያመለክታልን? አይደለም። ሁለንተናችንን የሰጠነው ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ይህንኑም በውኃ ጥምቀት ባሳየን ጊዜ ነው። ራሳችንን ከወሰንን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ያልሆነ ነገር የለንም። ይሁን እንጂ ግለሰቦች የራሳቸው የሆነን ነገር እንዲሰጡ ይሖዋ ይፈቅዳል። ስለዚህ አሥራት ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና የእርሱ ንብረቶች መሆናችንን እንደተገነዘብን የምንገልጥበት ምልክት አድርገን ለእርሱ የምናመጣውን ወይም ለይሖዋ አገልግሎት የምንጠቀምበትን የራሳችን ድርሻ የሆነ ነገርን ያመለክታል። ዘመናዊው አሥራት አንድ አሥረኛ ብቻ መሆን የለበትም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ያነሰም ሊሆን ይችላል። በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ የበለጠ ይሆናል። እያንዳንዱ ግለሰብ ልቡ እንዲያመጣ የገፋፋውንና ሁኔታው የፈቀደለትን ያመጣል።

15, 16. መንፈሳዊ አሥራታችን ምንን ይጨምራል?

15 በዚህ መንፈሳዊ አሥራት ውስጥ ምን ነገር ይጠቃለላል? መጀመሪያ ነገር ለይሖዋ የምንሰጠው ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በታላላቅና በዓመታዊ ስብሰባዎች በመካፈል፣ በመስክ አገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ መሰጠት ያለበት የአሥራታችን ክፍል ነው። የታመሙትን በመጠየቅና ሌሎችንም በመርዳት የምናሳልፈው ጊዜም የአሥራታችን ክፍል ነው። የመንግሥት አዳራሾችን በመሥራትና አዳራሹን በመጠገንና በማጽዳት መርዳትም የአሥራታችን ክፍል ነው።

16 አሥራታችን የገንዘብ መዋጮአችንንም ይጨምራል። በቅርብ ዓመታት የይሖዋ ድርጅት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፋ ሲሄድ ገንዘብ ነክ ግዴታዎችም እየጨመሩ ሄደዋል። ቀደም ሲል የተሠሩትን አዳራሾች መጠገንን ጨምሮ ከአዳዲስ የቅርንጫፍ ሕንፃዎችና አዳዲስ የትልቅ ስብሰባ አዳራሾች ጋር አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የግል መሥዋዕት አድርገው ለልዩ አገልግሎት ራሳቸውን ያቀረቡትን ወንድሞች ወጪ መሸፈን ከፍ ያለ ጥረት ይጠይቃል። በ1991 የሚስዮናውያን፣ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና የልዩ አቅኚዎችን ወጪ ለመሸፈን ብቻ የወጣው ገንዘብ ከ40 ሚልዮን ዶላር በላይ ሲሆን ሁሉም በፈቃደኝነት ከተደረገ መዋጮ የተገኘ ነበር።

17. መንፈሳዊ አሥራት አድርገን መስጠት ያለብን ምናችንን ነው?

17 ታዲያ መንፈሳዊ አሥራት አድርገን መስጠት የሚኖርብን ምንን ነው? ይሖዋ ከመቶ የተወሰነ እጅ አልወሰነም። ሆኖም ለሥራው ያለን የጋለ ፍቅር፣ ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ያለን እውነተኛ ፍቅር እንዲሁም ሊድኑ የሚገባቸው ሰዎች እንዳሉ ከመገንዘብ የሚመነጭ የአጣዳፊነት ስሜት መንፈሳዊ አሥራታችንን ሁሉ እንድናመጣ ያበረታታናል። ይሖዋን በተቻለን አቅም ሁሉ ለማገልገል እንገፋፋለን። ራሳችንን ወይም ሀብታችንን ለመስጠት ብንሳሳ ወይም በማጉረምረም ብንሰጥ አምላክን እንደመስረቅ ይቆጠራል።—ከሉቃስ 21:1-4

ምንም እስከማይጎድል ድረስ መባረክ

18, 19. የይሖዋ ሕዝቦች አሥራታቸውን ሁሉ በማግባታቸው የተባረኩት እንዴት ነው?

18 ከ1919 ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች በስብከቱ ሥራ ለሚያስፈልገው ሁሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘብ ነክ ጥሪታቸውን በለጋስነት በመስጠት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። በእርግጥ አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራው አግብተዋል። በውጤቱም ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ በመፈጸም ምንም እስከማይጎድላቸው ድረስ በረከቱን አዝንቦላቸዋል። ይህም በአኃዛዊ ዕድገታቸው ላይ በአስደናቂ ሁኔታ ታይቷል። ይሖዋ በ1918 ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ ሲያገለግሉት ካገኛቸው ጥቂት ሺህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተነስተው እስከአሁን ድረስ በማደግ ቅቡዓኑና ባልንጀሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች በ211 የተለያዩ አገሮች ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ ሆነዋል። (ኢሳይያስ 60:22) እውነትን በመረዳት በኩልም ያለማቋረጥ በማደግ ተባርከዋል። ትንቢታዊው ቃሉ ይበልጥ እርግጠኛ ሆኖላቸዋል። በይሖዋ ዓላማ አሠራር ላይ ያላቸው ትምክህትም ጸንቶ ተመሥርቷል። (2 ጴጥሮስ 1:19) እነርሱ በእርግጥም ‘ከይሖዋ የተማሩ’ ሕዝቦች ናቸው።—ኢሳይያስ 54:13

19 ይሖዋ በሚልክያስ በኩል ስለ አንድ ተጨማሪ በረከትም ተንብዮአል፦ “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም [ይሖዋንም አዓት] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” (ሚልክያስ 3:16) ክርስቲያን እንደሆኑ ከሚናገሩ የሃይማኖት ድርጅቶች ሁሉ ስለ ስሙ የሚያስቡና በአሕዛብ መካከልም ከፍ ከፍ የሚያደርጉት የይሖዋ ምስክሮች ብቻ ናቸው። (መዝሙር 34:3) ይሖዋ ታማኝነታቸውን እንደሚያስታውሰው እርግጠኞች በመሆናቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!

20, 21. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን የተባረከ ዝምድና አግኝተዋል? (ለ) ክርስትናን በሚመለከት እያደር ግልጽ እየሆነ የመጣው ምን ልዩነት ነው?

20 ቅቡዓን ቀሪዎቹ የይሖዋ ልዩ ሕዝቦች ሲሆኑ ከእነርሱ ጋር ለመተባበር የሚጎርፉት እጅግ ብዙ ሰዎች ደግሞ ከቅቡዓኑ ጋር የእውነተኛ አምልኮን በረከቶች ያጭዳሉ። (ዘካርያስ 8:23) ይሖዋ በሚልክያስ በኩል “እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፣ እንዲሁ እምራቸዋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ሚልክያስ 3:17) ይሖዋ ለእነርሱ እንዲህ ያለ የርኅራኄ አመለካከት ያለው መሆኑ ምንኛ በረከት ነው!

21 በእርግጥም በእውነተኛ ክርስቲያኖችና በሐሰተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት እያደር እየተገለጠ መጥቷል። የይሖዋ ሕዝቦች የእርሱን የሥነ ምግባር ደረጃ ለመጠበቅ ሲጥሩ ሕዝበ ክርስትና ደግሞ በዚህ ዓለም የርኩሰት ማጥ ውስጥ ይበልጡን እየተዘፈቀች ትሄዳለች። በእርግጥም “ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ” የሚሉት የይሖዋ ቃላት እውነት ሆነው ተገኝተዋል።—ሚልክያስ 3:18

22. አሥራታችንን ሁሉ ወደ ጎተራው ካገባን ምን በረከቶችን እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

22 በቅርቡ በሐሰተኛ ክርስቲያኖች ላይ የፍርድ ቀን ይመጣባቸዋል። “እነሆ፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፣ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት]።” (ሚልክያስ 4:1) ይሖዋ መንፈሳዊ ሕዝቡን በ70 እዘአ ከጥፋት እንደጠበቃቸው ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦች በመጪው የጥፋት ጊዜም እንደሚጠብቃቸው ያውቃሉ። (ሚልክያስ 4:2) ይህ ዋስትና ስላላቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው! እንግዲያስ እስከዚያ ቀን ድረስ እያንዳንዳችን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራው በማግባት ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አድናቆት እናሳይ። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ምንም እስከማይጎድለን ድረስ እኛን መባረኩን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ለተጨማሪ መረጃ የሰኔ 15, 1987 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14-20 ተመልከቱ።

ልታብራራ ትችላለህን?

◻ በዘመናችን ይሖዋ ከቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ የመጣው መቼ ነበር?

◻ ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ከ1918 በኋላ ምን ማጣሪያ አስፈልጓቸው ነበር?

◻ እውነተኛ ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ የሚያመጡት ምን ዓይነት መንፈሳዊ ቁርባን ነው?

◻ ክርስቲያኖች ወደ ጎተራ እንዲያገቡ የተጋበዙት አሥራት ምንድን ነው?

◻ የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ አሥራት በማቅረባቸው ምን በረከቶች ያገኛሉ?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈሳዊ አሥራታችን የመንግሥት አዳራሾችን ለመሥራት ጉልበታችንንና ሀብታችንን ማቅረብን ይጨምራል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሕዝቡን በመባረኩ ምክንያት የመንግሥት አዳራሾችንና የትልቅ ስብሰባ አዳራሾችን መሥራት ጨምሮ ብዙ የግንባታ ሥራ አስፈልጓል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ