የጊልያድ ትምህርት ቤት በረከቶች በዓለም ዙሪያ ተሰራጩ
በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ትምህርት ያለው ዋጋ በጣም ውስን ነው። የተመሠረተው በአምላክ እውነት ላይ ሳይሆን በአብዛኛው በሰዎች አመለካከቶች ላይ ስለሆነ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ዓላማ አያስጨብጥም። የጊልያድ ትምህርት ቤት ግን ከዚህ የተለየ ነው። የጊልያድ 93ኛ ክፍል የምረቃ በዓል ላይ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ ባቀረበው የመግቢያ ሐሳብ ላይ ይህ ትምህርት ቤት እውነተኛ መሠረት ያለው ትምህርት እንደሚሰጥ ተናገረ። በመዝሙር 119:160 እንደ 1980 ትርጉም “የቃልህ [የአምላክ ቃል] መሠረት እውነት ነው” ይላል። ስለዚህ ወደ 6,000 የሚጠጉት አድማጮች መስከረም 13, 1992 ላይ የተካሄደውን የምረቃ ፕሮግራም ያዳመጡት በታላቅ ስሜት ነበር።
በጠዋቱ ፕሮግራም ላይ የመጀመሪያው ንግግር በመጠበቂያ ግንብ እርሻ ኮሚቴ አባል በሆነው በሎንሺሊንግ የቀረበ ሲሆን ርዕሱም “ዓለምንና ገዢውን ማሸነፋችሁን ቀጥሉ” የሚል ነበር። ወንድም ሺሊንግ በራእይ 12:11 ላይ በማተኮር ጥቅሱ ለማሸነፍ የሚቻልባቸውን ሦስት መንገዶች እንደሚያሳይ አመለከተ። እነርሱም፦ (1) በበጉ ደም አማካኝነት፣ (2) ምስክርነት በመስጠትና (3) የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በመያዝ ናቸው። አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ ያለውን መንፈስ ማሳየታቸውን እንዲሁም ታማኝነታቸውንና ፍጹም አቋማቸውን ላለማጉደፍ ሲሉ ሞትን እንኳን በፈቃደኝነት እንደተቀበሉ ተማሪዎቹን አስታወሳቸው።
የአስተዳደር አካል አባል በሆነው በጆን ኢ ባር የቀረበው “የተሰጣችሁን አደራ ጠብቁ” የሚል አጠቃላይ መልእክት የሚያብራራ ነበር። ልዩ መለያ ጠባዩ በሆነው ሞቅ ያለ ቃና ባለው ድምፁ በይሖዋና በአገልጋዮቹ መካከል ያለውን መተማመን በጥሩ ትዳር ውስጥ ካለው መተማመን ጋር አወዳድሮታል። በ2 ጢሞቴዎስ 1:12, 13 ላይ ያለውን ነጥብ በመጠቀም “ጤናማ” የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ “ቃል ምሳሌ” በከፍተኛ ሁኔታ በመያዝ የተጣለባቸውን አደራ እንዲጠብቁ አጥብቆ አሳሰባቸው። የግል ጥናትን የየቀኑ ፕሮግራማቸው ዋና ክፍል ማድረግን በማጉላት ተማሪዎቹ በስብሰባዎች ላይ የሚሰጧቸው ሀሳቦች የልምድ ጉዳይ ሳይሆን ትርጉም ያላቸው እንዲያደርጓቸው በደግነት አጥብቆ አሳሰባቸው።
ቀጥሎም የአገልግሎት ዲፓርትመንት ኮሚቴ አባል የሆነው ዊልያም ቫን ደ ዎል “በግ መሰል ለሆኑ ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩ” የሚል ንግግር ሰጠ። ከአንድ የቤተሰብ ሐኪም ምን ትጠብቃላችሁ ሲል ተማሪዎቹን ጠየቃቸውና እነሱም ልክ እንደዚያው ነገሮችን በሌላው ቦታ ሆኖ የመመልከት፣ የርኅራኄና የምሕረት ስሜት እንዲያዳብሩ አጥብቆ አሳሰባቸው።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ይቻላል” በሚል ርዕስ ስሜትን በሚቀሰቅስ ሁኔታ ንግግር አደረገ። አብርሃምና ሣራ በእርጅና ዘመናቸው ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ በተሰጣቸው የማይቻል የሚመስል ተስፋ ስቀው እንደነበር ተማሪዎቹን አስታወሳቸው። ብዙዎቹ የአምላክ ተስፋዎች በሰው አመለካከት ሲታዩ የማይቻሉ ይመስላሉ። ይሁን እንጂ መልአኩ አብርሃምን እንደጠየቀው “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” (ዘፍጥረት 18:14) ወንድም ሲድሊክ አምላክ የማይቻለውን ነገር ለማድረግ ባለው ችሎታ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ እንዲሁም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸውም አሁን ያላቸው እምነት እንዲደበዝዝ ወይም እንዲያወላውል እንዳይፈቅዱ አጥብቆ አሳሰባቸው።
አስተማሪዎቹ ምክር ለገሱ
ቀጥሎም ሁለቱ የጊልያድ አስተማሪዎች ንግግር አደረጉ። በመጀመሪያ ጃክ ዲ ሬድፎርድ “በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ይኑራችሁ” የሚለውን አጠቃላይ መልዕክት በማዳበር ንግግር አደረገ። አንድን ስም ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርገው የስሙ ባለቤት ነው በማለት አስረዳ። እንደ አዳም፣ ናምሩድ፣ ኤልዛቤል፣ ሳኦልና ይሁዳ ያሉትን ስሞች እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሩት፣ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ካሉ ስሞች ጋር አነፃፀራቸው። እያንዳንዱ ስም የስሙ ባለቤት ከተከተላቸው የሕይወት መንገዶች ጋር የተያያዙ ብዙ ነገሮችን ይዘዋል። ከ10፣ 100 ወይም ከ1,000 ዓመት በኋላ ምን ዓይነት ስም ይኖራችሁ ይሆን በማለት ተማሪዎቹን ጠየቃቸው። ጀምሮ የማያቋርጥ ሰው ወይስ ብዙ የሚያማርር ሰው ወይስ ታማኝ ሚስዮናዊ? በችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በመፍትሔዎችና በዓላማችሁ ላይ አተኩሩ በማለት መከራቸው።
በዩሊሰስ ቪ ግላስ የተብራራው አእምሮን የሚቀሰቅስ ርዕስ “እምነታችሁን ምን ያህል ትጠብቁታላችሁ?” የሚል ነበር። ጠንካራ የሆነ እምነትን ሁልጊዜ ትክክለኛውን አቅጣጫ ከሚያሳይ ጥሩ ኮምፓስ ጋር አመሳሰለው። በመኪና ውስጥ ያለ ኮምፓስ ከመሬት ማግኔታዊ ስበት በተጨማሪ በሌሎች ማግኔታዊ ስበቶች ሊነካ ይችላል። ስለዚህ እነዚህን ስበቶች ማስወገድ ያስፈልጋል። በተመሳሳይም ይህ አሮጌ ዓለም የምንፈቅድላቸው ከሆነ እምነታችንን ሊያስለውጡ ወይም ሊያዳክሙ የሚችሉ ብዙ መሳቢያዎችን ያፈልቃል። ወንድም ግላስ ተማሪዎቹ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ስበቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ካስጠነቀቃቸው በኋላ ለሌሎች ሰዎች አመለካከቶችና ስሜቶች ያሳዩትን ጥንቃቄ አመስግኗል።
የጠዋቱ የመጨረሻ ንግግር የአስተዳደር አካል አባል በሆነው በአልበርት ዲ ሽሮደር ቀረበ። ተማሪዎቹን “የሚስዮናዊነትን መንፈስ አታጥፉ” ሲል አበረታታቸው። ያኔ በ1943 እሱ የትምህርት ቤቱ ሬጂስትራር ሆኖ ያገለግል በነበረበት ጊዜ የመጀመሪያው ክፍል ያሳየውን ዓይነት የሚስዮናዊነት መንፈስ እያሳዩ በመሆናቸውም አመሰገናቸው። በተፈጥሯቸው ሰው ወዳዶች የሆኑና በአምላክ መንፈስ ለመመራት የሚፈልጉ ሰባኪዎች መሆናቸውን እንደተገነዘበ ገለጸላቸው። በግል ጥናታችሁ ውስጥ በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ይህንን ዓይነቱን መንፈስ ማዳበራችሁን ቀጥሉ ሲል አጥብቆ መከራቸው። መዝሙር 24ን እንደምሳሌ አድርጎ ወስዶ ጥቅሶቹን አንድ በአንድ በማብራራት ንግግሩን ደመደመ።
ቀጥሎም የጊልያድ ተማሪዎች የጊልያድ ምሩቃን ሆኑ! ምድብ ቦታቸው ጮክ ተብሎ እየተነበበ ዲፕሎማዎቻቸውን በሚሰጣቸው ጊዜ አድማጮች በከፍተኛ ሁኔታ ያጨበጭቡ ነበር።
ከሰዓት በኋላ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የፋብሪካ ኮሚቴ አባል በሆነው በካልቪን ቺክ ተመራ። ከዚያም ደስ የሚል የተማሪዎች ፕሮግራም ተከተለ። ይህም ተማሪዎቹ በአምስት ወር ኮርሳቸው ውስጥ ያጋጠሟቸውን የመስክ ተሞክሮዎች የሚመለከት ነበር። እንዲሁም የተመደቡባቸውን አንዳንድ አገሮች የሚያሳይ የስላይድ ፊልም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በዕድሜ ገፋ ያሉ ባልና ሚስት ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸው ነበር። እነሱም ሚስዮናውያን ሆነው በቆዩባቸው ብዙ ዓመታት ያገኙትን ጥበብና ተሞክሮዎች አካፈሉ። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ሌላ ሰው አያስታችሁ፣ በአምላክም አትዘብቱ የሚል ርዕስ ባለው ለጊዜው በሚስማማ ድራማ ተደመደመ።
አድማጮቹ በአምላክ እውነት ላይ የተመሠረተ ትምህርት ምን ሊያደርግ እንደሚችል በማየታቸው ስሜታቸው በደስታ ተነክቶ መንፈሳቸው ተነቃቅቷል። እንዲሁም ይህን የመሰለው ትምህርት ጥቅም በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ስሜት መንካቱን እንደሚቀጥል በማወቃቸው ተደስተዋል። እነዚህ 48 ሚስዮናውያን ወደ ምድብ ቦታቸው በሚበታተኑበት ጊዜ ታማኞች የትም ቦታ ቢሄዱ ለአምላክ ሕዝቦች በረከት እንደሚሆኑ ልባዊ የሆነ ተስፋና እርግጠኝነት የያዙ ብዙ ጸሎቶች ተከትለዋቸዋል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የክፍሉ እታቲስቲክስ
የተወከሉት አገሮች ቁጥር፦ 7
የተመደቡባቸው አገሮች ቁጥር፦ 18
የተማሪዎች ቁጥር፦ 48
ባልና ሚስት፦ 24
አማካይ ዕድሜ፦ 32.8
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው አማካይ ዓመታት፦ 15.3
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው አማካይ ዓመታት፦ 10.4
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጊልያድ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች
ሰኔ 21, 1992 ጀርመን ካለው የጊልያድ ትምህርት ቤት ቅርንጫፍ በሴለተርስ/ታውነስ ውስጥ 24 ሚስዮናውያንን የያዘ አራተኛው የተማሪዎች ቡድን ተመረቀ። ክፍሉ ከ7 አገሮች የመጡ 11 ባልና ሚስት የሆኑና 2 ነጠላ እህቶችን የያዘ ነበር። አማካይ ዕድሜያቸው 32 ዓመት፣ ከተጠመቁ በአማካይ 14 ዓመታት የሆናቸውና በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ በአማካይ 8.5 የአገልግሎት ዓመት ያላቸው ናቸው። በምረቃው በዓል ላይ ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተው ነበር።
ወንድም ጃራዝ ፕሮግራሙን የከፈተው “ያለውን የሚበትን ሰው አለ፣ ይጨመርለታልም” የሚለውን ምሳሌ 11:24ን በማብራራት ነበር። ተማሪዎቹ ሊበታተኑ እንደሆነና ጭማሪ እንደሚያገኙም እርግጠኛ እንደሆነ አስገነዘበ።
የጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አስተባባሪ በሆነው በሪቻርድ ኬልሲይ፣ የአገልግሎት ዲፓርትመንት አባል በሆነው በውልፍጋንግ ግሩፕ፣ የቅርንጫፍ ቢሮው ኮሚቴ አባላት በሆኑት በዌርነር ሩደኬና በኤድመንድ አንስታድት እንዲሁም በሁለቱ አስተማሪዎች በዴሪክ ፎስተርና በሎታር ካኢሜር አማካኝነት የሚያበረታቱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮች ቀርበው ነበር። የአስተዳደር አካል አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር “መንፈሳዊ ዕንቁ ፈላጊዎች መሆናችሁን ቀጥሉ” የሚል ርዕስ ያለው ደስ የሚል ንግግር አደረገ። ተማሪዎቹ የተመደቡባቸውን በአፍሪካ፣ በመካከለኛው አሜሪካ እና በምሥራቅ አውሮፓ ውስጥ ያሉት 11 አገሮች ከተነገሯቸው በኋላ አንድ ተመራቂ ለአስተዳደር አካል የቀረበ የተማሪዎቹን ከልብ የመነጨ አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ በማንበብ የፕሮግራሙ መደምደሚያ ሆነ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች 93ኛ ክፍል
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ተርታዎች ቁጥር የተሰጣቸው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን የስም ዝርዝሮቹ ደግሞ በእያንዳንዱ ተርታ ከግራ ወደ ቀኝ በዝርዝር ተጽፈዋል።
(1) ሃይትስማን ሲ፤ ዌስት ፒ፤ ኢቫንስ ዲ፤ ሂፕስ ኤም፤ ሳይመንሊ ኤን፤ ዉድ ኤስ፤ ኮርክል ኤም፤ ፍሎሬስ ሲ፤ ቶማስ ጄ። (2) ጆንስ ኤም፤ ኒሲነን ጄ፤ ስፖነንበርግ ኤም፤ ዛቻሪ ኬ፤ ራቫን ጂ፤ ባክማን ኤም፤ ዌቴርግረን ኤ፤ ኢቫንስ ዲ፤ ፍሎረስ አር፤ ካፓሬሌ ጂ። (3) ሳይመንሊ ኤን፤ ሪችስቴይነር ኤም፤ ሪችስቴይነር ኤም፤ ሩይዝ ኢስፓርዛ ኤል፤ ገርቢግ ቢ፤ ሲምፕሰን ሲ፤ ዛኔዊች ሲ፤ ዛቻሪ ቢ፤ ሪኬትስ ኤል። (4) ሲምፕሰን ጄ፤ ባክማን ጄ፤ ኮርክል ጂ፤ ገርቢግ ኤም፤ ሪኬትስ ቢ፤ ባገር ሀንሰን ኤል፤ ጆንስ ኤ፤ ዛኔዊች ኬ፤ ራቫን ጄ፤ ሂፕስ ሲ። (5) ስፖነንበርግ ኤስ፤ ሃይትስማን ኤ፤ ካፓሬሌ ኤል፤ ሩይዝ ኢስፓርዛ ኤስ፤ ቶማስ አር፤ ባገር ሃንሰን ቢ፤ ዉድ ኤም፤ ዌስት ኤም፤ ዌቴርግረን ሲ፤ ኒሲነን ኢ።