አስደናቂ ነገሮችን የሚሠራው ይሖዋ
“አንተ ታላቅ ነህ፤ ድንቅ ነገሮችንም ታደርጋለህ፤ አንተ ብቻ አምላክ ነህ።”—መዝሙር 86:10 የ1980 ትርጉም
1, 2. (ሀ) ሰው የፈለሰፋቸው ነገሮች ዓለምን የነኩት እንዴት ነው? (ለ) የተሻሉ ነገሮችን ከየት ለማግኘት ተስፋ ልናደርግ እንችላለን?
ዘመናዊው ሰው እንደ ኤሌክትሪክ መሣሪያዎች፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ ቪዲዮ፣ አውቶሞቢል፣ የጄት አውሮፕላን ጉዞና በኮምፒዩተር የሚመራ ቴክኖሎጂ ያሉ የፈለሰፋቸው ነገሮች አስደናቂ ናቸው በማለት ይኩራራ ይሆናል። እነዚህ ነገሮች ዓለምን በጣም አቀራርበዋታል። ግን ምኑን መቀራረብ ይባላል! የሰው ዘር በሰላም፣ በብልጽግናና ለሁሉም በሚያስፈልጉ ብዙ ነገሮች ፈንታ ነፍስ ለማጥፋት በሚካሄዱት ጦርነቶች፣ በወንጀል፣ በሽብር፣ በአካባቢ ብክለት፣ በበሽታና በድህነት እየተሠቃየ ነው። በዓለም ዙሪያ የተሰራጩት የኑክሌር መሣሪያዎች በቁጥር ቢቀንሱም እንኳን የሰውን ዘር ብዙ ጊዜ እጥፍ ድምጥማጡን ለማጥፋት የሚችሉ ናቸው። የጦር መሣሪያ አምራቾች የሆኑት የሞት ነጋዴዎች በምድር ላይ ያለውን ትልቁን የንግድ ዘርፍ ይዘዋል። ሀብታሙ የበለጠ ሀብታም እየሆነ ሲሄድ ድሃው ደግሞ የባሰ ይደኸያል። ከዚህ ሁኔታ መውጫውን የሚያዘጋጅልን ይኖር ይሆን?
2 አዎን! ከመከራ እንደምንገላገል ቃል የገባልን “ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለው” ይሖዋ አምላክ አለ። (መክብብ 5:8) እርሱም በጭንቀት ጊዜ ብዙ ማጽናኛና ጥበብ ያለበትን ምክር የሚሰጡንን መዝሙራት በመንፈሱ አነሳሽነት አስጽፏል። ከነርሱም ውስጥ “የዳዊት ጸሎት” የሚል ርዕስ የተሰጠው መዝሙር 86 ይገኝበታል። አንተም የራስህ ማድረግ የምትችለው ጸሎት ነው።
በመከራ የተጠቃ፤ ግን በታማኝነት ከጎን የሚቆም
3. ዳዊት ለእነዚህ ጊዜያት የሚሆን ምን የሚያበረታታ ምሳሌ ሰጥቶናል?
3 ዳዊት ይህንን መዝሙር የጻፈው በመከራ እየተጠቃ በነበረበት ጊዜ ላይ ነው። “የሚያስጨንቅ ዘመን” በሆነውና የሰይጣን ሥርዓት የ‘መጨረሻ ቀን’ በሆነው በዛሬው ጊዜ የምንኖረው እኛም ተመሳሳይ መከራዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 24:9-13ን ተመልከት።) ዳዊትም በነበሩበት ችግሮች ምክንያት እንደኛው በስጋትና በጭንቀት ተሠቃይቷል። ይሁን እንጂ እነዚህ መከራዎች በፈጣሪው ላይ ያለውን የታማኝነት ትምክህት እንዲያዳክሙበት ፈጽሞ አልፈቀደላቸውም። “አቤቱ፣ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፣ ችግረኛና ምስኪን ነኝና። ቅዱስ [ታማኝ አዓት]ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፤ አምላኬ ሆይ፣ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው” ሲል ለመነ።—መዝሙር 86:1, 2
4. ልበ ሙሉ መሆናችንን እንዴት ማሳየት ይኖርብናል?
4 “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ጆሮውን ወደዚች ምድር እንደሚመልስና በትሕትና የቀረቡ ጸሎቶቻችንን እንደሚሰማ እኛም እንደ ዳዊት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ያለማወላወል በአምላካችን በመተማመን “ትካዜህን በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” የሚለውን የዳዊትን ምክር ልንከተል እንችላለን።—መዝሙር 55:22
ከይሖዋ ጋር በጣም መቀራረብ
5. (ሀ) ጥንቃቄ የተደረገባቸው አንዳንድ ትርጉሞች የአይሁድ ጻፎችን ስህተት ያረሙት እንዴት ነው? (ለ) 85ኛውና 86ኛው መዝሙሮች ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርጉት በምን መንገድ ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
5 በ86ኛው መዝሙር ውስጥ ዳዊት “ይሖዋ ሆይ” የሚለውን ሐረግ 11 ጊዜ ተጠቅሞበታል። የዳዊት ጸሎት እንዴት ያለ ልብን የሚነካ ነው! ከይሖዋ ጋር የነበረው ግንኙነትስ እንዴት በጣም የተቀራረበ ነበር! ከጊዜ በኋላ የቅርብ ግንኙነት ባለው ሁኔታ በአምላክ ስም መጠቀሙ በአይሁዳውያን ጻፎች በተለይም በሶፍሪም ዘንድ በጣም የተጠላ ሆነ። ስሙን አላግባብ እንጠቀምበት ይሆናል የሚል የፍራቻ አጉል እምነት ያዙ። ሰው የተፈጠረው በአምላክ አምሳያ የመሆኑን ሐቅ ችላ በማለት ሰዎች የሚያሳዩአቸውን በጎ ባሕርያት አምላክም ያሳያቸዋል ብለው ለመናገር አሻፈረን አሉ። ስለዚህ በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ ባለው በዚህ አንድ መዝሙር ውስጥ መለኮታዊው ስም ከሚገኝባቸው 11 ቦታዎች በሰባቱ ላይ ይሖዋ የሚለውን ስም አዶናይ (ጌታ) በሚለው የማዕረግ ስም ተክተውታል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም እንዲሁም ሌሎች በጥንቃቄ የተዘጋጁ ትርጉሞች መለኰታዊውን ስም በአምላክ ቃል ውስጥ በተገቢ ቦታው ላይ በመመለሳቸው አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን። በውጤቱም ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት መሆን ባለበት መንገድ ጎልቶ ተገልጾልናል።a
6. የይሖዋ ስም ለኛ ውድ እንደሆነ በምን በምን መንገዶች ልናሳይ እንችላለን?
6 የዳዊት ጸሎት “አቤቱ፣ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮሃለሁና ማረኝ። የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፣ አቤቱ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] ነፍሴን ወደ አንተ አነሳለሁና” በማለት ይቀጥላል። (መዝሙር 86:3, 4) ዳዊት “ቀኑን ሁሉ” ወደ ይሖዋ ሲጮህ እንደዋለ ልብ በሉ። በእርግጥም ብዙ ጊዜያት (ለምሳሌ ኮብልሎ በምድረበዳ ሲኖር) ሌሊቱን ሙሉ ይጸልይ ነበር። (መዝሙር 63:6, 7) ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንድ ምስክሮች በግድ በጾታ ሊነወሩ ሲሉ ወይም ሌላ የወንጀል ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ሲል ጮክ ብለው ወደ ይሖዋ ይጸልያሉ። አንዳንድ ጊዜ ባገኙት ያላሰቡት አስደሳች ውጤት ተደንቀዋል።b “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ” በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የይሖዋ ስም ለእርሱ ውድ ነገር እንደነበረ ሁሉ ለእኛም ውድ የሆነ ነገር ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለይሖዋ ስም መቀደስ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። እንዲሁም ስሙ ምንን እንደሚወክል አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 1:1፤ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6, 25, 26
7. ይሖዋ የአገልጋዮቹን ነፍስ እንደሚያነሳ የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉልን? ምላሽ መስጠት የሚኖርብንስ እንዴት ነው?
7 ዳዊት ነፍሱን ማለትም ሙሉውን ራሱን ወደ ይሖዋ አንስቷል። በመዝሙር 37:5 ላይ “መንገድህን ለእግዚአብሔር [ለይሖዋ አዓት] አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል” በማለት እኛም እንዲሁ እንድናደርግ ይመክረናል። እንግዲያው ነፍሳችንን ደስ እንዲያሰኛት ለይሖዋ የምናቀርበው ልመናችን ሳይመለስ አይቀርም። ፍጹም አቋማቸውን በመጠበቅ ላይ ያሉ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች ምንም እንኳን ችግር፣ ስደትና በሽታ ቢኖርባቸውም በአገልግሎቱ ደስታ ማግኘታቸውን ቀጥለዋል። በአፍሪካ ውስጥ እንደ አንጎላ፣ ላይቤሪያ፣ ሞዛምቢክና ዛየር ባሉ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችን በሕይወታቸው ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ለይሖዋ አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጥለዋል።c በእውነትም ይሖዋ በተትረፈረፈው መንፈሳዊ መከር እንዲደሰቱ አድርጓቸዋል። እነሱ እንደጸኑ ሁሉ እኛም መጽናት አለብን። (ሮሜ 5:3-5) ከጸናን ደግሞ “ራእዩ ገና እስከተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ . . . እርሱ አይዘገይም” ተብሎ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (ዕንባቆም 2:3) በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመመካትና በመተማመን እኛም ‘ወደ ፍጻሜው እንቸኩል።’
የይሖዋ ጥሩነት
8. ከይሖዋ ጋር ምን ዓይነት የቅርብ ግንኙነት ሊኖረን ይችላል? እርሱስ ጥሩነቱን የገለጸው እንዴት ነው?
8 ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩና ይቅር ለማለት የተዘጋጀህ ነህ፤ ለሚጠሩህም ሁሉ የምታሳያቸው ፍቅራዊ ደግነት ብዙ ነው። ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ የልመናዬንም ድምፅ አድምጥ። አንተ ጸሎቴን ስለምትሰማ በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጮሃለሁ” በማለት ሞቅ ባለ ስሜት ተጨማሪ ልመና አቀረበ። (መዝሙር 86:5-7) አሁንም አሁንም “ይሖዋ ሆይ” በሚለው የቅርብ ግንኙነትን በሚያሳየው አገላለጽ መንፈሳችን ይነቃቃል! በጸሎት አማካኝነት ዘወትር ሊኮተኮት የሚገባው የቅርብ ግንኙነት ነው። ዳዊት በሌላ አጋጣሚም “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፣ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] ስለ ቸርነትህ [ስለ ጥሩነትህ አዓት] ብዛት እንደ ምሕረትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት] አስበኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 25:7) ይሖዋ የኢየሱስን ቤዛ በመስጠቱ፣ ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች ምሕረትን በማድረጉና በታማኝነት ከጎኑ ለሚቆሙና አመስጋኝ ለሆኑ ምስክሮቹ ፍቅራዊ ደግነትን በማፍሰሱ ዋነኛው የጥሩነት ምሳሌ ነው።—መዝሙር 100:3-5፤ ሚልክያስ 3:10
9. ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ልብ ሊሉት የሚገባቸው ምን ማረጋገጫ ነው?
9 ባለፉት ስህተቶቻችን ምክንያት መጨነቅ ይኖርብናልን? አሁን በትክክለኛው መንገድ ቀጥ ብለን የምንሄድ ከሆነ ሐዋርያው ጴጥሮስ ንስሐ ለገቡት ሰዎች ከይሖዋ “የመጽናናት ዘመን” እንደሚመጣላቸው የሰጣቸውን ማረጋገጫ ስናስታውስ በደስታ እንዘላለን። (ሥራ 3:19) በፍቅር “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ባለው በቤዛችን በኢየሱስ በኩል ወደ ይሖዋ እየጸለይን ከእርሱ ጋር እንቀራረብ። በዛሬው ጊዜ ታማኝ የሆኑ ምስክሮች በኢየሱስ ውድ ስም ወደ ይሖዋ ሲጸልዩ በእርግጥም መጽናናትን ያገኛሉ።—ማቴዎስ 11:28, 29፤ ዮሐንስ 15:16
10. የመዝሙር መጽሐፍ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት ጎላ አድርጎ የሚያሳውቀው እንዴት ነው?
10 የመዝሙር መጽሐፍ የይሖዋን “ፍቅራዊ ደግነት” ከመቶ ጊዜ በላይ ይጠቅሰዋል። እንዲህ ያለው ፍቅራዊ ደግነት በእርግጥም ብዙ ነው! 118ኛው መዝሙር በመጀመሪያዎቹ አራት ቁጥሮች “ምሕረቱ [ፍቅራዊ ደግነቱ አዓት] ለዘላለም ናትና” የሚለውን በመደጋገም የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን እንዲያመሰግኑት ይጠይቃል። 136ኛው መዝሙር ይሖዋን በጣም የሚያስወድደውን የጥሩነትን ባሕርይ በማጉላት “ፍቅራዊ ደግነቱን” 26 ጊዜ ይጠቅሰዋል። በምንም መንገድ ይሁን ስህተት በመሥራት ያዕቆብ 3:2 እንደሚለው ‘ሁላችንም በብዙ ነገር ብንሰናከልም’ በምሕረቱና በፍቅራዊ ደግነቱ በመተማመን የይሖዋን ይቅርታ እንድናገኝ ለመጠየቅ ዝግጁዎች እንሁን። ፍቅራዊ ደግነቱ ይሖዋ ለኛ ያለው የታማኝ ፍቅሩ ማስረጃ ነው። እኛም በታማኝነት ከጎኑ በመቆም የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችንን ብንቀጥል እያንዳንዱን መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ በመስጠት ታማኝ ፍቅሩን ያሳየናል።—1 ቆሮንቶስ 10:13
11. ሽማግሌዎች የሚወስዱት እርምጃ አንድ ሰው ያደረበትን የጥፋተኝነት ስሜት ለማስወገድ እንዴት ሊረዳ ይችላል?
11 በሌሎች የምንደናቀፍባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። በሕፃንነታቸው የደረሰባቸው ስሜታዊ ወይም አካላዊ ጉዳት አንዳንዶች የጥፋተኝነትን ወይም ላላቸው ሁኔታ የሚገቡ እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ስሜት ጥሎባቸው አልፎ ይሆናል። የዚህ ዓይነቱ ጉዳት ተጠቂ የሆነ ሰው ይሖዋ መልስ እንደሚሰጠው በመተማመን ወደ እርሱ ሊጸልይ ይችላል። (መዝሙር 55:16, 17) ደግ የሆነ ሽማግሌ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጥፋቱ የሱ ያለመሆኑን ሐቅ እንዲቀበል በደስታ ሊረዳው ይፈልግ ይሆናል። ከዚያ በኋላም ሽማግሌው በየወቅቱ በወዳጅነት መንፈስ ስልክ እየደወለ ጥየቃ ቢያደርግለት በመጨረሻው እሱ (እርሷ) ‘ሸክማቸውን ራሳቸው መሸከም’ ይችላሉ።—ገላትያ 6:2, 5
12. መከራዎች እየጨመሩ የመጡት እንዴት ነው? ይሁን እንጂ በተሳካ ሁኔታ ልንቋቋማቸው የምንችለው እንዴት ሊሆን ይችላል?
12 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ሊቋቋሟቸው የሚገቡ ሌሎች ብዙ አስጨናቂ ሁኔታዎች አሉ። በ1914 ከተደረገው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ትልልቅ መቅሰፍቶች ምድርን እያጠቋት ይገኛሉ። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው እነዚህ “የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።” ‘ወደዚህ ሥርዓት የመደምደሚያ ቀኖች’ ይበልጥ ጠልቀን በገባን ቁጥር መከራዎች እየተደራረቡ ሄደዋል። (ማቴዎስ 24:3, 8) ዲያብሎስ የተሰጠው “ጥቂት ጊዜ” ወደ ማለቂያው በመሄድ ላይ ነው። (ራእይ 12:12) የሚበላውን በመፈለግ “እንደሚያገሣ አንበሳ” የሚዞረውን ታላቁ ባላጋራችን እኛን ከአምላክ መንጋ ለመለየትና ለማጥፋት ባለው ዘዴ ሁሉ ይጠቀማል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ይሁን እንጂ አይሳካለትም! ምክንያቱም ልክ እንደ ዳዊት እኛም በአንዱ አምላካችን በይሖዋ ላይ የእምነታችንን መልሕቅ እንጥላለን።
13. ወላጆችና ልጆቻቸው ከይሖዋ ጥሩነት ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
13 ዳዊት በይሖዋ ጥሩነት ላይ የመተማመንን አስፈላጊነት በልጁ በሰሎሞን ልብ ውስጥ እንደተከለ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ሰሎሞን የራሱን ልጅ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ” ብሎ ሊያስተምር ችሏል። (ምሳሌ 3:5-7) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችም እንደዚሁ ትንንሽ ልጆቻቸውን በእምነት ወደ ይሖዋ እንዴት መጸለይ እንደሚችሉና ጨካኝ ከሆነው ዓለም የሚሰነዘርባቸውን የዕድሜ እኩዮች ግፊትና የጾታ ብልግና የመፈጸም ፈተና ያሉ ጥቃቶችን እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ሊያስተምሯቸው ይችላሉ። በየቀኑ ከልጆቻችሁ ጋር እውነት ውስጥ መኖራችሁ ለጋ በሆነው ልባቸው ውስጥ ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅርና ጸሎት በተሞላበት ሁኔታ በእርሱ ላይ እምነት ማሳደር ሊቀረጽባቸው ይችላል።—ዘዳግም 6:4-9፤ 11:18, 19
ወደር የለሾቹ የይሖዋ ሥራዎች
14, 15. ወደር የለሽ ከሆኑት የይሖዋ ሥራዎች አንዳንዶቹ ምን ምን ናቸው?
14 ጥልቅ በሆነ እምነት ዳዊት “አቤቱ፣ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤ እንደ ሥራህም ያለ የለም” አለ። (መዝሙር 86:8) የይሖዋ ሥራዎች ማንም ሰው ሊያስበው እንኳን ከሚችለው በላይ ታላላቅ፣ ግርማ ሞገስ ያላቸውና ባለ ትልቅ ክብር ናቸው። ዘመናዊው ሳይንስ በአነስተኛ ሁኔታ እንደተመለከተው የጽንፈ ዓለሙ ስፋት፣ እርስ በርስ ያለው ስምምነትና ዕጹብ ድንቅነት ዳዊት ከተመለከተው ከማንኛውም ነገር የበለጠ የሚያስደንቅ ሆኖ ተገኝቷል። ይሁን እንጂ ዳዊት ራሱ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” ለማለት ተገፋፍቷል።—መዝሙር 19:1
15 የይሖዋ ሥራዎች በአስደናቂ ሁኔታ የተዘጋጁ ናቸው። ምድርን ያስቀመጣትና ያዘጋጃት ቀንና ሌሊትን፣ ወቅቶችን፣ የዘርና የመከር ጊዜን እንዲሁም ሰው ወደፊት የሚደሰትባቸውን እጅግ በጣም ብዙ አስደሳች ነገሮችን እንድትሰጥ አድርጎ ነው። እኛ ራሳችን በዙሪያችን ባሉት የይሖዋ ሥራዎች መደሰት እንድንችል ተደርገን እንዴት ባለ አስደናቂ ሁኔታ ተሠርተናል!—ዘፍጥረት 2:7-9፤ 8:22፤ መዝሙር 139:14
16. የይሖዋ ጥሩነት ትልቁ መግለጫ ምንድን ነው? ይህስ ወደምን ወደር የለሽ ሥራዎች መርቷል?
16 የመጀመሪያ ወላጆቻችን አምላክን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው እስከዚህ ዕለት ድረስ የሰውን ዘር የሚያሰቃየውን የመከራዎች ማዕበል ካስነሱ በኋላ ይሖዋ በፍቅሩ ተነሳስቶ ልጁን ወደ ምድር በመላክ የአምላክን መንግሥት እንዲያውጁና ለሰው ዘሮች ቤዛ ሆኖ እንዲሞት በማድረግ አስደናቂ ሥራ ሠርቷል። የድንቅ ድንቅ የሆነው ደግሞ ይሖዋ ክርስቶስን ከሞት አስነስቶ ከእርሱ ጋር ተባባሪ ንጉሥ እንዲሆን ማድረጉ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ሥራ 2:32, 34) አምላክ በታማኝነት ከጎኑ ከሚቆሙት የሰው ልጆች መካከል “አዲስ ፍጥረት” መርጧል። ይህ “አዲስ ፍጥረት” በጎ አድራጊ “አዲስ ሰማይ” በመሆን በቢልዮን የሚቆጠሩ ከሞት የሚነሱ ሰዎችን በሚጨምረው የ“አዲስ ምድር” ኅብረተሰብ ላይ ከክርስቶስ ጋር ሆኖ ይገዛል። (2 ቆሮንቶስ 5:17፤ ራእይ 21:1, 5-7፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22-26) በዚህ መንገድ የይሖዋ ሥራዎች ክብራማ ወደሆነው መደምደሚያቸው ይደርሳሉ! እውነትም “አቤቱ፣ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] . . . ለሚፈሩህም የሰወርሃት፣ ቸርነትህ [ጥሩነትህ አዓት] እንደ ምን በዛች!” በማለት በደስታ ልንናገር እንችላለን።—መዝሙር 31:17-19
17. የይሖዋን ሥራዎች በሚመለከት መዝሙር 86:9 በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
17 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሥራዎች ዳዊት በመዝሙር 86:9 ላይ “ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፣ አቤቱ፣ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] በፊትህም ይሰግዳሉ፣ ስምህንም ያከብራሉ” በማለት የገለጻቸውንም ያጠቃልላሉ። ይሖዋ አዲስ ፍጥረት ወይም የመንግሥት ወራሾች የሆኑትን “የታናሹ መንጋ” ቀሪዎች ከሰው ዘር መካከል ከጠራ በኋላ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም የሚያምኑ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “ከሁሉም ነገዶች” የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሰዎች”ን መሰብሰብ ጀምሯል። እነዚህንም ብርቱ ድርጅት አድርጎ አቋቁሟቸዋል። ይህም ድርጅት በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ሰላም ወዳድ የሆኑ ሰዎችን ያቀፈው ብቸኛው ዓለም አቀፍ ማኅበር ነው። ይህንን በመመልከት መላእክት በይሖዋ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው “በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን” እያሉ ያውጃሉ። እጅግ ብዙ ሰዎች የተባሉትም የዚህን ዓለም መጨረሻ በሕይወት ለማለፍና ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ በማድረግ “ሌሊትና ቀን” እያገለገሉት የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።—ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 7:9-17፤ ዮሐንስ 10:16
የይሖዋ ታላቅነት
18. ይሖዋ ‘እሱ ብቻ አምላክ’ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
18 ዳዊት በመቀጠል “አንተ ታላቅ ነህ፤ ድንቅ ነገሮችንም ታደርጋለህ፤ አንተ ብቻ አምላክ ነህ።” በማለት ትኩረቱን ወደ ይሖዋ አምላክነት ያዞራል። (መዝሙር 86:10 የ1980 ትርጉም) ከጥንት ጀምሮ ይሖዋ በእርግጥ ‘እርሱ ብቻ አምላክ’ እንደሆነ በተጨባጭ መንገድ ሲያሳይ ቆይቷል። “ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ማን ነው? እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] አላውቅም” በማለት ሙሴን በዕብሪተኛነት የተገዳደረው ጨቋኙ የግብፅ ፈርዖን ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ እንዲያውቀው ተደርጓል። ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ አጥፊ መቅሠፍቶችን በመስደድ፣ የግብፃውያንን የበኩር ወንዶች ልጆች በመግደል እንዲሁም ፈርዖንንና ምርጥ ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ውስጥ በማስጠም ድምጥማጣቸውን አጥፍቶ የግብፅን አማልክትና አስማተኛ ካህናት አዋረዳቸው። በእውነትም ከአማልክት መካከል ይሖዋን የሚመስል የለም!—ዘጸአት 5:2፤ 15:11, 12
19, 20. (ሀ) የራእይ 15:3, 4 መዝሙር ስሜት የሚነካ ታላቅ ደረጃ ላይ የሚደርሰው መቼ ነው? (ለ) በይሖዋ ሥራ አሁንም እንኳን ልንካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
19 እሱ ብቻ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ታዛዥ አምላኪዎቹን ከዘመናዊው ግብፅ ማለትም ከሰይጣን ዓለም ለማውጣት ዝግጅት ሲያደርግ አስደናቂ ሥራዎችን ሠርቷል። በታሪክ ሁሉ በስፋቱ ተወዳዳሪ በሌለው የስብከት ዘመቻ አማካኝነት ምስክር ይሆን ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ ስለ መለኮታዊ ፍርዱ እንዲታወጅ አድርጓል። በዚህም መንገድ በማቴዎስ 24:14 ላይ ያለው የኢየሱስ ትንቢት ተፈጽሟል። ይሖዋ በቅርቡ በምድር ላይ ያለውን ሁሉንም ክፋት በማጥፋት ታላቅነቱን ታይቶ በማይታወቅ መጠን የሚያሳይበት “መጨረሻው” መምጣት አለበት። (መዝሙር 145:20) ከዚያም “ሁሉን የምትገዛ ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ [ታማኝ አዓት] ነህና፣ የጽድቅ ሥራህ ስለተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ” የሚለው የሙሴ ቅኔና የበጉ ቅኔ በከፍተኛ ድምቀት ይዘመራል።—ራእይ 15:3, 4
20 እኛም በበኩላችን ስለነዚህ የአምላክ ዕጹብ ድንቅ ዓላማዎች ለሌሎች በመናገር በኩል ቀናተኞች እንሁን። (ከሥራ 2:11 ጋር አወዳድር።) የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንደሚገልጸው ይሖዋ በዘመናችንም ሆነ ወደፊት ታላላቅና አስደናቂ ሥራዎቹን መሥራቱን ይቀጥላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1874 የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ አንድሪው ኤ ቦናር የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “[በ85ኛው] መዝሙር የመጨረሻ መዝጊያ ላይ የአምላክን እጅግ በጣም ብዙ የተለዩ ባሕርያትና ክብራማው ስሙ በግልጽ ጎላ ተደርገዋል። እኩል በሆነ መጠን በይሖዋ ባሕርያት በተሞላ ሌላው ‘የዳዊት ጸሎት’ የተከተለው በዚህ ምክንያት ይሆናል። የዚህ [የ86ኛው] መዝሙር ዋና መንፈስ የይሖዋ ስም ነው።”
b በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የሰኔ 22, 1984 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትም ገጽ 28ን ተመልከት።
c ለዝርዝሩ በጥር 1, 1993 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የሚወጣውን “በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች የ1992 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት” የሚለውን ቻርት ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ የመዝሙር 86ን ጸሎት የግላችን ጸሎት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
◻ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ጥሩነቱን የገለጸልን እንዴት ነው?
◻ ወደር የለሽ ከሆኑት የይሖዋ ሥራዎች አንዳንዶቹ ምን ምን ናቸው?
◻ በታላቅነት በኩል ይሖዋ ‘እርሱ ብቻ አምላክ’ የሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጪው “አዲስ ዓለም” የይሖዋ ድንቅ ሥራዎች ክብሩንና ጥሩነቱን መመስከራቸውን ይቀጥላሉ