የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
ገሪዛን ‘በዚህ ተራራ ላይ ሰግደናል’
ከጉድጓድ ውኃ ልትቀዳ የመጣችው ሳምራዊት ሴት። ይህ ሐረግ ኢየሱስ የሰማርያ ከተማ በሆነችው በሲካር “በያዕቆብ ጉድጓድ” አጠገብ ለአንዲት ሴት ስለሰጠው የአጋጣሚ ምስክርነት የሚገልጸውን ታሪክ አያስታውስህምን? ለዚህ ትልቅ ትርጉም ያለው ታሪክ ያለህ ማስተዋል እንዲጨምር ትፈልጋለህን?—ዮሐንስ 4:5-7
ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን እነዚህን ተራራዎች ተመልከት።a በስተግራ (በስተ ደቡብ) በኩል የሚገኘው በዛፍ የተሸፈነው ገሪዛን ነው። ለምና ውብ እንዲሆን ያደረጉት ብዙ የውኃ ምንጮች አሉት። በስተቀኝ (በስተ ሰሜን) የሚገኘው በመጠኑ አለትማና የተራቆተ ሆኖ የሚታየው ጌባል ነው።
በሁለቱ ተራሮች መካከል የሴኬም ለም ሸለቆ ተንጣሏል። የአምላክ ወዳጅ የሆነው አብራም (በኋላ አብርሃም ተብሎ የተሰየመው) በተስፋይቱ ምድር በኩል አድርጎ ሲጓዝ በሴኬም እንዳረፈ ትዝ ይበልህ። እዚህ ቦታ ለተገለጠለትና ይህን ምድር ለዘሩ ለመስጠት ቃል ለገባለት ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ። (ዘፍጥረት 12:5-7) ይህ ሥፍራ ተስፋ የተገባው ምድር እምብርት ስለነበረ ተስፋውን በዚህ ቦታ መቀበሉ ተገቢ ነበር። ይህ የእሥራኤላውያን አባት ከገሪዛን ወይም ከጌባል ተራራ ራስ ላይ ሆኖ ከተስፋይቱ ምድር የሚበዛውን ክፍል ለመመልከት ይችል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ናብሉስ በመባል የምትታወቀው የሴኬም ከተማ ታላቅ መናኸሪያ የነበረች ስትሆን በባሕር ዳርቻውና በዮርዳኖስ ሸለቆ መካከል ከሰሜን እስከደቡብ ከሚወስደው መንገድ ከሰሜን እስከ ምዕራብ ወደሚወስደው መንገድ ድረስ ባለው ሥፍራ ትገኝ ነበር።
የአብርሃም መሠዊያ በዚህ ቦታ ከተደረጉት መታወስ የሚገባቸው ሃይማኖታዊ ክንውኖች አንዱ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ያዕቆብ በዚህ አካባቢ መሬት ገዛና እውነተኛውን አምልኮ ፈጸመ። በገሪዛን ተራራ ግርጌ አቅራቢያም አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ ወይም በገንዘቡ አስቆፍሮ ነበር። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ሳምራዊቷ ሴት ለኢየሱስ “ይህን ጉድጓድ የሰጠን አባታችን ያዕቆብ . . . ራሱን ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል” በማለት ነገረችው። ይህ ጉድጓድ ሐዋርያው ዮሐንስ “የያዕቆብ የውኃ ምንጭ” [አዓት] በማለት ስለጠራው የሚመነጭ የውኃ ጉድጓድ የነበረ ሊሆን ይችላል።
እውነተኛው አምልኮ ከገሪዛንና ከጌባል ጋር በተያያዘ ሁኔታ መጠቀሱ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት እሥራኤላውያንን እዚህ ቦታ እንዳመጣቸው ያስታውስህ ይሆናል። ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ አንድ መሠዊያ ሠርቶ ነበር። ኢያሱ “የሕጉን ቃሎች በረከቱንና እርግማኑን” ሲያነብ ሕዝቡ ግማሽ በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት፣ ግማሹ ደግሞ በጌባል ተራራ ፊት ቆመው በዓይነ ሕሊናህ ይታዩህ። (ኢያሱ 8:30-35፤ ዘዳግም 11:29) ከዓመታት በኋላ ኢያሱ እዚህ ቦታ ተመልሶ በመምጣት የመጨረሻ ምክሩን ሲሰጥ “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] እናመልካለን [እናገለግላለን አዓት]” ብሏል። ሕዝቡም እንዲሁ ለማድረግ ቃል ገቡ። (ኢያሱ 24:1, 15-18, 25) ይሁንና በእርግጥ ይሖዋን ያመልኩ ይሆንን?
የዚህ ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ያደረገውን ንግግር እንድትረዳ ይረዳህ ይሆናል። መገንዘብ እንደምትችለው በዚህ በሰማርያ አብርሃም፣ ያዕቆብና ኢያሱ የተከተሉት እውነተኛ አምልኮ አልቀጠለም ነበር።
አሥሩ ሰሜናዊ ነገዶች ከተገነጠሉ በኋላ ወደ ጥጃ አምልኮ አዘነበሉ። ስለዚህ ይሖዋ በ740 ከዘአበ በአሶራውያን ይህን አካባቢ ድል አድርገው እንዲገዙት ፈቀደ። አሶራውያንም የሚበዛውን ሕዝብ ማርከው በመውሰድ ከሌላ የአሦር ግዛት ክፍሎች እንግዳ አማልክትን የሚያመልኩ ባዕድ ሕዝቦችን አምጥተው አሠፈሩበት። ከእነዚህ አረማውያን አንዳንዶቹ ከእሥራኤላውያን ጋር ተጋብተው እንደ መገረዝ የመሳሰሉትን አንዳንድ የእውነተኛ አምልኮ ትምህርቶች ሳይማሩ አይቀሩም። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የተገኘው የሳምራውያን አምልኮ ሙሉ በሙሉ አምላክን የሚያስደስት አልነበረም።—2 ነገሥት 17:7-33
ሳምራውያን በቅይጥ አምልኮአቸው ውስጥ ቅዱስ ጽሑፍ ነው ብለው የተቀበሉት አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነበር። በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አካባቢ በኢየሩሳሌም ከነበረው የአምላክ ቤተ መቅደስ ጋር በመፎካከር በገሪዛን ተራራ ላይ አንድ ቤተ መቅደስ ሠርተው ጨረሱ። ከጊዜ በኋላ የገሪዛን ቤተ መቅደስ ለዚየስ (ወይም ጁፒተር) የተወሰነ ሆነና በመጨረሻም ተደመሰሰ። ሆኖም የሳምራውያን አምልኮ በገሪዛን ላይ እንዳተኮረ ቀጥሎ ነበር።
እስከአሁንም ድረስ ሳምራውያን በገሪዛን ተራራ ላይ ዓመታዊውን የማለፍ በዓል ያከብራሉ። በርካታ ጠቦቶች ይታረዳሉ። በጎቹ ከታረዱ በኋላ ጠጉራቸው በቀላሉ እንዲነቀል የፈላ ውኃ በያዙ በርሜሎች ውስጥ ይነከሩና ሥጋው እስኪበስል ድረስ ለበርካታ ሰዓታት ይቀቀላል። እኩለ ሌሊት ሲሆን ከኢየሩሳሌም የሚመጡ ብዙ ሰዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳምራውያን የፋሲካ ምግባቸውን ይበላሉ። ከታች ባለው ሥዕል ሳምራዊው ሊቀ ካህን ራሱን ሸፍኖ በገሪዛን ተራራ ላይ የማለፉን በዓል ሥነ ሥርዓት ሲመራ መመልከት ትችላለህ።
ሳምራዊቷ ሴት ለኢየሱስ “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ” ብላ እንደነገረችው አስታውስ። ኢየሱስ “በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። . . . ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋል” በማለት ለሴቲቱ፣ ለእኛም ጭምር ትክክለኛውን ማብራሪያ ሰጠ።—ዮሐንስ 4:20-24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን ፎቶግራፍ በ1993 የይሖዋ ምስክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ በትልቁ ለማየት ትችላለህ።
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[ምንጭ]
Garo Nalbandian
Garo Nalbandian