የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 1/1 ገጽ 26-30
  • አምላክ ‘ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ ‘ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም’
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ግዛቶች
  • ሩማንያ
  • የቀድሞይቱ ዩጎዝላቪያ ግዛቶች
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 1/1 ገጽ 26-30

አምላክ ‘ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም’

“እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው። ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።” (ዕብራውያን 6:10) እነዚህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት በምሥራቅ አውሮፓ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ በትክክል ተፈጽመዋል። እነዚህ ምሥክሮች በቀድሞዋ ሶቪዬት ቁጥጥር ይመሩ በነበሩት መንግሥታት በተጫነባቸው እገዳ ሥር ለበርካታ ዓመታት ብዙ ችግር ያሳለፉ ቢሆኑም ለአምላክ ስም መከበር በታማኝነት አገልግለዋል። ይሖዋ መልካም ሥራቸውን ስላስታወሰ የመንግሥቱን በረከቶች እያፈሰሰላቸው ነው። ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ አገሮች መካከል ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት የሶስቱን ብቻ እንመልከት።

የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ግዛቶች

በቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ግዛቶች 1992 የአገልግሎት ዓመት የመንግሥት አስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር 35 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከ49,171 ወደ 66,211 ከፍ እንዳለ ሪፖርት ተደርጎአል። ይሁን እንጂ እነዚህ አስፋፊዎች በከፍተኛ ትጋት ይሠሩ ስለነበረ ጭማሪው በዚህ ብቻ የተወሰነ አልሆነም። ይህንን ከተበረከቱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችና መጽሔቶች ብዛት መገንዘብ ይቻላል። በተጨማሪም በብሮሹሮችና በትናንሽ መጻሕፍት በሚገባ ተጠቅመዋል። 1,654,559 የሚያክሉ ብሮሹሮችና አነስተኛ መጻሕፍት አበርክተዋል። ይህም አምና ከተበረከቱት 477,235 የሚያክሉ ብሮሹሮችና ንዑስ መጻሕፍት በሶስት እጥፍ ይበልጣል። በእነዚህ በተበረከቱ ጽሑፎች የተገኘው ምላሽ ምን ነበር? የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ቁጥር እጥፍ አደረገው። በአሁኑ ጊዜ 38,484 የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ።

በተጨማሪም በረዳት አቅኚነት አገልግሎት የሚደረገው ተሳትፎ በ94 በመቶ ጨምሮአል። ይህም ለአዳዲስ ተጠማቂዎች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ግልጽ ነው። የአዳዲስ ተጠማቂዎች ቁጥር 26, 986 የደረሰ ሲሆን በወዲያኛው ዓመት ከተጠመቁት 6,570 ሰዎች ጋር ሲወዳደር 311 በመቶ ጭማሪ ተገኝቶአል ማለት ነው።

አዳዲስ ከተጠመቁት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ለእውነት ያላቸው ፍላጎት ሊቀሰቀስ የቻለው እንዴት ነበር? ፍላጎታቸው እንዲቀሰቀስ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ጥናቱን የሚመሩት ምሥክሮች የሚያሳዩት ልባዊ አሳቢነት ነበር። በሞልዶቫ የሚኖር መሪ የበላይ ተመልካች እንዲህ ይላል:-

“እኔና ባለቤቴ ቀደም ሲል ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት የነበራት አንዲት ሴት ጎበኘን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት። ባሏ ግን ምንም ፍላጎት አላሳየም ነበር። ጥናቱን ልንቀጥልላት በሄድንበት አንድ ቀን የአየሩ ሁኔታ በጣም ቀዝቃዛና በረዶአማ ሆኖ ነበር። በመንገዶች ላይ የሚታይ ሰው አልነበረም። እኛ ግን በቀጠሮው ሰዓት እቤትዋ ለመድረስ ቻልን። ይህች ሴት ለባልዋ ‘እነዚህ ሰዎች ምን ያህል እንደሚያስቡልን ተመልከት። ይህ ሁሉ በረዶ ቢኖርም በሰዓቱ ሊደርሱ ችለዋል’ አለችው። ይህ አጋጣሚ ባልዋ በጥሞና እንዲያስብ አደረገው። አስተሳሰቡን ለውጦ በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ እርሱና ሚስቱ የተጠመቁ ምስክሮች ሆነዋል።”

የምሥክሮቹ ትህትና ሰዎች ለምሥራቹ ፍላጎት እንዲያሳዩ የሚገፋፋበት ጊዜም አለ። በሞልዶቫ የሚኖር አንድ ሽማግሌ የሚከተለው ተሞክሮ አጋጥሞታል:-

“በምሰብክበት ክልል ያነጋገርኩት ሰው ስለይሖዋ ምሥክሮች ለማወቅ የማይፈልግ ሰው ነበር። እንደ አያቱና አባቱ እርሱም ኦርቶዶክስ እንደሆነ ነገረኝ። ከግቢውም እንድወጣለት ጠየቀኝ። ይሁን እንጂ ከመውጣቴ በፊት የመጣሁበትን ምክንያት እንድናገር ዕድል ሰጠኝ። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው” የሚለውን የማቴዎስ 28:19 ጥቅስ አሳየሁትና የመሰብሰቢያ ቦታችንን አድራሻ ሰጥቼው ሄድኩ። ይህ ሰው ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ስብሰባችን መጥቶ ሳየው በጣም ገረመኝ። ሙሉው ፕሮግራም እስኪያልቅ ድረስ ቆየ። ጥሩ አቀባበል ሳያደርግልኝ በመቅረቱ ሳምንቱን በሙሉ ሲፀፅተው እንደሰነበተ ነገረኝ። ወዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። በአሁኑ ጊዜ ወንድማችን ሆኖአል።

ሌላው በአገልግሎት ዓመቱ ጎልቶ የታየው ገጽታ በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ወንድሞቻችን ችግር እርዳታ ለመስጠት የተደረገው ጥረት ነበር። በ1991/1992 የክረምት ወራት ብቻ 4000 ኩንታል የሚያክል ምግብና መጠኑ እጅግ ብዙ የሆነ የወንዶች፣ የሴቶችና የሕጻናት ልብስ ለችግረኞች ተልኮአል። እነዚህ የእርዳታ ዕቃዎች በቀድሞይቱ የሶቪዬት ኅብረት ግዛቶች በሙሉ፣ በሳይቤሪያ በሚገኘው ከኢርኩትስክ እስከ ጃፓን ድንበር አጠገብ እስከሚገኘው ካበሮቭስክ ድረስ ለሚኖሩ ወንድሞች ታድለዋል። በእርግጥም ይሖዋ ወንድሞቻችን ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር እንዳልዘነጋ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነበር። ይህ በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት የታየው የወንድማማች ፍቅር እነዚህ ወንድሞች ከዓለም አቀፉ ቤተሰብ ጋር አንድ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ አስችሎአቸዋል። ለምሳሌ ያህል በዩክሬይን የምትኖር አንዲት እህት ለቅርንጫፍ ቢሮው እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች:-

“የሰጣችሁን እርዳታ ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል። ይሖዋ ስላልረሳን እንባ እየተናነቀን አመስግነነዋል። እርግጥ፣ በአሁኑ ጊዜ ቁሳዊ ችግር አለብን። ቢሆንም በምዕራብ ከሚገኙት ወንድሞቻችን በደረሰን ዕርዳታ አማካኝነት በሁለት እግራችን ለመቆም ችለናል። አሁን እርዳታ ስለሰጣችሁን ቤተሰባችን የበለጠ ጊዜ በይሖዋ አገልግሎት ሊያሳልፍ ይችላል። ይሖዋ ከፈቀደ እኔና ሴት ልጄ በበጋው ወራት በረዳት አቅኚነት እናገለግላለን።

በተጨማሪም የዕለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ የተደረገው ጥረት የውጭ ሰዎች ምሥክሮች ፍቅራቸውን በሥራ እንደሚያሳዩ ለመመልከት ስላስቻላቸው ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት አስችሎአል። በአንድ ሌላ ጉባኤ የሚኖር ቤተሰብ እንዲህ ሲል ጽፎአል። “የተላከልን የምግብና የልብስ እርዳታ ደርሶናል። በጣም ብዙ ነው። የሰጣችሁን ድጋፍና ማጽናኛ እኛም ለሌሎች መልካም ማድረግ እንደሚገባን አስተምሮናል። ይህ የፍቅር ድርጊት በማያምኑ ሰዎች ፍላጎት ባላቸው ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው መስተዋሉ አልቀረም። ስለእውነተኛው ወንድማማችነት ከፍተኛ ምሥክርነት ለመስጠት አስችሎአል።”

ባለፉት የሰኔና የሐምሌ ወራት “ብርሃን አብሪዎች” በሚል አጠቃላይ መልእክት የተደረጉት አምስት የወረዳ ስብሰባዎችና አንድ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ አማካኝነትም ይሖዋ ምሥክሮቹ ያደረጉትን ሥራና ለስሙም ያሳዩትን ፍቅር እንደባረከ የሚየሳዩ ማስረጃዎች ታይተዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ 91,673 ሰዎች ሲገኙ 8,562 ሰዎች ተጠምቀዋል። ከሁሉም የሚበልጥ ብዛት ያላቸው ሰዎች የተገኙት ብሔራት ኣቀፍ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት በሴይንት ፒተርስበርግ ነበር። በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ 30 አገሮች የመጡ ተወካዮችን ጨምሮ 46,214 ሰዎች በኪሮቭ ስታዲየም ተሰብስበው ነበር።

በሳይቤርያ አንድ የ60 ዓመት ሰው በኢርኩትስክ የሚደረገውን የስብሰባ ቦታ ለማየት ብቻ ሲል መጣ። እርሱም እንዲህ ብሎአል፣ “ሁሉም ተሰብሳቢዎች በሚገባ የለበሱ፣ ፈገግታ የተሞላ ፊት ያላቸውና እርስበርሳቸው የሚከባበሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እንደ አንድ ቤተሰብ ናቸው። በዚህ ስታዲየም ብቻ ሳይሆን በዕለታዊ ሕይወታቸውም በወዳጅነት የሚተያዩ ሰዎች እንደሆኑ ለማስተዋል ይቻል ነበር። በጣም ጥሩ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ለማግኘት በመቻሌ ምን ዓይነት ድርጅት እንደሆነ የተሻለ ዕውቀት ለማግኘት ችዬአለሁ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘትና አብሬአቸው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት እፈልጋለሁ።”

በዚሁ 5,051 ሰዎች በተገኙበት በኢርኩትስክ ስብሰባ አንዲት ከያኩት ሪፓብሊክ የመጣች ፍላጎት ያላት ሴት እንዲህ ብላለች። “እነዚህን ሰዎች ስመለከት ከደስታዬ የተነሣ ለማልቀስ ይቃጣኛል። ይሖዋ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር እንድተዋወቅ ስላስቻለኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። እዚህ ስብሰባ ላይ ጽሑፎችን አግኝቼአለሁ። ስለእነዚህም ጽሑፎች ከሰዎች ጋር ለመነጋገር እፈልጋለሁ። የይሖዋ አምላኪ ለመሆን በጣም እፈልጋለሁ።”

6,605 ሰዎች ተገኝተውበት የነበረው የካዛክስታን አልማ አታ ማዕከላዊ ስታዲየም ዲሬክተር የሚከተለውን ተናግረዋል። “በሁኔታችሁ በጣም እደነቃለሁ። ሁላችሁም፣ ወጣቶችም ሆናችሁ ሽማግሌዎች መከበር የሚገባችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ አሁን አምኜአለሁ። በአምላክ አምናለሁ ለማለት አልችልም። ይሁን እንጂ በወንድማማችነታችሁ፣ ለመንፈሳዊና ለቁሳዊ ነገሮች ባላችሁ አመለካከት በሚተላለፉት ቅዱሳን ነገሮች አምናለሁ።”

በአልማ አታ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረ አንድ ፖሊስ እንደሚከተለው ብሎአል። “ከእናንተ ጋር ስገናኝ ሁለተኛ ጊዜዬ ሲሆን ሁለቱንም ጊዜ ያገኘኋችሁ በትላልቅ ስብሰባ ላይ ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሥራት በጣም የሚያስደስት ነገር ነው።”

ሩማንያ

ይሖዋ በሩማንያ የሚኖሩ ወንድሞችም ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር አልረሳም። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ምሥክሮቹ ብዙ አስደሳች ነገር ለመመልከት ችለዋል። በመጀመሪያ በቡካሬስት የቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቁሞአል። ሕጋዊ እንቅስቃሴ የተቋረጠው በ1949 ነበር። በአዲስ ሕንጻ ውስጥ የተቋቋመው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ 20 ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ። ቅርንጫፍ ቢሮው 24,752 አስፋፊዎችን ያገለግላል። ይህም ምንም ጊዜ ተገኝቶ የማያውቅ ከፍተኛ ቁጥር ሲሆን ከአምናው አማካይ የአስፋፊዎች ቁጥር 21 በመቶ ብልጫ አለው።

አስፋፊዎቹ ለበርካታ ዓመታት በምሥጢር ሲሰብኩ የቆዩ ቢሆኑም ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን የስብከት ሥራ መለማመድ ጀምረዋል። ከሚዩርስ ክፍለ ሀገር የተገኘ አንድ ተመክሮ አንዳንድ ምሥክሮች ለመመስከር በሚያስችላቸው አጋጣሚ ሁሉ በጉዞ ላይ እንዳሉ እንኳን እንዴት በጥሩ ሁኔታ እንደሚጠቀሙ ያሳያል። ቅርንጫፍ ቢሮው እንዲህ በማለት ጽፎአል:-

“አንድ አስፋፊ ከአንድ ባቡር ፉርጎ ወደሌላው እየተዘዋወረ ለመስበክ ወሰነ። ሰዎቹ በአጠቃላይ የተቀባይነት ምላሽ ያሳዩ ቢሆኑም በመጨረሻው ፉርጎ ግን ችግር አጋጠመው። ከመንገደኞቹ መካከል መጽሔቶችቻንን ለመውሰድ የፈለገ አንድም ሰው አልነበረም። በመጨረሻም አንድ ሰው ከመካከላቸው በብስጭት ብድግ ብሎ ‘መጽሔቶችህን በሙሉ በመስኮት ወርውሬ እጥላለሁ። ይህን ያህል በሃይማኖታችሁ የምታሰለቹን ለመንድን ነው? ሲል ጮሀ። አስፋፊውም በደግነት መንፈስ መጽሔቶቹን ወደ ውጭ ቢወረውር እንኳን ከመሬት የሚያነሱአቸው ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው አለዋጋ እንደማይቀሩ ነገረው። ሰውዬው በአስፋፊው እርጋታ ተደንቆ መጽሔቶቹን ከአስፋፊው ተቀበለና በክፍሉ ውስጥ ለነበሩት ተጓዦች ማደል ጀመረ። መንገደኞቹ በሙሉ መጽሔቱን ተቀበሉ። ሰውዬው ሁሉንም አድሎ ስለጨረሰ ለራሱ የሚሆን መጽሔት አጣ። በዚህም ምክንያት አስፋፊው ‘ጌታዬ፣ ለራስዎስ አንድ ቅጂ አይፈልጉም?’ ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ሰውዬው ሁለት መጽሔት ወስዶ ከነበረ መንገደኛ አንዱን ነጠቀና ‘አሁን አንድ አግኝቼአለሁ’ አለ።”

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ በብዙ አገሮች የሕዝብ ክርስትና ቀሳውስት ተቃውሞ አስነስቶአል። በሩማንያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ብዙ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ይቆጣሉ። ይሁን እንጂ ይህ ቁጣቸው ለስሙ ባሳዩት ፍቅር ምክንያት ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዳይባርካቸው ሊያግደው አልቻለም። አንድ የክልል የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ጽፎአል።

“ከአካባቢው ጉባኤ ጋር ሆነን በገጠር አከባቢዎች ለመስበክ ሄድን። በጠቅላላው አንድ መቶ ወንድሞች ነበሩ። አንድ አውቶቡስ ተከራይተን 56 ኪሎሜትር ርቆ ወደሚገኝ አነስተኛ ከተማ ሄድን። በከተማው የባህል አዳራሽ ውስጥ በሚደረገው የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ ብዙ ሰዎችን ጋበዝን። ልክ ስብሰባው እንደጀመረ አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ መጥቶ ስብሰባችን መረበሽ ጀመረ። የፖሊስ ባለሥልጣኖች ቄሱን ለማስቆም ሞክረው ነበር። ቢሆንም ዝም ለማለት እምቢተኛ ሆነ። የዋናውን መግቢያ በር መስተዋት በመስበር ስብሰባውን ለማስቆም ቻለ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ቄሱ ያደረገው ነገር አላስደሰታቸውም ነበር። ከዚያ በኋላ በስብሰባው ለተገኙት ሁሉ ጥሩ ምሥክርነት ተሰጥቶ ብዙ ጽሑፎችን ለማበርከት ተቻለ።

በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። አንድ የዘወትር አቅኚ ወደ ኦልት ክፍለ ሀገር በሄደ ጊዜ በዚያ የነበሩ ዘጠኝ ወንድሞች ብቻ ነበሩ። ክልሉ በጣም ሠፊ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ የምሥክሮቹ ቁጥር 27 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አምስቱ እንደገና የተነቃቁ አስፋፊዎች ነበሩ። አቅኚው መኖሪያው ያደረገው አንድም ምሥክር ያልነበረበትን የኮራቢያ ከተማ ነበር። ምሥክሮቹ በመጡ በ45ኛው ቀን የአካባቢው ደብር አለቃ በክራይኦቫ ሬድዮ ሥራቸውን የሚቃወም መግለጫ ሰጡ። የኮራቢያን ከተማ በትምህርታቸው ወርረው ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ለማድረግ በመሞከር ላይ ናቸው አለ። በዚያ አካባቢ የሚደረገውን ሥራ ለማስቆምና የምሥክሮቹን ስም ለማጥፋት የሚደረገው ጥቃት ቀጠለ። ጥቃቱ ከፍተኛ ከደረጃ ላይ የደረሰው ወንድሞች በቡካሬስት ይደረግ በነበረው የወረዳ ስብሰባ ለመገኘት በሄዱ ጊዜ ነበር። የኮራቢያው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አለቃ ከቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ በኋላ የሚከተለውን ጠንካራ ማስታወቂያ አሰማ:- “መላውን አካባቢ በጽሑፋቸው በበከሉትና ሰዎችን በመረዙት ምሥክሮች ላይ ፖሊስ እርምጃ እንዲወስድ ለማነሳሳት ሁላችንም ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ይኖርብናል።” ይሁን እንጂ ስብሰባው ሊደረግ ከታሰበበት ቀን በፊት በነበረው ምሽት አንድ እንግዳ ነገር ተፈጠረ። ዘራፊዎች መጥተው ቤተ ክርስቲያኑንና ከተማውን የባሕል አዳራሽ አፈረሱት። በዚህ ምክንያት የተቃውሞ ስብሰባው ሳይደረግ ቀረ።

የቀድሞይቱ ዩጎዝላቪያ ግዛቶች

የ1992 የአገልግሎት ዓመት በዩጎዝላቪያ አካባቢ ለሚኖሩ ወንድሞች በጣም አስቸጋሪ ነበር። ቢሆንም አንዳንድ አስደሳች ተሞክሮዎች አጋጥመዋቸዋል። ይሖዋ ሥራቸውንና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር ስላልረሳ አመስጋኞች ናቸው።

ጦርነቱ መጀመሪያ በስሎቬንያ ከዚያም በክሮሺያ በኋላም በቦስኒያና ሄርዜጎቪና ጀመረ። ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ረፓብሊክ የተገነጠሉ አምስት አዳዲስ አገሮች የየራሳቸውን ድንበር፣ ሕግና ገንዘብ ለማቋቋም መጣጣር ጀመሩ። በመቶ የሚቆጠሩ ወንድሞች ቤታቸውን ትተው በመሸሽ በሌሎች አከባቢዎች በሚኖሩ ወንድሞቻቸው ቤት ለመጠለል ተገድደዋል። በምሥራቅ አውሮፓ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች እንደተደረገው በትላልቅ ከተሞች የድንገተኛ እርዳታ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ለችግረኛ ወንድሞቻችን መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ማቅረብ ጀመሩ። በዚህ የአገልግሎት ዓመት 550 ኩንታል የሚያክል ምግብ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ጉባኤዎች ለሚኖሩ ወንድሞች ታድሎአል። ብዙ የአድናቆት ደብዳቤዎች ደርሰውናል።

በዱብሮቭኒክ የሚኖሩ ወንድሞች ለተሰጣቸው እርዳታ ምን ያህል አመስጋኞች እንደሆኑ ገልጸዋል። አንዲት እህት የተሰጣትን የምግብ እርዳታ ይዛ ወደ ቤትዋ በምትሄድበት ጊዜ ጎረቤትዋ እንቁላል ከየት እንደገዛች ጠየቀቻት። እህትም በሌላ አካባቢ የሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞችዋ እንደላኩላት ነገረቻት። ጎረቤትዋ በጣም ተደነቀች። በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ያልታወቀ ሰው ለአንድ የስሎቬንያ ሽማግሌ ደውሎ እንዲህ አለው። “የይሖዋ ምሥክሮች ከወንድሞቻቸው የተላከውን ምግብ በትክክል እንደሚያከፋፍሉ ሰምቼአለሁ። ለብዙ ሰዎች የምግብ ጥቅል ልኬ ነበር። ግን አንዱም አልደረሳቸውም እነዚህን የእርዳታ ዕቃዎች ለእናንተ ብልክ እናንተ ልታከፋፍሉልኝ ትችላላችሁ?” በተጨማሪም ጋዜጦችና ሬዲዮ ጣቢያዎች ስለ አስቸኳይ እርዳታ አቅርቦታችን ጥሩ ሪፖርት አቅርበዋል።

አንድ በ1991 በዛግሬብ ከተማ ተደርጎ በነበረው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የተጠመቀ ወንድም ችግሩ እየከፋ መሄዱን ተገንዝቦ አንድን የምግብ መደብር እንዳለ ገዛና ምግቡን በሙሉ በጦርነቱ አካባቢ ወደሚገኘው ቤቱ ወስዶ አስቀመጠው። የምግብ እጥረት እየተባባሰ በሄደበት ጊዜ ይህ የምግብ ክምችት ለወንድሞች ትልቅ በረከት ሆኖ ነበር።

በሳራዬቮ በሚደረገው ጦርነት ምክንያት መውጫ ላጡት ወንድሞች በአንድ ትልቅ የጭነት መኪና ምግብ ለማድረስ ፈቃድ ለማግኘት ተችሎ ነበር። ጭነቱ በደህና መድረስ መቻሉን ሪፖርት ስናደርግላችሁ በጣም ደስ ይለናል።

ጦርነቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ብዙ ጉዳት አስከትሎአል። በአገልግሎት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ስድስት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ሁለት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ መሆናቸው በጣም ያሳዝናል። አንዳንዶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር መሆን ብዙውን ጊዜ ጥሩ ጥበቃ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ተሞክሮዎች አጋጥመዋል። አንድ ጊዜ ወንድሞች በቤልግሬድ በሚደረግ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በአውቶቡስ ይጓዙ ነበር። ወታደሮች አውቶቡሱን አስቆሙና የአንድ ሌላ ሃይማኖት አባል የሆነ በመካከላቸው ይገኝ እንደሆነ ጠየቁ። ወንድሞች ማንም እንደሌለ ነገሩአቸው። የመታወቂያ ወረቀቶቻቸውን እንዲያሳዩ ተጠየቁ። የአንዳንዶቹ ስም የዚያ ሃይማኖት አባሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ ነበሩ። ወታደሮቹ ውሸታሞች ናችሁ አሉአቸው። ይሁን እንጂ ወንድሞች ከዚህ ቤተ ክርስቲያን መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው ነበር። በዚያ ሃይማኖት ውስጥ የተወለዱ ቢሆኑም አሁን ግን የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ወደ ስብሰባ በመጓዝ ላይ እንደሚገኙ ነገሩአቸው። ወታደሮቹም ይህን ሲሰሙ ለቀቁአቸው።

አቅኚዎች አሁንም በጋለ ቅንዓት በአገልግሎታቸው ቀጥለዋል። ይህም ሥራውን በጣም አነቃቅቶአል። አስደሳች ሽፋን ይዞ የሚወጣው ባለቀለም መጠበቂያ ግንብ በአካባቢው ዋና ዋና ቋንቋዎች በሙሉ ይተረጎማል። ለእውነትና ለጽድቅ አፍቃሪዎች የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ በማቅረብ ላይ ይገኛል። (ሉቃስ 12:42) በ1992 የአገልግሎት ዓመት 674 አዳዲስ ወንድሞችና እህቶች ተጠምቀዋል።

በእርግጥ አምላክ በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙት ወንድሞች ያደረጉትን ሥራና ለስሙም ያሳዩትን ፍቅር አልረሳም። ከዚህም በላይ አምላኪዎቹ በሙሉ የትም ይኑሩ የት ጳውሎስ ቀጥሎ በዕብራውያን 6:11 ላይ የሰጠውን ግሩም ምክር እንዲከተሉ ይፈልጋል። “ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከመጨረሻ ድረስ እንድታሳዩ እንመኛለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ