የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 1/1 ገጽ 31
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምድርን መንከባከብ ያለብን ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2007
  • የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ከልብና ከአእምሮ ውስጥ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • አምላክ ንጹሕ የሆኑ ሰዎችን ይወዳል
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 1/1 ገጽ 31

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ክርስቲያኖች የአከባቢያችንን የምድር፣ የባሕርና የአየር መበከል በመቀነስ ረገድ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

የይሖዋ ምስክሮች በመሆናችን መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን በአሁኑ ጊዜ እያበላሹ ያሉት በርካታ ኢኮሎጂያዊ (ሥነ ምህዳራዊ) ችግሮች በጣም ያሳስቡናል። ከአብዛኞቹ ሰዎች ይልቅ ምድር ለፍጹም ሰብአዊ ቤተሰቦች ንጹሕና ጤናማ መኖሪያ እንድትሆን የተፈጠረች መሆንዋን የምንገነዘብ እኛ ነን። (ዘፍጥረት 1:31፤ 2:15-17፤ ኢሳይያስ 45:18) በተጨማሪም አምላክ “ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ” ዋስትና ሰጥቶናል። (ራእይ 11:18) ስለዚህ ሰው ያለማቋረጥ ምድራችንን እያበላሻት በመሆኑ በዚህ ብልሽት ላይ ላለመጨመር ሚዛናዊና ምክንያታዊ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው። ይሁንና “ምክንያታዊ” የሚለውን ቃል ልብ በል። ሐሳባችን በኢኮሎጂያዊ ጉዳዮችና ተግባሮች እንዲዋጥ እንዳንፈቅድ መጠንቀቅም ቅዱስ ጽሑፋዊ አግባብነት ያለው ነገር ነው።

የተለመደው የሰው አኗኗርም እንኳን ቆሻሻ ይፈጥራል። ለምሳሌ ያህል የምግብ ምርቶችን ማብቀል፣ ለምግብነት ማዘጋጀትና መብላት ራሱ የሚበዛው ክፍል በምድር ላይ ባሉ ጥቃቅን ፍጥረቶች አማካኝነት በስብሶ በጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ቆሻሻን የሚፈጥር ነው። (መዝሙር 1:4፤ ሉቃስ 3:17) ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ያዘጋጀው የተጠበሰ ዓሣ መጠነኛ ጢስ፣ አመድና የአጥንቶች ቆሻሻ ሳይፈጥር አልቀረም። (ዮሐንስ 21:9-13) ይሁን እንጂ ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው የመሬት ዑደቶች እንደነዚህ ያሉትን ቆሻሻዎች እንዲያስተናግዱ ሆነው የተሠሩ ናቸው።

የአምላክ ሕዝቦች ስለኢኮሎጂያዊ ጉዳዮች ግዴለሾች መሆን የለባቸውም። ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹ ኢኮሎጂያዊና የጤና አጠባበቅ ጥቅም ያለውን ቆሻሻ የማስወገድን እርምጃ እንዲወስዱ ይፈልግባቸው ነበር። (ዘዳግም 23:9-14) አምላክ ምድርን ስለሚያጠፉ ሰዎች ያለውን አመለካከት ስለምናውቅ አካባቢያችንን ንጹሕ አድርጎ ለመጠበቅ የምንችለውን ነገር ሁሉ ከማድረግ ችላ ማለት እንደሌለብን ጥርጥር የለውም። ይህንንም ልናንፀባርቅ የምንችለው ቆሻሻን፣ በተለይም ደግሞ መርዝነት ያላቸውን ነገሮች በተገቢው ሁኔታ በማስወገድ ወይም በመቅበር ነው። ያለቁ ወይም ያረጁ ነገሮችን እንደገና በሥራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት በትጋት እንተባበራለን፣ ይህ በቄሳር የታዘዘ ከሆነ ደግሞ ለመታዘዝ የሚያስገድደን ተጨማሪ ምክንያት ይኖረናል። (ሮሜ 13:1,5) በምድር ላይና በባሕር ውስጥ በተጠራቀመው የቆሻሻ ክምር ላይ ተጨማሪ ቆሻሻ በሚጨምሩ የሸቀጥ ውጤቶች ከመጠቀም ፈንታ በቀላሉ ሊበሰብሱ የሚችሉ ምርቶችን በመምረጥ ተጨማሪ እርምጃ በመውሰዳቸው እርካታ የሚያገኙ አንዳንድ ግለሰቦችም አሉ።

ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን በሕግ ካልተጠየቀ በቀር በዚህ ኣቅጣጫ እስከ ምን ደረጃ ድረስ መሄድ እንዳለበት የሚወስነው ራሱ ነው። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በቀላሉ ከልክ በማለፍ ወጥመድ እንደሚያዙ ከዜና ማሠራጫዎች በግልጽ መረዳት ይቻላል። ያለጥርጥር ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ . . . በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፣ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም?” በማለት የሰጠው ምክር እዚህ ላይ አግባብነት ያለው ነው። (በማቴዎስ 7:1, 3) ይህን ማስታወሳችን ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን እንዳንዘነጋ ሊረዳን ይችላል።

ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” በማለት ጽፎአል። (ኤርምያስ 10:23) የሰው ልጅ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ችላ ማለቱ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ እንደተገለጸው “የሚያስጨንቅ ዘመን” ከፊት ለፊቱ እንዲጋረጥበት አድርጓል። አምላክ በራእይ 11:18 ላይ ያስጻፈው ትንቢትም የአከባቢ መበከልን ጨምሮ ሰው ምድርን ከታላላቅ ኢኮሎጂያው ችግሮች ለማላቀቅ የሚደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ የተሳካ እንደማይሆን ያረጋግጣል። አለፍ አለፍ ብሎ አንዳንድ መሻሻል ሊኖር ይችል ይሆናል፣ ዘላቂው መፍትሔ ግን የአምላክ ጣልቃ ገብነት የሚጠይቅ ነው።

በዚህ ምክንያት ላይ ላዩን የሚታዩትን የችግሩን ምልክቶች ለማስወገድ ከመሞከር ይልቅ ጉልበታችንና ሀብታችን በመለኮታዊ መፍትሔዎች ላይ መዋል አለበት። በዚህም በኩል የሚበዛውን የአገልግሎቱን ክፍል ‘ለእውነት በመመስከር’ ላይ ያዋለውን የኢየሱስን ምሳሌነት እንከተላለን። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ የአከባቢ መበከልን ጨምሮ ዓለምን በመመገብ ወይም ስፋት ያላቸውን ማኅበራዊ ችግሮች በማስወገድ ፈንታ የገለጸው የሰው ዘርን ላጠቁት ችግሮች ፍጹም መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ ነው።—ዮሐንስ 6:10-15፤ 18:36

ለሰዎች ያለንን ፍቅር መሬቱን፣ ከባቢ አየሩን፣ ወይም የውኃ ምንጮችን አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ ከመበከል እንድንርቅ የሚገፋፋን ቢሆንም ለእውነት መመስከራችንንም እንቀጥላለን። ይህም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሥራ ላይ እንዲያውሉትና ሰውነታቸውን በጪስ፣ ከልክ ባለፈ አልኮል መጠጥ፣ ወይም በጎጂ ዕጾች ከማበላሸት እንዲቆጠቡ ማስተማርን ያጠቃልላል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደቀ መዛሙርት በመሆን የንጽሕና ልማዶችንና ለሌሎች አሳቢ መሆንን ተምረዋል። ስለዚህ የስብከቱ ሥራ በአሁኑ ጊዜ ያለውን አጠቃላይ የአከባቢ መበከል ችግር ለማቃለል አስተዋጽኦ አድርጎአል። ከዚህ ይበልጥ ግን ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት አምላክ ለእውነተኛ አምላኪዎቹ በቅርቡ በሚያመጣት ንጹሕ በሆነች ምድራዊ ገነት ውስጥ ለመኖር ተስማሚዎች ይሆኑ ዘንድ አሁን ባሕሪያቸውንና ልማዳቸውን ለማስተካከል ጥረት ያደርጋሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ