የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 2/15 ገጽ 12-17
  • “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን”
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሁኔታዎች በመለወጥ ላይ ናቸው
  • የክርስቲያን ጉባኤም ተነክቷል
  • በምኞት መሳብና መታለል
  • ለመቋቋም የሚረዳ ቁልፍ ነገር
  • ሁሉንም የሚያጋጥም ወደ ስህተት የሚገፋፋ ፈተና
  • በዘመናችን ትዳር የሰመረ ሊሆን ይችላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ይሖዋ ትዳራችሁን እንዲያጠናክረውና እንዲጠብቀው ፍቀዱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ‘ጋብቻ ክቡር ይሁን’
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ትዳር በቋፍ ላይ በሚሆንበት ጊዜ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 2/15 ገጽ 12-17

“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን”

“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን።” — ዕብራውያን 13:4

1. ብዙ ሰዎች ደህና ስለዘለቁ ትዳሮች የተማሩት ነገር ምንድን ነው?

ፍቺ በበዛበት በአሁኑ ዘመንም እንኳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጸና ትዳር አላቸው፤ በዚህም እየተደሰቱ ነው። የባሕርይና የአስተዳደግ ልዩነቶች ቢኖሩም ጋብቻቸውን የሰመረ እንዲሆን የሚያስችል ዘዴ አግኝተዋል። እንደዚህ ያለ ትዳር በይሖዋ ምስክሮች መካከል ይገኛል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ባልና ሚስት ትዳራቸው ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ እንደነበረበትና እርስ በርስ ቅር የሚሰኙባቸው ነገሮች እንዳጋጠሟቸው አይሸሽጉም። ሆኖም አንድ መርከብ የሚያጋጥሙትን ትንንሽ ማዕበሎች እየተቋቋመ ጉዞውን እንደሚቀጥል ሁሉ ትዳራቸውም የሚያጋጥሙትን ትንንሽ ችግሮች ተቋቁሞ እንዲቀጥል ማድረግን ተምረዋል። ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ያስቻሏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? — ቆላስይስ 3:​13

2. (ሀ) ጋብቻን ደግፈው የሚያቆሙ አንዳንድ አዎንታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ጋብቻን ሊያፈርሱ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ገጽ 14 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት)

2 ክርስቲያናዊ ጋብቻቸው ደስተኛና ዘላቂ የሆነላቸው ባልና ሚስት የሰጧቸው ሐሳቦች ብዙ ትምህርት የሚሰጡ ናቸው። ትዳር ከያዘ 16 ዓመት የሆነው አንድ ባል እንዲህ አለ:- “ችግር በሚነሳበት በማንኛውም ጊዜ አንዳችን የሌላውን ሐሳብ ለማዳመጥ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል።” ይህም ጋብቻን ከሚያጠነክሩት ነገሮች አንዱን ያጎላል። ይኸውም ግልጽና ልባዊ የሆነ የሀሳብ ግንኙነት ማድረግ ነው። ለ31 ዓመታት በትዳር ላይ የቆየች አንዲት ሚስት “በመካከላችን ያለው ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ ለማድረግ ስንል እጅ ለእጅ ተያይዘን አስቂኝ ነገሮችን ማድረግ ሁልጊዜ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ነው” በማለት ተናግራለች። ይህም የሀሳብ ግንኙነት የሚደረግበት ተጨማሪ ዘርፍ ነው። ወደ 40 ለሚጠጉ ዓመታት በጋብቻ ውስጥ የቆዩ ሌሎች ባልና ሚስት ደግሞ የተጫዋችነት መንፈስ የመያዝን ማለትም አንዱ በሌላው ላይ እንዲሁም በራስ ላይ ለመሳቅ የመቻልን አስፈላጊነት አጥብቀው ገልጸዋል። በተጨማሪም አንዳቸው የሌላውን ጥሩና መጥፎ ጎን እያዩ ታማኝ ፍቅር ማሳየታቸው ለትዳራቸው ጽናት እንደረዳም ተናግረዋል። ባልየው ስህተቶችን ለመቀበልና ከዚያም ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ መሆንም እንደረዳቸው ጠቅሷል። ግትር ወይም እልኸኛ አለመሆን ጋብቻው እንደ ደረቅ እንጨት ከመሰበር ይልቅ ለውጦችን ለማስተናገድ ላላ ይላል። — ፊልጵስዩስ 2:​1–4፤ 4:​5

ሁኔታዎች በመለወጥ ላይ ናቸው

3, 4. ለትዳር ታማኝ መሆንን በተመለከተ ምን የአመለካከት ለውጦች ተደርገዋል? ምሳሌ መስጠት ትችላለህን?

3 ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ለትዳር ታማኝ መሆንን በሚመለከት በዓለም ዙሪያ ያለው አስተሳሰብ ተለውጧል። አንዳንድ ባለ ትዳሮች ዘመናዊው የምንዝር ሌላ ስም የሆነው ከጋብቻ ውጭ በሚደረግ ምናልባትም የጾታ ግንኙነትንም ሊጨምር የሚችል ፍቅር በተለይ ሌላኛው ወገን ነገሩን ካወቀና ከተቀበለው ምንም ስህተት የለበትም ብለው ያምናሉ።

4 “ዓለም በሥነ ምግባር ሕግ ለመመራት ምንም ዓይነት ጠንከር ያለ ሙከራ ማድረጉን ትቷል ለማለት ይቻላል። ንጹሕ አኗኗር ጊዜ እንዳለፈበት ተደርጎ ወደሚታይበት ደረጃ ደርሰናል” በማለት አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ስለ ሁኔታው ያለውን አስተያየት ሰጥቷል። ታዋቂ የፖለቲካ፣ የስፖርትና የመዝናኛ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደረጃ በግልጽ ይጥሳሉ። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሰዎች ከፍ ተደርገው ይታያሉ። ማንኛውም ዓይነት በሥነ ምግባር መጥፎ የሆነ ወይም ተፈጥሯዊ ያልሆነ ድርጊት እንደ ነውር ተደርጎ አይታይም። ንጽሕናና ጥሩ አቋምን መጠበቅ ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ ባላቸው ሰዎች ዘንድ እምብዛም ዋጋ አይሰጣቸውም። ሕዝቡም ይህንን መጥፎ ምሳሌ እያየ አምላክ የሚያወግዘውን ነገር በቸልታ መመልከት ጀምሯል። ሁኔታው ጳውሎስ “ደንዝዘውም በመመኘት [በመስገብገብ አዓት] ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ” በማለት እንደገለጸው ነው። — ኤፌሶን 4:​19፤ ምሳሌ 17:​15፤ ሮሜ 1:​24–28፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11

5. (ሀ) አምላክ ለምንዝር ያለው አቋም ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙት” ብሎ በሚጠቀምበት ቃል የተካተቱት ነገሮች ምንድን ናቸው?

5 የአምላክ የአቋም ደረጃዎች አልተለወጡም። ሳይጋቡ አብሮ መኖርን እንደ ዝሙት አድርጎ ይመለከተዋል። ለትዳር ታማኝ አለመሆንም ምንዝር ነው።a ሐዋርያው ጳውሎስ በግልጽ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።” — 1 ቆሮንቶስ 6:9–11

6. በ1 ቆሮንቶስ 6:​9–11 ላይ ካሉት የጳውሎስ ቃላት ምን ማበረታቻ ልናገኝ እንችላለን?

6 በዚህ ጥቅስ ላይ ያለው አንድ የሚያበረታታ ነጥብ “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል” የሚለው የጳውሎስ አገላለጽ ነው። አዎን፤ በፊት በዓለም ልክስክስነትና “የመዳራት ብዛት” ይሮጡ የነበሩ ብዙዎች ወደ አእምሮአቸው ተመልሰው ክርስቶስንና መሥዋዕቱን በመቀበል ታጥበው ነጽተዋል። ሥነ ምግባራዊ የሆነ ሕይወት በመኖር አምላክን ለማስደሰት መርጠዋል፤ በውጤቱም ደስተኞች ሆነዋል። — 1 ጴጥሮስ 4:​3, 4

7. “የጾታ ብልግናን” ፍቺ በመረዳት በኩል ምን የሐሳብ ግጭት አለ? ስለዚህ ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው?

7 በሌላው በኩል ግን ዘመናዊው ዓለም ለጾታ ብልግና የሚሰጠው ትርጉም በጣም ከመላላቱ የተነሳ ከአምላክ አመለካከት ጋር አይጣጣምም። አንድ መዝገበ ቃላት “የሥነ ምግባር ብልግና” ለሚለው ቃል የሰጠው ፍቺ “በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለውን የሥነ ምግባር አቋም የሚጻረር” የሚል ነው። በዛሬው ጊዜ ያለው “በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሥነ ምግባር አቋም” ከጋብቻ በፊትና ከጋብቻ ውጭ የሚደረግን የጾታ ግንኙነት እንዲሁም ግብረ ሰዶምን በቸልታ የሚያልፍ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የጾታ ብልግና የሚለውና የሚያወግዘው ይህንን ነው። አዎን፤ ነገሩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ስንመለከተው የጾታ ብልግና የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግ በከፍተኛ ሁኔታ መጣስ ማለት ነው። — ዘጸአት 20:​14, 17፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18

የክርስቲያን ጉባኤም ተነክቷል

8. የጾታ ብልግና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉትንም ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?

8 በዛሬው ጊዜ የጾታ ብልግና በጣም ከመብዛቱ የተነሳ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉትም ላይ እንኳን ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በስፋት በተሰራጩት በሥነ ምግባር ዝቅ በሚያደርጉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በቪድዮዎችና የጾታ ስሜትን በሚቀሰቅሱ የሚነበቡ ጽሑፎች አማካኝነት ተፅዕኖ ሊያደርግባቸው ይችላል። በዚህ ነገር የሚነኩት ክርስቲያኖች በቁጥር በጣም አነስተኛ ቢሆኑም ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከይሖዋ ምስክሮች አባልነት ከሚወገዱባቸው ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ድርጊቶች ውስጥ አብዛኞቹ ከጾታ ብልግና ጋር የተያያዙ እንደሆኑ መታወቅ አለበት። ጥሩ የሆነው ጎኑ ግን ከተወገዱት መካከል አብዛኞቹ ከጊዜ በኋላ ስህተቶቻቸውን ይገነዘባሉ፤ እንደገና ንጹሑን የሕይወት ጎዳና በመጀመር ውሎ አድሮ ከውገዳ ተመልሰው ወደ ጉባኤ ይመጣሉ። — ከሉቃስ 15:​11–32 ጋር አወዳድር።

9. ሰይጣን የተዘናጉትን እጁ ውስጥ ሊያስገባ የሚችለው እንዴት ነው?

9 ሰይጣን እንደሚያገሳ አንበሳ ሆኖ እንደሚዞርና የተዘናጋውን ለመዋጥ እንደተዘጋጀ ምንም አያጠያይቅም። ሽንገላዎቹ ወይም ‘የተንኰል ሥራዎቹ’ የተዘናጉ ክርስቲያኖችን በየዓመቱ እያጠመዱ ናቸው። የሰይጣን ዓለም መንፈስ ምንጊዜም ራስ ወዳድነት፣ በሕይወት ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ደስታን ማግኘት ነው የሚል እምነትና ልክስክስነት ነው። የሥጋ ፍላጎትን ወደ ማርካት ያዘነብላል። ራስን መግዛትን አይቀበልም። — ኤፌሶን 2:​1, 2፤ 6:​11, 12 አዓት የግርጌ ማስታወሻ፤ 1 ጴጥሮስ 5:8

10. በፈተና ሊጠቁ የሚችሉት እነማን ናቸው? ለምንስ?

10 በጉባኤ ካሉት ውስጥ ለጾታ ብልግና ፈተና ሊጋለጡ የሚችሉት እነማን ናቸው? አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ማለትም የጉባኤ ሽማግሌዎችም ሆኑ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ቤቴላውያን፣ በየወሩ ብዙ ሰዓት በመስበክ የሚያሳልፉ አቅኚዎች፣ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ በሥራ የተወጠሩ ወላጆች ወይም ከዕድሜ እኩዮች ግፊት የሚመጣባቸው ወጣቶች የጾታ ብልግና ፈተና ያጋጥማቸዋል። የሥጋ ፈተናዎች ሁሉንም ሰው የሚያጋጥሙ ናቸው። የጾታ መሳሳብ ባልተጠበቀበት ወቅት ሊቀሰቀስ ይችላል። ስለዚህ ጳውሎስ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም” ብሏል። ነገሩ የሚያሳዝን ቢሆንም በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም በዚህ የጾታ ብልግና በመሳብ ተሸንፈዋል። — 1 ቆሮንቶስ 10:​12, 13

በምኞት መሳብና መታለል

11-13. ወደ ጾታ ብልግና የመሩ አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

11 አንዳንዶችን ምንዝርና ዝሙት ወደመፈጸም የሞኝነት መንገድ የመሯቸው ፈተናዎችና ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ፈተናዎቹና ሁኔታዎቹ ብዙና የተወሳሰቡ ናቸው፤ ከአገር ወደ አገር ወይም ከባሕል ወደ ባሕል ይለያያሉ። ይሁን እንጂ በብዙ አገሮች የሚያጋጥሙ አንዳንድ መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች የአልኮል መጠጦች ያለ ገደብ የሚጠጣባቸው ግብዣዎች እንዳዘጋጁ ሪፖርት ተደርጓል። ሌሎቹም ለጾታ ብልግና የሚጋብዙ ዓለማዊ ሙዚቃዎችንና መጥፎ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ውዝዋዜዎችን ወደዋል። በአንዳንድ የአፍሪካ አካባቢዎች ቁባቶች ያሏቸው አማኝ ያልሆኑ ሀብታም ወንዶች አሉ። አንዳንድ ሴቶች የጾታ ብልግናን የሚጨምር ቢሆንም እንኳን ቁባቶች በመሆን የኢኮኖሚ ዋስትና በመፈለግ ተፈትነዋል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ክርስቲያን ባሎች ማዕድን በማውጣት ሥራ ወይም በሌላ ቦታ መተዳደሪያ ለማግኘት ሲሉ ቤተሰቦቻቸውን ትተው ይሄዳሉ። ከዚያም የንጽሕና አቋማቸውና ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸው ታማኝነት እቤት ቢሆኑ ኖሮ ከሚደርስባቸው በተለየ መጠን ወይም መንገድ ይፈተናሉ።

12 በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ሦስተኛ ሰው ሳይኖር ከተቃራኒ ጾታ ጋር አብረው በመቆየታቸው ለምሳሌ መኪና መንዳትን ለማስተማር ሲባል አዘውትረው በመቀራረብ በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል።b የእረኝነት ጉብኝት የሚያደርጉ ሽማግሌዎችም አንዲትን እህት በሚመክሩበት ጊዜ ብቻቸውን እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። እርስ በእርስ የሚደረጉ ውይይቶች ስሜታዊ በመሆን ለሁለቱም ወገኖች አሳፋሪ የሆነ ውጤት ሊያስከትሉባቸው ይችላሉ። — ከማርቆስ 6:​7ና ከሥራ 15:​40 ጋር አወዳድር።

13 ከላይ የተጠቀሱት አጋጣሚዎች አንዳንድ ክርስቲያኖችን ጥበቃቸውን ወደ ማላላትና የብልግና ድርጊቶችን ወደ መፈጸም አድርሰዋቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደተፈጸመው ሁሉ አሁንም ‘በራሳቸው ምኞት እንዲሳቡና እንዲታለሉ’ መፍቀዳቸው ወደ ኃጢአት መርቷቸዋል። — ያዕቆብ 1:​14, 15፤ 1 ቆሮንቶስ 5:​1፤ ገላትያ 5:​19–21

14. የምንዝር አንዱ መሠረታዊው ምክንያት ራስ ወዳድነት የሆነው ለምንድን ነው?

14 ውገዳዎችን በጥንቃቄ ስንመረምር የተፈጸሙት የብልግና ድርጊቶች ሁሉ የጋራ የሆነ አንድ መሠረታዊ ምክንያት አላቸው፤ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ውስጥ አንድ ዓይነት ራስ ወዳድነት አለ። ለምን እንዲህ እንላለን? ምክንያቱም ምንዝር በሚፈጸምበት ጊዜ አንድ ንጹሕ የሆነ ሰው ወይም ሰዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል። ምናልባት ጉዳት የሚደርስበት ሰው ሕጋዊ የትዳር ጓደኛ ይሆናል። ልጆች ካሉ ደግሞ እነርሱም እንደሚጎዱ የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም ምንዝር ፍቺን ያስከተለ እንደሆነ አንድነት ባለው ቤተሰብ ውስጥ ተረጋግተው ለመኖር የሚፈልጉት ልጆች ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ምንዝር የፈጸመው ሰው በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስበው ስለራሱ ወይም ስለ ራስዋ ደስታና ጥቅም ነው። ይህም ራስ ወዳድነት ነው። — ፊልጵስዩስ 2:​1–4

15. ወደ ምንዝር የመሩ አንዳንድ ምክንያቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

15 ምንዝር አብዛኛውን ጊዜ በድካም ምክንያት በድንገት የሚፈጸም ድርጊት አይደለም። ቀስ እያለ ምናልባትም በማይታወቅ ሁኔታ ትዳሩን የሚቦረቡር ነገር መኖር አለበት። ምናልባት የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ መሰለቻቸት ይኖር ይሆናል፤ አለዚያም የሐሳብ ግንኙነታቸው ጭራሽ ተቋርጦ ይሆናል። እርስ በርስ መበረታታትን ትተው ሊሆን ይችላል። አንዳቸው ሌላውን በአድናቆት አይመለከት ይሆናል። የትዳር ጓደኛሞቹ ለተወሰነ ጊዜ የጾታ ግንኙነት ሳይፈጽሙ ቆይተው ሊሆን ይችላል። ምንዝር በሚፈጸምበት ጊዜ ሁሉ ከአምላክ ጋር የነበረው ዝምድናም እየቀነሰ ሄዶ እንደነበር የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ ሕልውና ያለውና ሃሳባችንን ወይም ድርጊታቸውን ሁሉ የሚቆጣጠር አምላክ ተደርጎ መታየቱ ሊያቆም ይችላል። ምንዝር በፈጸመው ሰው አእምሮ ውስጥ “አምላክ” ሲባል እንዲሁ ቃል ብቻ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ምንም ቦታ የሌለው ረቂቅ አካል ሊሆን ይችላል። ከዚያም በአምላክ ላይ ኃጢአት መሥራት ቀላል ይሆናል። — መዝሙር 51:​3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​3–5፤ ዕብራውያን 4:​13፤ 11:27

ለመቋቋም የሚረዳ ቁልፍ ነገር

16. አንድ ክርስቲያን የትዳር ከዳተኝነትን ፈተና ሊቋቋም የሚችለው እንዴት ነው?

16 ማንኛውም ክርስቲያን ታማኝነትን በማጉደል እየተፈተነ ወይም እየተፈተነች እንዳሉ ካወቁ ምን ነገሮችን እንዲያስቡባቸው ያስፈልጋል? በመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተው የክርስቲያናዊ ፍቅር ትርጉም ምን እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። የአንድ ሰው ስሜት በአካላዊም ሆነ በጾታዊ ፍቅር ተሸንፎ በሌሎች ላይ መከራን ወደሚያመጣው ራስ ወዳድነት ፈጥኖ እንዲወድቅ በጭራሽ መፍቀድ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታው ከይሖዋ አመለካከት አንፃር ሊታይ ይገባል። ጉባኤውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ ዓይነቱ መጥፎ ተግባር በጉባኤውና በይሖዋ ስም ላይ ከሚያመጣው ውርደት አንፃር መታየት ይኖርበታል። (መዝሙር 101:​3) ስለ ጉዳዩ የክርስቶስን አስተሳሰብ በመያዝና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ከታላቅ ውድቀት ለመዳን ይቻላል። ራስ ወዳድነት የሌለበት የክርስቶስን የሚመስል ፍቅር ፈጽሞ እንደማይወድቅ አስታውስ። — ምሳሌ 6:​32, 33፤ ማቴዎስ 22:​37–40፤ 1 ቆሮንቶስ 13:5, 8

17. ታማኝነትን በተመለከተ ምን ገንቢ ምሳሌዎች አሉልን?

17 አንድ ሰው ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችለው ቁልፍ ነገር እምነቱንና ስለወደፊቱ ተስፋ ያለውን እይታ ማጠናከሩ ነው። ይህም ማለት የጥንቶቹ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የተዉልንን እንዲሁም ኢየሱስ ራሱ የተወልንን የፍጹም አቋም ጠባቂነት ከፍተኛ ምሳሌ በልባችን ውስጥ ከፍ አድርገን ማስቀመጥ ማለት ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል [በመከራ እንጨት አዓት] ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።” (ዕብራውያን 12:​1–3) ጥበበኛ የሆነ ሰው የጋብቻውን መርከብ ሆን ብሎ በመበሳሳት ለማስጠም ከመሞከር ይልቅ ጋብቻውን ለማደስ እንዲችል የደረሱትን ጉዳቶች የሚጠግንበትን መንገድ ያስባል። በዚህም መንገድ በከዳተኝነትና በአታላይነት ከሚመጣው ሐዘን ይድናል። — ኢዮብ 24:​15

18. (ሀ) ምንዝርን ለመግለጽ ክህደት የሚለው ቃል ከልክ ያለፈ ጠንካራ ቃል ነው ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ቃለ መሐላን ስለ መፈጸም ምን አመለካከት አለው?

18 የጾታ ብልግናን በተመለከተ ክህደት የሚለውን ቃል መጠቀም ኃይለ ቃል መናገር ይሆናልን? አንድ ሰው የተጣለበት አደራ ወይም እምነት ካልቆመ ከዳተኛ ይሆናል። የጋብቻ መሐላ ምንም ዓይነት መከራ ቢመጣ፣ በመልካምም ሆነ በክፉ ቀን ለማፍቀርና ለመንከባከብ ቃል መግባትንና አደራ መቀበልን ይጨምራል። ብዙዎች እኛ በምንኖርበት በአሁኑ ጊዜ ዘመኑ እንዳለፈበት አድርገው የሚመለከቱትን ነገር ይኸውም አንድ ሰው በጋብቻ መሐላው ለገለጸው ቃል አክብሮት ማሳየትንም ይጨምራል። ይህንን የተጣለበትን እምነት መተው ማለት በትዳር ጓደኛ ላይ ክህደት መፈጸም ማለት ነው። ስዕለትን ወይም ቃለ መሐላን በሚመለከት አምላክ ያለው አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል:- “ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፤ የተሳልኸውን ፈጽመው።” — መክብብ 5:​4

19. አንድ ምስክር ሲወድቅ ሰይጣን የሚሰማው ደስታ ከምን ሁኔታ ጋር ይነፃጸራል?

19 በዚህ በኩል ምንም ጥርጣሬ አይኑርህ። ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ እንደሚኖር ሁሉ ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ንጹሕ አቋሙን ቢያጎድፍ በሚታዩትም ሆነ በማይታዩት የሰይጣን ጭፍሮች ዘንድ በምድር ላይ ታላቅ ደስታ ይኖራል። — ሉቃስ 15:​7፤ ራእይ 12:​12

ሁሉንም የሚያጋጥም ወደ ስህተት የሚገፋፋ ፈተና

20. ወደ ስህተት የሚገፋፋ ፈተናን ልንቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? (2 ጴጥሮስ 2:​9, 10)

20 የጾታ ብልግና በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር የማይቀር ነገር ነውን? ሥጋችንና ሰይጣን ክርስቲያኖች ሊቋቋሟቸው የማይችሉና ንጹሕ አቋማቸውን ሊጠብቁ እስከሚሳናቸው ድረስ በጣም ኃይለኞች ናቸውን? ጳውሎስ “ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” ሲል በተናገራቸው ቃላት ማበረታቻ ሰጥቶናል። አሁን ባለው ዓለም ወደ ስህተት ከሚገፋፋ ፈተና ሙሉ በሙሉ ለመላቀቅ አንችልም፤ ነገር ግን በጸሎት ወደ አምላክ ዘወር በማለት ልንጸና እንደምንችልና ማንኛውንም ፈተና እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። — 1 ቆሮንቶስ 10:​13

21. በሚቀጥለው ጥናታችን ምን ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ?

21 ወደ ስህተት በሚገፋፉ ፈተናዎች ጸንተን እንድንቋቋምና በድል ለመወጣት እንድንችል አምላክ ምን እርዳታ አቅርቦልናል? ትዳራችንን፣ ቤተሰቦቻችንን እንዲሁም የይሖዋንና የጉባኤውን ጥሩ ስም ለመጠበቅ በግለሰብ ደረጃ ምን ያስፈልገናል? በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “‘ዝሙትን’ ሰፋ ባለ መልኩ እንዲሁም በማቴዎስ 5:​32 እና 19:​9 ላይ ካለው አገባቡ አንፃር ስንመለከተው ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ሕጋዊ ያልሆነና የተከለከለ የጾታ ግንኙነት እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ፖርኒያ [በነዚህ ጥቅሶች ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል] ከሁለቱ ጾታዎች ከአንዱ ጋር ወይም ከእንስሳ ጋር ከፍተኛ የሆነ የጾታ ብልግና (በተፈጥሮአዊም ሆነ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ) ለመፈጸም ሲባል ቢያንስ በአንድ ሰው ብልት መጠቀምን ይጨምራል።” (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መጋቢት 15, 1983 ገጽ 30) ምንዝር:- “በአንድ ባለትዳርና ሕጋዊ ባል ወይም ሚስት ካልሆነ (ካልሆነች) ከሌላ ሰው ጋር በፈቃደኝነት የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ማለት ነው።” — ዘ አሜሪካን ሄሪቴጅ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኢንግሊሽ ላንጉዌጅ።

b አንድ ወንድም አንዲትን እህት በመኪና ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊወስዳት የሚችልባቸው ተገቢ አጋጣሚዎች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች በመጥፎ መንገድ መተርጎም አይኖርባቸውም።

ታስታውሳለህን?

◻ ጋብቻን ለማጠንከር የሚረዱ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ ዓለም ስለ ሥነ ምግባር ያለውን አመለካከት መሸሽ ያለብን ለምንድን ነው?

◻ ወደ ጾታ ብልግና ሊመሩ የሚችሉ አንዳንድ ፈተናዎችና ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

◻ ኃጢአትን ለመቋቋም የሚያስችለው ዋነኛ ቁልፍ ነገር ምንድን ነው?

◻ ወደ ስህተት የሚገፋፋ ፈተና ሲመጣብን አምላክ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለረጅም ጊዜ የዘለቁ ትዳሮች ያሏቸው የጋራ ሁኔታዎች

◻ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አጥብቀው ይከተላሉ

◻ ሁለቱም የትዳር ጓደኞች ከይሖዋ ጋር ጥብቅ ዝምድና አላቸው

◻ ባል ሚስቱን፣ ስሜቶቿንና ሐሳቧን ያከብራል

◻ ዕለት ተዕለት ጥሩ የሀሳብ ግንኙነት ያደርጋሉ

◻ አንዱ ሌላውን ለማስደሰት ይጥራል

◻ ተጫዋችነት፤ በራስ ላይ ለመሳቅ መቻል

◻ ጥፋቶችን ለማመን አይቸገሩም፤ በቀላሉ ይቅር ይላሉ

◻ ፍቅርን ሕያው አድርጎ መጠበቅ

◻ ልጆችን በማሳደግና በማሰልጠን በኩል የተባበሩ መሆን

◻ ዘወትር ወደ ይሖዋ አብሮ መጸለይ

ትዳርን የሚያቆረቁዙ አፍራሽ ሁኔታዎች

◻ ራስ ወዳድነትና እልህ

◻ ነገሮችን አብሮ አለመሥራት

◻ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አለማድረግ

◻ በትዳር ጓደኛሞች መካከል በቂ የሆነ ምክክር አለመኖሩ

◻ የገንዘብ አያያዝ አለማወቅ

◻ ከልጆች እና/ወይም ከእንጀራ ልጆች ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚኖሯቸው የመመዘኛ ነጥቦች ልዩነት

◻ እያመሸ የሚሠራ ወይም ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ብሎ ቤተሰቡን ችላ የሚል ባል

◻ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎቶች አለማሟላት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋብቻን ክቡር አድርጎ መያዝ ዘላቂ ደስታ ያመጣል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ