የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
ደስ ይበላችሁ! መጥመቂያዎቹ ዘይት አትረፍርፈው አፍሰዋል
ነቢዩ ኢዩኤል ‘የጽዮን ልጆች ደስ እንዲላቸውና በይሖዋ ሐሴት እንዲያደርጉ’ አሳስቧቸዋል። ደስታቸውንና ብልጽግናቸውን ለመግለጽ በወይራ ዘይት ተጠቅሞአል። “አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፣ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ።” — ኢዩኤል 2:23, 24
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በእስራኤል ምድር የምትኖር ቢሆን ኖሮ በቤትህ አጠገብ ወይም በእርሻ ቦታህ ከላይa እንደሚታየው የመሰለ የወይራ ዛፍ ቢኖርህ በጣም ደስ ይልህ ነበር። አኗኗርህን ቀላልና አስደሳች ያደርግልህ ነበር። የወይራ ዛፍ ይህን ያህል ተፈላጊነት የነበረው ለምንድን ነው? — ከመሳፍንት 9:8, 9 ጋር አወዳድር።
በመጀመሪያ ዛፉን በደንብ አድርገህ ተመልከት። የወይራ ዛፍ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሊኖር ይችላል። አንዳንዶቹ የወይራ ዛፎች ከአንድ ሺህ ለሚበልጥ ዘመን ሊኖሩ ስለሚችሉ ግንዳቸው የተጨረማመተና አመድማ መልክ ያለው ነው። ዛፉ ስድስት ሜትር የሚያክል ቁመት ሊኖረው ይችላል። ከዝግባ ጋር የሚተካከል ቁመት ወይም ከተምር ዛፍ ጋር የሚወዳደር ግርማ የለውም። በጋ ከክረምት የማይረግፈውና እንደ ብር የሚያብረቀርቀው ቅጠሉ ዓመቱን በሙሉ ከፀሐይ ያስጠልላል። ቢሆንም ለዚህ ዛፍ ከፍተኛ ዋጋ የምትሰጠው ቁመናው ስለሚያምር ወይም ከፀሐይ ስለሚያስጠልል አይደለም። ነገሩ ሌላ ነው።
ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው አረንጓዴ ወይም ጥቁር ቀለም ላላቸው በሺህ ለሚቆጠሩ የወይራ ፍሬዎች ነው! የወይራ ዛፍ በእሥራኤላውያን ሕይወትና ዕለታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ሊይዝ የቻለው በእነዚህ ፍሬዎች ምክንያት ነበር። ዛፉ የወይራ ፍሬ ለማፍራት ሲዘጋጅ በግንቦት ወር ደብዘዝ ያለ ቀለም ባለው አበባ ይሞላል። (ኢዮብ 15:33) ፍሬዎቹ ሲበስሉ ከቢጫማ አረንጓዴ ወደ ጥቁር ቡና ወይም ወደ ጥቁርነት ይለወጣሉ።
በጥቅምትና በህዳር ወራት የሚከናወነው ፍሬዎቹን የመሰብሰብ ሥራ በጣም ከባድ ነበር። የበሰሉት ፍሬዎች መሬት ላይ በተዘረጋው ጨርቅ ላይ እንዲረግፉ ዛፉን በበትር ትመታለህ። (ዘዳግም 24:20) የወይራው ፍሬ ከመጨመቁ በፊት መራራውን ጣዕም ለማጥፋት ጨው ባለበት ውኃ ውስጥ ተዘፍዝፎ ይታጠባል። ከዚያስ ቀጥሎ?
ከዚያ በኋላ የሚደረገው ነገር የወይራውን ምርት በምን መንገድ ልትጠቀምበት እንደምትፈልግ አይተህ የምትወስነው ነው። የወይራውን ፍሬ እንዲሁ እንዳለ ልትበላ ትችላለህ ወይም ቤተሰብህ ለብዙ ወራት ወይራ እንዲበላ ከፈለግህ በኮምጣጤ ውስጥ ዘፍዝፈህ ለማቆየት ትችላለህ። የወይራ ፍሬ ዋነኛ የምግብ ክፍል ሊሆን ይችላል። ከገብስ እንጎቻ ጋር ጣፍጦ የተዘጋጀ የወይራ ፍሬ ሊቀርብ ይችላል።
ይሁን እንጂ አብዛኛውን የወይራ ፍሬ በጣም ጠቃሚና ውድ የሆነውን የወይራ ዘይት ለማውጣት ትጠቀምበታለህ። ብዙ ዓይነት አገልግሎትና የተለያየ ደረጃ ያለው ዘይት ታገኛለህ። መጀመሪያ የበሰለውን ወይራ በሙቀጫ ልትወቅጥ ወይም በእግርህ ልትረግጥ ትችላለህ። (ሚክያስ 6:15) በዚህ ዘዴ የሚገኘው ዘይት ከፍተኛ ጥራት ያለው ሲሆን ኤክስትራ ቨርጅን ይባላል። ለማደሪያው ድንኳን መብራት የሚያገለግለው ይህ ዓይነቱ ዘይት ነበር። (ዘጸአት 25:37፤ 27:20, 21) ይህን ምርጥ ዘይት ልዩ ለሆነ አጋጣሚ ምግብ ለማብሰል መጠቀም ምን ያህል እንደሚያስደስት ልትገምት ትችላለህ።
ጥሩ ጥራት የሌለው የወይራ ፍሬ እንኳን መጭመቂያ ውስጥ አስገብቶ አነስተኛ ጥራት ያለው ዘይት ማውጣት ይቻላል። ከተወቀጠው ወይራ 50 በመቶ የሚሆነው ዘይት ነው። በተለያዩ ዓይነት መጭመቂያዎች መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም አንደኛው ዓይነት መጭመቂያ ሥዕሉ ላይ ያለው ነው። ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የደቀቀ ወይራ ክብ ቅርጽ ባለው ዕቃ ላይ ይደረጋል። በላዩም ላይ በአህያ ወይም በሰው የሚሽከረከር የወፍጮ ድንጋይ እንዲሄድ ይደረግና ከወይራው የሚወጣው ዘይት በማሰሮ ይጠራቀማል። — ማቴዎስ 18:6
የወይራ ዘይት ከፈሳሽ ወርቅ ጋር ሊወዳደር ይችላል። ከፍተኛ ዋጋ ያለው ከመሆኑም በላይ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል። አንድ ዛፍ አምስት ወይም ስድስት አባሎች ላሉት አንድ ቤተሰብ ለአንድ ዓመት የሚበቃ ዘይት ሊሰጥ ይችላል። በቀላሉ የሚፈጭና ከፍተኛ ኃይል የሚሰጥ ምግብ በመሆኑ ዋነኛ የምግብ ክፍል ሊሆን ይችላል። (ከኤርምያስ 41:8፤ ሕዝቅኤል 16:13 ጋር አወዳድር።) በዘይቱ ላይ ሽቶ ጨምረው በቅባትነት ወይም እንግዳ ተቀባይ መሆናቸውን ለማሳየት የእንግዳውን ራስ ለመቀባት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። (2 ሳሙኤል 12:20፤ መዝሙር 45:7፤ ሉቃስ 7:46) ለቁስልም መድኃኒት እንዲሆን ሊጨመር ይችላል። — ኢሳይያስ 1:6፤ ማርቆስ 6:13፤ ሉቃስ 10:34
የወይራ ዘይት አገልግሎት በዚህ ብቻ አያበቃም። ለቤት መብራት፣ ለአምላክ የሚቀርብ ቁርባን ወይም ተሸጦ ገንዘብ ለማስገኘት ሊያገለግል ይችላል። አዎ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የወይራ ዛፍ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ዛፍ ስለነበረ ኢዩኤል ይህን ዛፍ የብልጽግናና የደስታ ምሳሌ አድርጎ መጠቀሙ ተገቢ ነው። — ዘዳግም 6:11፤ መዝሙር 52:8፤ ኤርምያስ 11:16፤ ማቴዎስ 25:3–8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን ሥዕል በትልቁ ለመመልከት ከፈለግህ የ1993ን የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ተመልከት።
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.