የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 3/15 ገጽ 27-30
  • የሽበት ግርማ ሞገስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሽበት ግርማ ሞገስ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጎልማሳነት ጉልበት
  • ግርማ ሞገስ ማግኘት
  • ለሽበት አክብሮት ማሳየት
  • ወደፊት እንጂ ወደኋላ አትመልከቱ
  • ይሖዋ አረጋዊ ለሆኑ አገልጋዮቹ በጥልቅ ያስባል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ታማኝ አረጋውያንን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • የክርስቲያን ቤተሰብ አረጋውያንን ይረዳል
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • እርጅና “የክብር ዘውድ” ሲሆን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 3/15 ገጽ 27-30

የሽበት ግርማ ሞገስ

ከጥንቶቹ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ጋር መነጋገር ቢቻል እንዴት ግሩም ነበር! እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ የመሰሉትን ወንዶችና እንደ ሣራ፣ ረዓብ፣ ሩትና ዲቦራ የመሰሉትን ሴቶች ለማነጋገር መቻል ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስቡ! በጥንቶቹ ዘመናት የተፈጸሙት ታላላቅ ነገሮች ሲፈጸሙ የተመለከቱትን ሲተርኩላችሁ መስማት በጣም አያስደስታችሁምን?

ዛሬም እንኳ ቢሆን ታማኝ የሆኑ አረጋውያን እነርሱና ሌሎች ታማኝ ሰዎች ለጽድቅ ሲሉ ፈተና፣ እገዳ፣ ድብደባ፣ እሥራት ሲደርስባቸው ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት እንዴት ሊጠብቁ እንደቻሉ ተሞክሮአቸውን ሲነግሩአችሁ መስማት አያስደስታችሁምን? ስለሚሰማቸው ስሜትና በተለይ ደግሞ ይሖዋ ላደረገላቸው ፍቅራዊ ጥበቃ የሚሰማቸውን ልባዊ አድናቆት ሲነግሩን ለአምላክ ያለን ፍቅርና ለእነርሱም ያለን አክብሮት ከፍ አይል⁠ምን?

ታማኝ የሆኑ አረጋውያንና አረጋውያት ምን ጊዜም ቢሆን ስለ ተሞክሮአቸው፣ ስለ ዕውቀታቸውና ስለ ጥበባቸው በአምላክ ሕዝቦች ይከበሩ ነበር። እንዲያውም አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥ የሚከተለው ትዕዛዝ ተጨምሮ ነበር:- “በሽበታሙ ፊት ተነሳ፣ ሽማግሌውንም አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ።” (ዘሌዋውያን 19:​32) ዕድሜን ወይም እርጅናን የሚያመለክተው የዕብራይስጥ ቃል “መሸበት” የሚል ትርጉም ካለው ቃል በእርባታ የተገኘ ነው። በተጨማሪም “ሽበት” ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለዚህ እስራኤላውያን ለይሖዋ ቅዱስ ፍርሐት በማሳየት በሸመገለ ሰው ፊት በአክብሮት ብድግ እንዲሉ ይጠበቅባቸው ነበር።

ዛሬስ ይህን የመሰለ አክብሮት ይታያልን? ለምሳሌ ያህል ወጣቶች በአክብሮት ለአረጋውያን በር ይከፍቱላቸዋልን? ወጣቶች ሰው በሞላበት አሳንሰር ወይም ሊፍት ለአረጋውያን ቅድሚያ ይሰጣሉን? ሰው በሞላበት ባቡር ወይም አውቶቡስ ውስጥ መቀመጫቸውን ለአረጋውያን ይለቃሉን? ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ እንዲህ ሳያደርጉ እንደሚቀሩ ተስተውለዋል።

ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ከፈለጉ ‘ራሳቸውን የሚወዱትን፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙትን፣ የማያመሰግኑትንና ጥሩ የሆነውን የማይወዱትን’ ሰዎች አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አካሄድ ርቀው ከአምላክ አመለካከት ጋር የሚስማማ አካሄድ መከተል ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1–5) ታዲያ የአምላክ ቃል ወጣትነትና ሽበት ስላላቸው ዝምድና ምን ይናገራል?

የጎልማሳነት ጉልበት

መጽሐፍ ቅዱስ የጎልማሳነትን ጉልበትና ጥቅሙን ስለሚገነዘብ “የጎበዛዝት ክብር ጉልበታቸው ናት” ይላል። (ምሳሌ 20:​29) በጥንትዋ እስራኤል ከበድ ላሉት የቤተ መቅደስ ሥራዎች አገልግሎት ላይ ይውል የነበረው የወጣት ሌዋውያን ጉልበት ነበር። ዛሬም በፋብሪካዎች፣ በቤቴል ቤቶችና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በሚያከናውናቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች አብዛኛው ሥራ የሚከናወነው የመንግሥቱን ፍላጎት ለማስፋፋቱ ሥራ ጉልበታቸውንና ችሎታቸውን በሰጡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ነው። (ማቴዎስ 6:​33) በዚህ መንገድ በአምላክ አገልግሎት ውስጥ ባገኙት ግሩም መብት ይደሰታሉ።

ከላይ የተጠቀሰው ምሳሌ “የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው” በማለት ይደመድማል። የጎልማሳነት ጉልበት በበርካታ ዓመታት ከተገኘ ተሞክሮና ጥበብ ጋር ሲቀናጅ በጣም ጠንካራ ውኅደት ይፈጠራል።

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ የመስኮት እንጨት እንዲያስገባ የተጠየቀ ወጣት ተለማማጅ አናጢ ሥራውን በወጣትነት ጉልበቱ ተጠቅሞ ለማከናወን ይፈልጋል። አንድ ሸምገል ያለ ተሞክሮ ያለው አናጢ ወጣቱ ጉልበት ቢኖረውም ምስማሩን ብዙ ጊዜ ካልደበደበ እንደማይገባለት ያስተውላል። ሸምገል ያለው ሠራተኛ ይህን ተመልክቶ ወጣቱ መዶሻውን ከብረቱ አጠገብ ሳይሆን ራቅ አድርጎ ከእጀታው ጫፍ እንዲይዝ ይነግረዋል። ይህም ወጣቱ ሰው በበለጠ ኃይል ምስማሩን እንዲመታ ያስችለዋል። ጊዜና ጉልበትም ይቆጥባል።

በተመሳሳይም አንዲት ጥሩ ጉልበት ያላት ወጣት ሴት አንዳንድ ጨርቆች ከመመሪያ ውጭ ሲታጠቡ እንደሚበላሹ ከብዙ ሙከራ መገንዘብ ትችላለች። ተሞክሮ ያላት ሴት ግን ጊዜ ወስዳ ልብሶቹን ከለያየች በኋላ አንዳንዶቹን ልብሶች ለብቻ ማጠብ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ታውቃለች። በተጨማሪም ልብሶቹን ከመስቀያው በምታወርድበት ወይም ከማድረቂያው መሳሪያ በምታወጣበት ጊዜ ብታጣጥፋቸው በኋላ ከመተኮስ ልትድን እንደምትችል ታውቃለች።

ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች መማር ኑሮን በብዙ መንገድ ቀላል ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙ ተሞክሮ ያለው ሰው እንኳን ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀላሉ ይሠራቸው የነበሩት ሥራዎች መሥራት እንደማይችል የሚገነዘብበት ጊዜ ይመጣል። አንድ ፀሐፊ “ወጣቶች ዕውቀት ቢኖራቸው፣ ሽማግሌዎች አቅም ቢኖራቸው ምንኛ ጥሩ ይሆን ነበር!” በማለት በትክክል ተናግሮአል። ይሁን እንጂ ሸምገል ያሉ ሰዎች የወጣቶችን ጉልበት ተገንዝበው በበርካታ ዓመታት ያካበቱትን ተሞክሮ በትዕግሥት ቢያካፍሉና ወጣቶች ደግሞ በትህትና ምክራቸውን ቢሰሙ ምንኛ ጥሩ ይሆናል! ይህን ቢያደርጉ በሁለቱም የዕድሜ ክልሎች የሚኖሩት ይጠቀማሉ።

ግርማ ሞገስ ማግኘት

ዕድሜ ብቻውን አይበቃም። ወጣቱ ኤሊሁ “በዕድሜ ያረጁ [ሁሉ] ጠቢባን አይደሉም፣ ሽማግሌዎቹም [ሁሉ] ፍርድን አያስተውሉም” ብሎአል። (ኢዮብ 32:​9፤ መክብብ 4:​13) አንድ የሸመገለ ሰው በሽበቱ ምክንያት እንዲከበር ከፈለገ ዕድሜውን ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ስፖርት በማየት ወይም ደስታ በማሳደድ በስንፍና ያሳለፈ ሳይሆን ጠቃሚ ነገር በመሥራት ያሳለፈ መሆን ይኖርበታል። የሸመገሉ ሰዎች ባረጁበትም ጊዜ እንኳን ቢሆን መማራቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል።

አንዳንድ ሰዎች ነገሮችን በሚፈልጉት መንገድ ለመሥራት ስለመቻላቸው በኩራት ይናገራሉ። ወይም “ከሁሉ የሚሻለው አስተማሪ ልምድ ነው” ይላሉ። የአምላክ ቃል ግን “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብ ይጨምራል፣ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል” ይላል። (ምሳሌ 1:​5፤ ከ1 ቆሮንቶስ 10:​11 ጋር አወዳድር።) ተሞክሮ ሁልጊዜ ከሁሉ የተሻለ አስተማሪ አይሆንም። ምክንያቱም እኛ ራሳችን ስህተት መሥራት ሳያስፈልገን ከሌሎች ስህተት ልንማር እንችላለን። በተጨማሪም አንድ ክርስቲያን “የሸበተ ጠጉር በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው” የሚለውን ቃል ማስታወስ ይኖርበታል። (ምሳሌ 16:​31 አዓት) ለይሖዋ የታማኝነት አገልግሎት የሞላበት ሕይወት በአምላክ ዘንድ ውብ ሆኖ ስለሚታይ ሌሎች በጥሩ ምሳሌነቱ ሊያከብሩት ይገባል። እርግጥ፣ ስለ አምላክ መማርና “በጽድቅ መንገድ” ተሞክሮ ማግኘት በልጅነት ዕድሜ ሊጀምር ይችላል። በተጨማሪም መቆሚያ የሌለው ሂደት ነው። — ሮሜ 11:​33, 34

ይህንን ሁኔታ በስዊድን በሚኖር በአንድ የሰባት ዓመት ልጅ ተሞክሮ ለማስረዳት ይቻላል። ይህ ልጅ የጉባኤውን የቲኦክራቲካዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ይችል እንደሆነ ጠየቀው። እርሱም “ለምን ለመካፈል ፈለግህ?” ብሎ ጠየቀው። ልጁም ሲመልስለት “ሕይወትን በስንፍና ማባከን አይቻልም” አለው። (መክብብ 12:​1) ይህ ለወጣቶችም ሆነ ለትላልቆች እንዴት ያለ ምሳሌ ነው!

ለሽበት አክብሮት ማሳየት

በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚታይ መጥፎ ዝንባሌ አለ። እርሱም ለአካላዊ ብቃትና ለስፖርት ችሎታ ከፍተኛ ግመት መስጠትና አረጋውያንን በንቀት መመልከት ነው። አንድ ክርስቲያን በጉባኤ ውስጥ ላሉ የሸበቱ ሰዎች ሊኖረው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?

አረጋውያን ክርስቲያኖችን ችላ ከማለት ይልቅ ስለእነርሱ ማሰብና ከእነርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ሳምንታዊ ስብሰባዎች አስባችሁ አረጋውያንን ሰላም ትላላችሁን? ትንንሽ ልጆችና ሌሎች ክርስቲያኖች መጥተው ሲጨብጡአቸው ከልብ ይደሰታሉ። በተጨማሪም አረጋውያን በዕድሜ ከእነርሱ የሚለዩ ክርስቲያኖች ለመጫወት በርከት ብለው በሚገኙበት ቦታ እነርሱም ቢገኙ ደስ ይላቸዋል። ወጣት ባልና ሚስቶች የዕድሜ እኩዮቻቸው ከሆኑት ያገቡ ሌሎች ሰዎች ጋር የሚጨዋወቱት ብዙ የጋራ ጉዳይ ቢኖራቸውም እንደነዚህ ባሉት አስደሳች ስብሰባዎች ላይ ሸምገል ያሉትን ቢጨምሩ በአጸፋው ግሩም ዋጋ ይከፈላቸዋል። — 1 ተሰሎንቄ 3:​12፤ 5:⁠15

ከአረጋውያን ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ አሳቢነት ማሳየት ምንኛ አስፈላጊ ነው! አንድ ለ40 ዓመት ያህል ይሖዋን ያገለገለ አረጋዊ ወንድም የጉባኤውን ሽማግሌ ጉባኤውን በምን መንገድ ሊያገለግል እንደሚችል በጠየቀው ጊዜ ወጣቱ ሽማግሌ “ምንም ነገር ልታደርግልን አትችልም” ሲል መልሶለታል። እንዴት ያለ ደግነት የጎደለው አነጋገር ነው! አረጋዊው ወንድም ቀድሞ የነበረው ጉልበት አሁን የለውም። በመስክ አገልግሎት የነበረው ተሳትፎም እየቀነሰበት መጥቶአል። ስለዚህ አንዳንድ የበላይ ተመልካችነት መብቶችን ለመቀበል አቅሙ እንደማይፈቅድለት ግልጽ ነው። ቢሆንም ብዙ ሊያበረክት የሚችላቸው ነገሮች ነበሩ። በጽድቅ መንገድ ብዙ ጥበብና ተሞክሮ አካብቶአል። የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንፈስ ድጋፍ ያለው ጠንካራ ድርጅት ሊኖራቸው የቻለው እነዚህ አረጋውያን ጠንክረው መንግሥቱን በመስበካቸው፣ በስደት በመጽናታቸው፣ የክርስቲያናዊ ኃላፊነቶችን ከባድ ቀንበር በመሸከማቸውና ሌሎችን በማሰልጠናቸው ነው። ስለዚህ እነዚህን አረጋውያን እንደ ጥበበኛ መካሪዎች፣ እንደ አፍቃሪ እረኞችና እንደ ውጤታማ አስተማሪዎች አድርገን በመመልከት እናክብራቸው።

በተጨማሪም አረጋውያን ለሚሰጡት ምክርና ሐሳብ ትልቅ ግምት የምንሰጥበት በቂ ምክንያት አለ። ለምሳሌ ያህል ብዙ ልምድ ያለው አንድ ወንድም የመንግሥት አዳራሹ በር በሕንጻው ምዕራባዊ ጎን እንዳይሆን አሳብ አቀረበ። ወጣት ወንድሞች የሕንጻውን ውበት ይቀንሳል በማለት ሐሳቡን ሳይቀበሉት ቀሩ። ይሁን እንጂ ከበስተ ምዕራብ የሚመጣው ነፋስና ዝናብ በሩን አለጊዜው ስላስረጀው ከዓመታት በኋላ በሩን ወደሌላ አቅጣጫ ማዛወር ግድ ሆኖ ተገኘ። በዕድሜ የተገኘው ተግባራዊ ጥበብ ስለውበት በማሰብ ከተወሰደው እርምጃ ተሽሎ ተገኘ። ወጣት ግለሰቦች የአረጋውያንን ሐሳብና ተግባራዊ ጥበብ በመስማት አክብሮት ቢያሳዩአቸው ብዙ ጊዜና ገንዘብ ከመባከን ይድናል። የአረጋዊው ሰው ሐሳብ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳን ሐሳቡ ችላ እንዳልተባለና የተለየ ውሳኔ የተደረገው በሌሎች ምክንያቶች እንደሆነ ለአረጋዊው በማሳወቅ አክብሮት ማሳየት ይቻላል። — ከምሳሌ 1:​8 ጋር አወዳድር።

ወደፊት እንጂ ወደኋላ አትመልከቱ

አንዳንድ አረጋውያን “ወጣት የነበርንበትን ጊዜ የመሰለ ጥሩ ጊዜ ሊኖር አይችልም” የሚል አመለካከት አላቸው። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት አረጋውያን ስላለፈው ጊዜ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ሰማያዊው ሽልማታቸውን ወይም በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ የወጣትነት ጉልበት የሚያገኙበትን ጊዜ በናፍቆት እንዲጠባበቁ ሊበረታቱ ይችላሉ። ይህን ተስፋቸውን በሚጠባበቁበት ጊዜም በዕድሜያቸው ምክንያት ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር በጣም ውስን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። አንድ የሸመገለ ሰው የአገልግሎት መብት ሳይሰጠው በሚታለፍበት ጊዜ ይህን መገንዘቡና ነገሮችን ሳቅ ብሎ ማለፉ በጣም ይጠቅመዋል።

ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም በቀደሙት ዓመታት በወረዳ ስብሰባ ፕሮግራሞች ላይ ክፍል ሲሰጠው ቆይቶ ይሆናል። አሁን ግን ብዙ ብቃት ያላቸውና ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያላቸው ሽማግሌዎች ይኖራሉ። ከእነዚህ በአንጻራዊ ሁኔታ ወጣት ከሆኑት ሽማግሌዎች መካከል አንዳንዶቹ ቅንዓትና ችሎታ ያላቸው፣ በሚገባ ለማስተማርና በደግነት ለመምከር እንዲሁም ሌሎችን ለማበረታታት የሚችሉ መሆናቸውን አስመስክረዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:​12, 13፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​17) በዚህም ምክንያት የስብሰባ ፕሮግራም ያልተሰጠው አረጋዊ ወንድም ችላ እንደተባለ ሊሰማውና ከእርሱ ይልቅ ወጣት ለሆኑት ወንድሞች መብት መሰጠቱ ላያስደስተው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ከሰብዓዊ አለፍጽምና የሚመነጨውን አፍራሽ አስተሳሰብ ማሸነፍ ይቻላል። እንዲያውም በጉባኤው ውስጥ ያሉት አረጋውያን ሁሉ የሚፈለጉና ስለታማኝነታቸው የሚወደዱ መሆናቸውንና እንዲሁም የሚሰጡት ሐሳብ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን እንዲያውቁ በማድረግ ሊረዱአቸው ይችላሉ።

እርግጥ፣ አንድ አረጋዊ ወንድም እርሱ ሊከበር የሚፈልገውን ያህል የእምነት ባልደረቦቹም መከበር እንደሚኖርባቸው ማስታውስ ያስፈልገዋል። (ማቴዎስ 7:​12፤ ሮሜ 12:​10) አረጋውያን በማርጀታቸው ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ ሆነው እንዲቀመጡ እንደተደረጉ ከሚሰማቸው ይልቅ ባለፉት ዓመታት ባበረከቱት የታማኝነት አገልግሎት መደሰት ይኖርባቸዋል። በእርግጥ ሁላችንም የሌሎች በጎች መንጋ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ በጎረፈ መጠን የሥራውን ሸክም የሚካፈሉና የጉባኤ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ ብቃት ያላቸው የበላይ ተመልካቾች በመብዛታቸው ይሖዋን ልናመሰግን ይገባናል። — ዮሐንስ 10:​16፤ ኢሳይያስ 60:​8, 22፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:⁠2

የሸበቱ አረጋውያን ሕመም ስለሚሰማቸው፣ ጤንነታቸው እየቀነሰ ስለሚሄድ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ አንዳንዴ ነጭናጮች ይሆናሉ። በዚህም ምክንያት የቤተሰቦቻቸው ወይም የጉባኤዎቻቸው አባሎች ችግራቸውን የሚረዱና ነገሮችን በእነርሱ ቦታ ሆነው የሚያዩ መሆን ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም የሸመገሉት ግለሰቦች በልባቸውና በአእምሮአቸው ወጣቶች እንደሆኑ ለመቆየት እንዲችሉ ብሩህ አቋም እንዲኖራቸው ጠንካራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ጋር በአንድ ክፍል ይኖር የነበረ ወጣት ወንድም ከጥቂት ዓመታት በፊት ከቤቴል ሊወጣ ሲል በዕድሜ ያረጀው ወንድም በእርሱ ምትክ ማን አብሮት እንዲኖር እንደሚፈልግ ሐሳብ እንዲሰጠው ጠየቀው። ወጣትና ንቁ ሆኖ እንዲኖር የሚረዳው የጎለመሰ ወጣት ወንድም ቢያገኝ እንደሚመርጥ ነገረው። አረጋዊው ቅቡዕ ክርስቲያን ገና የሚሠራ ሥራ ስላለ እጁን አጣጥፎ ለመቀመጥ ወይም ጡረታ ለመውጣት አልተዘጋጀም ነበር። ይህ የወደፊትን ጊዜ ብሩህ አድርጎ በመመልከትና አዎንታዊ አስተሳሰብ በመያዝ ረገድ እንዴት ያለ ምሳሌ ነው!

‘የጎልማሶች ውበት ጉልበታቸው እንደሆነና የሽማግሌዎችም ግርማ ሞገስ ሽበታቸው እንደሆነ’ ምንም አያጠያይቅም። ወጣቶች በጉልበታቸው፣ አረጋውያን በጥበባቸው ተጠቅመው የጽድቅን መንገድ ሲከታተሉ ማየት እንዴት አስደናቂ ነው! ክርስቲያኖች በሙሉ ያረጁም ሆኑ ወጣቶች፣ በአንድነት ‘በዘመናት የሸመገለውን’ የይሖዋን እውነተኛ አምልኮ በአንድነት ተባብረው ሲያስፋፉ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። — ዳንኤል 7:​13

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሸበቱ ክርስቲያኖች ለሌሎች ሊያካፍሉት የሚችሉት ብዙ ጠቃሚ ሐብት አካብተዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ