የሲኦል እሳት እየተንቦገቦገ ነው ወይስ እየጠፋ?
ፕሮቴስታንት ሰባኪ የሆኑት ጆናታን ኢድዋርድስ በ18ኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩትን የአሜሪካ ቅኝ ተገዥዎች የሲኦልን እሳት በሥዕላዊ መንገድ እየገለጹ ያስፈራሩ ነበር። አንድ ጊዜ አምላክ ኃጢአተኞችን እንደ አስቀያሚ ሸረሪቶች በገመድ ጠላልፎ በእሳት ነበልባል ላይ እንደሚሰቅል ገልጸው ነበር። ኢድዋርድስ ጉባኤያቸውን ሲዘልፉ እንዲህ ብለው ነበር:- “አንተ ኃጢአተኛ፣ መለኮታዊው እሳት በሚንቀለቀልበት ነበልባል ላይ በእሳቱ ተቃጥሎ ሊበጠስ በተዘጋጀ ቀጭን ክር ላይ ትንጠለጠላለህ።”
ይሁን እንጂ ኢድዋርድስ ይህን በሰፊው የተወራለትና አስከፊ ስብከት ካሰሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሰዎቸ በሲኦል እሳት ያላቸው እምነት እየተዳከመ በመሄዱ የሲኦል እሳት ብልጭ እልም እያለ መጥፋት ጀመረ።a ዘ ዲክላይን ኦቭ ሄል የተባለው በዲ ፒ ወከር የተደረሰ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በ18ኛው መቶ ዘመን አራተኛ አሥርተ ዓመት ላይ የተኮነኑ ሁሉ ዘላለማዊ ሥቃይ ይቀበላሉ የሚለው መሠረተ ትምህርት ሐሰት ነው ብሎ በአደባባይ መከራከር ተጀመረ።” በ19ኛው መቶ ዘመን የሲኦል ነበልባል እየተዳፈነ መጥቶ በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ‘ሲኦል በዚያ የተጣሉ ሁሉ በአእምሮአቸውና በአካላቸው ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚሠቃዩበት የእቶን እሳት ነው’ የሚለው የኢድዋርድስ እምነት የውይይት ርዕስ መሆኑ ቀረ። ጄፍሪ ሸለር የተባሉት ጋዜጠኛ እንደተናገሩት “በዘመኑ ምሁራዊ አስተሳሰብ በመጠቃቱና ሆሎኮስት ከተባለው የናዚዎችና የሂሮሽማ እልቂት አይብስም ተብሎ ስለታሰበ የሲኦል አስፈሪ ሥዕል አስደንጋጭነቱን ማጣት ጀመረ።”
ብዙ ሰባኪዎች የእሳትና የድኝ ስብከት አልጥማቸው እያለ መጣ። ስለ ሲኦል ሥቃይና መከራ የሚገልጹ ስብከቶች ከዋናዎቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የስብከት መድረክ ጠፉ። ለብዙ የሃይማኖት ሊቃውንት ሲኦል ዘመኑ ያለፈበትና ምሁራዊ ውይይት ሊደረግበት የማይገባ ርዕሰ ጉዳይ ሆነ። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊ ለአንድ ዩኒቨርሲቲ ስለ ሲኦል የሚሰጠውን ንግግር በሚዘጋጅበት ጊዜ ባደረገው ምርምር የብዙ ምሁራዊ መጽሔቶችን ማውጫዎች አመሳክሮ ነበር። አንድም ጊዜ እንኳን ስለ ሲኦል አልተጠቀሰም ነበር። የኒውስ ዊክ መጽሔት እንደጻፈው ታሪክ ፀሐፊው “ሲኦል ማንም ሰው ልብ ሳይለው ጠፍቶአል” ሲሉ ደምድመዋል።
የሲኦል መመለስ
ሲኦል ፈጽሞ ጠፍቶአልን? በእርግጥ አልጠፋም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሲኦል መሠረተ ትምህርት በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጣጠል ጀምሮአል። በአሜሪካ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሲኦል እናምናለን የሚሉ ሰዎች ቁጥር በ1981 ከነበረው 53 በመቶ በ1990 ወደ 60 በመቶ ከፍ ብሎአል። በዚህ ላይ የሲኦል ሰባኪዎች ዓለም አቀፍ ወንጌላዊ እንቅስቃሴ ሲጨመር የሲኦል ትምህርት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመልሶ ማንሰራራቱ ግልጽ ይሆናል።
ይሁን እንጂ በዚህ ትምህርት ማንሰራራት የተነኩት ተራዎቹ ምዕመናን ብቻ ናቸው ወይስ ቀሳውስትም ጭምር? ከ250 ዓመት በፊት በጆናታን ኢድዋርድስ የተሰበከው ዓይነት የሲኦል እሳት ትምህርት ከአንዳንድ ወግ አጥባቂ አብያተ ክርስቲያናት አልጠፋም ነበር። በ1991 ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት እንደሚከተለው ጽፎ ነበር:- “ነፃ አስተሳሰብ ባላቸው ዋነኛ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን የሃይማኖት ሊቃውንት ከቀደሙት አሥርተ ዓመታት በበለጠ ሁኔታ ስለ ሲኦል በጥሞና ማሰብ ጀምረዋል።” የሲኦል እሳት ትምህርት ለበርካታ ዓመታት ተረስቶ ከቆየ በኋላ አሁን እንደገና በዓለም ዙሪያ መስፋፋትና መታወቅ እንደጀመረ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም የእሳትነት ባሕርዩን እንደያዘ ነው?
የሚነሱ ጥያቄዎች
በዚህ ረገድ የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ደብልዩ ኤፍ ዎልብሬኽት ምንም ዓይነት ጥርጣሬ እንደሌላቸው ገልጸዋል። “ሲኦል ሲኦል ነው። የማንም ሰው ምኞት የዘላለም ኩነኔ ቦታ መሆኑን ሊለውጥ አይችልም” ብለዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ይህን ያህል እርግጠኞች አይደሉም። ሲኦል ስለመኖሩ የማይጠራጠሩ ቢሆኑም ስለ ሲኦል ምንነት ግን የሚጠይቁአቸው ጥያቄዎች አሉ። ሌላው የሃይማኖት ሊቅ እንዲህ ብለዋል:- “ለእኔም ቢሆን ሲኦል በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተመሰከረለት የማያጠያይቅ እርግጠኛ ነገር ነው። ምንነቱን በትክክል ለማወቅ ግን አስቸጋሪ ነው።” ዛሬ በርካታ የሃይማኖት ሊቃውንትም ሆኑ ምዕመናን የሚጠይቁት ጥያቄ “ሲኦል አለን?” የሚል ሳይሆን “ሲኦል ምንድን ነው?” የሚል ነው።
አንተስ ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ? ስለ ሲኦል ምንነት ምን ሲነገርህ ቆይቶአል? ቅን የሆኑ ክርስቲያኖች በዚህ መሠረተ ትምህርት የሚረበሹት ለምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢድዋርድስ “ሲነርስ ኢን ዘ ሃንድስ ኦቭ አን አንግሪ ጐድ” የተባለውን ይህን ስብከት ያሰሙት ሐምሌ 8, 1741 ነበር።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Doré’s illustration of Devils and Virgil for Dante’s Divine Comedy