ጤናማ ካልሆነ ሙዚቃ ራሳችሁን ጠብቁ!
“እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” — ኤፌሶን 5:15, 16
1. ሙዚቃ መለኮታዊ ስጦታ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
“ሙዚቃ . . . መለኮታዊ ስጦታ ነው።” ይህን ቃል ዘ ባይብል ሚዩዚክ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የጻፉት ሉሉ ራምሴ ዊሊ ናቸው። ይህን ቁም ነገር ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ከጥንት ዘመን ጀምረው ተገንዝበዋል። የሰው ልጅ ጥልቅ ስሜቱን ይኸውም ደስታውን፣ ሐዘኑን፣ ቁጣውንና ፍቅሩን በሙዚቃ አማካኝነት ሲገልጥ ኖሮአል። በዚህም ምክንያት ሙዚቃ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ከፍተኛ ሚና ነበረው። በቅዱሳን ጽሑፎችም ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። — ዘፍጥረት 4:21፤ ራእይ 18:22
2. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ሙዚቃ ይሖዋን ለማወደስ ያገለግል የነበረው እንዴት ነው?
2 ሙዚቃ በጣም ክብራማ የሆነ መግለጫውን ያገኘው በይሖዋ አምልኮ ነው። በጣም ታላላቅ ከሆኑት የይሖዋ ውዳሴ መግለጫዎች አንዳንዶቹ ጥንት በሙዚቃ የተቀናበሩ ነበሩ። መዝሙራዊው ዳዊት “የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ” ሲል ጽፎአል። (መዝሙር 69:30) ሙዚቃ ለብቻ በሚኮንበት ጊዜ እየጸለዩ ለማሰላሰል አገልግሎአል። አሳፍ “በሌሊት የክር ሙዚቃዬን አስታውሳለሁ፣ በልቤም አስባለሁ። መንፈሴም በጥንቃቄ ይመረምራል” ሲል ጽፎአል። (መዝሙር 77:6 አዓት) በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሙዚቃ በከፍተኛ ደረጃ ተደራጅቶ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 23:1–5፤ 2 ዜና መዋዕል 29:25, 26) በርካታ ሙዚቀኞች አንድ ላይ ሆነው የተደራጁበት ጊዜም ነበር። ቤተ መቅደሱ በተመረቀ ጊዜ 120 መለከት ነፊዎች ተሰልፈው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 5:12, 13) ይህ ከፍተኛ ሙዚቃ ምን ዓይነት ድምፅ እንደነበረው የሚገልጽ መዝገብ አልቆየልንም። ይሁን እንጂ ዘ ሚዩዚክ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሎአል:- “በበዓል ቀናት ይሰማ የነበረው የቤተ መቅደስ ሙዚቃ የሚያሳድረውን ጠቅላላ ስሜት መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። . . . ከመካከላችን አንዳችን እንዲህ ወዳለው ቦታ ብንወሰድ በጣም ኃይለኛ በሆነ የመደነቅና የመመሰጥ ስሜት መዋጣችን አይቀርም።”a
ከአግባብ ውጭ የሆነ የሙዚቃ አጠቃቀም
3, 4. የአምላክ ሕዝቦችና አረማዊ ጎረቤቶቻቸው በሙዚቃ ስጦታ አለአግባብ የተጠቀሙት በምን መንገድ ነው?
3 ይሁን እንጂ ሙዚቃ እንዲህ ላለው ከፍተኛ ዓላማ ብቻ ውሎ አልቀረም። በሲና ተራራ ሙዚቃ ሰዎችን ለጥጃ አምልኮ ለማነሳሳት አገልግሎአል። (ዘጸአት 32:18) ሙዚቃ ከስካርና ከግልሙትና ጋር የተያያዘበት ጊዜም ነበር። (መዝሙር 69:12፤ ኢሳይያስ 23:15) የእስራኤላውያን ጎረቤት የነበሩት አረማውያን ብሔራትም ከዚህ ባላነሰ ሁኔታ ይህን መለኮታዊ ስጦታ ከአግባብ ውጭ በሆነ መንገድ ተገልግለውበታል። ዘ ኢንተርፕሬተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል “በፊንቄና በሦሪያ ይሰማ የነበረው ሙዚቃ በሙሉ የመራባት ሴት አምላክ የሆነችውን የአስታሮትን አምልኮ የሚያንጸባርቅ ነበር ለማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የታወቁ ዘፈኖች ቅጥ ለሌለው ሩካቤ ሥጋ የሚያዘጋጁ ነበሩ” ይላል። የጥንቶቹ ግሪካውያን ሙዚቃን “ለሩካቤ ሥጋ የሚያነሳሱ ጭፈራዎችን ለማጀብ ይጠቀሙበት ነበር።”
4 አዎ፤ ሙዚቃ የመቀስቀስ፣ የማነሳሳትና የመገፋፋት ኃይል አለው። ከአሥርተ ዓመታት በፊት የተጻፈው ዘ ሚዩዚክ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው የጆን ስቴይነር መጽሐፍ “በአሁኑ ጊዜ በሰው ዘር ላይ የሙዚቃን ያህል ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳድር ላይ የሚገኝ የሥነ ጥበብ ዘርፍ የለም” እስከማለት ደርሶአል። ዛሬም ቢሆን ሙዚቃ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛል። ስለዚህ መጥፎ ዓይነት ሙዚቃ ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ወጣቶች ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው
5. (ሀ) በአሥራዎቹ ዓመታት በሚገኙ በብዙ ወጣቶች ሕይወት ውስጥ ሙዚቃ ምን ዓይነት ከፍተኛ ሚና አለው? (ለ) አምላክ ወጣቶች ራሳቸውን ስለማስደሰታቸው ምን አመለካከት አለው?
5 ወጣት ከሆንክ ሙዚቃ በተለይም የተለያየ ዓይነት ያላቸው የፓፕ ወይም የሮክ ሙዚቃዎች በአንተ ዕድሜ በሚገኙ ወጣቶች ዘንድ ምን ያህል ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጣቸው ታውቃለህ። እንዲያውም “ሙዚቃ ከወጣቶች ሰውነት ጋር ተዋህዷል” ተብሎአል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ወጣት በትምህርት ቤት በሚያሳልፋቸው የመጨረሻ ስድስት ዓመታት በአማካይ በየቀኑ አራት ሰዓት የሚያክል ጊዜ የሮክ ሙዚቃ በመስማት እንደሚያሳልፍ ተገምቶአል። ይህም ሚዛናዊነትን አለመጠበቅ እንደሆነ ያመለክታል። ደስ የሚያሰኝህን ወይም ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ የሚያደርግህን ነገር ማዳመጥ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። አስደሳች የሆነውን ሙዚቃ የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ወጣቶች በሐዘንና በትካዜ እንዲዋጡ እንደማይፈልግ የተረጋገጠ ነው። እንዲያውም ሕዝቦቹን “ጻድቃን ሆይ፣ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፣ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ፣ እልል በሉ” ሲል አዝዞአል። (መዝሙር 32:11) ለወጣቶችም ቃሉ “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው” ይላል። — መክብብ 11:9
6. (ሀ) ወጣቶች በሙዚቃ ምርጫቸው ረገድ ጠንቃቆች መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚሰሙ ሙዚቃዎች በቀደሙት ትውልዶች ዘመን ከሚሰሙት ሙዚቃዎች የከፉ የሆኑት ለምንድን ነው?
6 ይሁን እንጂ ለማዳመጥ በምትመርጠው ሙዚቃ ረገድ ጠንቃቃ መሆን የሚያስፈልግበት በቂ ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፣ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” ብሎአል። አንዳንድ ወጣቶች አንዲት ልጃገረድ እንዳለችው “ወላጆቻችን በወጣትነታቸው ዘመን የነበረውን ሙዚቃ ይሰሙ ነበር። እኛስ የጊዜያችንን ሙዚቃ ለምን አንሰማም?” የሚል ተቃውሞ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ወላጆቻችሁ በእናንተ ዕድሜ ላይ በነበሩበት ጊዜ ያዳምጡአቸው ከነበሩት ሙዚቃዎች አንዳንዶቹ መጥፎ የሚሆኑበት ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። ብዙዎቹ በቅርብ ሲመረመሩ የሥነ ምግባር ርኩሰትን በተዘዋዋሪ ሁኔታ የሚያሞግሱና ወደ ብልግና የሚያመሩ ናቸው። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ይገለጹ የነበሩት ድርጊቶች በአሁኑ ጊዜ ግልጽ በሆኑ ቃላት መገለጽ ጀምረዋል። አንድ ጸሐፊ እንደታዘቡት “በአሁኑ ጊዜ በባህላችን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ግልጽ የሆኑ የብልግና መልእክቶች ውርጅብኝ በሕጻናት ላይ እየወረደባቸው ነው።”
ራፕ፣ የዓመፅ ሙዚቃ
7, 8. (ሀ) ራፕ ሙዚቃ ምንድን ነው? ይህን ያህል ተወዳጅነት ሊያገኝ የቻለውስ ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው የራፕ አኗኗር እንደሚከተል የሚያሳውቁ ነገሮች ምንድን ናቸው?
7 ለምሳሌ ያህል በጊዜያችን የተስፋፋውን የራፕ ሙዚቃ እንውሰድ። የታይም መጽሔት እንዳለው ራፕ “የወጣለት ምድር አቀፍ የእምቢተኝነት ምት ሆኖአል። በተጨማሪም በብራዚል፣ በአውሮፓ፣ በጃፓን፣ በሩስያና በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ተወዳጅነት አግኝቶአል።” አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት የዜማ ቅላጼ የሌለው ነው። ስንኞቹም ቢሆኑ የሚዜሙ ሳይሆኑ በቃል የሚነበነቡ ናቸው። ራፕ ከፍተኛ የሆነ ገበያ ያገኘበትም ምሥጢር ይህ ሰዎችን የሚያነሳሳው ኃይለኛ ምት ነው። አንድ ጃፓናዊ ወጣት እንዳለው “የራፕ ሙዚቃ በማዳምጥበት ጊዜ ሰውነቴ ሁሉ ይቀሰቀሳል። በምደንስበት ጊዜም ነፃ እንደሆንኩ ሆኖ ይሰማኛል” ብሎአል።
8 ሌላው ራፕ ተወዳጅነት ያተረፈበት ምክንያት ግጥሞቹ የብልግናና የወሮበሎች ቋንቋ ድብልቅ መሆኑ ነው። የራፕ ስንኞች እንደ ሮክ ሙዚቃ ስንኞች በወጣቶች ፍቅር ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ ከበድ ያሉ መልእክቶችን ያዘሉ ናቸው። ራፕ ስለ ፍትህ መጓደል፣ ስለ ዘር ልዩነት፣ ስለ ፖሊሶች ጭካኔ ይናገራል። ይሁን እንጂ የራፕ ግጥሞች በጣም ጸያፍ በሆኑና ለመስማት በሚቀፉ ቃላት የሚቀርቡበት ጊዜ አለ። በተጨማሪም ራፕ በተለመደው የአለባበስና የአጋጌጥ የአቋም ደረጃ በጾታ ሥነ ምግባር ላይ ዓምፆ የተነሣ ይመስላል። ራፕ ራሱን የቻለ የአኗኗር ዘዴ እየሆነ መምጣቱ አያስደንቅም። የራፕ አቀንቃኞች ቅጥ ባጣ አካላዊ አገላለጽ፣ በወሮበሎች አነጋገርና በልብሳቸው ማለትም በተንዘረፈፉ የባጊ ጂንስ ሱሪዎች፣ ክራቸው ባልታሰሩ የእስኒከር ጫማዎች፣ በወርቅ ሰንሰለቶች፣ የቤዝ ቦል ተጫዋቾች በሚያደርጉት ኮፍያና በጥቁር መነጽሮች ይታወቃሉ።
9, 10. (ሀ) የራፕ ሙዚቃና የራፕ አኗኗር ‘ጌታን ደስ የማያሰኝ’ መሆኑን ለማወቅ ወጣቶች ምን ነገሮችን መመልከት ይገባቸዋል? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ምን ነገርን አቃልለው የሚመለከቱ ይመስላል?
9 ክርስቲያኖች በኤፌሶን 5:10 ላይ “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” ተብለዋል። ራፕ ያገኘውን ስምና ዝና ስንመለከት ከራፕ ሙዚቃ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ብታደርግ “ለጌታ ደስ የሚያሰኘው” ይመስልሃልን? አንድ ክርስቲያን ወጣት ብዙ የዓለም ሰዎች እንኳን የማይወዱትን የአኗኗር ዘይቤ ለመከተል ይፈልጋልን? አንድ የሙዚቃ ተቺ ስለ አንድ የራፕ ሙዚቃ ዝግጅት የሰጠውን መግለጫ ልብ በል:- “የራፕ ዘፋኞች በብልግናቸውና በጸያፍ ንግግራቸው አንዳቸው ከሌላው ለመብለጥ ይፎካከሩ ነበር . . . ወንድና ሴት ዳንኪረኞች በመድረክ ላይ ሆነው የሩካቤ ሥጋ ድርጊትን የሚመስል እንቅስቃሴ ያሳዩ ነበር።” ከሙዚቃው አዘጋጆች አንዱ ስለ አንድ ትርዒት ሲናገር “ከአፋቸው የሚወጣው ቃል ሁሉ ብልግና ነበር” ብሎአል።
10 በዚህ ምሽት የቀረበው ሙዚቃ በሌሎች ጊዜያት ከሚሰማው የራፕ ሙዚቃ የተለየ አልነበረም። የሙዚቃው ዝግጅት የቀረበበት አዳራሽ ዲሬክተር “የምትሰሙት በየሱቁ ከሚሸጠው የራፕ ሙዚቃ ያልተለየ ሙዚቃ ነው” ብለዋል። በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ከተገኙት 4,000 የሚያክሉ ወጣቶች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ነን ባይ ወጣቶች መገኘታቸው ያሳዝናል! አንዳንዶች ሰይጣን የዚህ አየር ባለ ሥልጣን ገዥ መሆኑን ችላ ያሉ ይመስላል። ሰይጣን በአሁኑ ጊዜ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚሠራውን መንፈስ ወይም ዋነኛ ዝንባሌ ይገዛል። (ኤፌሶን 2:2) ከራፕ ሙዚቃ ወይም ከራፕ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ብታደርጉ የማንን ፍላጎት የምትፈጽሙ ይመስላችኋል? እርግጥ አንዳንድ የራፕ ሙዚቃዎች በግጥማቸው ይዘት የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በአብዛኛው ከክርስቲያን የአቋም ደረጃ ጋር የሚጻረር የሙዚቃ ዓይነት መውደድ ተገቢ ይሆናልን?
ሄቪ ሜታል — (ፈጣንና ጮክ ያለ ምት ያለው) የፆታ ብልግናን፣ ዓመፅንና የሰይጣን አምልኮን የሚያበረታታ ሙዚቃ
11, 12. ሄቪ ሜታል ሙዚቃ ምንድን ነው? ይህንን ዓይነቱን ሙዚቃ መጥፎ የሚያደርጉት ባሕርያት ምንድን ናቸው?
11 ሌላው በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋ የሙዚቃ ዓይነት ሄቪ ሜታል የሚባለው ፈጣንና ጮክ ያለ ምት ያለው ሙዚቃ ነው። ሄቪ ሜታል በከፍተኛ ጩኸት ብቻ የተወሰነ አይደለም። በዘ ጆርናል ኦፍ አሜሪካን ሜዲካል አሶሴሽን መጽሔት ላይ የቀረበ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በሄቪ ሜታል ሙዚቃ ጮክ ያለና ሰውነት የሚነዝር ምት ይቀርባል። ግጥሞቹም ጥላቻን፣ ጾታዊ ብልግናን፣ አንዳንድ ጊዜም የሰይጣን አምልኮትን ከፍ ከፍ በሚያደርጉ ስንኞች የተሞላ ነው።” የአንዳንዶቹ የሙዚቃ ቡድኖች ስም ብቻውን ይህ ዓይነቱ ሙዚቃ ምን ያህል በብልግና የተሞላና ወራዳ መሆኑን ያሳያል። እንደ “መርዝ”፣ “ጠመንጃ” እና “ሞት” የመሰሉትን ቃላት የያዙ ስሞች አሉአቸው። ይሁን እንጂ ሄቪ ሜታል ሙዚቃ ወደ ፓንክ ሮክ ከሚያደላው የትራሽ ሜታል ሙዚቃና የሞት መልእክት ከሚያስተላልፈው የዴዝ ሜታል ሙዚቃ ጋር ሲወዳደር በጣም የተሻለ ነው። የእነዚህ ሙዚቃ ቡድኖች እንደ “ሰው በላ” እና “መርዶ” በመሰሉት ቃሎች ይጠቀማሉ። በብዙ አገሮች ያሉ ወጣቶች እነዚህ ቃላት እንግሊዝኛ ወይም ሌላ የባዕድ ቋንቋ ስለሆኑ የቱን ያህል ዘግናኝ መሆናቸውን ላይገነዘቡት ይችላሉ።
12 ሄቪ ሜታል ሙዚቃ በወጣቶች ላይ ከሚታየው ራስን በራስ የመግደል፣ የጭንቀትና ተገቢ ካልሆነ የመድኃኒት አጠቃቀም ጋር ዝምድና እንዳለው ተረጋግጦአል። ይህ ዓይነቱ ሙዚቃ ከግልፍተኝነት ባሕርይ ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ስላለው አንድ የሬዲዮ አማካሪ “ወላጆቻችሁን ለመግደል የምትሰሙት ሙዚቃ” የሚል የቅጽል ስም ሰጥተውታል። ብዙ ወላጆችንና የፖሊስ መኮንኖችን የሚያስደነግጣቸው ከሰይጣን አምልኮ ጋር ያለው ግንኙነት ነው። አንድ መርማሪ “የሰይጣን አምልኮ የሚፈጽሙ ወጣቶች ወደዚህ አምልኮ የገቡት እንዲህ ያለውን ሙዚቃ በመስማት ነው” ብሎአል። አስተያየቱን ሲደመድም “እንዴት ወዳለ አቅጣጫ እያመሩ እንዳሉ አያውቁም” ብሎአል።
13. ሄቪ ሜታል ሙዚቃ ማዳመጥ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?
13 ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወጣቶች የሰይጣን ዘዴዎች የተሰወሩባቸው መሆን አይገባቸውም። (2 ቆሮንቶስ 2:11) “መጋደላችን . . . በሰማያዊም ሥፍራ ካለው የክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው።” (ኤፌሶን 6:12) አንድ ሰው በራሱ የሙዚቃ ምርጫ አጋንንትን ወደ ሕይወቱ ጋብዞ ቢያስገባ እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል? (1 ቆሮንቶስ 10:20, 21) ሆኖም ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች እንዲህ ያለውን ሙዚቃ የሚወዱ ይመስላል። አንዳንዶች ለዚህ ሙዚቃ ያላቸውን ጥማት ለማርካት ስውር ዘዴዎችን እስከመፈለግ ደርሰዋል። አንዲት ወጣት ልጃገረድ እንዲህ ብላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ሌሊት ሄቪ ሜታል ሙዚቃ ስሰማ አድር ነበር። በሄቪ ሜታል ወዳጆች የሚዘጋጁ መጽሔቶችን ገዝቼ በጫማ ካርቶን ውስጥ ከወላጆቼ ሸሽጌ አስቀምጥ ነበር። ወላጆቼን ዋሽቼአቸዋለሁ። ይሖዋ በዚህ እንደማይደሰት አውቅ ነበር።” ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ የተመለሰችው በንቁ! መጽሔት ላይ የቀረበ ርዕሰ ትምህርት ካነበበች በኋላ ነበር። እንደነዚህ ባሉ ሙዚቃዎች የሚጠመዱ ወጣቶች ምን ያህል ይሆኑ ይሆን?
የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ
14, 15. ጤናማ ያልሆነ ሙዚቃ መስማት አፍራሽና መጥፎ ውጤት በራሳችን ላይ እንደሚያመጣ እርግጠኛ ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
14 እንዲህ ያለው ሙዚቃ ሊያመጣባችሁ የሚችለውን አደጋ አቅልላችሁ አትመልከቱ። እርግጥ አንድ ዘፈን ስለሰማችሁ ብቻ ሰው ለመግደል ወይም የጾታ ብልግና ለመፈጸም አትነሳሱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ገላትያ 6:8 “በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳልና” ይላል። ምድራዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ የሆነ ሙዚቃ ማዳመጥ በራሳችሁ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። (ከያዕቆብ 3:15 ጋር አወዳድር።) ጆሴፍ ስቱሲ የተባሉ የሙዚቃ ፕሮፌሰር የሚከተለውን እንደተናገሩ ተጠቅሰዋል:- “ማንኛውም ዓይነት ሙዚቃ መንፈሳችንን፣ ስሜታችንን፣ ዝንባሌያችንን እንዲሁም የእነዚህ ውጤት የሆነውን ጠባያችንን ይነካል። . . . ‘ሄቪ ሜታል ሙዚቃ አዳምጣለሁ፣ ግን በእኔ ላይ ምንም ዓይነት ውጤት የለውም’ የሚል ሰው ተሳስቶአል። የተለያዩ ሰዎችን በተለያየ መንገድና መጠን ስለሚነካ ብቻ ነው።”
15 አንድ ክርስቲያን ወጣት “በትራሽ ሜታል ሙዚቃ ሳላውቀው በመጠመዴ መላው ባሕርዬ ተለውጦ ነበር” ብሎአል። ብዙ ሳይቆይ አጋንንቶች ችግር ሊያደርሱበት ጀመሩ። “ወዲያው የሙዚቃ ካሴቶቼንና ሸክላዎቼን አውጥቼ ከጣልኩ በኋላ ከአጋንንት ነጻ ሆንኩ።” ሌላው ወጣት ደግሞ “አዳምጣቸው የነበሩ ሙዚቃዎች መናፍስትነትን፣ አደንዛዥ መድኃኒቶችን ወይም የጾታን ብልግናን የሚያወድሱ ነበሩ። ብዙ ወጣቶች እኛን አይነካንም ይላሉ። እኔን ግን ነክቶኛል። ከእውነት የወጣሁ ያህል ነበር ለማለት እችላለሁ” ብሎአል። አንድ ምሳሌ “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?” ይላል። — ምሳሌ 6:27
ራሳችሁን ጠብቁ
16. የዛሬዎቹን ሙዚቃዎች ስለሚደርሱና ስለሚጫወቱ ሰዎች ምን ሊባል ይችላል?
16 ጳውሎስ በጥንትዋ ኤፌሶን ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸው ደንዳናነት ጠንቅ ልቦናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ።” (ኤፌሶን 4:17, 18) አብዛኞቹን የዘመናችን ሙዚቃዎች ስለሚደርሱና ስለሚጫወቱ ሰዎችስ ይህን የመሰለ ቃል ለመናገር አይቻልምን? ዛሬ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ማንኛውም ዓይነት ሙዚቃ የዚህ የነገሮች ሥርዓት አምላክ የሆነውን የሰይጣን ዲያብሎስን ተጽእኖ የሚያንጸባርቅ ሆኖአል። — 2 ቆሮንቶስ 4:4
17. ወጣቶች ሙዚቃን እንዴት ሊመዝኑና ሊፈትኑ ይችላሉ?
17 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻ ቀኖች ሲናገር “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ስለዚህ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ስለምትመርጠው ሙዚቃ ጠንቃቃ መሆን ያስፈልግሃል። አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ክር ርዕስ ራሱ መጥፎ ሙዚቃ መሆኑን ሊያሳይ ይችላል። ኢዮብ 12:11 “ምላስ መብልን እንደሚቀምስ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን?” ይላል። አንተም በተመሳሳይ ማንኛውንም ሙዚቃ ለናሙና ያህል ጥቂት በመስማት ጥሩ ወይም መጥፎ ሙዚቃ መሆኑን ለመወሰን ትችላለህ። ዜማው ምን ዓይነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል? በውስጥህ የአውሬነት፣ የወራዳነት ወይም የፉክክር መንፈስ ይቀሰቅስብሃልን? (ገላትያ 5:19–21) ግጥሞቹስ? የጾታ ብልግናን የሚያስፋፉ፣ በመድኃኒት አለአግባብ ለመጠቀም ወይም ለመናገር እንኳን የሚያሳፍሩ ነገሮችን ለማድረግ የሚያነሳሱ ናቸውን? (ኤፌሶን 5:12) መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ያሉት ነገሮች በሙዚቃ ምት ታጅበው በተደጋጋሚ መሰማት ይቅርና በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሊነገሩ እንኳን እንደማይገባ ይገልጻል። (ኤፌሶን 5:3) በካሴቱ ሽፋን ላይ የሚቀርበው ሥዕልስ? የመናፍስት አምልኮን የሚያስፋፋ ወይም የጾታ ስሜት የሚቀሰቅስ ሥዕል አለውን?
18. (ሀ) አንዳንድ ወጣቶች በሙዚቃ ረገድ ምን ለውጦችን ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል? (ለ) ወጣቶች ጤናማ ሙዚቃዎችን ሊወዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
18 በምትሰሙት የሙዚቃ ዓይነት ረገድ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ወይም አጋንንታዊ መልእክቶችን የሚያስተላልፉ ሸክላዎች ወይም ካሴቶች ካሉአችሁ ወዲያውኑ አስወግዱአቸው። (ከሥራ 19:19 ጋር አወዳድር።) ይህ ማለት ግን በሙዚቃ ልትደሰቱ አትችሉም ማለት አይደለም። ሁሉም ሙዚቃዎች መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንድ ወጣቶች የሙዚቃ ስሜታቸውን ሰፋ ስላደረጉ በአሁኑ ጊዜ በክላሲካል፣ በባሕላዊ፣ በለስላሳ ጃዝና በሌላ ዓይነት ሙዚቃዎች መደሰት ችለዋል። የመንግሥቱ ዝማሬ ካሴቶች ብዙ ወጣቶች የሚያንጽ የኦርኬስትራ ሙዚቃ እንዲወዱ ረድቶአቸዋል።
19. ሙዚቃ ተገቢ ቦታውን እንዲይዝ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
19 ሙዚቃ መለኮታዊ ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ ለብዙዎች ጊዜያቸውን የሚይዝባቸው ሆኖባቸዋል። እነዚህ ሰዎች “መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታ እየሰሙ የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ሥራ” እንዳልተመለከቱት የጥንት እስራኤላውያን ናቸው። (ኢሳይያስ 5:12) ለሙዚቃ ተገቢ ቦታ ሰጥታችሁ ትኩረታችሁንና አሳባችሁን በሙሉ በይሖዋ ሥራ ላይ ማድረግ ዓላማችሁ ይሁን። ስለምትመርጡት ሙዚቃ ጠንቃቆችና መራጮች ሁኑ። ይህን ካደረጋችሁ በዚህ መለኮታዊ ሥጦታ በአግባቡ ለመጠቀም ትችላላችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የእስራኤል ብሔር በሥነ ጥበብና በሙዚቃ ረገድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበረ ግልጽ ነው። የአሦራውያን የጥርብ ድንጋይ ቅርጽ ንጉሥ ሰናክሬብ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሕዝቅያስ እስራኤላውያን ሙዚቀኞችን ግብር አድርጎ እንዲሰጠው መጠየቁን ያመለክታል። ግሮቭስ ዲክሽነሪ ኦቭ ሚዩዚክ ኤንድ ሚዩዚሽያንስ “ሙዚቀኞች ግብር ሆነው እንዲሰጡ መጠየቅ የተለመደ ነገር አልነበረም” ብሎአል።
ታስታውሳለህን?
◻ ሙዚቃ መለኮታዊ ሥጦታ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ በጥንት ጊዜ ሰዎች ሙዚቃን አለአግባብ የተጠቀሙት እንዴት ነበር?
◻ የራፕና የሄቪ ሜታል ሙዚቃዎች በክርስቲያን ወጣቶች ላይ ምን ዓይነት አደጋዎችን ሊያመጡ ይችላሉ?
◻ ክርስቲያን ወጣቶች በሙዚቃ ምርጫቸው ረገድ ጥንቃቄ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙዚቃ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ይሖዋን ለማወደስ ብዙ ጊዜ አገልግሎአል