የሃይማኖታዊ ሥዕሎች ትክክለኛና ስህተተኛ አጠቃቀም
ቦታው ሩስያ፣ ሴይንት ፒተርስበርግ፤ ቀኑ ነሐሴ 2, 1914 ነው። በከፍተኛ ስሜት የተነሳሱና ምስሎችን በእጆቻቸው ይዘው የሚያወዛውዙ ሰዎች በዛሩ (በንጉሡ) ቤተ መንግሥት ተሰብስበዋል። ሠፊ በሆነ አዳራሽ ውስጥ አንድ መሠዊያ ይገኛል። በመሰዊያው ላይ ሕጻን ልጅ በእጆችዋ ያቀፈች ሴት ሥዕል ቆሞአል። የዚህ ምስል ስም “ቭላዲሚር የአምላክ እናት” ይባላል። በዚያ የተሰበሰቡት ብዙ ሰዎች ይህን ሥዕል በጣም ክቡር የሆነ የሩስያ ቅዱስ ሀብት እንደሆነ ይቆጥራሉ።
እንዲያውም ይህ ምስል ተአምራትን እንደሚሠራ ይታመን ነበር። የሩስያ ሠራዊት በናፖሊዮን ላይ በዘመተበት በ1812 ጀኔራል ኩቱዞቭ በዚህ ምስል ፊት ጸልየዋል። በዚህ ጊዜ ደግሞ ዛሩ ዳግማዊ ኒኮላስ አገራቸውን ለጦርነት ካስከተቱ በኋላ በዚህ ምስል ፊት ቆመዋል። ቀኝ እጃቸውን አንስተው “በሩስያ ምድር ላይ አንድ ጠላት እስከማይኖር ድረስ ሰላም እንደማላደርግ እምላለሁ” ሲሉ የመሐላ ቃላቸውን አሰሙ።
ዛሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ አምላክ ሠራዊታቸውን እንዲባርክላቸው ለመለማመን ወደ ሞስኮ ሄዱ። በፍልሰታ ካቴድራል ውስጥ በተለያዩ እንቁዎች ባሸበረቀው የኢየሱስ፣ የማርያም፣ የመላእክትና የቅዱሳን ምስል በሚገኝበት ሥፍራ ፊት ለፊት ተንበርክከው ጸለዩ።
እነዚህ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ከአደጋ አላዳኑአቸውም። የሩስያ ሠራዊት ከአራት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ስድስት ሚልዮን ሰዎች አልቀውበት ብዙ ግዛቶቹን አጣ። ከዚህም በላይ ዛሩ፣ እተጌይቱና አምስት ልጆቻቸው በአሠቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። ለብዙ መቶ ዘመናት የቆየው ዘውዳዊ አስተዳደር ተወግዶ አገሪቱ ሃይማኖት በሚቃወም አብዮታዊ መንግሥት መገዛት ጀመረች። ዛር ኒኮላስ በምስሎች ላይ የነበራቸው እምነትና ትምክህት ከንቱ ሆነ።
ቢሆንም በሩስያም ሆነ በሌሎች አገሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምስሎችን ቅዱስ አድርገው መመልከታቸው አሁንም አልቀረም። ይህም አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን ያስነሳል። አምላክ እንደነዚህ ባሉት ምስሎች ፊት የሚፈጸመውን የአምልኮ ድርጊት እንዴት ይመለከታል? በቤት ውስጥ ሥዕሎችን የመስቀል ልማድስ?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ኢየሱስ በምድር ሳለ በሙሴ በኩል የተሰጠውን የአምላክ ሕግ ያከብር ነበር። በዚህም ሕግ ውስጥ ከአሥሩ ትዕዛዛት ውስጥ ሁለተኛ የሆነው ትዕዛዝ ይገኛል። እንዲህ ይላል:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም።” — ዘጸአት 20:4, 5
በዚህ መሠረት ኢየሱስ በሰው እጅ በተሠሩ ሥዕሎች ወይም ምስሎች ረዳትነት አምላክን አላመለከም። ከዚህ ይልቅ የእርሱ አምልኮት አባቱ “እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምሥጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም [አላካፍልም አዓት] ” ሲል ከተናገረው ቃል ጋር የሚስማማ ነበር። — ኢሳይያስ 42:8
ከዚህም በላይ አምላክ አለምንም ግዑዝ ነገር ረዳትነት መመለክ የሚገባው ለምን እንደሆነ ኢየሱስ ገልጾአል። እንዲህ አለ:- “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በእውነትና በመንፈስ የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፣ አብ ሊሰግዱለት እንደነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” — ዮሐንስ 4:23, 24
እውነተኞቹ ደቀ መዛሙርትም ልክ እንደ ኢየሱስ አምላክ የሚመለክበትን ትክክለኛ መንገድ ለሌሎች አስተምረዋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ ጊዜ የማይታዩ አምላኮቻቸውን በጣዖታት አማካኝነት ያመልኩ ለነበሩ ግሪካውያን ፈላስፎች ተናግሮአል። ስለ ሰው ልጅ ፈጣሪ ሲነግራቸውም እንዲህ አለ:- “አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።” ቆየት ብሎም ይኸው ሐዋርያ ለክርስቲያኖች “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም” ብሎአል። ክርስቲያኖች “ጣዖትን ከማምለክ” እንዲሸሹም ተናግሮአል። — ሥራ 17:16–31፤ 2 ቆሮንቶስ 5:7፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14
ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደ ጣዖት አምልኮ ሊመሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሳይዘገይ ያርም እንደነበረ አንድ በራሱ ላይ የደረሰ ተሞክሮ ያሳየናል። ሮማዊው ወታደራዊ መኮንን ቆርኔሌዎስ እግሩ ላይ ወድቆ በሰገደ ጊዜ ጴጥሮስ ከልክሎታል። ቆርኔሌዎስን ብድግ አድርጎ “ተነሣ፤ እኔ ደግሞ ሰው ነኝ” ብሎታል። — ሥራ 10:26
ሐዋርያው ዮሐንስም በተመለከተው መለኮታዊ ራእይ በጣም በመደነቁ ምክንያት በመልአኩ እግር ሥር ተደፍቶአል። መልአኩ ግን “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” ብሎታል። (ራእይ 22:8, 9) ሐዋርያው ይህ ምክር ወዲያው ገባው። ለእኛም ጥቅም በማሰብ በጽሑፍ መዝግቦ አቆይቶልናል።
ይሁን እንጂ ከላይ የተገለጹት ተሞክሮዎች ከሃይማኖታዊ ሥዕሎች ጋር ምን ዝምድና ይኖራቸዋል? ቆርኔሌዎስ ከክርስቲያን ሐዋርያት ለአንዱ ወድቆ መስገዱ ስህተት ከሆነ ሕይወት የሌላቸውን የቅዱሳን ምስሎች ቅዱስ አድርጎ መመልከት ትክክል ይሆናልን? ከክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ ሕያው ለሆነ መልአክ ወድቆ መስገዱ ስህተት ከሆነ ሕይወት የሌላቸውን የመላእክት ሥዕሎች እንደ ቅዱስ ነገር ቆጥሮ መስገድ ትክክል ይሆናልን? በእርግጥም እንደዚህ ያለ ድርጊት ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” ሲል የሰጠውን ምክር የሚጻረር ነው። — 1 ዮሐንስ 5:21
ለማስተማሪያና ለማስጌጫ መጠቀም
ይህ ማለት ግን አንድ ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርዒት የሚያሳይ ሥዕል መስቀል ጣዖት አምልኮ ነው ማለት አይደለም። ይህ መጽሔት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥዕሎችን በማስተማሪያነት ይጠቀማል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥዕሎችን ቤቶችን፣ ግድግዳዎችንና ሕንጻዎችን ለማስጌጫ መጠቀም ይቻላል። ቢሆንም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሌሎች እንደ ቅዱስ ነገር አድርገው የሚቆጥሩትን ሥዕል ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ የሚወክልን ምስል ግድግዳው ላይ ለመስቀል አይፈልግም። — ሮሜ 14:13
አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሥዕሎችና ምስሎች በኢየሱስ፣ በማርያም በመላእክትና በቅዱሳን ራስ ዙሪያ የብርሃን አክሊል አላቸው። ይህም አክሊለ ብርሃን ተብሎ ይጠራል። ይህ አክሊለ ብርሃን ምንጩ ምንድን ነው? ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ (1987 እትም) “አረማውያን ሠዓሊዎችና ሐውልት ቀራጮች የተለያዩ አማልክትን ታላቅ ክብርና ኃይል ለማመልከት ይጠቀሙበት የነበረ በመሆኑ ምንጩ ክርስቲያናዊ አይደለም” ይላል። በባምበር ካስኮይን የተጻፈው ዘ ክርስቲያንስ የተባለ መጽሐፍ በሮማ ከሚገኘው የካፒቶሊኒ ቤተ መዘክር የተገኘ አክሊለ ብርሃን ያለው የፀሐይ ምሥል አውጥቶአል። ይህ አምላክ በአረመኔ ሮማውያን ይመለክ የነበረ አምላክ ነው። በኋላም ካስኮይኒ እንደገለጹት “ክርስቲያኖች የፀሐይን አክሊለ ብርሃን ተዋሱ።” አዎ፤ አክሊለ ብርሃን ከአረማውያን የፀሐይ አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለው ነው።
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሁኔታዎችን ከአረማውያን የጣዖት አምልኮ ምስሎች ጋር የሚቀላቅሉ ሥዕሎች በክርስቲያኖች ቤት ግድግዳ ላይ መሰቀል ይገባቸዋልን? አይገባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ አንዲህ በማለት ይመክራል:- “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? . . . ስለዚህም ጌታ [ይሖዋ አዓት]:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል። ሁሉን የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ . . . ይላል።” — 2 ቆሮንቶስ 6:16, 17
ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ይህን ምክር ችላ ማለት ጀመሩ። ኢየሱስና ሐዋርያት እንደተነበዩት ክህደት ተስፋፋ። (ማቴዎስ 24:24፤ ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1) የሮማ ንጉሠ ነገሥት የነበረው አፄ ቆስጠንጢኖስ በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ የክህደት ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ። በዚህ ጊዜ አንድ የአረማውያን ቡድን ራሱን “ክርስቲያን” ነኝ ብሎ በይፋ መጥራት ጀመረ። ይህ ቡድን የንጉሠ ነገሥቱን ምስል ማምለክ ይጨምር ነበር። በተጨማሪም የቅድመ አያቶቻቸውንና የዝነኛ ሰዎችን ሥዕል ይሰቅሉ ነበር። ጆን ቴይለር ኢይከን ፔይንቲንግ በተባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት “ንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ ይቀርብለት ስለነበረ ሰዎች የንጉሡ ምሥል የተሳለባቸውን ሸራዎችና እንጨቶች ያመልኩ ነበር። በዚህም ምክንያት ምስሎችን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ መመልከት ቀላል ነገር ሆነ።” በዚህ መንገድ የአረማውያን የሥዕል አምልኮ የኢየሱስን፣ የማርያምን፣ የመላእክትንና የቅዱሳንን ሥዕሎች ቅዱስ አድርጎ በማምለክ ተተካ።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህ ልማድ ትክክለኛ መሆኑን ለማሳመን የሞከሩት እንዴት ነው?
ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚለው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሥዕሎችን አምልኮ ለመደገፍ የሚያቀርቡት ምክንያት የጥንቶቹ አረመኔ ፈላስፎች ያቀርቡ ከነበረው ምክንያት የተለየ አይደለም። እንደ ፕሉታርክ፣ እንደ ዲዮ ክሪሶስቶም፣ እንደ ጢሮሱ ማክሲም፣ እንደ ሴልሰስ፣ ፕሮፊሪ እና እንደ ጁሊያን የመሰሉት ፈላስፎች ጣዖታት ሕይወት የሌላቸው በድኖች መሆናቸውን አምነዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አረማዊ ፈላስፎች ጣዖቶች የማይታዩትን አማልክት ለማምለክ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች እንደሆኑ በመግለጽ የጣዖት አምልኮ ትክክል መሆኑን ለማሳመን ሞክረዋል። ሊዮኒድ ኡዝቤንስኪ የተባሉት ሩስያዊ የአምልኮ ምስል ቀራጭ ዘ ሚኒንግ ኦፍ አይከንስ በተባለው መጽሐፋቸው “የቤተ ክርስቲያን አባቶች የግሪኮችን ፍልስፍና እንደ መሣሪያ አድርገው በመጠቀም የግሪኮችን አስተሳሰብና ቋንቋ ወደ ክርስትና ሃይማኖት አስገብተዋል” ብለዋል። — ከቆላስይስ 2:8 ጋር አወዳድር።
ብዙ ሰዎች ምስሎችን ቅዱስ አድርጎ መመልከት ትክክል ስላለመሆኑ የሚቀርቡትን ምክንያቶች መቀበል ይከብዳቸዋል። ጆን ቴለር ኢይከን ፔይንቲንግ በተባለው መጽሐፋቸው “አንድን ምስል ምስሉ በሚወክለው ነገር ምክንያት በማምለክና ምስሉን ራሱን በማምለክ መካከል ያለው ልዩነት በጣም በተማሩ ሰዎች ካልሆነ በቀር በግልጽ ሊታይ የሚችል አይደለም” ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሃይማኖታዊ ምስሎች የሚናገረው ግን ለመረዳት የማያዳግትና ግልጽ ነው። በደቡብ አፍሪካ፣ በጆሃንስበርግ የምትኖረውን ኤሚልያን እንውሰድ። ቀናተኛ ካቶሊክ ስለነበረች በሥዕሎች ፊት እየተንበረከከች ትጸልይ ነበር። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤትዋን አንኳኳች። ኤሚልያ ከዚህች የይሖዋ ምሥክር ጋር ባደረገችው ውይይት ከራስዋ የፖርቱጊዝ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ይሖዋ የተባለ ስም እንዳለው ስታውቅ በጣም ተደነቀች። (መዝሙር 83:18) ጥናትዋን እየቀጠለች ስትሄድ “ይሖዋን እንዳላስቀይመው ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ብላ ጠየቀች። ምሥክርዋ በግድግዳዋ ላይ የተሰቀሉትን ሥዕሎች ካመለከተቻት በኋላ መዝሙር 115:4–8ን እንድታነብ ጠየቀቻት። በዚያው ቀን ምሽት የኤሚልያ ባል ከሥራ እንደመጣ ሃይማኖታዊ ሥዕሎችዋን በሙሉ ማስወገድ እንደምትፈልግ ነገረችው። እርሱም ተስማማ። በማግስቱ ቶኒ እና ማንዌል የተባሉትን ሁለት ልጆችዋን አስነስታ ሥዕሎቹን ሰባብረው እንዲያቃጥሉ አደረገች። ኤሚልያ ይህን እርምጃ ከወሰደች 25 ዓመት ሆኖአታል። ታዲያ ይህን በማድረግዋ ተጸጽታለችን? አልተጸጸተችም። እንዲያውም ከቤተሰቦችዋ ጋር ሆና ከጎረቤቶችዋ መካከል ብዙዎቹ ደስተኛ የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ ረድታለች።
ይህን የመሰሉ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት ምድር አቀፍ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክን ተምረዋል። አንተም ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ አምልኮ ከሚያስገኘው በረከት ልትካፈል ትችላለህ። ኢየሱስ እንዳለው “አብ ሊሰግዱለት እንደነዚህ ያሉትን ይሻልና።” — ዮሐንስ 4:23, 24
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛር ኒኮላስ ዳግማዊ ሠራዊታቸውን በሃይማኖታዊ ምስል ሲባርኩ
[ምንጭ]
Photo by C.N.