መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናዊው ሰው የሚሆን ተግባራዊ መመሪያ
“ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለሆነ ጠቃሚ በሆነ መንገድ . . . የሰዎችን ሕይወት ለመምራት ሊያገለግል ይችላል።“—2 ጢሞቴዎስ 3:16፣ “ዘ ጀሩሳሌም ባይብል“
ይህ ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን ተግባራዊ የሆነበትን ዋና ምክንያት ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው። ፈጣሪያችን አምላክ ስለሆነ ከእርሱ ይበልጥ ስለ አካላችን፣ አእምሮአችን፣ ስሜታችንና ስለሚያስፈልገን ነገር የሚያውቅ የለም። እሥራኤላዊው ንጉሥ ዳዊት አንድ ጊዜ ስለ ይሖዋ አምላክ “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ [የአካሌ ክፍሎችም አንድስ እንኳን ሳይቀር በመጽሐፍህ ውስጥ ተጻፉ አዓት] በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 139:16) ፈጣሪያችን ይህን ያህል ስለ እኛ የሚያውቅ ከሆነ በሕይወታችን እንዴት ደስተኞችና የተሳካልን ልንሆን እንደምንችል እርሱ የሚሰጠን ምክር ልንመረምረው እንደሚገባ የታወቀ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለዘመናችንም ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉና ከሰው ትክክለኛ አቅም በላይ አለመሆናቸው በተሞክሮ ታይቷል። መሠረታዊ ሥርዓቶቹ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። የሚከተሉት አራት ምሳሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የዕለት ተዕለት ተግባራዊነት የሚገልጹ ናቸው፦
በሰዎች መካከል ያለ ዝምድናና የግል ጠባይ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጤናማና የተሳካ ግንኙነት ሊያስገኙ የሚችሉ ጥሩ ግላዊ የሥነ ምግባር ደንቦችን ለማዳበር ይረዳል። ለምሳሌ ያህል የእሥራኤል ብሔር “በሕዝብህ ልጆች ቂም አትያዝ፣ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ“ (ዘሌዋውያን 19:18) ምንም እንኳን ለእሥራኤል የተሰጠው ሕግ የሚገዛን ባይሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተል ከባልንጀሮቻችን ጋር በሰላም እንድንኖር ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ሁሉም ሰው በገላትያ 5:22,23 ላይ የሚገኙትን “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት [ደግነት አዓት] በጎነት [ጥሩነት አዓት]፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም“ በማለት የተገለጹትን መንፈሳዊ ባሕርያት ቢኮተኩት ምን ያህል ችግሮች ሊቃለሉ እንደሚችሉ አስብ።—ከሮሜ 8:5,6 ጋር አወዳድር።
መጥፎነቱ ግን የኑሮ ጭነቶች ሲደራረቡ ብዙውን ጊዜ ውጥረትና ግጭት ይፈጠራል። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በምሳሌ 29:11 ላይ የሚገኙትን “ሰነፍ ሰው ቁጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል“ የሚሉ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ቃላት በሥራ ላይ ማዋል ከብዙ ችግር ያድነናል።—ከምሳሌ 15:1፤ ከማቴዎስ 7:12ና ከቆላስይስ 3:12-14 ጋር አወዳድር።
ጥሩ ምክር ነው፤ ግን በእውነተኛው ሕይወት ላይ ይሠራልን? በፈረንሳይ አገር የግልፍተኝነት ጠባይ የነበረበትን አንድ ሰው ለአብነት ያህል እንጥቀስ። በረብሸኝነት ጠባዩ ምክንያት ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ችግሮችና እሥራትም ሳይቀር አጋጥሞታል። የቡጢ አዋቂ መሆኑንም ቢሆን ረብሸኝነቱን አባባሰው እንጂ አልረዳውም። ባንድ ወቅት በዚህ ሰውና በአባቱ መካከል ጠብ ተነሳ። ድንገት ሳያስበው አባቱን በአንድ የቡጢ ምት ወለሉ ላይ ዘረራቸው። በመካከላቸው መራራ የሆነ መለያየት ሆነ።
በመካከሉ ይህ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መማር ጀመረ። ጥናቱም ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ራሱን በጥሞና እንዲመረመር አደረገው። በብዙ ጥረት የግል ጠባዩ መለወጥ ጀመረና ሰላማዊ እየሆነ መጣ። ከዚህ በኋላ አንድ ቀን ከአባቱ ጋር ለመታረቅ ወደ አባቱ መጣ። አባትየውም ልጁ ባደረገው ለውጥ በጣም ከመደነቃቸውም የተነሳ የቀድሞው ግንኙነታቸው ተመለሰ።
ይህ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ ነው፣ . . . የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል“ የሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት እውነተኛ ለመሆናቸው ከሚመሰክሩት ብዙ ምሳሌዎች አንዱ ብቻ ነው።—ዕብራውያን 4:12
የቤተሰብ ሕይወት፦ ቤተሰብህ ደስተኛ ነውን? ብዙ ቤተሰቦች ደስተኞች አይደሉም። ዘ ናታል ዊትነስ የተሰኘ አንድ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ “የቤተሰብ ሕይወት እንደ አንድ ተቋም ሆኖ የመቀጠሉ ጉዳይ በአስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑ አሁን እርግጠኛ ነገር ሆኗል። የአሁኑ ጊዜ ልጆች የሚወለዱት በማኅበራዊ ነውጥ ውስጥ ነው“ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ችግሮች በሚነሱበት ጊዜም እንኳን ሳይቀር ደስተኛ ቤተሰብ ለማፍራት እንዲረዱ ታስበው በተዘጋጁ ተግባራዊ ምክሮች የተሞላ ነው። ለምሳሌ ያህል የባሎችን የሥራ ድርሻ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል“ ይላል። ባልየው ይህን አስፈላጊ ደንብ ሲፈጽም ሚስቱም ለባልዋ “ጥልቅ አክብሮት [አዓት] በማሳደር አጸፋውን መመለስ የሚያስደስት ነገር ይሆንላታል። (ኤፌሶን 5:25-29, 33) በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው ዝምድናም በኤፌሶን 6:4 ላይ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻቸሁን በጌታ [በይሖዋ አዓት] ምክርና ተግሳጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው“ በማለት ሐሳብ ተሰጥቶበታል። ይህም በምላሹ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ እንዲከተሉና ለወላጆቻቸው ታዛዦች እንዲሆኑ ቀላል የሚያደርግ የቤተሰብ ሁኔታን ይፈጥራል።—ኤፌሶን 6:1
ከላይ የተሰጠው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተሰብ ሕይወት ከሰጣቸው ገለፃዎች ውስጥ ለናሙና ያህል የተጠቀሰ ብቻ ነው። ብዙ ቤተሰቦች ለአምላክ አመራር አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በቤታቸው ውስጥ መልካም ውጤትና ደስታን አግኝተዋል። የሁለት ልጆች አባት የሆነው ኤድዋርድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋል ያገኛቸውን ጥቅሞች እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦ “ትዳሬ በመፈራረስ ላይ ነበር“ ይላል ሲያስታውስ። “ከልጆቼ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ለመገንባት ጊዜ አልነበረኝም እንድንቀራረብ ያደረገን ብቸኛው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚናገረውን በሥራ ላይ ማዋላችን ብቻ ነበር።“—ምሳሌ 13:24፤ 24:3 ቆላስይስ 3:18-21፤ 1 ጴጥሮስ 3:1-7
የአእምሮ፣ የአካልና የስሜት ጤንነት፦ የአንድ ሰው አካላዊ ጤንነት ከፊል ከአእምሮውና ከስሜታዊ ጤንነቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን የተደረገው ጥናት ይገልጻል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ ሲናገር “የተለመዱ የጭንቀት ምልክቶች የልብ ምት መፍጠንን፣ የደም ግፊት መጨመርን፣ የጡንቻ መወጣጠርን፣ የአእምሮ ጭንቀትንና ሐሳብን ለመሰብሰብ አለመቻልን ይጨምራሉ“ ይላል። ይሁንና የኃይል ድርጊቶችን መፈጸሙ ወይም የምማቱ ማስመሰል ጭንቀትን ለማቃለል የሚረዳ መንገድ ነው ብለው የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ዘ ስታር የተሰኘ አንድ የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ “ቡጢ ከፍተኛ የሆነ የጭንቀት ማቅለያ ሊሆን ይችላል“ በማለት ይናገራል። ይህ ጋዜጣ ይህን የተናገረው የተስማሚ ጠባይ አማካሪ የሆኑት ጄን ክላሴንስ የተባሉ ሴት “አንዲት ሴት በጣም የሚያበሳጭ ቀን ካጋጠማት ጭንቀቷን ለማስወገድ አንድ ቦርሳ ወስዳ በቡጢ ትምታ“ በማለት የተናገሯቸውን ቃላት በመጥቀስ ነው።
ከዚህ ይልቅ የጭንቀቱን መንስዔ ለመቆጣጠር መለማመድ በጣም የተሻለ አይሆንም? ስትረስ-ዘ ሞደርን ስኮርጅ በተሰኘው መጽሔት ውስጥ ዶክተር ማክል ስለትዝኪን “የጭንቀቱን ምክንያት ለይቶ ማወቅ . . . አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ የጭንቀት መንስዔዎች መፍትሔ ወይም መድኃኒት ስላላቸው ነው“ በማለት ይናገራሉ። ጨምረውም “ጭንቀትን ለመቆጣጠር መቻል ለመዳኑ ሒደት በተለያዩ መንገዶች ሊረዳ ይችላል“ ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል“ በማለት ጭንቀትን መቆጣጠር የሚቻልበትን በጣም ውጤታማ መንገድ ይገልጻል። (ፊልጵስዩስ 4:6,7) በዚህ መንገድ ጭንቀትን መቆጣጠር ለአካላዊ ጤንነትም እንኳን ብዙ ጥቅሞች አሉት። ጥቅሙንም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ትሑት [የተረጋጋ አዓት] ልብ ለሥጋ ሕይወት ነው“ በማለት ይገልጸዋል። (ምሳሌ 14:30) አንድ ሌላ ምሳሌ “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች“ ይላል።—ምሳሌ 17:22
ከጭንቀትና ከውጥረት ለመላቀቅ በሚደረገው ሙከራ ብዙ ሰዎች የሚመኩት በትንባሆ፣ በአልኮልና በአደንዛዥ መድኃኒቶች ላይ ነው። እንዲህ ያለው ሱስ የሚያስከትለው ጉዳት በማስረጃ ተረጋግጧል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ ’ሥጋን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን ስለማንጻት’ አበክሮ ያስገነዝባል። (2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ከምሳሌ 23:29-35 ጋር አወዳድር።) በእርግጥም በዛሬው ዓለም እንደዚህ ካሉት ጎጂ ልማዶች መራቅ ተግባራዊ መከላከያ ነው።
ሥራ፣ ገንዘብና ሐቀኝነት፦ ስንፍና ምንጊዜም ጥሩ አይደለም። ምሳሌ 20:4 “ታካች ሰው በብርድ ምክንያት አያርስም፤ ስለዚህ በመከር ይለምናል፣ ምንም አያገኝም“ ይላል። በሌላ በኩል ግን ጠንክሮ መሥራት ጠቃሚ ነው። ኤፌሶን 4:28 “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ“ ይላል። ይኸው ጥቅስ አንድ ሰው “ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም [ጠንክሮ ይሥራ አዓት]“ በማለት ይናገራል።—ከምሳሌ 13:4 ጋር አወዳድር።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ቦታ በሚኖረው ዝምድናም እንኳን በሥራ ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ታውቅ ነበርን? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበሩት “ባሪያዎች“ ሁሉ ሠራተኞች “በሥጋ ጌቶቻቸው [አለቆቻቸው አዓት] ለሆኑ ሁሉ ታዘዙ“ የሚለውን ምክር በሥራ ላይ ቢያውሉ መልካም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አለቆች ወይም “ጌቶች“ የሆኑትም ለሠራተኞቻቸው “በጽድቅና በቅንነት አድርጉላቸው’ ተብሎ የተሰጣቸውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል።-ቆላስይስ 3:22-24፤ 4:1፤ ከ1 ጴጥሮስ 2:18-20 ጋር አወዳድር።
በሐቀኝነት ስለሚደረጉ የንግድ ተግባሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ተብሎአል። በአሁኑ ጊዜ ሐቀኝነት መታጣቱ የሚያሳዝን ነገር ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ተፈላጊነቱ የታወቀና የሚደነቅ ባሕርይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም አጥብቆ የሚገልጸው ይህንኑ ነው። ኢየሱስ አንድ ጊዜ “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው“ ብሎ ነበር።-ሉቃስ 16:10፤ ከምሳሌ 20:10፤ 22:22,23ና ከሉቃስ 6:31 ጋር አወዳድር።
በአንድ የአፍሪካ አገር የአልማዝ ኢንዱስትሪ ውስጥ ብዙ ስርቆትና በሥልጣን መባለግ ነበረ። በኢንዱስትሪው ላይ ኃላፊ የሚሆን ሌላ ሰው ለማስቀመጥ ተወሰነ። የመንግሥት ሚኒስትሮች ለዚህ ሥልጣን ብቁ ናቸው ብለው የሚያስቡአቸውን ሰዎች ስም እንዲያቀርቡ ተጠየቁ። የመንግሥቱ ካቢኔ ይህን ጉዳይ ለመወሰን በተሰበሰበ ጊዜ ሚኒስትሮቹ ያቀረቡአቸው ሰዎች በአብዛኛው በሥልጣን ከመባለግ ነፃ ባለመሆናቸው ምክንያት ስማቸው አንድ ባንድ ተሰረዘ። በመጨረሻም በስም ዝርዝሩ መጨረሻ ላይ ወደ ተመዘገበው የፕሬዘዳንቱ ምርጫ ወደሆነው ሰው ደረሱ።
“እሱ እኮ የፓርቲው አባል አይደለም“ በማለት አንደኛው ሚኒስትር ተቃውሞ አቀረበ።
ፕሬዘዳንቱም ይህ እኮ ፓለቲካዊ ሥልጣን አይደለም በማለት መልስ ሰጡ።
ሌላው ሚኒስትር ደግሞ “የይሖዋ ምስክር ነው“ በማለት ገለጸ።
“ይህን ሥራ ማግኘት ያለበትም ለዚህ ነው“ በማለት ፕሬዘዳንቱ ተናገሩ። ጨምረውም “እነርሱ [የይሖዋ ምስክሮች] ሐቀኞች እንደሆኑ እናውቃለን። የሚያስፈልገንም እንዲህ ያለ ሰው ነው“ አሉ።
አዎን፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሐቀኝነታቸው በዛሬው ዓለምም እንኳን ሳይቀር ጠቃሚያቸው ሆኖ ያገኙታል።
ተግባራዊ ጥበብን እንደ ትልቅ ሀብት ቁጠሩ
እስካሁን “የእግዚአብሔርን ጥበብ ማግኘት“ ምን ማለት እንደሆነ ያየነው በትንሹ ብቻ ነው። (ምሳሌ 2:1-9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጠቃሚና ተግባራዊ የምክር ክምችት ይገኛል። ንጽሕና፣ ትጋት፣ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ፣ ሩካቤ ሥጋ፣ ፍቺ፣ ቀረጥ መክፈል፣ የባሕርይ ልዩነቶችን እንዴት መያዝ እንደሚቻልና ድህነትን መቋቋም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚዳስሳቸው የሕይወት ገጽታዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ናቸው። በኑሮአቸው ያገኙት የተቃና ውጤት ወይም ውድቀት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በሚያውሉበት መጠን ላይ የተመካ መሆኑን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይመሰክራሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስን ጊዜያዊ ተግባራዊነት አስተማማኝ ነው፤ በዚሁም ላይ ብዙ ዘለቄታዊ ጥቅሞች ያላቸው ተስፋዎችም አሉት። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ዓለም ላለው ሥቃይና መከራ ዋና መንስዔ የሆኑት በቅርቡ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት እንደሚስተካከሉ ተስፋ ይሰጣል።—ዳንኤል 2:44፤ 2 ጴጥሮስ 3:11-13፤ ራእይ 21:1-5
እንግዲያውስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የቻልከውን ያህል ብዙ እንድትማር እናበረታታሃለን። የራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለህ እንዲኖርህ አድርግ። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች በደስታ ይረዱሃል። ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙትን ተግባራዊ ሐሳብ በሥራ ላይ በማዋላቸው እንደተጠቀሙ ሁሉ አንተም የአምላክ ቃል አሁንና ለወደፊቱም ያለውን ጥቅም ለመገንዘብና ለማድነቅ ትችላለህ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ፎቶግራፍ]
መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ሕይወት ደስተኛ የሚያደርግ ሊሠራ የሚችል መመሪያ ይሰጣል