በክርስቶስ መገኘት ላይ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ማድረግ
“የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ . . . እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል።”—ማቴዎስ 25:31, 32
1. የሕዝበ ክርስትና ካህናት በማቴዎስ 24:3 ላይ ያሉትን ቃላት የተረጎሙአቸው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ከመሞቱ ከሦስት ቀናት በፊት አራት ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና [በግሪክኛ ፓሩሲያ] የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? ብለው አጥብቀው ጠየቁት። ለብዙ መቶ ዘመናት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና ጸሐፊዎች እነዚህን በማቴዎስ 24:3 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ኢየሱስ ዳግመኛ በሥጋ ተገልጦ ለሰው ልጆች በሙሉ እንደሚታይ በሚያስመስል መንገድ ሲተረጉሟቸው ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በታላቅ ትርዒቶች ታጅቦ በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚመለስ አስተምረዋል። ይህንንም የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ብለው ይጠሩታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ግምቶች ትክክል ናቸውን?
2, 3. (ሀ) ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ ጥራዝ 2 “መምጣት” እና “መገኘት” በሚሉት ቃላት መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ገልጾ ነበር? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች የክርስቶስን ፓሩሲያ በተመለከተ ምን ለመረዳት ቻሉ?
2 የይሖዋ ቅቡዓን የ19ኛው መቶ ዘመን ብርሃን አብሪዎች የነበሩ እንደመሆናቸው መጠን የ1889 ዓመት ከመድረሱ በፊት ስለ ክርስቶስ መመለስ ባላቸው አመለካከት ላይ እርማት አግኝተው ነበር። የመጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 158 እስከ 161 ላይ እንደሚከተለው ብሎ ጽፎ ነበር፦ “ፓሩሲያ . . . መገኘትን ያመለክታል። በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ በተለምዶ እንደሚደረገው መምጣት ተብሎ ፈጽሞ መተርጎም አይገባውም። በጣም ጥሩ የሆነው የአዲስ ኪዳን ትርጉም ‘ኢምፋትክ ዳያግሎት’ ፓሩሲያን መገኘት በማለት በትክክል ተርጉሞታል። [ኢየሱስ] ‘የሰው ልጅ ፓሩሲያ [መገኘት] እንደ ኖህ ዘመን ይሆናል’ ሲል የተናገረው በሂደት ላይ ስላለ የመምጣት ጉዞ ሳይሆን ከመጣ በኋላ መኖሩን ወይም መገኘቱን ለማመልከት ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ ያነፃፀረው የኖህን መምጣት ከጌታችን መምጣት ጋር እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ኢየሱስ ያነፃፀረው ኖህ ‘ከጥፋት ውኃ በፊት’ በነበሩት ሕዝቦች መካከል የተገኘበትን ዘመንና ይህ [ያለንበት] ዘመን የሚፈጸምበት የጌታ [የይሖዋ] የመከራ ቀን ‘እሳት ከመምጣቱ በፊት’ ክርስቶስ በዓለም ውስጥ በዳግም ምፅዓት የሚገኝበትን ጊዜ ነው።”—ማቴዎስ 24:37
3 ስለዚህ በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች የክርስቶስ መገኘት (ፓሩሲያ) በማይታይ ሁኔታ የሚከናወን መሆኑን በትክክል ተረድተው ነበር። በተጨማሪም የአሕዛብ ዘመን በ1914 የበልግ ወራት እንደሚፈጸም ተረድተው ነበር። ቆየት ብለውም መንፈሳዊው ብርሃን እየጨመረ ሲሄድ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚሁ ዓመት ማለትም በ1914 በሰማይ የመንግሥቱ ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ እንደተቀመጠ ተረድተዋል።—ምሳሌ 4:18፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ሉቃስ 21:24፤ ራእይ 11:15
“የጌታችን መገኘት”
4. ‘የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት [መገኘት አዓት] ምን ያመለክታል?
4 እንግዲያው ‘የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ በዘመናችን ምን ትርጉም አለው? (1 ተሰሎንቄ 5:23) አንድ ምሑር “መገኘት” ወይም ፓሩሲያ የሚለው ቃል “ትልቅ ሥልጣንና ማዕረግ ያለው ሰው [በተለይም] ነገሥታትና ንጉሠ ነገሥታት በአንድ ክፍለ ግዛት የሚያደርጉትን ጉብኝት የሚያመለክት ቃል ሆኗል” ብለዋል። ስለዚህ ይህ ቃል የሚያመለክተው ኢየሱስ በሰማይ መንገሥ ከጀመረበት ከ1914 ጀምሮ ያለውን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ መገኘት ነው። ‘በጠላቶቹ መካከል እንዲገዛ’ የተሰጠውን ትንቢታዊ ትዕዛዝ ለመፈጸምና በንጉሥነት ለማስተዳደር በማይታይ ሁኔታ ተገኝቷል ማለት ነው። (መዝሙር 110:2) በምድር ላይ የሚኖሩ የሰው ልጆች የማይታየው የክርስቶስ ንጉሣዊ መገኘት ያስከተላቸውን ውጤቶች መመልከት ከጀመሩ 79 ዓመታት አልፈዋል።
5. በዚህ መጽሔት ላይ በሰፈሩት ሦስት ርዕሰ ትምህርቶች ውስጥ ውይይት የሚደረግባቸው በፓሩሲያው ጊዜ የሚፈጸሙ ምን ሁኔታዎች ናቸው?
5 በዚህ ርዕስ በ3 ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች አማካኝነት በዚህ ዘመን ውስጥ የኢየሱስን መንግሥታዊ ክንውኖች በተመለከተ ጉልህ ማስረጃዎችን በመመርመር ደግመን እንመለከታለን። በመጀመሪያ እስካሁን የተፈጸሙትን ወይም በመፈጸም ላይ የሚገኙትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ትንቢቶች እንመለከታለን። ሁለተኛ ኢየሱስ በዚህ በንጉሣዊ መገኘቱ ዘመን የሚጠቀምበት ታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል በማከናወን ላይ ያለውን ታላቅ ሥራ እንገልጻለን። (ማቴዎስ 24:45-47) ሦስተኛው ርዕሰ ትምህርት የታላቁን ፍጻሜ ማለትም የ“ታላቁን መከራ” ጊዜ ይገልጽልናል። ያ ጊዜ ኢየሱስ ታላቅ ፈራጅ ሆኖ ዓመፀኞችን ለማጥፋትና ጻድቃንን ለማዳን የሚመጣበት ጊዜ ነው። (ማቴዎስ 24:21, 29-31) ይህ ጥፋት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጥበት ጊዜ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፣ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ” ይመልሳል ሲል የገለጸው ይህን የጥፋት ጊዜ ነው።—2 ተሰሎንቄ 1:7, 8
ምልክቱ
6. በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ ምን ብዙ ዘርፎችን ያጠቃለለ ምልክት ተገልጿል?
6 ከአሥራ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ብርሃን አብሪ የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ ፊት በመንግሥት ሥልጣን መገኘቱን የሚያሳይ ምልክት ወይም ማስረጃ እንዲሰጣቸው ጠይቀውት ነበር። በማቴዎስ ወንጌል 24ኛና 25ኛ ምዕራፎች ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የኢየሱስ መልስ በአሁኑ ጊዜ በመላው ምድር ላይ እየተፈጸመ ያለውን ብዙ ገጽታዎችን አጣምሮ የያዘ ምልክት ሰጥቷል። ኢየሱስ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፣ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው” በማለት አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 24:4-6
7. ከ1914 ወዲህ ሲፈጸሙ ያየናቸው የትኞቹ የምልክቱ ዘርፎች ናቸው?
7 በተጨማሪም ኢየሱስ ከዚያ ቀደም ተወዳዳሪ ያልነበራቸው ጦርነቶች እንደሚደረጉ ተንብዮአል። የትንቢቱ ፍጻሜ የሆኑ ሁለት ጦርነቶች የዓለም ጦርነት የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። አንደኛው የተደረገው ከ1914 እስከ 1918 ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከ1939 እስከ 1945 ነው። ኢየሱስ በየቦታው ረሀብና የምድር መናወጥ ይሆናል ብሏል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸዋል። በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የዘመናችን ብርሃን አብሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምስክሮች ባለፉት ስምንት አሥርተ ዓመታት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” በሚሰብኩበት ጊዜ ብዙ ስደት ደርሶባቸዋል። (ማቴዎስ 24:7-14) እያንዳንዱ የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ የምልክቱ ክፍል የሆነው ስደት እየደረሰባቸው እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ጨምሮ ይዟል።።
8, 9. (ሀ) የኢየሱስ ንጉሣዊ መገኘት ምንን ያጠቃልላል? (ለ) ኢየሱስ ሐሰተኛ ክርስቶሶችን በሚመለከት የሰጠው ትንቢት እርሱ ስለሚገኝበት ቦታና ሁኔታ ምን ያመለክታል?
8 የኢየሱስ ንግሥና መላዋን ምድር የሚያጠቃልል ስለሆነ እውነተኛ አምልኮ በሁሉም አህጉራት እየተስፋፋ ነው። ንጉሣዊ መገኘቱ (ፓሩሲያ) ምድር አቀፍ ምርመራ የሚካሄድበት ጊዜ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:12) ይሁን እንጂ ኢየሱስን አግኝቶ ምክር መጠየቅ የሚቻልበት ዋና ከተማ ወይም ማዕከል ይኖራልን? ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ የእርሱ መገኘት በሚጠበቅበት ጊዜ ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደሚነሱ ተንብዮአል። እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀ፦ “እንግዲህ እነሆ፣ [ክርስቶስ] በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፣ አትውጡ፤ እነሆ፣ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፣ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፣ የሰው ልጅ መገኘት [ፓሩሲያ] እንዲሁ ይሆናልና።”—ማቴዎስ 24:24, 26, 27 አዓት
9 በምድር ላይ ከሚኖር ከማንኛውም ሰው በተሻለ ሁኔታ “የሰው ልጅ” ማለትም ኢየሱስ በመገኘቱ ጊዜ እንዴትና የት ቦታ ሊገኝ እንደሚችል ያውቃል። እዚህ ወይም እዚያ ወይም በማንኛውም የምድር አካባቢ አይቀመጥም። መሲሑን የሚፈልጉ ሰዎች ከመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ዓይን ተሰውረው ከእርሱ ጋር እንዲመካከሩና ተከታዮቹም በእርሱ መሪነት ሠልጥነው ፖለቲካዊ ግልበጣ በማድረግ መሲሐዊ የዓለም ገዥ እንዲያደርጉት በሰዋራ ቦታ ወይም “በምድረ በዳ” አይገለጥም። የሚኖርበትን ቦታ የሚያውቁት ጥቂት ምርጥ ሰዎች ብቻ ሆነው ሳይታይና ሳይታወቅ ከተባባሪዎቹ ጋር የምሥጢር ሴራና ዕቅድ በማውጣት የዓለምን መንግሥታት ገልብጦ ራሱን በመሲሕነት ለመሾም እንዲችል ራሱን “በእልፍኝ” ውስጥ አይደብቅም። በፍጹም እንዲህ አያደርግም!
10. የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መብረቆች በመላው ምድር ላይ ብርሃናቸው የታየው እንዴት ነው?
10 እንዲያውም ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መምጣቱን ወይም ንጉሣዊ መገኘቱን ስለ መጀመሩ የሚደበቅ ምንም ነገር አይኖርም። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተነበየው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንደ መብረቅ በመላው ምድር ላይ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ማብራታቸውን ቀጥለዋል። በእርግጥም የይሖዋ ምስክሮች ዘመናዊ ብርሃን አብሪዎች በመሆን ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ [የይሖዋ] መድኃኒት ይመጣ ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን ሆነዋል።—ኢሳይያስ 49:6
የመላእክት ሥራ
11. (ሀ) የመላእክት ሠራዊት የመንግሥቱ ብርሃን እንዲበራ ለማድረግ ያገለገሉት በምን መንገዶች ነው? (ለ) የስንዴው ክፍል አባሎች የተሰባሰቡት መቼና ወደየትኛው ቡድን ነበር?
11 ከኢየሱስ መገኘት ጋር ዝምድና ያላቸው ሌሎች ጥቅሶች እርሱ በመላእክት ሠራዊት እንደሚታጀብ ወይም ‘መላእክቱን እንደሚልክ’ ይናገራሉ። (ማቴዎስ 16:27፤ 24:31) ኢየሱስ ስለ ስንዴና ስለ እንክርዳድ በተናገረው ምሳሌ ላይ “እርሻው ዓለም”፣ ‘መከሩም የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ፣ አጫጆችም መላእክት’ እንደሆኑ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት በመንግሥታዊ ሥልጣኑና ክብሩ በሚገኝበት ጊዜ ለምድራዊ ተልእኮ የሚጠቀመው መላእክትን በመላክ ብቻ ይሆናል ማለት አይደለም። ከ1919 ጀምሮ መላእክት በኢየሱስ መሪነት በምድር ላይ ይኖሩ የነበሩትን በመንፈስ የተወለዱ ቅቡዓን የስንዴ ክፍል አባሎች የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ካስከተለባቸው መበታተን አሰባሰቧቸውና እነርሱም በንጉሡ ስም ለሚጠብቃቸው ተጨማሪ ሥራ ተዘጋጁ። (ማቴዎስ 13:38-43) በ1920ዎቹ ዓመታት ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ቀደም ሲል ከተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት ጎን ተሰልፈው በአምላክ መንፈስ ተቀብተዋል። እነዚህም ቅቡዓን ከእነርሱ በፊት ከነበሩት ቀሪዎች ጋር ተቀላቅለዋል። እነዚህ አንድ ላይ ተጠቃለው የዘመናችን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ክፍል ሆኑ።
12. መላእክት የተሳተፉት በምን የማጥራት ሥራ ነው? ይህስ በምድር ላይ ምን ውጤት አስከተለ?
12 በ1914 ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ በነበረው የኢየሱስ መገኘት ጊዜ መላእክት በነገሮች ተሳታፊ ለመሆናቸው ሌላው ምሳሌ በራእይ 12:7-9 ላይ ተገልጿል፦ “ሚካኤልና [ኢየሱስ ክርስቶስና] መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” በዚህ መንገድ ሰማያት ጸዱ። የይሖዋ ስም እንዲቀደስና ገና ሙሉ በሙሉ መጽዳት የሚኖርበት የመንግሥቲቱ ምድራዊ ግዛት ቀረ። “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” የሚለው መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በዚህ በ1993 ዓመትም ይሠራል።—ራእይ 12:12
ሰማያዊ ትንሣኤ
13, 14. (ሀ) ቅዱሳን ጽሑፎች ከ1918 ጀምሮ ስለተፈጸሙት ነገሮች ምን ያመለክታሉ? (ለ) ጳውሎስና ዮሐንስ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ቅቡዓን ቀሪዎች በሚመለከት ምን የገለጹት ነገር አለ?
13 በክርስቶስ መገኘት ዘመን የተጀመረው ሌላው አስደናቂ ክንውን ሰማያዊው ትንሣኤ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመቃብር ውስጥ ለረጅም ዘመናት አንቀላፍተው የቆዩት ቅቡዓን ሕያው ለመሆንና በመንፈሳዊው ዓለም ከክርስቶስ ጋር ለመሆን የመጀመሪያዎቹ እንደሚሆኑ አመልክቷል። ይህም ከ1918 ጀምሮ መፈጸም ሳይጀምር እንዳልቀረ ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻል ባለፉት ዓመታት በቂ ማስረጃዎች ቀርበዋል። ጳውሎስ “ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፣ በኋላም በመምጣቱ [በመገኘቱ አዓት (በፓሩሲያው)] ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:22, 23) ቅቡዓኑ በክርስቶስ መገኘት ጊዜ እንደሚነሱ በ1 ተሰሎንቄ 4:15-17 ላይ ተረጋግጧል፦ “በጌታ [በይሖዋ አዓት] ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ [እስኪገኝ አዓት] [እስከ ፓሩሲያ] ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ . . . በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፣ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን።” በመጨረሻው ይህን አስደናቂ ሽልማት የሚቀበሉ የክርስቶስ ንብረት የሆኑ ቅቡዓን ቁጥራቸው 144,000 ነው።—ራእይ 14:1
14 ጳውሎስ እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩት ቅቡዓን ቀሪዎች ጥንት ከሞቱት ሰማዕታት፣ ደቀ መዛሙርትና ሐዋርያት ቀድመው ወደ መንግሥቱ አይገቡም። ሐዋርያው ዮሐንስ በአሁኑ ጊዜ ስለሚሞቱት ቅቡዓን እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፣ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፣ ሥራቸውም ይከተላቸዋል።” ይኸውም ከሙታን ተነስተው በሕይወት በሚኖሩበት ሁኔታ ሥራቸው ይከተላቸዋል። (ራእይ 14:13) ጳውሎስም በተጨማሪ እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ” (1 ቆሮንቶስ 15:51, 52) እንዴት ያለ አስደናቂ ተዓምር ነው!
15, 16. (ሀ) ኢየሱስ በሉቃስ 19:11-15 ላይ ምን ምሳሌ ሰጥቷል? ምሳሌውን የሰጠው በምን ምክንያት ነበር? (ለ) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ አንድ ጊዜ ለተከታዮቹ ስለ አምላክ መንግሥት ሲሰብክ የተሳሳተ አስተሳሰባቸውን ለማረም በአንድ ምሳሌ ተጠቅሟል። ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ። ስለዚህም እንዲህ አላቸው፦ አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለስ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና፦ እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው። . . . መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፣ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ።”—ሉቃስ 19:11-15
16 መንግሥትን ወደሚቀበልበት “ሩቅ አገር” ማለትም ወደ ሰማይ የሄደው ያ “መኰንን” ኢየሱስ ነው። ይህንንም መንግሥት በ1914 ተቀብሏል። ወዲያውም ንጉሥ ሆኖ ቅቡዓኑ ቀደም ሲል በአደራነት የተሰጧቸውን የመንግሥት ጉዳዮች ለማከናወን ምን እንዳደረጉ ለማወቅ ምርመራ አካሄደ። በቁጥር በጣም አናሳ የሆኑ ታማኞች ተመርጠው “መልካም፣ አንተ በጎ ባሪያ፣ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ” የሚል የምስጋና ቃል ተቀብለዋል። (ሉቃስ 19:17) ይህ የክርስቶስ መገኘት ዘመን “ለበጎው ባሪያ” በአደራ ከተሰጠው ሥልጣን መካከል አምላክ በክፉዎች ላይ የሚያመጣውን ፍርድ ማወጅንና ይህን ሥራ በበላይነት መቆጣጠርን ጨምሮ በጣም የተፋፋመ የመንግሥት ስብከት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ጊዜ ሆኖአል።
ዓለም አቀፍ ስብከት
17. ፓሩሲያው ምን ደስታ የተገኘበት ጊዜ ሆኗል?
17 በዚህ በፓሩሲያ ዘመን የሚፈጸም ምን ሌላ ነገር ይኖራል? በስብከቱ እና አዳዲስ ሰዎች ከመጪው ታላቅ መከራ ተርፈው ለሚያገኙት መዳን እንዲዘጋጁ በመርዳቱ ሥራ ታላቅ ደስታ የሚገኝበት ጊዜ ይሆናል። ቅቡዓኑን በሥራ የሚያግዙአቸው እነዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” “የማመስገኛ መልእክት” ይሆናሉ። (ራእይ 7:9፤ 2 ቆሮንቶስ 3:1-3) ጳውሎስ “ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ [በፓሩሲያው] እናንተ አይደላችሁምን?” ባለ ጊዜ ይህ የመከር ሥራ የሚያመጣውን ደስታ ገልጾታል።—1 ተሰሎንቄ 2:19
ንጹሖችና ያለነቀፋ ሆናችሁ ኑሩ
18. (ሀ) የትኛው የጳውሎስ ጸሎት ከፓሩሲያው ጋር ግንኙነት አለው? (ለ) በዚህ ጊዜ ሁላችንም ማሳየት ያለብን ምን ዓይነት መንፈስ ነው? በምንስ መንገዶች?
18 በተጨማሪም ጳውሎስ “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” በማለት በዚህ የክርስቶስ መገኘት ወቅት በሕይወት የሚኖሩት ሰዎች እንዲቀደሱ ጸልዮአል። (1 ተሰሎንቄ 5:23) አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ የቅቡዓን ቀሪዎች አባሎችም ሆንን እጅግ ብዙ ከሆኑት ሌሎች በጎች ክፍል በዚህ ልዩ በሆነው ወቅት ንጹሖችና አለነቀፋ ሆነን እንድንኖር የትብብር መንፈስ በታማኝነት እርስ በራሳችን እንድንተሳሰር ያደርገናል። በተመሳሳይም ታጋሾች መሆን ያስፈልገናል። ያዕቆብ “እንግዲህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ [እስከ ፓሩሲያ] ድረስ ታገሡ። . . . ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት [ፓሩሲያ] ቀርቦአልና” ብሏል።—ያዕቆብ 5:7, 8
19. ጴጥሮስ ፓሩሲያውን በሚመለከት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? እኛስ ለዚህ ማስጠንቀቂያ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት መሆን ይኖርበታል?
19 ሐዋርያው ጴጥሮስም በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛ የተናገረው ቃል አለ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከሞሉት ዘባቾች እንድንጠነቀቅ ነግሮናል። ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም፦ የመምጣቱ [የፓሩሲያው አዓት] የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) በክርስቶስ መገኘት ጊዜ ዘባቾች በጣም ቢበዙም የይሖዋ ሕዝቦች የዓለም ብርሃን ሆነው ማብራታቸውን በመቀጠል ለብዙዎች መዳን ምክንያት ይሆናሉ።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የይሖዋ ሕዝቦች የፓሩሲያ ሐሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበራላቸው የሄደው እንዴት ነው?
◻ ማቴዎስ 24:4-8 የተፈጸመውና አሁንም እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
◻ መላእክት በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ክርስቶስ ጋር በሥራ ሲተባበሩ የቆዩት እንዴት ነው?
◻ ከፓሩሲያው ጋር ምን አስደናቂ ተአምር ተከትሎት የመጣ ይመስላል?
◻ በዚህ ጊዜ የተገኘው ደስታ ምንድን ነው? በዚህ ደስታስ እነማን ይካፈላሉ?