መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ይሆናሉ ብሎ የተናገራቸው ነገሮች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው?
በዛሬው ጊዜ በጣም ብዙ የታሪክ መጻሕፍት አሉ። ከዚህ በፊት ስለተፈጸሙት ነገሮች የሚናገሩት እነዚህ የታሪክ ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ በጣም አስደናቂ ናቸው። እነዚህን መጻሕፍት በምናነባቸው ጊዜ ራሳችንን ጥንት በተፈጸሙት ሁኔታዎች ውስጥ እንዳለን አድርገን ልንመለከት እንችል ይሆናል። ጸጥ ካሉት የመጽሐፉ ገጾች ውስጥ ሰዎች፣ ቦታዎችና ድርጊቶች በድንገት ብቅ የሚሉ ሲመስለን የምናነበው ነገር ስሜታችንን ይነሽጠዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስሜት የሚቀሰቅሱ ታሪካዊ ዘገባዎችን የያዘ እንደዚህ ያለ መጽሐፍ ነው። በውስጡ ከተገለጹትም እንደ አብርሃም፣ ሚስቱ ሣራ፣ እንደ ንጉሥ ዳዊት፣ ንግሥት አስቴርና እንደ ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሳሰሉት ወንዶችና ሴቶች ጋር ልንተዋወቅ እንችላለን። አብረናቸው ልንጓዝ፣ የተናገሩትን ልንሰማና ያዩትን ልናይ እንችላለን። ነገር ግን ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ የታሪክ መጽሐፍ ብቻ አድርገው አይመለከቱትም። መጽሐፍ ቅዱስ ገና ያልተፈጸመ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። እንደዚህ ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ይፈጸማሉ ብሎ በሚናገርላቸው ነገሮች ወይም ትንቢቶች የተሞላ ስለሆነ ነው።
ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምን ያህል ተአማኒነት ያላቸው ናቸው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከዚህ በፊት በተከሰቱት ሁኔታዎች ላይ ከተፈጸሙ ወደፊት ስለሚሆኑት ሁኔታዎች የሚናገሩት እንደዚህ ዓይነቶቹ ትንቢቶችም እውን ይሆናሉ ብለን መጠበቅ አይገባንም? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስተማማኝ እንደሆኑ ለማወቅ እስቲ አሁን አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመርምር።
እስራኤልና አሦር በዓለም መድረክ ላይ
ከ778 ከዘአበ አካባቢ ጀምሮ ትንቢት መናገር የጀመረው የአምላክ ነቢይ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “የኤፍሬም [የእስራኤል] ሰካሮች ትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፤ በወፍራሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይበላታል።” (ኢሳይያስ 28:3, 4) በትንቢት እንደተነገረውም ከዘአበ በስምንተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የእስራኤል ዋና ከተማ ሰማርያ በአሦር ወታደራዊ ኃይሎች ተቀጥፋ ለመበላት እንደተዘጋጀች የበሰለች በለስ ሆና ነበር። በ740 ከዘአበ ሰማርያ በአሦራውያን ድል ስትመታ የተፈጸመው ሁኔታ ይህ ነበር። — 2 ነገ ሥት 17:6, 13, 18
አሦር በተራዋ በታሪክ መድረክ ላይ ገናና የምትሆንበት ጊዜ ነበር። የአሦር ዋና ከተማ ምርኮኞችን በጭካኔ በማሠቃየት ትታወቅ የነበረችው ነነዌ ነበረች። በዚህም ምክንያት ‘የደም ከተማ’ ተብላ ትጠራ ነበር። (ናሆም 3:1) ይሖዋ አምላክ ራሱ ነነዌ እንድትጠፋ ትእዛዝ አወጣ። ለምሳሌ አምላክ በነቢዩ በናሆም አማካኝነት እንደሚከተለው አለ:- “እነሆ፣ በአንቺ ላይ ነኝ፣ . . . እንቅሽማለሁ፣ ማላገጫም አደርግሻለሁ። የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ:- ነነዌ ባድማ ሆናለች . . . ይላል።” (ናሆም 3:5–7) እንዲሁም ሶፎንያስ ስለ አሦር መጥፋትና ስለ ነነዌ ባድማ መሆን ትንቢት ተናግሯል። (ሶፎንያስ 2:13–15) በ632 ከዘአበ የባቢሎኑ ንጉሥ የናቦፖላሳርና የሜዶኑ ንጉሥ የሲአክስሬዝ ጥምር ኃይሎች በድንገት መጥተው ነነዌን በዘረፉአትና ጨርሰው ባጠፉአት ጊዜ እነዚህ ትንቢቶች ተፈጽመዋል። ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ድምጥማጧ ስለጠፋ ከ2,000 በላይ ለሚሆኑ ዓመታት የነበረችበት ቦታ እንኳን የማይታወቅ ሆነ። ቀጥሎ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ያለው የባቢሎን መንግሥት ነበር።
ባቢሎን እንደምትጠፋ አስቀድሞ ተነገረ
የባቢሎኒያ መንግሥት እንደሚገለበጥና ዋና ከተማዋ ባቢሎንም እንዴት እንደምትወድቅ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ የኤፍራጥስ ወንዝ እንደሚደርቅ ሁለት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ አስታወቀ። ወንዙ በባቢሎን መሐል ያልፍ ነበር። የወንዙ መግቢያና መውጫ በሮች የከተማዋ ዋና የመከላከያ ክፍሎች ነበሩ። ትንቢቱ ድል አድርጎ የሚይዛት ቂሮስ መሆኑን በስም በመጥቀስ ይገልጻል። ባቢሎን “በሮቿም” ለወራሪዎች ክፍት ሆነው እንደሚቀሩ ያመለክታል። (ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:7) ልክ በዚህ ትንቢት መሠረት ታላቅ በዓል በሚከበርበት ምሽት ላይ የታላቁ ቂሮስ ወታደሮች ጥቃት በሚጀምሩበት ጊዜ በኤፍራጥስ ዳርቻ ላይ ያሉት ሁለት ተካፋች በሮች ክፍት እንደሆኑ መቆየታቸውን አምላክ አረጋግጦ ነበር። ስለዚህ ያለምንም ችግር በወንዙ መውረጃ በኩል ገብተው ባቢሎንን ያዙአት።
ታሪክ ጸሐፊው ሄሮድተስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ቂሮስ . . . ከፊል ሠራዊቱን የኤፍራጥስ ወንዝ ወደ [ባቢሎን] በሚገባበት በር ላይ ሌላውን የጦር ክፍል ደግሞ በተቃራኒው በኩል ወደ ውጭ በሚፈስበት ቦታ ላይ አሠፈረ። ውኃው በጣም መጉደሉን ሲያዩ በወንዙ መውረጃ በኩል በአስቸኳይ ወደ ውስጥ እንዲገቡ በሁለቱም አቅጣጫ ላሉት ወታደሮች ትእዛዝ ሰጣቸው። . . . ወንዙን ቆረጠና አቅጣጫውን በማስለወጥ (በዚያን ጊዜ ረግረግ ወደነበረው) ወደ ሐይቁ እንዲፈስ አደረገው፤ በዚህ መንገድ የውኃውን ጥልቀት በጣም ስለቀነሰው የወንዙ መውረጃ የሚያሻግር መልካ ሆነ። ከዚያም ሆነ ተብሎ በባቢሎን እንዲቀር ተደርጎ የነበረው የፋርስ ሠራዊት በወንዙ ገባ። አሁን የውኃው ጥልቀት እስከ ጭን ግማሽ ድረስ ብቻ የሚደርስ ሆነ። ስለዚህ በወንዙ በኩል አድርገው ወደ ከተማዋ ውስጥ ገቡ። . . . ሕዝቡ በዓል አድርገው እየበሉ እየጠጡ ነበር፤ መራራው ሐቅ እስኪያነቃቸው ድረስ ከተማዋ በምትወድቅበት ጊዜ እንኳን መጨፈራቸውንና መፈንጠዛቸውን አላቆሙም ነበር።” — ሄሮድተስ — ዘ ሂስትሪስ፣ ኦብሪ ደ ሰለንኩርት እንደተረጎመው።
በዚያው ምሽት ነበር የአምላክ ነቢይ የሆነው ዳንኤል የባቢሎንን ገዢ እየመጣ ስላለው ጥፋት ያስጠነቀቀው። (ዳንኤል ምዕራፍ 5) ከዚያ ወዲህ አነስተኛ ኃይል የነበራት ባቢሎን ለተወሰኑ መቶ ዘመናት ኖራለች። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የመጀመሪያ ደብዳቤውን የጻፈው እዚያ ሆኖ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:13) ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት “እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው . . . ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች። ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም” ሲል ገልጾ ነበር። በተጨማሪም እግዚአብሔር “ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፣ ዘርንና ትውልድንም እቆርጣለሁ” ብሎ ነበር። (ኢሳይያስ 13:19–22፤ 14:22) በትንቢት እንደተነገረው ባቢሎን በመጨረሻ የፍርስራሽ ክምር ሆነች። እንደምንም ብሎ ያችን ጥንታዊ ከተማ መልሶ መገንባት ቱሪስቶችን ሊስብ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በፊት የነበራትን “ዘርንና ትውልድን” መልሶ ማምጣት የማይቻል ነው።
ባቢሎን በወደቀችበት ጊዜ በዚያ የነበረው የይሖዋ ነቢይ ዳንኤል ድል አድራጊዎቹን ሜዶናውያንንና ፋርሳውያንን በተመለከተ አንድ ራእይ ተመልክቶ ነበር። ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግና በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል ተመልክቷል። ፍየሉም በአውራው በግ ላይ ጥቃት አደረሰበት፤ ወደ ምድርም ጣለው ሁለቱንም ቀንዶቹን ሰበራቸው። ከዚያም የፍየሉ ታላቅ ቀንድ ተሰበረና በቦታው አራት ቀንዶች ወጡ። (ዳንኤል 8:1–8) መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢት እንደተናገረውና ታሪክም እንዳረጋገጠው ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራው በግ ሜዶ ፋርስን የሚያመለክት ነበር። አውራው ፍየል ደግሞ ግሪክን ያመለክታል። ‘ታላቁ ቀንዱስ’ ምን ያመለክታል? ይህም ቢሆን ታላቁ እስክንድርን የሚያመለክት እንደሆነ ተረጋግጧል። ይህ ምሳሌያዊ ታላቅ ቀንድ በሚሰበርበት ጊዜ አራት ምሳሌያዊ ቀንዶች (ወይም መንግሥታት) በቦታው ተተኩ። ትንቢቱ እውነት ሆነ። እስክንድር ከሞተ በኋላ አራት ጄነራሎቹ የራሳቸውን ሥልጣን አቋቋሙ። ፒቶለሚ ላገስ በግብፅና በፍልስጤም፤ ሰልዩከስ ኒካቶር በመስጴጦምያና በሦርያ፤ ካሳንደር በመቄዶንያና በግሪክ እንዲሁም ሊሲማከስ በትሬስና በትንሿ እስያ ግዛታቸውን አቋቋሙ። — ዳንኤል 8:20–22
ወደፊት ብሩህ ጊዜ ስለመምጣቱ የተነገሩ ትንቢቶች
ስለ ባቢሎን መጥፋትና ስለ ሜዶ ፋርስ መገልበጥ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት እውን ከሆኑት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትንቢቶች መካከል ጥቂቶቹ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቀባው መሲህ አማካኝነት ስለሚመጣው ብሩህ የወደፊት ጊዜ የሚናገሩ ትንቢቶችንም ጭምር ይዟል።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉት አንዳንድ መሲሐዊ ትንቢቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደተፈጸሙ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል አስቀድሞ በነቢዩ ሚክያስ እንደተነገረው ኢየሱስ በቤተ ልሔም እንደተወለደ የወንጌል ጸሐፊዎች አመልክተዋል። (ሚክያስ 5:2፤ ሉቃስ 2:4–11፤ ዮሐንስ 7:42) ከኢየሱስ መወለድ በኋላ ሕፃናት ተገድለዋል። ይህም የኤርምያስ ትንቢት ፍጻሜ ነበር። (ኤርምያስ 31:15፤ ማቴዎስ 2:16–18) ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የዘካርያስ (9:9) ቃላት ፍጻሜአቸውን አግኝተዋል። (ዮሐንስ 12:12–15) እንዲሁም ከኢየሱስ ስቅለት በኋላ ወታደሮቹ ልብሱን በተከፋፈሉበት ጊዜ “ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፣ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ተፈጽመዋል። — መዝሙር 22:18
ሌሎች መሲሐዊ ትንቢቶች የሰው ዘር የሚጠብቀውን አስደሳች ጊዜ ይጠቁማሉ። ዳንኤል “የሰው ልጅ የሚመስል” “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ‘በዘመናት ከሸመገለው’ ከይሖዋ ሲቀበል በራእይ ተመልክቷል። (ዳንኤል 7:13, 14) የሰማያዊውን ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስን መሲሐዊ አገዛዝ በተመለከተ ኢሳይያስ እንደሚከተለው ብሏል:- “ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ቅንዓት ይህን ያደርጋል።” — ኢሳይያስ 9:6, 7
የመሲሑ የጽድቅ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ መግዛት ከመጀመሩ በፊት አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ቁምነገር መፈጸም አለበት። ይህም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት ተነግሯል። መሲሐዊውን ንጉሥ በተመለከተ መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ዘምሯል:- “ኃያል ሆይ፣ . . . ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም።” (መዝሙር 45:3, 4) ቅዱሳን ጽሑፎች የእኛን ዘመን ሲያመለክቱ የሚከተለውን ጭምር አስቀድመው ተናግረዋል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” — ዳንኤል 2:44
መዝሙር 72 በመሲሐዊው አገዛዝ ሥር ስለሚኖሩት ሁኔታዎች አስተማማኝ ጭላንጭል ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው” ይላል። (ቁጥር 7) በዚያን ጊዜ ጭቆና ወይም ብጥብና ውጊያ አይኖርም። (ቁጥር 14) “በምድር ላይ በብዛት እህል ይኖራል፤ በተራሮችም ራስ ላይ ይትረፈረፋል።” ስለዚህ ማንም አይራብም። (ቁጥር 16 አዓት) እስቲ ገምተው! የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም በሚተካበት ጊዜ እነዚህንና ሌሎች በረከቶችን አግኝተህ ደስ እያለህ ልትኖር ትችላለህ። — ሉቃስ 23:43፤ 2 ጴጥሮስ 3:11–13፤ ራእይ 21:1–5
እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ልትመረምራቸው የሚገቡ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። ታዲያ የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት ለምን የይሖዋ ምሥክሮችን አትጠይቃቸውም? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መመርመርህ በጊዜ ሂደት ውስጥ የት ላይ እንደደረስን ለማወቅ ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም እንዲህ ማድረግህ ለይሖዋ አምላክና እሱን የሚያፈቅሩና የሚታዘዙ ሁሉ ዘላለማዊ በረከት እንዲያገኙ ላደረገው ግሩም ዝግጅት በልብህ ውስጥ ጥልቅ አድናቆት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ አውራ ፍየልና በግ የሚናገረውን የዳንኤልን ራእይ ትርጉም ታውቀዋለህን?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገነት በሆነች ምድር ላይ ስለሚኖረው አስደሳች ሕይወት የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ በዚያ ተገኝተህ ትደሰታለህን?