የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት መመርመር ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? አንዳንዶች አምላክ ራሱን ለሰዎች የገለጠበት መጽሐፍ ነው ብለው በጥብቅ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ እንደማንኛውም ተራ መጽሐፍ ነው ብለው ያምናሉ። ይህ ነው ብሎ መናገር ያቃታቸው ሌሎችም አሉ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አመጣጥ የምትጠራጠር ከሆነ መጽሐፉን መርምረህ ጥርጣሬህን እንድታስወግድ የሚያስገድዱህ ምክንያቶች አሉ።
እስከ 18ኛው መቶ ዘመን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝበ ክርስትና አገሮች ውስጥ እንደ አምላክ ቃል ተደርጐ ሲከበር ቆይቷል። ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ግን ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ምሁራን፣ ሳይንቲስቶች፣ ቲኦሎጂያኖችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንኳ ሳይቀሩ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ስለመሆኑ ያላቸውን ጥርጣሬ በይፋ መግለጽ ጀመሩ።
ከዚህም የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስን መተቸት በጣም በመስፋፋቱ መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ምን እንደያዘ እንኳ የማያውቁ ብዙ ሰዎች የየራሳቸውን ፍርድ ይሰጡ ጀመር። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ምትክ በሰዎች ፍልስፍና ይተማመናሉ። ይህም ሆኖ ዘመናዊ ፍልስፍና ከአደጋ ነፃ የሆነ ወይም ደስተኛ ዓለም አላመጣም። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች ብንከተል ደስታና የተሳካ ሁኔታ የሚያስገኝልን እንደሆነና እንዳልሆነ መርምረን እንድንረዳ የሚያደርገን አንዱ ጥሩ ምክንያት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት እንድንመረምር የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ለሰው ልጆች የያዘው ግሩም ተስፋ ነው። ለምሳሌ መዝሙር 37:29 እንዲህ ይላል:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (ራእይ 21:3–5) እንደነዚህ ያሉት ተስፋዎች በአንተ ላይ ምን ስሜት ያሳድሩብሃል? በእርግጥም እነዚህ ተስፋዎች መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚችል መሆኑንና አለመሆኑን እንድትመረምር የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች ናቸው።
ይህ አሁን የምታነበው መጽሔት መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መሆኑን ሁልጊዜ ይደግፋል፤ ብዙ ጊዜም ለትክክለኛነቱ ማረጋገጫዎችን አቅርቧል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ሊመረመር የሚችልባቸው ብዙ መስኮች አሉ። በየጊዜው የወጡት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዱሃል:- ስለ ጥንት ታሪኮች የታወቁት ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማሉን? ትንቢቶቹ ትክክል ናቸውን? ምክሮቹ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ወይስ ዘመናዊ ምሁራንና ፈላስፎች መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜው ያለፈበት መሆኑን አረጋግጠዋል?
የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ከምንመረምርበት መስክ አንዱ መልክዓ ምድራዊ ገለፃ ነው። አረመኔያዊ አፈታሪኮች ብዙውን ጊዜ ከመልክዓ ምድራዊ ማስረጃዎች ጋር ይጋጫሉ። ለምሳሌ ያህል የሙታን ዓለም ተብሎ ወደሚጠራ ስፍራ ስለተደረገ የጉዞ ታሪክ ብዙዎቹ የጥንት ሰዎች ተናግረዋል። የጥንት ግሪካውያንን በተመለከተ ኤ ጋይድ ቱ ዘ ጎድስ የተባለው መጽሐፍ ሲያብራራ:- “መሬት ውቅያኖስ ተብሎ በሚጠራ ሰፊ የውኃ አካል እንደተከበበች ጠፍጣፋ ነገር ተደርጋ ትታይ ነበር። ከዚያ ባሻገር ፍሬ የማያፈሩ ተክሎች ያሉበትና ጨለማ የዋጠው ጠፍ መሬት ያለበት ሌላ ዓለም አለ” ይላል። ይህ አፈታሪክ መሆኑ ሲረጋገጥ፣ አረመኔዎቹ ፈላስፎች የወዲያኛው ዓለም ብለው የሚጠሩትን ቦታ እንደገና ለማመልከት ሞከሩ። “ተስማሚ ቦታ ተገኘለት፤ እርሱም ከመሬት በታች ነው። ከዚህም ቦታ ጋር የሚያገናኙ ብዙ ዋሻዎች አሉ” በማለት ሪቻርድ ካርሊየን የተባሉት ጸሐፊ ገለጹ። ዛሬ ይህም ቢሆን አፈ ታሪክ እንደሆነ እናውቃለን። ከመሬት በታች ያለ ዓለምም ሆነ ወደዚያ የሚያደርስ ዋሻ የለም።
መጽሐፍ ቅዱስ መሬት ጠፍጣፋ ነች የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ስላልያዘ ከጥንት ሰዎች አፈ ታሪክ የተለየ ነው። ከዚህ ይልቅ መሬት ክብ ሆና ምንም ነገር ሳይደግፋት እንደተንጠለጠለች የሚናገረውን ሳይንሳዊ እውነት ይዟል። (ኢዮብ 26:7፤ ኢሳይያስ 40:22) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሌሎች መልክዓ ምድራዊ መግለጫዎችስ ምን ሊባል ይቻላል? እነዚህ ታሪኮች በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ወይስ ዘመናዊዋን ግብጽ፣ የሲናን ልሳነ ምድርና ዘመናዊዋን እስራኤል በመጐብኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በትክክል አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል።” — ኢሳይያስ 40:22
“ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል።” — ኢዮብ 26:7