የመጽሐፍ ቅዱስ መልክዓ ምድራዊ ገለጻ ትክክለኛ ነውን?
በፍልስጥኤም ምድር ጀንበር ገና መጥለቋ ነው። ጊዜው 1799 ሲሆን ከሞቃታማው የቀኑ ጉዞ በኋላ የፈረንሳዩ ጦር አንድ ቦታ ላይ ሰፍሯል፤ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ አዛዥ ናፖሊዮንም በድንኳኑ ውስጥ አረፍ ብሏል። ከአሽከሮቹ አንዱ በሚርገበገብ የሻማ ብርሃን እየተረዳ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ከተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ጮክ ብሎ ያነብለታል።
በፍልስጥኤም ምድር ናፖሊዮን ባደረገው የጦር ዘመቻ ወቅት ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ማድረግ ልማዱ የነበረ ይመስላል። ናፖሊዮን ቀድሞ ያደረጋቸውን ነገሮች በማስታወስ በጻፈው ማስታወሻ ላይ እንዲህ ብሏል:- “በጥንቶቹ ከተማዎች ፍርስራሾች አካባቢ ስንሰፍር ማታ ማታ ከቅዱስ ጽሑፉ ጮክ ብለው ያነቡልኝ ነበር። . . . የገለጻዎቹ እውነተኝነትና ከአገሩ ጋር ያላቸው ስምምነት በጣም ያስገርማል። ብዙ መቶ ዓመታት ያለፉና ብዙ ለውጦች የተደረጉ ቢሆንም ከዚህ አገር ጋር ይስማማሉ።”
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሄዱ ተጓዦች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የጠቀሳቸው ሁኔታዎችና ዛሬ ያሉ ቦታዎች አንድ መሆናቸውን በቀላሉ ማየት ይችላሉ። የፈረንሳይ ጦር ሠራዊት ግብጽን ድል ከማድረጉ በፊት ስለዚያ ጥንታዊ አገር በውጭ አገር ዜጐች ዘንድ እምብዛም አይታወቅም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ናፖሊዮን ወደ ግብጽ የወሰዳቸው ሳይንቲስቶችና ምሁራን ስለ ግብጽ ጥንታዊ ክብርና ታላቅነት ብዙ ነገሮችን በዝርዝር ለዓለም ገለጡ። ይህም እስራኤላውያን በአንድ ወቅት ‘በከባድ ባርነት’ ሥር ወድቀው እንደነበረ የሚናገረውን ታሪክ በዓይነ ሕሊና ለመሣል ቀላል እንዲሆን አደረገው። — ዘጸአት 1:13, 14
እስራኤላውያን ከግብጽ ነፃ በወጡበት ሌሊት በራምሴ ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ ‘ምድረበዳው ዳርቻ’ ተጓዙ። (ዘጸአት 12:37፤ 13:20) ከዚህ በኋላ አምላክ “ተመልሰው” ‘በባሕር ዳር እንዲሰፍሩ’ አዘዛቸው። ይህ ያልተለመደ ጉዞ ‘እንደመቅበዝበዝ’ ተደርጐ ተተረጐመና የግብጽ ንጉሥ 600 የጦር ሠረገሎቹንና የጦር ሠራዊቱን አስከትሎ የቀድሞ ባሮቹን መልሶ ለመያዝ ገሰገሰ። — ዘጸአት 14:1–9
የእስራኤላውያን ከግብፅ መውጣት
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ እንደተናገረው የግብጻውያን ሠራዊት እስራኤላውያንን “ወደ ጠባብ ቦታ” እንዲገቡ በማድረግ “በገደላማ ቦታና በባሕሩ መካከል” አጠመዳቸው። በዛሬው ጊዜ እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ያቋረጡበት ትክክለኛ ቦታ አይታወቅም። ይሁን እንጂ የቀይ ባሕርን ሰሜናዊ ጫፍ ከሚያሳየው የተራራ ሰንሰለት ላይ ሆኖ ሁኔታውን በቀላሉ በዓይነ ሕሊና ማየት ይቻላል። በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ተራራው ጀብል አታክ ተብሎ መጠራቱ ነው፤ ትርጓሜውም “የማዳን ተራራ” ማለት ነው። በዚህ የተራራ ሰንሰለትና በቀይ ባሕር መካከል የሚገኘው ትንሽ ሜዳ እየጠበበ ሄዶ ባሕሩ ውስጥ ሊገባ ትንሽ ከቀረው የተራራ ግርጌ ጋር ይገናኛል። ከቀይ ባሕር ትይዩ ብዙ ምንጮች ያሉበት ‘አዩን ሙሳ’ ማለትም “የሙሴ የውኃ ጉድጓዶች” ተብሎ የሚጠራ አንድ ለምለም ቦታ አለ። ከእነዚህ ሁለት ቦታዎች ተነሥቶ የባሕሩ ወለል ቀስ በቀስ ጥልቀት ያለው እየሆነ ሲሄድ በሌሎች ቦታዎች ግን በድንገት ከ9 እስከ 18 ሜትር በሚያክል ጥልቀት ዝቅ ይላል።
እምነት የለሾቹ የሕዝበ ክርስትና ቲኦሎጂያንስ አምላክ ቀይ ባሕርን ከፍሎ እስራኤላውያንን በደረቅ ምድር እንዲያመልጡ ያስቻለበትን ተአምር ለማስተባበል ሙከራ አድርገው ነበር። እስራኤላውያን የተሻገሩት ከቀይ ባሕር በስተሰሜን በሚገኝ ብዙም ጥልቀት በሌለው በአንድ ረግረጋማ ቦታ ላይ ነው ይላሉ። ይህ አባባል ግን ሁኔታው የተከናወነው ፈርኦንንና ሠራዊቱን ሁሉ ሊያሰጥም እንዲያውም ሊውጥ የሚችል በቂ የውኃ መጠን ባለው የቀይ ባሕር ክፍል ላይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር አይስማማም። — ዘጸአት 14:26–31፤ መዝሙር 136:13–15፤ ዕብራውያን 11:29
የሲና ምድረበዳ
እስራኤላውያን በምድረበዳ እንደተቅበዘበዙ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በሲና ልሳነ ምድር ውስጥ የሚገኘውን መጥፎ ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። (ዘዳግም 8:15) ታዲያ ቦታው ጠቅላላው ሕዝብ የአምላክን ሕግ ለመቀበል በሲና ተራራ ግርጌ እንዲሰበሰብና ከዚያም “ራቅ” ብሎ እንዲቆም የሚያስችለው ነበርን? (ዘጸአት 19:1, 2፤ 20:18) ሦስት ሚልዮን የሚያክል ቁጥር ነበራቸው ተብለው የሚገመቱትን ሰዎች ለማስተናገድ የሚችል ሰፊ ቦታ አለውን?
አርተር ስታንሊ የተባሉ የ19ኛው መቶ ዘመን ተጓዥና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሲና ተራራን አካባቢ ሲጐበኙ ከሚመሩት ቡድን ጋር ሆነው ራስ ሰፍሰፋ የተባለውን ተራራ ሲወጡ የተመለከቱትን እንዲህ በማለት ገለጹ:- “ይህን ቦታ ያየና ሁኔታውን ያስረዳ ማንም ሰው የሚሰማውን ዓይነት ስሜት ወዲያውኑ ተሰምቶናል። . . . አንድ ትልቅ ቢጫ ሜዳ እስከ ተራራው ጥግ ተዘርግቷል። . . . በዚህ አካባቢ ተራራውና ሜዳው ያለምንም መገናኛ መጋጠማቸው ለትረካው እውነተኝነት ትልቅ ማስረጃ ሲሆን ይህ ሁኔታ በጥንታዊው ሲናና በአካባቢው መገኘቱ በጣም አስደናቂ ነው።”
የተስፋይቱ ምድር
እስራኤላውያን በምድረበዳ በተቅበዘበዙበት በ40ኛው ዓመት ላይ ሙሴ ስለሚገቡባት ምድር የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቶ ነበር:- “አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካም ምድር፣ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር” ያገባሃል። — ዘዳግም 8:7
የዚህ ተስፋ ትክክለኛነት ወዲያው የታየው ወንዶች፣ ሴቶች፣ ሕፃናትና መጻተኞች በቂ ውኃ በነበረው በሴኬም ሸለቆ ማለትም በጌባልና በገሪዛን ተራራ መካከል በተሰበሰቡበት ጊዜ ነበር። በገሪዛን ተራራ ስር ስድስት ነገዶች ቆሙ። ሌሎቹ ስድስት ነገዶች ደግሞ በሸለቆው ሌላ ወገን በጌባል ተራራ ሥር ቆመው የይሖዋን ሕግ ከታዘዙ ሕዝቡ ስለሚያገኘው መለኮታዊ በረከት፣ የአምላክን ሕግ በሥራ ላይ ካላዋሉ ደግሞ ስለሚደርስባቸው ርግማን ለመስማት ተሰብስበው ነበር። (ኢያሱ 8:33–35) በዚህ ጠባብ ሸለቆ ሕዝቡን ለመሰብሰብ የሚያስችል በቂ ቦታ ነበርን? ዘመናዊ የድምፅ ማጉያ ሳይኖራቸው እንዴት ሁሉም ሊሰሙ ቻሉ?
ይሖዋ አምላክ የሌዋውያኑን ድምፅ በተአምር እንዲጐላ ሊያደርገው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለው ተአምር አስፈላጊ የነበረ አይመስልም። በዚህ ሸለቆ ውስጥ የሚነገሩት ድምፆች በጥሩ ሁኔታ ይሰሙ ነበር። የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልፍረድ እደርሺም እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ወደዚያ የተጓዙ መንገደኞች ሁሉ በሁለት ነጥቦች ላይ ይስማማሉ:- 1. በሸለቆው ውስጥ በየትኛውም ቦታ ሆኖ የሚናገረውን ሰው በጌባልም ሆነ በገሪዛን ተራራ ላይ ሆኖ ያለምንም ችግር መስማት ይቻላል። 2. እነዚህ ሁለት ተራሮች ለእስራኤላውያን የሚሆን በቂ ቦታ ነበራቸው።”
ሌላው የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ዊልያም ቶምሰን ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ በዚያ ሸለቆ የገጠማቸውን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ድምፁ ነጥሮ ሲመለስ ለመስማት ፈልጌ ጮህኩ፤ ከዚያም ሌዋውያኑ ከፍ ባለ ድምፅ ‘በይሖዋ ዘንድ የተጠላ ነውና ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ ርጉም ይሁን’ ብለው ሲያውጁ ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበረ ለማሰብ ሞከርኩ። . . . ቀጥሎም አሜን! የሚለው ባለግርማ ድምፅ ከዚያ ታላቅ ጉባኤ አሥር እጥፍ ሆኖ ይሰማል። ድምፁ ከፍ ይላል፣ ይጐላል እንዲሁም ከጌባል ወደ ገሪዛን፣ ከገሪዛን ወደ ጌባል እየደጋገመ ያስተጋባል።” — ከዘዳግም 27:11–15 ጋር አወዳድር።
የኢይዝራኤል ሸለቆ
ከሴኬም በስተሰሜን ደግሞ ሌላ ለም የሆነ ሸለቆ አለ። ከባሕር ወለል በታች ተነሥቶ ከፍ እያለ ይሄድና ታላቅ ሜዳ ይሆናል። ኢይዝራኤል ከተባለው ከተማ ስሙን ያገኘው ይህ አካባቢ በጠቅላላ የኢይዝራኤል ሸለቆ ተብሎ ይጠራል። ከሸለቆው በስተሰሜን በሚገኙት የገሊላ ኮረብታዎች ኢየሱስ ያደገባትን የናዝሬትን ከተማ እናገኛለን። ጆርጅ ስሚዝ ዘ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል:- “ናዝሬት በተራሮች ተከባ ጎድጎድ ባለ ስፍራ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። የዚህን ሸለቋአማ ቦታ ዳር ይዘህ እየወጣህ ስትሄድ ግን . . . እንዴት ያለ የሚያምር ቦታ ታያለህ! [የኢይዝራኤል ሸለቆ] ከጦር ሜዳዎቹ ጋር በፊት ለፊትህ ተዘርግቶ ታየዋለህ። . . . ይህ የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚገልጽልን ካርታ ነው።”
በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪዎች በዚህ ሸለቋማ ሜዳ በኢያሱ ዘመን እስራኤላውያን ድል ያደረጓቸውን መንግሥታት የከተማ ፍርስራሾች አግኝተዋል። እነርሱም ታዕናክ፣ መጊዶ፣ ዮቅንዓም እና ምናልባትም ቃዴስ ናቸው። (ኢያሱ 12:7, 21, 22) በዚሁ አካባቢ ይሖዋ በመስፍኑ ባርቅና በመስፍኑ ጌዴዎን ዘመን በጣም አስፈሪ ኃይል ከነበራቸው የጠላት መንግሥታት ሕዝቡን ተአምራታዊ በሆነ መንገድ አድኗቸዋል። — መሳፍንት 5:1, 19–21፤ 6:33፤ 7:22
ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ኢዩ የይሖዋን ፍርድ በኤልዛቤልና በከሃዲው የአክአብ ቤት ላይ ለማስፈጸም ወደ ኢይዝራኤል ከተማ የጋለበው ይህን ሸለቆ አቋርጦ ነበር። በኢይዝራኤል ከነበረው ማማ ላይ በምሥራቅ በኩል የኢዩ ሠራዊት 19 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ እየገሰገሰ መቃረቡን መመልከት አያስቸግርም። ንጉሥ ኢዮራም የመጀመሪያውን ከዚያም ሁለተኛውን መልእክተኛ በፈረስ ለመላክና በመጨረሻም የእስራኤሉ ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳው ንጉሥ አካዝያስ ሠረገሎቻቸውን ጭነው ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ከመድረሱ በፊት ሊገናኙት እስኪወጡ ድረስ በቂ ጊዜ ያገኙት ለዚህ ነበር። ኢዩ ወዲያውኑ ኢዮራምን ገደለው። አካዝያስ ሊያመልጥ ሲሞክር ስለተወጋ መጊዶ ሲደርስ ሞተ። (2 ነገሥት 9:16–27) ጆርጅ ስሚዝ ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ጦርነት የተደረገባቸውን ቦታዎች አስመልክተው ሲጽፉ እንዲህ ይላሉ:- “ከተራኪዎቹ መካከል . . . አንዳቸውም ቢሆኑ የሌለ መልከዓ ምድር አለመጥቀሳቸው አስገራሚ ነው።”
ተስፋ የተደረገበት መሲህ በመሆን ኢየሱስ የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ልዕልና ለማረጋገጥ ሲል ታላቁ ኢያሱ፣ ታላቁ ባርቅ፣ ታላቁ ጌዴዎንና ታላቁ ኢዩ በመሆን ስለሚጫወተው ከፍተኛ ሚና በማሰብ አዘውትሮ የኢይዝራኤልን ሸለቆ ቁልቁል እየተመለከተ በዚህ ቦታ ላይ የተገኙትን አስደናቂ ድሎች ያሰላስል እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሸለቋማ በሆነ አካባቢ ከሁሉ ይበልጥ ስትራተጂያዊ ቦታ የሆነችውን መጊዶን ወደፊት በሐርማጌዶን (“የመጊዶ ተራራ” ማለት ነው) ለሚደረገው የአምላክ የጦርነት ቦታ ምሳሌ አድርጐ ጠቅሷታል። ያም ጦርነት የነገሥታት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክንና የአምላክ እውነተኛ ሕዝቦች የሆኑትን የክርስቲያን ጉባኤ ጠላቶች በሙሉ የሚያጠፋበት ምድር አቀፍ ጦርነት ይሆናል። — ራእይ 16:16፤ 17:14
መጽሐፍ ቅዱስ በቁጣ የተሞሉ የናዝሬት አይሁዶች ኢየሱስን “ከተማቸው ተሠርታባት ወደነበረች ወደ ተራራው አፋፍ” ጥለው ለመግደል በማሰብ እንደወሰዱት ይነግረናል። (ሉቃስ 4:29) በጣም የሚያስገርመው፣ በዘመናዊዋ የናዝሬት ከተማ ደቡባዊ ምዕራብ 12 ሜትር ርዝመት ያለው ገደል መኖሩ ይህ ሁኔታ ሊፈጸም ይችል እንደነበረ ያሳያል። ኢየሱስ ከጠላቶቹ እጅ አምልጦ “ወደ ቅፍርናሆም ወረደ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ ይናገራል። (ሉቃስ 4:30, 31) ቅፍርናሆም በገሊላ ባሕር አጠገብ ሆና ከናዝሬት ዝቅ ባለ የባሕር ወለል ላይ የምትገኝ ነበረች።
እነዚህና ሌሎች ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ናፖሊዮን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስ መልከዓ ምድራዊ ገለጻ ትክክለኛነት ያስገረማቸው መሆኑን እንዲገልጹ አድርገዋቸዋል። “መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸው ቦታዎች በጣም ብዙና ሙሉ በሙሉ አጥጋቢ በሆነ መንገድ የተገለጹ ናቸው” በማለት ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ቶምሰን ጽፈዋል። ሳይናይ ኤንድ ፓለስታይን በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ስታንሊ እንዲህ ሲሉ ጠቅሰዋል:- “በተመዘገቡት ታሪኮችና በብሉይና በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በተጠቀሰው መልከዓ ምድር መካከል ባለው ዘላቂ ስምምነት ሳይደነቅ የሚያልፍ ሰው አይኖርም።”
መጽሐፍ ቅዱስ መልከዓ ምድርን በተመለከተ የሚጠቅሳቸው ነገሮች በአስገራሚ ሁኔታ ትክክል መሆናቸው በሰዎች የተጻፈ ተራ መጽሐፍ እንዳልሆነ ከሚያሳዩት ብዙ ማስረጃዎች ውስጥ አንዱ ነው። ከዚህ በፊት የወጡት ሦስት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱ ተመሳሳይ ርዕሰ ትምህርቶችን ይዘዋል። በዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ላይ ቀደም ሲል የወጡትን ሦስቱን ክፍሎች አግኝተህ እንድታነብና እንድትጠቀምበት እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የኢይዝራኤል ሸለቆ
ኢይዝራኤል
ናዝሬት
ታአናክ
መጊዶ
ዮቅነአም
ቃዴሽ
N
የገሊላ ባሕር
ታላቁ ባሕር
ማይል
ኪሎ ሜትር
5
10
10
20
[ምንጭ]
Based on a map copy righted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel.
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን በሲና ተራራ ሕጉን ተቀበሉ
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.