የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 6/15 ገጽ 8-13
  • ፍጥረት ‘የሚያመካኙት የላቸውም’ ይላል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፍጥረት ‘የሚያመካኙት የላቸውም’ ይላል
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አስደናቂው የውኃ ዑደት
  • ሰሎሞን ጥበቡን ያገኘበት አንዱ ምንጭ
  • ያለ አንደበት ወይም ያለ ቃል ወይም ያለ ድምፅ ይናገራሉ
  • የዝግመተ ለውጥ አማኞች የመረጡት “ፈጣሪ”
  • ዝናብ በመኖሩ አመስጋኝ ሁን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • አስደናቂ የሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ይሖዋን ያወድሳሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የኢዮብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ለኢዮብ የተከፈለው ወሮታ የተስፋ ምንጭ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 6/15 ገጽ 8-13

ፍጥረት ‘የሚያመካኙት የላቸውም’ ይላል

“የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም . . . የሚያመካኙት አጡ።”  — ሮሜ 1:​20

1, 2. (ሀ) ኢዮብ በምሬት ለይሖዋ ያሰማው እሮሮ ምን ነበር? (ለ) ከጊዜ በኋላ ኢዮብ ምን የአቋም ለውጥ አደረገ?

ለይሖዋ አምላክ የማይታጠፍ ታማኝነት ባሳየውና በጥንት ዘመን ይኖር በነበረው በኢዮብ ላይ ሰይጣን አሠቃቂ ፈተና አድርሶበት ነበር። ዲያብሎስ ኢዮብ ቁሳዊ ሀብቱን በሙሉ እንዲያጣ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ እንዲሞቱበትና አስከፊ በሆነ ደዌ እንዲጠቃ አድርጓል። ኢዮብ እነዚህን አሰቃቂ መከራዎች ያመጣበት አምላክ ነው ብሎ በማሰቡ በምሬት የሚከተለውን እሮሮ ለይሖዋ አሰማ። “በአንተ ዘንድ መልካም ነውን? . . . ክፋቴን ትፈላልግ ዘንድ፣ ኃጢአቴንም ትመረምር ዘንድ፣ ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፣ . . . ታውቃለህ።” — ኢዮብ 1:​12-19፤ 2:​5-8፤ 10:​3, 6, 7

2 ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢዮብ እንደሚከተለው በማለት ለአምላክ የተናገራቸው ቃላት ፍጹም የአቋም ለውጥ ማድረጉን ያንጸባርቃሉ። “እኔ የማላስተውለውን፣ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።” (ኢዮብ 42:​3, 5, 6) የኢዮብን አቋም የሚለውጥ ምን ነገር ተከሰተ?

3. ኢዮብ ፍጥረትን በተመለከተ ምን አዲስ አመለካከት አገኘ?

3 ይሖዋ ጣልቃ ገባና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን ፊት ለፊት ተቃወመው። (ኢዮብ 38:​1) እሱም ለኢዮብ ብዙ ጥያቄዎች አቀረበለት። ‘ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርክ? የባሕር ሞገድ ከመንገዱ እንዳያልፍ መዝጊያ ያደረገለት ማን ነው? ደመናት በምድር ላይ እንዲያዘንቡ ልታደርግ ትችላለህን? ሣር እንዲበቅል ልታደርግ ትችላለህን? ከዋክብትን ባንድ ላይ ታስር ዘንድ በመንገዳቸው እንዲሄዱ ትመራቸውስ ዘንድ ትችላለህን?’ በኢዮብ መጽሐፍ ከምዕራፍ 38 እስከ 41 ላይ ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን የሚመለከቱ እነዚህንና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን በኢዮብ ላይ አዥጎደጎደበት። ኢዮብ ሊያደርጋቸው ቀርቶ ሊረዳቸው እንኳ የማይችላቸውን በአምላክ የፍጥረት ሥራ ውስጥ የተንጸባረቁትን ጥበቡንና ኃይሉን ሳይወድ በግዱ እንዲያስታውስ በማድረግ ሁሉን የሚችለው ይሖዋ በሰውና በአምላክ መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት እንዲገነዘብ አድርጎታል። አምላክ በፍጥረት ሥራዎቹ በኩል ባሳየው አስፈሪ ኃይሉና እፁብ ድንቅ በሆነው ጥበቡ ኢዮብ በፍርሃት ተዋጠ። ከይሖዋ ጋር ለመከራከር መዳፈሩ አስደነገጠው። ስለዚህ “መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ” በማለት ተናገረ። — ኢዮብ 42:⁠5

4. ከይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች መገንዘብ የሚኖርብን ነገር ምንድን ነው? ይህን መረዳት የተሳናቸው ሰዎች ሁኔታስ ምንድን ነው?

4 ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ በአምላክ መንፈስ የተገፋፋው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የይሖዋን ባሕርያት በፍጥረት ሥራዎቹ ማየት እንደሚቻል አረጋግጧል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1:​19, 20 ላይ እንደሚከተለው ሲል ጽፎአል:- “እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም . . . የሚያመካኙት አጡ።”

5. (ሀ) ሰዎች በተፈጥሮአቸው ምን ፍላጎት አላቸው? አንዳንዶች ይህን ፍላጎታቸውን በተሳሳተ መንገድ ያሟሉት እንዴት ነበር? (ለ) ጳውሎስ በአቴና ለሚገኙ ግሪካውያን የሰጣቸው ምክር ምን ነበር?

5 ሰው ከእሱ የሚበልጥ ከፍተኛ ኃይል ያለውን አንድ ነገር የማምለክ ፍላጎት እንዲኖረው ተደርጎ ተፈጥሯል። የሕክምና ዶክተር የሆኑት ኬ ጂ ጀንግ ዘ አንዲስከቨርድ ሰልፍ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ይህ ፍላጎት “ለሰው ልጅ ብቻ በተፈጥሮ የተሰጠ ዝንባሌ ሲሆን በሰው ዘር ታሪክ በግልጽ እንደታየ መረዳት ይቻላል” በማለት ጽፈዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና የነበሩ ግሪካውያን ለሚታወቁ እንዲሁም ለማይታወቁ ብዙ አማልክት ምስልና መሠዊያ የሠሩበትን ምክንያት ባብራራበት ጊዜ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለአምልኮ ጽኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን አስረድቷል። በተጨማሪም ጳውሎስ እውነተኛውን አምላክ ለይቶ በማሳወቅ ይህን የተፈጥሮ ፍላጎታቸውን በትክክለኛ መንገድ ለማርካት እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን መፈለግ የሚገባቸው መሆኑን እንዲህ በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው:- “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርን ይፈልጉ . . . ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” (ሥራ 17:​22–30) የፍጥረት ሥራዎቹን ቀረብ ብለን ባየን ቁጥር ስለ ባሕርይው የበለጠ እየተገነዘብን እንሄዳለን።

አስደናቂው የውኃ ዑደት

6. የውኃ ዑደትን በመመልከት የትኞቹን የይሖዋ ባሕርያት እንገነዘባለን?

6 ለምሳሌ ያህል አነስተኛ ክብደት ያላቸው ደመናት በብዙ ሺህ ኪሎ ግራም የሚቆጠር ክብደት ያለው የውኃ መጠን ለመያዝ መቻላቸው ይሖዋ ምን ዓይነት ባሕርያት ያሉት መሆኑን ያስገነዝበናል? ዝናብን በማዝነብ ምድር በረከትን እንድታስገኝ በማድረጉ ፍቅሩንና ጥበቡን እንገነዘባለን። ይህንንም የሚያደርገው በመክብብ 1:​7 ላይ የውኃ ዑደትን በተመለከተ “ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፣ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደገና ወደዚያው ይመለሳሉ” ተብሎ በተጠቀሰው መሠረት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ይህ እንዴት እንደሚከናወን በዝርዝር ያስረዳል።

7. ውኃ ከውቅያኖሶች ተነስቶ ወደ ደመናዎች የሚገባው እንዴት ነው? ቀላል የሆኑ ደመናዎች ብዙ ኪሎ ግራም የሚመዝን ውኃ መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው?

7 በክረምት ጊዜ ወንዞች ወደ ባሕር የሚፈሱ ቢሆንም እዚያ ብዙ አይቆዩም። ይሖዋ “የውኃውን ነጠብጣብ [ከባሕር] ወደ ላይ ይስባል፣ ዝናብም [እርሱ ከሠራው] ጉም ይንጠባጠባል።” ውኃው በእንፋሎት መልክ ይሆንና እየቆየ ሲሄድ ስስ ጉም ስለሚፈጥር “ጥበቡ ፍጹም” የሆነው አምላክ ‘ደመናዎች በሰማይ እንዲንሳፈፉ’ ያደርጋል። (ኢዮብ 36:​27፤ 37:​16 1980 ትርጉም ) ደመናዎች የሚንሳፈፉት በጉም መልክ እስካሉ ድረስ ነው። “ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል፣ ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም።” ሌላው ትርጉም ደግሞ “እግዚአብሔር፣ [ጥቁር] ደመናዎች ውኃን እንዲሸከሙ ያደርጋል፤ ከውኃውም የተነሣ ደመናዎቹ አይቀደዱም” ይላል። — ኢዮብ 26:​8 1980 ትርጉም

8. “ደመናት የተሸከሙትን ውኃ” የሚያዘንቡበት እና የውኃ ዑደት የተሟላ የሚሆንባቸው የተለያዩ ደረጃዎች ምንድን ናቸው?

8 “ደመናት የተሸከሙትን ውኃ ዝቅ ብለው” በማፍሰስ ለምድር ዝናብን እንዲሰጡ የሚያደርግ ማን ነው? (ኢዮብ 38:​37 1980 ትርጉም ) ‘ዝናብን እርሱ ከሠራው ጉም ውስጥ እንዲንጠባጠብ’ የሚያደርገው “በጥበቡ ፍጹም” የሆነው አምላክ በመጀመሪያ ደረጃ በደመናት ውስጥ የውኃ ጠብታዎች እንዲከማቹ ያደርጋል። ከጉሙ ውስጥ የዝናብ ጠብታዎች እንዲወጡ ለማድረግ ምን ያስፈልጋል? በእያንዳንዱ ኪዩቢክ ሴንቲ ሜትር አየር ላይ በዙሪያው ለሚጠራቀሙት ጠብታዎች እንደ ማዕከል ሆነው የሚያገለግሉ ከሺህ እስከ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጠጣርና የአቧራ ብናኝ ወይም የጨው ቅንጣት የሚመስሉ ረቂቅ ነገሮች መኖር አለባቸው። መካከለኛ መጠን ያለውን አንድ የዝናብ ጠብታ ለመሥራት በሚልዮን የሚቆጠሩ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ደመና ያዘላቸው የውኃ ጠብታዎች እንደሚፈጅ ተገምቷል። እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ደመናዎቹ ጅረቶችን የሚሞላውንና ከዚያም ወደ ባሕር የሚፈሰውን ውኃ ወደ ምድር ይለቁታል። በዚህ መንገድ የውኃው ዑደት የተሟላ ይሆናል። ታዲያ ይህ ሁሉ በአጋጣሚ የተገኘ ነውን? እንዲህ ብሎ የሚያምን ሰው ‘ማመካኛ የለውም!’

ሰሎሞን ጥበቡን ያገኘበት አንዱ ምንጭ

9. ሰሎሞን ስለ አንድ የጉንዳን ዝርያ ምን አስደናቂ ነገር ተመልክቶ ነበር?

9 በጥንቱ ዓለም የሰሎሞን ጥበብ ወደር የማይገኝለት ነበር። ይህ ጥበብ በአብዛኛው ክፍል በይሖዋ ፍጥረት ላይ ያተኮረ ነበር። “[ሰሎሞን] ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ስለ ተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር።” (1 ነገሥት 4:​33) እንደሚከተለው ብሎ የጻፈውም ይኸው ንጉሥ ሰሎሞን ነበር:- “አንተ ታካች፣ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፣ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፣ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች።” — ምሳሌ 6:​6–8

10. ሰሎሞን መኖአቸውን ስለሚሰበስቡ ጉንዳኖች የተናገረው ምሳሌ እውነተኛነት የተረጋገጠው እንዴት ነው?

10 ጉንዳኖች ለቀዝቃዛው የክረምት ወራት የሚሆናቸውን መኖ በበጋ እንዲሰበስቡ ያስተማራቸው ማን ነው? እነዚህ ጉንዳኖች ለክረምት የሚሆናቸውን መኖ በበጋ ይሰበስባሉ የሚለው የሰሎሞን ዘገባ እውነተኛነት ለብዙ መቶ ዘመናት አጠራጣሪ ሆኖ ቆይቶ ነበር። እንዲህ ዓይነት ጉንዳኖች ስለመኖራቸው ማረጋገጫ ያቀረበ ማንም አልነበረም። ይሁን እንጂ በ1871 የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ የነበሩ አንድ እንግሊዛዊ ሰው ጉንዳኖቹ እህል የሚያከማቹባቸውን ጎተራዎች ከመሬት በታች በማግኘታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉንዳኖቹ የመዘገበው ነገር ትክክለኛ መሆኑ ተረጋገጠ። ሆኖም እነዚህ ጉንዳኖች የክረምቱ ቅዝቃዜ እየመጣ መሆኑንና ምን ማድረግ እንዳለባቸው አስቀድመው የሚያውቁበትን ጥበብ እንዴት አገኙ? ብዙዎቹ የይሖዋ ፍጥረታት በሕይወት መኖራቸውን ይቀጥሉ ዘንድ በተፈጥሮ ያገኙት ጥበብ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይናገራል። መኖአቸውን አስቀድመው የሚሰበስቡት ጉንዳኖችም እንዲህ ያለውን በረከት ከፈጣሪያቸው አግኝተዋል። ምሳሌ 30:​24 ስለዚሁ ጉዳይ “እነርሱ ግን [በተፈጥሮአቸው] እጅግ ጠቢባን ናቸው” በማለት ይናገራል። እንዲህ ያለው እውቀት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አለመሆን ነው፤ ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በስተጀርባ ጥበበኛ ፈጣሪ መኖሩን ላለማመን ማመካኛ የሚሆን ምንም ነገር የለም።

11. (ሀ) ግዙፉ የሴኮያ ዛፍ ይህን ያህል አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በፎቶ ሲንተሲስ ውስጥ የሚካሄደው የመጀመሪያው እርምጃ በጣም አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?

11 አንድ ሰው በጣም ትልቅ በሆነው ሴኮያ በተባለው ዛፍ ግዙፍነት ተደንቆ እሥሩ ቢቆም ልክ እንደ አንድ ትንሽ ጉንዳን የሆነ ያህል እንደሚሰማው የታወቀ ነው። የዛፉ ትልቅነት አስፈሪ ነው። ርዝመቱ 90 ሜትር፣ መሃል ለመሃል ያለው ርዝመት 11 ሜትር፣ የቅርፊቱ ውፍረት 60 ሴንቲ ሜትር እንዲሁም ሥሮቹ ከ12,000 እስከ 16,000 ካሬ ሜትር በሚደርስ ስፋት የተዘረጉ ናቸው። ከዚህ ይበልጥ የሚያስገርመው ግን በዛፉ ዕድገት ላይ ሚና የተጫወቱት የኬሚስትሪና የፊዚክስ ሂደቶች ናቸው። ቅጠሎቹ በሥሩ አማካኝነት ውኃ ያገኛሉ፤ ከአካባቢው አየር ደግሞ ካርቦን ዳይኦክሳይድ የተባለውን ንጥረ ነገር በመውሰድ ከፀሐይ ብርሃን በሚገኘው ኃይል ተጠቅመው ስኳር ሲሠሩ ኦክሲጅንን ያስወጣሉ፤ ይህ ሂደት ፎቶ ሲንተሲስ ይባላል፤ ፎቶ ሲንተሲስ ወደ 70 የሚደርሱ የኬሚካል ለውጦችን ያጠቃልላል። ከሚካሄዱት የኬሚካል ለውጦች ሁሉ የታወቁት ሁሉም አይደሉም። ፎቶ ሲንተሲስ የተባለውን ሂደት በማስጀመር የሚካሄደው ለውጥ ከፀሐይ የሚደርሰው ብርሃን ቀለሙም ይሁን የሞገዱ መጠን ትክክለኛ በመሆኑ ላይ መመካቱ የሚያስደንቅ ነው። የፀሐይ ብርሃን በዚህ መንገድ ተመቻችቶ ካልቀረበ የፎቶ ሲንተሲስን ሂደት ለማስጀመር በቅጠሉ ሀመልማል የሚገኙ ሞለኪሎች አይቀበሉትም።

12. (ሀ) ስለ ሴኮያ ዛፍ የውኃ አጠቃቀም አስደናቂ የሆነው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ናይትሮጅን ለተክል እድገት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የናይትሮጅን ዑደት የተሟላ የሚሆነውስ እንዴት ነው?

12 ሌላው የሚያስደንቀው ነገር ዛፉ ከሥሩ አንስቶ 90 ሜትር እስከሚደርሰው ጫፉ ድረስ ውኃ ለመሳብ መቻሉ ነው። ለፎቶ ሲንተሲስ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ብዙ ውኃ ወደ ላይ ይስባል። ትርፍ የሆነው ውኃ በቅጠሉ በኩል እየተነነ ይወጣና ከአየር ጋር ይደባለቃል። እኛ ሲያልበን ሰውነታችን በረድ እንደሚል ሁሉ ይህም ሂደት ዛፉን በውኃው አማካኝነት ቀዝቀዝ እንዲል ያደርገዋል። ለእድገቱ የሚያስፈልገውን ፕሮቲን ለማዘጋጀት በስኳሩ ወይም በካርቦሃይድሬቱ ውስጥ ናይትሮጅን መጨመር ያስፈልጋል። ቅጠሉ ከአየር የሚያገኘውን ናይትሮጅን እንዳለ በጋዝ መልኩ ሊጠቀምበት አይችልም። ነገር ግን በአፈር ውስጥ የሚኖሩት ረቂቃን ነፍሳት በጋዝ መልክ የሚገኘውን ናይትሮጅን በውኃ ሊሟሙ ወደሚችሉት ናይትሬትስ እና ናይትራይትስ ይለውጡታል። ከዚያም በውኃ የሟሙት ናይትሬትስ እና ናይትራይትስ ከሥሮቹ ተነስተው እስከ ቅጠሎቹ ድረስ ይጓዛሉ። ፕሮቲን ለመሥራት ይህን ናይትሮጅን የተጠቀሙበት አትክልቶችም ሆነ ፕሮቲኑን የተመገቡት እንስሳት ሞተው ሲበሰብሱ ናይትሮጅኑ ተመልሶ አየር ውስጥ ይገባል። በዚህ መንገድ የናይትሮጅኑ ዑደት ይሟላል። የሂደቱን ውስብስብነት ስናይ እንኳንስ በአጋጣሚ ሊከናወን ቀርቶ አእምሮ እንኳን ሊረዳው የሚችል አይደለም።

ያለ አንደበት ወይም ያለ ቃል ወይም ያለ ድምፅ ይናገራሉ

13. በከዋከብት የተሞሉት ሰማያት ለዳዊት በግልጽ ያሳወቁት ነገር ምን ነበር? ለእኛስ ምን ነገር መናገራቸውን ቀጥለዋል?

13 ማታ ማታ በሰማይ ላይ ጥቅጥቅ ብለው የሚታዩት ከዋክብት የፈጣሪን ግርማ ሞገስ የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ተመልካቹን በከፍተኛ አክብሮትና ፍርሃት እንዲሞላ ያደርጉታል። በመዝሙር 8:​3, 4 ላይ ዳዊት ተሰምቶት የነበረውን አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” በከዋክብት የተሞሉት እነዚህ ሰማያት “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” ሲል ለጻፈው ለዳዊት በሚገባው ቋንቋ ተናግረዋል፤ ዛሬም የሚያዩ ዓይኖች፣ የሚሰሙ ጂሮዎችና ሁኔታዎች የሚሰሙት ልብ ላላቸው ሰዎች ይናገራሉ። — መዝሙር 19:​1–4

14. ከከዋከብት አንዷ ያላት ከፍተኛ ኃይል ለህልውናችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ስለ ከዋክብት ብዙ እያወቅን ስንሄድ ያለ ድምፅ ለእኛ የሚናገሩበት መጠን ከፍ ይላል። በኢሳይያስ 40:​26 ላይ ከዋክብት ያላቸውን አስገራሚ ኃይል ልብ እንድንል ተጋብዘናል:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።” ከከዋክብት አንዷ የሆነችው ፀሐይ ያላት ከፍተኛ ኃይልና በተቃራኒው የሚሠራው የስበት ኃይል ምድር ከምህዋሯ ዝንፍ እንዳትል፣ ተክሎች እንዲበቅሉ፣ እኛም ሙቀት እንድናገኝና በዚህች ምድር ላይ ሁሉም ዓይነት ሕይወት እንዲኖር ያስችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ “በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:​41) ሳይንስ እንደ ፀሐያችን ቢጫ ቀለም ያላቸው ኮከቦች፣ ሰማያዊ ኮከቦች፣ ሬድ ጃይንትስና ዋይት ዱዋርፍስ የተባሉ ኮከቦች፣ ኒውትሮን ኮከቦች እና ቢፈነዱ የሰው አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ ታላቅ ኃይል የሚለቁ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ፈንጂ ኮከቦች መኖራቸውን አውቋል።

15. አዳዲስ ነገሮችን የሚፈለስፉ ብዙ ሰዎች ከተፈጥሮ በመማር አስመስለው ለመሥራት የሞከሩት ምንድን ነው?

15 አዳዲስ ነገሮችን የሚፈለስፉ ብዙ ሰዎች ከተፈጥሮ በመማር የሕያዋን ፍጥረታትን ችሎታዎች ለመቅዳት ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። (ኢዮብ 12:​7–10) አስደናቂ ከሆኑት የፍጥረት ገጽታዎች ጥቂቶቹን ብቻ ተመልከት። ጨው የሚያስወግድ ዕጢ ያላቸው በባሕር የሚኖሩ ወፎች፣ ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ዓሣዎችና ኢልስ የተባሉ እባብ መሰል የባሕር ፍጥረታት፣ ሙቀት አልባ የሆነ ብርሃን የሚሰጡ ዓሦች፣ ትላትሎችና በራሪ ነፍሳት፣ በባሕር ውስጥ በርቀት ያሉ ነገሮችን በሞገድ መለየት የሚችሉ የሌሊት ወፎችና ዶልፊኖች፣ ወረቀት የሚሠሩ ተርቦች፣ ድልድይ የሚገነቡ ጉንዳኖች፣ ግድቦችን የሚሠሩ የአይጥ ዝርያዎች፣ በሰውነታቸው ውስጥ የሙቀት መለኪያ ያላቸው እባቦች፣ በውኃ ውስጥ ሲሆኑ አየር የሚስቡበትና ውኃ ውስጥ በሚጠልቁበት ጊዜ የሚያንሳፍፍ የአካል ክፍል ያላቸው በኩሬ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳት፣ እንደ ጀት አውሮፕላን መብረሪያ ያላቸው ኦክቶፐስ የተባሉት በባሕር የሚኖሩ ፍጥረታት፣ ሰባት ዓይነት ድሮችን፣ ወጥመዶችንና ማጥመጃዎችን የሚሠሩ እንዲሁም በከፍታ ተንሳፍፈው በአየር ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዙ ልጆች ያሏቸው ሸረሪቶች፣ ሰርጓጅ መርከቦች የሚጠቀሙበትን ዓይነት ማንሳፈፊያ የሚጠቀሙ ዓሣዎችና በባሕር ላይ የሚንሳፈፉ ዓሣ መሰል እንስሳት፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚያስገርም ሁኔታ ብዙ ርቀት አቋርጠው የሚሄዱ ወፎች፣ ነፍሳት፣ የባሕር ኤሊዎች፣ ዓሣዎችና የሚያጠቡ እንስሳት ሁሉ ያሏቸው ችሎታዎች ሳይንስ ካለው የማስረዳት ችሎታ በላይ ናቸው።

16. ሳይንስ ከማወቁ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ሳይንሳዊ እውነቶች ምንድን ናቸው?

16 ሳይንስ እነዚህን ነገሮች ከማወቁ ከብዙ ሺህ ዓመታት አስቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ እውነቶችን መዝግቦ አስቀምጧል። ፓስተር ረቂቅ ሕዋሳት በሽታ እንደሚያመጡ ከማግኘቱ ከብዙ ሺህ ዓመታት አስቀድሞ የሙሴ ሕግ (በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) ስለዚሁ ጉዳይ አስገንዝቦ ነበር። (ዘሌዋውያን ምዕራፍ 13 እና 14) በ17ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢዮብ “ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል” ሲል ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 26:​7) ከክርስቶስ ልደት 1,000 ዓመታት አስቀድሞ ሰሎሞን ደም በሰውነት ውስጥ ስለሚያደርገው ዝውውር ጽፎ ነበር። የሕክምና ሳይንስ ግን እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ድረስ ስለዚህ ጉዳይ አያውቅም ነበር። (መክብብ 12:​6) ከዚያ በፊት መዝሙር 139:​16 በሴል ውስጥ ስላለው ወደ ቀጣይ ዘሮች የሚተላለፉትን ሁለንተናዊ ባሕርያት ስለሚወስነው ንድፍ (ጀነቲክ ኮድ) “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” በማለት ዕውቀት ሰጥቶ ነበር። የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች ወፎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ስለሚያደርጉት ጉዞ ከመረዳታቸው በፊት በ7ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በኤርምያስ 8:​7 ላይ ኤርምያስ “ሽመላዎች እንኳ የሚመለሱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤ ዋኖሶች፣ ጨረባዎች፣ ዋርዳዎችም በኅብረት የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ” በማለት ጽፎ ነበር። — የ1980 ትርጉም

የዝግመተ ለውጥ አማኞች የመረጡት “ፈጣሪ”

17. (ሀ) ከአስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች በስተጀርባ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ መኖሩን ለማስተዋል እምቢተኞች ስለሆኑ አንዳንድ ሰዎች ሮሜ 1:​21–23 ምን ይላል? (ለ) የዝግመተ ለውጥ አማኞች “ፈጣሪያቸው” አድርገው የመረጡት ምንድን ነው ለማለት ይቻላል?

17 ከአስደናቂዎቹ የፍጥረት ሥራዎች በስተጀርባ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ መኖሩን ለማስተዋል እምቢተኞች የሆኑትን አስመልክቶ አንድ ጥቅስ እንዲህ ይላል:- “በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፣ የማይጠፋውንም የእግዚአብሔርን ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ።” እነርሱ ‘የአምላክን እውነት በውሸት ለውጠዋል፤ በፈጣሪ ፋንታ የተፈጠረውን አምልከዋል አገልግለዋልም።’ (ሮሜ 1:​21–23, 25) በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ሳይንቲስቶችም እንዲሁ ሰው ባለአንድ ሕዋስ ከሆነ እንስሳ ተነስቶ ወደ ትላትሎች ከዚያም ወደ ዓሦች ከዚያም በውኃም በየብስም ሊኖሩ ወደሚችሉ እንስሳት ከዚያም በሆዳቸው ወደሚሳቡ ቀጥሎም ወደ አጥቢዎች በመጨረሻም ወደ “ሰው መሰል ጦጣ” ተለወጡ የሚለውን የፍጥረትን አመጣጥ ይገልጻል ብለው የሚገምቱትን ሰንሰለት እንደ “ፈጣሪያቸው” አድርገው አምነዋል። ይሁን እንጂ ሰንሰለቱን ለመጀመር የሚያስችል ባለ አንድ ሕዋስ የሆነ አነስተኛ አካል አለመኖሩን ያውቃሉ። የመጨረሻ አነስተኛ ነው ተብሎ የሚታወቀው ሕያው አካል አንድ መቶ ቢልዮን አተሞችን ይይዛል፤ በውስጡም በሺህ የሚቆጠሩ ኬሚካላዊ ለውጦች በአንድ ጊዜ ይካሄዳሉ።

18, 19. (ሀ) ሕይወትን በማስገኘቱ የመመስገን መብት ያለው ማን ነው? (ለ) ከይሖዋ ፍጥረታት ልንረዳ የምንችለው ምን ያህሉን ነው?

18 የሕይወት ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ነው። (መዝሙር 36:​9) እርሱ የመጀመሪያውና ታላቁ የሕይወት አስገኚ ነው። ይሖዋ የሚለው ስሙ “እንዲሆን የሚያደርግ” ማለት ነው። ፍጥረቶቹ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ናቸው። ሰው የማያውቃቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ፍጥረታት መኖራቸው እሙን ነው። መዝሙር 104:​24, 25 “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ” በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ፍንጭ ይሰጣል። ኢዮብ 26:​14 በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የ1980 ትርጉም ላይ ይህን ግልጽ ሲያደርገው:- “እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ከሚሠራቸው ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፤ የምንሰማው ሹክሹክታውን ብቻ ነው፤ የኃይሉን ነጎድጓድማ ማን ሊያስተውል ይችላል?” ይላል። ያየነው የፍጥረቱን ጥቂት ክፍል ብቻ ነው። የሰማነው አነስተኛ ሹክሹክታውን ነው። በኃይሉ ውስጥ ያለውን ነጎድጓድ ሙሉ በሙሉ መረዳት ግን ከአቅማችን በላይ ነው።

19 ይሁን እንጂ ከሚታዩት ፍጥረቶቹ በተሻለ መንገድ እርሱን ለማወቅ የሚያስችለን ሌላ ምንጭ አለ። ይህ የተሻለው ምንጭ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህንን የሚመለከት ትምህርት እናቀርባለን።

ታስታውሳለህን?

◻ ይሖዋ በአውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ባነጋገረው ጊዜ ኢዮብ ምን ተማረ?

◻ ጳውሎስ አንዳንዶች የሚያመካኙት የላቸውም ያለው ለምንድን ነው?

◻ የውኃ ዑደት የሚካሄደው እንዴት ነው?

◻ የፀሐይ ብርሃን ምን ጠቃሚ ነገሮችን ያደርግልናል?

◻ ሳይንስ ሳይደርስበት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ሳይንሳዊ እውነቶች ምንድን ናቸው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ