የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 7/15 ገጽ 5-8
  • ይሖዋ እውነተኛውና ሕያው የሆነው አምላክ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ እውነተኛውና ሕያው የሆነው አምላክ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስሙና ዝናው
  • ይሖዋና ባሕሪያቱ
  • አቻ የሌለው ሰማያዊ ንጉሥ
  • ይሖዋ እውነተኛና ሕያው አምላክ ነው
  • እውነተኛው አምላክ ማን ነው?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • አምላክ ስም አለው
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • ይሖዋ ማን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የይሖዋን መንገድ መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 7/15 ገጽ 5-8

ይሖዋ እውነተኛውና ሕያው የሆነው አምላክ

የግብጹ ፈርዖን “ይሖዋ ማን ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ንግግሩ የዕብሪተኝነትና የንቀት አነጋገር ነበር። (ዘጸአት 5:​2 አዓት) ባለፈው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንደተገለጸው ይህ አቋም በግብጻውያን ላይ መቅሰፍቶችንና ሞትን አምጥቷል፤ ፈርኦንና ወታደራዊ ኃይሎቹ መቃብራቸው ውኃ እንዲሆን አድርጓል።

በጥንቷ ግብጽ ይሖዋ ከሐሰት አማልክት የላቀ መሆኑን አረጋግጧል። ይሁን እንጂ ስለ እርሱ የምንማረው ሌላም ተጨማሪ ነገር አለ። የባሕሪው አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? ከእኛ የሚሻውስ ምንድን ነው?

ስሙና ዝናው

ሙሴ ለግብጹ ፈርዖን ጥያቄ ባቀረበበት ጊዜ ‘ጌታ እንዲህ ይላል’ አላለውም። ፈርዖንና ሌሎቹ ግብጻውያን ብዙዎቹን የሐሰት አማልክቶቻቸውን እንደ ጌቶች አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሙሴ እንዲህ አላደረገም። ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም ተጠቅሟል። በምድያም ምድር በሚነድደው ቁጥቋጦ አጠገብ በነበረበት ጊዜ ይህ ስም ከሰማይ ሲነገር ሰምቷል። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው መዝገብ እንዲህ ይላል:-

“እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ሙሴን ተናገረው አለውም፣ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ፤ . . . ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው:- እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ፣ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፣ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፣ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፣ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። [ለአባቶቻችሁ] ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር [ወደ ከነዓን] አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነኝ”። — ዘጸአት 6:​1–8

ይሖዋ ያደረገው ይህንኑ ነበር። እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቶ የከነዓንን ምድር እንዲወርሱ አስችሏቸዋል። አምላክ ቃል በገባው መሠረት ይህ ሁሉ ነገር እንዲፈጸም አድርጓል። “እንዲሆን የሚያደርግ” የሚል ትርጉም ያለው ይሖዋ የሚለው ስሙ ምንኛ የሚስማማው ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “አምላክ”፣ “ሉዓላዊ ጌታ”፣ “ፈጣሪ”፣ “አባት”፣ “ሁሉን ማድረግ የሚችል” እና “ልዑሉ” በሚሉት ዓይነት የማዕረግ ስሞች ይጠራዋል። ሆኖም ይሖዋ የሚለው ስሙ ታላላቅ አላማዎቹ ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲፈፀሙ የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ለይቶ ያሳውቀዋል። — ኢሳይያስ 42:​8

መጽሐፍ ቅዱስን መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ብናነበው የአምላክን ስም በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ተጽፎ እናገኘዋለን። በዕብራይስጥ ቴትራግራማተን ተብለው በሚጠሩት ከቀኝ ወደ ግራ በሚነበቡ ዮድ ሄ ዋው ሄ (יהוה) በሚባሉት አራት የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት ተገልጿል። የዕብራይስጥ ቋንቋ ተናጋሪዎች አናባቢዎችን በማስገባት ያነብቡ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሰዎች ግን አናባቢዎቹን በትክክል አያውቋቸውም። አንዳንዶች ያህዌህ በሚለው ቃል መጠቀምን ቢመርጡም ይሖዋ (JEHOVAH) የሚለው ስም የተለመደና ተስማሚ በሆነ መንገድ ፈጣሪያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ ነው።

በተጨማሪም ይሖዋ በሚለው ስም መጠቀሙ አምላክን በመዝሙር 110:​1 ላይ ጌታዬ ከተባለው ለመለየት ያስችላል። የ1879 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ጌታ (יהוה) ጌታዬን አለው። በቀኜ ተቀመጥ ጸላቶችኽን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ።” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እዚህ ቦታ ላይ የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ ያለውን አገባብ በመቀበል እንዲህ በማለት ተርጉሞታል:- “ይሖዋ ጌታዬን:- ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።’” ይሖዋ አምላክ የተናገራቸው እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ጸሐፊው “ጌታዬ” ብሎ የጠራውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክቱ ናቸው።

ይሖዋ በፈርዖን ዘመን ለራሱ ገናና ስም አትርፏል። አምላክ በሙሴ አማካኝነት ልበ ደንዳናውን ገዥ እንዲህ ብሎታል:- “በምድር ሁሉ ላይ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎቸህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ። አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በመታሁህ ነበር፣ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነስቼአለሁ።” — ዘጸአት 9:​14–16

የእስራኤልን ከግብፅ መውጣትና አንዳንድ የከነዓናውያን ነገሥታትን መደምሰስ በተመለከተ የኢያሪኮዋ ረዓብ ለሁለት ዕብራውያን ሰላዮች እንዲህ ብላለች:- “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ምድሪቱን [ለእስራኤላውያን] እንደ ሰጣችሁ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፣ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፣ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፣ በሴዋንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም።” (ኢያሱ 2:​9–11) አዎ፣ የይሖዋ ዝና በየቦታው ተሰራጭቶ ነበር።

ይሖዋና ባሕሪያቱ

መዝሙራዊው:- “አሕዛብ ስምህ ይሖዋ የሆንከው አንተ ብቻ በምድር ላይ የሁሉ የበላይ እንደሆንህ ይወቁ” በማለት ይህን ከልብ የመነጨ ምኞቱን ገልጿል። (መዝሙር 83:​18 አዓት) ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ በመሆኑ ስደት የደረሰባቸው የኢየሱስ ተከታዮች:- “ጌታ ሆይ [ሉዓላዊ ጌታ ሆይ]፣ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ” በማለት ሊጸልዩ ችለዋል። (ሥራ 4:​24) ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ መሆኑንም ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! — መዝሙር 65:​2

የይሖዋ ዋነኛ ባሕሪይ ፍቅር ነው። በእርግጥም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” ይህንን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ የተላበሰ አምላክ ነው። (1 ዮሐንስ 4:​8) ከዚህም በላይ “በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ።” ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል ጥበብና ኃይል ቢኖረውም ኃይሉን አለአግባብ አይጠቀምበትም። (ኢዮብ 12:​13፤ 37:​23) በአገባቡ እንደሚይዘንም ሁልጊዜ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ “ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት” ናቸውና። (መዝሙር 97:​2) ስህተት ብንሠራና በኋላ ንስሐ ብንገባ ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን በማወቃችን ልንጽናና እንችላለን። (ዘጸአት 34:​6) ይሖዋን በማገልገል ደስታ ማግኘት የምንችል መሆኑ አያስደንቅም! — መዝሙር 100:​1–5

አቻ የሌለው ሰማያዊ ንጉሥ

የይሖዋ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ:- “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:​24) ስለዚህ ይሖዋ በሰብዓዊ ዓይን አይታይም። እንዲያውም ይሖዋ ሙሴን:- “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” ብሎታል። (ዘጸአት 33:​20) ይህ ሰማያዊ ንጉሥ አንጸባራቂ ክብር የተጎናጸፈ በመሆኑ ሰዎች እርሱን አይተው መቆም አይችሉም።

ይሖዋን በዓይናችን ልናየው ባንችልም ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ሆኖ እንደሚኖር የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። በእርግጥም “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል።” (ሮሜ 1:​20) በሣር፣ በዛፍ፣ በፍራፍሬዎች፣ በቅጠላቅጠሎችና በአበቦች የተሸፈነችው ምድር ለይሖዋ አምላክነት ምስክርነት ትሰጣለች። ይሖዋ ዝናብንና ፍሬያማ ወቅቶችን የሚሰጥ በመሆኑ እርባና ከሌላቸው ጣዖታት የተለየ ነው። (ሥራ 14:​16, 17) ጨለማ በነገሠበት ሰማይ ላይ የተረጩትን ከዋክብት አሻቅበህ ተመልከት። የይሖዋን አምላክነትና የማደራጀት ችሎታ የሚያሳይ እንዴት ያለ ታላቅ ማስረጃ ነው!

ይሖዋ በሰማይ ያሉትን የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ቅዱሳን ፍጥረታቱንም አደራጅቷቸዋል። መዝሙራዊው ቀጥሎ እንደተናገረው ስምምነት የሰፈነበት ድርጅት በመሆን የአምላክን ፈቃድ ይፈጽማሉ:- “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃያላን፣ የቃሉንም ደምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፣ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፣ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ባርኩ።” (መዝሙር 103:​20, 21) ይሖዋ በምድር ላይ የሚገኙትንም ሕዝቦቹን አደራጅቷቸዋል። የእስራኤልም ሕዝብ ሆነ የጥንቶቹ የአምላክ ልጅ ተከታዮች በደንብ የተደራጁ ነበሩ። ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ መንግሥቲቱ መጥታለች የሚለውን ምሥራች የሚያውጁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደራጁ ቀናተኛ ምስክሮች አሉት። — ማቴዎስ 24:​14

ይሖዋ እውነተኛና ሕያው አምላክ ነው

የይሖዋ አምላክነት በብዙ መንገዶች ተረጋግጧል! የግብጽን የሐሰት አማልክት የሃፍረት ማቅ አከናንቧቸዋል፤ እስራኤላውያንን ደግሞ በደህና ወደ ተስፋይቱ ምድር አስገብቷቸዋል። ፍጥረት ስለ ይሖዋ አምላክነት አያሌ ማስረጃዎችን ይሰጣል። ያለአንዳች ጥርጥር እርሱንና እርባና የለሽ የሆኑትን የሐሰት ሃይማኖት ጣዖታት ከቶውንም ማወዳደር አይቻልም።

ነቢዩ ኤርምያስ ሕያው በሆነው አምላክ በይሖዋና በድን በሆኑት ሰው ሠራሽ ጣዖታት መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት አሳይቷል። ይህ የጎላ ልዩነት በኤርምያስ ምዕራፍ 10 ላይ ቁልጭ ብሎ ተገልጿል። ኤርምያስ ከዘረዘራቸው ነገሮች አንዱ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው።” (ኤርምያስ 10:​10) ሕያውና እውነተኛ የሆነው አምላክ ይሖዋ ሁሉን ፈጥሯል። በግብፃውያን ባርነት ይማቅቁ የነበሩትን እስራኤላውያንን ነፃ አውጥቷቸዋል። ምንም የሚሳነው ነገር የለም።

‘የዘላለም ንጉሥ’ የሆነው ይሖዋ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ለሚለው ጸሎት መልስ ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​17፤ ማቴዎስ 6:​9, 10) በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተዳደራት ያለችው ሰማያዊቷ መሲሐዊት መንግሥት በክፉዎች ላይ እርምጃ ትወስዳለች፤ የይሖዋንም ጠላቶች በሙሉ ትደመስሳለች። (ዳንኤል 7:​13, 14) በተጨማሪም መንግሥቲቷ ለታዛዥ የሰው ዘሮች በአዲስ ዓለም ውስጥ ዘላለማዊ በረከቶችን ታስገኛለች። — 2 ጴጥሮስ 3:​13

ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ መማር የምንችላቸው ከዚህ በላይ ብዙ ነገሮች አሉ። ይህን እውቀት ለማግኘትና ከዚህ ዕውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ ቁርጥ ያለ አቋም ለምን አትወስድም? እንዲህ ካደረግህ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በገነቲቷ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት የመደሰት መብት ታገኛለህ። ኃዘን፣ ሥቃይ አልፎ ተርፎም ሞት በሌለበትና ምድር ይሖዋን በማወቅ በምትሞላበት ጊዜ ትኖራለህ። (ኢሳይያስ 11:​9፤ ራእይ 21:​1–4) “ይሖዋ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶችን ለማወቅ ከመረመርክ፣ መልሱንም ካገኘህና በዚያ መሠረት እርምጃ ከወሰድክ ይህ የአንተም ሕይወት ዕጣ ፈንታ ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ