“በሰላም መነጋገር አልቻልንም!”
ጠበቃ የሆነው ሚካኤል የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ የተዋጣለት ነበር። ሥራው ይህን ችሎታ ይጠይቅበታል። ሚካኤል በትዳር ዓለም ውስጥ 16 ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ግን ሥራ ውሎ ወደ ቤት ሲመለስ ከሚስቱ ከአድሬያን ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የነበረው ችሎታ እየተዳከመ እንደመጣ ለመገንዘብ ተገደደ። “መነጫነጭ፣ በሆነ ባልሆነው መተቸት፣ በአሽሙር መናገር” ሲል ሚካኤል ያስታውሳል፤ “ሁል ጊዜ በአድሬያንና በእኔ መካከል ለጠብ የሚያደርስ ግጭት ይፈጠራል። ይህም እየሠለቸን እንዳለ ተሰማኝ። ትዳር የቅሬታና የብስጭት አምባ ይሆንን ብዬ አሰብኩ። በቀጣዩ ጊዜ በአንድነት የመኖር ዕጣችን ይህ ከሆነ እውነቱን ለመናገር ትዳሩ እንዲፈርስ ፈልጌ ነበር። ብስጭትና ውጥረት የሚሰፍንባቸው ይህን የመሰሉ 20, 30 እና 40 ዓመታት መጋፈጥ አልችልም።”
እንዲህ ዓይነቱን ስሜት የሚገልጹ ሚካኤልና አንድሬያን ብቻ አይደሉም። ውጊያና ተኩስ አቁም የሚፈራረቅበት ግንኙነት ያላቸው የብዙ ባልና ሚስት ሁኔታ እንደዚህ ነው። በጨዋታ የተነሣው የሐሳብ ልውውጥ ድንገት ወደ ቃላት ጦርነት ይለወጣል። ያልተባሉ ነገሮችን “ይሰማሉ”። ያላሰቡትን ነገር ይናገራሉ። አንዱ አንዱን ይዘልፋል። ይከሳል፣ ከዚያም ይኮራረፋሉ። አልተለያዩም፤ ‘አንድ ሥጋም’ አልሆኑም። (ዘፍጥረት 2:24) ምንም ሊጣጣሙ ስለማይችሉ ግንኙነታቸው የሻከረ ነው። ወደ ኋላ መመለስ ማለት መለያየት ይሆናል፤ ወደፊት መሄድ ማለት ደግሞ ከልዩነቶች ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥ ይሆናል። እነዚህ ባልና ሚስቶች ሁለቱም ከሚያስከትሉአቸው ችግሮች ለመሸሽ የየራሳቸውን ስሜት በመጠበቅ ተራርቀው መኖርን ይመርጣሉ።
እንዲህ ዓይነት ባልና ሚስቶች በትዳራቸው ውስጥ ‘ጥሩ መመሪያ ማግኘት’ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 1:5) ይህ መመሪያ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈው ሁለተኛው መልዕክት መጽሐፍ ቅዱስ “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት . . . ይጠቅማል” በማለት ያረጋግጥልናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በዚህ መሠረት በጋብቻ ውስጥ የሚኖረውን የሐሳብ ግንኙነት መስመር ብልሽት መጠገን የሚቻልበት መንገድ ይህ እንደሆነ ቀጥሎ እንመለከታለን።