የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 8/1 ገጽ 26-30
  • ይሖዋ የታመሙትንና አረጋውያንን ያስታውሳል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ የታመሙትንና አረጋውያንን ያስታውሳል
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሌላውን ችግር ለመረዳት ሞክር
  • ለታመሙና ለአረጋውያን አክብሮት ማሳየት
  • መንፈሳዊ ብርታት እንዲያገኙ የሚደረግ እርዳታ
  • ክርስቲያኖች አረጋውያንን ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የክርስቲያን ቤተሰብ አረጋውያንን ይረዳል
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • አረጋውያንን መንከባከብ—ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ከቤተሰብና ከጉባኤ ርቀው ቢኖሩም አልተረሱም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 8/1 ገጽ 26-30

ይሖዋ የታመሙትንና አረጋውያንን ያስታውሳል

‘ክፉ ዘመንን’ ችሎ ማሳለፍ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 37:​18, 19) እንዲህ ዓይነቱ ዘመን በዕድሜ መግፋትና ከሱ ጋር ተያይዞ በሚመጣው ድካም መልክ ሊመጣ ይችላል። አንዳንዶች ጠና ባለ ሕመም ሲሠቃዩ ወደዚህ ክፉ ዘመን ይገባሉ። በሽታቸው ሕይወታቸውን እንደሚቆጣጠረው ማለትም በአስተሳሰባቸውና በድርጊታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል።

ቢሆንም ግን የይሖዋ ዓይኖች በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ መሆናቸውን ማወቁ የሚያጽናና ነው። እርጅና፣ ሕመም ወይም ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ለእርሱ ያደሩ አገልጋዮቹ ታማኝነትንና ጥበብን ማሳየታቸውን መቀጠላቸው ልቡን ደስ ያሰኘዋል። (2 ዜና መዋዕል 16:​9፤ ምሳሌ 27:​11) ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል:- “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው . . . ልመናቸውንም ይሰማል።” አዎ፣ ያለባቸውን ትግል ያውቃል፤ በመንፈሱም ያበረታቸዋል። “ያድናቸውማል።” ያስታውሳቸዋል እንዲሁም እንዲጸኑ ይረዳቸዋል። (መዝሙር 145:​18, 19) ግን እኛስ? ልክ እንደ ይሖዋ የታመሙትን እና አረጋውያንን እናስታውሳለንን?

በዚህ ባለንበት ሥርዓት በሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት የሚመጡ ድክመቶች የሕይወት እውነታዎች ናቸው። ይሖዋ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ እስከሚፈጽም ድረስ ልንቋቋማቸው የሚገቡ ነገሮች ናቸው። ዛሬ ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ ስለሆነም ብዙ ቁጥር ያላቸው ከእንዲህ ዓይነቱ ድክመት ጋር ተዋውቀዋል። በተጨማሪም ብዙዎች ወጣት እያሉም እንኳ ሕይወትን አደጋ ላይ በሚጥሉ ወይም አካለ ስንኩል በሚያደርጉ አደጋዎች ወይም በሽታዎች ይጐዳሉ። ይህ አሮጌ ዓለም እስኪያልፍ ድረስ ሕመምና እርጅና ከፍተኛ ችግር መሆናቸው ይቀጥላል።

በመካከላችን ያሉትን “የመከራ እና የትዕግሥት ምሳሌ” በመሆን የቀጠሉትን የታመሙ እና አረጋውያንን እንዴት ልናደንቃቸው ይገባናል! አዎን፣ “በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] እንላቸዋለን።” (ያዕቆብ 5:​10, 11) ዛሬ ጉልበታቸው የደከመባቸው ብዙዎቹ አረጋውያን አሁን በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ያሉትን በማስተማሩ፣ በማሠልጠኑና በማስተካከሉ ሥራ ለአሥርተ ዓመታት ተካፍለዋል። ብዙ አረጋውያንም ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ሲገቡ በማየት ይደሰታሉ። — መዝሙር 71:​17, 18፤ 3 ዮሐንስ 4

በተመሳሳይ መንገድም በጠና የታመሙት ነገር ግን ሥቃይም እያለባቸው ቢሆን በታማኝነታቸው ለእኛ ማበረታቻ የሚሆኑትን በመካከላችን ያሉትንም እናደንቃለን። እነዚህ ሳያወላውሉ ተስፋቸውን ሲያረጋግጡ ውጤቱ በጣም የሚያነቃቃና እምነትን የሚያጠነክር ይሆናል። የአእምሮ ሰላምና እርካታቸው በእርግጥ ልንመስለው የሚገባን እምነት እንደሆነ ያሳያል።

በካንሰር፣ በደም መርጋት በሽታ ወይም በሌላ የሰውን ሕይወት ሙሉ በሙሉ በሚለውጥ ሁኔታ በድንገት መያዝ ለአንድ ሰው አስደንጋጭ ነው። ልጆቻቸው ታመው ተኝተው ወይም በአደጋ ምክንያት ሲሠቃዩ ማየትም ለወላጆች ከባድ ፈተና ነው። ሌሎች እርዳታ ለመስጠት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? እንዲህ ያለው የመከራ ጊዜ ለመላው የክርስቲያን ወንድማማችነት ፈተና ነው። ‘እውነተኛ ወዳጅ ለመከራ ጊዜ የሚወለድ ወንድም’ መሆኑን ለማሳየት የሚረዳ አጋጣሚ ነው። (ምሳሌ 17:​17) በግል ከእያንዳንዱ እና ከሁሉም የጉባኤ አባል ድጋፍ ሊጠይቁ የሚችሉት ሁሉም የታመሙና አረጋውያን እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። ነገር ግን ይሖዋ ብዙዎችን በተለያየ አቅጣጫ እንዲረዱ በመንፈሱ ያነሳሣቸዋል። ሽማግሌዎች ማንም ሰው እንዳይረሳ ነቅተው ሊከታተሉ ይችላሉ። — ዘጸአት 18:​17, 18ን ተመልከት።

የሌላውን ችግር ለመረዳት ሞክር

አንድ ሰው ለመርዳት ስትሞክር ጊዜን፣ ትዕግሥትንና ችግሩን እንደ ራስ ማየት የሚጠይቅ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት መኖሩ አስፈላጊ ነው። የምትሄደው ለመርዳት ብለህ እስከሆነ ድረስ በቃላት ለማበረታታት እንደምትፈልግ ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ከመናገር ወይም አንድ ነገር ከማድረግህ በፊት በጥንቃቄ አዳምጥ። አለበለዚያ ‘አድካሚ አጽናኝ’ ልትሆን ትችላለህ። — ኢዮብ 16:​2, 5

የታመሙና አረጋውያን አንዳንድ ጊዜ ብስጭታቸውን መደበቅ አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙታል። ብዙዎቹ እስከ ታላቁ መከራ ድረስ በሕይወት እንቆያለን ብለው በናፍቆት ተስፋ አድርገው ነበር፤ አሁን ግን ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም እንደ ጀመሩ ይታያቸዋል። በዚህም እሽቅድምድም ስለማሸነፋቸው እርግጠኝነት አይሰማቸውም። ብዙ ጊዜም ሁኔታቸው ድካም እንዲሰማቸውና እንዲጓጉ ያደርጋቸዋል። እምነትን ሕያውና ጠንካራ አድርጎ መጠበቁ ያታግላል። ይልቁንም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ የልብን ምኞት መፈጸም የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ሁኔታው ትግልን ይጠይቃል። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ለአንዲት በዕድሜ የገፋች እኅት ጉብኝት አደረገላት፤ ከእርሷ ጋር ሲጸልይም ኃጢአታችንን ይቅር በለን ሲል ይሖዋን ጠየቀ። ጸሎቱን እንዳበቃም እኅት እያለቀሰች እንደነበረ አስተዋለ። ስትናገርም እንደወትሮው ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለመካፈል ባለመቻሏ የይሖዋ ምሕረት እንደሚያስፈልጋት እንደተሰማት ገለጸች። ምንም እንኳ አንድ ሰው ችሎታ ወይም ብቃት የለኝም ብሎ ብዙ ጊዜ አለምክንያት ሊጨነቅ ቢችልም ይህ ስሜቱ ልቡን በጣም ሊያሳዝነው ይችላል።

ጭንቀትና የአካል ድካም የአእምሮን ሚዛን ሊያዛቡ እንደሚችሉ ተገንዘብ። በእርጅና ምክንያት በሚመጡ ድክመቶች ወይም የሚያመነምን በሽታ በሚያስከትለው ውጥረት ምክንያት አንድ ሰው ይሖዋ እንደጣለው ሊሰማውና ምናልባት “ምን ጥፋት ሠራሁኝ? እኔ ላይ ብቻ ለምን ደረሰ?” ሊል ይችላል። የምሳሌ 12:​25ን ቃላት አስታውስ። “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።” ሊያጽናኑ የሚችሉ መልካም ቃላትን ለማግኘት ሞክር። በሥቃይ ላይ ያሉ አረጋውያን እንደ ኢዮብ ለመሞትም እንኳ እንደሚፈልጉ ይናገሩ ይሆናል። ይህ ሊያስደነግጥህ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ ችግሩን ለመረዳት ሞክር። እንደነዚህ ዓይነቶቹ የምሬት አነጋገሮች ሁልጊዜ የእምነት ወይም በአምላክ ላይ ትምክህት የማጣት ምልክት ሊሆኑ አይችሉም። ኢዮብ ‘በሲኦል እንዲሰወር’ ጸልዮ ነበር። ይሁንና ከዚህ አነጋገሩ ቀጥሎ ያሉት ቃላት ይሖዋ በኋላ ሊያስነሣው ስለመቻሉ የነበረውን ጠንካራ እምነት ያሳያሉ። ጠንካራ እምነት መከራንና ጭንቀትን ለማሸነፍና በዚህም ወቅት ቢሆን ከይሖዋ ጋር ተጠግተን እንድንቆይ ያስችለናል። — ኢዮብ 14:​13–15

ለታመሙና ለአረጋውያን አክብሮት ማሳየት

የታመሙትንና አረጋውያንን በአክብሮትና በክብር መያዙ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። (ሮሜ 12:​10) እንደ በፊቱ ፈጠን ብለው ምላሽ ባይሰጡ ወይም መሥራት ባይችሉ ትዕግሥትህ አይለቅ። ጣልቃ ገብተህ የእነርሱን ሥራ ለመፈጸም አትቸኩል። እነርሱን ለመርዳት ብለን ምንም ያህል ብናደርግ የኃይለኝነት ወይም የአዛዥነት ባሕርይ ማሳየታችን ያ ሰው ለራሱ ያለውን ግምት መቀነሱ የማይቀር ነው። በ1988 በታተመ በአንድ ለሕክምና ሙያ ለመመረቅ በተሠራ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ጄት አንገርስለቭ የተባሉ ተመራማሪ በ85 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ሕይወታችን ያማረ እንዲሆን በጣም አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን ነገሮች ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ለሦስት ነገሮች ቅድሚያ ሰጥተዋል። እነዚህም፣ ከዘመዶች ጋር አብሮ መሆን፣ ጥሩ ጤንነት ማግኘትና በመጨረሻም (እርግጥ በአስፈላጊነቱ መጨረሻ ማለት አይደለም) የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ መቻል ነው።” የእስራኤላውያን አባት የነበረው ያዕቆብ ባረጀ ጊዜ ልጆቹ ዝቅ አድርገው አልተመለከቱትም። ከዚህ ይልቅ ፍላጐቶቹ ተከብረውለታል። — ዘፍጥረት 47:​29, 30፤ 48:​17–20

የታመሙትም ቢሆኑ በክብር ሊያዙ ይገባል። አንድ ሽማግሌ የቀዶ ሕክምና ሲደረግለት በተሠራ ስሕተት ምክንያት ለመናገር፣ ለማንበብ እና ለመጻፍ የነበረውን ችሎታ አጣ። ይህ ከባድ ጉዳት ነበር። ሌሎቹ ሽማግሌዎች ግን ራሱን እንደማይጠቅም አድርጎ እንዳይቆጥር ለመጠበቅ ሲሉ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ወሰኑ። አሁን ሁሉንም የጉባኤ ደብዳቤዎች ያነቡለታል። እንዲሁም ስለ ሌሎች የጉባኤ ጉዳዮች እቅድ ሲያወጡ እርሱንም ይጨምሩታል። በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይም የእርሱ ሐሳብ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይሞክራሉ። አሁንም ቢሆን አብሯቸው የሚሠራ ሽማግሌ እንደሆነ አድርገው እንደሚቆጥሩትና በመካከላቸው በመገኘቱ እንደሚደሰቱ ያሳዩታል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ማንም የታመመ ወይም አረጋዊ የሆነ ሰው የተጣለና የተገለለ ሆኖ እንዳይሰማው ሁላችንም ጥረት ለማድረግ እንችላለን።  — መዝሙር 71:​9

መንፈሳዊ ብርታት እንዲያገኙ የሚደረግ እርዳታ

እምነታችንን ሕያውና ጠንካራ አድርጎ ለማቆየት ሁላችንም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በየዕለቱ እንድናነብና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲሁም በስብከቱ እንቅስቃሴ በቅንዓት እንድንካፈል ማበረታቻ የሚሰጠን ለዚህ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የታመሙትና አረጋውያን ይህንን ለማከናወን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ሁኔታቸው የሚፈቅደውን ነገር ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ብዙዎቹ መጓጓዣ ከቀረበላቸውና በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ትንሽ ድጋፍ ከተሰጣቸው በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት መቻላቸው ደስ ይላል። በእንዲህ ዓይነቱ ስብሰባዎች መካፈላቸው ለጉባኤው ትልቅ ማበረታቻ ነው። ጽናታቸውም የሚያነቃቃና እምነትን የሚያጠነክር ነው።

የታመሙና አረጋውያን በብዙ አጋጣሚዎች በክርስቲያናዊ አገልግሎት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዳንዶቹ በመኪና ለምስክርነት ከሚሄድ ቡድን ጋር አብረው ሊሄዱ ይችላሉ። ጥቂት ሰዎችንም ቢሆን ማነጋገር መቻላቸው እንደሚያነቃቃቸው አያጠራጥርም። ይህ የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ለሚያገኟቸው ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመስከር ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። አንዲት በካንሰር በሽታ የተያዘች እኅት የቀረውን የሕይወት ዘመኗን በሙሉ ምሥራቹን ለማስፋፋት ልዩ ጥረት በማድረግ ለማሳለፍ ወሰነች። የእርሷ የድፍረት ምስክርነት ሁሉንም የሚያበረታታ ነበር። የቀብር ስነ ሥርዓቷን እንኳ ሳይቀር ለማያምኑ ዘመዶች፣ የሥራ ባልደረቦችና ጐረቤቶች ጥሩ ምስክርነት ለመስጠት በሚያስችል መንገድ እንዲከናወን እቅድ አወጣች። አስጨናቂ የነበሩት ሁኔታዎቿ “ወንጌልን ለማስፋፋት አስችሏል።” እንዲሁም እምነቷንና ትምክህቷን ለመግለጽ የነበራት ቁርጠኝነት ለሕይወቷ የመጨረሻ ቀኖች ትርጉም ሰጥቶታል። — ፊልጵስዩስ 1:​12–14

የታመሙትንና አረጋውያንን በመንፈሳዊ እንዲበረቱ መርዳት መልካም ነው። ቤተሰቦች አብረው በሚያሳልፉት ምሽት እነርሱም እንዲገኙ ሊጋብዟቸው ወይም የቤተሰብ ጥናታቸውን አልፎ አልፎ ከቤታቸው መውጣት ወደማይችሉት ሰዎች ቤት በመሄድ ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዲት እናት ሁለት ሕፃናት ልጆቿን ማይ ቡክ ኦቭ ባይብል ስቶሪስ የተባለውን መጽሐፍ አብረው እንዲያነቡ ወደ አንድ በዕድሜ የገፋች እኅት ቤት አመጣቻቸው። ይህ በዕድሜ የገፋችውን እኅት አስደሰታት፤ ልጆቹም በትኩረት ስላዳመጠቻቸው ተደሰቱ።

ይሁን እንጂ አካለ ስንኩል የሆኑ ሰዎች ብዙ ግርግር የማይፈልጉበት ጊዜ አለ። በዚህ ወቅት አንድ ነገር ጮኽ ብለን ብናነብላቸው የተሻለ ይሆናል። ምንም እንኳ አንድ ሰው ንግግር ለመለዋወጥ እስከማይችል ድረስ አካሉ የደከመ ቢሆንም መንፈሳዊ ቅርርቦሽ እንደሚያስፈልገውና እንደሚፈልግም አስታውስ። እንደነዚህ ካሉት ጋር አብረን ልንጸልይ፣ ልናነብላቸው ወይም ተሞክሮ ልናካፍላቸው እንችላለን። ከአቅማቸው በላይ ጊዜ እንዳንወስድ ግን መጠንቀቅ ያስፈልገናል።

ያም ሆኖ ግን ሕሙማንና አረጋውያን የሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች ሊያከናውኑት የሚችሉ ቅዱስ አገልግሎት አለ። ይኸውም ስለ ሌሎች መጸለይ ነው። የጥንት ደቀ መዛሙርት ለዚህ አገልግሎት ትልቅ ቦታ ሰጥተዋል። በአንድ ወቅት የጉባኤውን የሥራ ጫና ሐዋርያት በጸሎት ሊተጉ በሚያስችላቸው መንገድ ለሌሎች አከፋፍለዋል። ታማኝ የነበረው ኤጳፍራ ‘ለሌሎች በመጸለይ ከፍተኛ ትጋት’ ማሳየቱ ተጠቅሷል። (ቆላስይስ 4:​12፤ ሥራ 6:​4) የዚህ ዓይነት ጸሎት እጅግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። — ሉቃስ 2:​36–38፤ ያዕቆብ 5:​16

ይሖዋ የታመሙትንና አረጋውያንን ያስታውሳል። እንዲሁም በመከራቸው ጊዜ ይንከባከባቸዋል። እነርሱን ለመርዳትና ለመደገፍ ምን ለማድረግ እችላለሁ ብለን እንድናስብ ይሖዋ ይጠብቅብናል። የምናሳየው አሳቢነት ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል። እንዲሁም የሚከተሉትን የንጉሥ ዳዊት ቃላት ማሰባችን ያስደስተናል:- “የንጹሐንን መንገድ ይሖዋ ያስባል፣ ርስታቸውም ለዘላለም ነው።” — መዝሙር 37:​18

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሰዎችን ችግር ተረድቶ ሊሠራ የሚችል እርዳታ መስጠት

ወዳጆችና ዘመዶች የታመሙትንና አረጋውያንን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው መሠረታዊና ትክክለኛ የሆነ እውቀት ማግኘት ይኖርባቸዋል። ከሁሉም በላይ እነርሱ ለሕይወት ያላቸውን አዎንታዊ አመለካከት ጠብቀው እንዲቆዩ፣ ተፈላጊና ተደናቂ እንደሆኑ እንዲሰማቸውና ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ልናበረታታቸው እንችላለን። ይህ ከተደረገ ሕይወታቸው ጎስቋላ ስለማይሆን ሥቃይና ሕመም ቢኖርባቸውም በይሖዋ ላይ ያላቸውን ደስታ ጠብቆ የሚያቆይላቸው ይሆናል። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ረጅም ዕድሜ እንደሚኖሩ ታይቷል። ለዚህ ሁኔታ ኃይለኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ከፊታቸው ላለው ተስፋ የማይቀንስ ፍላጎት ስለሚኖራቸው፣ ብሩኅ የሆነው የአእምሮ አመለካከታቸውና በተቻላቸው ሁሉ በመንግሥቱ የሥራ እንቅስቃሴዎች መሳተፋቸው እንደሆነ አያጠራጥርም። አስደሳችና ፍሬያማ ሕይወት ካሳለፈ በኋላ በ100ኛ ዓመቱ በሰላም ያረፈው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ፍሬድሪክ ደብሊው ፍራንዝ ለዚህ በጣም ግሩም ምሳሌ ነው።—ከ1 ዜና መዋዕል 29:28 ጋር አወዳድር።

በአጠቃላይ ለሚከተሉት የዕለታዊ እንክብካቤ መሠረታዊ ጉዳዮች ትኩረት መስጠቱ ትልቅ ጥቅም ሊያመጣ ይችላል። ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ፣ ተገቢ የአመጋገብ ሥርዓት፣ በቂ የፈሳሽና የጨው መጠን፣ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ ንጹሕ አየር፣ በቀስታ ሰውነትን ማሸት እና የሚያነቃቁ ውይይቶች ናቸው። ተገቢ የአመጋገብ ሥርዓት መኖሩ በተሻለ ሁኔታ ለመስማት፣ ለማየት፣ አእምሮን ለማሠራትና ጥሩ የሰውነት አቋም እንዲኖር እንዲሁም በሽታን በደንብ ለመቋቋም ያስችላል። ቀላል የሆነውን የአመጋገብ ሥርዓት መጠበቅና ብዙ ፈሳሽ መውሰድ ለአረጋዊ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ በመቆየታቸውና በመጃጃታቸው መሀከል ያለውን ልዩነት ሊያመጣ የሚችል ነው። ለግለሰቡ የሚስማማ የአካል እንቅስቃሴ ማግኘት ጥቂት ማሰብን ይጠይቅ ይሆናል። በዕድሜ ለገፋችና ዓይኗ ማየት ለተሳናት እኅት ልታነብላት የምትመጣ አንዲት እኅት በየሳምንቱ ጉብኝቷን ስትጀምር እንዲሁም ስትጨርስ ክፍሉን እየዞሩ ቀስ ብለው አብረው ይደንሳሉ። ሙዚቃው ተመርጦ ቴፑ ሁልጊዜ ይዘጋጃል። ከዚያ ሁለቱም በዚህ “የአካል እንቅስቃሴ“ ይዝናናሉ።

በብዙ አገሮች እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ተግባራዊ የሚሆኑ ጠቃሚ እርዳታዎችን ሊሰጡ ይችላሉ። እንዲሁም በአንድ አቅጣጫ ላይ ያተኮረና ችግሮቹን እንዴት መወጣት እንደሚቻል የሚጠቁም መረጃና ምክርም ይሰጣሉ። (በእርግጥ አንድ ክርስቲያን ከእውነተኛ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ሊያዘናጉ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይወሰድ መጠንቀቅ አለበት።) አንዳንድ ጊዜ እርዳታቸው የሆስፒታል ዓይነት አልጋ በማዋስ፣ እግርን ለመደገፍ በሚረዱ መሄጃዎች፣ በምርኩዞች፣ በተሽከርካሪ ወንበሮች፣ በመስሚያ መርጃ መሣሪያዎች እና በመሳሰሉት መልክ ሊሆን ይችላል። ብዙ አረጋውያን ምንም ነገር እንደማያስፈልጋቸው ወይም እንደነዚህ ያሉት አዳዲስ ነገሮችን ማግኘቱ ዋጋ እንደሌለው ሊሰማቸው ስለሚችል ዘመዶቻቸው አብዛኛውን ጊዜ ጤናማ ምክር መስጠት ወይም ማግባባት ያስፈልጋቸዋል። የመታጠቢያ ቤቱን በር ለእነርሱ የሚያመች እጀታ ብታስገቡለት ሽታው የሚያውድ እቅፍ አበባ ከማምጣት የበለጠ ደስታ ያመጣላቸዋል።

አረጋውያንን መንከባከብ በተለይም ጃጅተው ከሆነ ታላቅ የአእምሮ ጭንቀት ያስከትላል። አብዛኛውን ጊዜ መጃጃት የሚመጣው ቀስ ብሎና ሳይታወቅ ነው። አንድ ሰው ይህ እንዳይሆን ለመከላከል ሊሞክር የሚችለው ሕመምተኛው ሳያስፈልግ ሥራ ፈትቶ እንዳይቀመጥ ወይም በዝምታ እንዳይዋጥ ጥረት በማድረግ ነው። አንድ የጃጀ ሰው በጣም ይወደው በነበረ ሰው በቀላሉ ሊቀየም ይችላል። ያረጀ ሰው ከእውነት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች እንኳ ሊረሳ እንደሚችል ዘመዶቹ መገንዘብ አለባቸው፤ ይህም ከአካላዊ ድካም የሚመጣ አሳዛኝ ውጤት እንጂ የእምነት ማጣት አይደለም።

ታማሚው ያለው በሆስፒታል ወይም በእንክብካቤ መስጫ ጣቢያዎች ከሆነ የሠራተኞቹ አባላት የልደት በዓልን፣ ገናን ወይም ሌሎች ዓለማዊ በዓላትን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ከሠራተኞቹ ጉዳይ ኃላፊ ጋር መነጋገሩ አስፈላጊ ነው። ቀዶ ሕክምናም አስፈላጊ ከሆነ ዘመዶቹ በደም ጥያቄ ላይ ታማሚው ያለውን አቋም የሚገልጽ ሰነድ በማቅረብ ማስረዳት ይችላሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ