አንተን የሚመራህ መሠረታዊ ሥርዓት ነው ወይስ ሰው እንደሆነው መሆን?
የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ኖረሂቶ በአንድ የስፖርት ዝግጅት ላይ ተካፋይ ነበር። ድንገት አንድ ውሳኔ ማድረግ ያለበት ሁኔታ ገጠመው። ተማሪዎቹ ሁሉ በአንድ ዓይነት የብሔራዊ ስሜት መግለጫ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲካፈሉ ተጠየቁ። በዚህ የተለመደ በሚመስል የአካል እንቅስቃሴ ተማሪ የሆኑ ጓደኞቹን ይተባበራል ወይስ ምን ያደርጋል?
ኖረሂቶ ከይሖዋ በስተቀር ለማንኛውም ጣዖት አምልኮ ማቅረብ ስሕተት መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሯል። (ዘጸአት 20:4, 5፤ ማቴዎስ 4:10) ክርስቲያኖች በሁሉም የፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኞች መሆን እንዳለባቸውም ያውቃል። (ዳንኤል 3:1–30፤ ዮሐንስ 17:16) ስለዚህ ምንም እንኳ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ አብሯቸው በሥነ ሥርዓቱ እንዲሳተፍ ቢገፋፉትም በአክብሮትና በድፍረት በአቋሙ ጸና። ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?
ከሰው ያለመነጠል ምኞት
ሰዎች በአምላክ የተፈጠሩት ተግባቢዎች እንዲሆኑ፣ እርስ በርሳቸው ተስማምተው እንዲኖሩና አብረው አንዳንድ ነገሮችን በመሥራት እንዲደሰቱ መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች ይነግሩናል። ሰው ከእኩዮቹ ጋር አብሮ እንዲውል፣ እንደ እነርሱ እንዲሆንና እነሱን ለመምሰል የመፈለግ ምኞቱ በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። እንደነዚህ ያሉት ስሜቶች ሕይወትን አስደሳች ለማድረግና ከሌሎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ለሰላምና ተስማምቶ ለመኖር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። — ዘፍጥረት 2:18፤ መዝሙር 133:1፤ 1 ጴጥሮስ 3:8
ከሰዎች ላለመነጠል ያለው ተፈጥሮአዊ ምኞት ዛሬም እንኳ በአንዳንድ ባሕሎች በጣም ጎልቶ ይታያል። ለምሳሌ ያህል ጃፓናውያን ልጆች አብዛኛው ሰው የሚያደርገውን ነገር ነቅተው እንዲመለከቱና ያንኑ እንዲያደርጉ ገና ከልጅነታቸው ማሠልጠኛ ይሰጣቸዋል። የወረሱት ነገር የሚያስተምራቸው ትልቁ ግዴታ ከማኅበረሰቡ አለመነጠልን ነው። “ጃፓናውያን ከምዕራባውያን ይልቅ በሕብረት አንድን ነገር የመሥራት ባሕርይ ይታይባቸዋል” በማለት በጃፓን ቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና የጃፓናውያንን ባሕል በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩት ኤድዊን ሬስቻወር ተናግረዋል። ጨምረውም:- “ብዙዎቹ ምዕራባውያን በራስ የመመራትን መንፈስ ሲያሳዩና ግላዊ አመለካከትን ሲያስቀድሙ አብዛኛዎቹ ጃፓናውያን ግን በአለባበስ፣ በጠባይ፣ በኑሮ ዘይቤና ቡድኑ ባለው የአስተሳሰብ መንገድ አብሮ መጓዝ ያስደስታቸዋል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ተመሳስሎ የመኖር ምኞት የጃፓናውያን ጠባይ ብቻ አይደለም። የትም ቦታ የሚገኝ ነው።
ተመሳስሎ የመኖር ግፊት
ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር አንድ ሰው የሚችለውን ለማድረግ ቢመኝም በሰዎች ዘንድ የተለመዱ ናቸው የሚባሉትን ነገሮች በጭፍን መቀበሉ አደጋ አለው። ለምን? በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር አብዛኛውን ጊዜ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ካለው ነገር ጋር ይጋጫል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙም በሞላው በክፉው እንደተያዘ እናውቃለን” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን መሠሪ በሆነ መንገድ ፍቅረ ንዋይን፣ ወራዳ ሥነ ምግባርን፣ የዘር ኩራትን፣ የተሳሳተ ሃይማኖታዊ ቀናተኝነትን፣ ብሔራዊ ስሜትንና የመሳሰሉትን ዘዴዎች በመጠቀም ብዙኃኑን ከአምላክ ለማራቅ ተጽእኖ ያሳድራል። ከእነዚህ ድርጊቶች ጋር መስማማቱ አንድን ሰው ይሖዋንና ዓላማውን እንዲቃወም ያደርገዋል። ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ተብለው የተመከሩትም ለዚህ ነው:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” — ሮሜ 12:2
ክርስቲያኖች በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ሲኖሩ በአካባቢው ከተለመደው ነገር ጋር እንዲስማሙ የማያቋርጥ ግፊት ይደርስባቸዋል። በተለይ ወጣቶች ለዚህ ዓይነቱ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው። እንደ ትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው የመሆን ወይም የማድረግ ምኞታቸው በጣም ኃይለኛ ነው። በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለምን እንደማይካፈሉ ለእኩዮቻቸው ማስረዳት ትልቅ ድፍረት ይጠይቅባቸዋል። አቋማቸውን ለማስረዳት ካልቻሉ ግን መንፈሳዊ ውድቀት ሊደርስባቸው ይችላል። — ምሳሌ 24:1, 19, 20
ትልልቆችም ቢሆኑ በሚሠሩበት ቦታ እንደነዚህ ያሉ ግፊቶች ሊደርሱባቸው ይችላሉ። ከሥራ ሰዓት በኋላ በአንዳንድ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ወይም በአንዳንድ በዓሎች እንዲካፈሉ ይጠብቁባቸው ይሆናል። ከዚህ ሁኔታ ጋር አለመስማማታቸው ቸልተኞችና የማይተባበሩ ሊያስመስላቸውና በሥራ ቦታቸው ላይ ደስ የማይል ሁኔታን ሊፈጥር ይችል ይሆናል። ሌሎች ስላደረጉትና ከእነርሱም የሚጠበቅ ነገር አድርገው ስለተመለከቱት ብቻ አንዳንዶች ትርፍ ሰዓት መሥራት እንዳለባቸው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። እንደዚህ ለመሰለው ነገር መሸነፍ በመንፈሳዊ ሊጎዳቸውና ሌሎች ግዴታዎቻቸውን እንዳይወጡ ሊያግዳቸው ይችላል። — 1 ቆሮንቶስ 15:33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6–8
ተመሳስሎ የመኖር ተጽእኖ የሚደርሰው በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ ላይ ብቻ አይደለም። አንዲት ክርስቲያን እናት በአንድ ወቅት ልጅዋ መቀጣት በጣም የሚያስፈልገው ሆኖ ብታገኘውም በዚያ የነበሩት ሌሎች የቤት እመቤቶች ደስ ላይላቸው ይችላል በማለት ብቻ ልጅዋን ከመቅጣት ወደኋላ እንዳለች ተናግራለች። — ምሳሌ 29:15, 17
ብዙኃኑ ሊሳሳቱ ይችላሉ
ብዙ ሰዎችን መከተልን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ የሆኑ ብዙ ምክሮች ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል የእስራኤል ሕዝብ “ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር” ተብሎ ተነግሯቸዋል። (ዘጸአት 23:2፤ ከሮሜ 6:16 ጋር አወዳድር።) ይህ ምክር ሁልጊዜ አልተሠራበትም ነበር። አንድ ጊዜ፣ ግብጽን ለቀው እንደወጡ፣ ሙሴ በሌለበት አንዳንድ ሰዎች አሮንንና ሕዝቡን ገፋፍተው የወርቅ ጥጃ ከሠሩ በኋላ ‘የይሖዋ በዓል ነው’ ብለው አመለኩት። ሕዝቡ ለወርቁ ጥጃ መሥዋዕት አቅርበው በሉና ጠጡ በዘፈንና በጭፈራም ተደሰቱ። ለዚህ ቅጥ የለሽ የጾታ ብልግናቸውና የጣዖት አምልኮአቸው 3,000 የሚያህሉ ቀንደኛ መሪዎች ተገደሉ። ሌሎቹ ብዙ ሰዎችም ቢሆኑ ሳያመዛዝኑ ብዙኃኑን በመከተላቸው ምክንያት ይሖዋ አጥፍቷቸዋል። — ዘጸአት 32:1–35
ክፉ ለማድረግ ብዙ ሰዎችን ስለመከተል የሚጠቀሰው ሌላ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኢየሱስ ክርስቶስ መገደል ጋር የተያያዘው ነው። ብዙው ሕዝብ በምቀኞቹ የሃይማኖት መሪዎች ተገፋፍቶ በኢየሱስ መገደል ተባብሯል። (ማርቆስ 15:11) ከኢየሱስ ትንሣኤና እርገት በኋላ ጴጥሮስ የሠሩትን ትልቅ ስሕተት ባስገነዘባቸው ጊዜ ብዙዎቹ “ልባቸው ተነካ” ብዙኃኑን ተከትለው ያደረጉትን ነገር ተገነዘቡ። — ሥራ 2:36, 37
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ይሻላል
ከእነዚህ ታሪኮች እንደምንማረው በአካባቢው የተለመደውን ነገር በጭፍን መከተል ወደ ከባድ ችግሮች ሊያመራ ይችላል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን መከተልና መሠረታዊ ሥርዓቶቹም ሕይወታችንን እንዲመሩት ማድረጉ አይሻልምን? “ሰማይ፤ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” ይላል ይሖዋ። (ኢሳይያስ 55:9) ሥነ ምግባርንና ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ብዙኃኑን ከመከተል ይልቅ የይሖዋን መንገዶች መከተሉ እንደሚያዋጣ ተደጋግሞ በተጨባጭ ታይቷል። ለበለጠ ደስታና ለተሻለ አኗኗር ቁልፉ ይህን ማድረጉ ነው።
ለምሳሌ ካዙያ ያጋጠመውን እንውሰድ። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ለጥቂት ጊዜያት ቢያጠናም በብዙዎች ዘንድ የተለመደውን የአኗኗር መንገድ መከተሉን ቀጠለ። ይህም ሀብትና ሥልጣንን ለማግኘት መጣጣርን ይጨምር ነበር። አለቆቹን ለማስደሰትና በሥራ ጓደኞቹ ተወዳጅነትን ለማግኘት የነበረው ፍላጎት እስኪነጋ ድረስ አብሯቸው ያለልክ እንዲጠጣ አደረገው። ጨቅጫቃ፣ ነጭናጫና ቁጡ ሆነ። ቅጥ የሌለው ይህ ኑሮው በደም ግፊት መብዛት ምክንያት ደም በአንጎሉ ውስጥ በመፍሰሱ ግማሽ ጎኑ ሽባ እንዲሆን አደረገው። በሆስፒታል ተኝቶ በሚያገግምበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተማራቸው ነገሮችና እንዴት ሕይወቱን ይመራ እንደነበረ ለማሰብ ጊዜ አገኘ። የተማርኩትን በሥራ ላይ ማዋል ያለብኝ ጊዜ አሁን ነው ብሎ ወሰነ። የሥራ አስኪያጅነት ቦታውን በፈቃዱ ለመልቀቅ ጠየቀና ጓደኞቹን ለወጠ። ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለመልበስ ልባዊ ጥረት አደረገና ለቁሳዊ ሀብት የነበረውን አመለካከት ለወጠ። ከዚህም የተነሣ የሚመራባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለወጠ፣ ጤንነቱም ተሻሻለ። በመጨረሻም ሕይወቱን ለይሖዋ ወሰነና ተጠመቀ።
አንድ ሰው ብዙ ሰዎች የማይከተሉትን መንገድ ተከትሎ የተሳካ ውጤት ለማግኘት እንዲችል ለጉዳዩ የሚሠሩትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማወቅና ትክክል ናቸው ብሎ ማመን ያስፈልገዋል። ማሳሩ ያሳለፈው ሕይወት ይህንን ያስገነዝባል። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጊዜ በክፍል ጓደኞቹ ለተማሪዎች መማክርት ፕሬዘዳንትነት እጩ ሆኖ ቀረበ። ከዚህ ጋር የተያያዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በደንብ ስላልተረዳቸው በፖለቲካ መድረክ ውስጥ ለምን እንደማይካፈል ለክፍል ጓደኞቹ ለመግለጽ ባለመቻሉ ግራ እንደተጋባ ያስታውሳል። ሰውን መፍራቱ ክርስቲያን መሆኑን ገልጾ እንዳይናገር አግዶት ነበር። ማድረግ የቻለው ነገር ራሱን እየነቀነቀና እያለቀሰ “አልችልም!” እያለ ደጋግሞ መናገር ብቻ ነበር።
ይህ ሕሊናን የሚያሠቃይ ተሞክሮ አንድ ክርስቲያን በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለምን እንደማይካፈል የሚያሳዩትን ምክንያቶች እንዲመረምር አደረገው። (ከዮሐንስ 6:15 ጋር አወዳድር።) በኋላም በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጠመው። በዚህ ጊዜ ግን አቋሙን ለአስተማሪው በእርግጠኝነት ማስረዳት ችሎ ነበር። ጥቂት የክፍል ጓደኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረተው እምነቱ ላቀረቡለት ጥያቄ በሰጣቸው ማብራሪያ እንደተስማሙ ሁሉ አስተማሪውም ተስማማ።
ሁሉም ሰው ትክክለኛ የሆነውን የሚያደርግበት ጊዜ
በክርስቶስ በሚገዛው አዲስ ዓለም ውስጥ ሁሉም ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ትክክለኛ የሆነውን ነገር ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን በብዙዎች ዘንድ የተለመደውን እንድናደርግ ከሚደርስብን ውትወታ መጠንቀቅ አለብን። ከሚቀጥለው የጳውሎስ ምክር ማበረታቻ ልናገኝ እንችላለን:- “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ . . . በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።” — ዕብራውያን 12:1
የአቋም ጥያቄዎችና ፈተናዎች ሲያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ? በሰው ፍርሃት ወጥመድ ተሸንፈህ በሰዎች ዘንድ የተለመደውን ታደርጋለህ? ወይስ ወደ አምላክ ቃል ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር በማለት መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ትከተላለህ? የመጽሐፍ ቅዱስን መንገድ መከተሉ ለአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ‘በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል ከሚወርሱት’ መካከል የመሆን ተስፋ ይሰጥሃል። — ዕብራውያን 6:12