ለጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ቁልፍ የሆነውን ነገር ማግኘት
“ ለአምላክ ያደሩ በመሆን ላይ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድን ጨምሩ።” — 2 ጴጥሮስ 1:5–7 አዓት
1. የይሖዋ ሕዝቦች ስብሰባዎች የሚያስደስቱ ወቅቶች ከሆኑበት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ምንድን ነው?
የይሖዋ ምስክር ያልነበሩ አንድ ሐኪም በአንድ ወቅት ሴት ልጃቸው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚስዮናዊነት ሥልጠና ወስዳ በምትመረቅበት ጊዜ ተገኝተው ነበር። በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኙት ደስተኛ ተሰብሳቢዎች በጣም ከመገረማቸው የተነሳ በእነዚህ ሕዝቦች መካከል እምብዛም መታመም እንደማይኖር ገመቱ። እነዚያን በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ተሰብሳቢዎች ደስተኛ ያደረጋቸው ምን ነበር? ይህ ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ሕዝቦች በጉባኤዎች፣ በክልል ስብሰባዎችና በወረዳ ስብሰባዎች የሚያደርጓቸውን ሁሉንም ስብሰባዎች አስደሳች ወቅቶች የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? እርስ በርስ የሚያሳዩት የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ አይደለምን? የይሖዋ ምስክሮችን ያህል ከሃይማኖቱ ብዙ ደስታ የሚያገኝ ሌላ ሃይማኖታዊ ቡድን የለም የተባለበት ምክንያት የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
2, 3. እርስ በርሳችን እንዴት ዓይነት ስሜት ሊኖረን እንደሚገባ የሚገልጹ ምን ሁለት የግሪክኛ ቃላት ናቸው? እነዚህን የግሪክኛ ቃሎች አንዱን ከሌላው የሚለያቸው ልዩ ባሕሪያቸውስ ምንድን ነው?
2 ሐዋርያው ጴጥሮስ በ1 ጴጥሮስ 1:22 ላይ ከተናገራቸው ቃላት አንጻር እንዲህ ዓይነቱ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ መገለጽ አለበት ብለን ብንጠብቅ ትክክል ይሆናል:- “ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ [ለጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ አዓት] ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።” እዚህ ላይ “የወንድማማች መዋደድ (የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ)” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንዱ መሠረታዊ ትርጉም ፊሊያ (በእንግሊዝኛ አፌክሽን) ነው። ፍቺውም ብዙውን ጊዜ “ፍቅር” ተብሎ ከሚተረጎመው አጋፔ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ጋር የቅርብ ዝምድና አለው። (1 ዮሐንስ 4:8) የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ [ብራዘርሊ አፌክሽን]ና ፍቅር ብዙውን ጊዜ በማለዋወጥ የሚሠራባቸው ሲሆን የሚለያዩበት የተወሰነ ባሕሪ አላቸው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች እንደሚያደርጉት ትርጉማቸውን በማደናገር አንድ እንደሆኑ አድርገን ማሰብ የለብንም። (በዚህኛውና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ቃላት አንድ በአንድ እናብራራለን።)
3 በሁለቱ ግሪክኛ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተ አንድ ምሁር ፊሊያ “ግለትንና የጠበቀ መቀራረብን እንዲሁም ሞቅ ያለ የመዋደድ ስሜትን የሚያመለክት ቃል መሆኑ የማያጠያይቅ” መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ (አጋፔ ) ይበልጡን ከአእምሮ ጋር ግንኙነት ያለው ቃል ነው። በዚህ መሠረት ጠላቶቻችንን እንድንወድ (አጋፔ ) እንድናሳይ ታዘናል። ይሁን እንጂ ለእነርሱ የጠበቀ የመውደድ ስሜት የለንም። ለምን? ምክንያቱም “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” (1 ቆሮንቶስ 15:33) በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ “በጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ላይም ፍቅርን ጨምሩ” ያላቸው ቃላት በሁለቱ ቃላት መካከል ልዩነት መኖሩን ያመለክታሉ። — 2 ጴጥሮስ 1:5–7፤ ከዮሐንስ 21:15–17 ጋር አወዳድር።a
በጣም ልዩ ለሆነ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ የሚጠቀሱ ምሳሌዎች
4. ኢየሱስና ዮሐንስ እርስ በርሳቸው ልዩ መዋደድ የነበራቸው ለምን ነበር?
4 የአምላክ ቃል በጣም ልዩ ለሆነ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ በርካታ ጥሩ ምሳሌዎችን ይሰጠናል። ይህ ልዩ የሆነ የጠበቀ መዋደድ በአንድ ዓይነት የስሜት ግንፋሎት የሚመጣ ሳይሆን የላቁ ባሕሪያትን በማድነቅ ላይ የተመሠረተ ነው። በሠፊው የሚታወቅ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያው ዮሐንስ የነበረው የጠበቀ የመውደድ ስሜት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ለሁሉም ሐዋርያቱ የጠበቀ ወንድማዊ ፍቅር እንደነበረው አጠያያቂ አይደለም፣ ለዚህም በቂ ምክንያት ነበረው። (ሉቃስ 22:28) ይህን ወንድማዊ ፍቅር ያሳየበት አንዱ መንገድ እግራቸውን በማጠብ ሲሆን በዚህ መንገድም ስለ ትሕትና ትምህርት ሰጥቶአቸዋል። (ዮሐንስ 13:3–16) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለዮሐንስ ልዩ የሆነ የመውደድ ስሜት ነበረው። ይህንንም ዮሐንስ በተደጋጋሚ ጠቅሶታል። (ዮሐንስ 13:23፤ 19:26፤ 20:2) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱና ለሐዋርያቱ የጠበቀ የመውደድ ስሜት እንዲያሳይ የሚያበቁ ምክንያቶች እንደነበሩት ሁሉ ዮሐንስም ለኢየሱስ ጥልቅ አድናቆት በማሳየት ኢየሱስ ለእርሱ ልዩ የመውደድ ስሜት እንዲኖረው የበለጠ ምክንያት ሳይሰጠው አልቀረም። ይህንንም ከዮሐንስ ጽሑፎች ይኸውም ከወንጌሉና በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎቹ ለመረዳት እንችላለን። በእነዚህ ጽሑፎቹ ላይ ዮሐንስ ስለ ፍቅር ምን ያህል ደጋግሞ አውስቷል! ዮሐንስ ለኢየሱስ መንፈሳዊ ባሕርያት ከሌሎቹ ሐዋርያት የላቀ አድናቆት እንደነበረው በዮሐንስ ምዕራፍ 1 እና ምዕራፍ 13 እስከ 17 በጻፋቸው ላይ፣ እንዲሁም ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ስለነበረው ሕልውና በተደጋጋሚ ከጠቀሰው ለማየት ይቻላል። — ዮሐንስ 1:1–3፤ 3:13፤ 6:38, 42, 58፤ 17:5፤ 18:37
5. ጳውሎስና ጢሞቴዎስ እርስ በርሳቸው ስለነበራቸው ልዩ የመዋደድ ስሜት ምን ለማለት ይቻላል?
5 በተመሳሳይም በሐዋርያው ጳውሎስና በክርስቲያን ባልደረባው በጢሞቴዎስ መካከል የነበረውን ልዩ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ሳንጠቅስ ለማለፍ አንፈልግም። በመካከላቸው የነበረው ልዩ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ የተመሠረተው አንዱ የሌላውን መልካም ባሕርይ በመውደድ ላይ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። የጳውሎስ ጽሑፎች ስለ ጢሞቴዎስ “እንደ እርሱ ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፣ ማንም የለኝምና፤ . . . ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ” በማለት የጻፈውን የመሰሉ ጥሩ አስተያየቶች ይዘዋል። (ፊልጵስዩስ 2:20–22) ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ደብዳቤዎች ላይ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ያለውን የሞቀ የመውደድ ስሜት የሚገልጹ አባባሎች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ጢሞቴዎስ ሆይ፣ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ” የሚለውን 1 ጢሞቴዎስ 6:20ን ተመልከት። (በተጨማሪም 1 ጢሞቴዎስ 4:12–16፤ 5:23፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15ን ተመልከት።) በተለይም ደግሞ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈለትን ደብዳቤ ለቲቶ ከጻፈው ደብዳቤ ጋር ማወዳደር ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የነበረውን ልዩ የመውደድ ስሜት ያጎላል። ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 1:3, 4 ላይ “ሌትና ቀን በልመናዬ ስለ ማስብህ . . . እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ” በማለት ከጻፋቸው ቃላት ለመረዳት እንደምንችለው ጢሞቴዎስም ከጳውሎስ ጋር ስለነበረው ወዳጅነት የነበረው ስሜት እንደ ጳውሎስ እንደነበረ ግልጽ ነው።
6, 7. ዳዊትና ዮናታን እርስ በርሳቸው ምን ስሜት ነበራቸው? ለምንስ?
6 የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችም የዳዊትንና የዮናታንን የመሰሉ ጥሩ ምሳሌዎችን ይዘውልናል። ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ “የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች። ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው” የሚል ቃል እናነባለን። (1 ሳሙኤል 18:1) ዮናታን ለዳዊት ልዩ የመውደድ ስሜት እንዲኖረው ያደረገው ዳዊት ለይሖዋ ስም ባሳየው የቅንዓት ምሳሌነቱና ግዙፉን ጎልያድን ለመግጠም ሲሄድ ባሳየው ድፍረት ያደረበት አድናቆት መሆኑ አያጠራጥርም።
7 ዮናታን ዳዊትን አጥብቆ ይወደው ስለነበር ንጉሥ ሳኦል እንዳይገድለው በራሱ ሕይወት ቆርጦ ተከላክሎለታል። ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል በኋላ ንጉሥ እንዲሆን በይሖዋ በመመረጡ ዮናታን ቅር የተሰኘበት ጊዜ የለም። (1 ሳሙኤል 23:17) ዳዊትም ዮናታን በሞተ ጊዜ ከጻፈው ሙሾ ለመረዳት እንደምንችለው ለዮናታን ከዚያ ያላነሰ ጥልቅ የመውደድ ስሜት ነበረው:- “ወንድሜ ዮናታን ሆይ፣ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ።” በእርግጥም አንዱ ለሌላው የነበራቸው ጥልቅ አድናቆት የወዳጅነታቸው ዓይነተኛ ገጽታ ነበር። — 2 ሳሙኤል 1:26
8. እርስ በርሳቸው ልዩ የመውደድ ስሜት የነበራቸው ሁለት ሴቶች እነማን ናቸው? ለምንስ?
8 በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሁለት ሴቶች ማለትም በናኦሚና ባሏ በሞተባት ምራቷ በሩት መካከል የታየው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ልዩ መዋደድ ተገልጾልናል። ሩት ለናኦሚ “ወደምትሄጂበት እሄዳለሁና፣ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” ያለቻትን አስታውሱ። (ሩት 1:16) ናኦሚ ከሩት ይህን አድናቆት የተሞላበት ምላሽ ያገኘችው በጠባይዋና ስለ ይሖዋ በመናገሯ ነው ብለን መደምደም አይገባንምን? — ከሉቃስ 6:40 ጋር አወዳድር።
የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌነት
9. ጳውሎስ የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜትን በማሳየት ረገድ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን ምን ያሳያል?
9 ቀደም ብለን እንዳየነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ልዩ የሆነ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ነበረው። ይሁን እንጂ ለክርስቲያን ወንድሞቹ ባጠቃላይ የሞቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት በማሳየት በኩል ግሩም ምሳሌ ትቷል። ከኤፌሶን ወደ እርሱ መጥተው ለነበሩት ሽማግሌዎች ‘ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳቸውን ከመገሠጽ እንዳላቋረጠ’ ነግሯቸዋል። ታዲያ ይህ የጋለ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት አይደለምን? ምንም አያጠያይቅም! እነርሱም ስለ ጳውሎስ የተሰማቸው እንዲሁ ነበር። ዳግመኛ እንደማያዩት ሲነግራቸው “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፣ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር።” (ሥራ 20:31, 37) በአድናቆት ላይ የተመሠረተ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ነበርን? አዎን! በተጨማሪም የጳውሎስ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት በ2 ቆሮንቶስ 6:11–13 ላይ እንደሚከተለው በማለት ከጻፈው ሊታይ ይቻላል:- “እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፣ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤ በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤ ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን እላችኋለሁ፣ እናንተ ደግሞ ብድራት መልሳችሁልን ተስፋፉ።”
10. ጳውሎስ ስለደረሱበት መከራዎች በ2 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 11 ላይ ለመዘርዘር የተገደደው ምን የወንድማዊ መዋደድ ጉድለት አጋጥሞት ስለነበረ ነው?
10 በግልጽ እንደሚታየው ብዙዎቹ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለሐዋርያው ጳውሎስ ከአድናቆት የመነጨ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ጎድሏቸው ነበር። በመሆኑም አንዳንዶቹ “መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፣ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” በማለት አጉረምርመውበታል። (2 ቆሮንቶስ 10:10) በ2 ቆሮንቶስ 11:5, 22–33 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ጳውሎስ ‘ስለተራቀቁት ሐዋርያት’ ከጠቀሰ በኋላ በትዕግሥት ስለተቋቋማቸው መከራዎች ለመናገር የተገደደው በዚህ ምክንያት ነበር።
11. ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩት ክርስቲያኖች የነበረውን የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት በሚመለከት ምን ማስረጃ አለ?
11 ጳውሎስ ላገለገላቸው ሰዎች የነበረው የጋለ የመውደድ ስሜት በተለይ በ1 ተሰሎንቄ 2:8 ላይ እንደሚከተለው ተገልጾአል:- “እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።” እንዲያውም ለእነዚህ አዳዲስ ወንድሞች ከነበረው የጠበቀ የመውደድ ስሜት የተነሳ ስለደህንነታቸው ሳይሰማ መቆየት አላስቻለውም ነበር። የደረሰባቸውን ስደት እንዴት እየተቋቋሙት እንዳሉ ለማወቅ በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ ጢሞቴዎስን ልኮት ነበር። እርሱም ይዞለት የመጣው ጥሩ ሪፖርት ጳውሎስን በጣም አጽናንቶታል። (1 ተሰሎንቄ 3:1, 2, 6, 7) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ “በጳውሎስና ባገለገላቸው ሰዎች መካከል የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት የሰፈነበት ጥብቅ ትስስር ነበረ” ሲል ጥሩ አድርጎ ገልጾታል።
አድናቆት ለጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ቁልፍ ነው
12. ለወንድሞቻችን የሞቀ የመውደድ ስሜት የምናሳይባቸው ምን ምክንያቶች አሉን?
12 ያለጥርጥር ለጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ቁልፍ የሆነው ነገር አድናቆት ነው። የይሖዋ ውስን አገልጋዮች ሁሉ የመውደድ ስሜታችንን የሚቀሰቅሱ፣ እንድንወዳቸው የሚያደርጉን ተደናቂ ባሕሪያት ያላቸው አይደሉምን? ሁላችንም የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን አስቀድመን የምንፈልግ ነን። ሁላችንም በሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን ይኸውም ሰይጣንና አጋንንቱ፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ክፉው ዓለም፣ እና በውርስ ያገኘናቸው የውዳቂው ሥጋችን ራስ ወዳድ ዝንባሌዎች ላይ ከባድ ውጊያ እያካሄድን ነው። ወንድሞቻችን ከሁኔታዎቻቸው አንጻር አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ናቸው የሚል አቋም ሁልጊዜ መያዝ የለብንምን? በምድር ላይ ያለው ማንኛውም ሰው አንድም ከይሖዋ ጎን አለዚያም ከሰይጣን ጎን የቆመ ነው። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በይሖዋ ጎን፣ አዎን፣ በጎናችን የቆሙ ስለሆኑ የጠበቀ ወንድማዊ መውደድ ልናሳያቸው የሚገባቸው ናቸው።
13. ለሽማግሌዎች የሞቀ የመውደድ ስሜት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
13 ሽማግሌዎቻችንንስ ልናደንቃቸው አይገባንምን? ለጉባኤው ጥቅም ሲሉ ከሚደክሙት አንጻር በልባችን ውስጥ ለእነርሱ ሞቅ ያለ የመውደድ ስሜት ሊኖረን አይገባንምን? እነርሱም እንደማንኛችንም ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መተዳደሪያ ሠርተው ማቅረብ አለባቸው። እነርሱም እንደተቀረነው ክርስቲያኖች የግል ጥናት የማድረግ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች የመገኘትና በመስክ አገልግሎት የመካፈል ግዴታ አለባቸው። በተጨማሪም ለስብሰባዎች የሚሆኑትን የፕሮግራም ክፍሎች የማዘጋጀት፣ የሕዝብ ንግግር የመስጠትና በጉባኤው ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሰዓት ቁጭ ብለው ማዳመጥን የሚጠይቁ የፍርድ ጉዳዮችን የመስማት ግዴታ አለባቸው። በእርግጥም ‘እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች በክብር መያዛችንን’ ልንቀጥልበት እንፈልጋለን። — ፊልጵስዩስ 2:29
የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድን ማሳየት
14. የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት እንድናሳይ የሚያዙን የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
14 ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስና እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ለእምነት ወንድሞቻችን የሞቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ማሳየት አለብን። “[በወንድማዊ መዋደድ] ላይ እርስ በርሳችሁ ርህራሄ አዘል መዋደድ ይኑራችሁ” የሚል እናነባለን። (ሮሜ 12:10 ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ) “የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድን በተመለከተ እንድንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፣ ምክንያቱም እርስ በርስ እንድትፋቀሩ እናንተ ራሳችሁ በአምላክ ተምራችኋል።” (1 ተሰሎንቄ 4:9 ኢንተርሊኒየር ) “የጠበቀ ወንድማዊ መዋደዳችሁ ይቀጥል።” (ዕብራውያን 13:1 ኢንተርሊኒየር ) የሰማዩ አባታችን ለምድራዊ ልጆቹ የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ስናሳይ እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም!
15. የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
15 በሐዋርያት ዘመን ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው “በተቀደሰ አሳሳም” ወይም “በፍቅር አሳሳም” ሰላምታ የመለዋወጥ ልማድ ነበራቸው። (ሮሜ 16:16፤ 1 ጴጥሮስ 5:14) በእርግጥም የጠበቀ ወንድማዊ የመዋደድ ስሜት መግለጫ ነበር! በአሁኑ ጊዜም በአብዛኛው የምድር ክፍል ይበልጥ የተለመደው የሰላምታ መግለጫ ልባዊ የሆነ የወዳጅነት ፈገግታና ጠበቅ ያለ በእጅ መጨባበጥ ነው። እንደ ሜክሲኮ ባሉት የላቲን አሜሪካ አገሮች በመተቃቀፍ ሰላምታ ይለዋወጣሉ፣ ይህም በእርግጥ የጠበቀ የመውደድ ስሜት መግለጫ ነው። በእነዚህ አገሮች ለተገኘው ታላቅ ጭማሪ አንዱ ምክንያት ወንድሞች የሚያሳዩት ይህ የሞቀ የመውደድ ስሜት ሊሆን ይችላል።
16. በመንግሥት አዳራሾቻችን የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ለማሳየት ምን አጋጣሚዎች አሉን?
16 ወደ መንግሥት አዳራሹ ስትገቡ የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜትን ለመግለጽ ልዩ ጥረት ታደርጋላችሁን? እንዲህ ማድረጋችን የሚያበረታቱ ቃላትን እንድንናገር፣ በተለይም ደግሞ የተከዙ የሚመስሉትን እንድናበረታታቸው ያደርገናል። “ላዘኑት ነፍሳት በማጽናናት” እንድንናገር ተነግሮናል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት) ይህም የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜትን ግለት የምናስተላልፍበት አንዱ መንገድ ለመሆኑ አያጠራጥርም። ሌላው መልካም መንገድ ለጥሩ የሕዝብ ንግግር፣ በደንብ ለቀረበ የክፍል ፕሮግራም፣ በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ጥሩ ጥረት ለተደረገበት የተማሪ ንግግርና ለመሳሰሉት አድናቆታችንን መግለጽ ነው።
17. አንድ ሽማግሌ በጉባኤው ዘንድ በጥብቅ መወደድን ያተረፈው እንዴት ነው?
17 የተለያዩ ወንድሞችና እህቶች እቤታችን መጥተው ምግብ እንዲበሉ ወይም ከስብሰባ በኋላ የማይመሽ ከሆነ መክሰስ መጋበዝስ? ኢየሱስ በሉቃስ 14:12–14 ላይ በሰጠው ምክር መመራት አይገባንምን? በፊት ሚስዮናዊ የነበረ አንድ ወንድም በአንድ ወቅት ከእርሱ በስተቀር ሌሎቹ ሁሉ ከሌላ ዘር የሆኑ አባላት ባሉበት ጉባኤ ውስጥ መሪ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት በማሳየት በኩል ጉድለት እንዳለ ተመለከተና ሁኔታውን ለማረም ተነሳ። ምን አደረገ ይሆን? በየሳምንቱ እሁድ አንዳንድ ቤተሰብ እየጠራ የተለያዩ ቤተሰቦችን ምግብ መጋበዝ ጀመረ። በዓመቱ መጨረሻ ላይ ሁሉም ለእርሱ የሞቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ማሳየት ጀመሩ።
18. ለታመሙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
18 አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ታመው በቤት ወይም በሆስፒታል በሚተኙበት ጊዜ የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት በማሳየት የምናስብላቸው መሆኑን እንዲያውቁ ለማድረግ እንችላለን። ለአረጋውያን ልዩ እንክብካቤ በሚሰጥባቸው ተቋማት ለሚኖሩት ወንድሞችና እህቶችስ? ሄደን በመጠየቅ፣ ስልክ በመደወል፣ ወይም ደብዳቤ በመላክ የሞቀ ስሜታችንን ለምን አንገልጽላቸውም?
19, 20. የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜታችን እንደሰፋ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
19 እንዲህ ዓይነቶቹን የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ መግለጫዎች በምናሳይበት ጊዜ ‘የማሳየው የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት አድሎአዊ ነውን? የቆዳ ቀለም፣ የትምህርት ደረጃ ወይም ቁሳዊ ሀብት በማሳየው የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ላይ ተጽእኖ ያሳድሩብኛልን? ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ወንድማዊ የመውደድ ስሜታቸውን እንዲያሰፉት እንዳሳሰባቸው እኔም እንደዚሁ ማስፋት ያስፈልገኝ ይሆን?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ስለወንድሞቻችን ገንቢ አመለካከት እንዲኖረን፣ በጥሩ ጎናቸው እንድናደንቃቸው ያደርገናል። የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ወንድሞቻችን በሚያሳዩት መንፈሳዊ ዕድገት በመቅናት ፈንታ እንድንደሰት ይረዳናል።
20 በተጨማሪም የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ወንድሞቻችንን በአገልግሎት ለመርዳት ንቁ ሊያደርገን ይገባል። ከመዝሙራችን አንዱ (ቁጥር 92) እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:-
“ደካሞችን ሁሉ አግዙ በደግነት፤
“እነሱም መናገር እንዲችሉ በድፍረት።
“በዕድሜ ትንሾች የሆኑትንም ችላ አትበሉ፤
“ብትረዷቸው ከፍርሃት ተላቀው ይበረታሉ።”
21. የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ስናሳይ ምን ምላሽ ልንጠብቅ እንችላለን?
21 ስለዚህ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደዳችንን በምንገልጽበት ጊዜ ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ የገለጸው ቀጥሎ ያለው ሥርዓት ይሠራል:- “ስጡ፣ ይሰጣችሁማል፣ በምትሠፍሩበት መሥፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፣ የተጨቆነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መሥፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” (ሉቃስ 6:38) የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ስናሳይ፣ እንደ እኛው የይሖዋ አገልጋዮች ለሆኑት ክብር ስንሰጥ እራሳችንም እንጠቀማለን። የጠበቀ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ማሳየት የሚያስደስታቸው ሁሉ በእርግጥም ደስተኞች ናቸው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፍቅር (አጋፔ ) ምን አያደርግም? ምንስ ያደርጋል? የሚለውን ተከታዩን ርዕስ ተመልከት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ውስጣዊ ስሜቶቻችንን የሚመለከቱ የግሪክኛ ቃላት ምንድን ናቸው? የተለያዩ የሆኑትስ እንዴት ነው?
◻ ለጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ቁልፉ ምንድን ነው?
◻ ልዩ የሆነ የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድን በማሳየት በኩል ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉን?
◻ ለወንድሞቻችንና ለሽማግሌዎች የጋለ ወንድማዊ የመውደድ ስሜት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጴጥሮስ ወንድሞቹ በእምነታቸውና በሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርዮቻቸው ላይ የጠበቀ ወንድማዊ የመዋደድ ስሜት እንዲጨምሩ አሳስቧቸዋል