የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 11/1 ገጽ 3-5
  • ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ምሥጢር መግለጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ምሥጢር መግለጥ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ለማወቅ የተደረገ ፍለጋ
  • ስሙ ምሥጢር ለመሆን የበቃው እንዴት ነው?
  • ከሁሉ የሚበልጠው ስምና የወደፊት ተስፋችን
  • የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • አምላክን በስም ልታውቀው የምትችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2004
  • የአምላክ ስም
    ንቁ!—2017
  • የይሖዋን ታላቅ ስም አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 11/1 ገጽ 3-5

ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ምሥጢር መግለጥ

የእስላሞች ቁርአንም ሆነ የክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ ስለሚበልጠው ስም መጥቀሳቸው አዲስ ነገር ሊሆንብን ይችላል። ይህ ርዕስ ከሁሉ የሚበልጠው ስም የያዘውን ትርጉምና አስፈላጊነቱን ያብራራል። በተጨማሪም ይህ ስም ሁሉንም የሰው ዘሮች እንዴት እንደሚነካና በዚህ በምድር ላይ ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ያሳያ

በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች በዚህች ምድር ላይ ኖረው አልፈዋል። አብዛኛውን ጊዜ ስማቸው አብሯቸው የተቀበረ ሲሆን መታሰቢያቸውም ተረስቷል። ይሁን እንጂ እንደ አቪቼና፣ ኤዲሰን፣ ፓስተር፣ ቤቶቨን፣ ጋንዲ እና ኒውተን ያሉት ታላላቅ ስሞች ሕያው ናቸው። እነዚህ ስሞች የስም ባለቤቶቹ ካከናወኗቸው ውጤቶች፣ ከደረሱባቸው ግኝቶችና ከፈለሰፏቸው ነገሮች ጋር የተያያዙ ናቸው።

ሆኖም ከሌሎቹ ሁሉ የሚበልጥ አንድ ስም አለ። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ የሚገኙት ያለፉትም ሆኑ የአሁኖቹ አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ከዚህ ስም ጋር የተያያዙ ናቸው። እንዲያውም የሰው ዘር ረጅምና አስደሳች ሕይወትን ተስፋ የሚያደርገው ከዚህ ስም ጋር ግንኙነት ባለው መንገድ ነው።

ብዙዎች ይህንን ስም ለማወቅ ፈልገዋል። ስሙን ለማወቅ ፍለጋ አድርገዋል፤ አጠያይቀዋል፤ ነገር ግን አላገኙትም። ይህ ስም ዛሬም ለእነርሱ ምሥጢር ሆኖባቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ የስሙ ባለቤት ካልገለጸለት በስተቀር ማንም ሰው ይህንን ስም ሊያውቀው አይችልም። የዚህ ወደርየለሽ ስም ምሥጢር በመገለጡ ደስ ሊለን ይገባል። በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲያውቁት ሲል አምላክ ራሱ ይህንን ስም ገልጧል። ለአዳም፣ ቀጥሎም ለአብርሃም፣ ለሙሴ እና ለሌሎች የጥንት ታማኝ አገልጋዮቹ ስሙን ገልጦላቸዋል።

ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ለማወቅ የተደረገ ፍለጋ

“ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቆ የሚያውቅ” አንድ ሰው እንደነበረ ቁርአን ይናገራል። (27:​40) ይህንን ጥቅስ ሲያብራራ ታፍስር ዣህላልየን የተባለ ጽሑፍ:- “የበራክዩ ልጅ አሳፍ ጻድቅ ሰው ነበር። ከሁሉ የሚበልጠውን የአምላክን ስም ያውቅ ነበር። ይህን ስም በጠራ ቁጥር መልስ ያገኝ ነበር” ይላል። ይህም በመዝሙር 83:​18 ላይ “አሕዛብ ስምህ ይሖዋ የሆንከው አንተ ብቻ በምድር ሁሉ ላይ የበላይ እንደሆንክ ይወቁ” [አዓት ] በማለት የጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አሳፍን ያስታውሰናል።

በቁርአን 17:​2 ላይ:- “ለሙሴ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሰጠነውና ለእስራኤላውያን መመሪያ እንዲሆናቸው አደረግን” የሚል ቃል እናነባለን። በእነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሙሴ አምላክን “እነሆ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፣ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፣ ስሙ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፣ ምን እላቸዋለሁ? አለው።” አምላክም ለሙሴ:- “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ:- የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው” በማለት መልስ ሰጠው። — ዘጸአት 3:​13, 15

በጥንት ዘመን እስራኤላውያን ታላቅ የሆነውን ይህንን የአምላክ ስም ያውቁ ነበር። የራሳቸው ስሞች ክፍል ሆኖ እንኳ ሳይቀር ይሠራበት ነበር። ልክ አንድ ሰው አብዱላህ የሚባለው ስም “የአምላክ አገልጋይ” ማለት መሆኑን እንደሚያውቅ ሁሉ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብም ኦባድያህ የሚለው ስም “የይሖዋ አገልጋይ” የሚል ትርጉም ነበረው። የነቢዩ ሙሴ እናት ስሟ ኢዮካቤድ ሲሆን ትርጓሜውም “ይሖዋ ክብር ነው” ማለት ሳይሆን አይቀርም። ዮሐንስ የሚለው ስም “ይሖዋ ደግ ሆነልኝ” ማለት ነው። የነቢዩ የኤልያስ ስምም “አምላኬ ይሖዋ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ነቢያት ይህንን ታላቅ ስም ያውቁ ነበር። በጠለቀ አክብሮትም ይጠቀሙበት ነበር። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። የማርያም ልጅ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። . . . እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ” በማለት ጎላ አድርጎ ጠቅሶታል። (ዮሐንስ 17:​6, 26) ቁርአንን አስመልክቶ በሰጡት ታዋቂ ማብራሪያቸው ላይ ባይዳዊ በቁርአን 2:​87 ላይ ሐሳብ ሲሰጡ ኢየሱስ “የሞቱትን ሰዎች ለማስነሣት ከሁሉ በሚበልጠው የአምላክ ስም ተጠቅሟል” በማለት ተናግረዋል።

ታዲያ ይህ ስም ምሥጢር የሆነው ምን ነገር ስለተፈጠረ ነው? ይህ ስም ከእያንዳንዳችን የወደፊት ሕይወት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

ስሙ ምሥጢር ለመሆን የበቃው እንዴት ነው?

አንዳንዶች በዕብራይስጥ ቋንቋ “ይሖዋ” ማለት “አላህ” (እግዚአብሔር) ማለት ነው ብለው ያስባሉ። ነገር ግን “አላህ” የሚለው ቃል ግርማዊነትን የሚያመለክተው ኤሎአህ (አምላክ) የሚለው ቃል የብዙ ቁጥር ከሆነው ኤሎሂም ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ይመሳሰላል። አይሁዶች ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም እንዳይጠሩ የሚከለክል አጉል እምነት በመካከላቸው ተነሣ። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚያነቡበት ጊዜ ይሖዋ የሚለውን ስም ሲያገኙ አዶናይ ማለትም “ጌታ” እያሉ ማንበቡን የተለመደ አደረጉት። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ “ይሖዋ” የሚለውን አዶናይ ብለው ተክተዋል።

የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎችም ይህንኑ መንገድ ተከትለዋል። ይሖዋ የሚለውን ስም “እግዚአብሔር” (በአረብኛ ደግሞ “አላህ”) እና “ጌታ” በሚሉት ቃላት ተክተውታል። እንደዚህ የመሰለው አድራጎት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ድጋፍ ለሌለው ሥላሴ ለተባለው የሐሰት መሠረተ ትምህርት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚህም የተነሣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በስሕተት ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ ጋር እኩል እንደሆኑ አድርገው በመቁጠር ያመልኳቸዋል።a

በዚህም ምክንያት ከሁሉ የሚበልጠው ስም በስፋት እንዳይታወቅ በማድረጋቸው የአይሁድና የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት መሪዎች ተጠያቂዎች ናቸው። አምላክ ግን “ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ . . . እኔ ይሖዋ እንደሆንሁ አሕዛብ ማወቅ ይኖርባቸዋል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። አዎን፣ ይሖዋ በአሕዛብ ሁሉ ስሙ እንዲታወቅ ያደርጋል። ለምን? ምክንያቱም የአይሁዳውያን ወይም የአንድ አገር ወይም ሕዝብ ብቻ አምላክ አይደለም። ይሖዋ የሰው ዘር ሁሉ አምላክ ነው። — ሕዝቅኤል 36:​23 አዓት፤ ዘፍጥረት 22:​18፤ መዝሙር 145:​21፤ ሚልክያስ 1:⁠11

ከሁሉ የሚበልጠው ስምና የወደፊት ተስፋችን

ቅዱሳን ጽሑፎች “የጌታን [የይሖዋን አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በማለት ይናገራሉ። (ሮሜ 10:​13) በፍርድ ቀን የመዳናችን ጉዳይ የአምላክን ስም ከማወቃችን ጋር የተያያዘ ነው። ስሙን ማወቅ ባሕርዮቹን፣ ሥራዎቹንና ዓላማዎቹን ማወቅና ከፍተኛ ከሆኑት መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል አብርሃም የአምላክን ስም ያውቅና ይጠራ ነበር። ከዚህም የተነሣ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና አግኝቷል፣ በእርሱ እንደሚያምን አሳይቷል፣ በእርሱ ላይ ተደግፏል እንዲሁም ታዞታል። በዚህ መንገድ አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ሆነ። በተመሳሳይም የአምላክን ስም ማወቃችን ከእርሱ ጋር ያቀራርበናል፣ ፍቅሩን አጽንተን በመያዝ ከእርሱ ጋር የግል ዝምድና እንድንመሠርት ይረዳናል። — ዘፍጥረት 12:​8፤ መዝሙር 9:​10፤ ምሳሌ 18:​10፤ ያዕቆብ 2:⁠23

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም [ይሖዋንም አዓት] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ” የሚል ቃል እናነባለን። (ሚልክያስ 3:​16) ከሁሉ ስለሚበልጠው ስም ‘ልናስብ’ የሚገባን ለምንድን ነው? ይሖዋ የሚለው ስም ቃል በቃል ትርጉሙ “እንዲሆን የሚያደርግ” ማለት ነው። ይህም ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ዓላማዎቹ ምንጊዜም ግባቸውን እንዲመቱ ያደርጋል። እሱ ግሩም ጠባዮች ያሉት ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክና ብቸኛ ፈጣሪ ነው። የአምላክን መለኮታዊ ባሕርዮች ሙሉ በሙሉ ሊገልጽ የሚችል አንድ ብቸኛ ቃል የለም። ነገር ግን አምላክ ለራሱ ከሁሉ የሚበልጠውን ስም፣ ይሖዋ የተባለውን መረጠ። ይህ ስሙም አንድን ሰው የይሖዋን ባሕርያት በሙሉና ዓላማዎቹን እንዲያስታውስ ያደርገዋል።

በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ ይነግረናል። ይሖዋ አምላክ ሰው በገነት የዘላለም ሕይወት አግኝቶ እንዲደሰት በማሰብ ፈጠረው። ለሰው ዘር ያለው ዓላማውም ሰዎች ሁሉ በፍቅርና በሰላም ተሳስረው አንድ ቤተሰብ እንዲሆኑ ነው። አፍቃሪ የሆነው አምላክ ይህ ዓላማ በቅርቡ እንዲፈጸም ያደርጋል። — ማቴዎስ 24:​3–14, 32–42፤ 1 ዮሐንስ 4:​14–21

አምላክ የሰው ዘር ስለደረሰበት መከራ ማብራሪያ ይሰጣል፤ እንዲሁም መዳን እንደሚቻል ያሳያል። (ራእይ 21:​4) በመዝሙር 37:​10, 11 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናነባለን:- “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” — በተጨማሪም ቁርአን 21:​105ን ተመልከት።

አዎን፣ ወደፊት አምላክ በታላቅ ስሙ ይታወቃል። አሕዛብ እርሱ ይሖዋ እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከሁሉ የሚበልጠውን ስም ማወቅ፣ ለእርሱ ምስክር መሆንና ስሙንም የሙጥኝ ብሎ መያዝ እንዴት ያለ አስደናቂ መብት ነው! በዚህ መንገድ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እንዲህ የሚለው ደስ የሚያሰኘው የአምላክ ዓላማ ይፈጸማል:- “በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፣ . . . ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፣ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።” — መዝሙር 91:​14–16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሥላሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አለመሆኑን ለማረጋገጥ በሥላሴ ማመን ይኖርብሃልን? የተባለውን በ1989 በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚነድደው ቁጥቋጦ ውስጥ አምላክ ለሙሴ ‘የአብርሃም አምላክ ይሖዋ ’ ነኝ በማለት ራሱን ለይቶ ገልጿል

[ምንጭ]

Moses and the Burning Bush, by W. Thomas, Sr.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ