የዳንኤል ትንቢታዊ ቀኖችና እምነታችን
“የሚታገሥ፣ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው።” — ዳንኤል 12:12
1. ብዙዎች እውነተኛ ደስታ ያላገኙት ለምንድን ነው? እውነተኛ ደስታስ ከምን ጋር ተያይዟል?
ማንኛውም ሰው ደስተኛ መሆን ይፈልጋል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ደስተኛ የሆኑት በጣም ጥቂት ናቸው። ለምን? ከፊሉ ምክንያት ደስታን ለማግኘት የሚፈልጉት በተሳሳቱ ቦታዎች ላይ መሆኑ ነው። ደስታ ይገኛል ተብሎ የሚታሰስባቸው አቅጣጫዎች ትምህርት፣ ሀብት፣ ቋሚ ሥራ፣ ወይም ሥልጣን ፍለጋ የመሳሰሉት ናቸው። ኢየሱስ ግን በተራራ ስብከቱ መክፈቻ ላይ ደስታን አንድ ሰው ለሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ ከመሆኑ፣ ከመሐሪነቱ፣ ከልብ ንጽሕናውና ከመሳሰሉት ጠባዮቹ ጋር አያይዞታል። (ማቴዎስ 5:3–10) ኢየሱስ የጠቀሰው ዓይነት ደስታ እውነተኛ የሆነና ዘላቂነት ያለው ነው።
2. በትንቢቱ መሠረት በፍጻሜው ዘመን ደስታ ወደ ማግኘት ሊመራ የሚችለው ምንድን ነው? ይህንንስ በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
2 በፍጻሜው ዘመን ለሚኖሩት ቅቡዓን ቀሪዎች ደስታ ከሌላ ተጨማሪ ነገር ጋር ተያይዞላቸዋል። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን:- “ዳንኤል ሆይ፣ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤ የሚታገሥ፣ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው።” (ዳንኤል 12:9, 12) እነዚህ 1,335 ቀኖች ከየት እስከ የት ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናሉ? በእነዚህ ቀኖች የኖሩት ሰዎች ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? ይህ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ በእምነታችን ላይ የሚያስከትለው ነገር ይኖራልን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲረዳን በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ሦስተኛ ዓመት ላይ እስራኤላውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ከተለቀቁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዳንኤል እነዚህን ቃላት የጻፈበትን ጊዜ ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት። — ዳንኤል 10:1
ተመልሶ መቋቋም ደስታን አመጣ
3. በ537 ከዘአበ ለታመኑ አይሁዳውያን ትልቅ ደስታ ያመጣላቸው ንጉሥ ቂሮስ ያደረገው የትኛው ነገር ነው? ነገር ግን ቂሮስ ለአይሁዳውያን ያልሰጣቸው መብት ምን ነበር?
3 የአይሁዳውያን ከባቢሎን ነፃ መውጣት ታላቅ ደስታ የተገኘበት ወቅት ነበር። አይሁዳውያን 70 ዓመት ያህል በግዞት ከጸኑ በኋላ ታላቁ ቂሮስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠሩ ጥሪ አቀረበላቸው። (ዕዝራ 1:1, 2) ለዚህ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት ሁሉ ብዙ ነገሮችን ተስፋ በማድረግ በ537 ከዘአበ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ይሁን እንጂ ቂሮስ ከንጉሥ ዳዊት ዝርያዎች መካከል ንጉሥ አንግሠው መንግሥት አቋቁሙ አላላቸውም።
4, 5. (ሀ) የዳዊት ንግሥና የተገለበጠው መቼ ነበር? ለምንስ? (ለ) የዳዊት ንግሥና ተመልሶ እንደሚቋቋም ይሖዋ ምን ዋስትና ሰጥቶ ነበር?
4 ይህ ጉዳይ ልዩ ትርጉም ያለው ነው። ከአምስት መቶ ዘመናት በፊት ይሖዋ ለዳዊት “ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፣ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል” በማለት ቃል ገብቶለት ነበር። (2 ሳሙኤል 7:16) የሚያሳዝነው ግን የዳዊት ንጉሣዊ ዝርያዎች ዓመፀኞች በመሆናቸውና የብሔሩም የደም ዕዳ በጣም በመብዛቱ በ607 ከዘአበ ይሖዋ በዳዊት መስመር ይተላለፍ የነበረው ንግሥና እንዲገለበጥ ፈቀደ። ከመቃባውያን አጭር የግዛት ዘመን በስተቀር ኢየሩሳሌም በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ በድጋሚ እስከጠፋችበት እስከ 70 እዘአ ድረስ በባዕዳን አገዛዝ ሥር ስትረገጥ ኖራለች። ከዚህም የተነሣ የዳዊት ልጅ የሆነ ማንም ሰው ንጉሥ ሆኖ ያልገዛበት “የአሕዛብ ዘመን” በ537 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊትም እንደቀጠለ ነበር። — ሉቃስ 21:24
5 ይሁንና ይሖዋ ለዳዊት የገባውን ቃል አልረሳም። በተከታታይ በታዩ ራእዮችና ሕልሞች አማካኝነት ባቢሎን ዓለምን ከተቆጣጠረችበት ጊዜ አንሥቶ በዳዊት ንጉሣዊ መስመር የመጣ አንድ ንጉሥ በይሖዋ ሕዝቦች መንግሥት ላይ እንደገና እስከሚገዛበት ጊዜ ድረስ በዓለም ላይ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሚከናወኑትን ነገሮች በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት በዝርዝር ገልጿል። እነዚህ በዳንኤል ምዕራፍ 2, 7, 8 እና ከ10 እስከ 12 ላይ የተመዘገቡት ትንቢቶች የታመኑ አይሁዳውያን ውሎ አድሮ የዳዊት ዙፋን በእውነትም ‘ለዘላለም እንደሚጸና’ እርግጠኞች እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። ይህ እውነት መገለጹ በ537 ከዘአበ ወደ አገራቸው ለተመለሱት አይሁዳውያን ደስታ እንዳመጣላቸው ምንም አያጠራ ጥርም።
6. አንዳንዶቹ የዳንኤል ትንቢቶች በዘመናችን እንደሚፈጸሙ እንዴት እናውቃለን?
6 አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች የዳንኤል ትንቢቶች ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል በማለት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። በዳንኤል 12:4 ላይ አንድ መልአክ ለዳንኤል “አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፣ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፣ እውቀትም ይበዛል” በማለት ነግሮታል። የዳንኤል መጽሐፍ የሚከፈተው ማለትም ትርጉሙ ሙሉ በሙሉ የሚገለጸው በፍጻሜው ዘመን ብቻ ከሆነ ቢያንስ ቢያንስ የትንቢቶቹ ጥቂት ክፍሎች ያንን ዘመን የሚመለከቱ መሆን ይኖርባቸዋል። — ዳንኤል 2:28፤ 8:17 እና 10:14ን ተመልከት
7. (ሀ) የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት ያበቁት መቼ ነው? በዚያን ጊዜ በአስቸኳይ መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ምን ነበር? (ለ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ያልነበሩት እነማን ናቸው?
7 በ1914 የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት አበቁና ለዚህ ዓለም የፍጻሜ ዘመን ጀመረ። የዳዊት መንግሥት በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ሳይሆን በማይታይ ሁኔታ ‘በሰማይ ደመናት’ ውስጥ እንደገና ተቋቋመ። (ዳንኤል 7:13, 14) በዚያን ጊዜ “እንክርዳድ” የሆኑት አስመሳይ ክርስቲያኖች በጣም በመብዛታቸው ቢያንስ ለሰዎች ዓይን የእውነተኛው ክርስትና ሁኔታ ግልጽ ሆኖ አልታየም ነበር። ሆኖም አንድ በጣም አስፈላጊ ጥያቄ መልስ ማግኘት ነበረበት። ጥያቄውም “ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?” የሚል ነው። (ማቴዎስ 13:24–30፤ 24:45) እንደገና የተቋቋመውን የዳዊት መንግሥት በምድር ላይ የሚወክለው ማን ነው? የዳንኤል ሥጋዊ ወንድሞች የሆኑት አይሁዳውያን ሊሆኑ አይችሉም። እምነት ስለጎደላቸውና በመሲሑ ስለተሰናከሉ አምላክ ትቷቸው ነበር። (ሮሜ 9:31–33) ታማኙ ባሪያ በሕዝበ ክርስትና ድርጅቶች ውስጥ በምንም ዓይነት መንገድ ሊገኝ አልቻለም። ክፉ ሥራቸው ኢየሱስ ፈጽሞ እንዳያውቃቸው አድርጎታል። (ማቴዎስ 7:21–23) እንግዲያው ታማኙ ባሪያ ማን ሆኖ ተገኘ?
8. በፍጻሜው ዘመን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው የተገኙት እነማን ናቸው? እንዴትስ እናውቃለን?
8 በ1914 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩትና ከ1931 ጀምሮ ግን የይሖዋ ምስክሮች በመባል የሚታወቁት በቁጥር አነስተኛ የሆኑት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች አካል መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም። (ኢሳይያስ 43:10) በዳዊት መስመር የሚገዛው መንግሥት እንደገና መቋቋሙን ለሕዝብ ያስታወቁት እነርሱ ብቻ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14) ከዓለም ፈንጠር ብለው የቆሙትና የይሖዋ ስም ጎላ ብሎ እንዲታይ ያደረጉት እነርሱ ብቻ ናቸው። (ዮሐንስ 17:6, 14) በፍጻሜው ዘመን የአምላክን ሕዝቦች የሚመለከቱት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተፈጸሙት በእነርሱ ላይ ብቻ ነው። ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል ደስታ የሚያመጡት በዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ የተጠቀሱትን 1,335 ቀኖች ጨምሮ የተዘረዘሩት ተከታታይ ትንቢታዊ ወቅቶች ይገኙባቸዋል።
1,260ዎቹ ቀኖች
9, 10. በዳንኤል 7:25 ላይ ‘ዘመንና ዘመናት እኩሌታ ዘመን’ ተብለው የተጠቀሱትን ጊዜያት ልዩ ባሕርያት የሰጡት ክንውኖች ምንድን ናቸው? ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዘመን የተጠቀሰውስ በየትኞቹ በሌሎች ጥቅሶች ላይ ነው?
9 በዳንኤል 12:7 ላይ ስለ መጀመሪያው ትንቢታዊ ወቅት እንዲህ እናነባለን:- “ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኩሌታ ነው፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል።”a ይህ ተመሳሳይ ወቅት የአምላክ ምስክሮች ማቅ ለብሰው ለሦስት ዓመት ተኩል ከሰበኩ በኋላ ይገደላሉ በሚለው በራእይ 11:3–6 ላይም ተጠቅሶ እናገኘዋለን። እንደገናም በዳንኤል 7:25 ላይ እንደዚህ እናነባለን:- “በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፣ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፣ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኩሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።”
10 መጨረሻ ላይ በተጠቀሰው በዚህ ትንቢት ውስጥ “ይናገራል”፣ “ይሰባብራል” የተባለው ከባቢሎን ጀምሮ ሲቆጠር አምስተኛ የሆነው የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። በዚህ “ሌላ ትንሽ ቀንድ” ዘመን የሰው ልጅ “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ይቀበላል። (ዳንኤል 7:8, 14) ይህ ምሳሌያዊ ቀንድ በመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥታዊው የእንግሊዝ መንግሥት የነበረ ሲሆን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃያል መንግሥት በመሆን አድጎ በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የበላይነት የሚመራው ነው። ለሦስት ተኩል ዘመናት ወይም ዓመታት ይህ የዓለም ኃያል ቅዱሳንን ይሰባብራል እንዲሁም ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል ተብሎ በትንቢቱ ላይ ተገልጿል። በመጨረሻም ቅዱሳኑ በእጁ እንደሚሰጡ ተገልጿል። — በተጨማሪም ራእይ 13:5, 7ን ተመልከት።
11, 12. በትንቢት የተነገሩትን 1,260 ቀኖች እንዲጀምሩ ያደረጉት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
11 እነዚህ ሁሉ ጎን ለጎን የሚሄዱ ትንቢቶች የተፈጸሙት እንዴት ነበር? ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት ዓመታት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች 1914 የተወሰነው የአሕዛብ ዘመን ፍጻሜ እንደሚሆን በይፋ አስጠንቅቀዋል። ጦርነቱ ሲፈነዳ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ችላ እንደተባለ ግልጽ ነበር። ሰይጣን በቁጥጥሩ ሥር ያለውን “አውሬ” ማለትም በእንግሊዝ መንግሥት የሚገዛውን ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቱን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ‘ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ’ ማለትም የአምላክ መንግሥት መግዛት የምትጀምርበትን ጊዜ ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ጥረት አድርጎ ነበር። (ራእይ 13:1, 2) ግን ሳይሳካለት ቀረ። የአምላክ መንግሥት ሰዎች ሊደርሱበት በማይችሉት በሰማይ ተቋቋመች። — ራእይ 12:1–3
12 ጦርነቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ፈተና አመጣባቸው። ከጥር ወር 1914 ጀምረው የፍጥረት ፎቶ ድራማ የተባለ በዳንኤል ትንቢቶች ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፊልም ያሳዩ ነበር። በዚያ ዓመት በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ጦርነቱ ተቀሰቀሰ። የተወሰኑት ዘመናት ጥቅምት ላይ አበቁ። በዓመቱ ማለቂያ ላይ ቅቡዓን ቀሪዎች ስደት ይደርስብናል ብለው ይጠብቁ ነበር። ኢየሱስ በማቴዎስ 20:22 ላይ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ የ1915 የዓመት ጥቅሳቸው እንዲሆን መምረጣቸው ይህንን ያሳያል።
13. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በ1,260ዎቹ ቀኖች ወቅት ማቅ ለብሰው የሰበኩት እንዴት ነበር? በዚያ ወቅት መጨረሻ ላይስ ምን ሆነ?
13 ስለሆነም ከታህሣሥ 1914 ጀምሮ ይህ አነስተኛ የምስክሮች ቡድን የይሖዋን ፍርዶች እያስታወቀ በትሕትና በመጽናት ‘ማቅ ለብሶ መስበክ’ ጀመረ። የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዘዳንት የነበረው ሲ ቲ ራስል በ1916 መሞት ብዙዎቹን አስደነገጠ። ጦርነቱ እየተጋጋመ በሄደ መጠን ምስክሮቹ እየጨመረ የሚሄድ ተቃውሞ ያጋጥማቸው ጀመር። አንዳንዶቹ ታሰሩ። በእንግሊዝ አገር እንደ ፍራንክ ፕላት እና በካናዳ ደግሞ እንደ ሮበርት ክለግ ያሉት ግለሰቦች በጨካኝ ባለ ሥልጣኖች እጅ ወድቀው ተሠቃይተዋል። በመጨረሻም ሰኔ 21 ቀን 1918 አዲሱ ፕሬዘዳንት ጄ ኤፍ ራዘርፎርድና የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ድሬክተሮች በሐሰት ተከስሰው የረጅም ጊዜ እስራት ተበየነባቸው። በትንቢታዊው ዘመን መጨረሻ ላይ የተደራጀውን የስብከት ሥራ ‘ትንሹ ቀንድ’ በዚህ መንገድ ገደለው። — ዳንኤል 7:8
14. በ1919 እና ከዚያ በኋላ ነገሮች ለቅቡዓን ቀሪዎች የተለወጡላቸው እንዴት ነበር?
14 የራእይ መጽሐፍ ከዚያ ቀጥሎ የሚሆነውን ተንብዮ ነበር። እንቅስቃሴው ከቆመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማለትም ሞተው በአደባባይ ላይ ለሦስት ቀን ተኩል በድናቸው እንደሚተኛ በትንቢት የተነገረው ጊዜ ሲያበቃ ቅቡዓን ቀሪዎቹ ሕያው ሆኑና እንደገና ለሥራ ተንቀሳቀሱ። (ራእይ 11:11–13) መጋቢት 26, 1919 ፕሬዘዳንቱና የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ድሬክተሮች ከእስር ቤት ተፈቱና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ከቀረበባቸው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ተደረጉ። ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ቅቡዓን ቀሪዎች ወዲያውኑ ለተጨማሪ የሥራ እንቅስቃሴ ራሳቸውን እንደገና አደራጁ። በዚህ መንገድ በራእይ መጽሐፍ ላይ በተገለጸው የመጀመሪያ ወዮ ፍጻሜ መሠረት እንቅስቃሴ አልባ ከሆነው ጥልቅ ወጥተው የሐሰት ሃይማኖት ጥፋት እንደሚጠብቃት በሚያመለክተው ከታላቅ እቶን በወጣ ጢስ የታጀቡ መንፈሳውያን አንበጦች ሆነው ወጡ። (ራእይ 9:1–11) በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በመንፈሳዊ በሚገባ የተመገቡና በፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራም የታጠቁ ሆኑ። በ1921 አዲሶችንና ልጆችን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለማስተማር የሚረዳ የአምላክ በገና የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ አትመው አወጡ። (ራእይ 12:6, 14) እነዚህ ሁሉ ነገሮች ልዩ ትርጉም ባለው በሌላ ወቅት ውስጥ የተከናወኑ ነገሮች ናቸው።
1,290ዎቹ ቀኖች
15. በትንቢት የተነገሩት 1,290ዎቹ ቀኖች የሚጀምሩበትን ጊዜ እንዴት ልናሰላው እንችላለን? ይህ ዘመን መቼ ተፈጸመ?
15 መልአኩ ዳንኤልን “የዘወትሩም መሥዋዕት [“የማያቋርጠው መሥዋዕት” አዓት የግርጌ ማስታወሻ] ከቀረ ጀምሮ፣ የጥፋትም ርኩሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል” በማለት ነግሮታል። (ዳንኤል 12:11) በሙሴ ሕግ ሥር “የማያቋርጠው መሥዋዕት” በኢየሩሳሌም ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ ይቃጠል ነበር። ክርስቲያኖች የሚቃጠል መሥዋዕት ባያቀርቡም መንፈሳዊ የሆነ የማያቋርጥ መሥዋዕት ያቀርባሉ። ጳውሎስ “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት” ባለ ጊዜ ስለዚህ መንፈሳዊ መሥዋዕት መናገሩ ነበር። (ዕብራውያን 13:15፤ ከሆሴዕ 14:2 ጋር አወዳድር።) ይህ የማያቋርጥ መሥዋዕት በሰኔ 1918 እንዲቋረጥ ተደረገ። እዚህ ላይ የምንመለከተው ሁለተኛ ገጽታ ማለትም “ርኩሰት” የተባለው ምንድን ነበር? በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ድል አድራጊዎቹ ኃያላን ያቋቋሙት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ነበር።b ርኩስ ነበር ምክንያቱም የሕዝበ ክርስትና መሪዎች በአምላክ መንግሥት ምትክ የቃል ኪዳኑን ማኅበር ሰላም የሚያመጣ የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ አድርገው ስላስቀመጡት ነው። የቃል ኪዳኑ ማኅበር የተቋቋመው በጥር 1919 ነበር። ከዚያ ተነሥተን 1,290 ቀኖች (ሦስት ዓመት ከሰባት ወር) ብንቆጥር መስከረም 1922 ላይ እንደርሳለን።
16. በ1,290ዎቹ ቀኖች መጨረሻ ላይ ቅቡዓን ቀሪዎቹ የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደነበሩ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻል የነበረው ለምንድን ነው?
16 ታዲያ በዚያን ጊዜ ምን ነገር ሆነ? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ አሁን ተጠናክረዋል፤ ከታላቋ ባቢሎን ተላቅቀዋል እንዲሁም የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ሆነዋል። (ራእይ 18:4) በመስከረም 1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ ትልቅ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት የአምላክን የፍርድ መልእክት በሕዝበ ክርስትና ላይ በድፍረት ማወጅ ጀመሩ። (ራእይ 8:7–12) አንበጣዎቹ ሰዎቹን መናደፋቸው ሥቃይ ማስከተል ጀመረ! የተጨመረ ሌላ ነገር ቢኖር የራእዩ ሁለተኛ ወዮ መጀመር ነው። ታላቅ የሆነ የክርስቲያን ፈረሰኛ ሠራዊት ማለትም መጀመሪያ ከቅቡዓን ቀሪዎች በኋላም እጅግ ብዙ ሰዎች ተጨምረውበት ያደገው ሠራዊት ምድርን ሁሉ ወረራት። (ራእይ 7:9፤ 9:13–19) አዎን፣ የ1,290 ቀኖች ፍጻሜ ለአምላክ ሕዝቦች ደስታ አምጥቶላቸዋል።c ይሁን እንጂ ተጨማሪ ደስታም ይጠብቃቸው ነበር።
1,335ቱ ቀኖች
17. 1,335ቱ ቀኖች መቼ ጀመሩ? መቼስ ተፈጸሙ?
17 ዳንኤል 12:12 “የሚታገሥ፣ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” ይላል። እነዚህ 1,335 ቀኖች ወይም ሦስት ዓመት ከስምንት ወር ተኩል ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ከዚህ ቀደም ብሎ በተጠናቀቀው ዘመን መጨረሻ ላይ ይጀምራሉ። ከመስከረም 1922 ጀምረን ስንቆጥር (በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ) 1926 የፀደይ ወራት ላይ ያደርሰናል። በእነዚህ 1,335 ቀኖች ውስጥ ምን ነገር ተከናወነ?
18. በ1922 አሁንም መሻሻል ያስፈልግ እንደነበረ የትኞቹ እውነታዎች ይጠቁማሉ?
18 በ1922 የተከናወኑት ታሪካዊ ሁኔታዎች እያሉ አንዳንዶች አሁንም የቀድሞውን ዘመን በናፍቆት ዓይን መመልከታቸውን ቀጥለው ነበር። በሲ ቲ ራስል የተጻፉት የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታተሙ መጻሕፍት መሠረታዊ የሆኑ የማስተማሪያ መጻሕፍት ሆነው ቀጥለው ነበር። ከዚህም በላይ በስፋት ተሰራጭቶ የነበረው በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም የተባለው የእንግሊዝኛ ቡክሌት አምላክ ምድርን መልሶ ገነት ለማድረግ ያወጣው ዓላማና በጥንት ዘመን የነበሩት ታማኞች ትንሣኤ በ1925 ይጀምራል የሚለውን አመለካከት ይዞ ነበር። ቅቡዓኑ የመጽናታቸውን ዋጋ የሚያገኙበት ጊዜ የተቃረበ ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ጋር ተቀራርበው የነበሩ አንዳንዶች ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ውስጣዊ ግፊት አላደረባቸውም።
19, 20. (ሀ) በ1,335ቱ ቀኖች ውስጥ ለአምላክ ሕዝቦች ብዙ ነገሮች የተለወጡላቸው እንዴት ነበር? (ለ) የ1,335ቱ ቀኖች ወቅት የተፈጸመው በምን ክንውኖች ነበር? እነዚህስ ክንውኖች ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ምን የሚያመለክትቱት ነገር ነበራቸው?
19 1,335ቱ ቀኖች በቀጠሉ መጠን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተለወጡ። ወንድሞችን ለማጠናከር መጠበቂያ ግንብ አዘውትሮ በቡድን እንዲጠና ዝግጅት ተደረገ። የመስክ አገልግሎት ከፍተኛ ቦታ ተሰጠው። ከግንቦት 1923 ጀምሮ ወር በገባ በመጀመሪያው ማክሰኞ ሁሉም ሰው ወደ መስክ አገልግሎት እንዲወጣ ጥሪ ተደረገ። እንዲሁም በሳምንቱ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ለዚህ ሥራ የሚሆን ማበረታቻ እንዲሰጣቸው ጊዜ ተመደበ። በነሐሴ 1923 በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ስለ በጎችና ፍየሎች መለየት የሚናገረው የኢየሱስ ምሳሌ ከሺው ዓመት ግዛት በፊት እንደሚፈጸም ተገለጸ። (ማቴዎስ 25:31–40) በ1924 ደብሊው ቢ ቢ አር የተባለው የሬድዮ ጣቢያ ተመርቆ ተከፈተና የምሥራቹን በአየር ሞገድ ለማሰራጨት ማገልገል ጀመረ። “የአንድ ሕዝብ መወለድ” የሚለው ርዕስ መጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ መውጣቱ ራእይ ምዕራፍ 12ን በተስተካከለ መንገድ እንዲረዱት ለማድረግ አስችሏል። በመጨረሻም የታመኑ ክርስቲያኖች ከ1914 እስከ 1919 ድረስ የተከናወኑትን ነውጦች በሚገባ ለመረዳት ቻሉ።
20 የ1925 ዓመት አበቃ፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነበር! ከ1870ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጀመሪያ 1914ን ከዚያም 1925ን በአእምሮአቸው በመያዝ ቀንን ተመርኩዘው ሲያገለግሉ ቆይተው ነበር። አሁን ግን፣ ይሖዋ እስከ ፈቀደ ድረስ ማገልገል እንደሚኖርባቸው ተገነዘቡ። የጥር 1, 1926 መጠበቂያ ግንብ እትም “ይሖዋን ማን ያከብረዋል?” በሚል ርዕስ የወጣው ታሪካዊ ጽሑፍ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለአምላክ ስም ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ጎላ አድርጎት ነበር። በመጨረሻም ግንቦት 1926 በለንደን ኢንግላንድ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ “ለዓለም ገዥዎች የተሰጠ ምስክርነት” በሚል ርዕስ አንድ ውሳኔ ተላለፈ። ይህ ውሳኔ ስለ አምላክ መንግሥት እውነትና ስለ መጪው የሰይጣን ዓለም ጥፋት በግልጽ የሚናገር ነበር። በዚሁ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነፃ መውጣት የተባለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታተመ ኃይለኛ መጽሐፍ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባሉትን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታተሙ መጻሕፍት ከሚተኩት ተከታታይ መጻሕፍት የመጀመሪያው በመሆን እንዲወጣ ተደረገ። አሁን የአምላክ ሕዝቦች ወደኋላ መመልከታቸውን ትተው ወደፊት መመልከት ጀመሩ። 1,335ቱ ቀኖች በዚህ ተደመደሙ።
21. በዚያን ጊዜ ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች እስከ 1,335 ቀን ድረስ መጽናት ምን ትርጉም ነበረው? ስለዚህ ወቅት የሚናገረው ትንቢት መፈጸም ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
21 አንዳንዶች እንደዚህ የመሰለውን ማስተካከያ ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ነገር ግን የጸኑት እውነተኛ ደስታ አገኙ። የእነዚህን ትንቢታዊ ቀኖች ፍጻሜ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት እኛም ብንሆን ደስ ይለናል ምክንያቱም እነዚያን ቀኖች ያሳለፉ አነስተኛ የቅቡዓን ክርስቲያኖች አካል ታማኝና ልባም ባሪያ ስለመሆናቸው ያለንን እርግጠኝነት ያጠነክርልናል። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የይሖዋ ድርጅት ተስፋፍቶ ግዙፍ ሆኗል። ቢሆንም የድርጅቱ ማዕከል በመሆን የሚመራው አሁንም ታማኝና ልባም ባሪያ ነው። ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች በጎች የሚደሰቱበት ሰፊ ጊዜ ገና የሚጠብቃቸው መሆኑን ማወቃችን እንዴት ልብን ደስ የሚያሰኝ ነው! ይህም ሌላውን የዳንኤል ትንቢት ስንመረምር የምናየው ነገር ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እነዚህን ትንቢታዊ ወቅቶች እንዴት ማስላት እንደሚቻል ማብራሪያ ለማግኘት ዓለምን የሚገዛው መጪው የአምላክ መንግሥት የተባለውን በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ ተመልከት።
b የጥቅምት 1, 1985 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 8–18 ተመልከት።
c የጥር 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 12 እና የእንግሊዝኛውን 1975 የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 132 ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ አንዳንዶቹ የዳንኤል ትንቢቶች በዘመናችን እንደሚፈጸሙ እንዴት እናውቃለን?
◻ ቅቡዓን ቀሪዎች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ናቸው ብለን በልበ ሙሉነት ለመናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ 1,260ዎቹ ቀኖች መቼ ጀምረው መቼ አበቁ?
◻ 1,290ዎቹ ቀኖች ለቅቡዓን ቀሪዎቹ ምን ማጠናከሪያና ተመልሶ መቋቋሚያ አምጥተውላቸው ነበር?
◻ እስከ 1,335ቱ ቀን ፍጻሜ ድረስ የጸኑት ደስተኞች የነበሩት ለምንድን ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዳንኤል ትንቢታዊ ወቅቶች
1,260 ቀኖች:-
ከታህሣሥ 1914 እስከ ሰኔ 1918
1,290 ቀኖች:-
ከጥር 1919 እስከ መስከረም 1922
1,335 ቀኖች:-
ከመስከረም 1922 እስከ ግንቦት 1926
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ታማኝና ልባም ባሪያ ” ቅቡዓን ቀሪዎች እንደሆኑ ከ1919 ጀምሮ ግልጽ ሆኖ ቆይቷል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስዊዘርላንድ በጄኔቫ ከተማ የነበረው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ጽሕፈት ቤት
[ምንጭ]
UN photo