የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 11/15 ገጽ 12-17
  • በይሖዋ መንገድ በድፍረት ተመላለሱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋ መንገድ በድፍረት ተመላለሱ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ድፍረት ምንድን ነው?
  • የአምላክን መልእክት ለማወጅ ያሳዩት ድፍረት
  • በመከራ ጊዜ ያሳዩት ድፍረት
  • አምላክን ለመታዘዝ ያሳዩት ድፍረት
  • ከአምላክ ሕዝብ ጎን ለመቆም ያሳዩት ድፍረት
  • ይሖዋን ‘መሉ በሙሉ ለመከተል’ ያሳዩት ድፍረት
  • በአምላክ ለመተማመን ያሳዩት ድፍረት
  • ይሖዋን ለማክበርና ንፁሕ አምልኮን ለማስፋፋት ያሳዩት ድፍረት
  • “ደፋርና ብርቱ ሁን”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ደፋሮች ሁኑ!
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ደፋር ሁኑ​—ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • “ደፋር . . . ሁን፤ ሥራህንም ጀምር”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 11/15 ገጽ 12-17

በይሖዋ መንገድ በድፍረት ተመላለሱ

“ ይሖዋን የሚፈሩት ሁሉ፣ በመንገዶቹም የሚመላለሱ ደስተኞች ናቸው።”  — መዝሙር 128:​1 አዓት

1, 2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡልን የቀድሞ የይሖዋ ምስክሮች ቃላትና ተግባር ምን እርዳታ ይሰጡናል?

የይሖዋ ቅዱስ ቃል በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ የደረሱባቸውን መከራዎችና ያገኙትን ደስታ በሚተርኩ ዘገባዎች የተሞላ ነው። የኖኅን፣ የአብርሃምን፣ የሣራን፣ የኢያሱን፣ የዲቦራን፣ የባራቅን፣ የዳዊትንና የሌሎችንም ጎላ ብለው የሚታዩና ሕያው ተሞክሮዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ እናነባለን። ሁሉም ልዩ የሆነ የጋራ ባሕርይ የነበራቸው በምድር ላይ ኖረው ያለፉ ሰዎች ናቸው። በአምላክ ላይ እምነት ነበራቸው፤ በመንገዶቹም በድፍረት ተመላልሰዋል።

2 በአምላክ መንገዶች ለመመላለስ በምንጣጣርበት ጊዜ የቀድሞዎቹ የይሖዋ ምስክሮች የተናገሯቸው ቃላትና ተግባራቸው ማበረታቻ ሊሆኑን ይችላሉ። ከዚህም በላይ ለአምላክ የጠለቀ አክብሮት ካሳየንና እርሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት ካለን ደስታ ዕጣ ፈንታችን ይሆናል። በሕይወት ውስጥ መከራዎች ቢያጋጥሙንም እንኳን በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው መዝሙራዊ “ይሖዋን የሚፈሩት ሁሉ፣ በመንገዶቹም የሚመላለሱ ደስተኞች ናቸው” በማለት ስለዘመረ ደስተኞች መሆናችን የተረጋገጠ ነው።  — መዝሙር 128:​1 አዓት

ድፍረት ምንድን ነው?

3. ድፍረት ምንድን ነው?

3 በይሖዋ መንገዶች ለመመላስ ድፍረት ሊኖረን ይገባል። እንዲያውም ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ሕዝቦች ይህን ባሕሪ እንዲያሳዩ ያዛሉ። ለምሳሌ ያህል መዝሙራዊው ዳዊት “በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፣ በርቱ ልባችሁም ይጥና” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 31:​24) ድፍረት ተብሎ የተተረጎመው ካሬጅ የተሰኘው የእንግሊዝኛ ቃል “በአደገኛ ሁኔታዎች ሥር ለመቀጠል፣ ለመጽናትና አደጋን፣ ፍርሃትን፣ ወይም ችግርን ለመቋቋም የሚያስችል የአእምሮ ወይም የመንፈስ ጥንካሬ” ነው። (ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሌጂየት ዲክሽነሪ ) ደፋር ሰው ብርቱ፣ የማይፈራና ጀግና ነው። ይሖዋ ለሕዝቡ ድፍረት የሚሰጣቸው መሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ለአገልግሎት ጓደኛው ለጢሞቴዎስ እንደሚከተለው ሲል ከጻፈለት ቃላት በግልጽ ሊታይ ይችላል:- “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።” — 2 ጢሞቴዎስ 1:​7

4. ድፍረት ለማግኘት የሚረዳው አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

4 አምላክ የሚሰጠውን ድፍረት ለማግኘት አንዱ መንገድ ከጸሎት ጋር የይሖዋ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የቀረቡት ብዙ ታሪኮች ከበፊቱ የበለጠ ደፋሮች እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ። ስለዚህ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሠፍሮ ከሚገኘው በይሖዋ መንገድ በድፍረት ስለተመላለሱ አንዳንድ ሰዎች ከሚናገረው ታሪክ ምን ልንማር እንደምንችል አስቀድመን እንመልከት።

የአምላክን መልእክት ለማወጅ ያሳዩት ድፍረት

5. የሄኖክ ድፍረት በዘመናችን ያሉትን የይሖዋ አገልጋዮች እንዴት ሊጠቅማቸው ይችላል?

5 የሄኖክ ድፍረት በአሁኑ ጊዜ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን መልእክት በድፍረት እንዲናገሩ ሊረዳቸው ይችላል። ሄኖክ ከመወለዱ በፊት ‘በይሖዋ ስም መጠራት ተጀምሮ ነበር።’ ሰዎች የይሖዋን ስም “በከንቱ መጥራት ጀመሩ” ሲሉ አንዳንድ ምሁራን ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 4:​25, 26፤ 5:​3, 6) መለኮታዊው ስም ለሰዎች ወይም ለጣዖቶችም እንኳን ሳይቀር ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ሄኖክ በ3404 ከዘአበ በተወለደበት ጊዜ የሐሰት ሃይማኖት በመስፋፋት ላይ ነበር። እንዲያውም በዚያ ዘመን ይሖዋ ከገለጠው እውነት ጋር የሚስማማ የጽድቅ አካሄድን በመከተል ‘ከአምላክ ጋር የተመላለሰው’ እርሱ ብቻ የነበረ ይመስላል። — ዘፍጥረት 5:​18, 24

6. (ሀ) ሄኖክ ያውጅ የነበረው ምን ኃይለኛ መልእክት ነበር? (ለ) እኛስ ምን ትምክህት ሊኖረን ይችላል?

6 ሄኖክ የአምላክን መልእክት በድፍረት አድርሷል። ይህንንም ያደረገው በስብከት ሳይሆን አልቀረም። (ዕብራውያን 11:​5፤ ከ2 ጴጥሮስ 2:​5 ጋር አወዳድር።) ይህ ብቸኛ ምስክር “እነሆ፣ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና [ዘግናኝ] ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል” ሲል አውጆአል። (ይሁዳ 14, 15) ሄኖክ ለአምላክ ምንም ደንታ ያልነበራቸው ሰዎችን የሚያወግዘውን ያንን መልእክት ለማድረስ ይሖዋ በሚለው ስም ለመጠቀም ድፍረት ነበረው። አምላክም ሄኖክ ያንን ኃይለኛ መልእክት እንዲያደርስ ድፍረት እንደሰጠው ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ምስክሮቹንም በአገልግሎታቸው፣ በትምህርት ቤትና በሌላም ቦታ ቃሉን በድፍረት እንዲናገሩ ኃይል ሰጥቶአቸዋል። — ከሥራ 4:​29–31 ጋር አወዳድር።

በመከራ ጊዜ ያሳዩት ድፍረት

7. ኖኅ የድፍረት ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

7 የኖኅ ምሳሌ መከራ በሚደርስብን ጊዜ የጽድቅ ሥራዎችን በመፈጸም ረገድ ደፋሮች እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ኖህ ስለ ምድር አቀፍ የጥፋት ውኃ በተሰጠው መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ረገድ በድፍረትና በእምነት እርምጃ በመውሰድ “ቤተሰዎቹን ለማዳን መርከብን . . . አዘጋጀ።” ኖኅ በታዛዥነትና በጽድቅ ሥራዎች እምነት የለሹን ዓለም ስለክፉ ተግባሮቹ በመኮነን ጥፋት የሚገባው መሆኑን አረጋግጧል። (ዕብራውያን 11:​7፤ ዘፍጥረት 6:​13–22፤ 7:​16) ስለ ኖኅ አካሄድ ማሰላሰል የዘመናችን የአምላክ አገልጋዮች ክርስቲያናዊ አገልግሎትን በመሰሉ የጽድቅ ሥራዎች በድፍረት እንዲጠመዱ ይረዳቸዋል።

8. (ሀ) ኖኅ ደፋር ‘የጽድቅ ሰባኪ’ በመሆን ምን አጋጥሞታል? (ለ) እኛም ደፋር የጽድቅ ሰባኪዎች ከሆንን ይሖዋ ምን ያደርግልናል?

8 የጽድቅ አካሄድን የምንከተል ከሆነና አንድ ዓይነት መከራ ደርሶብን እንዴት ልንወጣው እንደምንችል ካላወቅን እንድንቋቋመው የሚያስችለንን ጥበብ እንድናገኝ እንጸልይ። (ያዕቆብ 1:​5–8) ኖኅ ችግር ሲደርስበት ለአምላክ ያሳየው ታማኝነት መከራን በድፍረትና በታማኝነት ለመቋቋም የሚቻል መሆኑን ያሳያል። ኖኅ ክፉ ከነበረው ዓለምና ሥጋ ከለበሱ መላእክትና ዲቃላ ከሆኑ ዘሮቻቸው ያጋጠመውን ግፊት ተቋቁሟል። አዎን፣ ኖኅ ወደ ጥፋት በማምራት ላይ ለነበረው “ለቀደመው ዓለም” ደፋር ‘የጽድቅ ሰባኪ’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:​4, 5፤ ዘፍጥረት 6:​1–9) ከጥፋት ውኃ በፊት ለነበሩት ሰዎች የአምላክን ማስጠንቀቂያ የሚያስታውቅ አዋጅ ነጋሪ በመሆን በድፍረት ቢነግራቸውም “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስከወሰደ ድረስ አላወቁም [አላስተዋሉም አዓት]።” (ማቴዎስ 24:​36–39) ስደት ቢደርስብንና ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን መልእክታችንን አንቀበልም ቢሉንም አምላክ ኖኅን እንደደገፈው ሁሉ እኛም በጽድቅ ሰባኪነታችን የእርሱን የመሰለ እምነትና ድፍረት ካሳየን ይሖዋ ደግፎ የሚያቆመን መሆኑን እናስታውስ።

አምላክን ለመታዘዝ ያሳዩት ድፍረት

9, 10. አብርሃም፣ ሣራና ይስሐቅ በድፍረት ታዛዥነትን ያሳዩት በምን መንገዶች ነበር?

9 ለአምላክ በድፍረት የምንታዘዝ እንድንሆን “የእግዚአብሔር ወዳጅ” አብርሃም ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። (ያዕቆብ 2:​23) አብርሃም ይሖዋን ለመታዘዝና ቁሳዊ ምቾት የሞላባትን የከለዳውያን ከተማ ዑርን ትቶ ለመሄድ እምነትና ድፍረት አስፈልጎታል። “የምድር ነገዶች ሁሉ” በእርሱ አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩና ዘሮቹ የሚኖሩበት ምድር እንደሚሰጣቸው አምላክ በሰጠው ተስፋ አመነ። (ዘፍጥረት 12:​1–9፤ 15:​18–21) አብርሃም ‘በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር እንደመጻተኛ በእምነት ተቀምጦ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ’ ተጠባብቋል። ይህችም ከተማ የአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ስትሆን በዚህች መንግሥት ግዛት ሥር ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ ይኖራል። — ዕብራውያን 11:​8–16

10 የአብርሃም ሚስት ሣራ ዑርን ለቃ ከባሏ ጋር ወደ ባዕድ ምድር ለመሄድና እዚያም የሚያጋጥማቸውን ችግር ሁሉ ለመቋቋም የሚያስፈልገው እምነትና ድፍረት ነበራት። ለአምላክ በድፍረት በመታዘዟ እንዴት ተባረከች! 90 ዓመት እስኪሆናት ድረስ መኻን ሆና ብትቆይም “ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ስለቆጠረች፣ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች።” ከጊዜ በኋላም ይስሐቅን ወለደች። (ዕብራውያን 11:​11, 12፤ ዘፍጥረት 17:​15–17፤ 18:​11፤ 21:​1–7) ዓመታት ካለፉ በኋላ አብርሃም በድፍረት አምላክን በመታዘዝ “ይስሐቅን በእምነት አቀረበ።” የእስራኤላውያን አባት የሆነው አብርሃም ልጁን እንዳያርደው የአምላክ መልአክ ስላገደው ደፋርና ታዛዥ የሆነ ልጁን ከሞት “በምሳሌ አገኘው።” በዚህ መንገድ አብርሃምና ይስሐቅ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያገኙ ዘንድ ይሖዋ አምላክ ልጁን ቤዛ አድርጎ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ትንቢታዊ ድራማ ሠርተዋል። (ዕብራውያን 11:​17–19፤ ዘፍጥረት 22:​1–19፤ ዮሐንስ 3:​16) በእርግጥም አብርሃም፣ ሣራና ይስሐቅ ያሳዩት ድፍረት የተሞላበት ታዛዥነት ይሖዋን እንድንታዘዝና ሁልጊዜ ፈቃዱን እንድናደርግ ሊያንቀሳቅሰን ይገባል።

ከአምላክ ሕዝብ ጎን ለመቆም ያሳዩት ድፍረት

11, 12. (ሀ) ሙሴ የይሖዋ ሕዝቦችን በተመለከተ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነበር? (ለ) ከሙሴ ደፋርነት አንፃር ምን ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል?

11 ሙሴ በድፍረት ከአምላክ ጭቁን ሕዝቦች ጎን ቆሟል። በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የሙሴ ወላጆች ራሳቸው ድፍረት አሳይተዋል። ዕብራውያን ወንዶች ልጆች ሲወለዱ እንዲገደሉ ንጉሡ ያስተላለፈውን ትእዛዝ ሳይፈሩ የደንገል ሣጥን አዘጋጅተው በአባይ ወንዝ ዳር በቄጠማ ውስጥ ሙሴን ሸሸጉት። ሙሴንም የፈርዖን ሴት ልጅ አገኘችውና እንደራሷ ልጅ አድርጋ አሳደገችው። አስቀድሞ ግን በወላጆቹ ቤት መንፈሳዊ ሥልጠና አግኝቷል። ሙሴ በፈርዖን ቤተሰብ አባልነቱ “የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ”፤ በአእምሮአዊና በአካላዊ ብቃቱ ጎበዝ በመሆን “በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ።” — ሥራ 7:​20–22፤ ዘጸአት 2:​1–10፤ 6:​20

12 ሙሴ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል በመሆኑ ቁሳዊ ጥቅም የነበረው ቢሆንም እንኳን በወቅቱ ግብፃውያን በባርነት ይዘዋቸው ከነበሩት የይሖዋ አምላኪዎች ጎን ለመቆም በድፍረት መርጧል። ለአንድ እስራኤላዊ በሚከላከልበት ጊዜ አንድ ግብፃዊ ገደለና ወደ ምድያም ምድር ሸሽቶ ሄደ። (ዘጸአት 2:​11–15) 40 ዓመታት ያህል ካለፉ በኋላ እስራኤላውያንን እየመራ ከባርነት እንዲያወጣ አምላክ ተጠቀመበት። በዚያን ጊዜ ሙሴ ስለ እስራኤል ሆኖ ይሖዋን በመወከሉ ምክንያት እንደሚገድለው የዛተበትን “የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር ተወ።” ሙሴ “የማይታየውን” ይሖዋ አምላክን እንደሚያየው ሆኖ ተመላልሷል። (ዕብራውያን 11:​23–29፤ ዘጸአት 10:​28) አንተስ መከራና ስደት ቢደርስብህም እንኳን ከይሖዋና ከሕዝቡ ጋር ተጣብቀህ ለመኖር የሚያስችልህ ይህን የመሰለ እምነትና ድፍረት አለህን?

ይሖዋን ‘መሉ በሙሉ ለመከተል’ ያሳዩት ድፍረት

13. ኢያሱና ካሌብ የድፍረት ምሳሌ የተውልን እንዴት ነው?

13 ደፋሮቹ ኢያሱና ካሌብ በአምላክ መንገድ ለመመላለስ እንደምንችል ማስረጃ ይሆኑናል። እነርሱ “ሙሉ በሙሉ ይሖዋን ተከትለዋል።” (ዘኁልቁ 32:​12 አዓት) ኢያሱና ካሌብ የተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ ከተላኩት 12 ሰዎች መካከል ነበሩ። አሥሩ ሰላዮች የምድሪቱን ነዋሪዎች በመፍራት እስራኤላውያን ወደ ከነዓን እንዳይገቡ ለማከላከል ሞክረዋል። ኢያሱና ካሌብ ግን በድፍረት እንደሚከተለው በማለት ተናገሩ:- “እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፣ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው።” (ዘኁልቁ 14:​8, 9) ያ የእስራኤላውያን ትውልድ እምነትና ድፍረት ጎድሎት ስለነበር ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገባ ቀርቷል። ኢያሱና ካሌብ ግን ከአዲሱ ትውልድ ጋር ገብ ተዋል።

14, 15. (ሀ) ኢያሱ በኢያሱ 1:​7, 8 ላይ የተጻፉትን ቃላት በሥራ ሲያውላቸው እሱና እስራኤላውያን ምን አጋጠማቸው? (ለ) ድፍረትን በተመለከተ ከኢያሱና ከካሌብ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

14 አምላክ ለኢያሱ እንዲህ አለው:- “ነገር ግን ጽና፣ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፣ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።”  — ኢያሱ 1:​7, 8

15 ኢያሱ እነዚህን ቃላት በሥራ ባዋላቸው ጊዜ ኢያሪኮና ሌሎችም ከተሞች በእስራኤላውያን እጅ ወደቁ። አልፎ ተርፎም እስራኤላውያን በገባዖን ምድር ላይ በተደረገው ውጊያ ድል እስኪያደርጉ ድረስ ቀኑ እንዳይመሽ አምላክ ፀሐይ ባለችበት እንድትቆም አድርጓል። (ኢያሱ 10:​6–14) “በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ” ከሆኑ የጠላት ሠራዊት ትልቅ አደጋ ባንዣበባቸው ጊዜ ኢያሱ በድፍረት እርምጃ ወስዷል፤ አምላክም እስራኤልን እንደገና ድል አቀዳጅቶታል። (ኢያሱ 11:​1–9) እኛም ፍጹማን ያልሆን ሰዎች ብንሆንም ኢያሱና ካሌብ እንዳደረጉት ሙሉ በሙሉ ይሖዋን ልንከተል እንችላለን፤ አምላክም በመንገዶቹ በድፍረት እንድንመላለስ ኃይል ሊሰጠን ይችላል።

በአምላክ ለመተማመን ያሳዩት ድፍረት

16. ዲቦራ፣ ባራቅና ኢያዔል ድፍረት ያሳዩት በምን መንገዶች ነው?

16 መሳፍንት በእስራኤል ላይ ይፈርዱ በነበሩበት ዘመን ከተፈጸሙት ሁኔታዎች እንደሚታየው በአምላክ ላይ በድፍረት መተማመን ዋጋ ያስገኛል። (ሩት 1:​1) ለምሳሌ ያህል መስፍኑ ባራቅና ነቢይቱ ዲቦራ በድፍረት በአምላክ ተማምነዋል። ይሖዋ ዲቦራን 10,000 ያህል ሰዎችን ወደ ታቦር ተራራ እንዲሰበስብ ባራቅን እንድታነሳሳው ባደረገበት ጊዜ ከነዓናዊው ንጉሥ ኢያቢስ እስራኤላውያንን ለ20 ዓመታት ጨቁኖ ሲገዛቸው ቆይቶ ነበር። የኢያቢስ የሠራዊት አለቃ የነበረው ሲሣራ የእስራኤል ሰዎች በደልዳላ ሜዳ ላይ በ900 የብረት ሠረገሎች የታጀበ ሠራዊቱን ሊገጥሙ አይችሉም ብሎ በማመን ፏፏቴ ወዳለበት የቂሶን ሸለቆ በፍጥነት ወረደ። እስራኤላውያን ወደ ሸለቆው ሜዳማ ሥፍራ በዘመቱ ጊዜ አምላክ ስለ እነርሱ ስለተዋጋላቸው ድንገት ደራሽ ውኃ መጥቶ የጦር ሜዳውን ወደ ረግረግነት ለወጠውና የሲሣራ ሠረገሎች መንቀሳቀስ ተሳናቸው። የባራቅ ሰዎች አየሉ፤ ስለዚህም “የሲሣራ ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ።” ሲሣራ ሸሽቶ ወደ ኢያዔል ድንኳን ገብቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢያዔል እንቅልፍ በወሰደው ጊዜ ካስማ ወስዳ በጆሮ ግንዱ ላይ በመቸከል እርሱን ለመግደል ድፍረት ነበራት። ዲቦራ ለባራቅ በትንቢት እንደነገረችው የዚህ ድል “ክብር” በዚህ መንገድ ለሴት ተሰጥቷል። ዲቦራ፣ ባራቅና ኢያዔል በድፍረት በአምላክ በመተማመናቸው እስራኤል “አርባ ዓመት ያህል አረፈች።”  — መሳፍንት 4:​1–22፤ 5:​31

17. በድፍረት በይሖዋ መተማመንን በተመለከተ መስፍኑ ጌዴዎን የተወልን ምሳሌ ምንድን ነው?

17 ምድያማውያንና ሌሎች እስራኤልን በወረሩ ጊዜ መስፍኑ ጌዴዎን በድፍረት በይሖዋ አምላክ ተማመነ። የእስራኤል 32,000 ተዋጊ ሰዎች በግምት 135,000 የሚያህሉት ወራሪዎቻቸው በቁጥር ቢበልጧቸውም ይህ ቁጥራቸውም ቢሆን ከፍተኛ ስለነበር አምላክ የሚሰጣቸውን ድል በራሳችን ጀግንነት የተገኘ ነው ለማለት ሊቃጣቸው ይችል ነበር። ስለዚህ ጌዴዎን በይሖዋ መመሪያ መሠረት ሠራዊቱን ወደ 300 ዝቅ አደረገና መቶ መቶውን አድርጎ በሦስት ቡድኖች ከፈላቸው። (መሳፍንት 7:​1–7, 16፤ 8:​10) ሦስት መቶው ሠራዊት የምድያማውያንን ሠፈር በከበቡ ጊዜ እያንዳንዳቸው ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ የያዘ ማሰሮ ይዘው ነበር። ምልክት በተሰጣቸው ጊዜ ቀንደ መለከታቸውን ነፉ፣ ማሰሮአቸውን ሰባበሩ፣ ችቦአቸውንም አበሩና ከፍ አድርገው በመያዝ “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጮኹ። (መሳፍንት 7:​20) የተሸበሩት ምድያማውያን መሸሽ ጀመሩና በቁጥጥር ሥር ዋሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች በድፍረት በአምላክ መተማመን በዛሬው ጊዜም በምላሹ ዋጋ የሚያስገኝ መሆኑን እንድናምን ሊያደርጉን ይገባል።

ይሖዋን ለማክበርና ንፁሕ አምልኮን ለማስፋፋት ያሳዩት ድፍረት

18. ዳዊት በድፍረት ጎልያድን መትቶ በገደለው ጊዜ ያደረገው ምን ነበር?

18 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ይሖዋን ለማክበርና ንፁሕ አምልኮን ለማስፋፋት የሚያስችል ድፍረት ይሰጣሉ። የአባቱን በጎች በድፍረት ከአራዊት ያስጥላቸው የነበረው ወጣቱ ዳዊት በግዙፉ ፍልስጥኤማዊ በጎልያድ ፊትም ደፋር መሆኑ ተረጋግጧል። “አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ” አለ ዳዊት “እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፣ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ . . . ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነው።” (1 ሳሙኤል 17:​32–37, 45–47) ዳዊት በመለኮታዊ እርዳታ በደፋርነት ይሖዋን ለማክበር፣ ጎልያድን መትቶ ለመግደልና እንዲህ በማድረጉም ፍልስጥኤማውያን በንፁሕ አምልኮ ላይ የፈጠሩትን ስጋት ለማስወገድ አስፈላጊ ሚና ተጫውቷል።

19. ሰሎሞን ድፍረት ያስፈለገው ለምን ፕሮጀክት ነበር? እርሱ ያደረገው ነገር በዘመናችንም ሊሠራ የሚችለውስ እንዴት ነው?

19 የንጉሥ ዳዊት ልጅ ሰሎሞን የአምላክን ቤተ መቅደስ ሊሠራ በተቃረበበት ጊዜ በዕድሜ የሸመገለው አባቱ “ጠንክር፣ አይዞህ፣ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፣ አትደንግጥም፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነው ሥራ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ እርሱ አይተውህም፣ አይጥልህምም” በማለት አጥብቆ መከረው። (1 ዜና መዋዕል 28:​20) ሰሎሞን በድፍረት እርምጃ በመውሰድ ቤተ መቅደሱን በተሳካ ሁኔታ ሠርቶ ጨረሰ። በአሁኑ ጊዜ አንድ ቲኦክራሲያዊ የሕንፃ ፕሮግራም ተፈታታኝ ሁኔታ በሚፈጥርበት ጊዜ “ጠንክር፣ አይዞህ፣ አድርገውም” የሚሉትን የዳዊትን ቃላት እናስታውስ። ይሖዋን ለማክበርና ንፁሕ አምልኮን ለማስፋፋት እንዴት ያለ ጥሩ መንገድ ነው!

20. ንጉሡ አሳ የበረታው በምን ረገድ ነበር?

20 ንጉሥ አሳ አምላክን ለማክበርና ንፁሕ አምልኮን ለማስፋፋት ስለፈለገ ይሁዳን ከጣዖትና በቤተ መቅደስ ውስጥ ዝሙት ይሠሩ ከነበሩት ወንድ አመንዝራዎች አጸዳት። በይሖዋ አምልኮ ላይ ክህደት የፈጸመችውን አያቱንም ከከፍተኛ ሥልጣኗ ሽሮ የሠራችውን “አስጸያፊ ጣዖት” አቃጠለው። (1 ነገሥት 15:​11–13 የ1980 ትርጉም ) አዎን፣ አሳ “ . . . ልቡ ጸና፣ ከይሁዳና ከብንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ።” (2 ዜና መዋዕል 15:​8) አንተም እንደዚሁ ሃይማኖታዊ ክህደትን በድፍረት በመቃወም ንፁሕ አምልኮን ታስፋፋለህን? ቁሳዊ ሀብትህን የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማራመድ እየተጠቀምክበት ነውን? ከምስክሮቹ እንደ አንዱ በመሆን የምሥራቹን በማወጅ መደበኛ ድርሻ እንዲኖርህ በማድረግ ይሖዋን ለማክበር እየጣርክ ነውን?

21. (ሀ) የቅድመ ክርስትና ፍጹም አቋም ጠባቂዎች ታሪክ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው። (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንመለከተው ምንድን ነው?

21 ደፋሮች የሆኑ የቅድመ ክርስትና ፍጹም አቋም ጠባቂዎችን በተመለከተ አምላክ ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪኮች ተመዝግበው እንዲቆዩልን ስላደረገ ምንኛ አመስጋኞች ነን! መልካም ምሳሌነታቸው ለይሖዋ በድፍረት፣ በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብለት ሊረዳን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። (ዕብራውያን 12:​28) ይሁን እንጂ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችም ቢሆኑ በተግባር የታዩ የአምላካዊ ድፍረት ምሳሌዎችን ይዘውልናል። ከእነዚህ ታሪኮች አንዳንዶቹ በይሖዋ መንገዶች በድፍረት እንድንመላለስ ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ድፍረት ምንድን ነው?

◻ ሄኖክና ኖኅ ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነበር?

◻ አብርሃም፣ ሣራና ይስሐቅ በድፍረት እርምጃ የወሰዱት በምን በምን ረገድ ነበር?

◻ ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብ ምን የድፍረት ምሳሌዎችን ትተውልናል?

◻ አንዳንዶች በአምላክ ለመተማመን ድፍረት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነበር?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጌዴዎንና አነስተኛ ጭፍራው በድፍረት በይሖዋ ተማምነዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ