የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 12/1 ገጽ 10-13
  • በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ የሚወስደው የማዳን እርምጃ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ የሚወስደው የማዳን እርምጃ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በተግባር የተገለጸ ፍቅር
  • ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት
  • የእውነተኛ ጥበቃ ምንጭ
  • የትኛውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ሊያጠፋው የማይችል ነገር
    ንቁ!—2003
  • የእርዳታ አገልግሎት
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • በማያንማር በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ሰዎች እርዳታ አገኙ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ በ2023—“የይሖዋን ፍቅር በዓይናችን አይተናል”
    የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 12/1 ገጽ 10-13

በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ የሚወስደው የማዳን እርምጃ

መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል” በተጨማሪም “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን . . . ያውቃል” በማለት ስለ ይሖዋ ይነግረናል። — መዝሙር 34:​19፤ 2 ጴጥሮስ 2:​9

ይሖዋ ሕዝቦቹ በሚቸገሩበት ጊዜ ለእርዳታ የሚደርስላቸው እንዴት ነው? አንዳንድ ሰዎች አምላክ ማድረግ አለበት ብለው እንደሚያስቡት የተፈጥሮ ኃይሎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ በመቀልበስ ወይም ሰው ሊያደርግ የማይችለው ልዩ ነገር በመፈጸም አይደለም። ከዚህ ይልቅ አብዛኞቹ ሰዎች ሊገነዘቡ በማይችሉት በሌላ ኃይል፣ ማለትም በፍቅር አማካኝነት ነው። አዎን፣ ይሖዋ ሕዝቡን ይወዳቸዋል፤ ስለዚህም በመካከላቸው ጠንካራ የሆነ የእርስ በርስ ፍቅር እንዲስፋፋ በማድረግ እንደተአምር ሊቆጠር የሚችል ድርጊት ሊፈጽምላቸው ችሎአል። — 1 ዮሐንስ 4:​10–12, 21

አንዳንድ ሰዎች ለአደጋ ጊዜ የሚያስፈልገው ምግብ፣ መድኃኒትና የመገልገያ መሣሪያ ነው እንጂ ፍቅር አይደለም ብለው ይከራከሩ ይሆናል። በእርግጥ ምግብ፣ መድኃኒትና የመገልገያ መሣሪያ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ያስረዳል:- “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።”  — 1 ቆሮንቶስ 13:​2, 3

ብዙ ጊዜ የሚያስፈልጓቸው እርዳታ የተላከላቸው ሕዝቦች በበሽታና በረሀብ እያለቁ ለእርዳታ የተላከው ምግብና ቁሳቁስ ግን በወደብ ላይ ተቀምጦ በመበስበስ ላይ እንደሚገኝ ወይም በአይጦች እየተበላ እንዳለ እናነባለን። ወይም ደግሞ ይባስ ብሎ እነዚህ የእርዳታ ቁሳቁሶች የግል ትርፍ በሚያግበሰብሱ ስግብግብና ይሉኝታ ቢስ በሆኑ ሰዎች እጅ ይገቡ ይሆናል። በመሆኑም የእርዳታ አቅርቦት እንዲገኝ ማድረግ አንድ ነገር ሲሆን የተቸገሩት ሰዎች እንዲጠቀሙበት ማድረግ ግን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው። እዚህ ላይ እውነተኛ ፍቅርና አሳቢነት ወሳኝነት አለው።

በተግባር የተገለጸ ፍቅር

በመስከረም ወር 1992 ሀሪኬን ኤኔኬ የተባለ አውሎ ነፋስ 55,000 ሕዝብ የሚኖርባትን በካዋይ የምትገኘውን የሀዋይ ደሴት መትቷት ነበር። አውሎ ነፋሱ በሰዓት 210 ኪሎ ሜትር ፍጥነት የሚጓዙ ነፋሶችን ይዞ በ260 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ይነፍስ ስለነበር 2 ሰዎችን ገድሎ 98 ሰዎችን አቁስሎአል። ካሉት ቤቶች ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑትን አፍርሶ 8,000 ሰዎችን ያለመጠለያ አስቀርቶአቸዋል። 1 ቢልዮን ዶላር የሚገመት የንብረት ጥፋትም አድርሷል። በዚያች አነስተኛ ከተማ ከሚኖሩት ሰዎች ውስጥ 800 የሚሆኑት በስድስት ጉባኤዎች የተደራጁ የይሖዋ ምስክሮች ነበሩ። ታዲያ እነርሱስ እንዴት ሆኑ?

ኤኔኬ ከመነሳቱ በፊትም የጉባኤ ሽማግሌዎቹ በተጓዥ የበላይ ተመልካቹ መሪነት የጉባኤዎቹ አባሎች በሙሉ ደህና መሆናቸውን ለማረጋገጥና አውሎ ነፋሱ ማጥቃት የሚጀምርበትን ጊዜ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ለማድረግ ሁሉንም አግኝተዋቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅራዊ አሳቢነት በምስክሮቹ መካከል የከፋ ጉዳት ወይም ሞት እንዳይደርስ ለመከላከል ረድቷል። — ከኢሳይያስ 32:​1, 2 ጋር አወዳድር።

መገናኛዎችና መጓጓዣዎች በጣም የተፋለሱ ቢሆንም በሆኖሉሉ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የላካቸው ሦስት ተወካዮች ወደ ኩዋይ በአይሮፕላን እንዲበሩ በሲቪል መከላከያው ድርጅት ልዩ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ስለነበረ አውሎ ነፋሱ እንደቆመ በአደጋው ቦታ ለመድረስ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለመሆን ችለዋል። እንደደረሱም ከአካባቢው የይሖዋ ምስክሮች ጋር ተገናኙና በተከታዩ ቀን እርዳታው ስለሚከፋፈልበት ዘዴ እቅድ ለማውጣት ስብሰባ አደረጉ። የሚያስፈልጉትን እርዳታዎች የሚገመግምና ቁሳቁሶቹን በሆኖሉሉ ቅርንጫፍ ቢሮ በኩል የሚቀበል የእርዳታ ኮሚቴ ተቋቋመ። ቀንና ሌሊት በመሥራት ቁሳቁሶቹን ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በማድረስና ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች በማጽዳትና በመጠገን ረገድ ለሚከናወነው ሥራ አመራር ሰጡ።

በሌሎች ደሴቶች የሚኖሩ ምስክሮችም ለተቸገሩት ወንድሞቻቸው በአፋጣኝ ደርሰውላቸዋል። በኩዋይ የሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ እንደተከፈተ 70 ምስክሮች በአይሮፕላን መጡ። የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን፣ የካምፕ ምድጃዎችን፣ ፋኖሶችንና ምግብ ጨምሮ 100,000 ዶላር የሚገመት የእርዳታ ቁሳቁስ በመርከብ ተጭኖ ደረሰ። በደሴቲቱ ካሉት የመንግሥት አዳራሾች አንዱ በግምጃ ቤትነት አገለገለ፤ ይሁን እንጂ ይዘረፋል የሚል ስጋት ነበረ። በዚህ ጊዜ የጦር ሠራዊት የጭነት መኪናዎች ወደ መንግሥት አዳራሹ የመኪና ማቆሚያ መጡና ሾፌሮቻቸው መኪናዎቻቸውን በዚያ ማቆም ይችሉ እንደሆነ ጠየቁ። የጭነት መኪናዎቹን እንዲጠብቁ በተመደቡት ወታደሮች ምክንያት የእርዳታ ዕቃዎቹ ከመዘረፍ ዳኑ።

ወንድሞች የኤሌክትሪክ ማመንጫዎቹን በየቤቱ እየወሰዱ የባለቤቶቹ ማቀዝቀዣዎች እንዲሠሩላቸው ለማስቻል ለሁለት ወይም ለሦስት ሰዓቶች ያሠሩአቸው ነበር። በተጨማሪም በቡድን በቡድን ሆነው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች እንዲያጸዱና እንዲጠግኑ ወደ ልዩ ልዩ ቤቶች ተላኩ። ወንድሞች ባሏ በእምነቷ ምክንያት በብርቱ ይቃወማት የነበረችን አንዲት እህት ቤት በሚጠግኑበት ጊዜ ባሏ ልቡ በጣም ከመነካቱ የተነሳ ቆሞ እየተመለከተ ያለቅስ ነበር። አንድ ሌላ የወንድሞች ቡድን በሥራ ላይ እንዳለ የተመለከተ ከመሃል አገር የመጣ አንድ ጎብኚ በምስክሮቹ ጠባይና ቅንጅት በጣም ከመደነቁ የተነሳ ወደነሱ ቀርቦ ይህን ያህል ልዩ ሰዎች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ ጠየቀ። ልዩ ያደረጋቸው ለአምላክና ለክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ያላቸው ፍቅር እንደሆነ አንድ ወንድም በገለጸለት ጊዜ የሰውየው መልስ “አምላክን ማወቅ የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ነበር። (ማቴዎስ 22:​37–40) ከዚያም ጨምሮ “እናንተ በጣም የተደራጃችሁ ስለሆናችሁ ወደ ፍሎሪዳ ስመለስ አንድ ሰው እቤቴ እንዲጠብቀኝ ለማድረግ ትችሉ ይሆናል” ብሏቸ⁠ዋል።

የይሖዋ ምስክሮች በኩዋይ በጠቅላላው 295 ቤቶችን በማጽዳትና በመጠገን እርዳታ አበርክተዋል። ከነዚህም ውስጥ 207 ቤቶች አነስተኛ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ 54ቱ ግን ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው፣ 19ኙ ደግሞ ጨርሶ የተደመሰሱ ነበሩ። የምሥክሮቹ ሥራ በደሴቲቱ የሚኖር የይሖዋ ምስክር እንደሆነ የታወቀ እያንዳንዱ ሰው አስፈላጊውን እንክብካቤ አግኝቶ አንደሆነ ለማረጋገጥ ሄዶ መጠየቅን ይጨምር ነበር። ለአንዲት እህት የእርዳታ አቅርቦቶቹ በደረሷት ጊዜ ቡዲሂስት የሆነ አንድ ጎረቤቷ ከቡዲሂስት ባልደረቦቹ አንድ እሽግ የሻይ ቅጠል እንኳን እንዳላገኘ ተናገረ። ቤቷ በምስክሮቹ ቡድኖች የጸዳላት ሌላ ወይዘሮ “ብዙ ጊዜ ወደ ቤቴ መጥታችኋል። ጥሩ ጎረቤቶች እንደሆናችሁም አስብ ነበር። የጎረቤት ፍቅር መግለጫ የሆነው ይህ ሥራችሁ ግን ስለ ድርጅታችሁ ምንነት እንዳውቅ አስችሎኛል። ለጥረታችሁ ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ” ብላለች።

እርዳታ ለማከፋፈሉ ሥራ ተጠሪ የሆኑ ወንድሞች የክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውን ቁሳዊ ፍላጎት በማሟላት ብቻ ሳይወሰኑ ስለመንፈሳዊ ደህንነታቸውም የዚያኑ ያህል ያስባሉ። አውሎ ነፋሱ ከደረሰ በኋላ ሁለት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚበዙት ጉባኤዎች ስብሰባቸውን እያደረጉ ነበር። ወዲያውም አነስተኛ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል። የኩዋይ ሽማግሌዎች በደሴቲቱ ላይ ላለ ለእያንዳንዱ ምስክር የእረኝነት ጉብኝት እንዲያደርጉላቸው ለመርዳት 10 ሽማግሌዎች ከሌላ ደሴት ወደ ኩዋይ መጥተው ነበር። በተከታዩ እሁድ በስድስቱም ጉባኤዎች የመጠበቂያ ግንብ ጥናት፣ የእርዳታ ኮሚቴ አባል የሆነ አንድ ወንድም የእርዳታ አሰጣጡን በተመለከተ ለ30 ደቂቃ ንግግር አድርጓል፤ እንዲሁም ለዚሁ ዓላማ ከሆኖሉሉ በመጣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የ30 ደቂቃ የማጠቃለያ ንግግር ተደርጓል። በሥፍራው የተገኘ አንድ የዓይን ምስክር እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “በተሰጠው መልካም አመራር ሁሉም ከመጽናናታቸውም በላይ የተቀሩትን ችግሮቻቸውን ለመቋቋም በመንፈሳዊ ዝግጁ እንደሆኑ ተሰምቷቸዋል። ፕሮግራሙ ሲያልቅ ብዙዎቹ ያለቅሱ ነበር፣ ጭብጨባውም ከልብ የመነጨ ነበር።”

ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት

ይህን የመሰለው ፍቅርና አሳቢነት በዓለም ዙሪያ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች መለያ ምልክት ነው። ከአንድ ዓመት በፊት ሳይክሎን ቫል የሚባል አውሎ ነፋስ ምዕራብ ሳሞአን በጠራረገ ጊዜ በጣም ብዙ ጉዳት ደርሷል፣ በሌላው የዓለም ክፍል የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮችም በዚህ አገር ያሉትን በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት በፍጥነት መጡ። በኋላ የአገሩ መንግሥት የይሖዋ ምስክሮችን ጨምሮ ለሁሉም ሃይማኖቶች ለግቢያቸው ማሳደሻ የሚሆን ገንዘብ በሰጣቸው ጊዜ በግቢዎቻቸው ላይ የደረሰው ጉዳት በሙሉ የተጠገነ መሆኑንና ገንዘቡ አንዳንድ የመንግሥት ሕንፃዎችን ለማስጠገን ሊውል እንደሚችል ከሚገልጽ ደብዳቤ ጋር ገንዘቡን መለሱ። ያደረጉት ነገርም በአካባቢው ጋዜጣ ላይ ተገለጸ። አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ይህን በማየት በአውሎ ነፋሱ የተጎዱ አጥሮቻቸውን በሙሉ ያስጠገኑበት ወጪ ከኢንሹራንስ በተገኘ ገንዘብ የተሸፈነ ቢሆንም የራሳቸው ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የሰጠውን ገንዘብ በመቀበሏ ያፈሩ መሆናቸውን ለአንድ ምስክር ነግረውታል።

በተመሳሳይም በመስከረም 1992 በፈረንሳይ ደቡባዊ ምሥራቅ የሚገኘው የኡቫዝ ወንዝ ሞልቶ ቫዞ ላ ሮሜንና በአካባቢው የሚገኙ 15 መንደሮችን በደመሰሰ ጊዜ ምስክሮች ለእርዳታ የደረሱት ባፋጣኝ ነበር። ጎርፉ ባንድ ሌሊት 40 ሰዎች ገድሎ 400 ቤቶችን የደመሰሰና በመቶዎች በሚቆጠሩ ሌሎች ቤቶች ላይ ጉዳት በማድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ያለ ውኃ ወይም ያለ ኤሌክትሪክ አስቀርቷል። በሚቀጥለው ጧት ማለዳ ከአካባቢው ጉባኤዎች የመጡ ምስክሮች ማንም ሳይቀድማቸው በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ደረሱ። በአካባቢው ያሉ ምስክሮች የሆኑ ቤተሰቦች መጠለያ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በፍቅር ወደ ቤታቸው ወስደዋቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮች እርዳታ ለመስጠት ከሩቅና ከቅርብ መጥተው ነበር። በአራት ቡድኖች የተደራጁትን ፈቃደኛ ሠራተኞች ጥረት ለማስተባበር በአቅራቢያው ከተማ የእርዳታ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስለነበር ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ጭቃውን በማውጣት ቤቶችን አጽድተዋል፣ በጭቃ የተለወሱ ቁልል ልብሶችን አጥበዋል፣ ጎርፉ ችግር ባደረሰባቸው ቦታዎች ለሚገኙ ሁሉ ምግብ እና የመጠጥ ውኃ አድለዋል። የአካባቢውን ትምህርት ቤትና አያሌ የማዘጋጃ ቤት ሕንፃዎችን እንኳን ሳይቀር ለማጽዳት ፈቃደኞች ሆነዋል። ያልተቆጠበ ጥረታቸውም በወንድሞቻቸውና በመንደሩ ውስጥ ባሉት ሰዎች ሁሉ ተደንቋል።

በሌሎች ቦታዎችም ጎርፍ፣ ማዕበልና የምድር መናወጥ የመሳሰሉት አደጋዎች በይሖዋ ምስክሮች ላይ ደርሰውባቸዋል። እነዚህ አደጋዎች ባልታሰቡ ወይም ከቁጥጥራቸው ውጭ በሆኑ ሁኔታዎች የሚመጡ መሆናቸውን በመገንዘብ አምላክንም ሆነ ሌላ አይወቅሱም። (መክብብ 9:​11) ከዚህ ይልቅ ምንም ዓይነት የከፋ ሁኔታ ቢደርስባቸው ክርስቲያን ባልደረቦቻቸው የሚያሳዩት መሥዋዕታዊ ፍቅር እንደሚደርስላቸው ይተማመናሉ። እንደዚህ ያሉት ፍቅራዊ ተግባሮች በጋራ የሚያምኑት እምነታቸው ያስገኛቸው ውጤቶች ናቸው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:- “ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ ከእናንተ አንዱም:- በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልገውን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” — ያዕቆብ 2:​15–17

የእውነተኛ ጥበቃ ምንጭ

የይሖዋ ምስክሮች አንድ ዓይነት መለኮታዊ ጣልቃ ገብነትን የሚያመለክት ተአምር እንዲፈጸምላቸው ከመጠበቅ ይልቅ ጥበቃ የሚገኘው ከዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት እንደሆነ ይገነዘባሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ወንድማማችነት በችግር ጊዜ ሊያከናውን የሚችለው ነገር ከተአምር አያንስም። የይሖዋ ምስክሮች በማቴዎስ 17:​20 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ያስታውሳሉ:- “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ:- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።” አዎን፣ ፍቅር የታከለበት እውነተኛ ክርስቲያናዊ እምነት በሥራ ላይ ሲውል ተራራ መሰል ችግሮች ይወገዳሉ።

በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች በእነዚህ ተለዋዋጭና አደገኛ ጊዜያት የአምላካቸውን ተከላካይ እጅ ያያሉ። “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፣ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና” እንዳለው መዝሙራዊ ያለ ስሜት አላቸው። (መዝሙር 4:​8) በዚህ በመተማመንም ሊደረግ በሚገባው ሥራ ላይ ትኩረታቸውን ያሳርፋሉ:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:​14) ማንኛውም ዓይነት አደጋ፣ ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ፣ የማይደርስበትን የይሖዋን ሰላማዊና ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለምም በእርግጠኝነት በጉጉት ይጠባበቃሉ።  — ሚክያስ 4:​4

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ምስክሮች ከሩቅና ከቅርብ መጡ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ