ልንመስላቸው የሚገቡ የትሕትና ምሳሌዎች
“የአንተ የራስህ ትሕትናም ታላቅ ያደርገኛል። ” — መዝሙር 18:35 አዓት
1. የቀድሞው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ትሑት ሰው እንደነበረ ሊያሳይ የሚችለው ማስረጃ ምንድን ነው?
ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ቁመቱ 1 ከ80 ክብደቱ 90 ኪሎ ግራም ስለነበረ ጥሩ ቁመና ያለው ሰው ነበር። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን የይሖዋን ስም ለማስታወቅ ብቻ ሳይሆን የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎችን ግብዝነት ለማጋለጥና ሃይማኖታቸው “ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” ብሎ ለመናገር የተጠቀመበት ኃይለኛ ድምፅም ነበረው። ንግግሮቹ ኃይለኞች ቢሆኑም በዋናው መሥሪያ ቤት የቤቴል ቤተሰብ መካከል ሲጸልይ ግን አባቱን የሚያነጋግር ትንሽ ልጅ ይመስላል። ይህም ከፈጣሪው ጋር ያለውን የቅርብ ዝምድናና ትሕትናውን ያረጋግጣል። አዎን፣ እንደ ሕፃን ልጅ ያለ ትሕትና ነበረው። — ማቴዎስ 18:3, 4
2. የይሖዋ አገልጋዮች በዓለም ውስጥ ካሉት ግለሰቦች ልዩ ሆነው የሚታዩት በምናቸው ነው?
2 እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ ትሑቶች ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። የአምላክ ሕዝቦች ባላቸው ትሕትና ረገድ ከዓለም ሕዝቦች የተለዩ ናቸው። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዓለም በትዕቢተኛ ግለሰቦች ተሞልታለች። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውና ኃያላን ሰዎች፣ ሀብታሞቹም ሆኑ የተማሩት፣ ብዙ ድሆችና በሌሎች መንገዶች ብዙ ነገር የጎደለባቸው ሰዎች ሳይቀሩ ትዕቢተኞች ናቸው።
3. ስለ ትዕቢት ፍሬዎች ምን ሊባል ይቻላል?
3 ትዕቢት የሚፈጥረው ጠብና ኀዘን እጅግ ብዙ ነው። እንዲያውም በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያለው ወዮታ በሙሉ የጀመረው አንድ መልአክ በትዕቢት ተነሣስቶ ፈጣሪ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ብቻ የሚገባውን የመመለክ መብት ለራሱ ለመውሰድ ስለፈለገ ነው። (ማቴዎስ 4:9, 10) ከዚህም በላይ ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ ያደረገው መልአክ የመጀመሪያዋን ሴት የሔዋንን የኩራት ስሜት አነሣስቷል። እሱም ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ መልካሙንም ክፉውንም በማወቅ ልክ እንደ አምላክ እንደምትሆን በመንገር አታሏታል። ሔዋን ትሑት ብትሆን ኖሮ ‘እንደ አምላክ መሆን የምፈልገው ለምንድን ነው?’ ብላ ትመልስለት ነበር። (ዘፍጥረት 3:4, 5) የሰው ልጅ የሚኖርበትን የአካል፣ የአእምሮና የስነ ምግባር ጉስቁልና ስንመለከት በሰዎች ላይ ለደረሰው ችግር ሁሉ መንስኤው ኩራት አይደለምን? ይሖዋ “ትዕቢትንና ዕብሪትን” እንደሚጠላ ማንበባችን አያስደንቅም! (ምሳሌ 8:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትዕቢተኛ ከሆኑ ሰዎች ተቃራኒ በሆነ መንገድ ደምቀው የሚታዩ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የትሕትና ምሳሌዎች አሉ።
ይሖዋ አምላክ ትሑት ነው
4. ይሖዋ ትሑት መሆኑን የትኞቹ ጥቅሶች ያሳያሉ?
4 የሁሉም የበላይ፣ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥና የዘላለም ንጉሥ የሆነው ይሖዋ አምላክ ትሑት ነው። (ዘፍጥረት 14:22) ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነውን? አዎን፣ ንጉሥ ዳዊት በመዝሙር 18:35 ላይ እንደ ተመዘገበው “የማዳን ጋሻህንም ትሰጠኛለህ፤ ቀኝ እጅህም ደግፎ ያቆመኛል፤ የአንተ የራስህ ትሕትናም ታላቅ ያደርገኛል” በማለት ተናግሯል። በግልጽ እንደሚታየው ንጉሥ ዳዊት ታላቅ እንዲሆን ያስቻለውን የይሖዋን ትሕትና አድንቋል። እንደገናም በመዝሙር 113:6 ላይ እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ይሖዋ “ሰማይንና ምድርን ለማየት ራሱን ዝቅ ያደርጋል” የሚል እናነባለን። ሌሎች ትርጉሞች ደግሞ ይህንን ጥቅስ “ጎንበስ ብሎ የሚመለከት”፣ (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ) “ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት” (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ) ብለው ተርጉመውታል።
5. ይሖዋ ትሑት መሆኑን የትኞቹ ሁኔታዎች ይመሰክራሉ?
5 ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት መወሰኑ የጽድቅ ፍርድ ስለመሆኑ አብርሃም እንዲጠይቅ በመፍቀዱ ራሱን በአብርሃም ፊት ዝቅ አድርጓል።a (ዘፍጥረት 18:23–32) ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ አንድ ጊዜ ጣዖት በማምለካቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ ዓመፀኛ በመሆናቸው ምክንያት ጠርጎ ሊያጠፋቸው መፈለጉን በተናገረ ጊዜ ሙሴ በሁለቱም ወቅቶች ተራ ከሆነ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ከይሖዋ ጋር ተነጋግሯል። በሁለቱም ጊዜያት ይሖዋ ጥያቄውን ተቀብሎለታል። ይሖዋ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ያቀረበውን ልመና ሰምቶ መፈጸሙ ትሑት መሆኑን ያሳያል። (ዘጸአት 32:9–14፤ ዘኁልቁ 14:11–20) ይሖዋ ከሰዎች ጋር አፍ ለአፍ በመነጋገር ትሕትና ያሳየባቸው ሌሎች ምሳሌዎች በመሳፍንት 6:36–40 እና በዮናስ 4:9–11 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት በጌዴዎንና በዮናስ ላይ የደረሱት ሁኔታዎች ናቸው።
6. ይሖዋ ትሑት መሆኑን የሚያሳየን የትኛው ጠባዩ ነው?
6 እንዲያውም ቢያንስ ዘጠኝ ጊዜ ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” እንደሆነ ተነግሯል።b ይሖዋ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ፍጹም ያልሆነውን ሰብአዊ ፍጡር ችሎና ለቁጣ ዘግይቶ መቆየቱ ትሑት ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ትዕቢተኛ ሰዎች ግልፍተኞችና ቁጣቸውን ለመግለጽ የሚቸኩሉ፣ ከቻይነት ባሕርይ በጣም የራቁ ናቸው። ይሖዋ ይህን ያህል ትሑት ሲሆን ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ኩሩ መሆናቸው ምንኛ ምክንያተ ቢስነት ነው! ‘እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምትመስሉ ሁኑ’ ተብለን ስለ ተመከርን እርሱ ትሑት እንደሆነ እኛም ትሑት መሆን ይኖርብናል። — ኤፌሶን 5:1
የክርስቶስ የትሕትና ምሳሌ
7, 8. ኢየሱስ ክርስቶስ ትሑት ስለመሆኑ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?
7 በሁለተኛ ደረጃ ልንመስለው የሚገባ ከፍተኛ የትሕትና ምሳሌ በ1 ጴጥሮስ 2:21 የተጠቀሰው ነው። “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” ይላል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ዘመን በፊት በዘካርያስ 9:9 ላይ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሮለት ነበር:- “አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ እልል በዪ፤ እነሆ፣ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።” ኢየሱስ ክርስቶስ ኩራተኛ ቢሆን ኖሮ አንድ ጊዜ ብቻ ሰግዶ ዲያብሎስን በማምለክ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው ያቀረበለትን ስጦታ ተቀብሎ ሊሆን ይችል ነበር። (ማቴዎስ 4:9, 10) በተጨማሪም ትምህርቶቹን ያገኘው ከይሖዋ እንደሆነ በመናገር ትሑት መሆኑን አሳይቷል። “የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ” ብሏል። — ዮሐንስ 8:28
8 በትክክል “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ለማለት ችሎ ነበር። (ማቴዎስ 11:29) ሰው ሆኖ አብሯቸው ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት የሐዋርያቱን እግር በማጠብ በጣም ግሩም የሆነ የትሕትና ምሳሌ ትቷል። (ዮሐንስ 13:3–15) ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:3–8 ላይ ክርስቲያኖች “ትሕትና” እንዲኖራቸው ሲመክር ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።” በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠሙት ሁሉ ይበልጥ አስጨናቂ በሆነው ወቅት ላይ ሳለ “አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” በማለት ወደ አባቱ በትሕትና ጸልዮአል። (ማቴዎስ 26:39) የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ የምንከተልና እርሱን የምንመስል ለመሆን ከፈለግን ያለምንም ጥርጥር ትሑቶች መሆን ይኖርብናል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም የትሕትና ምሳሌ ነው
9-12. ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም የሆነ የትሕትና ምሳሌ የተወው በምን መንገዶች ነው?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ሐዋርያው ጳውሎስ በትሕትና ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰሉ ምክንያት እኛ ደግሞ እሱን ልንመስለው የሚገባ ጥሩ የትሕትና ምሳሌ ነውን? ምሳሌ እንደሚሆነን አያጠራጥርም። በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ መሆኑን በትሕትና ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 1:1) በኤፌሶን ለሚገኙት ሽማግሌዎች ‘በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰበት ፈተና ለጌታ እየተገዛ እንዴት እንደኖረ’ ነግሯቸዋል። (ሥራ 20:17–19) ትሑት ባይሆን ኖሮ “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ . . . የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም” በማለት በሮሜ 7:18, 19 ላይ የሚገኙትን ቃላት አይጽፍም ነበር።
10 በተጨማሪም በቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች በ1 ቆሮንቶስ 2:3 ላይ “እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ” በማለት መጻፉ ጳውሎስ የነበረውን ትሕትና ያሳያል። ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ያሳለፈውን ሕይወት ጠቅሶ “አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፣ . . . ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ . . . ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” በማለት በትሕትና ጽፏል። — 1 ጢሞቴዎስ 1:13, 15
11 ትሕትናውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ደግሞ ላገኘው የተሳካ ውጤት መመስገን የሚገባው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ መናገሩ ነው። አገልግሎቱን በተመለከተ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7) በኤፌሶን 6:18–20 ላይ እንደምናነበው ጥሩ ምስክርነት መስጠት ይችል ዘንድ ወንድሞቹ እንዲጸልዩለት ጠይቋቸዋል:- “ጸልዩ፤ . . . አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ . . . መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ [ስለ ምሥራቹ ቅዱስ ምሥጢር] በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ።”
12 በተጨማሪም ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ተባብሮ በመሥራቱ ትሑት መሆኑን አሳይቷል:- “ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን” ብሏል። (ገላትያ 2:9) በተጨማሪም ስእለት በማቅረብ ከኢየሩሳሌም ጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ለመተባበር ያለውን ፈቃደኝነት አራት ሰዎችን ይዞ ወደ መቅደስ በመሄድና ስእለታቸውንም እንዲፈጽሙ ገንዘብ በመክፈል አሳይቷል። — ሥራ 21:23–26
13. የጳውሎስን ትሕትና በጣም ልዩ ያደረገው ምንድን ነው?
13 ይሖዋ አምላክ ምን ያህል በጳውሎስ እንደተጠቀመበት ስናስብ የጳውሎስ ትሕትና በጣም ልዩ መሆኑን እንገነዘባለን። ለምሳሌ “እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር” የሚል ቃል እናነባለን። (ሥራ 19:11, 12) ከዚህም በተጨማሪ ልዩ የሆነ ራእይና መግለጫ ከአምላክ ተቀብሏል። (2 ቆሮንቶስ 12:1–7) እንዲሁም ከ27 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 14ቱን በመንፈስ አነሣሽነት እንዲጽፍ መደረጉንም አንርሳ። ይህ ሁሉ አላስታበየውም። ትሑት ሆኖ ኖሯል።
የዘመናችን ምሳሌዎች
14-16. (ሀ) የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ግሩም የትሕትና ምሳሌ የሆነው እንዴት ነበር? (ለ) የእርሱ ምሳሌስ ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነው ከማን ባሕርይ ጋር ነው?
14 ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 13:7 ላይ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” በማለት የጻፈውን ምክር እናነባለን። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሮአችን ይዘን በዘመናችን ከሚገኙት ምሳሌዎቻችን አንዱ የሆነውን የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዘዳንት ቻርልስ ቴዝ ራስልን በእምነቱ ልንመስለው የሚገባን ሰው አድርገን ልንወስደው እንችል ይሆናል። ትሑት ሰው ነበርን? በእርግጥ ትሑት ነበር! የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በተባለው ባለ ስድስት ጥራዝና 3,000 ገጽ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ላይ እንደታየው በጽሑፉ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ ስለ ራሱ አልጠቀሰም። ዛሬም የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ጽሑፎች ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት በመከተል የጸሐፊዎቻቸውን ማንነት በመግለጥ የሰዎችን ትኩረት አይስቡም።
15 ራስል በአንድ ወቅት በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ ተቃዋሚዎቹ “ራስሊዝም” ወይም “ራስላውያን” በማለት የሚጠቀሙባቸውን ቃላት እንደሚቃወምና እንደዚህ ያለውንም ነገር እንደማያውቅ ጽፏል። “ሥራችን . . . ተበታትነው የነበሩትን የእውነት ዘሮች ሰባስበን እንደ አዲስ ሳይሆን፣ እንደ ራሳችንም ሳይሆን፣ እንደ ጌታ አድርገን ለጌታ ሕዝብ ማቅረብ ነው። . . . ጌታ በትንሹ ችሎታችን ሊጠቀምበት ፈቅዶ የፈጸምነው ሥራ መልሶ የመጠገን፣ የማስተካከል፣ የማስማማት ሥራ እንጂ ከራሳችን አመንጭተን የሠራነው አዲስ ሥራ አይደለም።” በእውነትም በ1 ቆሮንቶስ 3:5–7 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን የሚመስል አባባል ነው ሊባል ይቻላል።
16 የራስል ዝንባሌ ቻርልስ ዳርዊን ከነበረው ዝንባሌ ፈጽሞ ተቃራኒ ነበር። ዳርዊን በ1859 በተጻፈው ዘ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ በተባለው የመጀመሪያ መጽሐፉ ላይ እየደጋገመ “የእኔ” ጽንሰ ሐሳብ እያለ በመጥቀስ ከእርሱ በፊት ስለ ኢቮሉሽን የተናገሩትን ሰዎች ሁሉ እቁጥር ሳያስገባቸው ቀርቷል። በዚያው ዘመን የነበረ ሳሙኤል በትለር የተባለ የታወቀ ጸሐፊ ዳርዊንን በጥብቅ በመቃወም ስለ ኢሾሉሽን ጽንሰ ሐሳብ ብዙ ሰዎች ከእርሱ በፊት ይናገሩ ስለነበር ዳርዊን ያመነጨው ንድፈ ሐሳብ አለመሆኑን አጋልጧል።
17. ወንድም ራዘርፎርድ ትሑት እንደነበረ የሚያሳዩ ተጨማሪ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
17 ሌላው ይሖዋ አምላክ በጣም ከተጠቀመባቸው የዘመናችን ታማኝ አገልጋዮቹ አንዱ በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በተለይም የይሖዋ ስም ደፋር ጠበቃ ነበር። ጀጅ (ዳኛው) ራዘርፎድ እየተባለ ይጠራ የነበረ ቢሆንም በልቡ ግን ትሑት ሰው ነበር። ለምሳሌ አንድ ጊዜ ክርስቲያኖች በ1925 ይሆናል ብለው ሊጠባበቁ ስለሚችሉት ነገር አንድ ሐሳብ በጭፍን ተናግሮ ነበር። እርሱ እንደጠበቀው ሳይፈጸም ሲቀር ግን ለብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ አባሎች በጣም ተሳስቶ እንደነበረ በትሕትና ተናግሯል። ከእርሱ ጋር በጣም ይቀራረብ የነበረ አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ወንድም ራዘርፎርድ ክርስቲያን ወንድሞቹን የሚጎዳ ያልታሰበበት ንግግር በመናገሩ በማቴዎስ 5:23, 24 መንፈስ በስብሰባዎችና በግል ብዙ ጊዜ ይቅርታ ሲጠይቅ መስማቱን ተናግሯል። በሥልጣን ላይ ያለ አንድ ሰው በበታቹ ያሉትን ይቅርታ የሚጠይቀው ትሑት ከሆነ ብቻ ነው። ወንድም ራዘርፎርድ በጉባኤ ውስጥም ይሁን በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ወይም በማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ለሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች በሙሉ ግሩም ምሳሌ ትቷል።
18. ሦስተኛው የማኅበሩ ፕሬዘዳንት የትሕትና ባሕርይ እንደነበረው የሚያሳዩት የትኞቹ የተናገራቸው ነገሮች ናቸው?
18 እንዲሁም ሦስተኛው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዘዳንት ናታን ኤች ኖር በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ትልቅ ቦታ ቢኖረውም በዚህ ምክንያት ራሱን ከፍ አድርጎ የማየት ዝንባሌ አልነበረውም። በማደራጀት ችሎታውና በሕዝብ ተናጋሪነቱ ከሌሎቹ ቢበልጥም ሌሎች ለሠሩት ሥራ ታላቅ አክብሮት ነበረው። ስለዚህም በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ይሠሩ ከነበሩት ወንድሞች ወደ አንዱ ቢሮ ሄዶ “በጣም አስፈላጊና በጣም አስቸጋሪ የሆነው ሥራ የሚሠራው እዚህ ነው። በዚህ ሥራ እምብዛም የማልካፈለው ለዚህ ነው” ሲል ተናግሯል። አዎን፣ በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ የሚገኘውን ‘እያንዳንዱ ሌሎች ከእሱ ይልቅ እንዲሻሉ በትሕትና ይቁጠር’ የሚለውን ምክር በትሕትና ሥራ ላይ ማዋሉ ነበር። የማኅበሩ ፕሬዘዳንት ሆኖ ማገልገል በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ሌሎች ሥራዎችም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው መሆኑን ተገንዝቧል። እንዲህ ያለ ስሜት ሊኖረውና ይህንኑም ስሜቱን በግልጽ ለመናገር የቻለው ትሕትና ስለነበረው ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም በከፍተኛ የበላይ ተመልካችነት ቦታ ላይ ያሉት ሊመስሉት የሚገባ ሌላው ግሩም ምሳሌ ነው።
19, 20. (ሀ) አራተኛው የማኅበሩ ፕሬዘዳንት ምን የትሕትና ምሳሌ ትቷል? (ለ) ትሕትና በማሳየት ረገድ የሚቀጥለው ርዕስ ምን እርዳታ ያቀርብልናል?
19 አራተኛው የማኅበሩ ፕሬዘዳንት ፍሬድ ደብሊው ፍራንዝም በትሕትና ረገድ በጣም ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነበር። ለ32 ዓመታት ያህል የማኅበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት ሆኖ ሲያገለግል በመጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ጽሑፎችና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ፕሮግራሞች በብዛት ይጽፍ የነበረው እሱ ቢሆንም ራሱን ደብቆ ትኩረት ለማግኘት ምንም ጥረት ሳያደርግ ኖሯል። ከዚህ ጋር ሊመሳሰል የሚችል የጥንት ዘመን ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። ኢዮአብ የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወግቶ ድል ባደረጋት ቀን የድሉን ምስጋና ንጉሥ ዳዊት እንዲያገኝ የሚያደርግ እርምጃ ወስዷል። — 2 ሳሙኤል 12:26–28
20 እንደ እውነቱ ከሆነ በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን ትሑቶች መሆን እንደሚያስፈልገን የሚያሳምኑ ግሩም ምሳሌዎች ሞልተዋል። ይሁን እንጂ ትሑቶች የምንሆንባቸው ሌሎች ብዙ ተጨማሪ ምክንያቶችም አሉ። እነዚህ ምክንያቶችና ትሑቶች እንድንሆን የሚረዱን ሐሳቦች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይቀርቡልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ኮንድሰንድ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “የበላይ ሆኖ መታየት” የሚል ትርጉም እንዳለው ሆኖ ይሠራበታል። ዋነኛ ትርጉሙ ግን “ቀና ማለት”፣ “ማዕረግ የሚያስገኘውን መብት አለመፈለግ” ማለት ነው። በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥም የተሠራበት በዚህ ትርጉሙ ነው። — በተጨማሪም ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮልጅየት ዲክሽነሪ ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ ትዕቢት ያስገኛቸው ፍሬዎች ምንድን ናቸው?
◻ በትሕትና ረገድ ብልጫ ያለው ግሩም ምሳሌ ያሳየው ማን ነው?
◻ በትሕትና ረገድ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ግሩም ምሳሌ ማን መሆኑን የሚያሳየን ምንድን ነው?
◻ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ግሩም የትሕትና ምሳሌ ትቷል?
◻ በዘመናችን ምን ታዋቂ የሆኑ የትሕትና ምሳሌዎች አሉልን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ፣ ግሩም የትሕትና ምሳሌ አሳይቷል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በትሕትና ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድም ራስል ለጻፋቸው ነገሮች ተመስጋኙ እርሱ እንዲሆን አልፈለገም