የይሖዋ ምስክሮች በዓለም ዙሪያ
አንድ ላይ ፊሊፒንስ ሪፑብሊክ በመባል የሚታወቁት ወጣ ገባዎቹና በሞቃታማ የአየር ንብረት የሚገኙት 7,083 ደሴቶች ግማሽ አካሉ ውኃ ውስጥ የገባ የተራራ ሰንሠለት የላይኛው አካል ክፍል ናቸው።a 62,000,000 የሚሆኑት የፊሊፒንስ ነዋሪዎችም በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ መወያየት ይወዳሉ ማለት ይቻላል። ይህ አስደሳችና በቀላሉ ሊቀረብ የሚችል መንፈስ ለመንግሥቱ ምስክርነት ፍሬያማ መስክ ፈጥሯል።
በትምህርት ቤት መመስከር
በማስቤት ደሴት ውስጥ አንዲት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እውነት ወይም ሐሰት ብለህ መልስ የሚል ፈተና በቀረበበት ወቅት ለአስተማሪዋና ለክፍሏ ተማሪዎች ምስክርነት ለመስጠት ችላ ነበር። እንዲህ ስትል ሪፖርት አድርጋለች:
“ዓረፍተ ነገሩ ‘አምላክ የሚያፈቅረኝ ከሆነ መከራ አያደርስብኝም ወይም ስሰቃይ ዝም ብሎ አይመለከተኝም’ የሚል ነበር። አስተማሪዬ የፈተና ወረቀቶቹን በምታርምበት ጊዜ ከእኔ በስተቀር ሁሉም እውነት ብለው መመለሳቸውን ተመለከተች። አስተማሪዬ ሐሰት ብዬ የመለስኩበትን ምክንያት ለክፍሉ ተማሪዎች እንዳስረዳ ፈቀደችልኝ። ምንም እንኳን መከራ እንዲቀጥልና ፈተና እንዲደርስብን ቢፈቅድም መከራ እንዲደርስብን የሚያደርገው አምላክ እንዳልሆነ ተናገርሁ። ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ዘወትር ከእጄ የማይለየውን መጽሐፍ ቅዱሴን ገልጬ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በሚሉት የ1 ዮሐንስ 4:8 ቃላት በመጠቀም የክፍሉን ተማሪዎች በሚገባ አስረዳኋቸው። ማብራሪያውን ከሰጠሁ በኋላ አስተማሪዬ በሰጠሁት መልስ ተስማማች፤ የተቀመጠችበትን ዴስክ መታ መታ አደረገችና: ‘ማሪሉ ትክክል ናት’ ስትል ተናገረች። የዚህን ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ያገኘሁትና ከፍተኛው ማርክ የተሰጠኝ እኔ ብቻ ነበርኩ።”
የመንግሥቱ መልእክት በየትኛውም ሥፍራ ይገኛል
በሌላ የፊሊፒንስ ክፍለ ሀገር ውስጥ አንዲት የዘወትር አቅኚ (የምሥራቹ የሙሉ ጊዜ አዋጅ ነጋሪ) ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል የሦስት ትንንሽ ልጆች እናት ታገኛለች። ሴትዬዋ ለመንግሥቱ መልእክት ከፍተኛ ፍላጎት አሳየች፤ ይህም በቀላሉ ከሴትዬዋ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር አስችሏል። ምንም እንኳን ባልዋ በተለይ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቷ ባይደሰትም ጥናቱ ቀጠለ።
ሰውየው ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሌላ ከተማ ሄደ። እንዲህ ያደረገው ሚስቱ ከምስክሮቹ ጋር ያላት ግንኙነት በዚህ መንገድ ይቋረጣል ብሎ አስቦ ነው። ይሁን እንጂ እርሷን ለማግኘት ጊዜ አልወሰደባቸውም፤ ሴትየዋም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን እንደገና ጀመረች። እርግጥ ነው፣ ባልዋ መበሳጨቱ አልቀረም። ቁጣው ሳይበርድለት ወደ ሥራ ቦታው ሄደ። ንዴቱንም መኪና ሊያሠራ በመጣ ሰው ላይ ተወጣ። ሰውዬው ባለመኪናው ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ መሆኑን አላወቀም ነበር።
ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷን ብትቀጥል ለመላው ቤተሰብ በጣም እንደሚጠቅም ምስክሩ ገለጸለት። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እዚያው እቤት ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል ልትጀምር ትችላለች ሲል ነገረው። ባልየው ራሱም ስለ አምላክ መንግሥት በመማር ሊጠቀም እንደሚችል ተገለጸለት።
ይህ ውይይት ምን ውጤት አስገኘ? የሰውየው ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የበለጠ ነፃነት አገኘች፤ ሰውየውም ቀድሞ ወደነበሩበት ቦታ ቤተሰቡን ይዞ ለመሄድ ወሰነ። በዚያ ቦታም ሴትየዋ በመንፈሳዊ ዕድገት አድርጋ ያልተጠመቀች የመንግሥቱ አስፋፊ ወደመሆን ደረጃ ደረሰች። ባልዋም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ ሆነና ቤተሰቡ በሙሉ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘት ጀመረ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የ1994 የይሖዋ ምስክሮችን የቀን መቁጠሪያ ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቷ ሪፖርት መግለጫ
የ1993 የአገልግሎት ዓመት
የምስክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦116,576
ሬሾ፦1 ምስክር፦ ለ549
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ብዛት፦357,388
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦22,705
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛት በአማካይ፦94,370
የተጠማቂዎች ብዛት፦7,559
የጉባኤዎች ብዛት፦3,332
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ማኒላ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በገበያ ቦታ የሚሰጠው ምስክርነት ጥሩ ውጤቶች አስገኝቷል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በማኒላ ውስጥ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የፊሊፒንስ ሪፑብሊክ