የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 2/1 ገጽ 25-29
  • ምክር በምትሰጥበት ጊዜ ሌሎችን ታከብራለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምክር በምትሰጥበት ጊዜ ሌሎችን ታከብራለህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰው በተፈጥሮው የመከበር መብት አለው
  • ይሖዋ የሰውን ልጅ የመከበር ባሕርይ እንዲኖረው አድርጎ ፈጥሮአል
  • የሰዎችን ክብር የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ሥርዓቶች
  • ሌሎችን አክብር፤ ዲያብሎስንም ተቃወም
  • ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ይሖዋን ማክበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ክብራቸውን ትጠብቅላቸዋለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ሁሉም ሰው ክብር ያገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ሰብዓዊ ክብር—ብዙውን ጊዜ የሚጣስ መብት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 2/1 ገጽ 25-29

ምክር በምትሰጥበት ጊዜ ሌሎችን ታከብራለህን?

ክብር ባለው መንገድ መመከር እንዴት ጥሩና ጠቃሚ ነው! ኤድዋርድ “በደግነት፣ በአሳቢነት እና በጥንቃቄ የተሰጠ ምክር ጥሩ ወዳጅነት ያፈራል” ብሏል። ዋረን ደግሞ “ምክር ሰጪው በአንተ በኩል ያለውን ሁኔታ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑን በማሳየት ሲያከብርህ ምክሩን መቀበሉ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል” ይላል። “አንድ ምክር ሰጪ በአክብሮት ሲይዘኝ ምክር እንዲሰጠኝ እርሱን ለመጠየቅ ነፃነት ይሰማኛል” በማለት ኖርመን ሐሳቡን ገልጿል።

ሰው በተፈጥሮው የመከበር መብት አለው

በጥሩ ስሜት፣ በወዳጅነት እና በፍቅር የቀረበ ምክር ተቀባይነት ያገኛል። አንተ እንድትመከር በምትፈልገው መንገድ ሌሎችን መምከር ጥቅም አለው። (ማቴዎስ 7:12) አንድ ጥሩ ምክር ሰጪ በመመከር ላይ ያለው ሰው የሚናገረውን ሁሉ ለመስማት ማለትም አስተሳሰቡን፣ ያለበትን ሁኔታ እና ስሜቱን ጭምር ለመረዳት ጊዜ ይወስዳል እንጂ አይተቸውም ወይም አያወግዘውም።—ምሳሌ 18:13

በዛሬው ጊዜ ያሉ ምክር ሰጪዎች ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ጭምር ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ሌሎችን ለማክበር ንቁ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ለምን? ሰዎችን ማዋረድ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለመደ በመሆኑ ነው። ይህ ዝንባሌ ከአንዱ ወደ ሌላው ሊተላለፍ ይችላል። በጣም የተማሩ ናቸው የሚባሉ ሰዎችም ሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ወይም ሌሎች አክብሮት ማሳየት ይገባቸዋል ብለህ የምትጠብቅባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ በዚህ በኩል ጉድለት ይታይባቸዋል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አንድ ሰው ከሥራ ሲባረር በአሠሪውም ላይ ሆነ በሠራተኛው ላይ አስጨናቂ ውጥረት ይፈጥራል። በተለይ ከሥራው የሚባረረው ሰው በክብር ሳይያዝ ከቀረ ለራሱ የሚኖረው ግምት ይጎዳል። የበላይ ተቆጣጣሪዎች አንድን ሰው ከሥራው እንዲባረር ሲያደርጉ “የግለሰቡን ክብር ሳይነኩ ይህንን አሳዛኝ መልእክት በግልጽና የማያስፈልግ ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ” እንዴት መናገር እንደሚችሉ መማር ይኖርባቸዋል በማለት ዘ ቫንኮቨር ሰን ዘግቧል። አዎን፣ ሁሉም ሰዎች ሊከበሩ ይገባቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ “ሰዎች ሁሉ ነፃና እኩል ክብርና መብት ያላቸው ሆነው ተወልደዋል። የሚያስብ አእምሮና ሕሊና ያላቸው ስለሆኑ በወንድማማችነት መንፈስ እርስ በርሳቸው ሊተያዩ ይገባል” የሚል አዋጅ አውጥቷል። የሰው ልጅ ክብር በመደፈር ላይ ስለሆነ የተባባሩት መንግሥታት ቻርተር እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ መግቢያ ይህንን የሰው ልጅ ባሕርይ ማስፈራቸው ተገቢ ነው። “በመሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች፣ በሰው ልጅ ክብርና ዋጋ” እንደሚያምኑ አረጋግጠዋል።

ይሖዋ የሰውን ልጅ የመከበር ባሕርይ እንዲኖረው አድርጎ ፈጥሮአል

ይሖዋ የክብር አምላክ ነው። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ቃሉ “ክብርና ግርማ በፊቱ . . . ናቸው” ይላል። እንዲሁም “ምስጋናህ [ክብርህ አዓት] በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና” ይላል።—1 ዜና መዋዕል 16:27፤ መዝሙር 8:1

የተከበረ አምላክና የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን ለሁሉም ሰማያዊና ምድራዊ ፍጥረታት ክብር ሰጥቷል። ክብር ከተሰጣቸው ከእነዚህ ፍጥረታት ሁሉ የሚበልጠው የተከበረውና ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ያለው ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ዳዊት “ክብርንና ምስጋናን ጨመርህለት” በማለት ተንብዮአል።—መዝሙር 21:5፤ ዳንኤል 7:14

የሚያሳዝነው ግን ይህ መሠረታዊ የሆነ ሰብአዊ መብት በሰው ልጅ ታሪክ ሁሉ ሲረገጥ መኖሩ ነው። በገዛ አድራጎቱ ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ ያደረገ አንድ ኃያል መልአክ የአምላክ ሉዓላዊነት ትክክለኛ፣ ጻድቅ እና ተገቢ መሆኑን ተገዳደረ። ይህን በማድረጉም ይሖዋን ከመናቅ እና የተከበረውን ስሙን ከማቃለል በተጨማሪ የመግዛት መብቱን ተገዳደረ። ከልክ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበረው እንደ ናቡከደናጾር ያሉ ኃያላን ሰብአዊ ነገሥታት ‘ስለ ብርታታቸውና ስለ ግርማቸው’ ልክ እንደ ዲያብሎስ በጉረኝነት የተናገሩበት ጊዜ አለ። ለራሳቸው ምክንያታዊ ያልሆነ ክብር በመስጠት የይሖዋን ክብር አዋርደዋል። (ዳንኤል 4:30) በሰው ዘር ዓለም ላይ የተጣለው የሰይጣን የጭቆና አገዛዝ የሰውን ልጅ ክብር እንዳዋረደና በመዋረድም ላይ እንደሆነ እናያለን።

ክብርህ ተነክቶብህ ያውቃልን? ምክር በተሰጠህ ጊዜ ከመጠን በላይ በደለኛና የማይገባህ ሰው መሆንህ እንዲሰማህ፣ ከመጠን በላይ እንድታፍር ወይም ራስህን እንድታዋርድ ተደርገህ ነበርን? “የአሳቢነት፣ የርኅራኄ እና የአክብሮት መንፈስ አላየሁባቸውም። የማልረባ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ነው የተደረግሁት። ይህም የብስጭት እና የመንፈስ ጭንቀት አስከትሎብኛል” በማለት አንድሬ ይናገራል። “ስለ አንተ ደህንነት ግድ እንደሌለው ሆኖ ከሚሰማህ ሰው አንደበት ምክር መቀበል በጣም ይከብዳል” በማለት ሎራ ትናገራለች።

በዚህ ምክንያት ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የአምላክን መንጋ በእንክብካቤና በክብር እንዲይዙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ሌሎችን መምከር አስፈላጊና ጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ሲፈጠር አለምንም ቅሬታ የሌሎችን ክብር የሚያዋርዱ ዓለማዊ ሰዎች አስተሳሰብና ባሕርይ እንዳይታይብህ ራስህን የምትጠብቀው እንዴት ነው? የክርስቲያን ጓደኞችህን ክብርም ሆነ የራስህን ክብር እንድትጠብቅ የሚረዳህ ምንድን ነው?—ምሳሌ 27:6፤ ገላትያ 6:1

የሰዎችን ክብር የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ሥርዓቶች

የአምላክ ቃል ስለምክር አሰጣጥ ይናገራል። ጥሩ ችሎታ ያለው ምክር ሰጭ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ይተማመናል እንጂ የዚህን ዓለም ጥበብ አይከተልም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ምክሮች ይገኛሉ። እነዚህ ምክሮች በሥራ ላይ ሲውሉ ለምክር ሰጪውም ሆነ ለምክር ተቀባዩ ክብር ያስገኛሉ። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ለነበረው ለጢሞቴዎስ “ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፣ እርሱን ግን እንደ አባት፣ ጐበዞችን እንደ ወንድሞች፣ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፣ ቈነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው” የሚል መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ይህን ሥርዓት በመከተል ብዙ ኀዘን፣ የመጐዳት ስሜት እና ሐፍረት ማስወገድ ይቻላል።

ውጤት ያለው ምክር ለመስጠት ቁልፉ ለሌላው ሰው ተገቢ አክብሮት ማሳየት እና በክብርና በጥንቃቄ የመያዝ መብት እንዳለው መገንዘብ መሆኑን አስታውስ። ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም ጭምር ይህንን ምክር ለመከተል ጥረት ሊያደርጉና መስተካከል የሚያስፈልገው ሰው ለምን የተለየ አስተሳሰብና ድርጊት እንደኖረው ለማወቅ መፈለግ አለባቸው። የራሱን አስተያየትና አመለካከት ለመስማትና እርዳታ የሚሰጠው ሰው የእፍረት፣ የመዋረድ ወይም ዝቅ የመደረግ ስሜት እንዳይሰማው ማንኛውንም ጥረት ለማድረግ መፈለግ ይገባቸዋል።

ሽማግሌ እንደመሆንህ መጠን ለወንድምህ እንደምታስብለትና ልትረዳው እንደምትፈልግ እንዲያውቅ አድርገው። ይህም ለምርመራ ስትሄድ አንድ ጥሩ ሐኪም እንደሚያደርግልህ ነው። ባልለመድከው ክፍል ውስጥ ልብስህን በሙሉ አውልቀህ ራቁትህን መተኛት ሊያሳፍርህ ወይም ደስ ላያሰኝህ ይችላል። የበሽታህን መነሻ ለማወቅ አስፈላጊውን ምርመራ በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉ ስሜትህን ተረድቶ ገላህን የምትሸፈንበት ልብስ በመስጠት የሚጠነቀቅልህን ሐኪም በጣም ታደንቃለህ። በተመሳሳይም ለሚመከረው ግለሰብ ተገቢውን አክብሮት የሚያሳይ ክርስቲያን መካሪ ደግና ጥብቅ ቢሆንም ለምክር ተቀባዩ ክብር ያለብሰዋል። (ራእይ 2:13, 14, 19, 20) በተቃራኒው ግን ሻካራ፣ ቀዝቃዛ እና ስሜት አልባ የሆነ ምክር እንድታፍር፣ ወራዳ እንደሆንክና ክብርህን እንደተገፈፍህ ሆኖ እንዲሰማህ ያደርጋል።

በተለይ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካቾች የሚመከረውን ሰው ክብር ጠብቀው ለመምከር መጠንቀቅ አለባቸው። አረጋውያንን በሚመክሩበት ጊዜ ለሥጋዊ ወላጆቻቸው የሚያሳዩትን ፍቅር ማሳየት አለባቸው። በአሳቢነት፣ በወዳጅነት እና ሞቅ ባለ ስሜት ይናገራሉ። በዚህ መንገድ ለሰው ስሜት መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። ተገቢ የሆነ ምክር የመስጠትና የመቀበል መንፈስ እንዲስፋፋ ያደርጋል።

ሽማግሌዎች ሆይ፣ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር እንደሚያነቃቃ፣ እንደሚያበረታታ፣ እንደሚገነባና ቀና አመለካከት እንደሚያሳድር ምንጊዜም አስታውሱ። ኤፌሶን 4:29 “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” ይላል።

ሻካራ የሆኑ ቃሎችን፣ የአነጋገር ዘይቤዎችን ወይም ምክንያቶችን መጠቀም አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ የሚመከረውን ሰው ማክበራችሁ እና ለራሱ ያለውን ግምትና ጥሩ ስሜት እንዳያጣ ለማድረግ ያላችሁ ምኞት ጉዳዩን ቀና በሆነና በሚገነባ መንገድ እንድታቀርቡ ያነሣሳችኋል። ማንኛውንም ሐሳብ በቅንነትና ላደረጋቸው መልካም ነገሮች ወይም ላሳያቸው ጥሩ ጠባዮች በማመስገን ተናገሩ እንጂ እንዲጨነቅና የዋጋ ቢስነት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርጉ አመለካከቶችን አጋንናችሁ አትናገሩ። ሽማግሌ ሆነህ የምታገለግል ከሆነ የተሰጠህን ‘ሥልጣን ለመገንባት እንጂ ለማፍረስ አትጠቀምበት።’—2 ቆሮንቶስ 10:8

አዎን፣ ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚሰጠው ምክር የሚያበረታታና ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ መሆን ይገባዋል። ተስፋ የሚያስቆርጥ ወይም “የሚያስደነግጥ” መሆን የለበትም። (2 ቆሮንቶስ 10:9) ከባድ ስሕተት የፈጸመ ሰው እንኳ ቢሆን መከበር ይኖርበታል። የሚሰጠው ምክር ለንስሐ የሚገፋፋ እንዲሆን ጠበቅ ባሉ የወቀሳ ቃሎች መቅረብ ቢኖርበትም ደግነት ሊታከልበት ይገባል።—መዝሙር 44:15፤ 1 ቆሮንቶስ 15:34

ለእስራኤላውያን ተሰጥቶ በነበረው የአምላክ ሕግ ውስጥ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይገኙ ነበር። በምክር ብቻ ሳይወሰን አካላዊ ቅጣት ጭምር እንዲሰጥ ይፈቅድ የነበረው ይህ ሕግ የሚቀጣው ግለሰብ ከአግባብ ውጭ ክብሩ እንዳይነካ ያዝ ነበር። “የግርፋቱ ቁጥር እንደ ኃጢአቱ መጠን” እንዲሆን ቢፈቅድም ከልክ ያለፈ መሆን አልነበረበትም። በደለኛው “ነውረኛ” እንዳይሆን በግርፋቱ ቁጥር ላይ ገደብ ተበጅቶ ነበር።—ዘዳግም 25:2, 3

ኢየሱስም ንስሐ ለገቡ በደል ፈጻሚዎች ስሜት የማሰብ ባሕርይ ነበረው። ኢሳይያስ ስለ ኢየሱስ ትንቢት ሲናገር “የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፣ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል” ብሎ ነበር።—ኢሳይያስ 42:3፤ ማቴዎስ 12:17, 20፤ ሉቃስ 7:37, 38, 44–50

ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ የተናገራቸው ቃላትም ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባሉ። “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” ይላሉ። (ማቴዎስ 7:12) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ጥሩ መግባባት እንዲኖር የሚያስችል ልዩ ምክር ስለሆነ ብዙ ጊዜ ወርቃማው ሕግ እየተባለ ይጠራል። ታዲያ ክርስቲያን ሽማግሌ እንደ መሆንህ ምክር ስትሰጥ ሌሎችን በደግነትና በክብር እንድትይዝ የሚረዳህ እንዴት ነው?

አንተም ስሕተት እንደምትሠራ ፈጽሞ አትርሳ። ያዕቆብ እንዳለው “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን።” (ያዕቆብ 3:2) ይህንን ማስታወስህ ከሌሎች ጋር ስለ ድክመታቸው ስትነጋገር አነጋገርህን እንድታለዝብና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ስሜትህን እንድትቆጣጠር ይረዳሃል። ስሜታቸው በቀላሉ ሊነካባቸው እንደሚችል አስታውስ። ይህም ከልክ ያለፈ ትችት እንዳትሰነዝርና ጥቃቅን ለሆኑ ስሕተቶችና ጉድለቶች ትኩረት ከመስጠት እንድትርቅ ይረዳሃል። ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፣ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል” በማለት የዚህን አስፈላጊነት ጎላ አድርጓል።—ማቴዎስ 7:1, 2

ሌሎችን አክብር፤ ዲያብሎስንም ተቃወም

የሰይጣን ዘዴዎች ለራስህ ክብር እንዳይኖርህ፣ ዋጋ ቢስ፣ ወራዳና ተስፋ ቢስ የመሆን ስሜት እንዲሰማህ ለማድረግ የታቀዱ ናቸው። ሰይጣን ታማኝ በነበረው በኢዮብ አእምሮ ውስጥ አፍራሽ ዝንባሌዎችን ለማሳደር ሰዎችን እንደ መሣሪያ እንዴት እንደተጠቀመ ልብ በል። ግብዝ የነበረው ኤልፋዝ “እነሆ፣ [ይሖዋ] በባሪያዎቹ አይታመንም፤ [ቅዱሳን] መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፤ ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ [ኃጢአተኛ ሰዎች]፣ መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፣ ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 4:18, 19) ስለዚህ እንደሱ አባባል ኢዮብ በአምላክ ዘንድ ከብል የተሻለ ዋጋ የለውም ማለት ነው። የኤልፋዝ እና የጓደኞቹ ምክር የሚገነባ ሊሆን ቀርቶ ኢዮብ ድሮ ያሳለፈውን ጥሩ ጊዜ እንኳን እንዳያስታውስ የሚያደርግ ነበር። በእነርሱ አመለካከት ኢዮብ በቀድሞ ጊዜ ያሳየው ታማኝነት፣ ቤተሰቡን ያሠለጠነበት መንገድ፣ ከአምላክ ጋር የነበረው ዝምድና እንዲሁም ለተቸገሩ ሰዎች ያደረገው ቸርነት ሁሉ ምንም ዋጋ የሌላቸው ነገሮች ነበሩ።

ዛሬም በተመሳሳይ ንስሐ የገቡ ስሕተት ፈጻሚዎች እንደዚህ በመሰለው ስሜት በጣም የሚነኩ ስለሆኑ ‘ከልክ በሚበዛ ኀዘን የመዋጥ’ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ሽማግሌዎች ሆይ፣ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ስትመክሩ ለራሳቸው ያላቸውን ክብር እንዳያጡ በማድረግ ፍቅራችሁን አረጋግጡላቸው። (2 ቆ ሮንቶስ 2:7, 8) “ክብር የጎደለው አያያዝ ምክር መቀበልን ከባድ ያደርገዋል” በማለት ዊልያም ይናገራል። በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳላቸው እንዲያምኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሖዋ ባለፉት ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግሉ “[ያደረጉትን] ሥራ ለስሙም [ያሳዩትን] ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ” አለመሆኑን አስታውሷቸው።—ዕብራውያን 6:10

ምክር በምትሰጥበት ጊዜ ሌሎችን እንድታከብር ሊረዱህ የሚችሉ ምን ተጨማሪ ነገሮች ይኖራሉ? ሰዎች ሁሉ በአምላክ ምሳሌ የተፈጠሩ ስለሆኑ በተፈጥሯቸው የመከበር መብት ያላቸው መሆኑን አስታውስ። በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ አላቸው። የቤዛውና የትንሣኤ ዝግጅት ለዚህ ማስረጃ ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ። ይሖዋ በተለይ ክርስቲያኖችን “ለአገልግሎቱ [በመሾም]” ተጨማሪ ክብር ሰጥቶአቸዋል። ይህ ክፉ ትውልድ ከአምላክ ጋር እንዲታረቅ እንዲማልዱ በማድረግ ይጠቀምባቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:12

ሽማግሌዎች ሆይ፣ አብዛኛዎቹ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁ በጸዳችው ምድር ላይ ለሚቋቋመው አዲስ ሰብአዊ ኅብረተሰብ መሠረት የመሆን መብት እንደሚኖራቸው አስታውሱ። በጣም ጠቃሚ እና ውድ ግለሰቦች በመሆናቸው ሊከበሩ ይገባል። ምክር በምትሰጡበት ጊዜም ይሖዋና ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚያስቡላቸው አስታውሱ። ለራሳቸው ክብርና ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው በማድረግ ሰይጣን የሚያመጣባቸውን ፈተና እንዲያሸንፉ መርዳታችሁን ቀጥሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ከ1 ጴጥሮስ 3:7 ጋር አወዳድር።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሚያስከብር ምክር

(1) እውነተኛና ልባዊ ምስጋና ስጥ። (ራእይ 2:2, 3)

(2) ጥሩ አድማጭ ሁን። የተፈጠረውን ችግር እና ምክሩ ለምን መሰጠት እንዳስፈለገው በግልጽ እና በደግነት አስረዳ። (2 ሳሙኤል 12:1–14፤ ምሳሌ 18:13፤ ራእይ 2:4)

(3) ምክርህን በቅዱስ ጽሑፉ ላይ መሥርት። ቀና አመለካከት ያለህ፣ ምክንያታዊ እና የምታበረታታ ሁን፤ እንዲሁም ራስህን በሚመከረው ሰው ቦታ አድርገህ ተመልከት። የምክር ተቀባዩን ክብር እና ለራሱ ያለውን ግምት ጠብቅለት። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ቲቶ 3:2፤ ራእይ 2:5, 6)

(4) የሚመከረው ሰው ምክሩን ቢቀበል እና ሥራ ላይ ቢያውል በረከት እንደሚያገኝ አስገንዝበው። (ዕብራውያን 12:7, 11፤ ራእይ 2:7)

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ሌሎችን ማክበር ያስፈልጋቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ