የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት፤ ይሳካለት ይሆንን?
በመቶ የሚቆጠሩ የሃይማኖት መሪዎች በ1993 የበጋ ወራት በአሜሪካን አገር በቺካጎ ኢሊኖይስ በተደረገው ሁለተኛው የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። ቡድሂዝም፣ ሕዝበ ክርስትና፣ ሂንዱይዝም፣ ጁዳይዝም እና እስላም ተገኝተው ነበር። ጠንቋዮች እና የሴት አማልክት አምላኪዎችም ተገኝተው ነበር። ጦርነትን ለማስቆም በየበኩላቸው ስለሚጫወቱት ሚና ተወያዩ። የምክር ቤቱ ሊቀ መንበር “በዓለም ላይ ከሚደረጉት ታላላቅ ጦርነቶች መካከል ሁለት ሦስተኛው የሃይማኖት እጅ እንዳለበት” አምነዋል።
ከመቶ ዓመት በፊት
ምክር ቤቱ ተሳክቶለት ነበርን? ከመቶ ዓመት በፊት በዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የነበረውን ሁኔታ ተመልከት። ስብሰባው በ1893 የበጋ ወራት እዚሁ ችካጎ ውስጥ ተደርጎ ከ40 የሚበልጡ ሃይማኖቶች ተወካዮቻቸውን ልከው ነበር። የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት በ1893 በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙት ሁሉ “መግባባት፣ ሰላምና ብልጽግና በማምጣቱ በኩል አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ሃይማኖቶች ለመቀላቀል የሚረዳ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ተከታታይ ስብሰባ ነው ብለው አምነው ነበር።” ነገር ግን እንደታሰበው ሳይሆን ቀረ። ሃይማኖታዊ አለመግባባትና ዓመፅ ባለፉት 100 ዓመታት ለተካሄዱት እና አሁንም ጭምር ለሚካሄዱት ጦርነቶች የመንስኤው ክፍል ሆኖ ቆይቷል” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ምክር ቤቱ ያልተሳካለት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሃይማኖትን መቀላቀል የሚባለው ሐሳብ በአምላክ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 6:14–17
የመስከረም 1893 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ከምጸታዊ ትችት የራቀ ሐሳብ በሰጠ ጊዜ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው መሆኑን አበክሮ ገልጿል፦ “አርኪዮሎጂስቶች ከባቢሎንና ከሌሎች ጥንታዊ ከተማዎች ፍርስራሾች አስደናቂ የሆኑ ታሪክ የተጻፈባቸውን ብዙ ሸክላዎች አግኝተዋል። ሆኖም ገና ያልተገኙ አሉ። . . . ሙሴ እና ኢያሱ ‘የሃይማኖት ምክር ቤት’ የሚባል ነገር ከሞዓባውያን እና ከአሞናውያን እንዲሁም ከኤዶማውያን ጋር ስለ መፍጠራቸው የሚተርክ ሸክላ አላገኙም። . . . ቆራጥ የነበረው ሽማግሌው ሳሙኤል ወደ ጌት እና ወደ አስቀሎና መልእክተኛ በመላክ የዳጎን ካህናት ወኪሎቻቸውን ወደ ሴሎ እንዲልኩና ከይሖዋ ካህናት ጋር ስብሰባ እንዲደረግ መጥራቱን የሚናገር ሸክላ አላገኙም። . . . በወገቡ ጠፍር ታጥቆ ይዞር የነበረው ኤልያስ ከበኣል እና ከሞሎክ ካህናት ጋር ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ‘ሸንጎ’ ሰብስቦ የእያንዳንዳቸው እምነት ስለሚያስተምራቸው ትምህርቶች ለመወያየትና በዚህም ሳቢያ አንዳቸው የሌላውን ሃይማኖት እንዲያከብሩ ያስችላቸዋል የሚል አሳብ አቅርቦ እንደነበረ የሚናገር ሸክላ አላገኙም።”
ብቸኛው ተስፋ የአምላክ መንግሥት
የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት እቅዱ ፈጽሞ አይሳካለትም። ጋዜጦችና የስብሰባው ተካፋዮች “ዝብርቅ”፣ “ብጥብጥ” እና “ግራ መጋባት” በሚሉት ቃሎች የምክር ቤቱን ሁኔታ ገልጸዋል። በአንድ ዘገባ መሠረት በፖለቲካዊ መከፋፈል የተነሣ ረብሻ የፈጠሩትን ሁለት ሰዎች ዝም ለማሰኘት ፖሊሶች ጣልቃ መግባት አስፈልጓቸው ነበር። በ1952 በተደረገው ስምምነት ላይ ምክር ቤቱ ከዓላማዎቹ አንዱ አድርጎ የሚከተለውን ሐሳብ መዝግቧል፦ “ከተባበሩት መንግሥታት ጋር አብሮ የሚሠራ በሰዎች መካከል ሰላምና መግባባት እንዲኖር የሚረዳ አንድ ቋሚ የሃይማኖቶች ምክር ቤት ማቋቋም ነው።” ኢየሱስ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ አቋም በመውሰድ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነች ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሔውን የያዘችው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኗን ያመለክታል።—ዳንኤል 2:44፤ ዮሐንስ 18:36