የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 2/15 ገጽ 8-14
  • የመገኘትህ ምልክት ምን ይሆናል?’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመገኘትህ ምልክት ምን ይሆናል?’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሐዋርያቱ ለማወቅ ፈለጉ
  • ‘ከዚያ በኋላ’ መጨረሻው ይመጣል
  • በትንቢቱ መሠረት ወደፊት የሚፈጸሙ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ
  • ወደ ምን ይመራል?
  • “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል?”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • “ይህ ሊሆን ግድ ነውና”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ሐዋርያቱ ምልክት እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠየቁት
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • አምላክ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት ከጥፋት ትድን ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 2/15 ገጽ 8-14

የመገኘትህ ምልክት ምን ይሆናል?’

“እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?”—ማቴዎስ 24:3 አዓት

1, 2. ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ እንደሚፈልጉ የሚያሳየው ምንድን ነው?

አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ፍላጎት አላቸው። አንተስ? ፕሮፌሰር አልቪን ቶፍለር ፊውቸር ሾክ በተባለው መጽሐፋቸው “ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚያጠኑ ድርጅቶች በድንገት እንደ አሸን ፈልተዋል” ብለዋል። ጨምረውም ‘ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚያጠኑ የምርምር ተቋሞች መፈጠራቸውን፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሣይ፣ በኢጣልያ፣ በጀርመንና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚተነብዩ መጽሔቶች ብቅ ብቅ ማለታቸውንና፣ ስለ ትንበያ የሚያስተምሩ የዩንቨርሲቲ ኮርሶች መብዛታቸውን ተመልክተናል’ ብለዋል። ቶፍለር አስተያየታቸውን ሲደመድሙ “እርግጥ፣ ስለ ወደፊቱ ሁኔታ በተሟላ ሁኔታ ‘ሊያውቅ’ የሚችል ማንም ሰው የለም” ብለዋል።

2 ሳይንስ ኦቭ ቲንግስ ቱ ካም የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “መዳፍ ማየት፣ ዶቃ መመልከት፣ ኮከብ መቁጠር፣ በካርታ መጠንቆል፣ ዪ ጂን [እንደ አውደ ነገሥት ያለ የምሥራቃውያን መጠንቆያ መጽሐፍ ነው] መመልከት . . . እነዚህ ሁሉ በቴክኒክ ደረጃቸው ይበላለጡ እንጂ ሁሉም የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘልን የምናውቅባቸው ዘዴዎች ናቸው።” ይሁን እንጂ የወደፊቱ ጊዜ ስለሚያመጣቸው ሁኔታዎች ለማወቅ በእነዚህ ሰብዓዊ ዘዴዎች ከመጠቀም ይልቅ ወደታመነው ምንጭ ማለትም ወደ ይሖዋ ዘወር ብንል ይሻለናል።

3. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ወደ አምላክ ዘወር ማለቱ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?

3 እውነተኛው አምላክ “እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል” ብሏል። (ኢሳይያስ 14:24, 27፤ 42:9) አዎን፣ ይሖዋ አብዛኛውን ጊዜ ሰብዓዊ ቃል አቀባዮችን በመጠቀም የሰው ልጆች ወደፊት ስለሚሆኑት ነገሮች እንዲያውቁ ሲያደርግ ቆይቷል። ከእነዚህ ነቢያት አንዱ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” ሲል ጽፏል።—አሞጽ 3:7, 8፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ሊረዳን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሐዋርያቱ የጠየቁት ጥምር ጥያቄ ምን ነበር?

4 ዋነኛው የአምላክ ነቢይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዕብራውያን 1:1, 2) እስቲ ኢየሱስ ከተናገራቸው ቁልፍ ትንቢቶች መካከል አንዱ በሆነውና በአሁኑ ጊዜ በአካባቢያችን እየተፈጸሙ ስላሉት ነገሮች በሚተነብየው ትንቢት ላይ እናተኩር። ይህ ትንቢት አምላክ በምድራዊት ገነት ለመተካት ይህ የአሁኑን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ የሚፈጸሙትን ነገሮችም እንድናስተውል ያስችለናል።

5 ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን አስመስክሯል። (ማርቆስ 6:4፤ ሉቃስ 13:33፤ 24:19፤ ዮሐንስ 4:19፤ 6:14፤ 9:17) ስለዚህ ሐዋርያቱ ከእርሱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጠው ኢየሩሳሌምን አሻግረው እየተመለከቱ “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ብለው የጠየቁት ለምን እንደሆነ ይገባናል።—ማቴዎስ 24:3 አዓት፤ ማርቆስ 13:4

6. ማቴዎስ 24፣ ማርቆስ 13ና ሉቃስ 21 ምን ግንኙነት አላቸው? በጣም ሊያጓጓን የሚገባው የትኛው ጥያቄ ነው?

6 የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄና ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ በማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ ይገኛል።a እነዚህ ሦስት ዘገባዎች ሙሉ በሙሉ አንድ ባይሆኑም አንዳቸው ሌላውን የሚያዳብሩ ናቸው። ለምሳሌ ‘በየቦታው ቸነፈር እንደሚሆን’ የጻፈው ሉቃስ ብቻ ነው። (ሉቃስ 21:10, 11፤ ማቴዎስ 24:7 አዓት፤ ማርቆስ 13:8) ኢየሱስ የተነበየው ያዳምጡት በነበሩት ሰዎች የሕይወት ዘመን ውስጥ ስለሚፈጸሙ ነገሮች ብቻ ነው ወይስ ስለ ዘመናችንና ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው ጊዜ ጭምር? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

ሐዋርያቱ ለማወቅ ፈለጉ

7. ሐዋርያቱ ይበልጥ የጠየቁት ስለምን ነገር ነበር? የኢየሱስ መልስ ግን የቱን ያህል ሰፊ ነበር?

7 ኢየሱስ ከመገደሉ ከጥቂት ቀናት በፊት አምላክ የአይሁድ ርዕሰ ከተማ የነበረችውን ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ እንደተዋት ተናግሮ ነበር። ከተማይቱና በከተማይቱ ይገኝ የነበረው ታላቅ ቤተ መቅደስ ይወድማሉ። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ሐዋርያት ‘ስለ ኢየሱስ መገኘትና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ዘመን’ ምልክት እንዲሰጣቸው ጠየቁት። (ማቴዎስ 23:37 እስከ 24:3) ሐዋርያቱ ወደፊት የሚፈጸመው ነገር ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው ስላልተገነዘቡ ይበልጥ ያሰቡት ስለ አይሁድ ሥርዓትና ስለ ኢየሩሳሌም ብቻ እንደነበር አያጠራጥርም። ኢየሱስ ግን መልስ ሲሰጣቸው በ70 እዘአና ይህ ዓመት ካለፈ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚሆነውን ነገር በአእምሮው ይዞ ነበር።—ሉቃስ 19:11፤ ሥራ 1:6, 7

8. ኢየሱስ ይከሰታሉ ብሎ የተነበያቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

8 በእነዚህ ሦስት የወንጌል ዘገባዎች ላይ ኢየሱስ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሣ፣ የምግብ እጥረት እንደሚኖር፣ የምድር መናወጥ እንደሚሆን፣ አስፈሪ ነገሮችና ከሰማይም ምልክቶች እንደሚታዩ መናገሩን ማንበብ ይቻላል። ኢየሱስ ይህንን ምልክት ከሰጠበት ጊዜ (ከ33 እዘአ) ጀምሮ ኢየሩሳሌም እስከ ወደመችበት ጊዜ ድረስ (66– 70 እዘአ) ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ ክርስቶሶች ይነሣሉ። አይሁዳውያንም የኢየሱስን መልእክት የሚሰብኩበትን ክርስቲያኖች ያሳድዳሉ።

9. የኢየሱስ ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የተፈጸመው እንዴት ነበር?

9 እነዚህ የምልክቱ ገጽታዎች በትክክል መፈጸማቸውን ታሪክ ጸሐፊው ፍላቭየስ ጆሴፈስ አረጋግጧል። ሮማውያን ለጥቃት ከመዝመታቸው በፊት ሐሰተኛ መሲሖች ሕዝቡን ለዓመፅ አነሳስተው እንደነበረ ጽፏል። በይሁዳና በተለያዩ ሌሎች ቦታዎች ከባድ የምድር መናወጦች ተከስተው ነበር። በብዙዎቹ የሮማ ግዛት ክፍሎች ጦርነቶች ተነስተው ነበር። ከባድ ረሃብስ ነበር? አዎን ነበር። (ከሥራ 11:27–30 ጋር አወዳድር።) መንግሥቱን የመስበኩ ሥራስ? በ60 ወይም በ61 እዘአ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች ደብዳቤ በጻፈ ጊዜ ‘የዚህ ወንጌል ተስፋ’ በአፍሪካ፣ በእስያና በአውሮፓ በሰፊው ተሰምቶ ነበር።b—ቆላስይስ 1:23

‘ከዚያ በኋላ’ መጨረሻው ይመጣል

10. ቶት የተባለውን የግሪክኛ ቃል የምናተኩርበት ለምንድን ነው? ትርጉሙስ ምንድን ነው?

10 ኢየሱስ የአንዳንድ ሁኔታዎችን የአፈጻጸም ቅደም ተከተል ተናግሯል። እንዲህ አለ፦ “ይህ የመንግሥት ወንጌል . . . ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “በዚያን ጊዜ” በሚለው ቃል ቦታ የገባውን “ዜን” የተባለ ቃል አብዛኛውን ጊዜ “ስለዚህ” ወይም “ነገር ግን” የሚል ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ይጠቀሙበታል። (ማርቆስ 4:15, 17፤ 13:23) ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሰው በማቴዎስ 24:14 ላይ የገባው “ዜን” የሚለው ቃል ቶት ከተባለው የግሪክኛ ተውሳከ ግሥ የተገኘ ነው።c የግሪክኛ ቋንቋ ሊቃውንት ቶት “በቀጣይነት የሚፈጸምን አንድ ነገር” ወይም “በጊዜ ረገድ ቀጥሎ የሚፈጸምን ሁኔታ” ለማስተዋወቅ የሚያገለግል “የጊዜ አመልካች ተውሳከ ግሥ” እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ኢየሱስ መንግሥቱ እንደሚሰበክና በዚያን ጊዜ (‘ከዚያ በኋላ’ ወይም ‘ቀጥሎ’) “መጨረሻው” እንደሚመጣ ተንብዮአል። ይህ “መጨረሻ” የትኛው ነው?

11. ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው ነገሮች ላይ ያተኮረው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት አንዱ ፍጻሜ የኢየሩሳሌምና የአይሁድ ሥርዓት መጥፋት ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረትና ኢየሱስ የተነበያቸው ሌሎች ነገሮች ከጥፋቱ በፊት በነበሩት ሦስት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ተፈጽመዋል። ይሁን እንጂ ከማቴዎስ 24:15፣ ከማርቆስ 13:14 እና ከሉቃስ 21:20 ጀምረን የምናነባቸው ነገሮች ጥፋቱ በደጅ ሲቀርብ የሚፈጸሙ ናቸው።—በቻርቱ ላይ ያለውን በነጠብጣብ የተሰመረውን ነጠላ መስመር ተመልከት።

12. የሮም ሠራዊት በማቴዎስ 24:15 ትንቢት ፍጻሜ ውስጥ የገባው እንዴት ነበር?

12 አይሁዳውያን በ66 እዘአ በማመፃቸው ምክንያት በሴስትየስ ጋለስ መሪነት ሮማውያን በኢየሩሳሌም ላይ ዘምተው አይሁዳውያን ቅድስት አድርገው ይመለከቷት የነበረችውን ከተማ ከበቧት። (ማቴዎስ 5:35) አይሁዳውያኑ ጥቃቱን ለመመከት የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም ሮማውያን ወደ ከተማዋ ዘልቀው ገቡ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:15 እና ማርቆስ 13:14 ላይ እንደተነበየው የሮማውያን ሠራዊት “በተቀደሰችው ስፍራ” ሊቆም ቻለ። ከዚያ በኋላ ግን ያልተጠበቀ ነገር ተፈጸመ። ከተማይቱን የከበቧት ቢሆንም ሮማውያኑ ሳይታሰብ ወደ ኋላቸው ተመለሱ። ሮማውያን ከተማይቱን መክበባቸው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ያስተዋሉት ክርስቲያኖች የሮማውያኑ ወደ ኋላቸው መመለስ ከይሁዳ ምድር በመውጣት በዮርዳኖስ ማዶ ወደሚገኙት ተራሮች እንዲሸሹ አስቻላቸው። ታሪክ እንዲህ እንዳደረጉ ይናገራል።

13. ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንዲሸሹ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እንዲሸሹ ያስቻላቸው ምን ነበር?

13 ይሁን እንጂ ሮማውያኑ ከኢየሩሳሌም አካባቢ ከተመለሱ ከከተማይቱ መሸሽ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የኢየሱስ ቃላት የተፈጸመው ነገር ‘የኢየሩሳሌም ጥፋት መቅረቡን’ እንደሚያመለክት በግልጽ ስለሚያሳዩ ነው። (ሉቃስ 21:20) አዎን፣ ጥፋት መቅረቡን ያመለክት ነበር። ኢየሱስ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” ይደርሳል በማለት ተንብዮ ነበር። ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ማለትም በ70 እዘአ በጄኔራል ቲቶ ይመራ የነበረው የሮም ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ታላቅ መከራ አደረሰ። (ማቴዎስ 24:21፤ ማርቆስ 13:19) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ጥፋት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከደረሱት መከራዎች የሚበልጥ መከራ እንደሆነ የገለጸው ለምን ነበር?

14. በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ በኋላ ያልደረሰ “ታላቅ መከራ” ነው ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

14 ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ባድማ አድርገዋት ነበር። በዚህ መቶ ዘመናችንም ይህች ከተማ አስከፊ ጦርነቶችም ተፈጽመውባታል። ያም ሆኖ ግን በ70 እዘአ የተፈጸመው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ታላቅ መከራ ነበር። ለአምስት ወራት ያህል በቆየው ዘመቻ በቲቶ ይመራ የነበረው የሮማውያን ሠራዊት አይሁዳውያንን ድል አድርጎ 1,100,000 ሰዎችን ሲገድል 100,000 የሚያክሉ ሰዎችን ባሪያ አድርጎ ወስዷል። ከዚህም በላይ ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ጨርሰው አፈራረሷት። ይህም በፊት ተቀባይነት የነበረው በቤተ መቅደሳቸው ማዕከልነት ይፈጸም የነበረው ተቀባይነት ያለው የአይሁዳውያን የአምልኮ ሥርዓት ለዘለቄታው እንዳበቃለት ያረጋግጣል። (ዕብራውያን 1:2) አዎን፣ በ70 እዘአ የተፈጸመው ነገር “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ [በዚያ ከተማ፣ ሕዝብና ሥርዓት ላይ ደርሶ የማያውቅ] ከእንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” ተደርጎ ቢቆጠር ትክክል ነው።—ማቴዎስ 24:21d

በትንቢቱ መሠረት ወደፊት የሚፈጸሙ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ

15. (ሀ) ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ መከራ ከደረሰ በኋላ ምን ነገሮች ይፈጸማሉ አለ? (ለ) ማቴዎስ 24:23–28ን ስንመለከት ስለ ኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ ምን ብለን መደምደም ይኖርብናል?

15 ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተነበየው በ70 እዘአ ስለደረሰው መከራ ብቻ አልነበረም። በማቴዎስ 24:23 እና በማርቆስ 13:21 ላይ የጠቀሰው ቶት ወይም “በዚያን ጊዜ” የሚለው ቃል እንደሚያመለክተው ከዚያ መከራ በኋላ የሚፈጸሙ ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ከ70 እዘአ በኋላ በነበሩት ዓመታት ምን የሚፈጸሙ ነገሮች ነበሩ? የአይሁድ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ብዙ የሐሰት ክርስቶሶችና የሐሰት ነቢያት ይነሣሉ። (ማርቆስ 13:6ን ከ13:21–23 ጋር አወዳድር።) ከ70 እዘአ በኋላ ባሉት መቶ ዘመናት ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት የሆኑ ግለሰቦች ተነሥተው እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። አጥርቶ የሚያይ መንፈሳዊ ዓይን ያላቸውንና የሚበሉትን እንስሳ በርቀት እንደሚከታተሉ ንስሮች በመሆን የክርስቶስን “መገኘት” በትኩረት የሚከታተሉትን ሰዎች ማሳት ግን አልሆነላቸውም። (ማቴዎስ 24:27, 28) በ70 እዘአ ከደረሰው መከራ በኋላ እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች መፈጸማቸው ኢየሱስ ትንቢቱን ሲናገር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከደረሰው መከራ ሌላ አሻግሮ የተመለከተው ነገር እንደነበረ የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ነው። ይህ መከራ የትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ ብቻ ነበር።

16. ሉቃስ 21:24 በኢየሱስ ትንቢት ላይ ምን ይጨምራል? ይህስ ምን ትርጉም አለው?

16 ማቴዎስ 24:15–28ንና ማርቆስ 13:14–23ን ከሉቃስ 21:20–24 ጋር እያወዳደርን ብንመለከት የኢየሱስ ትንቢት ከኢየሩሳሌም ጥፋት በኋላ ብዙ ቆይቶ የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን የሚጨምር መሆኑን የሚያመለክት ሁለተኛ ምክንያት እናገኛለን። ስለ ቸነፈር የጠቀሰው ሉቃስ ብቻ እንደነበረ ሁሉ ይህን የኢየሱስ ትንቢት ክፍል “የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም [የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪያበቁ አዓት] ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” በሚሉት ቃላት የደመደመው ሉቃስ ብቻ ነው።e (ሉቃስ 21:24) ባቢሎናውያን የመጨረሻውን የአይሁድ ንጉሥ ከሥልጣን ያስወገዱት በ607 ከዘአበ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአምላክን መንግሥት የምትወክለው ኢየሩሳሌም እንደተረገጠች ቆይታ ነበር። (2 ነገሥት 25:1–26፤ 1 ዜና መዋዕል 29:23፤ ሕዝቅኤል 21:25–27) ኢየሱስ በሉቃስ 21:24 ላይ ይህ ሁኔታ አምላክ መንግሥቱን እንደገና እስከሚያቋቁምበት ጊዜ ድረስ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

17. የኢየሱስ ትንቢት ወደፊት ከረዥም ጊዜ በኋላ ስለሚፈጸሙ ነገሮች የሚናገር እንደነበረ የሚያመለክተን ሦስተኛው ነገር ምንድን ነው?

17 የኢየሱስ ትንቢት ከረዥም ዘመን በኋላ የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን የሚጨምር መሆኑን የሚያመለክት ሌላ ሦስተኛ ማስረጃም አለ። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት መሲሑ ሞቶ መነሳት ይኖርበታል። ከዚያ በኋላ አባቱ ጠላቶቹን በቁጥጥር ሥር እንዲያደርግ እስኪልከው ድረስ በአምላክ ቀኝ ይቀመጣል። (መዝሙር 110:1, 2) በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ የሚቆይ መሆኑን ኢየሱስም ተናግሯል። (ማርቆስ 14:62) ሐዋርያው ጳውሎስም ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ንጉሥ የሚሆንበትንና የመለኮታዊው ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ የሚያገለግልበትን ጊዜ እየተጠባበቀ በአባቱ ቀኝ እንደሚቆይ አረጋግጧል።—ሮሜ 8:34፤ ቆላስይስ 3:1፤ ዕብራውያን 10:12, 13

18, 19. ራእይ 6:2–8 በወንጌሎች ውስጥ ካለው ትንቢት ጋር የሚመሳሰል ምን ሐሳብ ይዟል?

18 ኢየሱስ ስለ ሥርዓቱ ፍጻሜ የተናገረው ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን የሚያሳየን አራተኛና የመጨረሻ የሆነውን ማስረጃ ለመመልከት ራእይ ምዕራፍ 6ን ልናወጣ እንችላለን። ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ ከጠፋች ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ ይህን ሲጽፍ ትኩረት የሚስቡ ፈጣን ፈረሰኞችን እንደተመለከተ ገልጿል። (ራእይ 6:2–8) ይህ ስለ “ጌታ ቀን” ማለትም ስለመገኘቱ ዘመን የሚገልጸው ትንቢታዊ ራእይ 20ኛው መቶ ዘመናችንን አጠቃላይ የሆነ ጦርነት (ቁጥር 4)፣ ሰፊ አካባቢ የሚሸፍን የምግብ እጥረት (ቁጥር 5 እና 6) እንዲሁም ‘ቀሳፊ ቸነፈር’ (ቁጥር 8) የሚኖርበት ዘመን እንደሚሆን ይገልጻል። በግልጽ እንደሚታየው ይህ መግለጫ ኢየሱስ በወንጌሎች ውስጥ ከተነበየው ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ የኢየሱስ ትንቢት በዚህ ‘በጌታ ቀን’ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ያረጋግጣል።—ራእይ 1:10

19 ይህን ትንቢት ያጠኑ ሰዎች ማቴዎስ 24:7–14 እና ራእይ 6:2–8 ላይ የተተነበየው ጥምር ምልክት የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ እየታዩ መሆናቸውን ተገንዝበዋል። የይሖዋ ምስክሮችም የኢየሱስ ትንቢት በዚህ በዘመናችን ሁለተኛውንና ከፍተኛውን ፍጻሜ በማግኘት ላይ መሆኑን በመላው ዓለም አስታውቀዋል። አሰቃቂ ጦርነቶች፣ አውዳሚ የመሬት መናወጦች፣ አስከፊ ረሃብና ተዛማች በሽታዎች ለዚህ ማስረጃ ናቸው። በዚህ የመጨረሻ ነጥብ ላይ ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት (ሐምሌ 27, 1992) እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በሞት እየሸኘ ያለው የኤድስ ወረርሽኝ . . . ከጥቂት ጊዜ በኋላ በታሪክ ዘመናት ከታዩት ሁሉ የበለጠ ኪሣራና እልቂት የሚያስከትል ወረርሽኝ ይሆናል። በ14ኛው መቶ ዘመን ተነሥቶ የነበረው ብላክ ዴዝ የተባለ ቸነፈር 25 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን ገድሎ ነበር። በ2000 ዓመት ገደማ ግን ለኤድስ በሽታ ምክንያት የሆነው ቫይረስ ማለትም የኤች አይ ቪ ተሸካሚዎች ቁጥር አሁን ካለበት 12 ሚልዮን ተነስቶ ከ30 እስከ 110 ሚልዮን ይደርሳል። በሽታው ምንም ዓይነት መድኃኒት ያልተገኘለት በመሆኑ እነዚህ ሁሉ በሞት ይቀሰፋሉ።”

20. የማቴዎስ 24:4–22 የመጀመሪያ ፍጻሜ ምንን የሚጨምር ይሆናል? ይሁን እንጂ ምን ሌላ ፍጻሜ እንደሚኖረው ግልጽ ነው?

20 ታዲያ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ጥያቄ የሰጠውን መልስ በሚመለከት ምን ብለን ልንደመድም እንችላለን? ትንቢቱ ወደ ኢየሩሳሌም ጥፋት የሚያደርሱና በጥፋቱ ጊዜ የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን በትክክል ተንብዮአል። ከ70 እዘአ በኋላ የሚፈጸሙ አንዳንድ ነገሮችንም ጠቅሷል። ይሁን እንጂ ከተናገራቸው ነገሮች አብዛኞቹ ገና ወደፊት በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈጸሙና የአሁኑን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋው ታላቅ መከራ ድምድማት ላይ የሚደርሱ ናቸው። በሌላ አነጋገር በማቴዎስ 24:4–22 እና በማርቆስና በሉቃስ ወንጌሎች ውስጥ በሚገኙት ተመሳሳይ ዘገባዎች ላይ የተገለጸው የኢየሱስ ትንቢት ከ33 እዘአ እስከ 70 እዘአ ባለው ጊዜ ውስጥ ተፈጽሟል። ይሁን እንጂ እነኚሁ ቁጥሮች ሁለተኛና ከዚህ የበለጠ ታላቅ ፍጻሜ ይኖራቸዋል። ይህም ወደፊት የሚመጣውን ከኢየሩሳሌም ጥፋት የሚበልጠውን ታላቅ መከራ ይጨምራል። ይህ ትንቢት በታላቅ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው አሁን ነው። ይህን የሚያረጋግጡልንን ማስረጃዎች በየቀኑ ለመመልከት እንችላለን።f

ወደ ምን ይመራል?

21, 22. ተጨማሪ ነገሮች እንደሚመጡ የሚያመለክት ትንቢት የምናገኘው የት ላይ ነው?

21 ኢየሱስ ትንቢቱን “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ” ባለው ዘመን አታላይ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሐሰተኛ ነቢያት እንደሚነሱ በመናገር አልደመደመም። (ሉቃስ 21:24፤ ማቴዎስ 24:23–26፤ ማርቆስ 13:21–23) ከዚህ ይልቅ በመላው ዓለም የሚታዩ ሌሎች አስደንጋጭ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተናግሯል። እነዚህ ነገሮች የሰው ልጅ በግርማና በክብር ከመምጣቱ ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል። ማርቆስ 13:24–27 የኢየሱስ ትንቢት የቀጠለ መሆኑን ያመለክታል። እንዲህ ይላል፦

22 “በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።”

23. ማቴዎስ 24:29–31 ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በኋላ ረዥም ጊዜ ቆይቶ ፍጻሜውን ያገኛል ብለን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?

23 የሰው ልጅ ማለትም ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ሥርዓት በ70 እዘአ በጠፋበት ጊዜ እንዲህ ባለ አስፈሪ ሁኔታ አልመጣም። በተጨማሪም ማቴዎስ 24:30 እንደሚገልጸው በዚያን ጊዜ የምድር ወገኖች በሙሉ ኢየሱስን አላወቁትም፤ የሰማይ መላእክትም ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ከምድር ሁሉ አልሰበሰቡም። ታዲያ የኢየሱስ ታላቅ ትንቢት ተጨማሪ ክፍል የሚፈጸመው መቼ ነው? አሁን በአካባቢያችን እየተከናወኑ ባሉ ሁኔታዎች በመፈጸም ላይ የሚገኝ ነው ወይስ በቅርቡ ስለሚፈጸሙ ነገሮች እንድናስተውል የሚያስችለን ትንቢት ነው? ስለዚህ ጉዳይ ለማወቅ መፈለግ ይገባናል፤ ምክንያቱም የሉቃስ ዘገባ ኢየሱስ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” ሲል እንዳሳሰበ ይገልጻል።—ሉቃስ 21:28

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የነዚህ ምዕራፎች አንዳንድ ክፍሎች በገጽ 14 እና 15 ላይ ባለው ቻርት ውስጥ ይገኛሉ። በነጠብጣብ የተሰመሩት መስመሮች ተመሳሳይ የሆኑትን ክፍሎች ያመለክታሉ።

b እነዚህ ነገሮች እንደተከሰቱ የሚገልጹ ታሪካዊ ማስረጃዎች ለማግኘት የጥር 15, 1970 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 43–45 ተመልከት።

c ቶት የተባለው ቃል በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ 80 ጊዜ (9 ጊዜ በምዕራፍ 24 ውስጥ) በሉቃስ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ 15 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ማርቆስ ቶት የተባለውን ቃል የተጠቀመበት ስድስት ጊዜ ብቻ ሲሆን አራቱ የተጠቀሱት ‘በምልክቱ’ ውስጥ ነው።

d ማቲው ሄንሪ የተባሉት እንግሊዛዊ ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “ከለዳውያን በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሱት ጥፋት በጣም አስከፊ ቢሆንም ይኸኛው ይበልጥ የከፋ ነበር። የአይሁዳውያንን ዘር . . . ፈጽሞ ለማጥፋት የቃጣ ነበር።”

e ብዙዎች የሉቃስ ዘገባ ከሉቃስ 21:24 ጀምሮ ሌላ ዓይነት ሐሳብ ይገልጻል ይላሉ። ዶክተር ሊየን ሞሪስ እንዲህ ሲሉ አስገንዝበዋል፦ “ኢየሱስ በመቀጠል ስለ አሕዛብ ዘመን ይናገራል። . . . እንደ አብዛኞቹ ምሑራን አስተያየት ከዚህ በኋላ የኢየሱስ ትንቢት የሚያተኩረው የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ ላይ ነው።” ፕሮፌሰር አር ጊንስ “የሰው ልጅ መምጣት (ማቴ 24:29–31፤ ማር 13:24–27)” በሚለው ንዑስ ርዕሳቸው ሥር እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “‘የአሕዛብ ዘመን’ የሚለው አባባል መጠቀሱ ለዚህ አዲስ ርዕስ መግቢያ ሆኖ ያገለግላል። [ሉቃስ] የትኩረት አቅጣጫውን በመቀየር ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት መናገር ያቆምና ወደፊት ስለሚመጣው ዘመን ይገልጻል።”

f ፕሮፌሰር ዎልተር ኤል ሌይፌልድ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “የኢየሱስ ትንቢት ሁለት ክፍል አለው ብሎ ማሰብ ይቻላል። እነሱም፦ (1) በቤተ መቅደሱ ላይ የደረሱትን ጨምሮ በ70 ዓ. ም. የተፈጸሙት ነገሮችና (2) ወደፊት ከረዥም ጊዜ በኋላ የሚፈጸሙትና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት አነጋገሮች ጋር ተመሳሳይ በሆኑ ቃላት የተናገራቸው ነገሮች ናቸው።” በጄ አር ደሜሎ የተዘጋጀው ማብራሪያ እንዲህ ይላል፦ “ጌታችን የተናገረው ስለ አንድ ነገር ሳይሆን ስለ ሁለት ነገሮች እንደሆነና የመጀመሪያው ለሁለተኛው ጥላ እንደሚሆንለት ከተገነዘብን ይህንን ታላቅ ንግግሩን ለመረዳት አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ አብዛኞቹ ይወገዳሉ። . . . በተለይ ‘ስለ አሕዛብ ዘመን’ የሚናገረው [ሉቃስ] 21:24 . . . ኢየሩሳሌም ከጠፋችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ መሐል ረዥም ዘመን እንዳለ በግልጽ ያሳያል።”

ታስታውሳለህን?

◻ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:3 ላይ ላለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ወደ 70 እዘአ የሚያደርስ ምን ፍጻሜ ነበረው?

◻ ቶት የሚለው ቃል አጠቃቀም የኢየሱስን ትንቢት እንድንረዳ የሚያግዘን እንዴት ነው?

◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዚያ በፊት ደርሶ የማያውቅ ዓይነት “ታላቅ መከራ” የሆነው እንዴት ነው?

◻ ሉቃስ በዛሬው ጊዜ የምንኖረውን እኛንም የሚመለከቱ ምን ሁለት የኢየሱስ ትንቢት ክፍሎች የሆኑ ነገሮችን ገልጿል?

◻ በማቴዎስ 24:4–22 ላይ የሚገኘው ትንቢት ሁለተኛና ታላቅ ፍጻሜ እንደሚኖረው የሚያመለክቱት ምን ነገሮች ናቸው?

[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

ማቴዎስ 24

4“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 5ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። 6ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፣ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። 7ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ረሀብና የምድርም መናወጥ ይሆናል፤ [እንደ 1980 ትርጉም] 8እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

9“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 10በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ 11ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ 12ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። 13እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 14ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።

------------------------------------------------------

15“እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል፣ 16በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ 17በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፣ 18በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 19በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 20ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 21በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። 22እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።

---------------------------------------

23 በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ 24ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። 25እነሆ፣ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። 26እንግዲህ፦ እነሆ፣ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፣ አትውጡ፤ እነሆ፣ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፣ አትመኑ፤ 27መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፣ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ 28በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ።

-----------------------------

-----------------------------

29 “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። 30በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ 31መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፣ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።”

ማርቆስ 13

5 “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 6ብዙዎች፦ እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፣ ብዙዎችንም ያስታሉ። 7ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፣ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው።

8 ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

9 “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኩራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 10አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። 11ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፣ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 12ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል፤ 13በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።

-----------------------------------------------

14“ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፣ አንባቢው ያስተውል፣ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፣ 15በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፣ 16በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 17በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 18ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 19በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። 20ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፣ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።

--------------------------------------------------

21 በዚያን ጊዜም ማንም፦ እነሆ፣ ክርስቶስ በዚህ አለ፣ ወይም፦ እነሆ፣ በዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ 22ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። 23እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፣ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ።

---------------------------------------------------

---------------------------------------------------

24 “በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ 25ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። 26በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 27በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።”

ሉቃስ 21

8 “እንዲህም አለ፦ እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፦ እኔ ነኝ፣ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። 9ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፣ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።

10 “በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ 11ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።

12 ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኩራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ 13ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። 14ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤ 15ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። 16ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ 17በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 18ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ 19በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።

----------------------------------------------------------------

20 “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። 21የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉትም ወደ እርስዋ አይግቡ፤ 22የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና። 23በዚያን ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፣ በዚህም ሕዝብ ላይ ቁጣ ይሆናልና፤ 24በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብም ሁሉ ይማረካሉ፤

-----------------------------------------------------------------

የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።

---------------------------------------------

---------------------------------------------

25 “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ 26ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉና። 27በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ70 እዘአ የደረሰው መከራ በኢየሩሳሌምም ሆነ በአይሁዳውያን ሥርዓት ላይ ከደረሱት መከራዎች ሁሉ የሚበልጥ ነበር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ