“አምላካዊ ፍርሃት” ወደተባለው የወረዳ ስብሰባ ኑ
ጥንት ይኖሩ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች በየዓመቱ ሦስት ጊዜ ተሰብስበው በዓል እንዲያደርጉ በሙሴ ሕግ ታዘው ነበር። በእነዚህ ቀናት አስደሳች ጊዜ ያሳልፉና በመንፈሳዊ ይታነጹ ነበር።—ዘዳግም 16:16
በዛሬው ጊዜም ቢሆን የይሖዋ አገልጋዮች በየዓመቱ ሦስት ጊዜ ይሰበሰባሉ። በልዩ ስብሰባ ቀን፣ ለሁለት ቀናት በሚደረገው የክልል ስብሰባና ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት በሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ይገኛሉ። በ1994 የአገልግሎት ዓመትም የይሖዋ ምስክሮች “አምላካዊ ፍርሃት” የሚል መልእክት በሚኖረው የወረዳ ስብሰባ ላይ ይገኛሉ።
የአምላክ ቃል በማያሻማ መንገድ ስለ አምላካዊ ፍርሃት ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት 200 የሚያክል ጊዜ ተጠቅሷል። አምላካዊ ፍርሃት ከመጥፎ ነገር ሊጠብቀን እንደሚችል “እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል” በሚሉት የምሳሌ 16:6 ቃላት ተገልጿል። በመዝሙር 111:10 ላይም ይሖዋን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ መሆኑ ተነግሮናል!
አምላካዊ ፍርሃት ሁለት ዘርፎች አሉት ሊባል ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ከፍቅር ይመነጫል። ለአምላክ ባለን ታላቅ ፍቅር ምክንያት እርሱን ለማስከፋት እንፈራለን። (ምሳሌ 27:11) በተጨማሪም ክፉ ለሚያደርጉ ሁሉ አምላክ “የሚያጠፋ እሳት” መሆኑን ስለምናውቅ አምላካዊ ፍርሃት ቢያድርብን ጥበበኞች እንሆናለን።—ዕብራውያን 12:29
“አምላካዊ ፍርሃት” በሚል መልእክት ላይ የተመሠረተው የወረዳ ስብሰባችን ላይም በአምላካዊ ፍርሃት ለማደግ የሚያስችሉ ብዙ መመሪያዎችና ማበረታቻዎች እናገኛለን። ይህም ትምህርት በንግግሮች፣ በትዕይንቶችና በድራማ እንዲሁም በሚቀርቡት ተሞክሮዎች አማካኝነት ይተላለፋል።
የጥንቶቹ እስራኤላውያን ወደ ስብሰባዎቻቸው ባዶ እጃቸውን እንዳይመጡ እንደታዘዙ ሁሉ እኛም ብንሆን ለስብሰባው አስደሳች መሆንና መሳካት የበኩላችንን ለማድረግ መነሳሳት አለብን። (ዘዳግም 16:17) ይህንንም ማድረግ የምንችለው ይሖዋ ላቀረበልን ማዕድ ያለንን አክብሮት በማሳየት ነው። ግን እንዴት? በሰዓቱ በመድረስ፣ ከመድረክ የሚነገረውን ነገር ትኩረት ሰጥተን በማዳመጥ፣ መዝሙር ሲዘመር በሙሉ ልብ በመካፈል ነው። በስብሰባው ወቅት አናወራም ወይም ወዲያና ወዲህ አንልም። በስብሰባው ላይ ለሚሰጠው አገልግሎት የተቻለንን ያህል ራሳችንን በፈቃደኝነት በማቅረብ አስተዋፅኦ ለማድረግ እንፈልግ ይሆናል። ትላልቅ ስብሰባዎችን ማዘጋጀት ብዙ የሥራ ክፍሎችን ይጠይቃል። እነዚህ ሁሉ ክፍሎች ደግሞ ሊያንቀሳቅሳቸው የሚችል የሰው ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ እንደባረከን መጠንም የገንዘብ አስተዋፅኦ ለማድረግ እንፈልግ ይሆናል።
እንግዲያው የይሖዋ አገልጋዮች የሆንን ሁላችን “አምላካዊ ፍርሃት” በሚል መልእክት ላይ የተመሠረተው የወረዳ ስብሰባ በሚደረግባቸው ሦስት ቀናት ከዓርብ ዕለት የመክፈቻ መዝሙር እስከ እሁድ ዕለት የመደምደሚያ ጸሎት ድረስ ባሉት ፕሮግራሞች ሁሉ ላይ ለመገኘት ከአሁኑ ዕቅድ እናውጣ።