የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 4/15 ገጽ 26-29
  • ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠዋል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠዋል!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ብቸኝነትን ማሸነፍ
  • ተቃውሞ ቢኖርባቸውም ጸንተዋል
  • አቋምን ሳያላሉ መገዛት
  • ‘ያለ ቃል አሸንፉ’
  • ‘በለቅሶ ዘርቶ በደስታ ማጨድ’
  • ‘የሴት ራስ ወንድ ነው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • በጋብቻ ውስጥ መገዛት ማለት ምን ማለት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ባሎች—ቤታችሁ ስጋት የሌለበት ቦታ እንዲሆን አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 4/15 ገጽ 26-29

ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠዋል!

“ለመስበክ አትወጪም!” “እነዚያ ሰዎችሽ እዚህ እንዳያንኳኩ!” ብዙ ክርስቲያን ሴቶች ተቃዋሚ የሆኑት ባሎቻቸው እነዚህንና ከነዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን ይናገሯቸዋል። ባሎቻቸው በጦር ሠራዊት ውስጥ የሚሠሩ ሲሆኑ ደግሞ እምነታቸው በተለየ መንገድ ይፈተናል። (ኢሳይያስ 2:4፤ ዮሐንስ 17:16) ታዲያ እንዲህ ዓይነት ባሎች ያሏቸው ክርስቲያን ሚስቶች በመንፈሳዊ ጠንካሮችና በመንግሥቱ አገልግሎትም ንቁዎች ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉት እንዴት ነው?

በታማኝነት ከይሖዋ አምላክ ጎን መቆማቸውና ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋቸው እንዲጸኑ ይረዳቸዋል። የወታደር ሚስት የሆነችው ኢቮን “ይህ ቁርጥ ውሳኔዬ ነበረ፤ የባለቤቴን ተቃውሞ በዘዴ የማከሽፍባቸው መንገዶች እንዳሉ አውቃለሁ” ብላለች። አዎን፣ በርግጥም ነበሩ።

አንድ የጦር አዛዥ ያገባች ሌላዋ ክርስቲያን ሴት ደግሞ ቁርጥ ያለ አቋሟ ባሏ እንዳይጨነቅ ለማድረግ እንኳን እንዴት እንደረዳት ትናገራለች። “የኔንም ሆነ የራሱን ፕሮግራም ያውቃል። የውትድርና ሰዎች ደግሞ በፕሮግራም መመራት ይወዳሉ” ትላለች። ያም ሆኖ ግን ይሖዋን በማገልገል መቀጠል ቀላል አልሆነላትም።

ብቸኝነትን ማሸነፍ

አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ባሎች ያሏቸው ሚስቶች ባሎቻቸው ከቤታቸው ርቀው በመሄድ እንዲሠሩ በሚታዘዙበት ቦታ አብረዋቸው የሚሄዱ ከሆነ በሚነገራቸው ማስታወቂያ መሠረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ቤት ለቅቆ የመሄድ ተደጋጋሚ ፈተና ያጋጥማቸዋል። ከዚያም ባልለመዱት አካባቢ መኖር ሲጀምሩ ገለልተኛ መሆናቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ሊሰማቸው ግን አይገባም። ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች የተሻለ ሁኔታ አላቸው። ይህ የተሻለ ሁኔታ ምንድን ነው? ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጴጥሮስ እንደተናገረው “ወንድሞች” አሉን። በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩት የይሖዋ ምስክሮች በ231 አገሮች በሚገኝ በአንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ እንዳሉ ‘ወንድማማቾች’ ናቸው። በማንኛውም ቦታ ታገኛቸዋለህ ማለት ይቻላል።—1 ጴጥሮስ 2:17 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ።

ሱዛን ትኖርበት የነበረውን አካባቢ በድንገት ለቅቃ ባለቤቷ እንዲሠራ በተመደበበት የአየር ኃይል የጦር ሠፈር ውስጥ መኖር ጀመረች። በጊዜው በእውነት ውስጥ ገና አዲስ ከመሆኗ ሌላ የማያምነው ባሏ በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈሏን እንድታቆም ተጽዕኖ ያደርግባት ነበር። በዚህ ጊዜ ምን እንዳደረገች እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ወዲያውኑ በአካባቢው ወደሚደረጉት ስብሰባዎች ሄድኩ። እዚያም ከሌሎች እኅቶች ጋር ለመቀመጥና ለመጫወት ቻልኩ። እውነቴን ነው የምላችሁ፤ በጽናት እንድቀጥል ያደረገኝ ይህ ኅብረት ነው።”

አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት የመንፈስ ጭንቀት ይፈጥራል። በዚያ ጊዜ አንድ አስደሳች ዜና መስማት ከጭንቀት ያላቅቃል። ባሏ ውጭ አገር እንዲሠራ ሲሾም አብራው የሄደችው ግሌኒስ የተባለች አንዲት እንግሊዛዊት እህት እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ተክዤ እያለሁ ከብዙ ዓመታት በፊት እኔ ራሴ በጦር ሠራዊት ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ የማውቃት አንዲት ሴት የጻፈችልኝ ደብዳቤ ሳላስበው ደረሰኝ። ደብዳቤው ሴትዬዋ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተጠምቃ የይሖዋ ምስክር መሆኗን የሚገልጽ ነበር። ይህ ዜና ልክ ማበረታቻ ያስፈልገኝ በነበረበት ጊዜ ስለመጣልኝ አበረታታኝ።”

ከባለቤቷ ጋር ወደ ኬንያ የሄደችው ጄን ምንም እንኳን ስብሰባዎቹ የሚደረጉት በማታውቀው ቋንቋ ቢሆንም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እጅግ የሚረዳ ሆኖ አግኝታዋለች። “ይሖዋ እዚህ እንድሆን እንደሚፈልግ አወቅሁ” ትላለች። “ከወንድሞቼ ጋር ነበርኩ። እነሱ በጣም ያበረታቱኝ ነበር። በጥሩ ሁኔታ ስለተቀበሉን ልክ ቤተሰቦቼ እንደሆኑ ያህል ይሰማኛል።”

ጄን እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር ሆነው መንፈሳዊ ዘመዶች ካገኙት ብዙ ወንድሞችና እኅቶች መካከል አንዷ ብቻ ነች። እሷ እንዲያውም መንፈሳዊ ዘመዶች እንዳሏት አታውቅም ነበር።—ማርቆስ 10:29, 30

ተቃውሞ ቢኖርባቸውም ጸንተዋል

ኢየሱስ “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤” ሲል አስጠነቅቋል። “ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።” (ማቴዎስ 10:34) ምን ማለቱ ነበር? ኤ ቲ ሮቤርትሰን ወርድ ፒክቸርስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት በተባለ መጽሐፋቸው ውስጥ ሰላም ይኖራል ተብሎ በሚታሰብበት በቤተሰብ ውስጥ እንኳን “በድንገት ሰይፍ መማዘዝ” ሊኖር ይችላል ማለቱ ነው ሲሉ ሐሳብ ሰጥተዋል። “ለሰውም ቤተሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” አለ ኢየሱስ። (ማቴዎስ 10:36) አንደኛው የትዳር ጓደኛ ለእውነት ጠላት በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸው ይረጋገጣል።

ዳያን ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር የአየር ኃይል መኰንን የሆነው ባለቤቷ በጭራሽ ደስ አላለውም ነበር። ይህ በትዳራቸው ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ? “በመካከላችን የበረዶ ግድግዳ የቆመ ይመስል ነበር” ትላለች ዳያን ሁኔታውን ስታስረዳ። “የተጋባነው በደስታ ነበር። በኋላ ግን ሳናስበው በአንድ ቤት ውስጥ የምንኖር ደባሎች ሆንን።” ታዲያ ሁኔታውን እንዴት ልትቋቋመው ቻለች? “በነበረኝ እምነትና ባደረግሁት ቁርጥ ውሳኔ እንዲሁም ከይሖዋና ከመንፈሱ ባገኘሁት እርዳታ ልቋቋመው ቻልኩ።” ዳያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የነቢዩ ዳንኤልን ምሳሌ ልብ ብላው ነበር።

ዳንኤል በባቢሎን በግዞት ሳለ የአምላክ አገልጋይ ሊበላው የማይገባ ምግብ ሲቀርብለት “ደስ የሚያሰኘውን የንጉሡን ምግብ በመመገብ . . . ራሱን ላለማርከስ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ።” አዎን፣ ዳንኤል ጥንቃቄ የተሞላበት ውሳኔ አደረገ። ያንን ምግብ በመብላት ራሱን ላለመበከል በልቡ ወሰነ። “እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ [ደጋግሞ አዓት] ለመነ።” እንዲህ በማድረጉ እንዴት ያለ ጥንካሬ አሳየ! ውጤቱስ? ይሖዋ ቁርጥ አቋሙን ባረከለት።—ዳንኤል 1:8 የ1980 ትርጉም ፣ 9, 17

ዛሬም በተመሳሳይ ተቃዋሚ የሆነው ባል ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች መሄዷን እንድታቆም ሚስቱን ሊጠይቃት ይችላል። ምን ማድረግ አለባት? ጄን እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። እንዲህ አለች፦ “ተጽዕኖ ቢመጣብኝም በጭራሽ ከአቋሜ ዝንፍ አላልሁም። አቋሜን ማላላት እንደሌለብኝ አውቅ ነበር። ስብሰባ መሄዴ ምን ያህል እንደሚያስፈልገኝ መግለጽ ነበረብኝ።” በስብሰባዎች ላይ መገኘቷን በመቀጠሏ ይሖዋ ያደረገችውን ቁርጥ ውሳኔ ባረከላት።

“ባለቤቴ ወደ ስብሰባዎች እንዳልሄድ ሊከለክለኝ ሞክሮ ነበር፤ ግን ለብዙ ጊዜ አልገፋበትም” ትላለች ግሌኒዝ። “ስብሰባ መሄዴን ቀጠልኩ። ወደ ቤት ስመጣ አንዳንድ ጊዜ ይደበድበኛል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ያኮርፈኛል።” ሆኖም በተደጋገሚ ትጸልይ ስለነበር ሁኔታውን ተቋቋመችው። ሁለት የጉባኤው ሽማግሌዎችም አብረዋት አዘውትረው ይጸልዩ ነበር። ይህም በስብሰባዎች መገኘቷን እንድትቀጥል በጣም አበረታቷታል።—ያዕቆብ 5:13–15፤ 1 ጴጥሮስ 2:23

አንዳንድ ጊዜ ባል ከፍተኛ ማዕረግ ካለው ሚስቱ የምሥራቹን እንዳትሰብክ ተስፋ የሚያስቆርጥ ግፊት ያሳድርባት ይሆናል። ለባለቤቷ ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር ምን እንደሆነ ዳያን በግልጽ መንገር ነበረባት። “መስበኬን በመቀጠሌ ሊመጣብኝ የሚችለውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ተዘጋጅቼ ነበር” አለች። ይህ አቋሟ ከሐዋርያት አቋም ጋር በጣም ይመሳሰላል። (ሥራ 4:29, 31) ያም ሆኖ ግን የምትሰብከው በዘዴ ነበር። እንዲህ አለች፦ “ቡና እጠራቸውና ለሁሉም የእውነት ን መጽሐፍ እሰጣቸው ነበር።”—ማቴዎስ 10:16፤ 24:14

አቋምን ሳያላሉ መገዛት

በትዳራቸው ውስጥ ባለው ሁኔታ ቢረበሹም እንኳን ክርስቲያን ሚስቶች የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት በመጠባበቅ በይሖዋ ላይ ይመካሉ። ይህም ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። እምነታቸውን ሳይክዱ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ለባሎቻቸው ማንኛውንም ድጋፍ ይሰጧቸዋል። እንዲህ በማድረግ “እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ . . . [ለባሎቻችሁ] ተገዙላቸው” ሲል ጴጥሮስ በመንፈስ ተነሳስቶ የሰጠውን ምክር ይከተላሉ። (1 ጴጥሮስ 3:1) ዘ አምፕሊፋይድ ኒው ቴስታመንት በተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሐዋርያው የሰጠው ይህ መመሪያ እንዲህ ይነበባል፦ “ከነሱ ያነሳችሁና እነሱን ተማምናችሁ የምትኖሩ የበታቾቻቸው ሁኑላቸው።” ጄን ይህንን ምክር እንዴት እንደተከተለች ተመልከቱ። እንዲህ ትላለች፦ “ባለቤቴ እኔ ማድረግ የምፈልገው ነገር ሥራውን የማያደናቅፍበት መሆን እንዳለበት ነገረኝ። ስለዚህ እርሱን ልረዳው የምችልበትን መንገድ መፈለግ ጀመርኩ።”

አንዳንድ ክርስቲያን ሚስቶች ባሎቻቸው የተጋበዙባቸው ግብዣዎች ላይ ለመገኘት ፈቃደኞች ሆነዋል። ይሁን እንጂ እምነታቸውን በፍጹም ላለማላላት ቆርጠዋል። ጄን ጊዜ ወስዳ ከባለቤቷ ጋር ስለ ጉዳዩ ተነጋገረችበት። በግብዣው ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ እንደሆነች ግን እዚያ ተገኝታ እሱን የሚያሳፍር ነገር ማድረግ እንደማትፈልግ ረጋ ብላ ገለጸችለት። “እንዲህ ባለ ግብዣ ላይ እዚያ የተገኙት ሁሉ ከመቀመጫቸው ተነስተው ‘ለጤናችን’ ወይም ‘ስለ እገሌ ጤንነት’ ብለው እንደሚጠጡ አውቃለሁ። የታማኝነት መግለጫ መሰጠት ያለበት ለይሖዋ አምላክ ብቻ መሆኑን ደግሞ ተምሬአለሁ። ይህ ዓይነቱ ድርጊት ደግሞ የአክብሮት መግለጫ ብቻ አይደለም፤ ከዚያ የበለጠ ነው። ባለቤቴ እኔ በግብዣው ላይ ተገኝቼ በዚህ ድርጊት አልካፈልም ስል እንዴት እንደሚያሳፍረው ተገነዘበና ‘ባትመጪ ይሻላል!’ አለኝ። እኔም ታዘዝኩት።”

ግሌኒስ ግን ከባሏ ጋር አብራ ወደ ግብዣው ቦታ ሄደች። ሆኖም ግብዣውን የሚመራውን አዛዥ ትከታተለዋለች። ‘ለጤናችን’ ብለው ለመጠጣት ሲዘጋጁ ቀስ ብላ ወደ መታጠቢያ ቤት ትሄዳለች! አዎን፣ እነዚህ ሴቶች ካሉበት ሁኔታ ጋር ተመሳስለው ይኖራሉ፤ ሆኖም በጭራሽ አቋማቸውን አያላሉም።

‘ያለ ቃል አሸንፉ’

“የሚስትነት ችሎታዬን ለማሻሻል ከጣርኩ፣ ባለቤቴ እውነት እኔን እየለወጠኝ እንዳለ ይገነዘባል” ትላለች ኢቮን። ስለዚህ የቤተሰብ ኑሮ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያለውን “እጅግ የምትወደድ ሚስት” የሚለውን ምዕራፍ ደጋግማ አነበበችው።a “‘እያለቀሱ የሚነዘንዙ’ በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን ሐሳብ ደግሞ ይበልጥ አተኩርበታለሁ። ስለ ጉዳዩ ባለቤቴን ላነጋግረው በሞከርኩ ቁጥር ነገሩ እየባሰበት ይሄዳል።” በመጨረሻ ግን ባለቤቷ ይሖዋን የሚያገለግል እንዲሆን ልትረዳው ቻለች። እንዴት? በ1 ጴጥሮስ 3:1 ላይ የተገለጸውን ባሎችን ‘ያለ ቃል ማሸነፍ’ እንደሚገባ የሚናገረውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ነው።

ክርስቲያን ሴቶች ቤተሰቦቻቸውን የሚይዙበት ሁኔታ ሌሎች ሰዎች ክርስትናን እንዲያደንቁ ሊያደርግ ይችላል። “እውነት የሚማርክ እንዲሆን ለማድረግ የቻልኩትን ያህል እጥር ነበር” አለች ዳያን። “ወደ ስብሰባ ስሄድ ባለቤቴ እንደተተወ ሆኖ ይሰማዋል፤ ስለዚህ ልጆቹ ወደ ቤት ስንመጣ ከሌላው ጊዜ ይበልጥ ጨዋዎች እንዲሆኑ እነግራቸዋለሁ። ከስብሰባ ስንመለስ እኔም ለርሱ የበለጠ ትኩረት ለመስጠት እሞክራለሁ።” ቀስ በቀስ ባለቤቷ ቤተሰቡ በደግነት እንደሚንከባከበው ሲያይ አመለካከቱ እየተለወጠ ሄደ።

መሰል የይሖዋ አገልጋዮችም ሊረዱ ይችላሉ። ጄን ባለቤቷ ኬንያ ውስጥ ካገኛቸው የይሖዋ ምስክሮች ሚስዮናውያን ጋር አብሮ መሆን በጣም ደስ ይለዋል ትላለች። “ጓደኞቹ ሆኑለት። ስለ እግር ኳስ ጨዋታም ያወራሉ፤ እንዲሁም እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። ብዙ ጊዜ የተለያዩ ሚስዮናውያን እቤታቸው ይጋብዙን ነበር።” ከጊዜ በኋላ ባለቤቷ እንዲህ አለ፦ “የጄንን እምነት ሙሉ በሙሉ ከተለየ ሁኔታ አንፃር እመለከተው ጀመር። ጓደኞቿ ስለ ተለያዩ ጉዳዮች አንስተው መናገር የሚችሉ በጣም አዋቂዎች ነበሩ።” የዳያንም ባል ለእውነት የነበረው አመለካከት ተለወጠ። መኪናው መንገድ ላይ ስትበላሽበት አንድ ወጣት ምስክር መጥቶ ረዳው። “ይህ በጣም ነካኝ” ብሏል።

እርግጥ ወደ እውነት የሚመጡት ሁሉም የትዳር ጓደኞች አይደሉም። ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል? ይሖዋ ታማኝ የሆኑት ለመጽናት እንዲችሉ እርዳታ ያደርግላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ግሌኒስ እሷ ካለችበት ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሁሉ የሰጠችውን ማበረታቻ ልብ በሉ፦ “ጋብቻን የመሠረተው ይሖዋ መሆኑንና ባልና ሚስቱ አብረው እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ምንም አትጠራጠሩ። ስለዚህ ባለቤታችሁ ምንም ቢያደርግ ወይም አብረዋችሁ የሚኖሩ ሰዎች ምንም ተቃውሞ ቢያደርሱባችሁ ይሖዋ በፍጹም እንድትሠቃዩ አያደርጋችሁም።” ምንም እንኳን ባለቤቷ እስካሁን ይሖዋን ማምለክ ባይጀምርም ለሷና ለእውነት የነበረው አመለካከት ግን ተለውጧል።

‘በለቅሶ ዘርቶ በደስታ ማጨድ’

እነዚህ ክርስቲያን ሴቶች በርግጥም ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠዋል። እናንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ሥር ካላችሁ ቁርጥ ውሳኔያችሁ ይኸው ይሁን። “አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፣ እርሱንም አምልክ፤ ከእርሱም ተጣበቅ” የሚለውን ጥብቅ ምክር አስታውሱ።—ዘዳግም 10:20

“በሄዱ ጊዜ፣ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” ብሏል መዝሙራዊው። (መዝሙር 126:6) አንዲት ምስክር እንዲህ አለች፦ “ያለ ቃልም ይሁን በቃል የትዳር ጓደኛችሁ እውነትን እንዲያውቅ ለማድረግ ስትጥሩ ብዙ እንባ ታፈስሳላችሁ። በመጨረሻ ግን እውነትን ባይቀበል እንኳን እናንተ ላደረጋችሁት ጥረት ይሖዋ ስለሚባርካችሁ በደስታ እልል ትላላችሁ።”

በቤታቸው ውስጥ ተቃውሞ እያለባቸው ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ ከልብ ሊመሰገኑ ይገባል። ድጋፍና ፍቅር ማግኘት ይገባቸዋል። ይሖዋን ለማገልገል ባላቸው ቁርጥ ውሳኔ አቋማቸውን ሳያላሉ የሚቀጥሉ ያድርጋቸው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው፤ በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ። (1978)

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጸሎት የሚደረግ ጥናት ክርስቲያናዊ ውሳኔን ያጠነክራል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ