ሊዋሽ የማይችለው አምላክ የሰጠኝ ድጋፍ
ሜሪ ዊሊስ እንደተናገረችው
ዓለምን የመታው የኢኮኖሚ ቀውስ በ1932 የምዕራብ አውስትራሊያንም ገጠር አዳርሶ ነበር። በዚያ ዓመት ገና የ19 ዓመት ልጅ ሳለሁ ኤለን ዴቪስና እኔ ወደ 100,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋት ባለው ክልል ውስጥ እንድንሰብክ ተመደብን። የስብከት ሥራችንን የጀመርነው የትውልድ ሥፍራችን ከሆነችው የምዕራብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ ከፐርዝ 950 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ በዊሉና ነው።
ኤለንና እኔ ወደዚች ከተማ የተጓዝነው ከአንድ ጥሩ ባሕርይ ያለው የባቡር ጣቢያ ዘበኛ ጋር ለባቡሩ ሠራተኞች በተዘጋጀ የባቡር ፉርጎ ውስጥ ተሳፍረን ነበር። ባቡሩ በየጣቢያው ሲቆም ዘበኛው በጣቢያው ለምን ያህል ጊዜ እንደምንቆይ በደግነት ይነግረን ነበር። ይህም ከባቡሩ ወርደን ባቡር ጣቢያዎቹ በሚገኙባቸው በእነዚህ ራቅ ብለው በሚገኙ ሥፍራዎች ለሚኖሩ ሰዎች እንድንመሰክርላቸው ያስችለን ነበር። በመጨረሻም ንፋስ አቧራውን ያቦን በነበረበት ወቅት የማዕድን አውጪዎች መኖሪያ ወደሆነችው ዊሉና ከተማ ደረስን።
ነገር ግን በዊሉና የሚገኘው የባቡር ጣቢያ ከመሐል ከተማው 3 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቅ ነበር። በጽሑፍ የተሞሉ ሦስት ከባድ ካርቶኖችና ሁለት ሻንጣዎች ይዘን ነበር፤ ግን ሁለታችንም ያን ያህል ጠንካሮች አልነበርንም። ምን እናድርግ? ካርቶኑን እንጨት ላይ አንጠለጠልነውና እንጨቱን ከጫፍና ከጫፍ ሆነን ያዝነው። በዚህ መንገድ ካርቶኖቹን አንድ በአንድ ተሸክመን ወሰድናቸው። ሦስቱን ካርቶኖችና ሻንጣዎቹን 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው መሐል ከተማ ለመውሰድ ሰባት ጊዜ ተመላለስን። እጆቻችን ውኃ በመቋጠራቸው የተነሣ አሁንም አሁንም እናርፍ ነበር።
አቧራው ቢያስቸግረንም፣ እጆቻችን ውኃ ቢቋጥሩና እግሮቻችን ቢዝሉም ፈታኝ የሆነውን ይህን ሥራና ያጋጠመንን ያልተለመደና አስቸጋሪ ሁኔታ በደስታ ተወጣነው። ሁለታችንም ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደነበረና ራቅ ብለው በሚገኙ ቦታዎች ለመስበክ ስንሄድ ገና ከጅምሩ የገጠመንን አቅምንና ችሎታን የሚፈታተን ሁኔታ እንድንቋቋም እንደረዳን ተሰምቶናል። በዚህ ጉዟችን ወቅት ባደረግነው ጥረት ቦብ ሆርን የተባለ ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመቀበሉ ይሖዋ ሥራችንንም እንደባረከው ወዲያውኑ ለመመልከት ቻልን። ቦብ በቤቴል አገልግሎት የተወሰኑ ዓመታት ማሳለፍ በመቻሉና በ1982 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት በማገልገሉ ከፍተኛ እርካታ አግኝተናል።
ከዊሉና ተነስተን በባህር ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ ጀራልድተን ከ725 ኪሎ ሜትር በላይ ስንጓዝ በቆምንባቸው ቦታዎች ባሉ መንደሮች ውስጥ እንሰብክ ነበር። ከዚህች ከተማ ተነስተን እንደገና ወደ ፐርዝ አቀናን። ባቡር በሚጠበቅባቸው ኦና ቤቶች ውስጥ ያደርንባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዲያውም አንድ ጊዜ በባቡር ጣቢያው አጠገብ በነበረ የድርቆሽ ክምር ላይ ተኝተናል።
ለጉዞ እንዲሆነን ብለን እቤት ውስጥ የተጋገሩ ከስንዴ ዱቄት የተሠሩ ብስኩቶችን በትራስ ልብስ ውስጥ ከተን ይዘን ነበር። በመጀመሪያው ጉዟችን ግማሹን መንገድ ስንጓዝ የነበረን ስንቅ ይኸው ብቻ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ለምግብ የሚሆን ገንዘብ የምናገኘው በአልቤርጎዎችና በምግብ ቤቶች ውስጥ ዕቃ በማጠብና ቤት በመወልወል ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ በዚያ ሐሩር ለአተር ወይም ለባቄላ ለቀማ እንቀጠር ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የሚወስዱ ሰዎች የሚከፍሉት ገንዘብ ወጪዎቻችንን ለመሸፈን እንድንችል ረድቶናል።
በይሖዋ ላይ እምነት እንዲኖረኝና በእነዚያ ወቅቶች የገጠሙኝን ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በደስታ እንድቋቋም ያጠነከረኝ የእናቴ ምሳሌነትና በልጅነቴ የሰጠችኝ ማሠልጠኛ ነው።
ክርስቲያናዊ ውርስ
እናቴ በፈጣሪ ላይ ጠንካራ እምነት ነበራት። እኛ ልጆች ብንሆንም ስለ እርሱ ትነግረን እንደነበረ በደንብ ትዝ ይለኛል። ይሁን እንጂ የሰባት ዓመት ወንድማችን በትምህርት ቤት ሳለ በደረሰበት አሳዛኝ አደጋ በመሞቱ እምነቷ በእጅጉ ተፈትኖ ነበር። ሆኖም አምላክን ከማማረር ይልቅ እናቴ ከልቧ ተነሳስታ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። የሚቻል ከሆነ የእንዲህ ዓይነቶቹን አሳዛኝ ክስተቶች መንስዔ ለማወቅ ፈልጋ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ያደረገችው ፍለጋ ከንቱ ድካም ሆኖ አልቀረም። በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ ራሷን መወሰኗን በውኃ ጥምቀት አሳየች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእኛ ጋር ታደርገው በነበረው ውይይት የአምላክ ተስፋዎች መፈጸማቸው የማይቀር መሆኑን ብዙውን ጊዜ ጫን አድርጋ ትገልጽልን ነበር። ምንም ይሁን ምን ‘አምላክ የማይዋሽ መሆኑን’ ሁልጊዜ በአእምሮአችን እንድንይዝ ታሳስበን ነበር። (ቲቶ 1:2) እንዲህ በማድረጓም በዛሬው ጊዜ እህቴና እኔ እንዲሁም ሁለቱ ወንድሞቻችን ከቤተሰቦቻችንና ከልጅ ልጆቻችን ጋር በአንድነት ይሖዋ አምላክን በማወደስ ላይ እንገኛለን። ሁለቱ የእህቴ ልጆች አለንና ፖል ሜሰን በአሁኑ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ያገለግላሉ።
የወንጌላዊነትን ሥራ ለመሥራት በልጅነቴ የነበረኝ ምኞት
ሰነፍ ተማሪ ስለነበርኩ በ1926 በ13 ዓመቴ ትምህርቴን አቋረጥኩ። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ለሌሎች የማካፈል ጠንካራ ምኞት ነበረኝ። አባቴ ማንንም ሰው ለመርዳት የሚያስችል በቂ እውቀት እንደሌለኝ አድርጎ ያስብ ነበር። እናቴ ግን “የአርማጌዶን ጦርነት እየቀረበ እንዳለና ገሮች ምድርን እንደሚወርሱ ብቻ ብትናገር እንኳን ይህ ራሱ የአምላክን መንግሥት ለማስታወቅ ያስችላል” ትል ነበር። ስለዚህ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያ ላይ እያለሁ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ በሚደረገው የስብከቱ ሥራ መሳተፍ ጀመርኩ። ሆኖም እስከ 1930 ድርስ ሳልጠመቅ ቆየሁ። ልክ እንደተጠመቅኩ በፐርዝ አካባቢ የሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ መሥራት ጀመርኩ።
በተከታዩ ዓመት ማለትም በ1931 “የይሖዋ ምሥክሮች” በተባለው አዲሱ ስማችን መጠቀም ጀመርን። ይሁን እንጂ ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ከምናገኛቸው ሰዎች ብዙዎቹ ይህን ቅዱስ የሆነ የአምላክ ስም መጠቀማችንን በመቃወም ያመናጭቁን ነበር። ሆኖም ደስ የማይሉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙም እንኳን በአገልግሎቱ ገፋሁበት። አምላክ አገልጋዮቹ ‘እርሱ በሚሰጠው ኃይል መተማመን’ እንደሚችሉ ተስፋ ሲሰጥ ውሸቱን እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበርኩ።—1 ጴጥሮስ 4:11፤ ፊልጵስዩስ 4:13 አዓት
‘እጅግ ብዙ ሰዎችን’ ለይቶ ማወቅ
በ1935 ሰፊ በሆነው የአውስትራሊያ አህጉር ሌላኛው ክፍል የሚገኝ የአገልግሎት ክልል ተሰጠኝ። ከዚያ በኋላ ለበርካታ ዓመታት ቀደም ሲል እኖርበት ከነበረው ፐርዝ ከተባለው ከተማ ወደ 4,000 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ውስጥ ባለው የኒው ኢንግላንድ ክልል አካባቢ አቅኚ ሆኜ አገልግያለሁ።
እስከዚያ ጊዜ ድረስ በኢየሱስ ሞት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል ላይ ከምሳሌያዊዎቹ ያልቦካ ቂጣና ቀይ ወይን ጠጅ እካፈል ነበር። በዚያን ጊዜ በተለይ ቀናተኛ የሆኑ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከቂጣና ከወይኑ መካፈላቸው ትክክለኛ ድርጊት ተደርጎ ይታይ የነበረ ቢሆንም ሰማያዊ ተስፋ አለኝ ብዬ አምኜ ግን አላውቅም ነበር። በኋላ በ1935 በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ እጅግ ብዙ ሰዎች እየተሰበሰቡ መሆኑ ተገለጸ። ብዙዎቻችን የዚያ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል መሆናችንን በማወቃችን ተደሰትን፤ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ መካፈላችንንም አቆምን። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይሖዋ እንደተናገረው ቀስ በቀስ ይበልጥ ብሩህ እየሆነ ይሄድ ነበር።—ምሳሌ 4:18
አዳዲስ የስብከት መንገዶች
በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ የሸክላ ማጫወቻ በመጠቀም ማገልገል ጀመርን። በመሆኑም ጠንካሮቹ ብስክሌቶቻችን ለከባድ የሸክላ ማጫወቻዎች ብቻ ሳይሆን ለሸክላዎችና ለጽሑፍ ቦርሳዎቻችንም የሚሆኑ የዕቃ መያዣዎች ከፊትና ከኋላ ተገጠመላቸው። ብስክሌቴ ብዙ ዕቃ ከተጫነበት በጣም ተጠንቅቄ መንዳት ነበረበኝ። ምክንያቱም ብስክሌቱ ከወደቀ እንደገና ለማንሣት በጣም ይከብደኛል!
የማስታወቂያ ሰልፎች ይባሉ የነበሩትን ሰልፎች ማድረግ የጀመርነው በዚያ ጊዜ አካባቢ ነበር። ትኩረት የሚስቡ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች የተጻፉባቸው ፖስተሮችን ጀርባችንና ደረታችን ላይ ለጥፈን ወይም በአንገታችን አጥልቀን በከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይ እንሄድ ነበር። ይህ ሥራ በተለይ ሊዝሞር ከተማ ውስጥ ተይዤ በአንዲት አነስተኛ እስር ቤት ውስጥ ተዘግቶብኝ ያደርኩ ዕለት ለየት ያለ የእምነት ፈተና ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በማግስቱ ጸጉሬን እንኳን እንዳላበጥር ተከልክዬ ወደ ፍርድ ቤት መቅረቤ የሚያሳፍር ነበር! ይሁን እንጂ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት በዚያን ጊዜም ደግፎ አቁሞኛል። የያዘኝ ጸጥታ አስከባሪ ሊያቀርበው የቻለው ክስ ይዛው የነበረው ፖስተር ሃይማኖቴን ያወግዛል የሚል ብቻ ስለነበር ክሱ ተነሣልኝ።
እንደገና ወደ ምዕራብ ተመለስኩ
በ1940ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ እንደገና ወደ ምዕራብ አውስትራሊያ የገጠር ከተሞች ተመልሼ የአቅኚነት የስብከት ሥራዬን ቀጠልኩ። በዚህ ቦታ ምንጊዜም የማይረሱ ተሞክሮዎችና መንፈሳዊ በረከቶች አግኝቼአለሁ። በኖርቴም ውስጥ ተመድቤ ሳገለግል ከከተማው አሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትኖር አንዲት ፍሎ ቲሜንስ የምትባል ሥራ የሚበዛባት የቤት እመቤት አገኘሁ። ሪኮንሲሌሽን (መጽናናት) የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ወሰደች። ብዙም ሳይቆይ ራሷን ለይሖዋ አምላክ የወሰነች ምሥክር ሆነች። እስከ አሁንም ድረስ በመንግሥቱ አገልግሎት እየተሳተፈች ናት፤ በዚያን ጊዜ አራት ዓመቷ የነበረው ልጅዋ አሁን አድጋ ልዩ አቅኚ በመሆን ታገለግላለች።
ይሁን አንጂ ሌሎች የማይረሱ ተሞክሮዎችም ነበሩ። አንድ ጊዜ እኔና አብራኝ ታገለግል የነበረችው እህት በኖርቴም ውስጥ በፈረስ በሚጎተት ጋሪ ላይ ተቀምጠን አንድ ድልድይ እናቋርጥ ነበር። ፈረሱ ድንገት በጣም መጋለብ ጀመረና ከታች በርቀት እየተጥመለመለ ሲፈስ የሚታየውን የአቮንን ወንዝ በፍርሃት ተውጠን ተሻገርነው። ፈረሱ ፍጥነቱን የቀነሰው ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ከጋለበ በኋላ ነበር።
ጋብቻና ቤተሰብ
በ1950 አርተር ዊሊስን አገባሁ። እርሱም እንደዚሁ ለብዙ ዓመታት አቅኚ ሆኖ አገልግሏል። በምዕራብ አውስትራሊያ የገጠር ከተማ በሆነችው በፒንጄሊ መኖር ጀመርን። እዚያም ቤንትሊ የተባለ ወንድ ልጅና ዩኔስ የተባለች ሴት ልጅ በመውለድ ተባረክን። ልጆቹ ትምህርታቸውን ወደመጨረሱ ሲቃረቡ አርተር እንደገና አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ወሰነ። የአባታቸው ጥሩ ምሳሌነት ሁለቱም ልጆቻችን ብቃቱን እንዳሟሉ ወዲያውኑ የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል እንዲጀምሩ አነሳሳቸው።
ብዙውን ጊዜ አርተር ልጆቹን ይዞ በጣም ሩቅ ወደሆኑ የገጠር አካባቢዎች ለመስበክ ይሄድ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከልጆቹ ጋር በመሆን በሄደበት ቦታ በድንኳን በማደር ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ይቆይ ነበር። እነርሱ በማይኖሩባቸው በእነዚህ ጊዜያት ሦስቱም አቅኚ ሆነው ማገልገል እንዲችሉ ስል እኔ የቤት ቁሳቁስ በሚሸጥበት የቤተሰባችን ሱቅ ውስጥ ስሠራ እቆይ ነበር።
በአቦርጅን ኅብረተሰብ መካከል ማገልገል
አንድ ቀን ጠዋት ቤተሰቡ ወደ ገጠር አካባቢዎች ሄዶ በተመለሰ ማግስት አንድ ያልጠበቅነው ሰው ወደ ቤታችን መጣ። ሰውዬው የአቦርጅን ተወላጅ ሲሆን “እንደገና ለመመለስ ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቀን። በመጀመሪያ ግራ ተጋብተን ነበር። በኋላ አርተር ሰውዬው በሰካራምነቱ የተነሣ ከብዙ ዓመታት በፊት ከክርስቲያን ጉባኤ የተወገደ ሰው መሆኑን አስታወሰ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በሰካራምነቱና ዕዳ ውስጥ በመዘፈቁ መጥፎ ስም አትርፎ ነበር።
አርተር ወደ ይሖዋ ንጹሕ ድርጅት ለመመለስ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገው ነገረው። ሰውዬው ብዙም ሳይናገር ዝም ብሎ ሄደ። ሁላችንም ምን ያደርግ ይሆን ብለን ማሰብ ጀመርን። አንዳችንም ብንሆን በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ውስጥ የተከናወኑትን ሁኔታዎች እናያለን ብለን አልጠበቅንም ነበር። ይህ ሰው ያደረገው ለውጥ ለማመን የሚያዳግት ነው ማለት ይቻላል! ማሸነፍ የቻለው የመጠጣት ልማዱን ብቻ አልነበረም። አበድረውት ወደነበሩ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እየሄደ የተበደራቸውን ነገሮች እያስታወሳቸው ብድሩን ከፈላቸው! ዛሬ ይህ ሰው እንደገና የእምነት ወንድማችን ሆኗል። ለተወሰነ ጊዜም አቅኚ ሆኖ አገልግሏል።
በፒንጄሊ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ አቦርጅኖች ነበሩ። እነዚህ ትሑት ሰዎች የአምላክን ቃል እውነት እንዲማሩና እንዲቀበሉ በመርዳት እጅግ አርኪ በሆነ አገልግሎት ተደስተናል። ብዙ የአውስትራሊያ አቦርጅኖች እውነትን እንዲያውቁ በመርዳቱ ሥራ መካፈሌ ምንኛ እምነቴን የሚያጠነክር ነገር ነበር!
በፒንጄሊ ውስጥ አንድ ጉባኤ ተቋቋመ። በመጀመሪያ አብዛኛዎቹ የጉባኤው አባላት አቦርጅኖች ነበሩ። ብዙዎቹን ማንበብና መጻፍ ማስተማር ነበረብን። በእነዚያ ቀደም ባሉት ዓመታት ዘራቸው በጣም የተጠላ ነበር። ይሁን እንጂ በንጹሕ አኗኗራቸውና እምነት የሚጣልባቸው ዜጎች በመሆናቸው ቀስ በቀስ የከተማው ነዋሪዎች የአቦርጅን ተወላጅ የሆኑትን ምሥክሮች አከበሯቸው።
ይሖዋ ያደረገልኝ ያልተቋረጠ እርዳታ
ለ57 ዓመታት አምላክን በታማኝነት ያገለገለው ውዱ ባለቤቴ አርተር በ1986 መጀመሪያ ላይ ሞተ። በፒንጄሊ ውስጥ በሚኖሩ ነጋዴዎችና በወረዳው ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ሰዎች ሁሉ እጅግ የተከበረ ሰው ነበር። ባለቤቴ በድንገት በመሞቱ የደረሰብኝን ሐዘን እንድቋቋም ጥንካሬ በመስጠት ይሖዋ እንደገና ደግፎኛል።
ወንዱ ልጄ ቤንትሌይ እርሱና ሚስቱ ሎርና ልጆቻቸውን በእውነት ውስጥ እያሳደጉ ባሉበት በምዕራብ አውስትራሊያ ሰሜናዊ ክፍል ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። ሴቷ ልጄ ዩኔስ እስካሁን ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠሏም ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል። እሷና ባሏ ጄፍ አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። በአሁኑ ጊዜ የምኖረው ከእነርሱ ጋር ሲሆን ሳላቋርጥ ረዳት አቅኚ ሆኜ ማገልገል በመቻሌ ተባርኬያለሁ።
ይሖዋ አገልጋዮቹ ምንም ዓይነት ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም የገጠሟቸውን ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ እንደሚረዳቸውና እንደሚያጠነክራቸው የሰጠው ፍቅራዊ ተስፋ ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በራሴ ላይ ሲፈጸም ተመልክቻለሁ። በእርሱ ላይ ጥርጣሬ ካላደረብንና ለሚያደርግልን ነገር አድናቆት ማሳየታችንን ካላቋረጥን የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላልናል። የይሖዋ እጅ እየሠራ እንዳለ ሳውቅ እምነቴ ተጠናክሯል። እኛ ልንገምተው ከምንችለው በላይ እንዴት በረከቱን እንደሚያፈስም ተመልክቻለሁ። (ሚልክያስ 3:10) እውነትም አምላክ ሊዋሽ አይችልም!
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሜሪ በ1933
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሜሪና አርተር በኋለኞቹ ዓመታት