የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 5/15 ገጽ 15-20
  • ወጣቶች፣ የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወጣቶች፣ የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አጋንንቶችና ትምህርቶቻቸው
  • የአጋንንትን ትምህርት ማስፋፋት
  • ራሳችሁን መርምሩ
  • የአጋንንትን ትምህርቶች ተከላከሉ
  • ከመለኮታዊው ትምህርት ተጠቀሙ
  • ትክክለኛውን ምርጫ አድርጉ
  • መለኮታዊ ትምህርትና የአጋንንት ትምህርት የሚያደርጉት ውጊያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ኢየሱስ ከአጋንንት የበለጠ ኃይል አለው
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • መላእክትንና አጋንንትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • አጋንንት እነማን ናቸው?
    ንቁ!—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 5/15 ገጽ 15-20

ወጣቶች፣ የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው?

“አንዳንዶች . . . የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 4:1

1. (ሀ) ወጣቶች ምን ምርጫ አላቸው? (ለ) ይሖዋ የሚያስተምረው እንዴት ነው?

እዚህ ላይ ለወጣቶች የቀረበው ጥያቄ የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው? የሚል ነው። ይህም እናንት ወጣቶች ምርጫ እንዳላችሁ ያሳያል። ምርጫው መለኮታዊውን ትምህርት ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግና የአጋንንትን ትምህርቶች በመከተል መካከል ነው። ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስና በምድር ላይ እንደ ወኪሎቹ አድርጎ በሚጠቀምባቸው ሰዎች አገልግሎት አማካኝነት ያስተምራል። (ኢሳይያስ 54:13፤ ሥራ 8:26–39፤ ማቴዎስ 24:45–47) ይሁን እንጂ አጋንንትም ያስተምራሉ መባሉ ያስገርማችኋልን?

2. በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከአጋንንት ትምህርቶች ራስን መጠበቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ “በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) የምንኖረው በተለይ ሰይጣንንና አጋንንቱ በኃይል እየተንቀሳቀሱ ባሉባቸው ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ ስለሆነ የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለምን እንዳቀረብንላችሁ ለመረዳት ቻላችሁን? (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ራእይ 12:7–12) ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ለማሳሳት በሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ረገድ በጣም ብልሃተኞችና አታላዮች ስለሆኑ ይህን ጥያቄ በጥንቃቄ መመርመራችሁ የግድ አስፈላጊ ነው።—2 ቆሮንቶስ 11:14, 15

አጋንንቶችና ትምህርቶቻቸው

3. አጋንንት እነማን ናቸው? ዓላማቸውስ ምንድን ነው? ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩትስ እንዴት ነው?

3 አጋንንት በአንድ ወቅት የይሖዋ መላእክት ነበሩ፤ ይሁን እንጂ በፈጣሪያቸው ላይ ዓመጹና የሰይጣን ጭፍራ ሆኑ። (ማቴዎስ 12:24) ዓላማቸው ሰዎችን ለማበላሸትና አምላክን ከማገልገል ዘወር እንዲሉ ለማድረግ ነው። አጋንንት ይህን ዓላማቸውን ለማከናወን ሲሉ ይሖዋ የሚያወግዘውን ራስ ወዳድነትንና የብልግና አኗኗርን ለማስፋፋት በሰብአዊ አስተማሪዎች ይጠቀማሉ። (ከ2 ጴጥሮስ 2:1, 12–15 ጋር አወዳድር) ቀደም ሲል ታማኝ የነበሩት መላእክት እንዴት አጋንንት ሊሆኑ እንደቻሉ መመርመሩ ትምህርቶቻቸው ምን ዓይነት እንደሆኑና እነዚህ ትምህርቶች ምን ዓይነት አኗኗርን እንደሚያበረታቱ ለይታችሁ ለማወቅ ይረዳችኋል።

4. (ሀ) በኖኅ ዘመን እምቢተኛ መላእክት ወደ ምድር የመጡት ለምንድን ነው? (ለ) በውኃ ጥፋቱ ወቅት ክፉዎቹ መላእክትና ልጆቻቸው ምን ሆኑ?

4 በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት ውብ በሆኑት ሴቶች ልጆች ተማረኩ። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሰማይ የነበራቸውን ቦታ ተዉና ወደ ምድር መጡ። እነዚህ መላእክት ከሴቶች ጋር ባደረጉት የጾታ ግንኙነት ኔፍሊሞች ተብለው የሚጠሩ ዲቃላዎች ተወለዱ። መንፈሳዊ ፍጥረታት ከሰዎች ጋር አብረው መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ስላልሆነ ዓመፀኞቹ መላእክት ከሴቶች ጋር የፈጸሙት ድርጊት የሰዶም ወንዶች ከጊዜ በኋላ ከፈጸሙት ግብረ ሰዶም ጋር የሚተካከል መጥፎ ድርጊት ነው። (ዘፍጥረት 6:1–4፤ 19:4–11፤ ይሁዳ 6, 7) ምንም እንኳን መላእክቱ ያገቧቸው ሴቶች ከዲቃላ ልጆቻቸው ጋር በጎርፍ ቢደመሰሱም ክፉዎቹ መላእክት ግን ሥጋዊ አካላቸውን ጥለው ወደ ሰማይ በመመለስ የሰይጣን ዲያብሎስ አጋንንታዊ ጭፍራ ሆነዋል።—2 ጴጥሮስ 2:4

5. አጋንንት ምን ዓይነት ፍጡሮች ናቸው? የአምላክን ሕጎች ለማፍረስ የሚሞክሩትስ እንዴት ነው?

5 ከዚህ ታሪካዊ መግለጫ በመነሣት አጋንንት በእርግጥ ምን ዓይነት ፍጥረታት እንደሆኑ አስተዋላችሁን? ስለ ፆታ ድርጊት የተጣመመ አስተሳሰብ ያላቸው እነዚህ አጋንንት ይህን በፆታ ስሜት ያበደ ዓለም ከእይታ ተሰውረው መዳፋቸው ውስጥ አስገብተውታል። ምንም እንኳን በድጋሚ ሰብአዊ አካል እንዳይለብሱ ቢከለከሉም በምድር ላይ ያሉ በእነርሱ ሊበላሹ የቻሉ ሰዎች በሚፈጽሙት መጥፎ የጾታ ድርጊት ይረካሉ። (ኤፌሶን 6:11, 12) አጋንንት ስለ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና የሚናገሩት የይሖዋ ሕጎች ሳያስፈልግ ጥብቅ እገዳዎች እንደሆኑ በማስመሰል እነዚህን ሕጎች ለማፍረስ ይጥራሉ። እነዚህ ክፉ መላእክት የሥነ ምግባር ብልግናን ምንም ስህተት የሌለበት እንዲያውም አስደሳች የኑሮ ክፍል ነው ብለው ይከራከራሉ።

የአጋንንትን ትምህርት ማስፋፋት

6. አጋንንት ትምህርታቸውን በረቀቀ ዘዴ ማስፋፋታቸው የማያስደንቀን ለምንድን ነው?

6 አጋንንቶች ትምህርቶቻቸውን በረቀቀ ዘዴ ማስፋፋታቸው ሊያስደንቀን አይገባም፤ ምክንያቱም መሪያቸው ሰይጣን ዲያብሎስ ሔዋንን ለማሳሳት የተጠቀመበት ዘዴ ይህ ነው። ተቆርቋሪ መስሎ በመቅረብ እንዳነጋገራት አስታውሱ። ሰይጣን “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” ሲል ጠየቀ። ከዚያም ሰይጣን ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ ብትበላ እንደምትጠቀም በመንገር በተንኮል የአምላክን ትምህርት ለማዳከም ሞክሮ ነበር። ዲያብሎስ ‘ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ ይከፈታሉ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ’ ሲል ተስፋ ሰጠ። (ዘፍጥረት 3:1–5) በዚህ መንገድ ሔዋን ተታለለች፤ አዎን፣ ሰይጣን አሳስቷት የአምላክን ትእዛዝ አፈረሰች።—2 ቆሮንቶስ 11:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14

7. የረቀቁ የአጋንንት ትምህርቶች የሚያስከትሉት ውጤት ምንድን ነው? ይህስ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል?

7 በቅርብ ጊዜያትም ብዙዎች ተታልለዋል። ቀደም ሲል የሥነ ምግባር ብልግናን ያወግዙ በነበሩ ብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ አጋንንት በጣም በረቀቀ ዘዴ የሥነ ምግባር ብልግናን ያስፋፋሉ። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንዲት የታወቀች የምክር አምድ አዘጋጅ ያልተጋቡ ሰዎች የሚያደርጉትን የጾታ ግንኙነት አስመልክቶ ለቀረበላት አንድ ደብዳቤ ስትመልስ እንዲህ ብላ ጽፋለች፦ “በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን አመለካከት እለውጣለሁ ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም ነበር፤ አሁን ግን ለመጋባት የተፈላለጉ ሰዎች በእርግጥ የሚጣጣሙ መሆናቸውን ለመሞከር ለጥቂት ጊዜያት ቅዳሜና እሁድ አብረው መውጣት ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ።” አክላም “ይህን የጻፍኩት እኔ ነኝ ብዬ ለማመን አልችልም!” ብላለች። ምንም እንኳን ዝሙት መፈጸምን የሚያበረታታ ሐሳብ ሰጥታ እንደነበረ ለማመን ቢያቅታትም ዝሙትን የሚደግፍ ምክር ሰጥታ ነበር። የአጋንንት ትምህርቶች አምላክ የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች በተመለከተ ያለንን አመለካከት እንዳይነኩብን መጠንቀቅ እንዳለብን ግልጽ ነው።—ሮሜ 1:26, 27፤ ኤፌሶን 5:5, 10–12

8. (ሀ) “ዓለም” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው? (ለ) ዓለምን የሚገዛው ማን ነው? የኢየሱስ ተከታዮችስ ዓለምን እንዴት መመልከት አለባቸው?

8 ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” መሆኑን በፍጹም መርሳት የለብንም። እንዲያውም ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም በሞላው በክፉው” ተይዟል ብሏል። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ “ዓለም” የሚለውን ቃል አልፎ አልፎ ጠቅላላ የሰው ዘርን ለማመልከት ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 26:13፤ ዮሐንስ 3:16፤ 12:46) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያለውን የተደራጀውን ሰብአዊ ኅብረተሰብ ለማመልከት “ዓለም” በሚለው ቃል ደጋግሞ ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ‘ተከታዮቹ የዓለም (አመጸኛ የሆነው ሰብአዊ ኅብረተሰብ) ክፍል እንዳልሆኑና’ ከዚህም የተነሣ ዓለም እንደሚጠላቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14–16) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በሰይጣን የሚገዛው ዓለም ወዳጆች ከመሆን መራቅ እንዳለብን አስጠንቅቆናል።—ያዕቆብ 4:4

9, 10. (ሀ) ተገቢ ያልሆነ የጾታ ፍላጎት የሚቀሰቅሱት ዓለማዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) የዓለም መዝናኛ ከሚያስተምረው ነገር በስተጀርባ ያለው ማን መሆኑን ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

9 ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ” ሲል አጥብቆ አሳስቦናል። በተጨማሪም እንዲህ አለ፦ “በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” (1 ዮሐንስ 2:15, 16) እስቲ ስለዚህ ጉዳይ አስቡ። ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ለምሳሌ እንደ ልቅ የጾታ ግንኙነት የመሳሰለውን መጥፎ ምኞት የሚቀሰቅስ ምን ነገር አለ? (1 ተሰሎንቄ 4:3–5) ለምሳሌ አብዛኛው የዓለም ሙዚቃ እንዴት ነው? በአመክሮ እንዲቆዩ የሚደረጉ እስረኞችን ሁኔታ የሚቆጣጠሩ አንዲት የካሊፎርኒያ የፖሊስ መኮንን እንዲህ ብለዋል፦ “በመሠረቱ ሙዚቃው ወላጆቻችሁን መስማት የለባችሁም፤ እንደፈለጋችሁ መኖር አለባችሁ የሚል ትምህርት ያስተምራል።” በዚህ ዓይነቱ ሙዚቃ አማካኝነት የሚቀርበው ትምህርት ምንጭ ማን እንደሆነ ታውቁታላችሁን?

10 ሰይጣን ለሔዋን ‘ብዙ ነገር ቀርቶብሻል። እንደፈለግሽ ኑሪ። ጥሩና መጥፎ ስለሆነው ነገር ራስሽ ወስኚ። አምላክን መስማት አያስፈልግሽም’ ሲል በተዘዋዋሪ እንደነገራት አስታውሱ። (ዘፍጥረት 3:1–5) አብዛኛው የዓለም ሙዚቃ የሚያስተላልፈው መልእክት ይህንኑ አይደለምን? ይሁን እንጂ አጋንንት የሚያስተምሩት በሙዚቃ ብቻ አይደለም። አጋንንት የንግድ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ፊልሞችንና ቪዲዮችን ጭምር ለማስተማር ይጠቀሙባቸዋል። እንዴት ቢባል የዓለም የመገናኛ ዘዴዎች የአምላክ የሥነ ምግባር ትምህርቶች ጨቋኞች እንዲመስሉ የሚያደርግ መዝናኛ በማቅረብ ነው። አጋንነውና ተፈላጊ እንደሆነ ነገር አስመስለው በማቅረብ ምንዝርን ይደግፋሉ።

11. ከሥነ ምግባር አንጻር ሲታይ ቴሌቪዥን ብዙውን ጊዜ የሚያስተምረው ምንድን ነው?

11 ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል፦ “በ1991 ሦስት የአሜሪካ የቴሌቪዥን ሥርጭት ኩባንያዎች ብዙ ሰው እቤቱ ተቀምጦ ቴሌቪዥን የሚያይበትን ሰዓት መርጠው ከ10,000 በላይ የሚሆኑ የጾታ ግንኙነቶችን አሳይተዋል። ኩባንያዎቹ በትዳር ተጓዳኞች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን ለሚያሳይ ለእያንዳንዱ ትዕይንት ከጋብቻ ውጭ የሚደረጉ 14 የጾታ ግንኙነት ትዕይንቶችን አሳይተዋል።” ቴሌቪዥን በአንድ ዓመት ውስጥ ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ባለው ብዙ የቴሌቪዥን ተመልካቾች በሚኖሩበት ጊዜ ከ9,000 በላይ የሚሆኑ ልቅ የጾታ ድርጊቶችን አሳይቷል። ታዲያ ቴሌቪዥን ምን እያስተማረ ነው ትላላችሁ? “ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት በሚቀርበው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የሚታየው የጾታ ግንኙነት፦ በ1979 የነበረው በ1989 ከነበረው ጋር ሲወዳደር” የሚለው ዘገባ ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት ባሪ ኤስ ሳፖልስኪ እንዲህ ሲሉ መልሰዋል፦ “አንድ ወጣት ሰዎች ሲዳሩ ወይም በግልጽ ከጾታ ጋር የተያያዙ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የሚያሳየውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለብዙ ዓመታት ከተመለከተ እነዚህ ለብዙ ዓመታት በአእምሮው ላይ የተቀረጹ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምስሎች የጾታ ግንኙነት አስደሳች እንደሆነ፣ እንዲያውም ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ያስተምረዋል።” የዓለም መዝናኛ ሕግ የለም፣ ምንዝር ተቀባይነት አለው፣ አምላክ በሚያወግዘው መንገድ መኖር መጥፎ ውጤት አያስከትልም እያለ ወጣቶችን እንደሚያስተምር ምንም አያጠያይቅም።—1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ኤፌሶን 5:3–5

12. የዓለም መዝናኛ በተለይ ለክርስቲያን ወጣቶች አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

12 የዓለም ሙዚቃዎች፣ ፊልሞች፣ ቪዲዮዎችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወጣቶችን እንደሚማርኩ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው። ብልሹ የሆኑትን የአጋንንት ትምህርቶች የሚደግፍ ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ። ይሁን እንጂ ይህ የሚያስደንቅ ነውን? እስቲ ስለ ነገሩ አስቡ። የሐሰት ሃይማኖትና ፖለቲካ የሰይጣን ዓለም ክፍል ከሆኑ፣ (ደግሞም ናቸው) ታዲያ ዓለም የሚያስፋፋው መዝናኛ ከአጋንንት ተጽዕኖ ነፃ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? በተለይ እናንተ ወጣቶች “በዙሪያችሁ ያለው ዓለም በራሱ መልክ እንዳይቀርጻችሁ ተጠንቀቁ።”—ሮሜ 12:2 ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ፤ በጄ ቢ ፊሊፕስ

ራሳችሁን መርምሩ

13. ምን ብለን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል?

13 የማንን ትምህርቶች እየተከተላችሁ እንዳላችሁ የሚወስነው የምትናገሩት ብቻ ሳይሆን የምታደርጉት ነገር ጭምር ነው። (ሮሜ 6:16) ስለዚህ ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘በዓለም የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫዎች አማካኝነት በማገኘው ትምህርት ዝንባሌዬና አኗኗሬ ከመጠን በላይ እየተነካ ነውን? የአጋንንት ትምህርት ወደ ሕይወቴ ውስጥ ሰርጎ እየገባ ነውን?’ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመገኘትና ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በመናገር የምታጠፉትን ጊዜና ጉልበት ቴሌቪዥን በማየት፣ ሙዚቃ በመስማት፣ በምትወዱት የስፖርት ዓይነት በመሳተፍ ወይም በመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ከምታጠፉት ጊዜና ጉልበት ጋር ለምን አታወዳድሩትም? ነገሩ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ፤ እንዲያውም ሕይወታችሁ ራሱ አደጋ ላይ ስለወደቀ ራሳችሁን በሐቀኝነት መርምሩ።—2 ቆሮንቶስ 13:5

14. መንፈሳዊ ጤንነታችንን የሚነካው ምንድን ነው? ምን ተገቢ የሆነ አስተሳሰብስ መያዝ አለብን?

14 የምትበሉት ሰብአዊ ምግብ አካላዊ ጤንነታችሁን እንደሚነካ በሚገባ ታውቃላችሁ። በተመሳሳይም አእምሮአችሁንና ልባችሁን በምትመግቡት ነገር መንፈሳዊ ጤንነታችሁ ይነካል። (1 ጴጥሮስ 2:1, 2) እውነተኛ ፍላጎታችሁን በተመለከተ ራሳችሁን ማታለል ትችሉ ይሆናል፤ ዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ግን ማታለል አትችሉም። (ዮሐንስ 5:30) ስለዚህ ‘ኢየሱስ ምድር ላይ ቢሆን ኖሮ ወደ ክፍላችን ድንገት ቢገባና የምንሰማውን ሙዚቃ ቢሰማ ወይም የምናየውን ነገር ቢያይ እፍረት ይውጠን ነበርን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። አስደንጋጩ ሐቅ ግን ኢየሱስ አሁንም ድርጊቶቻችንን ሁሉ የሚያይና የሚያውቅ መሆኑ ነው።—ራእይ 3:15

የአጋንንትን ትምህርቶች ተከላከሉ

15. ክርስቲያኖች የአጋንንትን ትምህርቶች ለመከላከል በኃይል መታገል ያለባቸው ለምንድን ነው?

15 አጋንንት የእነሱን ትምህርቶች እንዲከተሉ ለማድረግ በወጣቶች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በጣም ብዙ ነው። እነዚህ ክፉ መናፍስት ወዲያው ደስታና እርካታ የሚገኝበት ሕይወት የሚሰጡ ይመስላሉ። ጥንት የነበረው ሙሴ አምላክን ለማስደሰት ሲል በፈርዖን ቤት ውስጥ በጣም የታወቀ ሰው በመሆን ‘በኃጢአት ሊያገኝ ይችል የነበረውን ጊዜያዊ ደስታ’ አልፈልግም ብሏል። (ዕብራውያን 11:24–27) አጋንንት የሚያቀርቡትን ነገር አልፈልግም ማለት ቀላል አይደለም፤ ስለዚህ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለማድረግ በኃይል መታገል አለባችሁ። በተለይም ደግሞ ኃጢአትን ስለወረስንና ልባችን ብዙውን ጊዜ መጥፎ የሆነውን ለማድረግ ስለሚፈልግ እንዲህ ማድረጉ ቀላል አይሆንም። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 5:12) ከኃጢአት ዝንባሌ የተነሣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን በራሱ ላይ ጨከን ማለትና የሥጋ ምኞቱ እንዳያሸንፈው መጠንቀቅ ነበረበት።—1 ቆሮንቶስ 9:27፤ ሮሜ 7:21–23

16. ወጣቶች ብልግና እንዲፈጽሙ የሚያደርጓቸውን ግፊቶች መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

16 ምንም እንኳን ‘ክፉውን ለማድረግ ብዙዎችን ለመከተል’ ልትፈተን ብትችልም የእነሱን መጥፎ መንገድ እንድትከተል ከጓደኞችህ የሚመጣብህን ግፊት እንድትቋቋም አምላክ ሊረዳህ ይችላል። (ዘጸአት 23:2፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) ይሁን እንጂ የአምላክን መመሪያዎች መስማትና ቃሎቹን በልብህ ሸሽገህ መያዝ አለብህ። (መዝሙር 119:9, 11) ወጣቶች ራሳቸውን ሲያገሉ በውስጣቸው የጾታ ፍላጎት ሊቀሰቀስና በዚህ ሳቢያ የአምላክን ሕጎች ወደማፍረስ ሊደርሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋችኋል። “እኔና የወንድ ጓደኛዬ ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ ሰውነቴ አንድ ነገር ለማድረግ ይፈልጋል፤ አእምሮዬ ደግሞ ሌላ ነገር እንዳደርግ ይነግረኛል” ስትል አንዲት ወጣት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ስለዚህ አቅማችሁን ማወቅና ልባችሁ ደግሞ ተንኮለኛ መሆኑን መገንዘብ አለባችሁ። (ኤርምያስ 17:9) ራሳችሁን አታግልሉ። (ምሳሌ 18:1) የፍቅር መግለጫ በሆኑ አነጋገሮች ረገድ ገደብ አብጁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ከሚወዱና ለሕጎቹ ጥልቅ አክብሮት ካላቸው ጋር የጠበቀ ቅርርብ ይኑራችሁ።—መዝሙር 119:63፤ ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33

17. ክርስቲያን ወጣቶች የአጋንንትን ትምህርቶች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ለማግኘት የሚረዳቸው ምንድን ነው?

17 ለእናንተ መንፈሳዊ ጥንካሬ ተብለው የተዘጋጁትን የክርስቲያን ጽሑፎች በጥንቃቄ ማጥናት ይረዳችኋል። ለምሳሌ ያህል ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተባለው መጽሐፍ እንዲሁም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ “ትክክል የሆነውን ለማድረግ ያለብን ትግል” የሚለው ምዕራፍ አለ። የሚሰጧችሁ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ወደ አእምሮአችሁና ልባችሁ ዘልቀው እንዲገቡ አድርጉ። ይህን ማድረጋችሁ በጣም ያጠነክራችኋል። በዚህ በአጋንንት ቁጥጥር ሥር ባለ ዓለም ውስጥ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ በፍጹም መዘንጋት የለባችሁም። እንግዲያው ከባድ ውጊያ አድርጉ። (ሉቃስ 13:24) መንፈሳዊ ኃይላችሁን በደንብ ገንቡት። ብዙሃኑን የሚከተሉትን ደካማና ፈሪ ሰዎች አትምሰሉ።

ከመለኮታዊው ትምህርት ተጠቀሙ

18. መለኮታዊውን ትምህርት መከተል የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

18 በተጨማሪም የይሖዋን ትምህርት በመከተላችሁ ጠቃሚ የሆነ ምንም ነገር እንደማይቀርባችሁ አስታውሱ። ይሖዋ በእርግጥ ይወዳችኋል፤ ለዚህም ነው ‘የሚረባችሁን ነገር የሚያስተምራችሁ።’ (ኢሳይያስ 48:17) ስለዚህ የይሖዋን ትምህርት በመከተል የኅሊና ወቀሳ ከሚያስከትለው ሥቃይ፣ ከውርደት፣ ካልተፈለገ እርግዝና፣ በጾታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ወይም ከሌሎች አደጋዎች ራሳችሁን ጠብቁ። ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ ሆነው አይቀጥሉም በማለት ሰይጣን ላቀረበው ክስ አገልጋዮቹ መልስ ለመስጠት ሲያስችሉት ይሖዋ በጣም ይደሰታል። (ኢዮብ 1:6–12) ለእሱ ታማኝ በመሆን የይሖዋን ልብ ካስደሰታችሁ በዚህ ዓለም ላይ የጥላቻ ፍርዱን ሲያመጣና ሕጎቹን ይንቁ የነበሩት ሁሉ ተጠራርገው ሲጠፉ እናንተ ከጥፋቱ ትተርፋላችሁ።—ምሳሌ 27:11፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 1 ዮሐንስ 2:17

19. ከይሖዋ የሚገኘው ትምህርት የሚሰጣቸውን ጥቅሞች ከሚያደንቁ ሰዎች ጋር መቀራረብ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው?

19 ይሖዋ ላደረገላቸው ነገር አድናቆት ካላቸው ሰዎች ጋር በጣም ከተቀራረባችሁ ከተሞክሮአቸው ልትማሩ ትችላለሁ። ቀደም ሲል የዕፅ ሱሰኛ የነበረችና የሥነ ምግባር ብልግና ትፈጽም የነበረች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን ባልሰማ ኖሮ ሞቼ ነበር። ላገባው አስቤው የነበረው ሰው በኤድስ ሞተ። የቀድሞ ዓለማዊ የቅርብ ጓደኞቼ በሙሉ በኤድስ ሞተዋል ወይም በቅርቡ ይሞታሉ። ብዙ ጊዜ መንገድ ላይ አያቸዋለሁ፤ ሕዝቦቹን ለሚመሩትና በሥራ ላይ ካዋልናቸው ቅዱስ ሆነን እንድንቀጥል ለሚያደርጉን ሕጎቹ ይሖዋን ዘወትር አመሰግነዋለሁ። በሕይወቴ ውስጥ በፍጹም እንደዚህ ደስተኛ ሆኜና የተረጋጋ ሕይወት ኖሮኝ አያውቅም።” እውነት ነው፣ የይሖዋን ትምህርት መከተል ዘወትር ይጠቅመናል!

ትክክለኛውን ምርጫ አድርጉ

20, 21. (ሀ) ወጣቶች ምን ሁለት ምርጫዎች ቀርበውላቸዋል? (ለ) መለኮታዊውን ትምህርት መከተል ምን ዘላቂ ጥቅም ያስገኛል?

20 እናንት ወጣቶች፣ ይሖዋን በማገልገል ትክክለኛውን ምርጫ እንድታደርጉ አጥብቀን እናሳስባችኋለን። ከዚያም ይህን ውሳኔያችሁን የሙጥኝ ብላችሁ ለመያዝ የቆረጣችሁ ሁኑ። (ኢያሱ 24:15) የቀረበላችሁ ምርጫ ሁለት ብቻ ነው። ኢየሱስ አንድ ሰፊና ትልቅ መንገድ እንዳለ ተናግሯል። ይህም አንድ ሰው ደስ ያለውን የሚያደርግበት ቀላል መንገድ ነው። በመጨረሻው ግን ይህ መንገድ ወደ ሞትና ወደ ጥፋት ያደርሳል። ሌላው መንገድ ደግሞ ጠባብ ነው። በዚህ ሥነ ምግባር በጎደለውና በአጋንንት ቁጥጥር ሥር ባለ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ አስቸጋሪ የሆነ መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መንገድ ተጓዦቹን በመጨረሻው ግሩም ወደሆነው የአምላክ አዲስ ዓለም ይወስዳቸዋል። (ማቴዎስ 7:13, 14) የትኛውን መንገድ ትመርጣላችሁ? የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው?

21 ይሖዋ ምርጫውን ለእናንተው ትቶታል። ይሖዋ እሱን እንድታገለግሉት ሊያስገድዳችሁ አይፈልግም። የአምላክ ነቢይ የነበረው ሙሴ ‘በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን አስቀምጫለሁ’ ካለ በኋላ “ሕይወትን ምረጥ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። ይህን ምርጫ የምታደርገው ‘አምላክህን ይሖዋን በመውደድ፣ እሱን በመጠባበቅና ቃሉን በመስማት’ ነው። (ዘዳግም 29:2፤ 30:19, 20) አዋቂ ሆናችሁ መለኮታዊውን ትምህርት ለመከተል የምትመርጡና በክብራማው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ መጨረሻ የሌለውን ሕይወት አግኝታችሁ ለመደሰት የምትችሉ ያድርጋችሁ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ አጋንንት እነማን ናቸው? የሚያስተምሩትስ ምንድን ነው?

◻ በዛሬው ጊዜ አጋንንት ትምህርታቸውን የሚያስፋፉት እንዴት ነው?

◻ የአጋንንትን ትምህርት መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

◻ የይሖዋን ትምህርት ከመከተል የሚገኙት ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከውኃ ጥፋት በፊት ዓመፀኞቹ መላእክትና ልጆቻቸው ዓመፅንና ክፋትን አስፋፍተዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጣም የምትወደውን ሙዚቃ ኢየሱስ ቢሰማው ታፍር ነበርን?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ