የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 5/15 ገጽ 21-23
  • መታገስ ትችላለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መታገስ ትችላለህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትዕግሥት ያጣው ዘመናዊው ዓለማችን
  • ይሖዋ ትዕግሥትህን ሊያጠናክርልህ ይችላል
  • ስለ ራስህና ስለሌሎች ሊኖርህ የሚገባው ተገቢ አመለካከት
  • ትዕግሥት ከፍተኛ ዋጋ አለው።
  • ትዕግሥት ማሳየታችሁን ቀጥሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ይሖዋና ኢየሱስ ካሳዩት ትዕግሥት ትምህርት ማግኘት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • የይሖዋን ትዕግሥት ኮርጁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ትዕግሥት—በተስፋ መጽናት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 5/15 ገጽ 21-23

መታገስ ትችላለህን?

ይሖዋ ለአብርም እንዲህ አለው፦ “ከአገርህ . . . ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ።” (ዘፍጥረት 12:1, 2) በዚያን ጊዜ አብራም የ75 ዓመት ሰው ነበር። አብርሃም ይሖዋ ያለውን ታዘዘ፣ በቀረው የሕይወቱ ዘመንም ትዕግሥት አሳይቷል። ይሖዋን ጠብቋል።

በመጨረሻም አምላክ ትዕግሥተኛ ለነበረው አብርሃም (አብራም) የሚከተለውን ቃል ገብቶለታል፦ “በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁ አበዛሃለሁ።” ሐዋርያው ጳውሎስም በመጨመር እንዲህ ብሏል፦ “እንዲሁም እርሱ [አብርሃም] ከታገሠ በኋላ ተስፋውን አገኘ።”—ዕብራውያን 6:13–15.

ትዕግሥት ምንድን ነው? የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት “ፔሸንስ” የሚለውን ቃል “አንድን ነገር በተረጋጋ መንፈስ የመጠበቅ ችሎታ” ወይም “የሚያስጨንቅንና የሚያበሳጭን ሁኔታ መቻል” ብለው ይተረጉሙታል። ስለዚህ አንድ ሰው ወይም አንድ ነገር መጠበቅ ሲኖርብህ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ሲገጥምህ አለበለዚያም በውጥረት ውስጥ ስትሆን ትዕግሥትህ ይፈተናል። እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመው ትዕግስተኛ ሰው እንደተረጋጋ ይቆያል ትዕግሥት የሌለው ሰው ግን ይቸኩላል፣ ይረበሻል።

ትዕግሥት ያጣው ዘመናዊው ዓለማችን

በተለይ በብዙ የከተማ አካባቢዎች ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ለትዕግሥት ሳይሆን ለፍጥነት ነው። በተጨናነቁ ከተሞች ለሚኖሩ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ቀኑ የሚጀምረው የጠዋቱ የሰዓት ደወል ሲሰማ ነው። ያኔ ሩጫው ይጀምራል። አንድ ቦታ ለመድረስ፣ አንድ ሰው ለማግኘት፣ አንድ ነገር ለማከናወን ጥድፊያው ይጀምራል። ታዲያ ብዙዎቹ ውጥረት ውስጥ ቢገቡና ትዕግሥት ቢያጡ ያስገርማልን?

ሌሎች ሰዎች በሚያሳዩት ድክመት ትበሳጫለህን? “ሰዓት የማያከብር ሰው አልወድም” ይላል አልበርት። አብዛኞቹ ሰዎች ሰዓት የማያከብርን ሰው መጠበቅ በተለይም ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ማለቅ ያለበት ነገር ካለ ሁኔታው አስጨናቂ እንደሆነ ይስማማሉ። የ18ኛው መቶ ዘመን የእንግሊዝ የፖለቲካ ሰው የነበረውን የኒውካስል መስፍን አስመልክቶ እንዲህ ተብሏል፦ ‘ገና በጠዋቱ ግማሽ ሰዓት ይባክንበታል። በቀሪው የቀኑ ክፍል ያንን ሰዓት ለማካካስ ይጥራል ግን አይሳካለትም።’ በየዕለቱ ከዚህ ዓይነት ሰው ጋር መሥራት ቢኖርብህ በትዕግሥት ትቀጥል ነበርን?

መኪና ስትነዳ መጠበቅ ተስኖህ ቶሎ ትናደዳለህን? ወይም መኪናዋን በኃይል ለማብረር ትፈተናለህን? በእንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ትዕግሥት ማጣት ብዙውን ጊዜ ትልቅ አደጋ ያስከትላል። በ1989 በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን ተብላ ትጠራ በነበረችው አገር በአውራ ጎዳና ላይ ከ400, 000 በላይ የሚሆኑ አደጋዎች ደርሰው የአካል ጉዳትና ሞት አስከትለዋል። ከእነዚህም መካከል ከሦስቱ አንዱ አደጋ የደረሰው ከፊት ያለውን መኪና በከፍተኛ ፍጥነት በመከተል ወይም በጣም ተጠግቶ በመንዳት ነው። እንግዲያው 137, 000 በሚያክሉ ሰዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ወይም ሞት ትዕግሥት ማጣት የተወሰነ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ነው። ትዕግሥት ማጣት የሚያስከትለው ኪሣራ እንዴት ከፍተኛ ነው!

“አንድ ሰው አሁንም አሁንም ጣልቃ እየገባ ሲያቋርጠኝ ወይም ጉራውን ሲነዛ መታገሥ አልችልም” በማለት አን ታማርራለች። ካርል ሄርማን ደግሞ “አረጋውያንን የማያከብሩ ልጆች” ትዕግሥቱን እንደሚፈትኑት በመናገር የግል ችግሩን አምኗል።

እነዚህና ሌሎች ነገሮች ትዕግሥትህን ሊያሳጡህ ይችሉ ይሆናል። ታዲያ ትዕግሥትን በይበልጥ ልታዳብር የምትችለው እንዴት ነው?

ይሖዋ ትዕግሥትህን ሊያጠናክርልህ ይችላል

አንዳንድ ሰዎች ትዕግሥት የቆራጥነት ማነስ ወይም የድክመት ምልክት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በይሖዋ ፊት ግን የጥንካሬያችን ምልክት ነው። እርሱ ራሱ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ [ሲል] . . . ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) እንግዲያው ችግርን ችሎ የመታገሥ ችሎታህን ይበልጥ ለማጠናከር ከይሖዋ ጋር ተጣበቅ፤ በሙሉ ልብህ በእርሱ ታመን። የታጋሽነትን ባህርይ ለማዳበር ብቸኛውና ከሁሉም የተሻለው መንገድ ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ማጠናከር ነው።

ከዚህም በላይ ይሖዋ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ማወቅም በጣም አስፈላጊ ነው። አብርሃም “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ [የአምላክን መንግሥት] ይጠብቅ ነበር።” (ዕብራውያን 11:10) እኛም በተመሳሳይ መለኮታዊ ተስፋዎች በዓይነ ሕሊናችን ጥርት ብለው እንዲታዩን ማድረጋቸንና ይሖዋን በደስታ መጠበቃችን ይጠቅመናል። ይህን ካደረግህ ትዕግሥት ዳተኝነትን ከማመልከት ይልቅ ሰዎች ወደ እውነተኛ አምልኮ እንዲመጡ የሚያስችል መሆኑን ታስተውላለህ። እንግዲያው ‘የጌታችን ትዕግሥት መዳንህ እንደሆነ አድርገህ ቁጠረው።’—2 ጴጥሮስ 3:15

የራስህ የግል ሁኔታዎች መሸከም እስከማትችለው ድረስ ትዕግሥትህን ቢፈትኑብህስ? የማያምኑ ሰዎች ጭንቀትና ውጥረት ይፈጥሩብሃልን? ማለቂያ የሌለው ለሚመስል ረጅም ጊዜ ታመህ ቆይተሃልን? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካለብህ ሐዋርያው ያዕቆብ የተናገረውን ልብ በለው። ነቢያት ያሳዩትን የትዕግሥት ምሳሌነት ከጠቀሰ በኋላ በከባድ ውጥረት ጊዜ መንፈስን ማረጋጋት የሚቻልበትን ምስጢር ገለጠ። ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፦ “ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ።” ያዕቆብ 5:10, 13

አምላክ ትዕግሥትህን እንዲያጠናክርልህና በፈተና ወቅት መንፈስህን ለመቆጣጠር እንዲረዳህ በጸሎት አጥብቀህ ጠይቀው። በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ በጸሎት ቅረብ፤ እርሱም መረጋጋትህን ሊያናጉብህ የሚችሉትን ነገሮች ወይም የሌሎች ሰዎች ልማዶች ለይተህ እንድታውቃቸው ይረድሃል። ፈታኝ ሊሆኑብህ ስለሚችሉት ሁኔታዎች በቅድሚያ መጸለይህ ተረጋግተህ ዝም እንድትል ሊረዳህ ይችላል።

ስለ ራስህና ስለሌሎች ሊኖርህ የሚገባው ተገቢ አመለካከት

የአእምሮህን መረጋጋት ለመጠበቅ ራስህንና ሌሎችን በተገቢው መንገድ መመልከት ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለዚህ ይረዳል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው ኃጢአት እንደወረሰና የሞኝነት ተግባር ሊፈጽም እንደሚችል ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ፍቅርን እንድታዳብር ይረድሃል። ለሌሎች ትዕግሥትን ለማሳየት ደግሞ ይህ ባሕርይ በጣም አስፈላጊ ነው።—ዮሐንስ 13:34, 35፤ ሮሜ 5:12፤ ፊልጵስዮስ 1:9

ፍቅርና ሌሎችን ይቅር ለማለት ያለህ ዝግጁነት በምትበሳጭበት ጊዜ እንድትረጋጋ ይረዱሃል። አንድ ሰው መንፈስህን የሚያበሳጭ ባህርይ ካለው ያልወደድኸው ሰውዬውን ሳይሆን ልማዶቹን እንደሆነ ፍቅር ያስታውስሃል። የአንተ የራስህ ድክመቶች የአምላክን ትዕግሥት ምን ያህል እንደሚፈታተንና ሌሎችን እንደሚያበሳጭ አስብ።

ስለራስህ ያለህ ትክክለኛ አመለካከት በትዕግሥት እንድትጠብቅ ያደርግሃል። ለምሳሌ ያህል በይሖዋ አገልግሎት አንድ መብት ላይ ለመድረስ ስትጠባበቅ ቆይተህ የጠበቅኸው ሳይፈጸም ቀርቶ አዝነህ ታውቃለህን? ትዕግሥትህ እየተሟጠጠ በመሄድ ላይ እንዳለ ይሰማሃልን? እንዲህ ከሆነ እንግዲያው ብዙውን ጊዜ ትዕግሥት ማጣት የሚመጣው ከኩራት እንደሆነ አስታውስ። ሰሎሞን “ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል” ብሏል። (መክብብ 7:8) አዎን፣ ትዕግሥትን እንዳናፈራ ትልቁ ማነቆ ኩራት ነው። በዝምታ መጠበቅ ትሑት ለሆነ ሰው ቀላል ነው ቢባል ትክክል አይደለምን? ስለዚህ ትሕትናን አዳብር፤ ይህን ካደረግህ አንዳንድ የዘገዩ ነገሮችን አእምሮህ ሳይረበሽ ለመጠበቅ ትችላለህ።—ምሳሌ 15:33

ትዕግሥት ከፍተኛ ዋጋ አለው።

አብርሃም በተለይ የሚታወቀው በእምነቱ ነው። (ሮሜ 4:11) ይሁንና እምነቱን ደልዳላ ያደረገለት ትዕግሥቱ ነበር። ይሖዋን በትዕግሥት በመጠበቁ ምን ዋጋ አገኘ?

አብርሃም በይሖዋ ዘንድ ከበፊቱ የበለጠ አመኔታን አትርፏል። በዚህ መንገድ የአብርሃም ስም ከፍ ብሏል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝብ ሆነዋል። የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሱ ዘር አማካኝነት ራሳቸውን መባረክ ይችላሉ። አብርሃም የአምላክ አፈ ቀላጤ ሆኖ አገልግሏል፤ እንዲያውም በጥላነት ፈጣሪን የሚያመለክት ሆኖ አገልግሏል። አብርሃም ላሳየው እምነትና ትዕግሥት ከዚህ የሚበልጥ ዋጋ ሊከፈለው ይችላልን?

ፈተና ሲደርስባቸው በትዕግሥት ለሚጸኑ ክርስቲያኖች “ይሖዋ ርኅራኄና ፍቅር አለው።” (ያዕቆብ 5:10, 11 አዓት) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የእርሱን ፈቃድ በማድረጋቸው ንጹህ ኅሊና ይኖራቸዋል። አንተም ብትሆን ይሖዋን የምትጠባበቅ ከሆነና ፈተናዎችን በትዕግሥት የምትቋቋም ከሆነ መከራን ችለህ መታገሥ ከይሖዋ ዘንድ ተቀባይነትና በረከትን ያስገኝልሃል።

ትዕግሥት በሁሉም የኑሮ ዘርፎች የአምላክን ሕዝቦች በሚገባ ይጠቅማቸዋል። ክርስቲያንና አግነስ የሚባሉ ሁለት የአምላክ አገልጋዮች ለመጋባት ሲወስኑ ይህን እውነት ሆኖ አግኝተውታል። የእርሱን ወላጆች ስሜት ለማክበር ሲሉ መተጫጨቱን ለማዘግየት ወሰኑ፤ ምክንያቱም ወላጆቹ አንገስን በይበልጥ ለማወቅ ጊዜ አስፈልጓቸው ነበር። ይህ እርምጃ ምን ውጤት ነበረው?

“ያሳየነው ትዕግሥት ለወላጆቼ ምን ያህል ትልቅ ነገር እንደነበር ያስተዋልነው በኋላ ነበር” ሲል ክርስቲያን ተናግሯል። “በትዕግሥት መጠበቃችን በእኔና በሚስቴ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ አላደረገም። ከዚያ ይልቅ ከወላጆቼ ጋር ለሚኖረን ግንኙነት እንደ መሠረት ድንጋይ ሆኗል።” አዎን፣ ትዕግሥት ጥሩ አድርጎ ይክሳል።

ትዕግሥት ሰላምንም ያስገኛል። ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ እያንዳንዱን ጥቃቅን ስህተት እያነሣህ ጭቅጭቅ የማትፈጥር ከሆነ ደስ ይላቸዋል። ሌሎች ስህተት ሲሠሩ ረጋ ማለትህና ችግራቸውን መረዳትህ በእፍረት እንዳይዋጡ ይረዳል። አንድ የቻይናውያን ምሳሌ፦ “ጊዜያዊ ቁጣን በትዕግሥት ማሳለፍ ከመቶ ቀናት ሥቃይ ያድንሃል” ይላል።

ትዕግሥት ሌሎች መልካም ጠባዮችህ ለዘለቄታው እንዲጠበቁ በመርዳት ሁለንተናዊ ባህርይህን ያጠናክረዋል። እምነትህን ያጠነክርልሃል፣ ሰላምህ ዘላቂ ይሆንልሃል፣ ፍቅርህም አይናወጥም። ትዕግሥተኛ መሆንህ ደግነትን፣ ጥሩነትንና የዋህነትን ስታሳይ ደስተኛ እንድትሆን ይረዳሃል። ትዕግሥት ለቻይነትና ራስን ለመግዛት የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ይገነባልሃል።

እንግዲያው ይሖዋ ቃል የገባልን ተስፋዎች እስኪፈጸሙ ድረስ በትዕግሥት ተጠባበቅ። ይሖዋ ወደፊት አስደናቂ ሕይወት እንደሚሰጥህ ቃል ገብቶልሃል። ልክ እንደ አብርሃም ‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የምትወርስ’ ያድርግህ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከይሖዋ ጋር ያለህ የተቀራረበ ዝምድና ልክ እንደ አብርሃም ትዕግሥትን ለማሳየት ይረዳሃል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ