ትክክለኛውን ሃይማኖት አግኝተኸዋልን?
“ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው።”—ያዕቆብ 1:27
1, 2. (ሀ) እንደ ብዙዎቹ ሰዎች አስተሳሰብ ሃይማኖታቸው ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን የሚወስነው ምንድን ነው? (ለ) የሃይማኖትን ትክክለኛነት በምንመዝንበት ጊዜ በጥሞና ልናስብበት የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
የምንኖረው ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለሃይማኖት ምንም ያህል ቦታ በማይሰጡበት ዘመን ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ይገኙ ይሆናል፤ በፕሮግራሞቹ ላይ አዘውትረው የሚገኙት ግን ጥቂቶች ናቸው። አብዛኞቹ ሰዎች የእኔ ሃይማኖት ትክክል ነው፤ ሌሎቹ ሃይማኖቶች በሙሉ ግን ትክክል አይደሉም የሚል እምነት የላቸውም። የእኔ ሃይማኖት ለኔ ትክክል ነው ይሉ ይሆናል።
2 ታዲያ እንዲህ ከሆነ ‘ትክክለኛውን ሃይማኖት አግኝተኸዋልን?’ የሚለው ጥያቄ ‘አንተ የምትወደውን ሃይማኖት አግኝተኸዋል?’ እንደማለት ሊሆን ይችላልን? ሃይማኖቱን ለመውደድ መሠረት የሚሆንህ ምንድን ነው? ቤተሰብህ? ጓደኞችህ? ወይስ የራስህ ስሜት? አምላክ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ምን ያህል በጥሞና አስበህበታል?
የአምላክን አመለካከት እንዴት ልናውቅ እንችላለን?
3. (ሀ) አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ከተፈለገ የግድ ምን ማግኘት አለብን? (ለ) እኛ በግላችን መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ መሆኑን የምናምነው ለምን እንደሆነ ለማወቅ ምን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል?
3 አምላክ ራሱ ስለጉዳዩ ምን ብሎ እንደሚያስብ ለማወቅ ከራሱ የተገኘ አንድ ዓይነት መግለጫ የግድ መኖር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ አነሣሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚናገር በረጅም ዕድሜው ተወዳዳሪ የሌለው ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ ተለይቶ አምላክ ለሁሉም የሰው ልጆች ሊያስተላልፈው የፈለገውን መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው ተብሎ በትክክል ሊነገርለት ይችላልን? ይህን ጥያቄ እንዴት ብለህ ትመልሳለህ? ለምንስ? ወላጆችህ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ስላላቸው ነውን? ወይስ የጓደኞችህ አቋም ይህ ስለሆነ ነው? ማስረጃዎቹን ራስህ መርምረሃቸዋልን? የሚከተሉትን አራት ማስረጃዎች ተመርኩዘህ ለምን አሁን አትመረምረውም?
4. መጽሐፍ ቅዱስ በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ ከአምላክ የመጣው መጽሐፍ ሌላ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንደሆነ የሚያመለክተው እንዴት ነው?
4 በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ፦ ለጠቅላላው ሰብዓዊ ቤተሰብ መነገር ያለበት ከአምላክ የመጣ መልእክት ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው ይችላልን? ቀጥሎ ያሉትን ሁኔታዎች ተመልከት፦ በአሁኑ ጊዜ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከፊሉ ከ2,000 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ይገኛል። የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በገለጸው መሠረት ከአሥር ዓመት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች በመታተሙ ወደ 98 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን አግኝቶ ሊያነበው ይችል ነበር። ጊነስ ቡክ ኦቭ ወርልድ ሬከርድስ እንደሚያመለክተው መጽሐፍ ቅዱስ እስካሁን ድረስ “ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በዓለም ዙሪያ በብዛት የተሠራጨ መጽሐፍ ነው።” ለሁሉም ዘር፣ ብሔርና ጎሣ ከአምላክ የመጣ መልእክት እንዲህ መሆን አለበት ብለን የምንጠብቀው ነገር ነው። (ከራእይ 14:6 ጋር አወዳድር።) በዓለም ዙሪያ ይህን ክብረ ወሰን የያዘ ሌላ መጽሐፍ የለም።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ትክክለኛነት ትርጉም ያለው የሆነው ለምንድን ነው?
5 ታሪካዊነቱ፦ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች በደንብ ብንመረምራቸው ቅዱሳን ናቸው ከሚባሉት ከሌሎቹ መጻሕፍት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገውን ሌላ ነገር እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ በማስረጃ ሊረጋገጡ የማይችሉ አፈ ታሪኮች ጥርቅም ሳይሆን እውነተኛ ታሪኮችን የያዘ መጽሐፍ ነው። በሕግ ችሎት ፊት የሚፈለግ ማስረጃ ምን እንደሆነ የመመርመር ልምድ የነበራቸው ኧርዊን ሊንተን የተባሉ ጠበቃ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ልብ ወለድ ጽሑፎች፣ አፈ ታሪኮችና የሐሰት የምሥክርነት ቃሎች የሚተርኳቸውን ነገሮች ሩቅ ቦታና ባልታወቀ ጊዜ የተፈጸሙ አድርገው ሲያቀርቧቸው . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን የሚጽፉት ታሪክ ስለተፈጸመበት ዘመንና ቦታ እጅግ ትክክለኛ የሆነ መግለጫ ይሰጣሉ።” (ለምሳሌ 1 ነገሥት 14:25ን፣ ኢሳይያስ 36:1ንና ሉቃስ 3:1, 2ን ተመልከት።) ከሐቁ ለመሸሽ ሳይሆን እውነትን ለማግኘት ብለው ፊታቸውን ወደ ሃይማኖት የሚያዞሩ ሰዎች ለዚህ ሁኔታ ከፍተኛ ክብደት ይሰ ጡታል።
6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች እንዲቋቋም ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው የሚገጥሙትን አስጨናቂ የሕይወት እውነታዎች ለመቋቋም በምን ሦስት መንገዶች ሊረዳው ይችላል?
6 ተግባራዊነቱ፦ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር የሚመረምሩ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዛትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰዎችን ለመጨቆን የታቀዱ አለመሆናቸውን ወዲያው ይገነዘባሉ። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ትዕዛዞችና መሠረታዊ ሥርዓቶች አጥብቀው ለሚከተሏቸው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ጥቅም ያመጡላቸዋል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) መጽሐፍ ቅዱስ ለተጨነቁ ሰዎች የሚሰጠው ማጽናኛ ውስጡ ባዶ በሆነ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ነገሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንዲችሉ ይረዳቸዋል። እንዴት? በሚከተሉት ሦስት መንገዶች አማካኝነት ነው፦ (1) ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል የሚረዳ ትክክለኛ ምክር በመስጠት፣ (2) አምላክ በአሁኑ ጊዜ ለአገልጋዮቹ እየሰጣቸው ያለውን ፍቅራዊ ድጋፍ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በማብራራትና (3) አምላክ እርሱን ለሚያገለግሉት ያዘጋጀላቸውን አስደሳች የወደፊት ጊዜ በመግለጽና እነዚህ ተስፋዎች ይመጣሉ ብለው ለማመን የሚያስችሉ ትክክለኛ ምክንያቶችን በማቅረብ ነው።
7. (ሀ) በግርጌ ማስታወሻው ላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ተጠቅመህ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱን በመውሰድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ አብራራ። (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመሸሽ ወይም ለመቋቋም እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ግለጽ።
7 ሥልጣንን የማይቀበሉና የራሳቸውን ድሎት ብቻ የሚያሳድዱ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር የማይወዱት ቢሆንም ብዙዎቹ ይህ ዓይነት አኗኗር እውነተኛ ደስታ እንዳላመጣላቸው ተገንዝበዋል። (ገላትያ 6:7, 8) መጽሐፍ ቅዱስ ፅንስ ማስወረድን፣ ፍችንና ሰዶማዊነትን በሚመለከት ለሚነሡ ጥያቄዎች የማያሻማ መልስ ይሰጣል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አደንዛዥ ዕፅ ከመውሰድና ከልክ በላይ ከመጠጣት እንድንቆጠብ፣ በኤድስ የተበከለ ደም በመውሰድ ወይም በጾታ ብልግና ምክንያት በበሽታው ከመያዝ ይጠብቀናል። ደስተኛ ቤተሰብ እንዴት ሊኖረን እንደሚችል ይነግረናል። አንድ ሰው ከቅርብ የቤተሰብ አባሎቹ ጥላቻ ሲያጋጥመው፣ ከባድ ሕመም ሲደርስበትና የሚወደው ሰው ሲሞትበት የሚሰማውን ጭንቀትና ሌሎችም በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ በጣም አስጨናቂ ሁኔታዎችን እንዴት መቋቋም እንደሚችልም ምክር ይሰጣል። ሕይወታችን በጸጸት ሳይሆን ትርጉም ባለው ሥራ የተሞላ ይሆን ዘንድ ለየትኞቹ ነገሮች ቅድሚያ ልንሰጥ እንደሚገባን ለማወቅ እንድንችል ይረዳናል።a
8, 9. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው እንድትል የሚያደርግህ በተለይ አንተን በግል የሚነካህ የትኛው ትንቢት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አመንጪያቸው ማን ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ይሰጣሉ?
8 ትንቢታዊነቱ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በመናገርም አቻ የማይገኝለት መጽሐፍ ነው። ወደፊት የሚሆነውን ነገር አንድ በአንድ በመዘርዘር ይናገራል። ስለጥንቷ ጢሮስ መጥፋት፣ ስለ ባቢሎን መውደቅ፣ ስለ ኢየሩሳሌም እንደገና መታነጽ፣ ስለ ሜዶንና ፋርስ እንዲሁም ስለ ግሪክ ነገሥታት አነሳስና አወዳደቅ በተጨማሪም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ስለሚፈጸሙ ብዙ ነገሮች አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ በዓለም ዙሪያ የተፈጸሙትን ክስተቶች አስቀድሞ በዝርዝር ተናግሯል፤ ትርጉማቸውንም ያብራራል። ሰብዓዊ ገዥዎችን ያስጨነቁ ችግሮች ሁሉ እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኙ ይገልጻል። ለሰው ልጆች ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ሕይወት የሚያመጣው ገዥ ማን እንደሆነም ለይቶ ይገልጻል።b—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:1–5, 9፤ 53:4–6
9 መጽሐፍ ቅዱስ ስለወደፊቱ ጊዜ በትክክል የመተንበይን ችሎታ የአምላክነት ማረጋገጫ አድርጎ ይገልጸዋል። ይህም ልዩ ትርጉም አለው። (ኢሳይያስ 41:1 እስከ 46:13) ሕይወት የለሽ ጣዖት እንዲህ ማድረግ አይችልም፤ ወይም ሌሎች እንዲህ እንዲያደርጉ ማነሣሣት አይችልም። ለአምላክ ያደረ ተራ ሰውም ይህን ሊያደርግ አይችልም። ትክክለኛ ትንቢት መናገር የሚችለው እውነተኛው አምላክ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹን ትንቢቶች የያዘውም መጽሐፍ የሱ ቃል ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13
በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀሙ ሁሉ ትክክለኛ ናቸውን?
10, 11. ኢየሱስ እንደተናገረው አንድ ቄስ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀም ቢሆንም እንኳን ሃይማኖቱን ምን ነገር ከንቱ ሊያደርግበት ይችላል?
10 ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን የሚሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በሙሉ እውነተኛ ሃይማኖቶች ናቸው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነውን? ከዚህም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት ነውን? መጽሐፍ ቅዱስን የያዘ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅስ ሁሉ ትክክለኛውን ሃይማኖት ይከተላል ማለት ነውን?
11 ብዙዎቹ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸውም ሃይማኖታቸውን ለራሳቸው ክብር ማግኛ አድርገው ይጠቀሙበታል። ንጹሑን እውነት ከሰብዓዊ ወግና ፍልስፍና ጋር ደባልቀውታል። አምልኮታቸው በአምላክ ፊት ተቀባይነት አለውን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ኢየሱስም “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል” ሲል አምላክ በነቢዩ በኩል የተናገረው ቃል በእነርሱ ላይ እንደሚሠራ በትክክል ገልጿል። (ማቴዎስ 15:8, 9፤ 23:5–10) እንዲህ ዓይነት ሃይማኖት እውነተኛ ሃይማኖት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
12, 13. (ሀ) የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባሎች የሚሠሩት ነገር አንድ ሰው ሃይማኖቱ ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚያስችለው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ እሱ ከሚጠላቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ብንመርጥ አምልኮታችንን እንዴት ይመለከተዋል? (2 ዜና መዋዕል 19:2)
12 አንዳንድ ሃይማኖቶች ጥሩ አቋም አላቸው በሚሏቸው አባሎቻቸው ሕይወት ውስጥ የሚታዩት ሃይማኖቶቹ የሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ያፈሯቸው ፍሬዎች የተበላሹ ከሆኑስ? ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። . . . መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል” በማለት አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴዎስ 7:15–17) ግለሰቦች መጥፎ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ፤ እንዲህ ያደረጉ ሰዎችም መታረም የሚያስፈልጋቸው መሆኑ አይካድም። የቤተ ክርስቲያን አባሎቻቸው፣ ቀሳውስቱ ጭምር በዝሙትና በምንዝር፣ በድብድብ፣ በስካር፣ በስግብግብነት፣ በውሸት፣ በጥንቆላ፣ በጣዖት አምልኮ ሁሉ ወይም ከነዚህ ነገሮች በአንዱ ተዘፍቀው እያሉ ምንም እርማት የማይሰጣቸው ከሆነ፣ በዚህ ድርጊታቸው የሚቀጥሉትም ከማኀበሩ የማይባረሩ ከሆነ ነገሩን ለየት ያደርገዋል። እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን እያዘወተሩ የሚኖሩ ሰዎች ከማኅበሩ መባረር እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። በአምላክ መንግሥት ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም። (ገላትያ 5:19–21) አምልኮታቸው እግዚአብሔርን የሚያስደስት አይደለም። አምላክ ከሚጠላቸው ጋር ለመቀራረብ ከመረጥን የእኛም አምልኮ እርሱን አያስደስትም።—1 ቆሮንቶስ 5:11–13፤ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8
13 መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን እውነተኛ ሃይማኖት የያዙት በመጽሐፍ ቅዱስ እንጠቀማለን የሚሉ ሃይማኖቶች በሙሉ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የእውነተኛው ሃይማኖት መለያ ምልክቶች ናቸው ብሎ የሚገልጻቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው?
እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ የሚታወቅባቸው ምልክቶች
14. (ሀ) እውነተኛው ሃይማኖት የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በሙሉ በምን ላይ የተመሠረቱ ናቸው? (ለ) ሕዝበ ክርስትና ስለ አምላክና ስለ ነፍስ የምታስተምረው ትምህርት በዚህ ቢፈተን ምን ሆኖ ይገኛል?
14 የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በጥብቅ የተመሠረቱ ናቸው። “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት . . . የሚጠቅም ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝበ ክርስትና የምታስተምረውን የሥላሴ እምነት የት ላይ ይጠቅሰዋል? ቀሳውስት እንደሚያስተምሩት ከሆነ ሰው አካሉ ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትኖር ነፍስ አለችው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ ብሎ የሚያስተምረው የት ላይ ነው? አንድ ቄስ እነዚህ ትምህርቶች የሚገኙበትን ቦታ ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያሳይህ ጠይቀኸው ታውቃለህን? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ “ሥላሴ የሚለው ቃልም ሆነ የሥላሴ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም” ብሏል። (በ1992 የታተመ፣ ማይክሮፔድያ፣ ጥራዝ 11፣ ገጽ 928) ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ ደግሞ “ከሐዋርያዊ አባቶች መካከል ወደዚህ አስተሳሰብ በትንሹ እንኳን ቀረብ የሚል አስተሳሰብ የነበረው የለም” ሲል አምኗል። (በ1967 የታተመ፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 299) ሰው ሲሞት ከአካሉ ተለይታ የምትሄድ ነፍስ አለችው የሚለውን የሕዝበ ክርስትና አስተሳሰብ ከግሪክ ፍልስፍና የወሰዱት መሆኑን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አምነዋል። እውነተኛው ሃይማኖት ግን ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችን ለማስተናገድ ሲል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ገሸሽ አያደርግም።—1 ቆሮንቶስ 15:45፤ ዘዳግም 6:4፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ ዮሐንስ 14:28
15. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ሊመለክ የሚገባውን አምላክ ማንነት ለይቶ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ አምላኪዎች ወደ ይሖዋ ስለመጠጋት ምን ይሰማቸዋል?
15 እውነተኛው ሃይማኖት መመለክ ያለበት አንድ እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው የሚል ጥብቅ አቋም አለው። (ዘዳግም 4:35፤ ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዳግም 5:9ንና 6:13ን በቀላል አባባል በመጥቀስ “ለጌታ [ለይሖዋ አዓት] ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ” ሲል ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:10) ኢየሱስ ከዚህ ጋር የሚስማማ መንገድ በመከተል የአባቱን ስም ለደቀ መዛሙርቱ አሳውቋቸዋል። (ዮሐንስ 17:26) ሃይማኖትህ ይሖዋን እንድታመልክ አስተምሮሃልን? በርሱ ተማምነህ ወደርሱ ይበልጥ መቅረብ እንደምትችል ይሰማህ ዘንድ በዚህ ስም የሚታወቀውን አምላክ ማንነት፣ ዓላማዎቹን፣ የሠራቸውን ሥራዎች፣ ባሕርያቱን ታውቃለህን? ሃይማኖትህ እውነተኛ ሃይማኖት ከሆነ ለነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ አዎን የሚል ይሆናል።—ሉቃስ 10:22፤ 1 ዮሐንስ 5:14
16. እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች በክርስቶስ ማመንን ምን ቦታ ይሰጡታል?
16 አምላክን የሚያስደስት እውነተኛ አምልኮ አንዱ ዐቢይ ክፍል በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። (ዮሐንስ 3:36፤ ሥራ 4:12) ይህም በአንድ ወቅት ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ ነበረ ወይም ከሰው ሁሉ የተለየ ነበር ብሎ ማመን ማለት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት ያለውን ዋጋ አስመልክቶ የሚያስተምረውን ትምህርት መገንዘብንና በአሁኑ ጊዜ በሰማይ የንግሥና ሥልጣን ያለው መሆኑን አምኖ መቀበልንም ይጨምራል። (መዝሙር 2:6–8፤ ዮሐንስ 3:16፤ ራእይ 12:10) እውነተኛውን ሃይማኖት ከሚከተሉት ሰዎች ጋር የምትቀራረብ ከሆነ በዕለታዊ ኑሯቸው ኢየሱስን ለመታዘዝ፣ እርሱን ለመምሰልና ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው ሥራ በግለሰብ ደረጃ በቅንዓት ለመካፈል ምን ያህል ተግተው እንደሚጥሩ ታውቃለህ። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 15:14፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) በአምልኮ የምትተባበራቸው ሰዎች ሁኔታ ከዚህ የተለየ ከሆነ ግን እነዚህን ሰዎች መፈለግ አለብህ።
17. እውነተኛ አምላኪዎች የዓለም እድፍ እንዳይነካቸው የሚጠነቀቁት ለምንድን ነው? ይህስ ምንን ይጨምራል?
17 እውነተኛው አምልኮ በፖለቲካ ወይም በዓለም ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የተበከለ አይደለም። (ያዕቆብ 1:27) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) ኢየሱስ በፖለቲካ ውስጥ አልገባም ነበር። ተከታዮቹንም በጦር መሣሪያ እንዳይጠቀሙ ከልክሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:52) የአምላክ ቃል የሚናገረውን ከልብ የሚቀበሉ ሁሉ ‘ከእንግዲህ ወዲህ የጦር ትምህርት አይማሩም።’ (ኢሳይያስ 2:2–4 የ1980 ትርጉም) ሃይማኖትህን የያዝከው ለስሙ ያህል ብቻ ቢሆንም እንኳን ይህን ብቃት የማያሟላ ከሆነ ከሃይማኖቱ ጋር ያለህን ግንኙነት ለማቋረጥ ጊዜው አሁን ነው።—ያዕቆብ 4:4፤ ራእይ 18:4, 5
18. (ሀ) በዮሐንስ 13:35 ላይ የተገለጸው የእውነተኛው ሃይማኖት አንዱ ጉልህ መለያ ምንድን ነው? (ለ) ዮሐንስ 13:35ን ተግባራዊ የሚያደርገው የትኛው ቡድን እንደሆነ እንዲያውቅ አንድን ሰው ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?
18 እውነተኛ ሃይማኖት ራስ ወዳድነት የሌለበትን ፍቅር ያስተምራል፤ በተግባርም ያሳያል። (ዮሐንስ 13:35፤ 1 ዮሐንስ 3:10–12) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በስብከት ብቻ የሚነገር አይደለም። ከሁሉም ዘር፣ ከሁሉም የኑሮ ደረጃ፣ ከሁሉም ቋንቋና ብሔር የተውጣጡ ሕዝቦችን በእውነተኛ ወንድማማችነት የሚያስተሳስር ነው። (ራእይ 7:9, 10) እውነተኛ ክርስቲያኖችን በዙሪያቸው ካለው ዓለም ለየት ብለው እንዲታዩ ያደርጋል። እስካሁን የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት አዳራሻቸው ውስጥ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎችና በትልልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ ተገኝተህ የማታውቅ ከሆነ አሁን እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። የመንግሥት አዳራሻቸውን በአንድነት ሲሠሩ ሁኔታቸውን ተመልከት። በዕድሜ የገፉ ሰዎችን (ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ጭምር) እንዲሁም ወጣቶችን (አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸውን ወይም ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን ጭምር) እንዴት እንደሚይዟቸው አስተውል። (ያዕቆብ 1:27) ያየኸውን በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ከተመለከትከው ነገር ጋር አወዳድረው። ከዚያም ‘እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉት እነማን ናቸው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
19. (ሀ) እውነተኛው ሃይማኖት ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔ የሚሆነው ምን መሆኑን አጥብቆ ያምናል? (ለ) የእውነተኛው ሃይማኖት አባላት ምን ሲያደርጉ መታየት ይኖርባቸዋል?
19 እውነተኛው ሃይማኖት ለሰው ልጅ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የምታመጣው የአምላክ መንግሥት ናት የሚል የጸና አቋም አለው። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:4, 5) እንዲህ የሚያደርግ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት አለን? አንድ ቄስ ስለ አምላክ መንግሥትና ቅዱሳን ጽሑፎች መንግሥቲቱ ትፈጽማለች ስለሚላቸው ነገሮች ሲያብራራ የሰማህበት ቀን አለ? አባል የሆንክበት ድርጅት ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች እንድትናገር ያበረታታሃልን? ከሆነስ የሃይማኖቱ አባላት በሙሉ በዚህ ሥራ ይካፈላሉን? ኢየሱስ ስለ መንግሥቲቱ መስክሯል፤ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ አድርገዋል። አንተም በዚህ ሥራ የመካፈል መብት ልታገኝ ትችላለህ። ይህ ሥራ በዛሬው ጊዜ በዚች ምድር ላይ በመሠራት ላይ ያለ ከማንኛውም ሥራ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሥራ ነው።—ማቴዎስ 24:14
20. ትክክለኛውን ሃይማኖት ለይተን ከማወቅ በተጨማሪ ምን ልናደርግ ይገባናል?
20 ምንም እንኳን በሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ቢኖሩም ግራ ከመጋባት ድነን እውነተኛውን ሃይማኖት በቀላሉ ለይተን የምናውቅበትን አቋራጭ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል። ሆኖም እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተን ማወቃችን ብቻ አይበቃም። ያን ሃይማኖት መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ምን ማድረግን እንደሚጨምር የሚቀጥለው ርዕሳችን ሰፋ አድርጎ ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፅንስ ማስወረድ፦ ሥራ 17:28፤ መዝሙር 139:1, 16፤ ዘጸአት 21:22, 23፤ ፍቺ፦ ማቴዎስ 19:8, 9፤ ሮሜ 7:2, 3፤ ሰዶማዊነት፦ ሮሜ 1:24–27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11፤ ዕፅ መውሰድና ከልክ በላይ መጠጣት፦ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ሉቃስ 10:25–27፤ ምሳሌ 23:20, 21፤ ገላትያ 5:19–21፤ ደምና የጾታ ብልግና፦ ሥራ 15:28, 29፤ ምሳሌ 5:15–23፤ ኤርምያስ 5:7–9፤ ቤተሰብ፦ ኤፌሶን 5:22 እስከ 6:4፤ ቆላስይስ 3:18–21፤ በሌሎች መጠላት፦ መዝሙር 27:10፤ ሚልክያስ 2:13–16፤ ሮሜ 8:35–39፤ ሕመም፦ ራእይ 21:4, 5፤ 22:1, 2፤ ቲቶ 1:2፤ መዝሙር 23:1–4፤ ሞት፦ ኢሳይያስ 25:8፤ ሥራ 24:15፤ መቅደም ስለሚገባቸው ነገሮች፦ ማቴዎስ 6:19–34፤ ሉቃስ 12:16–21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6–12
b ስለ ትንቢቶችና ስላፈጻጸማቸው ምሳሌ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 117–61 እንዲሁም ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 60–2, 225–32, 234–40 ተመልከት። ሁለቱም ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ ናቸው።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ ለመወሰን ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈልገው የማን አመለካከት ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያረጋግጡ አራት ማስረጃዎች ምን ምን ናቸው?
◻ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀሙ ሃይማኖቶች በሙሉ ያልሆኑት ለምንድን ነው?
◻ ትክክለኛው አንድ ሃይማኖት ተለይቶ የሚታወቅባቸው ስድስት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የይሖዋ ምሥክሮች . . .
◆ የሚያስተምሯቸው ትምህርቶች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
◆ ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ያመልካሉ።
◆ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ካላቸው እምነት ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖራሉ።
◆ በፖለቲካና በዓለም ግጭቶች ውስጥ አይገቡም።
◆ በዕለታዊ ኑሮቸው ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ለማሳየት ይጥራሉ።
◆ ለሰው ልጅ ችግሮች ሁሉ ዘላቂ መፍትሔ የምታመጣው የአምላክ መንግሥት ናት የሚል ጥብቅ አቋም አላቸው።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች በሙሉ ያስተላለፈውን መልእክት የያዘ መሆኑን የሚያመለክተው ምንድን ነው?