ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራችሁ መንገድ አድርጉት
“ለአምላክ ያደሩ መሆን ለሁሉም ነገር ጠቃሚ ነው”—1 ጢሞቴዎስ 4:8 አዓት
1, 2. ሰዎች ለጤንነታቸው ምን ያህል ይጨነቃሉ? ከምንስ ውጤት ጋር?
በሕይወት ውስጥ አንድ ሰው እንዲኖሩት ከሚፈልጋቸው በጣም ውድ ነገሮች አንዱ መልካም ጤንነት ነው ቢባል አብዛኞቹ ሰዎች ያለምንም ማመንታት ይስማማሉ። ሰዎች አካላዊ ጤንነታቸውን ለመጠበቅና አስፈላጊም ከሆነ ተገቢውን የጤና ክትትል ለማድረግ ሲሉ በጣም ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ ያጠፋሉ። ለምሳሌ ያክል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቅርብ ዓመት ዓመታዊው የጤና እንክብካቤ ወጪ 900 ቢልዮን ዶላር ነበር። ይህም በዚያ አገር የሚገኝ እያንዳንዱ ወንድ፣ ሴት እንዲሁም ልጅ በዓመት ከ3000 ዶላር በላይ የሕክምና ወጪ አለው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ባደጉት ሌሎች አገሮች ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር ተመጣጣኝ ነው።
2 ይህ ሁሉ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪ ያስገኘው ፋይዳ ምንድን ነው? እርግጥ ነው በታሪክ ውስጥ ከምን ጊዜውም የበለጠ ዛሬ በጣም ዘመናዊ የሕክምና መገልገያዎችና ዝግጅቶች አሉ ቢባል ማንም አይክድም። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ጤናማ ሕይወት ሊያስገኝ አልቻለም። እንዲያውም ፕሬዘዳንቱ ለዩናይትድ ስቴትስ የወጣውን የጤና አጠባበቅ ፕሮግራም የሚገልጽ ንግግር ሲያቀርቡ “በዚህ አገር ውስጥ ዓመፅ ከሚያስወጣው ከፍተኛ ወጪ” በተጨማሪ ከማንኛውም ያደገ አገር የበለጠ “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤድስ በሽተኞች፣ አጫሾችና ከመጠን በላይ የሚጠጡ፣ በአሥራዎቹ እድሜ የሚያረግዙ፣ በጣም አነስተኛ ክብደት ያላቸው ሆነው የሚወለዱ ሕፃናት” የሚገኙባት አገር ዩናይትድ ስቴትስ ናት ብለዋል። ፕሬዘዳንቱ ንግግራቸውን ሲደመድሙ “በሕዝብ ደረጃ ጤናማ ለመሆን የምንፈልግ ከሆነ አካሄዳችንን መለወጥ አለብን” ብለዋል።—ገላትያ 6:7, 8
ጤናማ አኗኗር
3. ጳውሎስ ከጥንት ግሪኮች ልማድ በመነሣት ምን ምክር ሰጠ?
3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ግሪኮች ለአካል ብቃትና ጥንካሬ እንዲሁም ለሰውነት ማጎልመሻና ለአትሌቲክስ ውድድሮች ከፍተኛ ቦታ በመስጠት የታወቁ ነበሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከዚህ በመነሣት ለወጣቱ ጢሞቴዎስ እንደሚከተለው ብሎ ለመጻፍ በመንፈስ ተነሣስቷል፦ “የአካል ማሠልጠኛ ለጥቂት ይጠቅማል፣ ለአምላክ ያደሩ መሆን ግን የአሁኑም የሚመጣውም ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁሉም ነገር ጠቃሚ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 4:8 አዓት) እዚህ ላይ ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ሰዎች ጠቃሚ ናቸው የሚሏቸው ማለትም የሕክምና ወይም የአካል እንቅስቃሴ ዝግጅቶች እውነተኛ የሆነ ጤናማ ሕይወት ለማስገኘት ዋስትና እንደማይሰጡ ማመልከቱ ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ፈጽሞ ሊቀር የማይችለው ነገር መንፈሳዊ ጤንነትን መንከባከብና ለአምላክ ያደሩ መሆን እንደሆነ አረጋግጦልናል።
4. ለአምላክ ያደሩ መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
4 አምላካዊ ያልሆኑ ወይም ‘የአምልኮ መልክ ብቻ ያላቸው’ ሰዎች በራሳቸው ላይ ከሚያመጧቸው ጎጂ ነገሮች ሁሉ ስለሚጠብቀን እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ‘ለአሁኑ ሕይወትም’ ጠቃሚ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:5፤ ምሳሌ 23:29, 30፤ ሉቃስ 15:11–16፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ለአምላክ ያደሩ የመሆን ፍላጎት ሕይወታቸውን እንዲቀርጸው የሚፈቅዱ ሰዎች ለአምላክ ሕጎችና ትእዛዛት ጤናማ አክብሮት አላቸው። ይህ ደግሞ የአምላክን ጤናማ ትምህርት የአኗኗራቸው መንገድ እንዲያደርጉት ይገፋፋቸዋል። ይህ ዓይነቱ አኗኗር መንፈሳዊና አካላዊ ጤና፣ እርካታ እንዲሁም ደስታ ያመጣላቸዋል። በተጨማሪም “እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ” ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 6:19
5. ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ምን መመሪያዎችን ሰጥቷል?
5 በጤናማው የአምላክ ትምህርት የሚመራ ሕይወት አሁንም ሆነ ወደፊት እንደነዚህ የመሳሰሉ በረከቶችን ስለሚያመጣ የአምላክን ጤናማ ትምህርት እንዴት የአኗኗር መንገድ ልናደርገው እንደምንችል ተግባራዊ በሆነ መንገድ ማወቅ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤው ላይ መልሱን አስቀምጦልናል። ጳውሎስ “አንተ ግን ለጤናማው ትምህርት የሚስማሙ ነገሮችን መናገርህን ቀጥል” ሲል ለቲቶ መመሪያ የሰጠበትን የዚህን መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ልዩ ትኩረት እንሰጠዋለን። ዛሬ ወጣቶችም ሆንን የሸመገልን፣ ወንድም ሆንን ሴት ከእንዲህ ዓይነቱ “ጤናማ ትምህርት” ልንጠቀም እንደምንችል የተረጋገጠ ነው።—ቲቶ 1:4, 5፤ 2:1 አዓት
ለሸመገሉ ወንዶች የተሰጠ ምክር
6. ጳውሎስ ‘ለሸመገሉ ወንዶች’ ምን ምክር ሰጥቷል? እንዲህ ማድረጉስ ደግነት የሆነው ለምንድን ነው?
6 ጳውሎስ በመጀመሪያ በጉባኤ ውስጥ ላሉ የሸመገሉ ወንዶች ምክር ሰጥቷል። እባካችሁ ቲቶ 2:2ን አንብቡት። “ሽማግሌዎች” በአጠቃላይ ይከበራሉ፤ እንዲሁም የእምነትና የታማኝነት ምሳሌዎች ተደርገው ይታያሉ። (ዘሌዋውያን 19:32፤ ምሳሌ 16:31) ከዚህ የተነሣ ሌሎች ሰዎች በጣም ከባድ የሆኑ ጉዳዮች ካላጋጠሙ በስተቀር ለሸመገሉ ወንዶች ምክር ወይም አስተያየት ከመስጠት ሊቆጠቡ ይችላሉ። (ኢዮብ 32:6, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:1) ስለዚህ ጳውሎስ በመጀመሪያ ሽማግሌዎችን መምከሩ ደግነት ማሳየቱ ነው። የጳውሎስን ቃላት ከልብ ቢቀበሉና እንደ ጳውሎስ ሁሉ ሌሎች ሊመስሏቸው የሚገቡ ዓይነት ሰዎች ቢሆኑ መልካም ነው።—1 ቆሮንቶስ 11:1፤ ፊልጵስዩስ 3:17
7, 8. (ሀ) ‘በተለያዩ ልማዶች’ ልከኛ መሆን ምንን ይጨምራል? (ለ) “ጭምትነት” “በአስተሳሰብ ጤናማ” ከመሆን ጋር ሚዛናዊ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
7 የሸመገሉ ክርስቲያን ወንዶች በመጀመሪያ ደረጃ “ልከኞች” መሆን አለባቸው። ምንም እንኳን የቃሉ መሠረታዊ ትርጉም የመጠጥ ልማድን (“አለመስከርን” ኪንግደም ኢንተርሊነር) የሚያመለክት ቢሆንም ንቁ መሆንን፣ አስተዋይ መሆንን ወይም ስሜትን መጠበቅን ጭምር የሚያመለክት ትርጉም አለው። (2 ጢሞቴዎስ 4:5፤ 1 ጴጥሮስ 1:13) እንግዲያው ሽማግሌዎች በመጠጥም ሆነ በሌሎች ነገሮች መጠናቸውን የሚጠብቁ ልከኞች መሆን አለባቸው።
8 በተጨማሪም “ጭምቶች” እና “በአስተሳሰብ ጤናሞች” መሆን አለባቸው። ጭምት ወይም ግርማ ሞገስ ያለው፣ ጨዋነትና ክብር የሚገባው መሆን ከዕድሜ ጋር ይመጣል። ሆኖም አንዳንዶች ከልክ በላይ ኮስታሮች ይሆኑና ወጣቶች በትኩስ ኃይላቸው የሚያደርጓቸውን ነገሮች የማይታገሱ ሊሆኑ ይችላሉ። (ምሳሌ 20:29) “ጭምትነት” ወይም ኮስታራ ጠባይ “በአስተሳሰብ ጤናማ” ከመሆን ጋር ተመጣጥኖ መታየት ያስፈለገው ለዚህ ነው። የሸመገሉ ወንዶች ከዕድሜያቸው ጋር የሚመጣጠን ጭምትነት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ስሜቶቻቸውንና ውስጣዊ ግፊቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ረገድ ሚዛናዊ መሆንም አለባቸው።
9. የሸመገሉ ወንዶች በእምነት፣ በፍቅር በተለይ ደግሞ በጽናት ጤናሞች መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
9 በመጨረሻም የሸመገሉ ወንዶች “በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች” መሆን አለባቸው። ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሲጽፍ እምነትንና ፍቅርን ከተስፋ ጋር አብሮ ይጠቅሳል። (1 ቆሮንቶስ 13:13፤ 1 ተሰሎንቄ 1:3፤ 5:8) እዚህ ላይ ግን “ተስፋን” “በጽናት” ተክቶታል። ምናልባትም እንዲህ ያደረገበት ምክንያት ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ተስፋ ቆርጦ እጅ የመስጠት ስሜት ስለሚያጠቃ ይሆናል። (መክብብ 12:1) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በግልጽ እንዳስቀመጠው “እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” (ማቴዎስ 24:13) ከዚህም በተጨማሪ ሽማግሌዎች በዕድሜያቸው ወይም ባካበቱት ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን ባሏቸው ጠንካራ መንፈሳዊ ባሕርያት፣ ማለትም በእምነት፣ በፍቅርና በጽናት ለሌሎች ምሳሌ መሆን አለባቸው።
ለአሮጊቶች
10. ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ላሉ “አሮጊቶች” ምን ምክር ሰጥቷል?
10 ቀጥሎም ጳውሎስ ትኩረቱን በጉባኤው ውስጥ ወዳሉት አሮጊቶች መልሷል። እባካችሁ ቲቶ 2:3ን አንብቡት። “አሮጊቶች” በጉባኤ ውስጥ ካሉት ሴቶች በዕድሜ የሚበልጡት ናቸው። እነሱም “የሸመገሉ ወንዶች” ሚስቶችን፣ የሌሎች የጉባኤ አባላትን እናቶችና ሴት አያቶች ይጨምራሉ። በዚህም ምክንያት በሌሎች ላይ ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ጳውሎስ “እንዲሁም” በማለት ምክሩን የጀመረው ለዚህ ነው። ይህም ማለት “አሮጊቶች” ጭምር በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለመፈጸም ሊወጧቸው የሚገቡ አንዳንድ ኃላፊነቶች አሏቸው ማለት ነው።
11. የሚያስከብር ጠባይ ምንድን ነው?
11 ጳውሎስ በመጀመሪያ “አሮጊቶች ሴቶች የሚያስከብር ጠባይ ያላቸው ይሁኑ” ብሏል። (አዓት) “ጠባይ” የአንድ ሰው ውስጣዊ ባሕርይና ማንነት ውጫዊ መግለጫ ነው። ይህም በአኗኗርና በውጫዊ ሁኔታ ይንጸባረቃል። (ማቴዎስ 12:34, 35) ታዲያ የአንዲት አሮጊት ክርስቲያን ጠባይ ወይም ባሕርይ ምን መሆን ይኖርበታል? በአጭር ቃል “የሚያስከብር” መሆን ይኖርበታል። ይህም “አንድ ሰው ለአምላክ ከሚያደርጋቸው ድርጊቶች ወይም ከሚሰጣቸው ነገሮች ጋር የሚስማማ” የሚል ትርጉም ካለው አንድ የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። አሮጊቶች በሌሎች ላይ በተለይም በጉባኤው ውስጥ ባሉት ወጣት ሴቶች ላይ ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ አንፃር ሲታይ ይህ በእርግጥም ተገቢ ምክር ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10
12. ሁሉም ሊርቀው የሚገባ ምን የተሳሳተ የምላስ አጠቃቀም ነው?
12 ቀጥሎ “የማያሙ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ” የሚሉት ሁለት አሉታዊ ነገሮች ተጠቅሰዋል። እነዚህ ሁለት ቃላት በአንድነት መጠቀሳቸው በጣም ጥሩ ነው። “ወይን ብቸኛው መጠጥ በነበረበት በጥንት ዘመን አሮጊቶች በአነስተኛ የወይን ግብዣቸው ላይ ጎረቤቶቻቸውን በሐሜት ይቦጫጭቁ ነበር” ሲሉ ፕሮፌሰር ኢ ኤፍ ስኮት ተናግረዋል። በአጠቃላይ ሲታይ ከወንዶች ይልቅ የሌላ ሰው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሴቶች ናቸው፤ ይህ ደግሞ የሚያስመሰግን ነው። ይሁን እንጂ ይህ አሳቢነት ቀስ በቀስ ወደ ሐሜት አልፎ ተርፎም ስም ወደማጥፋት ሊሄድ ይችላል። በተለይ ምላስ በመጠጥ በሚፈታበት ጊዜ። (ምሳሌ 23:33) ጤናማ የአኗኗር መንገድ የሚከተሉት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከዚህ አደጋ ለመጠንቀቀ እንደሚጥሩ የተረጋገጠ ነው።
13. አሮጊቶች አስተማሪ ሊሆኑ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
13 አሮጊቶች ያላቸውን ጊዜ ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙበት “በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ” እንዲሆኑ ተበረታተዋል። ጳውሎስ በሌላ ቦታ ላይ ሴቶች በጉባኤ ውስጥ አስተማሪዎች መሆን እንደሌለባቸው ግልጽ መመሪያ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 14:34፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:12) ይሁን እንጂ ይህ መመሪያ ውድ የሆነውን የአምላክ እውቀት በቤታቸው ውስጥና በውጭ ላሉ ሰዎች ከመናገር አያግዳቸውም። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15) በተጨማሪም ቀጥሎ ያሉት ጥቅሶች እንደሚያሳዩት በጉባኤው ውስጥ ለሚገኙት ወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ምሳሌዎች በመሆን ብዙ መልካም ነገሮችን ሊያከናውኑ ይችላሉ።
ለወጣት ሴቶች
14. ወጣት ክርስቲያን ሴቶች ያሉባቸውን ሥራዎች በማከናወን ረገድ ሚዛናዊነትን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ አሮጊቶች “በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ” እንዲሆኑ ካበረታታ በኋላ ወጣት ሴቶችን ለይቶ ጠቅሷል። እባካችሁ ቲቶ 2:4, 5ን አንብቡት። ምንም እንኳን አብዛኛው መመሪያ በቤት ውስጥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ቢሆንም ወጣት ክርስቲያን ሴቶች ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠረው በመፍቀድ ከሚገባው በላይ መሄድ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ “በአስተሳሰብ ጤናሞች፣ ንጹሖች . . . በጎዎች” ከሁሉ በላይ ደግሞ “የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ” ክርስቲያናዊ የራስነት ዝግጅትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆን አለባቸው።
15. በጉባኤ ውስጥ ያሉ ብዙ ወጣት ሴቶች መመስገን የሚገባቸው ለምንድን ነው?
15 ዛሬ ያለው የቤተሰብ ሁኔታ ጳውሎስ ከነበረበት ጊዜ በጣም ተለውጧል። ብዙ ቤተሰቦች በእምነት የተከፋፈሉ ናቸው። ሌሎች ደግሞ አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸው ናቸው። የቀድሞ ልማዶችን በሚያጠብቁ ቤተሰቦችም እንኳ ሚስት የቤት እመቤት መሆኗ እየቀረ መጥቷል። ይህ ሁሉ በወጣት ክርስቲያን ሴቶች ላይ ከባድ ውጥረትና ኃላፊነት ያመጣል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ከቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎቻቸው ነፃ አያደርጋቸውም። እንግዲያው ያሉባቸውን ብዙ ሥራዎች ሚዛናዊ ለማድረግና የመንግሥቱን ፍላጎት ለማስቀደም በኃይል እየጣሩ ያሉ ታማኝ ወጣት ሴቶችን ማየት በጣም ያስደስታል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ረዳት አቅኚ ወይም የዘወትር አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ እያገለገሉ ነው። (ማቴዎስ 6:33) በእርግጥ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል!
ለወጣት ወንዶች
16. ጳውሎስ ለወጣት ወንዶች ምን ምክር ሰጥቷል? ይህስ ወቅታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ከዚያም ጳውሎስ ትኩረቱን ቲቶን ጨምሮ ወደ ወጣት ወንዶች አድርጓል። እባካችሁ ቲቶ 2:6–8ን አንብቡት። ዛሬ ያሉ የአብዛኞቹ ወጣቶች የግለዴለሽነትና ወደ ጥፋት የሚወስድ አኗኗር ማለትም የዕፅና የአልኮል ሱሰኝነት፣ ልቅ የጾታ ድርጊት እንዲሁም እንደ አረመኒያዊ ስፖርቶችና ወራዳ ሙዚቃዎች እንዲሁም መዝናኛዎች የመሳሰሉትን ሌሎች ዓለማዊ ግቦችን የሚከተል አካሄድ ሲታይ ጤናማና አርኪ የሕይወት መንገድ ለመከተል ለሚፈልጉ ክርስቲያን ወጣቶች ይህ በእርግጥ ወቅታዊ ምክር ነው።
17. አንድ ወጣት ‘በአስተሳሰብ ጤናማ’ ‘በመልካም ሥራም በኩል ጥሩ ምሳሌ’ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
17 በዓለም ካሉት ወጣቶች አንፃር ሲታይ አንድ ወጣት ክርስቲያን “በአስተሳሰብ ጤናማ” እና “በመልካም ሥራ ምሳሌ” መሆን ይኖርበታል። ጳውሎስ ጤናማና የጎለመሰ አእምሮ ሊያገኙ የሚችሉት እንዲሁ የሚያጠኑ ብቻ ሳይሆኑ “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና” ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ገልጿል። (ዕብራውያን 5:14) ወጣቶች የልጅነት ጉልበታቸውን የራስወዳድነት ፍላጎቶችን በማሳደድ ከማባከን ይልቅ በጉባኤ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ሥራዎች ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ጊዜያቸውንና ኃይላቸው በፈቃደኝነት ሲሰጡ ማየት እንዴት ግሩም ነው! እንዲህ ማድረጋቸው እንደ ቲቶ በጉባኤው ውስጥ ላሉት ‘በመልካም ተግባር’ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 4:12
18. ያልተዛባ ትምህርት ማስተማር፣ በድርጊት ጭምት መሆንና በአነጋገር ጤናማ መሆን ምን ማለት ነው?
18 ወጣት ወንዶች ‘ባልተዛባ ትምህርታቸው ጭምትነትን፣ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ’ ማሳየት እንደሚኖርባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ‘ያልተዛባ’ ትምህርት በአምላክ ቃል ላይ በደንብ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። እንግዲያው ወጣት ወንዶች ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆን አለባቸው። እንደ ሸመገሉት ወንዶች ሁሉ ወጣት ወንዶችም ጭምቶች መሆን አለባቸው። የአምላክ ቃል አገልጋይ መሆን ከባድ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ስለዚህ ‘ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ’ ይገባቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:27) በተመሳሳይም ተቃዋሚዎች የሚነቅፉበት ነገር እንዳያገኙ ንግግራቸው “ጤናማ” እና “የማይነቀፍ” መሆን አለበት።—2 ቆሮንቶስ 6:3፤ 1 ጴጥሮስ 2:12, 15
ለባሪያዎችና ለአገልጋዮች
19, 20. ለሌላ ሰው ተቀጥረው የሚሠሩ ‘ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት ሊያስመሰግኑ’ የሚችሉት እንዴት ነው?
19 በመጨረሻም ጳውሎስ ትኩረቱን ለሌሎች ሰዎች ተቀጥረው ወደሚሠሩ ሰዎች መልሷል። እባካችሁ ቲቶ 2:9, 10ን አንብቡት። ዛሬ ብዙዎቻችን ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች አይደለንም። ይሁን እንጂ ብዙዎቻችን ለሌሎች አገልግሎት የምንሰጥ ተቀጣሪዎች ወይም ሠራተኞች ነን። ስለሆነም ጳውሎስ የገለጻቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ዛሬም ይሠራሉ።
20 “ለገዛ ጌቶቻቸው በሁሉ ነገር የሚገዙ ይሁኑ” ሲባል ክርስቲያን ተቀጣሪዎች ለቀጣሪዎቻቸውና ለአለቆቻቸው እውነተኛ አክብሮት ማሳየት አለባቸው ማለት ነው። (ቆላስይስ 3:22) በተጨማሪም ቀጣሪዎቻቸው የሚፈልጉባቸውን ያህል የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመስጠት ሐቀኛ ሠራተኞች መሆን አለባቸው። አብረዋቸው የሚሠሩ የሌሎች ሰዎች ጠባይ ምንም ዓይነት ይሁን በሥራ ቦታ በክርስቲያናዊ ጠባይ ከፍተኛ የአቋም ደረጃ ማሳየት አለባቸው። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ‘ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር የሚያስመሰግኑ ’ እንዲሆኑ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም ተቀጣሪዎቻቸው በሚያሳዩት ጥሩ ጠባይ ምክንያት ቅንና አስተዋይ የሆኑ ሰዎች እውነትን እንደተቀበሉ የሚያሳዩ አስደሳች ውጤቶችን ብዙ ጊዜ እንሰማለን። ይህም ተቀጥረው በሚሠሩበት ቦታ እንኳ ሳይቀር ጤናማ ትምህርቱን ለሚከተሉ ሰዎች ይሖዋ የሚከፍላቸው ዋጋ ነው።—ኤፌሶን 6:7, 8
እንዲነፃ የተደረገ ሕዝብ
21. ይሖዋ ጤናማውን ትምህርት ያዘጋጀው ለምንድን ነው? እኛስ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
21 ጳውሎስ ያብራራው ጤናማ ትምህርት እንዲያው በፈለግነው ጊዜ የምንመለከተው አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር ሕግ ወይም አስተሳሰብ አይደለም። ጳውሎስ የጤናማውን ትምህርት ዓላማ ማብራራቱን ቀጥሏል። እባካችሁ ቲቶ 2:11, 12ን አንብቡት። ይሖዋ አምላክ ከፍቅሩና ይገባናል ከማንለው ደግነቱ የተነሣ በእነዚህ የመጨረሻና አደገኛ ቀኖች ውስጥ ዓላማ ያለውና አርኪ የሆነ ሕይወት እንድንኖር ሲል ጤናማውን ትምህርት ሰጥቶናል። ጤናማውን ትምህርት ለመቀበልና የአኗኗራችሁ መንገድ ለማድረግ ፈቃደኛ ናችሁን? እንዲህ በማድረግ ለመዳን ብቁ ትሆናላችሁ።
22, 23. ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራችን መንገድ በማድረጋችን ምን በረከቶችን እናጭዳለን?
22 ከዚህም በላይ ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራችን መንገድ ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ ትልቅ መብት ያስገኝልናል፤ ለወደፊቱ ጊዜ ደግሞ አስደሳች ተስፋ ይሰጠናል። እባካችሁ ቲቶ 2:13, 14ን አንብቡት። በእርግጥም ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራችን መንገድ ማድረጋችን ከዚህ ከተበላሸና እየሞተ ካለ ዓለም ንጹህ ሕዝብ አድርጎ ይለየናል። የጳውሎስ ቃላት ሙሴ በሲና ተራራ ለእስራኤል ልጆች ከሰጠው ቀጥሎ ካለው ማሳሰቢያ ጋር ይመሳሰላሉ፦ “እግዚአብሔርም . . . ከፈጠራቸው አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፣ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል።”—ዘዳግም 26:18, 19
23 ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራችን መንገድ በማድረግ የይሖዋ ንጹሕ ሕዝብ የመሆን መብታችንን ለዘላለም እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንያዘው። ማንኛውንም ዓይነት አምላካዊ ያልሆነ ባሕርይና ዓለማዊ ምኞት ለማስወገድ ሁልጊዜ ንቁ እንሁን። በዚህ መንገድ ንጹሕ ሆነን እንቀጥላለን፤ እንዲሁም ይሖዋ ዛሬ እያሠራው ያለውን ትልቅ ሥራ ለመሥራት ሊጠቀምብን የሚያስችል አቋም ይኖረናል።
ታስታውሳለህን?
◻ ለአምላክ ያደሩ መሆን ለሁሉም ነገር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የሸመገሉ ወንዶችና ሴቶች ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራቸው መንገድ አድርገው ሊከተሉት የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ምን ጤናማ ትምህርት ሰጥቷል?
◻ ጤናማውን ትምህርት የአኗኗራችን መንገድ ካደረግን ምን በረከትና መብት ልናገኝ እንችላለን?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛሬ ብዙዎች የቲቶ 2:2–4ን ምክር እየሠሩበት ነው