“የአምላክን ቤት” በአድናቆት መመልከት
“እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም [በአድናቆት አዓት] እመለከት ዘንድ።”—መዝሙር 27:4
አድናቂው ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ቤተ መቅደስ በደስታ ስሜት ተመልክቶታል። በዛሬው ጊዜ ስላሉት የእውነተኛ አምልኮ ማዕከሎች ልክ እንደዚህ ይሰማሃልን? በመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚገኙት ከ95 የሚበልጡት የቤቴል ቤቶች በጊዜያችን ካለው የይሖዋ አምልኮ ጋር ቁርኝት ካላቸው ስፍራዎች መካከል ናቸው።
“በቤቴል አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ብዙ ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ በመጣ ጥልቅ ምስጋናና ከፍተኛ አድናቆት እሞላለሁ” በማለት በ1948 በጀርመን ቤቴል መሥራት የጀመረችው ሄልጋ ገልጻለች። ሄልጋ በ1993 የአገልግሎት ዓመት ‘ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ካዩት’ በዓለም ዙሪያ ካሉት 13,828 ደስተኛ የቤቴል ሠራተኞች አንዷ ናት። ቤቴል የሚለው ስም ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድን ነው? አምላክን በቤቴልም ሆነ ከቤቴል ውጪ የሚያገለግል እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ይህን ዝግጅት በአድናቆት ማየት የሚችለው እንዴት ነው?
ፍቅራዊ አድናቆት የሚገባው ስም
ቤትኤል የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የአምላክ ቤት” ማለት ስለሆነ “ቤቴል” እጅግ ተስማሚ የሆነ መጠሪያ ነው። (ዘፍጥረት 28:19፣ አዓት የግርጌ ማስታወሻ) አዎን፣ ቤቴል በአምላክ በደንብ የተደራጀን ቤት ወይም በአምላክ አማካኝነት ‘በጥበብ የተሠራን ቤት’ እና ፈቃዱ ማዕከላዊ ስፍራ የያዘበትን ቦታ ይመስላል። (ምሳሌ 24:3) “ልክ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ መኖር ማለት ነው። በደንብ የተደራጀ የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴ አለን” በማለት ሄርታ በአድናቆት ተናግራለች። እርሷም ሄልጋ ባለችበት ቤቴል ውስጥ ከ45 ዓመታት በላይ አገልግላለች። እያንዳንዱ የዚህ ትልቅ ቤተሰብ አባል ደስታ እንዲሰማውና ያለ ስጋት እንዲኖር የሚያደርግ የራሱ የሥራ ድርሻና ቦታ አለው። እያንዳንዱ መምሪያ ቤቴል ከሚለው ስም ጋር በሚስማማ መንገድ ጥሩ ዝግጅትና አደረጃጀት አለው። ይህም ለሰላም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ ውጤታማ የምሥራቹ ስብከት እንዲከናወን ያስችላል፤ እንዲሁም ጉባኤዎች “ለአምላክ ቤት” ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት እንዲያድርባቸው ጥሩ ምክንያት ይሆናቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 14:33, 40
እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው? ለምሳሌ ይህ መጽሔት የታተመው በቤቴል ማተሚያ ነው። አስቀድሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ለተነገሩት የመንግሥቱ መልዕክት ስብከትና ለመንፈሳዊ ምግብ ሥርጭት በፈቃደኛ ሠራተኞች የሚደገፈውንና በሁሉም የይሖዋ አምላኪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን ቤቴልን የመሰሉ ድርጅታዊ ዝግጅቶች የግድ ያስፈልጋሉ።—ማቴዎስ 24:14, 45
በዚህ ቦታ በየዕለቱ በሥራ ቀኖች የሚከናወነውን የሥራ እንቅስቃሴ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህን? ሄልጋ እና ሄርታ በሚኖሩበት ቤቴል ምንም እንኳ ከ800 በላይ ከሆኑት ቋሚ ሠራተኞች መካከል ብዙዎቹ ለቀኑ ለመዘጋጀት ከዚያ በፊት የሚነሡ ቢሆንም ከጠዋቱ 12:30 ላይ በሁሉም የመኖሪያ ሕንጻዎች ውስጥ አንድ ደወል ጣዕመ ዜማ ያለው ድምፅ ያሰማል። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባሉት ቀናት 1:00 ላይ ቤተሰቡ ለዕለት ጥቅስ ውይይት ወይም ለጠዋት አምልኮ በመመገቢያ አዳራሾች ውስጥ ይሰበሰባል። ከዚያ ቀጥሎ የተመጣጠነ ጥሩ ምግብ ይመገባሉ። እያንዳንዱ የሥራ ቀን በ2:00 ሰዓት ጀምሮ ከስምንት ሰዓታት በኋላ ይጠናቀቃል። በመሐሉ የሚኖረው ጊዜ የምሳ ሰዓት ብቻ ነው። (በአብዛኛው ቤተሰቡ ቅዳሜ የሚሠራው ግማሽ ቀን ነው።) በወጥ ቤት፣ በማተሚያ ክፍል፣ በልብስ ማጠቢያ ቤት፣ በቢሮዎች፣ በጥገና መስጫ ክፍሎች፣ በመጽሐፍ መጠረዣ ክፍሎችም ሆነ በሌላ የሥራ ክፍል ውስጥ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ።
ማታ ማታና በሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች የቤተሰቡ አባላት በአካባቢው ካሉ ጉባኤዎች ጋር በስብሰባዎችና ለሕዝብ በሚደረገው ስብከት ይገናኛሉ። ብዙዎቹ የቤቴል ወንድሞች በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎች ወይም ዲያቆናት ናቸው። የጉባኤው ምሥክሮች ይህን ትብብር ከልብ ያደንቃሉ። ሁለቱም ቡድኖች እርስ በእርስ በመከባበርና በመተሳሰብ እንደ አንድ አካል ሆነው ይሠራሉ። (ቆላስይስ 2:19) እያንዳንዱ የቤቴል ሠራተኛ “በአምላክ ቤት” ውስጥ ያለው ምድብ ሥራ ከሌሎች የሥራ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ እንደሚሰጠው ያውቃል። ይሁን እንጂ ለስብከት ያለው የጋለ ስሜትና በጉባኤው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከሚዛናዊ አመለካከት ጋር ተዳምረው የቤቴል ሠራተኛውን መንፈሳዊነት ያጠነክሩለታል፣ ደስታውን ይጨምሩለታል፣ እንዲሁም ይበልጥ ፍሬያማ የቤቴል ቤተሰብ አባል ያደርጉታል። በሙሉ ነፍስ ከማገልገል ጋር ዝምድና ያለው ስም ባለው “ቤት” ውስጥ ለሚሠራ ሰው እነዚህ ብቃቶች ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው!
በቤቴል አገልግሎት ስኬታማ መሆን
ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በቤቴል አገልግሎት ስኬታማ ለመሆን የረዳቸው ምንድን ነው? የፈረንሳይ ቤቴል ቤተሰብ አባላት ካሳለፉአቸው የብዙ ዓመታት ተሞክሮ በመነሣት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነው። በየትኛውም ቦታ ላይ እንድንሠራ ቢመድበን ጸንተን ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን ጠቅሞናል። በማኅበሩ ለሚሰጠን መመሪያ የትሕትና፣ የተገዢነትና የታዛዥነት መንፈስ ማሳየታችን ረድቶናል።” (ዴኒዝ) “ጳውሎስ በሮሜ 12:10 (የ1980 ትርጉም) ላይ ‘እርስ በእርሳችሁ ለመከባበር ተሽቀዳደሙ’ በማለት የጠቀሰውን መሠረታዊ ሥርዓት ማክበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ። ጥቅሱ የራሳችን የግል አመለካከት ተቀባይነት ካላገኘ ብለን ድርቅ ከማለት ይልቅ ለሌሎች አመለካከት ቦታ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል። በሌላ አነጋገር በሌሎች ላይ የበላይ ለመሆን መፈለግ የለብንም ማለት ነው።” (ዦን ዣክ) “ነገሮችን ከሥጋዊና ከሰብአዊ አመለካከት አንጻር ካየን ለቤቴል አገልግሎት ያለን አክብሮት ሊጠፋ ይችላል” በማለት ባርባራ ተናግራለች፤ “ምክንያቱም ይህ አመለካከት ድርጅቱን የሚመራው ይሖዋ የመሆኑን ሐቅ እንድንዘነጋ ሊያደርገን ይችላል። በሌሎች አለፍጽምና የምንደናቀፍ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ አክብሮት ሊጠፋ ይችላል።”
በቤቴል ያለው ማንኛውም ሰው ፍጹም አይደለም። ስለዚህ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በጥንቃቄ ማሰብ ይገባዋል። ወጣቶች ወይም በቅርብ ጊዜ ቤቴል የገቡ ሰዎች ግንኙነታቸው ከእኩዮቻቸው ጋር ብቻ መወሰን የለበትም። አጉረምራሚዎች ወይም አፍራሽ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በቤቴልም ሆነ በጉባኤ የሚያንጹ ጓደኞች ሊሆኑ አይችሉም። በሌላ በኩል ግን በያዕቆብ 3:17 ላይ እንደተገለጸው “ላይኛይቱን ጥበብ” መከተል በረከቶችን ያስገኛል። እርሷም “በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፣ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።” እነዚህን የመሰሉ ባሕርያት ከመቻልና ከደግነት ባሕርያት ጋር ጎን ለጎን “በአምላክ ቤት ውስጥ” የሚንጸባረቁና አንድ ሰው በዚህ ቦታ ተደስቶና ተነቃቅቶ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው። ቤቴልን የጎበኙ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎች እንኳ ብዙውን ጊዜ የሠራተኞቹን ጥሩ ጠባይ፣ ወዳጃዊ አቀባበልና የደስተኝነት መንፈስ በመመልከት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ከ70 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆናትና ከ1956 ጀምሮ የጀርመን ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆና የቆየችው አኒ ለማገልገል ያላትን የዝግጁነት መንፈስ እንዴት ጠብቃ እንደቆየች ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “መንፈሳዊ አቋሜን ለመጠበቅ ስል ማኅበሩ የሚያወጣቸውን ጹሑፎች በየጊዜው ለማንበብ፣ በስብሰባዎች ዘወትር ለመገኘትና በስብከቱ ሥራ ዘወትር ለመሳተፍ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ። በተጨማሪም በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ አብዛኛውን ጊዜ በአሳንሰር (በሊፍት) ከመጠቀም በመቆጠብና የቻልኩትን ያህል በተለይ በመስክ አገልግሎት ብዙ ጊዜ በእግር በመጓዝ ጥሩ አካላዊ አቋም እንዲኖረኝ እጥራለሁ።”
በቤቴል ኑሮ ብዙ ተሞክሮ ያላቸው ብዙዎች በአኒ አባባል ይስማማሉ። መማራቸውን አቋርጠው አያውቁም፤ ሥራቸውንም ፈጽሞ አላቋረጡም። አካላዊ ጤንነት ለማግኘት በቂ እንቅልፍ መውሰድና የተወሰነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም በአመጋገብና በሚጠጡት ነገር ረገድ ልከኛነትን ማሳየት ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የግል ጸሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ቸል አይሉም።
በቤቴል ለሚከናወነው ቅዱስ አገልግሎት ከፍተኛ አክብሮት ማሳየት
“የምትሠራው በየትኛው ክፍል ውስጥ ነው?” የሚለው ጥያቄ ለቤቴል አባላት የሚቀርብ የተለመደ ጥያቄ ነው። የሥራ ምድቦች የተለያዩ ናቸው፤ ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው ለእያንዳንዱ ሥራ ከፍተኛ አክብሮት ሊኖረው ይገባል። ለምን? ምክንያቱም መንፈሳዊ ምግብ የሚያትም መሣሪያን ማንቀሳቀስም ሆነ ልብሶችን ማጠብ፣ ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰልና የጽዳት ሥራ ማከናወን ወይም የቢሮ ሥራን ማካሄድ ሁሉም ሥራዎች ቅዱስ አገልግሎት ናቸው። ከላይ እንደተጠቀሰው ክርስቲያኖች አንዱን ከአንዱ አያበላልጡም። በቤተ መቅደሱ አደባባዮችና መመገቢያ አዳራሾች ውስጥ በካህናትና በሌዋውያን ይከናወኑ የነበሩት አስፈላጊ ሥራዎች ሁሉ ለይሖዋ የሚቀርቡ ቅዱስ አገልግሎቶች ተደርገው ይታዩ እንደነበር አስታውስ። ይህም እንስሳትን ማረድንና ለመሥዋዕት ማዘጋጀትን፣ መብራቶች ዘይት ሲጨርሱ ዘይት መሙላትን፣ አልፎ ተርፎም ማጽዳትንና የጥበቃ ሥራን ያጠቃልላል። ልክ እንደዚሁም በቤቴል ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሥራ በ“ጌታ ሥራ” እርካታን የሚያስገኝና ጠቃሚ ነው። በመሆኑም የቤቴል አገልግሎት ልዩ መብት ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:58
“የአምላክን ቤት” በአድናቆት እንዳንመለከት ዕንቅፋት ሊሆንብን የሚችል አንድ ጠባይ በአጭሩ ተመልከት። በቤቴል ውስጥም ሆነ ከቤቴል ውጪ ያሉ ክርስቲያኖች ‘አጥንትን ከሚያነቅዙት’ ከቅናትና ከምቀኝነት ራሳቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል። (ምሳሌ 14:30) ማንኛውም ሰው የቤቴል ሠራተኞች ባሉአቸው የአገልግሎት መብቶች የሚቀናበት ምክንያት የለም። ከዚህም በተጨማሪ በቤቴል ቤተሰብ ውስጥ ከሥጋ ሥራዎች አንዱ የሆነው ምቀኝነት ቦታ የለውም። ሌሎች የተሻሉ መብቶችን ሲያገኙ እርሱ ግን ቸል እንደተባለ ሆኖ የሚሰማው ሰው የሚሰጠው ጥሩ ምክር በትህትና ታገስ የሚል ነው። ከዚህም ሌላ በገንዘብ አቅም በኩል በፊተኛው ኑሮአቸው ትልቅ ልዩነት የነበራቸው ሰዎች በቤቴል ውስጥ አንድ ላይ ይኖራሉ። አንድ ሰው ያለበትን ሁኔታ “ከሌሎች ጋር በማወዳደር” የሚመለከት ከሆነ ትርፉ ብስጭት ብቻ ይሆናል! ብዙዎች ባላቸው “ምግብና ልብስ” መርካታቸው “በአምላክ ቤት” ውስጥ ለአያሌ አሥርተ ዓመታት ታማኞች ሆነው እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።—ገላትያ 5:20, 26፤ 6:4 የ1980 ትርጉም፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8
የይሖዋ ምሥክሮችና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ያለ ክፍያ ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ መንገድ አምላክንና ጎረቤትን ከማፍቀር በመነሣት በቤቴል ውስጥ በሚከናወነው ሥራ ትልቅ ጥቅም አግኝተዋል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የቤቴል ቤቶችና ማተሚያዎች ለቲኦክራሲያዊ ሥራ ግልጋሎት እንደሚሰጡት እንደ ሌሎቹ መገልገያዎች ሁሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት፣ የእስራኤል አለቆችና የጦር መሪዎች ሁሉ እኛም ለማኅበሩ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት ለ“አምላክ ቤት” ያለንን አክብሮትና አድናቆት ማሳየት እንችላለን። (1 ዜና መዋዕል 29:3–7) በቤቴል ውስጥ ‘ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማየት’ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ደግሞ እስቲ እንመልከት።
“በአምላክ ቤት” ውስጥ ያሉ በረከቶች
በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ በምትገኝበት ጊዜ ደስተኛ በሆኑ የይሖዋ አምላኪዎች ስትከበብ ጥልቅ የእርካታ ስሜት ተሰምቶሃልን? አንድ የቤቴል ሠራተኛ በየቀኑ ብዛት ያለው ቁጥር ባላቸው ወንድሞች መካከል ይሖዋን የማገልገል መብት ሲያገኝ የሚኖረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል እስቲ ገምት! (መዝሙር 26:12) ይህ ሁኔታ ለመንፈሳዊ እድገት እንዴት ያሉ ግሩም አጋጣሚዎችን ያስገኛል! አንድ ወንድም በቤቴል ውስጥ በአንድ ዓመት ያገኘው ሥልጠና በሦስት ዓመት ውስጥ በሌላ ቦታ ካገኘው እውቀት በበለጠ አቋሙን ለማስተካከል አንደረዳው አስተውሏል። ለምን? ምክንያቱም በሌላ በየትም ቦታ የብዙ የበሰሉ ክርስቲያናዊ አቋሞችን እምነት የመመልከትና የመምሰል አጋጣሚ አልነበረውም።—ምሳሌ 13:20
አንድ ሰው በቤቴል ውስጥ ብዙ ልምድ ባካበቱ መካሪዎች ተከቦ ይኖራል ማለት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በጠዋት አምልኮ ላይና በቤቴል ቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የሚሰጡትን ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸውን ሐሳቦች የመስማት እንዲሁም ሰኞ ማታ የሚቀርበውን ንግግር በማዳመጥ ጥቅም ይገኛል። አዲስ ገቢዎች በቤቴል አዲስ ገቢዎች ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ በመጀመሪያዎቹ 12 ወሮች ውስጥም መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር እንዲያነቡ ይጠየቃሉ።
ከሌሎች አገሮች የሚመጡ ጎብኚዎች የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶችና ተሞክሮዎችም ተጨማሪ ማበረታቻ ይሰጣሉ። ከዚህም በላይ የአስተዳደር አካል አባላት ወይም የእነርሱ ተወካዮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ይጎበኛሉ። “ብዙ ሥራ ቢኖራቸውም እንኳን” ትላለች ሄልጋ “እነዚህ ወንድሞች ሁልጊዜ ወዳጃዊ ቃል ጣል ለማድረግ ወይም ፈገግታ ለማሳየት ጊዜ ያገኛሉ።” የእንደነዚህ ዓይነቶቹን ታማኝ ሆነው የዘለቁ ሰዎች የሚያነቃቃና ልከኛ ጠባይ እንዲሁም ትሕትና በግለሰብ ደረጃ ማየቱ ምንኛ የሚያበረታታ ነው!
አንድ ሰው በተለይ በቤቴል ውስጥ የአምላክ ድርጅት እንዴት እንደሚንቀሳቀስና ቅዱስ መንፈሱ ፈቃደኛ የሆኑ ልቦችንና እጆችን እንዴት ለሥራ እንደሚያነሳሳቸው በቅርብ መመልከት ይችላል። “አንድ ሰው በቤቴል ውስጥ ‘ሥራውን ወደሚያንቀሳቅሰው እምብርት’ በጣም እንደቀረበ ሆኖ ይሰማዋል” በማለት አንድ ከ1949 ጀምሮ ፈረንሳይ ውስጥ በሚገኘው ቤቴል ያገለገለ ወንድም ገልጿል። በመቀጠልም እንዲህ አለ፦ “ለእኔ ቤቴል ለይሖዋ አገልግሎት ከፍተኛውን ጊዜና ጉልበት እንዳውልና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እንዳገለግል የረዳኝ የአገልግሎት ዓይነት ነው ብዬ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።” በሕይወት ውስጥ ያለን እውነተኛ ዓላማ ይህ አይደለምን? ዓላማችን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አይደለምን? አንድ ሰው በቤቴል ውስጥ ‘ቀኑን በሙሉ ምስጋና ማቅረብ’ ይችላል። እንዴት ያለ በረከት ነው!—መዝሙር 44:8
አንድ በቤቴል ቤት ውስጥ የሚሠራ ሰው ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማየት እንደሚችልና የተትረፈረፉ በረከቶችን እንደሚያገኝ ተገንዝበናል። (ዕብራውያን 6:10) “በአምላክ ቤት” ማገልገል ለአንተ የሚስማማ ሥራ ነውን? ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ቢያንስ ቢያንስ 19 ዓመት የሞላቸው፣ ጥሩ መንፈሳዊና አካላዊ ጤንነት ያላቸውና ልክ እንደ ጢሞቴዎስ ‘በወንድሞች የተመሠከረላቸው’ በቤቴል ለማገልገል ሊያመለክቱ ይችላሉ። (ሥራ 16:2) ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ብዙ ሰዎች የቤቴል አገልግሎትን የዕድሜ ልክ ሥራቸው አድርገውታል። ‘በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በይሖዋ ቤት ለመኖር’ መዝሙራዊው ያደረበት ጉጉት ለእነርሱ እውን ሆኖላቸዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን በፈቃደኝነትና በደስታ የሚያከናውኑት በቤቴል የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ለሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ከፍተኛ አክብሮት አላቸው። ይሖዋን የምናገለግለው በቤቴልም ሆነ በሌላ በማንኛውም ቦታ እያንዳንዳችን እንደ ንጉሥ ዳዊት የ“አምላክን ቤት” በአድናቆት ወይም በደስታ ስሜት የምናይበት ጥሩ ምክንያት አለን።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እነዚህ ክርስቲያኖች በጀርመን ቤቴል በቅዱስ አገልግሎት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በማገልገል ደስታ አግኝተዋል