የምትመገበው ከየትኛው ማዕድ ነው?
“ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።” —1 ቆሮንቶስ 10:21
1. በፊታችን ምን ማዕዶች ቀርበዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ እነርሱን አስመልክቶ የሰጠው ማስጠንቀቂያስ ምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በሰው ዘር ፊት ሁለት ምሳሌያዊ ማዕዶች እንደቀረቡ ያሳያሉ። ሁለቱም ማዕዶች በላያቸው ላይ በተቀመጠው ምሳሌያዊ የምግብ ዓይነት ተለይተው ይታወቃሉ፤ ሁላችንም ከአንደኛው አለዚያም ከሌላኛው እየተመገብን ነው። ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ከእሱ ማዕድ እየተመገብን በሌላ በኩል ደግሞ ከአጋንንት ማዕድ ለመቀላወጥ አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።”—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21
2. (ሀ) በጥንት እስራኤላውያን ዘመን ምን ዓይነት የይሖዋ ማዕድ ነበር? በአንድ ማዕድ ይቀርቡ ከነበሩት መሥዋዕቶች የሚካፈሉት እነማን ነበሩ? (ለ) በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ማዕድ መመገብ ማለት ምን ማለት ነው?
2 የጳውሎስ ቃላት ጥንት እስራኤላውያን የይሖዋ ሕግ በሚያዘው መሠረት ያቀርቡት የነበረውን ከይሖዋ ጋር በአንድ ማዕድ እንዲካፈሉ ያደርጓቸው የነበሩትን የኅብረት መሥዋዕቶች ያስታውሱናል። የአምላክ መሠዊያ ማዕድ ተብሎ ይጠራ ነበር፤ መሥዋዕት የሚሆነውን እንስሳ ይዞ የሚመጣው ሰው ደግሞ ከይሖዋና ከካህናቱ ጋር በአንድ ማዕድ ተካፍሏል ይባል ነበር። እንዴት? አንደኛ፣ ደሙ በመሠዊያው ላይ ስለሚረጭና ስቡ ከመሠዊያው ሥር በእሳት ስለሚቃጠል ይሖዋ ከመሥዋዕቱ ይካፈላል። ሁለተኛ፣ ካህኑ (እና ቤተሰቡ) ለመሥዋዕት የቀረበውን እንስሳ የተጠበሰ ፍርምባና ቀኝ ቅልጥሙን ስለሚበሉ እርሱም በመሥዋዕቱ ተካፋይ ይሆናል። ሦስተኛ፣ መሥዋዕቱን ያቀረበው ሰው የተቀሩትን ብልቶች በመመገብ ከመሥዋዕቱ ይካፈላል። (ዘሌዋውያን 7:11–36) በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ማዕድ መብላት ማለት በኢየሱስና በሐዋርያቱ ምሳሌ እንደተንጸባረቀው እርሱ የሚፈልገውን የአምልኮ ዓይነት መስጠት አለብን ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን መንፈሳዊ ምግብ መመገብ አለብን። በይሖዋ ማዕድ ከእርሱ ጋር የመካፈል ልዩ አጋጣሚ ያገኙ እስራኤላውያን በአጋንንት ማዕድ ላይ ለእነርሱ መሥዋዕቶችን እንዳያቀረቡ ተከልክለው ነበር። መንፈሳዊ እስራኤላውያንና ባልደረቦቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” በዚሁ መለኮታዊ እገዳ ሥር ናቸው።—ዮሐንስ 10:16
3. በጊዜያችን አንድ ሰው ከአጋንንት ማዕድ በመመገብ ጥፋተኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
3 በጊዜያችን አንድ ሰው ከአጋንንት ማዕድ በመመገብ ጥፋተኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋን የሚጻረርን የማንኛውም ነገር ዓላማ ለማሳካት ተባባሪ በመሆን ነው። የአጋንንት ማዕድ እኛን ለማሳትና ከይሖዋ ዘወር ለማድረግ ታስበው የተዘጋጁትን አጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳዎች በሙሉ ያካተተ ነው። ልቡንና አእምሮውን እንዲህ በመሰለ መርዝ ለመሙላት የሚፈልግ ማን ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ አብዛኛዎቹ ሰዎች ለሚሠዉላቸው የጦርነትና የሀብት አማልክት በሚቀርቡት መሥዋዕቶች ለመካፈል አይከጅሉም።—ማቴዎስ 6:24
“ከአጋንንት ማዕድ” መራቅ
4. በሁላችንም ፊት የሚደቀነው ጥያቄ ምንድን ነው? እያወቅን ከአጋንንት ማዕድ መመገብ የማንፈልገውስ ለምንድን ነው?
4 በሁላችንም ፊት የሚደቀነው ጥያቄ የምመገበው ከየትኛው ማዕድ ነው? የሚል ነው። ከአንደኛው ማዕድ መመገቡ የማይቀር ነገር ነው። (ከማቴዎስ 12:30 ጋር አወዳድር።) እያወቅን ከአጋንንት ማዕድ ለመመገብ አንፈልግም። ይህን ማድረጉ እርሱ ብቻ እውነተኛና ሕያው አምላክ የሆነውን የይሖዋን ሞገስ ያሳጣናል። በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ ማዕድ ከሚቀርበው ምግብ ብቻ መመገብ ደስታ ወደሞላበት የዘላለም ሕይወት ይመራናል! (ዮሐንስ 17:3) ሰው ኑሮውን ይመስላል የሚል አባባል አለ። እንግዲያው ጥሩ አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነት እንዲኖረው የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚመገበውን ምግብ መምረጥ አለበት። የኬሚካል ማጣፈጫዎች ተጨምረውበት ጣፋጭ ሆኖ የተዘጋጀ ቢሆንም እንኳን አሸርባሸር የሆነ ምግብ አካላዊ ጤንነታችንን ለመጠበቅ እንደማይረዳ ሁሉ አጋንንታዊ ሐሳቦች የተቀላቀሉበት የዚህ ዓለም ፕሮፓጋንዳም አእምሮአችንን የሚበክል ምሳሌያዊ አሸርባሸር የሆነ ምግብ ነው።
5. በዛሬው ጊዜ አጋንንታዊ ትምህርቶችን ከመቅሰም መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ሰዎች በ“አጋንንት ትምህርት” እንደሚታለሉ ተንብዮአል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) እነዚህ አጋንንታዊ ትምህርቶች የሚገኙት በሐሰት ሃይማኖታዊ እምነቶች ውስጥ ብቻ አይደለም፤ በሌሎች መንገዶችም በስፋት ይነገራሉ። ለምሳሌ ያህል እኛና ልጆቻችን ምን ዓይነት መጽሐፎችንና መጽሔቶችን እንደምናነብ፣ ምን ዓይነት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እንደምንመለከትና ምን ዓይነት ቲያትሮችንና ፊልሞችን እንደምናይ አውጥተን አውርደን ማመዛዘን ይገባናል። (ምሳሌ 14:15) ለመዝናናት ብለን ልበ ወለድ መጻሕፍት የምናነብ ከሆነ ትርጉም የለሽ ዓመፅን፣ ልቅ የጾታ ግንኙነትን ወይም አስማታዊ ድርጊቶችን ያንጸባርቃልን? ትምህርት ለማግኘት ብለን ልበ ወለድ ያልሆነ መጽሐፍን የምናነብ ከሆነ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት” ያልሆነን ፍልስፍና ወይም አኗኗር የሚያብራራ ነውን? (ቆላስይስ 2:8) ሊጨበጡ የማይችሉ ግምታዊ ሐሳቦችን ያቀርባልን? ወይም ደግሞ በዓለማዊ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍን በይፋ ያበረታታልን? ሰዎች ባለጸጋ ለመሆን ቆርጠው እንዲነሡ የሚገፋፋ ነውን? (1 ጢሞቴዎስ 6:9) ከክርስቶስ ትምህርቶች የተለዩ የሚከፋፍሉ ትምህርቶችን በረቀቀ መንገድ የሚያቀርብ ጽሑፍ ነውን? መልሱ አዎን፣ የሚል ከሆነና ማንበባችንን ወይም መመልከታችንን ከቀጠልን ራሳችንን ከአጋንንት ማዕድ ለመመገብ አደጋ እናጋልጣለን። በዛሬው ጊዜ ከፍተኛ እውቀት የሚገኝባቸውና በጣም ወቅታዊ የሆኑ የሚመስሉ ዓለማዊ ፍልስፍናዎችን የሚያራምዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎች አሉ። (መክብብ 12:12) ይሁን እንጂ እውነት ለመናገር ከዚህ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ አንዱም ቢሆን አዲስ አይደለም። ለአንድ ሰው የሚጠቅምና የተሻለ ነገርን የሚያስገኝም አይደለም። ሰይጣን ሔዋን ለእርሷ የሚበጅ ነገር እንደፈጸመች አድርጎ ዓላማውን ለማሳካት ካቀረበላት ሐሳብ የሚለይ አይደለም።—2 ቆሮንቶስ 11:3
6. ሰይጣን አሸርባሸር የሆነውን አጋንንታዊ ምግቡን እንድንቀምስ ሲጋብዘን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
6 እንግዲያው ሰይጣን አጋንንታዊ የሆነ አሸርባሸር ምግቡን እንድንቀምስ ሲጋብዘን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ድንጋዮቹን ወደ እንጀራ እንዲለውጥ በሰይጣን በተፈተነበት ጊዜ ኢየሱስ የሰጠውን ዓይነት መልስ መስጠት አለብን። ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” በማለት መልሷል። ዲያብሎስ ኢየሱስን ወድቀህ ብትሰግድልኝ “የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም” እሰጥሃለሁ ባለው ጊዜ ኢየሱስ “ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት መልስ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 4:3, 4, 8–10
7. ምንም ጉዳት ሳይደርስብን ከይሖዋ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ መመገብ እንችላለን ብለን ብናስብ ራሳችንን የምናታልለው ለምንድን ነው?
7 የይሖዋ ማዕድና በአጋንንታዊ ጠላቶቹ የተሰናዳው ማዕድ ፈጽሞ ዕርቅ ሊፈጥሩ አይችሉም! ቀደም ሲል ይህን ለማድረግ ተሞክሮ ነበር። በነቢዩ ኤልያስ ዘመን የነበሩትን የጥንት እስራኤላውያን አስታውስ። ሕዝቡ ይሖዋን እናመልካለን ይሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ ብልጽግናን ያስገኛሉ የሚሏቸውን እንደ በኣል ያሉ አማልክትን ያምኑ ነበር። ኤልያስ ሕዝቡን ቀርቦ በማናገር እንዲህ አላቸው፦ “እስከ መቼ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ።” እስራኤላውያን “አንዴ በአንደኛው እግራቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ በሌላኛው እግራቸው” ይውተረተሩ እንደነበረ አያጠራጥርም። (1 ነገሥት 18:21 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ኤልያስ የበኣል ካህናት የጣዖታቸውን አምላክነት እንዲያረጋግጡ ፈተና አቀረበላቸው። በመሥዋዕት ላይ ከሰማይ እሳትን ማውረድ የሚችለው አምላክ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል ተባለ። ብዙ ጥረት ቢያደርጉም የበኣል ካህናት አልሰመረላቸውም። ከዚያም ኤልያስ “አንተ፣ አቤቱ፣ አምላክ እንደ ሆንህ . . . ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ” የሚል ጸሎት ብቻ አቀረበ። ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ከይሖዋ ዘንድ ወርዶ ሙሉ በሙሉ በውኃ የረጠበውን የእንስሳ መሥዋዕት በላው። የይሖዋን አምላክነት በሚያሳየው አሳማኝ ትዕይንት የተነኩት ሰዎች ኤልያስን በመታዘዝ የበኣልን 450 ነቢያት በሙሉ ገደሏቸው። (1 ነገሥት 18:24–40) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ እስከ አሁን አላደረግነው ከሆነ ይሖዋን እንደ እውነተኛ አምላክ አድርገን ማወቅና ያለምንም ማመንታት ከእርሱ ማዕድ ብቻ ለመመገብ ወደ ማዕዱ መቅረብ አለብን።
‘ታማኙ ባሪያ’ የይሖዋን ማዕድ ያሰናዳል
8. ኢየሱስ በሚገኝበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን በመንፈሳዊ ለመመገብ በምን ዓይነት ባሪያ እንደሚጠቀም ተንብዮ ነበር? የባሪያው መለያስ ምንድን ነው?
8 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ መገኘት ጊዜ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያቀርብ ተንብዮ ነበር። “ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴዎስ 24:45–47) ይህ ባሪያ የትኛውም አንድ ግለሰብ እንዳልሆነ ተረጋግጧል፤ ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን የወሰኑ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ነው። ይህ ቡድን ለቅቡዓን ቀሪዎችና ለ“እጅግ ብዙ ሰዎች” በይሖዋ ማዕድ ላይ እጅግ ግሩም የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል። በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሚልዮን በላይ የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች የይሖዋ አምላክን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትና ቅዱስ ስሙን የሚያስቀድስበትን መንግሥት በመደገፍ ከቅቡዓን ቀሪዎች ጎን ቆመዋል።—ራእይ 7:9–17
9. የባሪያው ክፍል ለይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በምን መሣሪያ ሲጠቀም ቆይቷል? መንፈሳዊ ድግሳቸውስ በትንቢት የተገለጸው እንዴት ነው?
9 ይህ የታማኝ ባሪያ ቡድን የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበርን ለይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ አስፈላጊውን መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ሲጠቀምበት ቆይቷል። ሕዝበ ክርስትናና የተቀሩት የዚህ የነገሮች ሥርዓት ክፍሎች ሕይወት ሰጪ የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ አጥተው ሲራቡ የይሖዋ ሕዝብ ግን በተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እየተደሰቱ ነው። (አሞፅ 8:11) ይህም የኢሳይያስ 25:6 ትንቢት ፍጻሜ ነው:– “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።” ቁጥር 7 እና 8 እንደሚያሳዩት ይህ ግብዣ ለዘላለም ይቀጥላል። በአሁኑ ጊዜ በሚታየው የአምላክ ድርጅት ውስጥ ላሉ ሁሉ ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው! ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑ እንዴት ያለ በረከት ነው!
በአጋንንት ማዕድ ላይ ከሚቀርበው መርዘኛ ምግብ ተጠበቅ
10. (ሀ) በክፉው ባሪያ ክፍል የሚቀርበው ምግብ ምን ዓይነት ነው? እንዲህ የሚያደርጉትስ ለምንድን ነው? (ለ) የክፉው ባሪያ ቡድን ቀደም ሲል አብረዋቸው ሲያገለግሉ የነበሩትን ባሪያዎች ምን ያደርጉባቸዋል?
10 በአጋንንት ማዕድ ላይ የሚቀርበው ምግብ መርዘኛ ነው። ለምሳሌ ያህል በክፉው ባሪያ ቡድንና በከሃዲዎች የሚከፋፈለውን ምግብ ተመልከት። መንፈሳዊነትን አያፋፋም ወይም አይገነባም። ለጤንነት አይስማማም። ከሐዲዎች ከይሖዋ ማዕድ መመገባቸውን አቁመዋልና ተስማሚ ሊሆን አይችልም። በዚህም ምክንያት ከዚህ በፊት አዳብረውት የነበረው ማንኛውም የአዲሱ ሰውነት ባሕርይ ተለይቷቸዋል። የሚያንቀሳቅሳቸው መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ጥላቻ የተሞላበት ብሽቀት ነው። ኢየሱስ እንደተነበየው ዓላማቸው አንድ ነው፤ ይኸውም ቀደም ሲል አብረዋቸው የነበሩትን ባሪያዎች መምታት ነው።—ማቴዎስ 24:48, 49
11. ሲ ቲ ራስል አንድ ሰው ስለሚመርጠው መንፈሳዊ ምግብ ምን ብሎ ጻፈ? የአምላክን ማዕድ የተዉትን ሰዎች የገለጻቸውስ እንዴት ነው?
11 ለምሳሌ ያህል ከብዙ ዓመታት በፊት ማለትም በ1909 በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ሲ ቲ ራስል የይሖዋን ማዕድ ጥለው ስለሄዱትና በኋላም ቀደም ሲል አብረዋቸው ያገለግሉ የነበሩትን ባሪያዎች ማንገላታት ስለጀመሩት ሰዎች ጽፎ ነበር። የጥቅምት 1, 1909 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል:– “ራሳቸውን ከማኅበሩና ከሥራው ያገለሉ ሰዎች በእምነትና በመንፈስ ጸጋ ከመበልጸግና ሌሎችን ከማነጽ ይልቅ ተገላቢጦሽ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል። ከዚህ በፊት የቆሙለትን ዓላማ ለመጉዳት ሞክረዋል። በኃይልም ይሁን በትንሹ እየጮኹ ቀስ በቀስ ከስመዋል። የሚጎዱት ራሳቸውንና እንዲህ ዓይነት የጠበኝነት መንፈስ ያላቸውን ሌሎች ሰዎች ብቻ ነው። . . . አንዳንዶች በሌሎች ማዕዶች ላይ ጥሩ ወይም የተሻለ ምግብ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ወይም ራሳቸው ጥሩ ወይም የተሻለ ምግብ ማዘጋጀት እንችላለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ የራሳቸውን መንገድ ይከተሉ። . . . ነገር ግን ሌሎች የትም ሆነ የት ለራሳቸው ደስታ የሚያሰጥ ምግብና ብርሃን ለማግኘት እንዲሄዱ ብንተዋቸውም የኛ ተቃሚዎች የሆኑት ሰዎች የሚከተሉት መንገድ እጅግ የተለየ መሆኑ ያስገርማል። በዓለም እንደተለመደው ጨዋነት ‘ለእኔ የሚሆን የተሻለ ነገር አግኝቻለሁ፤ ደህና ሰንበቱ!’ ከማለት ይልቅ እነዚህ ሰዎች ‘የሰይጣንና የሥጋ ሥራ’ የሆኑትን ቁጣን፣ ተንኮልን፣ ጥላቻንና ጠብን የዓለም ሰዎች እንኳ ሲያደርጉት አይተነው በማናውቀው መልኩ ያንጸባርቃሉ። እብደትና ሰይጣናዊ የአእምሮ ቀውስ የተጠናወታቸው ይመስላሉ። አንዳንዶቹ ራሳቸው ይመቱንና የተማታነው እኛ እንደሆንን አድርገው ይናገራሉ። ተራ የሆኑ ውሸቶችን ለመናገርና ለመጻፍ እንዲሁም ወራዳ ድርጊት በመፈጸም የሥነ ምግባር አቋማቸውን ዝቅ ለማድረግ ወደኋላ አይሉም።”
12. (ሀ) ከሐዲዎች አብረዋቸው ሲያገለግሉ የነበሩትን ባሪያዎች የሚደበድቡት እንዴት ነው? (ለ) በጉጉት በመነሳሳት የከሐዲዎችን መጣጥፎች መመገቡ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
12 አዎን፣ ከሐዲዎች የተዛባ ሐሳብን፣ ሐሰት የተቀላቀለባቸው እውነቶችንና ዓይን ያወጣ ውሸት የያዙ ጽሑፎችን ያትማሉ። አልፎ ተርፎም ያልተጠነቀቀውን ለማጥመድ በምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የሆነ ያልሆነውን ይቀባጥራሉ። በመሆኑም ለማወቅ ያለን ጉጉት እንዲህ ዓይነቶቹን ጽሑፎች ለመመገብ ወይም የዘለፋ ንግግራቸውን ለመስማት እንዲገፋፋን መፍቀዱ አደገኛ ነገር ነው! በግለሰብ ደረጃ ለራሳችን አደገኛ እንደሆነ አድርገን ባናስበውም እንኳ አደገኛ መሆኑ አይቀርም። ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ የከሐዲያን ጽሑፎች የሐሰት ትምህርቶችን “በመልካም . . . ንግግር” እና “አስመሳይ በሆኑ ቃላት” ያቀርባሉ። (ሮሜ 16:17, 18፤ 2 ጴጥሮስ 2:3 አዓት) ከዚህ ሌላ ከአጋንንት ማዕድ ምን ትጠብቃላችሁ? ምንም እንኳን ከሐዲዎቹ አንዳንድ እውነት የሆኑ ነገሮችን ሊያቀርቡ ቢችሉም ብዙውን ጊዜ ዓላማቸው ሌሎችን ከይሖዋ ማዕድ ለማራቅ ስለሆነ እነዚህን ነገሮች አዛብተው ወይም አለቦታቸው ይጠቅሷቸዋል። መጣጥፎቻቸው በሙሉ እንዲሁ በትችትና በማንቋሸሽ የተሞሉ ናቸው! አንድም የሚያንጽ ነገር የለባቸውም።
13, 14. የከሐዲዎችና የፕሮፓጋንዳቸው ፍሬዎች ምንድን ናቸው?
13 ኢየሱስ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:16) ታዲያ የከሐዲዎችና የጽሑፎቻቸው ፍሬዎች ምንድን ናቸው? ፕሮፓጋንዳቸውን አራት ነገሮች ለይተው ያመለክቷቸዋል። (1) አፈ ጮሌነት። ኤፌሶን 4:14 ‘በሽንገላ ያታልላሉ’ ይላል። (2) በእውቀት መታበይ። (3) የፍቅር ማጣት። (4) በተለያየ መንገድ ሐቁን መደበቅ። በአጋንንት ማዕድ ላይ የሚቀርበው ምግብ የሚዘጋጀው ከእነዚህ ነገሮች ነው። ይህ ሁሉ የይሖዋን ሕዝብ እምነት ለማዳከም የተወጠነ ሴራ ነው።
14 ሌላ ገጽታም አለ። ከሐዲዎቹ የተመለሱት ወደ ምን ነገሮች ነው? በአብዛኛው ወደ ጨለማዋ ሕዝበ ክርስትናና ሁሉም ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለውን ወደመሰሉ መሠረተ ትምህርቶቿ ተመልሰው ገብተዋል። ከዚህም በላይ አብዛኛዎቹ ደምን፣ ገለልተኝነትንና ስለ አምላክ መንግሥት የመመሥከርን አስፈላጊነት በተመለከተ የጸና ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም መያዛቸው ያከተመለት ነገር ሆኗል። እኛ ግን ከታላቂቱ ባቢሎን ጨለማ ወጥተናል፤ ዳግም ወደ እርሱ መመለስ አንፈልግም። (ራእይ 18:2, 4) ከይሖዋ ጎን በታማኝነት የቆምን አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን በአሁኑ ጊዜ “ጤናማ ቃል” እንድንመገብ የሚረዱንን ሰዎች በቃላት የሚደበድቡት የይሖዋን ማዕድ አንፈልግም ያሉ ሰዎች የሚያስተላልፉትን ፕሮፓጋንዳ በጨረፍታ እንኳ ለመመልከት የምንፈልግበት ምን ምክንያት አለ?—2 ጢሞቴዎስ 1:13
15. ከሐዲዎች የሚያቀርቡትን ክስ ስንሰማ የጥበብን መንገድ እንድንከተል የሚረዳን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ነው?
15 አንዳንዶች ከሐዲዎች ስለሚያቀርቡት ክስ ማብራሪያ ለማግኘት ያጠያይቁ ይሆናል። እኛ ግን በዘዳግም 12:30, 31 ላይ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት በልባችን ውስጥ ማኖር ይገባናል። በዚህ ጥቅስ ላይ እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር በዚያ ይኖሩ ከነበሩት አረማውያን ከወሰዱ በኋላ ከምን ነገር መራቅ እንደሚኖርባቸው ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት አስጠንቅቋቸው ነበር። “በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፣ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትጠመድ:– እነዚህስ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩት እንዴት ነው? እንዲሁ ደግሞ እኔ አደርጋለሁ ብለህ ስለ አማልክቶቻቸው እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ። . . . አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ።” አዎን፣ ሰው አንድን ነገር ለማወቅ ያለው ጉጉት እንዴት እንደሚሠራ ይሖዋ አምላክ ያውቃል። ሔዋንንና የሎጥን ሚስት አስታውስ! (ሉቃስ 17:32፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14) ከሐዲዎች ለሚናገሩት ወይም ለሚያደርጉት ነገር ጆሮአችንን አንስጥ። ከዚህ ይልቅ ጊዜያችንን ሰዎችን በማነጽና በታማኝነት በይሖዋ ማዕድ በመመገብ እንጠቀምበት!
የይሖዋ ማዕድ ብቻ ይቀራል
16. (ሀ) ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን፣ አጋንንቱና የዓለም ሕዝቦች እየተመገቡበት ያለው ምሳሌያዊ ማዕድ ምን ይደርስበታል? (ለ) በአጋንንት ማዕድ ላይ መመገባቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች በሙሉ ምን ይደርስባቸዋል?
16 በቅርቡ ታላቁ መከራ በድንገት ይፈነዳል። ከዚያም ወደ መደምደሚያው ይኸውም “በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር” በፍጥነት ይገሰግሳል። (ራእይ 16:14, 16) ይህም ይሖዋ ይህን የነገሮች ሥርዓትና የዓለም ሕዝቦች እየተመገቡ ያሉበትን ምሳሌያዊ ማዕድ ሲያጠፋ ወደ ከፍተኛ መደምደሚያው ይደርሳል። በተጨማሪም ይሖዋ የማይታየውን የሰይጣን ዲያብሎስ ድርጅት በሙሉ ሥፍር ቁጥር ከሌላቸው አጋንንቶቹ ጋር አሽቀንጥሮ ይጥለዋል። በሰይጣን መንፈሳዊ ማዕድ ይኸውም በአጋንንት ማዕድ መመገባቸውን የቀጠሉ ሰዎች ወደዱም ጠሉም ቃል በቃል በምግቡ ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው ይደረጋል። የምግቡ ተቋዳሾች አይሆኑም፤ ከዚህ ይልቅ ለጥፋታቸው ራሳቸው መብል ሆነው ይቀርባሉ!—ሕዝቅኤል 39:4፤ ራእይ 19:17, 18 ተመልከት።
17. ከይሖዋ ማዕድ ብቻ የሚመገቡ ሰዎች ምን በረከቶችን ያገኛሉ?
17 ሌላው ሁሉ ሲጠፋ የይሖዋ ማዕድ ብቻ ይቀራል። በአድናቆት ከዚህ ማዕድ የሚመገቡ ሰዎች ከጥፋቱ ይተርፋሉ፤ እንዲሁም ከዚህ ማዕድ ለዘላለም የመመገብ መብት ያገኛሉ። የትኛውም ዓይነት የምግብ እጥረት ዳግመኛ አይፈታተናቸውም። (መዝሙር 67:6፤ 72:16) በፍጹም ጤንነት ይሖዋ አምላክን በገነት ውስጥ ያገለግሉታል! በመጨረሻም በደስታ የሚያፍለቀልቁት የራእይ 21:4 ቃላት ዕጹብ ድንቅ በሆነ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:– “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” ማብቂያ የሌለው መለኮታዊ ሞገስ ገነቲቷን ምድር በወረሱ የተቤዡ የሰው ዘሮች ላይ ሲፈስ የይሖዋ አምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት አንዳችም ተቃውሞ ሳያጋጥመው ከዘላለም እስከ ዘላለም በየትኛውም ቦታ የተረጋገጠ ይሆናል። ይህን ሽልማት ለማግኘት ሁላችንም ከሁሉ በተሻለ መንፈሳዊ ምግብ ከተሞላው የይሖዋ ማዕድ ብቻ ለመመገብ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በአጋንንታዊ ትምህርቶች ከመታለል መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ምንም ጉዳት ሳይደርስብን ከይሖዋ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ መመገብ የማንችለው ለምንድን ነው?
◻ በከሐዲዎች የሚከፋፈለው ምግብ ምን ዓይነት ነው?
◻ ከሐዲዎች የሚያቀርቧቸውን ክሶች ለማወቅ መጓጓት አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የከሐዲዎች ፍሬዎች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ማዕድ ከሁሉ በተሻለ መንፈሳዊ ምግብ ተሞልቷል