የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 7/1 ገጽ 14-17
  • ሥልጣን ምን ደርሶበታል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሥልጣን ምን ደርሶበታል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሥልጣን ቀውስ
  • ሕጋዊ ባለ ሥልጣን እንዲኖር ሰው ያደረገው ጥረት
  • “ሁለት ኃይሎች” “ሁለት ሰይፎች”
  • ሉዓላዊነት የሕዝብ ነው የሚለው እምነት
  • የብሔር ሉዓላዊነት እምነት አመጣጥ
  • የሰው ድካም ከንቱነት
  • አንድ ክርስቲያን ለባለ ሥልጣን ያለው አመለካከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • የይሖዋ ሉዓላዊነትና የአምላክ መንግሥት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 7/1 ገጽ 14-17

ሥልጣን ምን ደርሶበታል?

የሚያስቡ ሰዎች የሥልጣን አስፈላጊነት ይታያቸዋል። አንድ ዓይነት የሥልጣን መዋቅር ባይዘረጋ ኖሮ ሰብአዊው ኅብረተሰብ ምስቅልቅሉ ይወጣ ነበር። ይህም በመሆኑ የሕገ መንግሥትን ትርጉም የሚያብራራ በድሮ ጊዜ የተጻፈ አንድ የፈረንሳይኛ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በማንኛውም ሰብአዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ሁለት ዓይነት የሰዎች መደብ አለ። አዛዥና ታዛዥ፣ ትዕዛዝ ሰጪና ትዕዛዝ አክባሪ፣ መሪና አባላት፣ ገዢና ተገዢ አሉ። . . . በማንኛውም ሰብአዊ ኅብረተሰብ ውስጥ የሥልጣን መዋቅር ይታያል።”a

ይሁን እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በተለይም ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ሰዎች ለሥልጣን የነበራቸው አመለካከት ተለውጧል። በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ኡኒቨርሳሊ ኢንሳይክሎፔዲያ ያ ጊዜ “የሥልጣን ቀውስ” የደረሰበት ጊዜ ነው ብሏል። እንዲህ ዓይነቱ ቀውስ መድረሱ የመጽሐፍ ቅዱስን ተማሪዎች አያስደንቅም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል፦ “የዚህ ዓለም መጨረሻ የሁከት ጊዜ እንደሚሆን አስታውስ! ሰዎች ራሳቸውንና ገንዘብን ብቻ የሚወዱ ይሆናሉ፤ ጉረኞችና ጀብደኞች ይሆናሉ፤ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ . . . ጥላቻ የማይበርድላቸው፣ . . . ራሳቸውን የማይቆጣጠሩና ጨካኞች፣ . . . ከልክ በላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ይሆናሉ። ከአምላካቸው ይበልጥ የራሳቸውን ደስታ ይወዳሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1–4 ዘ ሪቫይዝድ ኢንግሊሽ ባይብል።

የሥልጣን ቀውስ

ይህ ትንቢት የእኛን ጊዜና ዘመን በሚገባ ይገልጻል። ሥልጣን በሁሉም አቅጣጫ ማለትም በቤተሰብ፣ በሕዝብ ትምህርት ቤት፣ በዩኒቨርሲቲ፣ በንግድ ተቋሞች፣ በአካባቢ አስተዳደርና በመንግሥት ደረጃ ተፈታታኝ ሁኔታ እየገጠመው ነው። የጾታ አብዮት እየተባለ የሚጠራው፣ ከኃይለኛ ምት ጋር የሚያንቧርቀው የራፕ ሙዚቃ፣ የተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ፣ የሥራ ማቆም አድማ፣ የሲቪሉ ሕዝብ አልታዘዝም ባይነትና ሽብር ፈጠራ እነዚህ ሁሉ ለሥልጣን አክብሮት የመስጠቱ ጉዳይ ቀውስ የደረሰበት መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው።

በፈረንሳይ የፖለቲካዊ ሳይንስ ተቋምና ለ ሞንድ በተባለው በፓሪስ ዕለታዊ ጋዜጣ አማካኝነት ፓሪስ ውስጥ በተዘጋጀው አንድ ሲምፖዚየም ላይ ፕሮፌሰር ኢቭ ሜኒ “ሥልጣን ሊኖር የሚችለው ሕጋዊ ድጋፍ ካለው ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ዛሬ ላለው የሥልጣን ውዝግብ አንዱ ምክንያት ብዙዎች በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ሕጋዊነት መጠራጠራቸው ነው። በሌላ አነጋገር ሥልጣን ላይ ለመቀመጥ ያላቸውን መብት ይጠራጠራሉ። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተጠናቀረ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ እንደሚያሳየው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 9 በመቶ፣ በአውስትራሊያ 10 በመቶ፣ በብሪታንያ 24 በመቶ፣ በፈረንሳይ 26 በመቶ በሕንድ ደግሞ 41 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መንግሥታቸው ሕጋዊ እንዳልሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ሕጋዊ ባለ ሥልጣን እንዲኖር ሰው ያደረገው ጥረት

በመጀመሪያ ሰው ቀጥታ በአምላክ ሥልጣን ሥር ይተዳደር እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:16, 17) ይሁን እንጂ ገና ከጅምሩ ሰዎች ያሻቸውን ማድረግ እንዲችሉ ከፈጣሪያቸው ነፃ መሆን ፈለጉ። (ዘፍጥረት 3:1–6) ቲኦክራሲን ወይም የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን ስላሉ ሌላ የሥልጣን ሥርዓት መፍጠር ነበረባቸው። (መክብብ 8:9) አንዳንዶች አፄ በጉልበቱ ሆኑ። በእነርሱ አመለካከት የመብታቸው ማረጋገጫ ጉልበት ነበር። ፈቃዳቸውን ለማስፈጸም በቂ ጉልበት ያላቸው መሆኑ ለአስተዳደር በቂ ሆኖ ተገኘ። አብዛኞቹ ግን የመግዛት መብታቸውን ሕጋዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

ከጥንት ጀምሮ ብዙ ገዢዎች እነሱ ራሳቸው አማልክት እንደሆኑ ወይም ከአማልክት ኃይል እንደተቀበሉ በመናገር ሕጋዊነታቸውን ለማረጋገጥ ሞክረዋል። ይህም በጥንት የሜሶጶጣሚያ ገዢዎችና የግብጽ ፈርዖኖች ዘንድ “ቅዱስ ንግሥና” እየተባለ ይጠራ የነበረው አፈታሪካዊ ጽንሰ ሐሳብ ነው።

ታላቁ እስክንድርና ከእሱ በኋላ የመጡት የግሪክ ነገሥታት እንዲሁም ብዙዎቹ የሮማ ንጉሠ ነገሥታት ጭምር አማልክት ነን ይሉ ነበር። እንዲያውም እንዲመለኩ ያዙ ነበር። በእነዚህ ገዢዎች ሥር የነበሩት የመስተዳድር ሥርዓቶች “ገዥው የሚመለክበት ሃይማኖት” በመባል ይታወቁ ነበር። ዓላማቸውም ድል ተደርገው በተያዙት ድብልቅ ሕዝቦች ላይ የገዥውን ሥልጣን ማጠናከር ነበር። ገዢውን አላመልክም ማለት መንግሥትን የሚጻረር የእምቢተኝነት እርምጃ ተደርጎ ይወገዝ ነበር። ፕሮፌሰር ኧርነስት ባርከር ዘ ለጋሲ ኦቭ ሮም በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “[የሮማ] ንጉሠ ነገሥት አምላክ ተደርጎ መቆጠርና በመለኮታዊነቱ ምክንያት የሚያገኘው የሕዝቡ ታማኝነት የግዛቱ መሠረት እንደነበር፤ ወይም ቢያንስ ቢያንስ የግዛቱ አንድነት ማጠናከሪያ እንደነበረ ግልጽ ነው።”

ከ306–337 እዘአ በገዛው በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ዘመን “ክርስትና” ሕጋዊ ዕውቅና ካገኘ በኋላና ከ379–395 እዘአ በገዛው በንጉሠ ነገሥት ቲዮዶሲየስ ዘመን የመንግሥቱ ሃይማኖት እንድትሆን ከተደረገ በኋላም እንኳ ይህ ነገር እንዳለ ቀጥሏል። እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ አንዳንድ “ክርስቲያን” ንጉሠ ነገሥታት እንደ አማልክት ተደርገው ተመልከዋል።

“ሁለት ኃይሎች” “ሁለት ሰይፎች”

የጵጵስና ሥልጣን ይበልጥ እየተጠናከረ ሲመጣ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ እየተካረረ ሄደ። ስለዚህ በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ ላይ ጳጳስ ገላሲየስ ቀዳማዊ “ሁለት ኃይሎች” የሚል አዲስ ፈሊጥ አመጣ። በዚህ መሠረት የጳጳሳት ቅዱስ ሥልጣን ከነገሥታት ሥልጣን ጋር ጐን ለጐን የሚሄድ ሲሆን ነገሥታቱ የጳጳሱ የበታች ይሆናሉ። ከጊዜ በኋላ ከዚህ ፈሊጥ “ሁለት ሰይፎች” የሚል ሌላ ፈሊጥ በቀለ። “መንፈሳዊው ሰይፍ በጳጳሱ እጅ ሲሆን ዓለማዊውን ሰይፍ ለአገሩ ገዢዎች በውክልና ይሰጣል፤ ሆኖም ገዢዎቹ ዓለማዊውን ሰይፍ የሚጠቀሙበት በጳጳሱ መመሪያ መሠረት ብቻ ይሆናል።” (ዘ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ) በዚህ ድንጋጌ መሠረት በመካከለኛው ዘመን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለንጉሠ ነገሥታትና ለንጉሦች ዘውድ የመጫን መብት ይገባኛል አለች። የሕጋዊነታቸው ማረጋገጫ ይህ ሆነ። በዚህ መንገድ የጥንቱ “የቅዱስ ንግሥና” አፈታሪክ ሕልውናውን እንደያዘ እንዲዘልቅ አድርጋለች።

ይሁን እንጂ ይህ አባባል ነገሥታት ለመግዛት መለኮታዊ መብት አላቸው ከሚለውና የፖለቲካ ገዢዎችን ከጵጵስና እጅ ለማስለቀቅ ከታለመው አባባል ጋር አንድ እንደሆነ ተደርጎ መታየት አይገባውም። መለኮታዊ የመግዛት መብት ጽንሰ ሐሳብ ነገሥታት ሥልጣናቸውን በሮማ ጳጳስ አማካኝነት ሳይሆን በቀጥታ ከአምላክ ያገኛሉ የሚል ነበር። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ጳጳሱ በየአገሩ መራሔ መንግሥት ላይ መንፈሣዊና ሰብዓዊ ሥልጣን ጨብጦ በነበረበት ዘመን፣ መለኰታዊ የመግዛት መብት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ፣ የየአገሩ ነገሥታት ሥልጣናቸው ከጳጳሱ ሥልጣን ባልተናነሰ መንገድ መለኰታዊ ነው ብለው ሕጋዊነቱን ለማረጋገጥ እንዲከራከሩ በሚያስገድድ ሁኔታ ላይ አስቀመጣቸው።”b[20]

ሉዓላዊነት የሕዝብ ነው የሚለው እምነት

ከጊዜ በኋላ ሰዎች ሌላ የሥልጣን ምንጭ አለ የሚል ሐሳብ አቀረቡ። ከእነዚህም አንዱ የሕዝብ ሉዓላዊነት ነው። ብዙዎች ይህ ሐሳብ ከግሪክ እንደመነጨ ያምናሉ። ይሁን እንጂ በጥንቱ ግሪክ ዲሞክራሲ ይሠራበት የነበረው የራሳቸው መንግሥት በነበራቸው በጥቂት ከተሞች ብቻ ነበር። እዚህም ቢሆን በምርጫ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡት ወንዶች ብቻ ነበሩ። ሴቶች፣ ባሪያዎችና የባዕድ አገር ነዋሪዎች ከዚህ ውጭ ተደርገዋል። ይህም ማለት ከግማሽ እስከ አራት አምስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ድምፅ የመስጠት መብት አልነበረውም ማለት ነው። ታዲያ ይህ የሕዝቦች ሉዓላዊነት ነበር ለማለት ያስደፍራል?

ሉዓላዊነት የሕዝብ ነው የሚለውን ሐሳብ ያመነጨው ማን ነው? በጣም የሚያስገርመው ይህን ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠሩት በመካከለኛው ዘመን የነበሩት የሮማ ካቶሊክ የሃይማኖት ሊቃውንት ናቸው። በ13ኛው መቶ ዘመን ቶማስ አኪናስ ሉዓላዊነት ከአምላክ የመነጨ ቢሆንም ለሰዎች ተሰጥቷል ብሎ ያምን ነበር። ይህ ሐሳብ በብዙሐኑ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ነው የሚለው ይህ አመለካከት በ17ኛው መቶ ዘመን በብዙ የካቶሊክ ሃይማኖት ሊቃውንት ዘንድ ድጋፍ አግኝቶ ነበር።”

ጳጳስ፣ አቡን ወይም ቄስ በሚመረጥበት ጊዜ ሕዝቡ ምንም ድምፅ እንደማይሰጥ እየታወቀ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ያመነጩት ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንዳንድ የአውሮፓ ነገሥታት በጳጳስ ሥልጣን ሥር መሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበሳጫቸው መጥቶ ነበር። ሉዓላዊነት የሕዝብ ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ጳጳሱ አስፈላጊ መስሎ ከታየው አንድን ንጉሥ ወይም ገዢ ከሥልጣን ለማውረድ ያስችለዋል። የታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ዊል እና አሪየል ዱራንት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ይህ ጽንሰ ሐሳብ የጳጳሱን ሥልጣን የሚቃወመውን ንጉሥ ለማዳከም እንደ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለው ያምኑ ከነበሩት የሕዝብ ሉዓላዊነት አቀንቃኞች መካከል ብዙ ኢየሱሳውያን ይገኙበታል። የነገሥታት ሥልጣን ከሕዝብ የሚገኝና ለሕዝብ የሚገዛ ከሆነ ከጳጳሳት ሥልጣን በታች መሆኑ ግልጽ ነው ሲሉ ካሪዲናል ቤልአርሚን ተከራከሩ። . . . ሉዊስ ሞሊና የተባለ የስፓኝ ኢየሱሳዊ ሰባኪ ሕዝቡ የዓለማዊ ሥልጣን ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ፍትሕ ያጓደለውን ንጉሥ ከሥልጣን ለማውረድ ይችላል፤ ይህን ሲያደርግ ግን ሥርዓት ባለው መንገድ መሆን አለበት ሲል ደምድሟል።”

እርግጥ ሥርዓት ያለው መንገድ የሚቀነባበረው በጳጳሱ ነበር። ኢስትዋር ኡኒቨርሴል ደ ሌግሊዝ ካቶሊከ የተባለው በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተዘጋጀ የካቶሊክ ኢንሳይክሌፔዲያ ባዮግራፊ ኡኒቨርሴል የጻፈውን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “ቤላርመን . . . መሳፍንቶች ሥልጣናቸውን ያገኙት በሕዝብ ምርጫ እንደሆነና ሕዝቡ ይህን መብቱን ሊጠቀምበት የሚችለው ጳጳሱ በሚያዘው መንገድ ብቻ መሆኑን የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርት አድርጎ ያስተምራል።” (ጋደል ባሉ ፊደላት የጻፍናቸው እኛ ነን።) በዚህ መንገድ ጳጳሱ የሕዝብ ሉዓላዊነት በገዢዎች አመራረጥና ከዚያም አልፎ ከሥልጣን መውረድ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሊጠቀምበት የሚችል መሣሪያ ሆነለት። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የካቶሊክ ባለ ሥልጣኖች ይህን ትምህርት ዲሞክራሲን በሚከተሉ አገሮች ካቶሊክ የሆኑ ድምፅ ሰጪዎችን ወደተፈለገው አቅጣጫ ለማዘንበል ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

ባሁኑ ዘመን ዲሞክራሲን በሚከተሉ አገሮች የመንግሥት ሕጋዊነት የተመሠረተው “በተገዢዎች ፍላጎት” ላይ ነው። ይሁን እንጂ ግፋ ቢል ይህ “የብዙኀኑ ፍላጎት” ብቻ የሚያንፀባርቅ ነው፤ እንዲሁም ብዙዎች ድምፅ ለመስጠት ካላቸው ግዴለሽነትና ከፖለቲካ ማጭበርበር አንፃር ሲታይ እነዚህ “ብዙኀን” የተባሉት ዞሮ ዞሮ በቁጥር አናሳ የሆነው ሕዝብ ብቻ ነው። ዛሬ “በተገዢዎች ፍላጎት” ላይ የተመሠረተ ነው የሚለው አባባል አብዛኛውን ጊዜ “የተገዢዎች ዝምታ ወይም የፈለገው ይግዛ” የሚል የግድየለሽነት ስሜት ነው።

የብሔር ሉዓላዊነት እምነት አመጣጥ

ቅዱስ ንግሥና የሚለው አፈታሪካዊ እምነት ቀስ በቀስ ነገሥታት ለመግዛት መለኮታዊ መብት አላቸው ወደሚለው ጽንሰ ሐሳብ ሲለወጥ መልሶ ጳጳሳቱን የሚጐዳ ሆነ። የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብም እንደዚሁ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዞሮ ጉዳት አስከተለባት። በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን እንደ እንግሊዛዊዎቹ ቶማስ ሆብስና ጆን ሎክ እንዲሁም እንደ ፈረንሳዊው ዣንዣክ ሩሶ የመሳሰሉት ዓለማዊ ፈላስፎች የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ የሚደግፍ አቋም አንፀባርቀዋል። ከዚያ በመነሳት በገዢዎችና በተገዢዎች መካከል የሚኖር “ማኅበራዊ ውል” የሚል ፅንሰ ሐሳብ ፈጠሩ። መርሆዎቻቸው በሃይማኖታዊ ትምህርት ላይ ሳይሆን “በተፈጥሮ ሕግ” ላይ የተመሠረቱ ሲሆን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና መንበረ ጵጵስናውን በእጅጉ የጎዳ ፍልስፍና ነበር።

ሩሶ እንደሞተ ብዙም ሳይቆይ የፈረንሳይ አብዮት ፈነዳ። ይህ አብዮት አንዳንድ የሕጋዊነት ፅንሰ ሐሳቦችን አጥፍቷል። ይሁን እንጂ የብሔር ሉዓላዊነት የሚል አዲስ ፅንሰ ሐሳብ ይዞ ተነሣ። ዘ ኒው ኢንሳክሎፔዲያ ብሪታኒካ “ፈረንሳዮቹ የነገሥታትን መለኮታዊ የመግዛት መብት፣ የመኳንንትን የበላይነት፣ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የነበሯትን ልዩ መብቶች ውድቅ አደረጉ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ይሁን እንጂ፣ ይላል ብሪታኒካ “አብዮቱ አዲስ ብልሃት ፈልስፏል። ይህም የብሔር መስተዳድርን ፍልስፍና እንዲጐለብት አድርጓል።” አብዮተኞቹ ይህ አዲስ “ብልሃት” አስፈልጓቸው ነበር። ለምን?

ምክንያቱም ሩሶ ይሟገትለት በነበረው የአስተዳደር ሥርዓት መሠረት በመሪዎች አመራረጥ ላይ ሁሉም ዜጎች እኩል ድምፅ ይኖራቸዋል። ይህም ሁሉንም በሚያሳትፍ የመምረጥ መብት ላይ የተመሠረተ አንድ ዲሞክራሲ እንዲያስገኝ የታሰበ ነበር። የፈረንሳይ አብዮት መሪዎች ግን ይህ አልተዋጠላቸውም ነበር። ፕሮፌሰር ዱቨርዠ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የነበሩት ቡርዡዋዎች ከ1789–1792 በነበሩት ዓመታት የብሔር ሉዓላዊነትን ሐሳብ ያመጡት ይህን ያልተፈለገ ውጤት ለማስቀረት ነበር። ‘ብሔር’ ማለት ሕዝብ ማለት ነው ይሉ ነበር። በውስጡ ከተካተቱት ክፍሎች ተነጥሎ ሲታይ ደግሞ ራሱን የቻለ አካል እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። በተወካዮቹ አማካኝነት ሉዓላዊ ሥልጣን ለመጨበጥ የሚችለው ሕዝቡ ብቻ ነበር። . . . የብሔር ሉዓላዊነት ዲሞክራሲያዊ መልክ የለበሰ ቢመስልም በእርግጥ ዲሞክራሲያዊ አልነበረም፤ ምክንያቱም የትኛውንም ዓይነት መስተዳድር (በተለይ አምባገነናዊ መስተዳድርን) ለመደገፍ ሊሠራበት ይችላል።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)

የሰው ድካም ከንቱነት

መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው የሚለው ፍልስፍና ለሥልጣን ሕጋዊነት መሠረት ነው ተብሎ ተቀባይነት ማግኘቱ ብሔራዊ ስሜትን ወለደ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “ብሔራዊ ስሜት ብዙውን ጊዜ ከረጅም ዘመን ጀምሮ እንደኖረ ተደርጎ ይታሰባል። አንዳንድ ጊዜ በስህተት ከፖለቲካዊ ባሕርይ ሊነጣጠል እንደማይችል ተደርጎ ይቆጠራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ብሔራዊ ስሜት ለመጀመሪያ ጊዜ ተጧጡፎ ብቅ ያለው በአሜሪካና በፈረንሳይ አብዮቶች ጊዜ ነው ለማለት ይቻላል።” ከእነዚያ አብዮቶች በኋላ የብሔራዊ ስሜት ማዕበል ወደ ደቡብና ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አፍሪካና እስያ ተዛመተ። በብሔራዊ ጥቅም ስም የተካሄዱ ዘግናኝ ጦርነቶች ሕጋዊ ተደርገው ተቆጥረዋል።

እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ አርኖልድ ቶይንቢ የሚከተለውን ጽፈዋል፦ “የብሔረተኝነት መንፈስ በአሮጌ የጐሠኝነት ደንበጃን ላይ የተጠመቀው አዲሱ የዲሞክራሲ የወይን ጠጅ እንዲፈላ የረዳ ኮምጣጣ እርሾ ነው። . . . ይህ እንግዳ የሆነ ዲሞክራሲና ጐሠኝነት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው የፈጠሩት ስምምነት በዘመናዊው የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ከራሱ ከዲሞክራሲ የበለጠ ገናና ሆኗል።” ብሔራዊ ስሜት ሰላማዊ ዓለም አላመጣም። ቶይንቢ እንዲህ ብለዋል፦ “የሃይማኖት ጦርነቶችን ተከትሎ ምንም ያህል ጊዜ ሳይቆይ የብሔረተኝነት ጦርነት መጣ። በዘመናዊው የምዕራቡ ዓለማችንም ላይ ጭፍን ሃይማኖታዊ አክራሪነትና ጭፍን ብሔራዊ አክራሪነት አንዱ ከሌላው የማይለይ እኩይ መንፈስ ናቸው።”

ገዥዎች “ቅዱሱ ንግሥና” “የነገሥታት መለኰታዊ የመግዛት መብት” “ሕዝባዊ ሉዓላዊነት” “የብሔር ሉዓላዊነት” እያሉ በሌሎች ሰዎች ላይ ያላቸውን የገዥነት ሥልጣን ሕጋዊ ለማድረግ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን የሰብዓዊ መሪዎችን የታሪክ መዝገብ ከተመለከተ በኋላ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ሲል ሰሎሞን ከተናገረው ቃል ለመስማማት ይገደዳል።”—መክብብ 8:9 አዓት

ክርስቲያኖች የፖለቲካ መንግሥትን ሳይሆን አምላክን ያመልካሉ፤ የማንኛውም ሕጋዊ ሥልጣን ምንጭ እርሱ እንደሆነም ይቀበላሉ። መዝሙራዊው ዳዊት የተናገራቸውን ቀጥሎ ያሉትን ቃላት ይስማሙባቸዋል፦ “አቤቱ፣ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም፣ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ።” (1 ዜና መዋዕል 29:11) ይሁን እንጂ ለአምላክ ካላቸው አክብሮት በመነሣት በሰብዓዊውም ይሁን በመንፈሣዊው መስክ ለባለ ሥልጣን ተገቢ አክብሮት ያሳያሉ። ይህንን ኃላፊነት እንዴትና ለምን በደስታ ሊያከናውኑት እንደሚችሉ ቀጥሎ ባሉት ርዕሶች ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ድሯ ኮንስቲቱሲዮኔል ኤ ኤንስቲቱሲዮን ፖሊቲክ የተባለ በሞሪስ ዱቨርዠር የተደረሰ መጽሐፍ።

b ዘ ካሮሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል፤ “ማንኛውም ሥልጣን (ሪፑብሊካዊውም ይሁን ንጉሣዊ) ከአምላክ የተገኘ ነው ከሚለው ጽንሰ ሐሳብ በጣም የተራራቀ ልዩነት የነበረው መለኰታዊ የመግዛት መብት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ አግኝቶ አያውቅም። በፕሮቴስታንት የተሐድሶ ንቅናቄ ዘመን ይህ አቋም ተጧጡፎ የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን ክፉኛ የሚጻረርበት ደረጃ ላይ ደረሰ። እንደ ሔንሪ 8ኛና ቀዳማዊ ያዕቆብ የመሳሰሉ የእንግሊዝ ነገሥታት መንፈሣዊውንና ሥጋዊውን ሥልጣን ራሳቸው ጨበጡት።”[21]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለንጉሠ ነገሥታትና ለንጉሦች ዘውድ የመጫን መብት ይገባኛል አለች

[ምንጭ]

Consecration of Charlemagne: Bibliothèque Nationale, Paris

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ