‘እምነትን ጠብቄአለሁ’
የብሩኔላ ኢንኮንዴቲ ወዳጆች እንደተናገሩት
“ዕለቱ ቅዳሜ ነበር። በጣም ረጅምና ቅፍፍ የሚል ቀን። ተስፋ በመቁረጥ ስሜት በክፍሉ ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ። ወደ ውጭ ለመውጣት በኮሪደር በኩል እንደምራመድ ሆኖ ተሰማኝ። ሁሉም ነገር ደህና ይመስል ነበር፤ በድንገት ግን አንድ ሰው በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘጋብኝ። የቱንም ያህል ብፍጨረጨር መውጫ መንገድ አልነበረም።”
የ15 ዓመቷ ብሩኔላ ኢንኮንዴቲ ባጋጠማት ከአቅም በላይ በሆነ ሕመም ምክንያት ልቧ በኀዘን ተውጧል። የለጋ ሕይወቷ በመጨረሻዋ ዕለት እየሸሻት ነበር። በዚያው ዓመት ትንሽ ወራት ቀደም ብሎ ለይሖዋና ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበራት ከፍተኛ ፍቅር ራሷን ለይሖዋ እንድትወስን ገፋፍቷት ነበር። በሐምሌ ወር 1990 በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች “ንጹሕ ልሳን” የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ተዘጋጅታ ነበር። ሆኖም ወዲያው በቀሪው ሕይወቷ ሙሉ እምነቷን የሚፈትን ነገር ይጠብቃት ነበር።
ብሩኔላ ውሳኔዋን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት ሁለት ቀን ብቻ ሲቀራት ሉኪሚያ የሚባል በሽታ እንዳለባት ተነገራት። በአካባቢው የሚገኘው የሕፃናት ሆስፒታል ዶክተሮች ሕክምናውን ያኔውኑ ሊጀምሩላት ስለፈለጉ ብሩኔላ በሆስፒታሉ ውስጥ ቆየች።
የተናገረቻቸው ቃላት የዶክተሮቹን ስሜት ነኩ
ብሩኔላ ደም ለይሖዋ አምላክ የተቀደሰ መሆኑን ታውቅ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:11) አባቷ ኤድሞንዶ እና እናቷ ኒኮሌታ ልጃቸው በሕክምናው ወቅት ደም እንደማትወስድ በግልጽ አስታወቁ። “ብሩኔላ ራሷ መወሰን በምትችልበት ዕድሜ ላይ ያልደረሰች ብትሆንም ደም እንዲሰጣት የማትፈልግ መሆኗን ዶክተሮቹ ከራሷ አፍ እንዲሰሙ ፈልጋ ነበር” በማለት አባቷ ያስታውሳል። “‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የሚያስጥስ ሕክምና እንዲደረግላት የማትፈልግ መሆኗን አጥብቃ ነገረቻቸው።”—ሥራ 15:20
ሐምሌ 10, 1990 ሦስት ዶክተሮችና አንዲት የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ ከብሩኔላ ወላጆችና በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ካሉ ሁለት አገልጋዮች ጋር ቁጭ ብለው ተወያዩ። የተደረጉት ምርመራዎች ብሩኔላ ጊዜ የማይሰጥ ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ የሚባል (ከተለመደው ሂደት ውጭ የሆነ የነጭ የደም ሴሎች መራባት) በሽታ እንዳለባት አረጋግጠዋል። ዶክተሮቹ በሽታውን በምን ዘዴ ለመዋጋት እንዳሰቡ ገለጹ። በሽታውን ለማከም ግን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን በዘዴ አስረዱ። “የብሩኔላ ጠባይና አምላክን ለመታዘዝ ያላት ቆራጥ አቋም ዶክተሮቹንና የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛዋን በጥልቅ ነካቸው። ወላጆቿ ያሳዩትን ፍቅርና በክርስቲያን ጉባኤ ያሉት ወዳጆቻቸው የሰጡትን ድጋፍ በጣም አደነቁ። በተጨማሪም ሐኪሞቹ ያላቸውን ቦታ ማወቃችንና ማክበራችን አስደስቷቸው ነበር” በማለት ከጉባኤው ሽማግሌዎች አንዱ ያስታውሳል።
ዶክተሮቹ ደም ላለመስጠት ፈቃደኞች ሆኑ። ብሩኔላ ከመደበኛው መጠን አነስ ያለ ግን ረጅም ጊዜ የሚወስድ የኬሞቴራፒ ሕክምና እንዲሰጣት ተወሰነ። ይህም በሕክምናው ምክንያት በደም ሴሎቿ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ይቀንሰዋል። “ዶክተሮቹ የብሩኔላን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ግምት ውስጥ አስገብተው ነበር” ስትል ኒኮሌታ ተናግራለች። “በሕፃናት ላይ የሚከሰተውን የሉኪሚያ በሽታ ያለ ደም በማከም ብዙ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች እንዲያማክሩ በጠየቅናቸው ጊዜ አልተቃወሙም።” በብሩኔላና በሆስፒታሉ ሠራተኞች መካከል ሞቅ ያለ የወዳጅነት መንፈስ ነበር።
መንፈሳዊ ግቦች
ምንም እንኳ የመጀመሪያው ሕክምና አንዳንድ ጥሩ ውጤቶች ቢያስገኝም የብሩኔላ ሥቃይ ገና መጀመሩ ነበር። በ1990 የኅዳር ወር መግቢያ ላይ ሕመሙ ትንሽ ታግሦላት ስለነበር ወዲያው ተጠመቀች። ብሩኔላ ባሳለፈቻቸው ጥቂት ወራት ስለተሰማት ነገር በግልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በፍጹም ቀላል አልነበረም። ብዙ ብርታትና ብሩህ የሆነ አመለካከት መያዝን ይጠይቃል። . . . እምነቴ ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። ሆኖም ቆራጥ አቋም ይዤ ቆይቻለሁ። አሁንም በቋሚነት የዘወትር አቅኚ [የሙሉ ጊዜ አገልጋይ] ሆኜ ለማገልገል እቅድ አለኝ።”
ብሩኔላ በ1991 መጀመሪያ ላይ ሕመሟ አገረሸባትና ተዳከመች። በኬሞቴራፒ ሕክምና ላይ እያለች ልትሞት ምንም ያህል አልቀራትም ነበር፤ ሆኖም ሳይጠበቅ ተሻላትና ሁሉም ተደሰቱ። ነሐሴ ላይ ወሩን ረዳት አቅኚ ሆና በማገልገል ማሳለፍ እስክትችል ድረስ ደህና ሆና ነበር። ሕመሟ እንደገና ተባባሰና ኅዳር 1991 ላይ የሰውነቷ ልዩ ልዩ ክፍል በካንሰር ተያዘ። የሌላ ሆስፒታል ዶክተሮች በጨረር ሕክምና ያደርጉላት ጀመር።
ብሩኔላ እንዲህ ባሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር እያለችም እንኳ ጽኑ አቋም ይዛለች። ለራሷ መንፈሳዊ ግቦች አውጥታም ነበር። ሉኪሚያ እንዳለባት በተነገራት ጊዜ ለስድስት ወር ብቻ ልትኖር እንደምትችል ተገልጾላት ነበር። ያ ከሆነ አሁን አንድ ዓመት ተኩል ቢያልፍም ብሩኔላ ለመጭዎቹ ጊዜያት ግቦችን ታወጣ ነበር። “ግቦቿ ላይ ለመድረስ ምንም ጊዜ አላበከነችም” በማለት አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ተናግሯል። “ብሩኔላ አምላክ በሰጠው የገነት ተስፋ ላይ የነበራት እምነት በሥቃይዋ ወቅት ሁሉ ደግፎ አቁሟታል። በዕድሜ ገና ትንሽ ብትሆንም ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ደርሳ ነበር። ጠባይዋና አቋሟ የጉባኤውን መንፈስ አነቃቅቷል። የሆስፒታል ሠራተኞችን ጨምሮ የሚያውቋትን ሰዎች ሁሉ ልብ ማርኳል።” እናቷ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “በፍጹም አማርራ አታውቅም። ደህንነቷን ለሚጠይቋት ሁሉ ‘ደህና ነኝ’ ወይም ‘ምንም አልል፤ አንቺስ እንዴት ነሽ?’ ብላ ትመልስ ነበር።”
አስተማማኝ ተስፋ
ብሩኔላ በሐምሌ 1992 በሚደረገው “ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አስባ ነበር። ይሁን እንጂ የስብሰባው ጊዜ ሲደርስ ብሩኔላ ሆስፒታል ገባች። ሕይወቷም በቋፍ ላይ ነበር። ሆኖም በይሖዋ ዓይን ቅን የሆነውን ማድረግ የሚለውን ድራማ ለማየት ቆርጣ በመነሣቷ በሚገፋ ወንበር ላይ ሆና በስብሰባው ለመገኘት ችላ ነበር።
የቀሩትን ጥቂት ቀናት ከቤተሰቦቿ ጋር ለማሳለፍ ወደ ቤት ተመለሰች። “በመጨረሻም ከራሷ ይልቅ ስለ ሌሎች ታስብ ነበር” በማለት ኒኮሌታ ትናገራለች። “‘አይዟችሁ በገነት አብረን እንሆናለን’ መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑ እያለች ታበረታታቸው ነበር።”
ብሩኔላ በምድር ላይ በገነት ለመኖር ትንሣኤ እንደምታገኝ ያላትን ተስፋ አጽንታ እንደያዘች ሐምሌ 27, 1992 አረፈች። ግቧን መከታተል ገና መጀመሯ ነበር። ትንሣኤ ካገኘች በኋላ በውሳኔዋ ለመቀጠል አቅዳለች። ከመሞቷ ጥቂት ቀደም ባሉት ቀናት በቀብሯ ላይ የሚነበብ ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ጽፋ ነበር። እንዲህ ይላል፦
“ውድ ወዳጆቼ፦
“ስለመጣችሁ አመሰግናችኋለሁ። በዚህ ሰዓት የእናንተ መገኘት ቤተሰቦቼን ብዙ ያጽናናቸዋል።
“ከእኔ ጋር ቅርበት የነበራችሁ ሁሉ አብረን ብዙ ነገሮችን አሳልፈናል። አያሌ መጥፎ ቀናት አሳልፈናል፤ አንዳንድ አስደሳች ወቅቶችም ነበሩ። ረጅምና ከባድ ውጊያ አድርገን ነበር፤ ሆኖም እንደተሸነፍኩ አልቆጥረውም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ እምነትን ጠብቄአለሁ’ ይላልና።—2 ጢሞቴዎስ 4:7
“በተጨማሪም ብዙ ተምሬአለሁ፣ ብዙም አድጌአለሁ። ወዳጆቼና ከእኔ ጋር የነበሩት ሁሉ ያደረግሁትን ለውጥ ተመልክተዋል። ድጋፋቸውን ያልነፈጉኝን ሰዎች ሁሉ አመሰግናለሁ።
“በአዲሱ ሥርዓትና በይሖዋ የምታምኑ ሁሉ በዮሐንስ 5:28, 29 መሠረት ትንሣኤ እንደሚኖር ታውቃላችሁ። ስለዚህ እንደገና እርስ በእርስ መተያየት እስከምንችልበት ጊዜ ድረስ በእውነት ውስጥ ጠንካሮች ሆናችሁ ቀጥሉ።
“ያሳለፍኩትን መከራ የምታውቁትን ሁሉ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። እያንዳንዳችሁን እቅፍ አድርጌ ለረጅም ጊዜ ስሜያችኋለሁ። ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ።”
ብሩኔላ ወጣትነቷ ወይም ያደረባት ሕመም ራሷን ለአምላክ ከመወሰን አላዘገያትም። የእርሷ የእምነት ምሳሌና ቆራጥነት ወጣቶችም ሆነ አረጋውያን ሊያደናቅፏቸው በሚችሉ ነገሮች ለሕይወት የሚያደርጉትን ተመሳሳይ ሩጫ ለሌላ ጊዜ እንዳያስተላልፉ ያበረታታቸዋል።—ዕብራውያን 12:1