የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 7/15 ገጽ 10-15
  • ትዳራችሁን ዘላቂ ጥምረት አድርጉት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ትዳራችሁን ዘላቂ ጥምረት አድርጉት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የትዳር ዘላቂነት
  • የራስነት ሥልጣንና ተገዢነት
  • መነጋገር የትዳር የደም ሥር ነው
  • አለመግባባትን መፍታት
  • ምን ጊዜም አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሁኑ
  • ክርስቲያኖች ትዳራቸውን የሰመረ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • አምላክ ያጣመረውን እናንተ አትለያዩት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር ምን ይላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ የሚረዱ ሁለት ቁልፍ ነገሮች
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 7/15 ገጽ 10-15

ትዳራችሁን ዘላቂ ጥምረት አድርጉት

“እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:6

1. በዛሬው ጊዜ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ላለው የትዳር መሳካት ምክንያቱ ምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስደሳችና ዘላቂ ትዳር አላቸው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ስኬታማ የሆነ ትዳር ሊኖራቸው የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች (1) አምላክ ለትዳር ያለውን አመለካከት ሲያከብሩና (2) የቃሉን መሠረታዊ ሥርዓቶች በኑሯቸው ውስጥ ለመተግበር ሲጥሩ የክርስቲያኖች ትዳር የሰመረ ይሆናል። ጋብቻን ያቋቋመው ራሱ አምላክ ነው። ‘በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ የሚጠራበትን ስም’ ማግኘት የቻለው በእርሱ ነው። (ኤፌሶን 3:14, 15) ትዳር ስኬታማ መሆን እንዲችል ምን እንደሚያስፈልግ ይሖዋ ስለሚያውቅ መመሪያውን ብንከተል እንጠቀማለን።—ኢሳይያስ 48:17

2. በትዳር ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ አለማዋል ምን መዘዞችን ያስከትላል?

2 በተቃራኒው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ አለማዋል ትዳር እንዲበጠበጥ ያደርጋል። አንዳንድ ጠበብት በዛሬው ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚፈጸሙት ጋብቻዎች ውስጥ ውሎ አድሮ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በፍቺ መፍረሳቸው እንደማይቀር ያምናሉ። ሌላው ቀርቶ ክርስቲያኖችም እንኳ ይህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ካስከተለው ጭንቀትና ውጥረት አላመለጡም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የኢኮኖሚ ውጥረትና በሥራ ቦታ ያለው ተጽዕኖ በማንኛውም ትዳር ላይ አሉታዊ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖችም የትዳር ጓደኞቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ አለማዋላቸው ያልጠበቁትና የሚያስመርር ሆኖ አግኝተውታል። “ይሖዋን እወደዋለሁ” ስትል አንድ ክርስቲያን ተናግራለች፤ “ሆኖም ትዳሬ ለ20 ዓመታት የተመሰቃቀለ ሆኖ ቆይቷል። ባሌ ራሱን በጣም ይወዳል፤ ምንም ዓይነት ለውጥ ለማድረግ አይፈልግም። ወጥመድ ውስጥ እንደገባሁ ሆኖ ይሰማኛል።” ጥቂት ያይደሉ ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች ተመሳሳይ እሮሮ ያሰማሉ። ችግሩ ምንድን ነው? አንድ ትዳር የኩርፊያ ኑሮ እንዳይሆን ወይም ወደ ጠላትነት እንዳይለወጥ በምን መከላከል ይቻላል?

የትዳር ዘላቂነት

3, 4. (ሀ) አምላክ ለትዳር ያወጣው የአቋም ደረጃ ምንድን ነው? (ለ) የትዳር ዘላቂነት ተገቢና ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ሁሉም ነገር ቢሟላም እንኳ ትዳር ፍጹማን ያልሆኑ ግለሰቦች ጥምረት ነው። (ዘዳግም 32:5) በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ የሚያገቡ “በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) አንዳንድ ችግሮች ተባብሰው እስከ መለያየት ወይም መፋታት ሊያደርሱ ይችላሉ። (ማቴዎስ 19:9፤ 1 ቆሮንቶስ 7:12–15) በአብዛኛው ግን ክርስቲያኖች “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፣ . . . ባልም ሚስቱን አይተዋት” የሚለውን የጳውሎስ ምክር በሥራ ያውላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) ኢየሱስ “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ስለተናገረ በእርግጥም ትዳር ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ታስቦ ነበር።—ማቴዎስ 19:6

4 ጥላቻ ባለበትና ፍቅር በጎደለበት ትዳር ታስሮ እንደተያዘ ሆኖ የሚሰማው ሰው ይሖዋ ያወጣው የአቋም ደረጃ በጣም ከባድና ምክንያተ ቢስ መስሎ ሊታየው ይችላል። ሁኔታው ግን እንደዚያ አይደለም። የጋብቻቸው ሰንሰለት ለዘለቄታው ጥብቅ ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈልጉ አምላክን የሚፈሩ ባልና ሚስት ገና ትንሽ የችግር ምልክት ሲያዩ ግዴታቸውን ጥለው ወደ ኋላ ከማፈግፈግ ይልቅ ችግሩን ለመጋፈጥና መፍትሔ ለመፈለግ ይገፋፋሉ። ከ20 ዓመታት በላይ በትዳር ዓለም ያሳለፈ አንድ ሰው ነገሩን በዚህ መንገድ አስቀምጦታል፦ “አስቸጋሪ ጊዜያት እንዳይከሰቱ ማድረግ አትችሉም። ሁልጊዜ በመካከላችሁ ደስታ ሊሰፍን አይችልም። የገቡትን ቃል ኪዳን ማስታወስ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም እንዲህ ዓይነቱ ወቅት ነው።” እርግጥ ክርስቲያን የሆኑ የትዳር ጓደኛሞች በቅድሚያ ግዴታ ያለባቸው የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ እንደሆነ ያውቃሉ።—ከመክብብ 5:4 ጋር አወዳድር።

የራስነት ሥልጣንና ተገዢነት

5. ጳውሎስ ለባልና ሚስት ምን ምክር ሰጥቷል?

5 እንግዲያው ችግሮች በሚነሡበት ጊዜ የአምላክን ቃል በተሻለ መንገድ በሥራ ለማዋል ጥረት የሚደረግበት ጊዜ እንጂ ማምለጫ መንገድ የሚፈለግበት ጊዜ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በኤፌሶን 5:22–25, 28, 29 ላይ የሚገኙትን ቀጥሎ ያሉትን የጳውሎስ ቃላት ልብ በሉ፦ “ሚስቶች ሆይ፣ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ . . . ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ . . . ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት ይመግበዋል ይከባከበውማል።”

6. ክርስቲያን ባሎች ከዓለም ወንዶች የተለዩ መሆን ያለባቸው እንዴት ነው?

6 ወንዶች ብዙውን ጊዜ የባልነት ሥልጣናቸውን አላግባብ ይጠቀሙበታል። ሚስቶቻቸውን ይጨቁናሉ። (ዘፍጥረት 3:16) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ክርስቲያን ባሎች ከዓለም ወንዶች የተለዩና ክርስቶስን የሚመስሉ እንዲሆኑ እንዲሁም እያንዳንዱን የሚስቶቻቸውን የኑሮ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ አምባገነኖች እንዳይሆኑ አሳስቧቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን የሚያስጨንቅ ወይም ቁጥጥር የሚያበዛ አልነበረም። እንዲህ በማለት ተከታዮቹን በአክብሮት ይዟቸዋል፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና።”—ማቴዎስ 11:28, 29

7. አንድ ሰው ሚስቱ ሰብዓዊ ሥራ ካላት አክብሮት ሊያሳያት የሚችለው እንዴት ነው?

7 አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን ልክ እንደ ተሰባሪ ዕቃ በክብር ይይዛል። (1 ጴጥሮስ 3:7 አዓት) ለምሳሌ ያህል ሰብዓዊ ሥራ ትሠራለች እንበል። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚችለውን ያህል ሊረዳትና ሊያስብላት ይጥራል። ሴቶች ለፍቺ ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት አንዱ ነገር ባሎቻችን ልጆቻቸውን ወይም ቤቱን ችላ ይላሉ የሚል ነው። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ባል በቤት ውስጥ መላውን ቤተሰብ በሚጠቅም መንገድ ሚስቱን ለመርዳት ይጥራል።

8. ተገዢነት ክርስቲያን ሚስቶች ምን እንዲያሳዩ ይጠይቅባቸዋል?

8 ክርስቲያን ሚስቶች በአክብሮት መያዛቸው ለባሎቻቸው ተገዢ መሆኑን ቀላል ያደርግላቸዋል። ይህ ማለት ግን ባርነት ማለት አይደለም። አምላክ ሴትን የፈጠራት ወንድን ‘የተሟላ ለማድረግ’ እንጂ ባሪያው እንድትሆን አልነበረም። ይህም ለወንዱ ተስማሚው መሆኗን ያመለክታል። (ዘፍጥረት 2:18 አዓት) በሚልክያስ 2:14 ላይ ሚስት የወንድ “ባልንጀራ” ተደርጋ ተገልጻለች። ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሚስቶች የማይናቅ ነጻነትና ውሳኔ ለማድረግ የሚችሉበት መስክ ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ልባም ሴት” ሲናገር “የባልዋ ልብ ይታመንባታል” ይላል። በእርግጥም ቤተሰቡን ማስተዳደር፣ የምግብ ግዢውን መቆጣጠር፣ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ መዋዋል፣ አነስተኛ የንግድ ሥራን ማካሄድና የመሳሰሉት ጉዳዮችን ማከናወን እንድትችል እምነት ይጣልባት ነበር።—ምሳሌ 31:10–31

9. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች እውነተኛ ተገዢነትን ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ተገዢ ሆና እንድትቀጥል ምን ሊረዳት ይችላል?

9 ያም ሆኖ ግን ፈሪሃ አምላክ ያላት ሚስት የባልዋን ሥልጣን ታከብራለች። ለምሳሌ ያህል ሣራ ‘ለአብርሃም፦ ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት።’ ይህም ለይስሙላ ያደረገችው የትሕትና መግለጫ ሳይሆን የተገዢነቷ እውነተኛ ነጸብራቅ ነበር። (1 ጴጥሮስ 3:6፤ ዘፍጥረት 18:12) በተጨማሪም ከባሏ ጋር በድንኳን ውስጥ ለመኖር በዑር ከተማ የነበራትን ምቹ ቤት ለመተው ፈቃደኛ ሆናለች። (ዕብራውያን 11:8, 9) ይሁን እንጂ ተገዢነት ሲባል አንዲት ሚስት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በኃላፊነት የሚያስጠይቁ ጉዳዮችን ማከናወን አትችልም ማለት አይደለም። ሙሴ አምላክ ስለ ግዝረት ያወጣውን ሕግ ሳይፈጽም በቀረ ጊዜ ሚስቱ ሲፓራ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ሊመጣ የነበረውን መዓት አስቀርታለች። (ዘጸአት 4:24–26) ሁኔታው ፍጹም ያልሆነን ሰው በማስደሰት የሚያበቃ አልነበረም። ሚስቶች ‘ለጌታ እንደሚገዙ [ቆጥረው አዓት] ለባሎቻቸው መገዛት አለባቸው።’ (ኤፌሶን 5:22) አንዲት ክርስቲያን ሚስት ሁኔታውን ከአምላክ ጋር ካላት ዝምድና አንጻር የምትመለከት ከሆነ የባሏን ጉድለቶችና ድክመቶች ለማለፍ ቀላል ይሆንላታል። ባሏ እርሷን ልክ እንደዚሁ አድርጎ እንዲይዛት እንደታዘዘው ማለት ነው።

መነጋገር የትዳር የደም ሥር ነው

10. እርስ በእርስ መነጋገር ለትዳር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

10 አንድ የፍቺ ነገረ ፈጅ የትዳር ጓደኟሞች የሚለያዩበት አንዱ ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ “ሁሉንም ግልጥልጥ አድርገው መነጋገር አለመቻላቸው ነው፤ በልባቸው ያለውን አውጥተው አይነጋገሩም። አንደኛው ሌላውን የቅርብ ጓደኛው አድርጎ አይመለከትም” ብለዋል። አዎን፣ እርስ በእርስ መነጋገር ለጠንካራ ትዳር የደም ሥር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል።” (ምሳሌ 15:22) ባልና ሚስት የሞቀና የተቀራረበ ዝምድና ያላቸው ‘የምሥጢር ጓደኛሞች’ መሆን አለባቸው። (ምሳሌ 2:17) ሆኖም ብዙ ባልና ሚስቶች እርስ በእርስ መነጋገር አዳጋች ሆኖባቸዋል፤ በመሆኑም ቅሬታ በትንሹ ይጀምርና እያደገ ሄዶ ድብልቅልቅ ያለ ጠብ ይሆናል። ወይም የትዳር ጓደኛሞች በመሐከላቸው ስስ የጨዋነት መጋረጃ ይዘረጉና አልደርስብህም አትድረስብኝ ተባብለው ይኖራሉ።

11. በባልና በሚስት መካከል የሚደረገው ንግግር መሻሻል የሚችለው እንዴት ነው?

11 የችግሩ አንዱ ክፍል ብዙውን ጊዜ ወንዶችና ሴቶች የተለያየ የንግግር ስልት ያላቸው መሆኑ ይመስላል። አብዛኛዎቹ ሴቶች ስሜት ነክ የሆኑ ነገሮችን አንስቶ መወያየቱ ደስ ይላቸዋል፤ ወንዶቹ ግን በጥቅሉ ቁም ነገሮችን የሚዳስስ ውይይት ማድረጉን ይመርጣሉ። ሴቶች በይበልጥ አዘኔታ የማሳየትና ስሜታዊ ድጋፍ የመስጠት ዝንባሌ አላቸው፤ ወንዶቹ ግን መፍትሔ ወደ መሻትና ወደ መስጠት ያዘነብላሉ። ያም ሆኖ ግን ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች “ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቁጣም የዘገየ” በመሆን እርስ በእርስ መነጋገር የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ አለ። (ያዕቆብ 1:19) ፊት ለፊት እየተያያችሁ ንግግሩን በጥሞና ተከታተሉ። አሳቢነት የተሞላባቸው ጥያቄዎችን በመጠያየቅ ተጨማሪ ሐሳብ እንዲናገር ጋብዙ። (ከ1 ሳሙኤል 1:8፤ ምሳሌ 20:5 ጋር አወዳድር።) የትዳር ጓደኛችሁ የደረሰበትን ችግር በሚገልጽበት ጊዜ ወዲያውኑ መፍትሔ ለመስጠት ከመጣደፍ ይልቅ በጥሞና ተደማምጣችሁ መፍትሔ ፈልጉ። አንድ ላይ ሆናችሁ በትሕትና በመጸለይ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ጣሩ።—መዝሙር 65:2፤ ሮሜ 12:12

12. ክርስቲያን የሆኑ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በእርስ መወያየት የሚችሉበትን ጊዜ መዋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

12 አንዳንድ ጊዜ የኑሮ ጫናዎችና ውጥረቶች የትዳር ጓደኛሞች ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ እንዳይችሉ ጊዜ ወይም ጉልበት አሳጥቷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ትዳራቸው የተከበረ እንዲሆንና ከመርከስ እንዲጠበቅ እስከፈለጉ ድረስ እርስ በእርስ መቀራረብ አለባቸው። ጥምረታቸውን እንደ ውድና ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ነገር አድርገው መመልከት ይገባቸዋል። ለዚህ ጥምረታቸውም ሆነ ቁጭ ብለው ለመነጋገር ጊዜ መዋጀት አለባቸው። (ከቆላስይስ 4:5 ጋር አወዳድር።) በአንዳንድ ሁኔታዎች ገንቢ ለሆነ ውይይት ጊዜ ለማግኘት መፍትሔው ቴሌቪዥንን የመዝጋት ያህል የቀለለ ነገር ሊሆን ይችላል። ዘወትር አንድ ላይ ሆኖ ሻይ ወይም ቡና መጠጣት የትዳር ጓደኛሞች ስሜታዊ ቅርርብ እንዲፈጥሩ ሊረዳቸው ይችላል። ይህን በመሰሉ አጋጣሚዎች ቤተሰባቸውን የሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሣት ‘መመካከር’ ይችላሉ። (ምሳሌ 13:10) ትንሽ በስጨት የሚያደርጉ ወይም ሳይግባቡባቸው የቀሩ ቀላል ነገሮች ከፍተኛ የጸብ መንስኤ ወደ መሆን ከመሸጋገራቸው በፊት የመወያየት ልማድን ማዳበር እንዴት ያለ ጥበብ ነው!—ከማቴዎስ 5:23, 24፤ ኤፌሶን 4:26 ጋር አወዳድር።

13. (ሀ) ኢየሱስ ግልጽና ሐቀኛ በመሆን ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል? (ለ) የትዳር ጓደኛሞች መቀራረብ የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

13 አንድ ሰው “ብዙውን ጊዜ ሐሳቤን መግለጽና ልክ እንደተሰማኝ አድርጌ መናገር ያስቸግረኛል” በማለት ድክመቱን ሳይሸሽግ ተናግሯል። የቅርብ ግንኙነትን ለማጎልበት ግን ውስጣዊ ስሜትን ሁሉ ግልጽልጽ አድርጎ መናገር አስፈላጊ የሆነ ቁልፍ ነው። ኢየሱስ የሙሽራው አካል እንዲሆኑ ለታጩት ተከታዮቹ ምን ያህል ግልጽና ሐቀኛ እንደነበረ አስተውል። እንዲህ ብሏል፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።” (ዮሐንስ 15:15) ስለዚህ ባለቤታችሁን እንደ ወዳጅ አድርጋችሁ ተመልከቱ። የትዳር ጓደኞቻችሁን በማመን ስሜቶቻችሁን ሁሉ ንገሩአቸው። ቀላልና ምንም ያልተሸፋፈነ “የፍቅር መግለጫ” የሆነ ቃል ለመናገር ጥረት አድርጉ። (መኃልየ መኃልይ 1:2 አዓት) አንዳንድ ጊዜ ግልጽ የሆነ ንግግር ማድረግ አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች የሚፈለገውን ያህል ጥረት ሲያደርጉ ግን ትዳራቸው ዘለቄታ ያለው ጥምረት ይሆንላቸዋል።

አለመግባባትን መፍታት

14, 15. ጸብ ሊወገድ የሚችለው እንዴት ነው?

14 መሠረት ያለው አለመግባባት በየጊዜው እንደሚከሰት አሌ አይባልም። ይሁን እንጂ የቤታችሁ ሁኔታ ተባብሶ ‘በጸብ የተሞላ ቤት’ መሆን አለበት ማለት አይደለም። (ምሳሌ 17:1) በምሥጢር መያዝ ያለባቸውን ጉዳዮች ልጆቹ እየሰሙ እንዳትወያዩ ተጠንቀቁ። ለትዳር ጓደኛችሁ ስሜትም አስቡ። ራሔል መካን በመሆኗ የተሰማትን ምሬት በመግለጽ ያዕቆብ ልጅ እንዲሰጣት በጠየቀችው ጊዜ “በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን?” በማለት በቁጣ መልሶላታል። (ዘፍጥረት 30:1, 2) ቤተሰቡን የሚያውኩ ችግሮች ከተነሡ የጥቃት ቀስታችሁን በሰውዬው ላይ ሳይሆን በችግሩ ላይ አነጣጥሩ። የግል ውይይት በምታደርጉበት ጊዜ ‘ሳታስቡ የምትናገሩ’ አትሁኑ፤ ሌላው እየተናገረ ሳያስፈልግ ጣልቃ አትግቡ።—ምሳሌ 12:18

15 እውነት ነው፣ ነገሩ በኃይል ተሰምቷችሁ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም “መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም” ሳይታከልበት ሊገለጽ ይችላል። (ኤፌሶን 4:31) “ችግሮቻችሁን በተለመደ የድምጽ ቃና ተወያዩ” በማለት አንድ ባል ይናገራል። “ድምጹ ካየለ ውይይታችሁን አቁሙ። ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ ተመለሱና ውይይታችሁን እንደገና ጀምሩ።” ምሳሌ 17:14 “ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው” በማለት ጥሩ ምክር ይሰጣል። ሁለታችሁም ንዴታችሁ ከበረደላችሁ በኋላ እንደገና ለመወያየት ሞክሩ።

ምን ጊዜም አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሁኑ

16. ምንዝር ይህን ያህል ከባድ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ዕብራውያን 13:4 “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” ይላል። ምንዝር አምላክን ባለመታዘዝ የሚፈጸም ኃጢአት ነው። ትዳርንም ያቃውሳል። (ዘፍጥረት 39:9) አንዲት የትዳር አማካሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ምንዝር እንደተፈጸመ አንዴ ከታወቀ እንደ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ መላውን ቤተሰብ ያናጋዋል። ቤተሰቦችን ይበታትናል፤ እምነትንና በራስ መተማመንን ያሳጣል፤ ልጆቹንም ይጎዳል።” እርግዝና ወይም በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሊከሰቱም ይችላሉ።

17. ምንዝር የመፈጸም ዝንባሌዎችን ከሩቁ መከላከል፣ አለዚያም ጀምሮ ከሆነ ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?

17 አንዳንድ ሰዎች በመጻሕፍት፣ በቴሌቪዥንና በፊልሞች በረቀቀ መንገድ የሚተላለፈውን የዓለምን የተበላሸ የጾታ ብልግና ወደ አእምሮአቸው በማንቆርቆር ምንዝር የመፈጸም ዝንባሌ እንዲያይልባቸው ይፈቅዳሉ። (ገላትያ 6:8) ነገር ግን ምንዝር የሚከሰተው እንዲሁ የጾታ ግንኙነት የመፈጸም ፍላጎት ስላለ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው አሁንም ቢሆን እማርካለሁ የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት በተግባር ለማሳየት ወይም ይበልጥ እንደሚወደድ ሆኖ እንዲሰማው ስለሚፈልግ የሚያደርገው ነገር እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ይናገራሉ። (ከምሳሌ 7:18 ጋር አወዳድር።) ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አንድ ክርስቲያን በሐሳብ ውስጥ የሚጉላሉ የጾታ ብልግና ቅዠቶችን ማስተናገድ የለበትም። ምንም ነገር ሳትደብቁ የተሰማችሁን ነገር ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩ። አስፈላጊ ከሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ ጠይቁ። እንዲህ ማድረጉ ወደ ኃጢአት ከመውደቅ ሊጠብቃችሁ ይችላል። ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ተቃራኒ ጾታ ከሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር አንዳንድ ነገሮችን በሚያከናውኑበት ጊዜ ጠንቃቆች መሆን ያስፈልጋቸዋል። አንድን ሰው አግብቶ ሌላን ሰው በጾታ መመኘት ከቅዱሳን ጽሑፎች መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ነው። (ኢዮብ 31:1፤ ማቴዎስ 5:28) ክርስቲያኖች በተለይ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ስሜታዊ ቅርርብ እንዳይፈጥሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ግንኙነቶች ወዳጃዊ ይሁኑ፤ ግን በሩቁ።

18. በትዳር ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከጾታ ግንኙነት ጋር ለተያያዙ ችግሮች መንስኤ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

18 ከአደጋ ይበልጥ ሊጠብቅ የሚችለው ከትዳር ጓደኛ ጋር የሞቀና ግልጽ የሆነ ግንኙነት መኖሩ ነው። በትዳር ውስጥ ከጾታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እምብዛም አካላዊ ባሕርይ እንደሌላቸው፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በእርስ ንግግር ባለመኖሩ የሚከሰቱ ችግሮች እንደሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱ ሰዎች ይናገራሉ። አንድ ባልና ሚስት በግልጽ የሚነጋገሩ ከሆነና የወሲብ ግዴታን እንደ ግዴታ ሳይሆን እንደ ፍቅር መግለጫ አድርገው ሲመለከቱት ከጾታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እምብዛም አይኖሩም።a ይህን የመሰሉ ትክክለኛ ሁኔታዎች ካሉ ወሲባዊ ግንኙነት የትዳር ማሰሪያን ለማጠንከር ይረዳል።—1 ቆሮንቶስ 7:2–5፤ 10:24

19. “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ” የሆነው ነገር ምንድን ነው? በትዳርስ ላይ ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

19 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ” ፍቅር ነው። አምላክን የሚፈሩ ባልና ሚስት ፍቅርን በመኮትኮት ዘወትር ‘እርስ በርሳቸው ትዕግሥትን ማድረግና በነጻ ይቅር መባባል ይችላሉ።’ (ቆላስይስ 3:13, 14 አዓት) በመሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተገነባ ፍቅር ስለ ሌሎች ደህንነት ያስባል። (1 ቆሮንቶስ 13:4–8) እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ኮትኩቱ። የጋብቻ ማሰሪያችሁን ለማጠንከር ይረዳችኋል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በትዳር ዓለማችሁ ውስጥ በሥራ ላይ አውሏቸው። እንደዚህ ካደረጋችሁ ትዳራችሁ ዘለቄታ ያለው ጥምረት ይሆናል፤ ለይሖዋ አምላክም ውዳሴና ክብር ያመጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በነሐሴ 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “የሐሳብ ግንኙነት ሲባል መነጋገር ማለት ብቻ አይደለም” የሚለው ርዕስ ባልና ሚስት በዚህ ረገድ ያሉትን ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ገልጿል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ትዳር ምን ጊዜም የማይበጠስ ማሰሪያ መሆን የሚገባው ለምንድን ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራስነት ሥልጣንና ስለ ተገዢነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

◻ ባልና ሚስቶች የእርስ በርስ ንግግራቸውን ማሻሻል የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ ባልና ሚስቶች አለመግባባትን በክርስቲያናዊ መንገድ መፍታት የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ የትዳርን ማሰሪያ ለማጠንከር ምን ይረዳል?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱ ሰብዓዊ ሥራ የምትሠራ ከሆነ ከአቅሟ በላይ የሆነ ሸክም እንዲወድቅባት አያደርግም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ