ለአረጋውያን ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት
በ18ተኛው መቶ ዘመን የነበሩ አንድ ሳሙኤል ጆንሰን የተባሉ ደራሲ ከጻፏቸው ልብ ወለድ ታሪኮች በአንዱ ላይ ጓደኞቹን ለመጠየቅ ወደየቤታቸው ከሄደ በኋላ ባርኔጣውን የት እንደጣለ ማስታወስ ስላቃተው አንድ ወጣት ተርከው ነበር። ወጣቱ ያሳየው ግድየለሽነት ምንም ትችት አላመጣበትም። ሳሙኤል ጆንሰን በመቀጠል ሲናገሩ “ይህን ዓይነቱን የግዴለሽነት ድርጊት የፈጸመው አንድ አረጋዊ ቢሆን ኖሮ ግን ‘በቃ መርሳት ጀመረ ማለት ነው’ ብለው ሰዎች ሁሉ በተዘባበቱበት ነበር” ብለዋል።
ጆንሰን የጻፉት ልብ ወለድ ታሪክ እንደ ሌሎቹ አናሳ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ሁሉ አረጋውያንም አግባብ የሌለው የተለመደ ትችት እንደሚደርስባቸው ያሳያል። አረጋውያንን መጦር ጥረት የሚጠይቅ ሥራ ቢሆንም ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ከጥቅሙ ይቋደሳሉ። ፈታኝ የሆኑትና በኋላ ግን የሚክሱት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ይህስ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎችን የሚያሳስባቸው ለምንድን ነው?
በተገኘው አኅዛዊ መረጃ መሠረት 6 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ዕድሜ 65 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ነው። በአደጉት አገሮች ደግሞ ቁጥሩ ከዚህ በሁለት እጥፍ ይበልጣል። 1993 “ለአረጋውያንና በትውልዶች መካከል ለተፈጠረው ኅብረት መታሰቢያ የሚሆን የአውሮፓውያን ዓመት” እንዲሆን በሰየመው በአውሮፓ ማኅበረሰብ ውስጥ ከሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ዕድሜው ከ50 ዓመት በላይ ነው። በአብዛኞቹ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በዚያም የወሊድ ቁጥር መቀነስና የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ ከፍ ማለት አብዛኛው የኅብረተሰቡ ክፍል ከመካከለኛው ዕድሜ እንዲያልፍ እያደረገው ነው። እንደነዚህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር በዕድሜ በጣም የገፉ ሰዎችን መንከባከብ ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ መሆኑ አያጠያይቅም። በጥንት ምሥራቃውያን ዘንድ ሁኔታዎቹ ምንኛ የተለዩ ነበሩ!
“የእውቀት ጎተራዎች”
ሃንትዋርተርባች ዴስ ቢብሊሸን አልተርተምስ ፈር ጌቢልዴቴ ቢቤልሌሰር (ለተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥንታዊነት የሚያስረዳ መመሪያ መጽሐፍ) የተባለው መጽሐፍ እንደጠቆመው በጥንቱ የምሥራቃውያን ትውልድ ዘንድ “አረጋውያን የጥበብን ባህላዊ ጥቅሞችና ከፍተኛ እውቀትን ጠብቀው የሚያቆዩ ተደርገው ይታዩ ስለነበር ወጣቶች ከእነርሱ ጋር እንዲጎዳኙና ትምህርት እንዲቀስሙ ይመከሩ ነበር።” የስሚዝ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይህንን ሲያብራራ፦ “በሰዎች የግል ሕይወት ውስጥ [አረጋውያን] የእውቀት ጎተራ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር . . . [ወጣቶች] በመጀመሪያ አረጋውያኑ ያላቸውን ሐሳብ እንዲገልጹ ዕድል ይሰጧቸው ነበር።”
በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሊሰጣቸው የሚገባው ክብር በሙሴ ሕግ ውስጥም በዘሌዋውያን 19:32 ላይ እንደሚከተለው በማለት ተገልጿል፦ “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር።” ስለዚህ ያረጁ ሰዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸውና እንደ ብርቅ የሚታዩ ነበሩ። ይህም ሞዓባዊቷ ሩት እስራኤላዊ ለነበረችው ለአማቷ ለኑኃሚን ከነበራት አመለካከት ጋር አንድ ነው።
ሩት ከኑኃሚን ጋር ከሞዓብ ወደ እስራኤል አብራ ለመጓዝና ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ ቢሆን የምትሰጣትን ምክር በጥንቃቄ ለማዳመጥ ቆርጣ ነበር። ቤቴልሔም ከደረሱም በኋላ ይሖዋ ነገሮችን መስመር እያስያዘ መሆኑን የተረዳችውና ሩት ምን ማድረግ እንዳለባት የነገረቻት ኑኃሚን ነበረች። (ሩት 2:20፤ 3:3, 4, 18) ሩት ተሞክሮ ከነበራት ከኑኃሚን ትምህርት ስለቀሰመች ሕይወቷ ቲኦክራሲያዊ ፈር ይዞ ነበር። አማቷ ኑኃሚን የእውቀት ጎተራ እንደነበረች አስመሥክራለች።
ዛሬም በተመሳሳይ ወጣት ክርስቲያን ሴቶች በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ በዕድሜ የገፉ ሴቶች ጋር በመቀራረብ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ምናልባት አንዲት እኅት ትዳር ለመመሥረት እያሰበች ወይም ከአንድ ከባድ ከሆነ የግል ችግሯ ጋር እየታገለች ሊሆን ይችላል። በጉዳዩ ላይ ተሞክሮ ያላትን የአንዲት የበሰለች አረጋዊት እኅት ምክርና ድጋፍ መጠየቋ ምንኛ ጥበብ ነው!
ከዚህም በላይ የሽማግሌዎች አካል በመካከላቸው ያሉትን አረጋውያን ተሞክሮ በመቅሰም ሊጠቀም ይችላል። ሎጥ ይህን ለማድረግ ባለመቻሉ ከደረሰበት ነገር ትምህርት ማግኘት እንችላለን። የአብርሃምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት እረኞች መካከል የተነሣው ጥል ሁሉንም የሚነካ ውሳኔ ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። ሎጥ ጥበብ የጎደለው ምርጫ አደረገ። አስቀድሞ የአብርሃምን ምክር ጠይቆ ቢሆን ኖሮ እንዴት የተሻለ ይሆን ነበር! ሎጥ የበሰለ ሰው የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ቸኩሎ ባደረገው ምርጫ ምክንያት ከመጣበት መከራ ቤተሰቡን ባዳነ ነበር። (ዘፍጥረት 13:7–13፤ 14:12፤ 19:4, 5, 9, 26, 29) በአንድ ጥያቄ ላይ ወደ ራስህ መደምደሚያ ከመድረስህ በፊት የበሰሉ አረጋውያን የሚነግሩህን በጥንቃቄ ታዳምጣለህን?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖሩት እንደ ስምዖንና ሐና ሁሉ ዛሬም ለይሖዋ ሥራ የማይከስም ቅንዓት ያላቸው በጣም ብዙ በዕድሜ የገፉ ሰዎች አሉ። (ሉቃስ 2:25, 36, 37) ምንም እንኳ ዕድሜያቸው የገፋ ቢሆንም እንደዚህ ያሉትን አረጋውያን አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን በጉባኤው እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረጉ ለእነርሱ ያለንን አክብሮት የሚያንጸባርቅና እንደምንንከባከባቸው የሚያሳይ ነው። ምናልባት አንድ ወጣት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተሰጠውን ክፍል ለመዘጋጀት እርዳታ ያስፈልገው ይሆናል። በዚህ ጊዜ አንድ አስተዋይ የሆነ ሽማግሌ የክፍሉ ረዳት ሆኖ ለመሥራት ተስማሚ የሆነው ሰው በዕድሜ ተሞክሮ ጥበብን ያካበቱ ደግና ጊዜ ያላቸው በዕድሜ የገፉ አረጋዊ ወንድም ወይም እኅት እንዲሆኑ ሊወስን ይችላል።
ይሁን እንጂ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ያሏቸውን ልዩ ፍላጎቶች ማሟላት በዚህ ብቻ አያበቃም። ብዙዎቹ በብቸኝነት ስሜት፣ ወንጀል ይፈጸምብኛል በሚል ስጋትና በኢኮኖሚ ችግር ይደቆሳሉ። ከዚህም በላይ አረጋውያኑ አንዴ መደካከም ከጀመሩ እነዚህ ችግሮች በጤና እክሎችና ጉልበታቸው መድከሙን በማሰብ በሚመጣባቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይባባሳሉ። በዚህ ወቅት ከምን ጊዜውም የበለጠ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል። ግለሰብ ክርስቲያኖችና መላው ጉባኤ ለዚህ ነገር ምላሽ መስጠት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን አሳዩ’
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት በ1 ጢሞቴዎስ 5:4, 16 ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር፦ “ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ (ለአምላክ ያደሩ ይሆኑ አዓት) ዘንድ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ ነውና። ባልቴቶች ያሉት የሚያምን ቢሆን ወይም የምታምን ብትሆን ይርዷቸው፣ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞቹን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት።” አረጋውያንን መጦር የቤተሰብ ኃላፊነት ነበር። አንድ በዕድሜ የገፉ የጉባኤው አባል ቤተሰቡ የሚችለውን ሁሉ ካደረገላቸውም በኋላ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ኃላፊነቱ በጉባኤው ጫንቃ ላይ ይወድቅ ነበር። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ዛሬም አልተለወጡም።
ክርስቲያኖች በቤተሰባቸው መካከል ለአምላክ ያደሩ ሆነው በመመላለስ ለአረጋውያን ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲያሳዩ የረዳቸው ምንድን ነው? በዕድሜ የገፉ ሰዎችን በመንከባከብ አንዳንድ ተሞክሮዎች ያሏቸው በርከት ያሉ ምሥክሮች የሰጧቸውን የሚከተሉትን አስተያየቶች ልብ በሉ።
ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ያላሰለሰ ትኩረት መስጠት
ሚስቱ ወላጆቿን ስትጦር ከጎኗ ሆኖ ይረዳት የነበረው ፌሊክስ “የዕለት ጥቅሱን አንድ ላይ መወያየት ይህ ነው የማይባል እገዛ ነበረው” ብሏል። “የግል የሕይወት ተሞክሯችንና እነርሱን ለመርዳት ያለን ጠንካራ ፍላጎት ከይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የተጣመረ ነበር።” በእርግጥም አረጋውያንን የመጦሩን ከባድ ሥራ በሚገባ ለመወጣት ዋነኛው መንገድ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መንፈሳዊነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር ነው። ይህም ኢየሱስ በማቴዎስ 5:3 [አዓት] ላይ “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” በማለት ከተናገራቸው ቃላት አንጻር ስናየው ተገቢ ነው። ከዕለት ጥቅሱ ጎን ለጎን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራምን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ላይ የሚደረግ ውይይትንና ጸሎትን መጨመር ይቻላል። ፒተር “አረጋውያኑ አንድ ነገር ከተጀመረ ያለማሰለስ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ይመስላል” ሲል ተናግሯል።
አዎን፣ በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ አዘውታሪ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። አረጋውያን ለመንፈሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ለሚደረግላቸው ያላሰለሰ እርዳታም አመስጋኞች ናቸው። ቀላል የሆነ አካላዊ እክል ያለባቸውም እንኳ “በየዕለቱ ከአልጋቸው እንዲነሡና ልብሳቸውን በትክክል እንዲለብሱ” በደግነት ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይችላል በማለት ኡርስላ አስተያየቷን ሰጥታለች። እርግጥ ነው በዕድሜ የገፉት ሰዎች አዛዥ የሆንባቸው እንዳይመስላቸው መጠንቀቅ እንፈልጋለን። ዶሪስ ብዙውን ጊዜ በቅንነትና በደግነት የምታደርጋቸውን ነገሮች እንደሚያጣጥሉባት ተናግራለች። “የማልሠራው ስህተት የለም። አንድ ቀን አባቴን ሸሚዙን በየቀኑ እንዲቀይር ነገርኩት። እናቴ ግን ‘አሁንም ቢሆን ባለቤቴ መሆኑን አትርሺ!’ ስትል አሳሰበችኝ።”
የዛሬዎቹ አረጋውያን በአንድ ወቅት ወጣቶች ነበሩ፤ ወጣቶች ግን ራሳቸውን በአረጋውያኑ ቦታ አስቀምጠው ችግራቸውን መረዳት ያዳግታቸዋል። ይሁንና ግን አረጋውያን ያሏቸውን ለየት ያሉ ፍላጎቶች ለመረዳት ደግሞ ቁልፉ ይህ ነው። ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ሆደባሻ ያደርጋል። ጌርሃርድ ይህንን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አማቴ በፊት ያደርጓቸው የነበሩትን ነገሮች አሁን ለመሥራት ባለመቻላቸው በራሳቸው በጣም ይበሳጫሉ። ያለውን ሁኔታ በጸጋ መቀበል ፈጽሞ የማይዋጥላቸው ነገር ነው። ጠባያቸው ሁሉ ተቀይሯል።”
አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው ሁኔታዎቹ እየተለወጡ ሲሄዱ በውስጡ የሚፈጠረውን የሆደባሻነት ስሜት በሌሎች ሰዎች በተለይም በሚንከባከቡት ሰዎች ላይ ነቀፋ በመሰንዘር መግለጹ እንግዳ ነገር አይደለም። ምክንያቱ ግልጽ ነው። የሚያደርጉለት ፍቅራዊ እንክብካቤ ጉልበቱ መድከሙን ያስታውሰዋል። ለዚህ ተገቢ ያልሆነ ነቀፋ ወይም ቅሬታ የምትሰጠው ምላሽ ምን መሆን አለበት?
እንደዚህ ዓይነቶቹ አፍራሽ ስሜቶች እናንተ ለምታደርጉት ጥረት ይሖዋ ያለውን አመለካከት እንደማያንጸባርቁ አስታውሱ። አልፎ አልፎ አለምክንያት በቃላት ቢወርፏችሁም እንኳ መልካም ማድረጋችሁን በመቀጠል ንጹህ ሕሊና ይዛችሁ ኑሩ። (ከ1 ጴጥሮስ 2:19 ጋር አወዳድር።) አረጋውያኑ ያሉበት ጉባኤም ብዙ ድጋፍ ሊሰጣቸው ይችላል።
ጉባኤው ምን ሊያደርግ ይችላል?
ብዙ ጉባኤዎች ውድ አረጋዊ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ቀደም ሲል ላደረጓቸው ነገሮች ከልብ አመስጋኝ የሚሆኑበት ምክንያት አላቸው። ምናልባት ከአሥርተ ዓመታት በፊት የጉባኤውን መሠረት የጣሉትና ጥቂት አስፋፊዎች ብቻ ከነበሩበት ሁኔታ ተነሥተው ጉባኤውን የገነቡት እነዚሁ አረጋውያን ይሆናሉ። ያኔ የእነርሱ ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴ ባይኖርና ምናልባትም ዛሬ የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ጉባኤው የት ይደርስ ነበር?
ለአንድ በዕድሜ ለገፉ አስፋፊ ተጨማሪ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኃላፊነቱ ለቤተሰቡ አባላት ብቻ መተው የለበትም። ሌሎችም በመላላክ፣ ምግብ በማብሰል፣ በማጽዳት፣ በዕድሜ የገፉትን ሰው በእግር በማንሸራሸር፣ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመኪና በመውሰድ ወይም በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ቀረብ ብሎ በማጫወት ሊደግፏቸው ይችላሉ። በሥራው ሁሉም ሊሳተፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን አረጋውያኑን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ያለማሰለስ በደንብ መርዳት የሚቻለው የሚደረጉትን ጥረቶች ማቀናጀት ሲቻል ነው።
ሽማግሌዎች እረኝነት ለማድረግ ፕሮግራም በሚያወጡበት ጊዜ እንዴት አድርገው ቅንጅቱን መፍጠር እንደሚችሉ ሊያስቡበት ይችላሉ። አንዳንድ ጉባኤዎች በዚህ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። ሽማግሌዎች በዕድሜ ለገፉትና አቅማቸው ለደከመው ወንድሞችና እህቶች፣ ሌላው ቀርቶ በቤተሰቦቻቸው በደንብ እንክብካቤ ለሚያደርጉላቸው እንኳ ሳይቀር ቋሚ ጉብኝት ያደርጉላቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጉባኤዎች አረጋውያንን በመንከባከብ ረገድ ስላለባቸው ግዴታ ይበልጥ ሊያስቡበት የሚገባ ይመስላል።
ወደ 90 ዓመት ዕድሜ እየተጠጉ ያሉ አንድ ታማኝ ወንድም እሳቸውን ለመንከባከብ ሲሉ የቤቴል አገልግሎታቸውን ያቋረጡት ሴት ልጃቸውና የልጃቸው ባል ይንከባከቧቸው ነበር። ያም ሆኖ ግን ሌሎቹ የጉባኤ አባሎች እየመጡ እንዲጠይቋቸው በጣም ይፈልጉ ነበር። እኚህ ወንድም እንዲህ ሲሉ አማረዋል:– “እኔ የታመሙትን እጠይቅ በነበረበት ጊዜ አብሬያቸው እጸልይ ነበር። ከእኔ ጋር ግን እስከ ዛሬ ድረስ አብሮኝ የጸለየ አንድም ሰው የለም።” ዘመዶቻቸው ለአረጋውያኑ ፍቅራዊ እንክብካቤ ማድረጋቸው ሽማግሌዎች ‘በእነርሱ ዘንድ ያለውን መንጋ መጠበቅን’ በተመለከተ ካለባቸው ግዴታ ነጻ አያደርጋቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:2) ከዚህም በተጨማሪ አረጋውያንን የሚንከባከቡትም ቢሆኑ በመልካም ሥራቸው እንዲገፉበት ሊታነጹና ሊበረታቱ ይገባቸዋል።
‘የሸመገሉና በዕድሜያቸው የረኩ ሰዎች’
በ19ኛው መቶ ዘመን የጀርመን ሳይንቲስት የነበሩት ቮን ሃምቦልት አንዲት ወጣት ሴት ‘እርጅናን አሰልቺ ሆኖ አላገኙትም?’ ብላ በጠየቀቻቸው ወቅት ዕድሜያቸው በጣም ገፍቶ ነበር። እኚህ ምሑር “አልተሳሳትሽም፤ ግን ረጅም ዕድሜ ለመኖር ያለው አማራጭ ይህ ብቻ ነው” ሲሉ መለሱላት። በተመሳሳይም ዛሬ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ላገኙት ረጅም ዕድሜ አድናቆት ስላላቸው በእርጅና ምክንያት የሚመጡትን መከራዎች በፀጋ በመቀበል ጥሩ ምሳሌ ትተዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ‘የሸመገሉትና በዕድሜያቸው የረኩት’ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ዳዊትና ኢዮብ ያሳዩትን ዓይነት ዝንባሌ ያንጸባርቃሉ።—ዘፍጥረት 25:8፤ 35:29፤ 1 ዜና መዋዕል 23:1፤ ኢዮብ 42:17
ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ የሌሎችን እርዳታ በጸጋ የመቀበልንና ከልብ የማመስገንን ፈታኝ ሁኔታ ያስከትላል። ጥበብ እያንዳንዱ ሰው አቅሙን እንዲያውቅ ይጠይቅበታል። ይሁን እንጂ አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው እጁን አጣጥፎ መቀመጥ አለበት ማለት አይደለም። አንድ ማሪያ የሚባሉ እህት ወደ መቶ ዓመት ዕድሜያቸው እየተጠጉ ቢሆንም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ፤ እንዲሁም እጃቸውን እያወጡ ሐሳብ ይሰጣሉ። ይህንን የሚያደርጉት እንዴት ነው? “የማንበቡ ነገር እንደሆነ ያከተመለት ጉዳይ ሆኗል፤ ሆኖም በካሴት የተቀዳውን መጠበቂያ ግንብ አዳምጣለሁ። ከሰማሁት ውስጥ አንዳንዱን እረሳዋለሁ፤ ሆኖም ብዙውን ጊዜ መልስ ለመመለስ እችላለሁ” ብለዋል። አንድ ሰው ልክ እንደ ማሪያ ጊዜው በሚገነቡ ነገሮች የተያዘ እንዲሆን ካደረገ ንቁ እንዲሆንና ክርስቲያናዊ አቋሙን ዘወትር መጠበቅ እንዲችል ይረዳዋል።
በአምላክ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ እርጅና አይኖርም። በዚህ ሥርዓት ያረጁትና አልፎ ተርፎም ለሞት የበቁት በዚያን ጊዜ አሁን ስለተደረገላቸው እንክብካቤና ስለተሰጣቸው ትኩረት ጥሩ ትዝታ ይኖራቸዋል። እንደነዚህ ያሉ አረጋውያን ሕይወታቸውና ጉልበታቸው ሲመለስላቸው ለይሖዋ አምላክ የጠለቀ ፍቅር ያድርባቸዋል፤ እንዲሁም በዚህ አሮጌ ሥርዓት በችግራቸው ጊዜ ከጎናቸው ያልተለዩትን ሰዎች በጣም ያመሰግኗቸዋል።—ከሉቃስ 22:28 ጋር አወዳድር።
አሁን አረጋውያንን በመንከባከብ ላይ ያሉትስ? በቅርቡ መንግሥቲቱ ምድርን ሙሉ በሙሉ ስትቆጣጠር ከግዴታቸው ከመሸሽ ይልቅ ለአረጋውያን ፍቅር በማሳየት ለአምላክ ያደሩ በመሆን ያሳለፉትን ጊዜ ሁሉ በደስታና በእፎይታ ወደ ኋላ መለስ ብለው ይመለከታሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:4
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አረጋውያን ብትጠይቋቸው ደስ ይላቸዋል
ከስብከት ሥራችሁ በኋላ ለ15 ደቂቃ ያህል እንኳን አንድን በዕድሜ የገፉ ወንድም ወይም እህት ለመጠየቅ እቅድ ብታወጡ አንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መልካም ነገር ማከናወን ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጥየቃ ሲያመቻችሁ ብቻ የምታደርጉት ነገር ባይሆን ይመረጣል። የሚቀጥለው ተሞክሮ ይህንን ያሳያል።
ብሪጊቴ እና ሃኔሎሬ ለስብከት ሥራ አንድ ላይ ተሰማርተው እያለ አንድን አረጋዊ ሰው ቤታቸውን አንኳኩተው ያነጋግሯቸዋል። እነዚህ እኅቶች እያነጋገሯቸው ያሉት አረጋዊ ሰውም በጉባኤያቸው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክር መሆናቸውን እስካወቁበት ጊዜ ድረስ ለአምስት ደቂቃ ያህል አነጋገሯቸው። እንዴት የሚያሳፍር ነው! ይሁንና ተሞክሮው ገንቢ ማሳሰቢያ ትቶ አልፏል። ሃኔሎሬ እኚህን ወንድም ለመጠየቅና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለመርዳት ወዲያውኑ እቅድ አወጣች።
አንተ በምትሰብክበት ክልል ውስጥ ያሉትን አረጋውያን አስፋፊዎች ስምና አድራሻ ታውቃለህን? እነርሱን ለመጠየቅ አጭር ጊዜ ልትመድብ ትችላለህን? እንዲህ ማድረግህ በጣም ሊያስመሰግንህ ይችላል።