የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል”
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ “አስማተኞች” ለጥንቆላ ይጠቀሙባቸው የነበሩትን መጻሕፍት በሕዝብ ፊት በማቃጠል ለደረሳቸው ክርስቲያናዊ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር። (ሥራ 19:19) የእነዚህ መጻሕፍት ዋጋ 50,000 ብር እንደሚሆን ተሰልቶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ የጠቀሰው ዲናር የተባለው የሮማውያን ሣንቲም ዋጋው ቢያንስ ቢያንስ 37,000 ዶላር ይሆን ነበር ማለት ነው!
በዛሬው ጊዜም በአንድ ወቅት ላይ ከጥንቆላ ሥራዎች ጋር የሚዛመዱ ጽሑፎች የነበሯቸው ግን የጥንቶቹ የኤፌሶን ነዋሪዎች የወሰኑትን ዓይነት ቆራጥ ውሳኔ ያደረጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ቀጥሎ ያለውን ከካናዳ የተገኘ ተሞክሮ ተመልከት።
ከአምስት ዓመታት በፊት አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሰበከች ሳለ ከአንዱ በር ላይ ስትደርስ ኖራ የተባለች ሴት ወደ ቤቷ ጎትታ አስገባቻት። ኖራ ለብዙ ዓመታት ያህል ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ምርምር ካደረገች በኋላ በበዙ መቶ የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊና መናፍስታዊ መጻሕፍትን ሰብስባለች፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ምን ተስፋ እንደሚሰጥ ማወቅ ትፈልግ ነበር። ምሥክሯም እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው? የሚለውን ትራክት ሰጠቻት። ኖራ ለጥያቄዎቿ መልስ አገኘች። የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት እንድትገባ የቀረበላትንም ሐሳብ ተቀበለች።
ከጊዜ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረችና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበራት ግንኙነት ተቋረጠ። ሆኖም መጽሔቶቹን በአዲሱ አድራሻዋ በፖስታ ቤት በኩል ማግኘቷን ቀጠለች። በተጨማሪም መጽሔቶቹ ላይ የተጠቀሱትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አንዳንድ ጽሑፎች እንዲላኩላት አዘዘች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ በሯ መጥታ አንኳኳች። ምሥክሯ ለሚቀርቡላት ጥያቄዎች በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመመለሷ ኖራ ተነካች። ተጨማሪ ውይይቶች ለማድረግ ተመልሳ እንድትመጣ ጋበዘቻት።
ሆኖም ምሥክሯ ኖራን እንደገና ማግኘት አስቸገራት። ከቀኑ በተለያዩ ጊዜያት እንዲሁም ከሳምንቱ በተለያዩ ቀናት ብትሄድም ሊሳካለት አልቻለም። ከጊዜ በኋላ ግን ጽናቷ ዋጋ አስገኘላት። ጥሩ ውጤትም አገኘች። ኖራ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት። በኖራ ጥያቄ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ብዙውን ጊዜ በሳምንት ሦስቴ ይደረግ ነበር። የምትማረው ነገር ለጓደኞቿና ለቤተሰቦቿ እንድትናገር ከውስጥ የሚፈነቅል ፍላጎት አደረባት። ይህን በማድረጓ ከነገረቻቸው ሰዎች መካከል ሦስቱ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲያስጠኗቸው ጥያቄ አቀረቡ።
ኖራ በጥናቷ አማካኝነት ብዙ የሐሰት ሃይማኖቶችና ሐሰተኛ ነቢያት እንዳሉ ወደ ሕይወት የሚመራው መንገድ ግን አንድ ብቻ መሆኑን ለመገንዘብ ቻለች። በሐሰት ሃይማኖቶች ውስጥ ለጥያቄዎቿ መልስ ለማግኘት ለብዙ ዓመታት ፍለጋ ስታደርግ ቆይታ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አጋንንት ምን እንደሚል ከተማረች በኋላ ግን በሥራ 19:19 ላይ የተጠቀሱት የጥንቶቹ የኤፌሶን ሰዎች የወሰዱትን ዓይነት እርምጃ ወሰደች። የመጻሕፍት መደርደሪያዋን አጸዳች። ከብዙ ቀናት ሥራ በኋላ ከጥንቆላና ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ጋር ዝምድና ያለቸው ከአንድ ሺህ የሚበልጡ መጻሕፍትን አቃጠለች። ካቃጠለቻቸው መጻሕፍት መካከል አራቱ መጽሐፎች ከ800 ዶላር በላይ ያወጡ ነበር።
ኖራ በወሰደቻቸው እርምጃዎች የተከፉት አጋንንት ለሁለት ሳምንታት ያህል ችግር ፈጠሩባት። ይሁን እንጂ እነዚህ ክፉ መናፍስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን እንዳትቀጥል ወይም ከዘመናዊው የይሖዋ ድርጅት ጋር ኅብረት እንዳይኖራት ሊያግዷት አልቻሉም።
እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት እውነት መሆናቸውን በግልጽ ያሳያሉ።—ያዕቆብ 4:7