ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
አይሁዳዊው ምሁርና ደራሲ ጆሴፍ ጃኮብዝ በአንድ ወቅት ይቅር ባይነትን “ከሁሉም የሥነ ምግባር ትምህርቶች እጅግ የላቀና በጣሙን አስቸጋሪ የሆነ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። እውነት ነው፣ ብዙዎች “ይቅርታ አድርጌልሃለሁ” የሚሉት ቃላት ይተናነቋቸዋል።
ይቅር ባይነት ከገንዘብ ጋር ይመሳሰላል። ለሌሎች በነፃና በምሕረት ሊሰጥ ይችላል፤ ወይም ደግሞ መስቆንቆን ይቻላል። የመጀመሪያው አምላካዊ መንገድ ነው። ይቅር ባይነትን በልግስና የመስጠትን ልማድ መኮትኮት ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም አምላክ እንዲህ እንድናደርግ ስለሚያበረታታና ይቅር ያለማለትና የበቀል መንፈስ ሁኔታዎችን ከማባባስ ሌላ ምንም ላይፈይድ ስለሚችል ነው።
“ምን አናደደኝ፤ ዋጋውን እሰጠዋለሁ!” የሚሉት ቃላት ብዙውን ጊዜ ይሰማሉ። በጊዜያችን ይህ አባባል ብዙ ሰዎች የሚመሩበት መሠረታዊ ሥርዓት መሆኑ ያሳዝናል። ለምሳሌ አንዲት ሴት የወንድሟን ሚስት ከሰባት ዓመት በላይ አኮረፈቻት። ሴትየዋ ለዚህ ያቀረበችው ምክንያት “በጣም በድላኝ ስለነበረ እርሷን ይቅር ለማለት ከብዶኝ ነበር” የሚል ነው። ይሁን እንጂ በዳዩ ይቅርታ እንዲጠይቅ ለማድረግ በዚህ ዓይነቱ ኩርፊያ መጠቀም ወይም ሰውዬውን ለመቅጣት እንደ መሣሪያ አድርጎ ኩርፊያን መጠቀም የበቀልን ፍላጎት እምብዛም አያረካም። ከዚህ ይልቅ አለመግባባቱን ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥልና ቂም እየጎለበተ እንዲሄድ በር ሊከፍት ይችላል። ይህ እርስ በእርስ የመቆሳሰሉ ሂደት ካልተገታ ኃይለኛው የተበቃይነት ማነቆ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያሻክርብን፤ ብሎም ጤንነታችንን ሊያቃውስብን ይችላል።
ይቅር ያለማለት መንፈስ የሚያስከትለው ጉዳት
አንድ ሰው ይቅር ሳይል በሚቀርበት ጊዜ የሚከሰተው ቅራኔ የአእምሮ ውጥረት ይፈጥራል። ጭንቀቱ ደግሞ ከባድ የሆነ ሕመም ሊያስከትል ይችላል። ዶክተር ዊልያም ኤስ ሳድለር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “አብዛኛው የሰው ልጅ በሽታና ሥቃይ ከጭንቀት፣ ከፍርሃት፣ ከቅራኔ፣ . . . ጤናማ ካልሆነ አስተሳሰብና ከረከሰ አኗኗር ጋር በሚያስደንቅ ሁኔታ በቀጥታ የሚዛመዱ መሆናቸውን ማንም ሰው የዶክተርን ያህል ሙሉ በሙሉ መገንዘብ አይችልም።” ታዲያ እንዲህ ከሆነ የስሜት መረበሽ የሚያስከትለው ጉዳት ምን ያህል ነው? አንድ የሕክምና ጽሑፍ “ወደ ሐኪም ከሚሄዱት ታካሚዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በአእምሮ ውጥረት ሳቢያ የተከሰቱ ወይም የተባባሱ የበሽታ ምልክቶች እንደተገኙባቸው አኃዛዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ” የሚል መልስ ሰጥቷል።
አዎን፣ መራርነት፣ ቅሬታና እልህ የማይጎዱ ነገሮች አይደሉም። እነዚህ መርዘኛ ስሜቶች የአንድን መኪና አካል ቀስ በቀስ እንደሚበላ ዝገት ናቸው። መኪናዋ ከውጭ ስትታይ ውብ ልትመስል ትችላለች፤ ከቅቡ በስተጀርባ ግን አጥፊ የሆነ ሂደት እየተካሄደ ነው።
ከዚህ ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ ምሕረት ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት እያለ ይቅር ለማለት አሻፈረኝ ማለታችን መንፈሳዊነታችንንም ሊጎዳው የሚችል መሆኑ ነው። በይሖዋ አምላክ ዓይን በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ባሪያ ሆነን ልንታይ እንችላለን። ባሪያው የነበረበትን ከፍተኛ ዕዳ ጌታው ማረው። ሆኖም እርሱ ከነበረበት ዕዳ ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ዕዳ የነበረበት አብሮት ይሠራ የነበረው ባሪያ እንዲምረው ሲማጸነው አመናጨቀው፤ ሊምረውም አልፈቀደም። እኛም በተመሳሳይ ይቅር ለማለት አሻፈረኝ የምንል ከሆነ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይል ኢየሱስ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 18:21–35) ስለዚህ ይቅር የማንል ከሆነ በአምላክ ፊት ያለንን ንጹሕ ሕሊናና አልፎ ተርፎም ለወደፊቱ ጊዜ ያለንን ተስፋ ልናጣ እንችላለን! (ከ2 ጢሞቴዎስ 1:3) ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?
ይቅር ማለትን ተማር
እውነተኛ ይቅር ባይነት የሚፈልቀው ከልብ ነው። የበዳዩን ስሕተት ከአእምሮ ማውጣትንና ማንኛውንም የበቀል ፍላጎት ማስወገድን ያካትታል። በዚህ መንገድ የመጨረሻው ፍትሕና ምናልባትም አስፈላጊ ከሆነ የበቀል እርምጃ ለይሖዋ ይተዋል።—ሮሜ 12:19
ይሁን እንጂ “ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ” ስለሆነች ሁልጊዜ ይቅር ወደ ማለት እንደማታዘነብል መዘንጋት የለበትም። ሌላው ቀርቶ ይቅርታ ማድረግ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይቅር ወደ ማለት ላታዘነብል ትችላለች። (ኤርምያስ 17:9) ኢየሱስ ራሱ “ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና” ብሏል።—ማቴዎስ 15:19
ደስ የሚለው ግን ልባችን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ መሠልጠን የምትችል መሆኗ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የሚያስፈልገን ማሠልጠኛ ከእኛ በላይ ከሆነ አካል መምጣት አለበት። ብቻችንን ልናደርገው የምንችለው ነገር አይደለም። (ኤርምያስ 10:23) በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት የጻፈው መዝሙራዊ ይህን በመገንዘብ የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ጸልዮ ነበር። “ሥርዓትህን አስተምረኝ። የሥርዓትህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ” በማለት ይሖዋን በጸሎት ተማጽኗል።—መዝሙር 119:26, 27
ሌላው መዝሙር እንደሚለው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ‘መንገድ ማስተዋል’ ችሎ ነበር። ይህ ሁኔታ በራሱ ላይ ደርሶበት ተምሯል። በመሆኑም እንዲህ ሲል መናገር ችሎ ነበር፦ “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል።”—መዝሙር 103:8, 13
እኛም እንደ ዳዊት ‘የይሖዋን መንገድ’ መማር ይገባናል። ወደ አምላክ እየጸለይን የእርሱን ፍጹም የይቅር ባይነት ምሳሌም ሆነ ልጁ በዚህ ረገድ ያሳየውን ምሳሌነት ማጥናት ያስፈልገናል። በዚህ መንገድ ከልብ ይቅር ማለትን ልንማር እንችላለን።
ሆኖም አንዳንዶች ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜስ ምን ማድረግ ይቻላል? ሁሉም ዓይነት ኃጢአቶች ይቅር መባል አለባቸውን? የሚሉ ተገቢ ጥያቄዎችን ሊያነሡ ይችላሉ።
ሚዛናዊ ለመሆን መጣር
አንድ ሰው ከባድ በደል ሲፈጸምበት የሚሰማው ሐዘን ጥልቅ ሊሆን ይችላል። በተለይም ምንም ጥፋት ሳያጠፋ ከባድ በደል ከተፈጸመበት በጣም ሊያዝን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች ‘በተንኮል ያታለለኝንና የበደለኝን ሰው እንዴት ይቅርታ ላደርግለት እችላለሁ?’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ሊያስወግድ የሚችል ከባድ በደል በሚፈጸምበት ጊዜ ተበዳዩ በማቴዎስ 18:15–17 ላይ ያለውን ምክር መጠቀም ሊያስፈልገው ይችላል።
በማንኛውም ሁኔታ መወሰድ ያለበት እርምጃ በአብዛኛው በበዳዩ ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል። በደሉን ከፈጸመ ወዲህ ከልቡ ንስሐ መግባቱን የሚጠቁም ነገር አለን? በደሉን የፈጸመው ሰው ተለውጧልን? አልፎ ተርፎም ከልቡ ተነሳስቶ የፈጸመውን ስሕተት የሚያካክስ ነገር ለማድረግ ሞክሯልን? እጅግ የሚሰቀጥጥ ኃጢአት በሚፈጸምበትም ጊዜ እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ንስሐ በይሖዋ ፊት ይቅር ባይነትን የሚያስገኝ ቁልፍ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በእስራኤል ታሪክ እጅግ መጥፎ ድርጊት ከፈጸሙት ነገሥታት መካከል አንዱ የሆነውን ምናሴን ይቅር ብሎታል። ለይቅርታው መሠረት የሆነው ነገር ምን ነበር? አምላክ እንዲህ ሊያደርግ የቻለበት ምክንያት ምናሴ በመጨረሻ ራሱን ዝቅ በማድረጉና ይከተለው ከነበረው መጥፎ አካሄድ በመመለሱ ነው።—2 ዜና መዋዕል 33:12, 13
መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት እውነተኛ ንስሐ በአመለካከት ላይ ልባዊ ለውጥ ማድረግንና በተፈጸመው ማንኛውም ዓይነት ስሕተት ከልብ መጸጸትን የሚያካትት ነው። ተገቢና የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ንስሐ ከመግባት በተጨማሪ ተበዳዩን ለመካስ ጥረት ይደረጋል። (ሉቃስ 19:7–10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:11) እንዲህ ዓይነት ንስሐ ካልታየ ግን ይሖዋ ይቅር አይልም።a ከዚህም በላይ በአንድ ወቅት መንፈሳዊ እውቀት የነበራቸውን አሁን ግን አንዳችም ዓይነት የንስሐ ፍሬ ሳያሳዩ ሆን ብለው መጥፎ ተግባር መፈጸማቸውን የቀጠሉ ሰዎችን ይቅር እንዲሉ አምላክ ክርስቲያኖችን አይጠይቅባቸውም። (ዕብራውያን 10:26–31) ይቅርታ ሊደረግላቸው የማይገቡ እጅግ የከፉ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ።—መዝሙር 139:21, 22፤ ሕዝቅኤል 18:30–32
ይቅርታ ማድረግ የሚቻል ሆነም አልሆነ ከባድ በደል የተፈጸመበት ሰው ‘ችግሩ ሙሉ በሙሉ እስኪፈታ ድረስ ከባድ የስሜት መረበሽ፣ እጅግ የመጎዳት ስሜትና ንዴት ሊሰማኝ ይገባልን?’ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል። አንድ ምሳሌ ተመልከት። ንጉሥ ዳዊት የጦር አዛዡ ኢዮአብ “ከእርሱ [ከኢዮአብ] የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች” አበኔርንና አሜሳይን በግፍ በመግደሉ እርር ድብን ብሎ ነበር። (1 ነገሥት 2:32) ዳዊት ቁጣውን በቃላት ገልጿል፤ ለይሖዋም በጸሎት እንደገለጸ አያጠራጥርም። ይሁንና በቁጣ ገንፍሎ የነበረው የዳዊት ስሜት ከጊዜ በኋላ የሰከነ ይመስላል። እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ በቁጣ ስሜት አልተብከነከነም። እንዲያውም ዳዊት ከኢዮአብ ጋር መሥራቱን ቀጥሏል፤ ሆኖም ይህን ንስሐ ያልገባ ነፍሰ ገዳይ እንዲሁ ይቅር አላለውም። ዳዊት መጨረሻ ላይ ፍትሐዊ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል።—2 ሳሙኤል 3:28–39፤ 1 ነገሥት 2:5, 6
ሌሎች በፈጸሙባቸው ከባድ በደል ሳቢያ የተጎዱ ሰዎች መጀመሪያ ላይ የተሰማቸው ንዴት እስኪበርድላቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜና ጥረት ሊጠይቅ ይችላል። በዳዩ ሰው ስሕተቱን አምኖ ሲቀበልና ንስሐ ሲገባ ከንዴት የማገገሙ ሂደት የቀለለ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ምንም ነገር ሳያጠፋ በደል የተፈጸመበት ሰው በዳዩ ምንም አደረገ ምን ስለ ይሖዋ ፍትሕና ጥበብ ባለው እውቀትና በክርስቲያን ጉባኤ መጽናናት ይኖርበታል።
አንድን በደለኛ ይቅር ስትለው በደሉን ተቀብለኸዋል ማለት እንዳልሆነም ተገንዘብ። አንድ ክርስቲያን ይቅር አለ ሲባል ጉዳዩን በእምነት ለይሖዋ ተወው ማለት ነው። ይሖዋ የመላው ጽንፈ ዓለም ጻድቅ ፈራጅ ነው፤ ፍትሕንም በተገቢው ጊዜ ላይ ይሰጣል። ይህም በአታላዮቹ ‘ሴሰኞችና አመንዝሮች’ ላይ መፍረድን ይጨምራል።—ዕብራውያን 13:4
ይቅር ማለት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
መዝሙራዊው ዳዊት “አቤቱ፣ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ [ይቅር ለማለት ዝግጁ አዓት] ነህና፣ ምሕረትህም [ፍቅራዊ ደግነትህም አዓት] ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 86:5) አንተስ ልክ እንደ ይሖዋ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” ነህን? ይቅር ባይነት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ብዙ ናቸው።
በመጀመሪያ ደረጃ ሌሎችን ይቅር ማለት ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በእርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግም በክርስቶስ [በነፃ አዓት] ይቅር እንዳላችሁ [በነፃ አዓት] ይቅር ተባባሉ” በማለት ክርስቲያኖችን ያሳስባቸዋል።—ኤፌሶን 4:32
በሁለተኛ ደረጃ ይቅር ባይነት ሰላምን ያስገኛል። ይህም ከሰዎች ጋር የሚኖረን ሰላም ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ሰላም ማግኘትንም ይጨምራል።—ሮሜ 14:19፤ ቆላስይስ 3:13–15
በሦስተኛ ደረጃ ሌሎችን ይቅር ማለታችን እኛ ራሳችን ይቅር መባል እንደሚያስፈልገን ያስታውሰናል። አዎን፣ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል።”—ሮሜ 3:23
በመጨረሻም ሌሎችን ይቅር ማለታችን ኃጢአታችን በአምላክ ይቅር እንዲባልልን ጥርጊያውን ያመቻቻል። ኢየሱስ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና” ብሏል።—ማቴዎስ 6:14
ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ከቀትር በኋላ በነበረው ጊዜ በአእምሮው ውስጥ ይመላለሱ የነበሩትን ብዙ ነገሮች እስቲ አስብ። ስለ ደቀ መዛሙርቱ፣ ስለ ስብከቱ ሥራና በተለይም ለይሖዋ ፍጹም አቋሙን ጠብቆ ስለ መገኘቱ አጥብቆ ያስብ ነበር። ሆኖም በመከራው እንጨት ላይ ሆኖ በጣም እየተሠቃየ እንኳ ምን ብሎ ተናግሯል? መጨረሻ ላይ ከተናገራቸው ቃላት መካከል “አባት ሆይ . . . ይቅር በላቸው” የሚሉት ቃላት ይገኙበታል። (ሉቃስ 23:34) እኛም እርስ በርሳችን ከልብ ይቅር በመባባል የኢየሱስን ፍጹም ምሳሌ ልንኮርጅ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህ ሰው ይቅርታ ሊደረግለት ይገባል ወይም አይገባም ብሎ ሲወስን ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ መጥፎ ድርጊት የፈጸመ ሰው የአምላክን የአቋም ደረጃዎች የማያውቅ ከሆነ የኃጢአቱን ሸክም ሊቀንስለት ይችላል። ኢየሱስ የገደሉትን ሰዎች አባቱ ይቅር እንዲላቸው በጠየቀ ጊዜ የሰቀሉትን የሮማ ወታደሮች ማለቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። “የሚያደርጉትን አያውቁም” ነበር፤ እርሱ በእርግጥ ማን እንደሆነ አላወቁም። ከግድያው በስተጀርባ የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ግን የበለጠ በደል ፈጽመዋል። ከእነርሱ መካከል ብዙዎቹ ይቅርታ ሊያገኙ አይችሉም።—ዮሐንስ 11:45–53ን ከሥራ 17:30 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ይቅር ስላላለው ባሪያ የተናገረው ምሳሌ ምን ቁም ነገር እንዳዘለ ገብቶሃልን?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌሎችን ይቅር ማለት ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል፤ ደስታንም ያስገኛል