ሙታንን መፍራት በጣም ተስፋፍቷል
ጀንበሯ ከጠለቀች ሰዓታት ተቆጥረዋል። ለመመለስ ካሰብክበት ሰዓት ትንሽ ዘግየት ብለህ ወደ ቤትህ እየተመለስክ ነው። በአካባቢው ወዳለ መካነ መቃብር ስትደርስ ልብህ ምቱን ይጨምራል። ረጭ ያለው የምሽት ጨለማ እምብዛም የማይሰሙ ድምፆችን ሁሉ እንድትሰማ ያደርግሃል። ድንገት ከርቀት የሚሰቀጥጥ እንግዳ የሆነ ድምፅ ትሰማለህ። በዚህ ጊዜ ቤትህን ተገን ለማድረግ በፍጥነት መራመድ ትጀምራለህ።
በመካነ መቃብር ውስጥ ወይም አጠገብ ስትሆን ፍርሃት ፍርሃት ብሎህ ያውቃልን? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ በዓለም ዙሪያ የተስፋፋው የሙታን መናፍስት ሕያዋንን ሊረዱ አለዚያም ሊጎዱ ይችላሉ የሚለው ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳብ ተጽእኖ አድርጎብህ ሊሆን ይችላል።
ሙታን የሕያዋንን እርዳታ ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ወይም የሚፈልጓቸውን ነገሮች ካላሟሉላቸው በሕይወት ያሉትን ሰዎች ሊጎዷቸው ይችላሉ በሚለው እምነት ሳቢያ ብዙ የአጉል እምነት ልማዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መጥተዋል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገሮች ብዙዎች በአንድ አደጋ የሞተ ሰው በተቀበረበት ቦታ በላዩ መስቀል ያለበት በጣም አነስተኛ ቤት የመሥራት ልማድ አላቸው። ሰዎች ለሞተው ሰው እንደሚያስቡ ለመግለጽ ወይም የሞተውን ሰው ነፍስ ወይም መንፈስ ለመርዳት በመቃብሩ ላይ ሻማ ያበራሉ፤ እንዲሁም አበባ ያስቀምጣሉ። አንዳንድ ጊዜ ለጸሎቶች ስለተሰጡ “ተአምራዊ” መልሶች የሚገልጽ ወሬ ይናፈሳል፤ በዚህም ሳቢያ ሰዎች የሞተው ሰው ነፍስ ወይም መንፈስ አነስተኛ መኖሪያ ወደሆነችው አኒሚታ አዘውትረው መሄድ ጀምረዋል። እዚያም ከሄዱ በኋላ የሞተው ሰው አንድ ነገር እንዲሳካላቸው ወይም እንዲያገኙ ከረዳቸው (ምናልባትም የሚጠይቁት ነገር ተአምራዊ ፈውስ ሊሆን ይችላል) ምስጋናቸውን ልዩ በሆነ መንገድ እንደሚገልጹለት ማንዳስ ወይም ቃል ይገባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የሞተው ሰው ነፍስ በውድቅት ሌሊት በመታየት በሕይወት ያሉትን ታስፈራራለች የሚል ወሬም ሊሰማ ይችላል። በተለምዶ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ነፍሳት ቀደም ሲል ተከናውነው በነበሩ ነገሮች ሳቢያ ሕያዋንን የሚያበሳጩ ፔናንዶ ናቸው ይባላል።
በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች የሙታንን “መናፍስት” ደስ ለማሰኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ድል ያለ ድግስ ይደገሳል፤ መሥዋዕቶች ይቀርባሉ፤ የሞተውን ሰው መንፈስ የሚያለዝቡ ነገሮችን ይናገራሉ። ይህ ሁሉ የሚደረገው የሞተው ሰው መንፈስ የሚወስደውን የበቀል እርምጃ ለመግታት ተብሎ ነው። የሞተውን ሰው መንፈስ ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረግ ቁጣውን ማብረድ በሕይወት ለቀሩት ሰዎች ካሣና በረከት ያስገኛል ተብሎ ይታመናል።
“ብዙ ሰዎች ‘እንዲሁ በተለምዶ ወይም በተፈጥሮ’ የሚከሰት አንድም ክስተት የለም ብለው ያምናሉ” በማለት አንድ በአፍሪካ ውስጥ የወጣ ሪፖርት ገልጿል። “በሽታ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ መካንነት፣ የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ የሚያስከትል ዶፍ ዝናብ ወይም ሐሩር ፀሐይ፣ ድንገተኛ የሆኑ አደጋዎች፣ የቤተሰብ መከፋፈልም ሆነ ሞት በአጠቃላይ ማንኛውም ክንውን የሚከሰተው ከሰው በላይ ኃይል ባላቸው የማይታዩ መናፍስት አማካኝነት ነው ተብሎ ይታመናል።” አንድ ሌላ ሪፖርት ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸው መናፍስት በሰማይ ቦታ ይዘው በምድር ያሉ ዘመዶቻቸውን ያለማቋረጥ በንቃት እንደሚከታተሉ አድርገው ያምናሉ። የቀድሞ አባቶች በምድር ያሉት ዘመዶቻቸው ለሞቱት ከበሬታ የሚያሳዩ ከሆነ እነርሱን ሊባርኩና ሊጠብቁ የሚችሉበት አሊያም የሞቱትን ቸል የሚሉ ከሆነ ደግሞ ሊቀጡ የሚችሉበት ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አግኝተዋል ተብሎ ይታመናል።”
ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው እምነት ከአምላክ ቃል ጋር ይስማማልን? አንተስ በዚህ ረገድ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቺሊ የሚገኝ አንድ “አኒሚታ”