ኢየሱስ ያስተምር በነበረበት መንገድ ታስተምራለህን?
“ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።”—ማቴዎስ 7:28, 29
1. ኢየሱስ በገሊላ ሲያስተምር እነማን ተከተሉት? ኢየሱስ ያሳየውስ ምላሽ ምን ነበር?
ኢየሱስ በሄደበት ሁሉ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር። “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።” ያከናወናቸውን ነገሮች የሚገልጽ ወሬ በየአካባቢው ሲናፈስ “ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።” (ማቴዎስ 4:23, 25) ኢየሱስም ባያቸው ጊዜ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” ሲያስተምራቸው ለእነርሱ የነበረውን ጥልቅ ኀዘንና ከልብ የመነጨ የመውደድ ስሜት መረዳት ይችሉ ነበር። ወደ እርሱ እንዲሳቡ ያደረጋቸው ይህ ስሜት የሚጠዘጥዛቸውን ቁስል እንደሚያበርድላቸው ቅባት ያህል ሆኖላቸው ነበር።—ማቴዎስ 9:35, 36
2. ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት ሌላ ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ እንዲሳቡ ያደረጋቸው ነገር ምን ነበር?
2 ኢየሱስ የፈጸማቸው አካላዊ ፈውሶች እጅግ አስደናቂ ተአምራት ነበሩ! ለምጻሞችን አንጽቷል፣ መስማት የተሳናቸውን ጆሮዎች ከፍቷል፣ የዓይነ ስውራንን ዓይን አብርቷል፣ አንካሶች መራመድ ችለዋል፣ ሙታንን እንደገና ሕያው አድርጓቸዋል። በእርግጥም የይሖዋ ኃይል በኢየሱስ በኩል ሲሠራ የታየባቸው እነዚህ ትኩረትን የሚማርኩ ትዕይንቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ስበው መሆን አለበት! ይሁን እንጂ ሰዎቹ የተሳቡት በእነዚህ ተአምራት ብቻ አልነበረም። ኢየሱስ ሲያስተምር ይከናወን የነበረውን መንፈሳዊ ፈውስም ለማግኘት ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተዋል። ለምሳሌ ያህል ዝነኛ የተራራ ስብከቱን ከሰሙ በኋላ ያሳዩትን ምላሽ እስቲ ልብ በሉ፦ “ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።” (ማቴዎስ 7:28, 29) ረቢዎቻቸው [የአይሁድ መምህራን] ትምህርቶቻቸውን ለመደገፍ ከጥንት ረቢዎች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ወግና ልማድ ይጠቅሱላቸው ነበር። ኢየሱስ ግን አምላክ የተናገረውን እየጠቀሰ ያስተምራቸው ነበር፦ “እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።”—ዮሐንስ 12:50
ትምህርቶቹ ወደ ልብ ዘልቀው የሚገቡ ነበሩ
3. ኢየሱስ መልእክቱን ያቀረበበት መንገድ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከሚያስተምሩበት መንገድ የሚለየው እንዴት ነው?
3 በኢየሱስ ትምህርቶችና በጻፎችና በፈሪሳውያን ትምህርቶች መካከል ያለው ልዩነት በይዘታቸው ብቻ አልነበረም። ይህም ማለት ልዩነቱ የኢየሱስ ትምህርቶች አምላክ የተናገራቸው እውነቶች መሆናቸው የእነርሱ ግን ከሰው የመነጨ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሸክም የሆነ ወግና ልማድ መሆኑ ብቻ አልነበረም ማለት ነው። የትምህርት አቀራረባቸውም የተለያየ ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያን ጠብራሮችና ለሌላው ምንም ደንታ የሌላቸው፣ በትዕቢት ተወጥረው በማዕረግ ስሞች መወደስ የሚፈልጉ እንዲሁም ሕዝቡን እንደ “ርጉም” አድርገው በማየት የሚንቁ ነበሩ። ኢየሱስ ግን ገር፣ የዋህ፣ ደግ፣ የሰውን ችግር የሚረዳና ብዙውን ጊዜ እሺ ባይ እንዲሁም ለእነርሱ ጥልቅ ኀዘን የሚሰማው ነበር። ኢየሱስ ያስተምር የነበረው ትክክለኛ ቃላትን በመጠቀም ብቻ አልነበረም፤ ከልቡ እየፈለቁ ወደ አድማጮቹ ልብ ውስጥ ይንቆረቆሩ በነበሩ ለዛ ያላቸው ቃላትም ይጠቀም ነበር። አስደሳች መልእክቱ ሰዎች ወደ እርሱ እንዲሳቡ፣ እሱን ለመስማት ማልደው ወደ ቤተ መቅደስ እንዲመጡና በሄደበት ሁሉ እንዲከተሉት እንዲሁም ደስ እያላቸው እንዲያዳምጡት አድርጓቸዋል። “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” እያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እሱን ለመስማት ይመጡ ነበር።—ዮሐንስ 7:46–49፤ ማርቆስ 12:37፤ ሉቃስ 4:22፤ 19:48፤ 21:38
4. ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ስብከት እንዲሳቡ ያደረጋቸው በተለይ ምን ነበር?
4 ሰዎቹ በትምህርቱ ሊሳቡ የቻሉበት አንደኛው ምክንያት የምሳሌ አጠቃቀሙ እንደሆነ አያጠራጥርም። ኢየሱስ ያያቸው ነገሮች ሌሎች ሰዎች ካዩአቸው ነገሮች የተለዩ አልነበሩም። ሆኖም ኢየሱስ እነርሱ ፈጽሞ ያላስተዋሏቸውን ነገሮች አስተውሎ ነበር። በሜዳ የሚበቅሉትን አበቦች፣ ጎጆአቸውን የሚሠሩ ወፎችን፣ ዘር የሚዘሩ ሰዎችን፣ የባዘኑ በጎችን ፈልገው የሚያመጡ እረኞችን፣ ያረጁ ልብሶችን የሚጥፉ ሴቶችን፣ በገበያ ቦታ የሚጫወቱ ልጆችን፣ በመረቦቻቸው ዓሣ የሚያጠምዱ ሰዎችን የመሰሉ ሁሉም ሰው የሚያያቸው በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ነገሮች ለኢየሱስ የተለመዱ ተራ ነገሮች አልነበሩም። አምላክንና መንግሥቱን በምሳሌ ለማስረዳት ወይም በዙሪያው ስላለው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ አንድ የሆነ ነጥብ ለመግለጽ በማንኛውም ቦታ የሚያያቸውን ነገሮች እንዴት ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ያስብ ነበር።
5. የኢየሱስ ምሳሌዎች በምን ላይ የተመሠረቱ ነበሩ? ምሳሌዎቹን ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረገውስ ምን ነበር?
5 የኢየሱስ ምሳሌዎች ሰዎች ብዙ ጊዜ በተመለከቷቸው በየዕለቱ በሚታዩ ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። እውነት ከእነዚህ የተለመዱ ነገሮች ጋር ተጣምሮ ሲቀርብ ደግሞ በሚያዳምጡት ሰዎች አእምሮ ላይ ወዲያውኑ ይቀረጻል። ይህን የመሰሉ እውነቶች እንዲሁ የተሰሙ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ በአእምሮ ውስጥ የተቀረጹ ምስሎች ይሆናሉ። ከጊዜ በኋላም ለማስታወስ አይቸግሩም። የኢየሱስ ምሳሌዎች ልዩ ባሕርይ ነበራቸው። በቀላሉ የሚገቡ እንዲሁም ነገሮችን በሚያወሳስቡና ሰዎች እውነትን ለመረዳት እንዲቸገሩ በሚያደርጉ አላስፈላጊ ሐሳቦች ያልተሞሉ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ለምሳሌ ያህል ሰው ወዳድ የሆነውን ሳምራዊ ምሳሌ ተመልከት። መልካም ባልንጀራ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታይሃል። (ሉቃስ 10:29–37) ኢየሱስ የሁለት ልጆችን ምሳሌም ሰጥቷል። አንደኛው በወይኑ የአትክልት ስፍራ አልሠራም ካለ በኋላ ተመልሶ የሠራው ሲሆን ሌላው ደግሞ እሠራለሁ ብሎ ሳይሠራ የቀረው ልጅ ነው። ታዛዥነት ሲባል ዋናው ተፈላጊ ነገር የታዘዙትን ሥራ መሥራት እንደሆነ ወዲያውኑ መረዳት ትችላለህ። (ማቴዎስ 21:28–31) አፍ የሚያስከፍተውን የኢየሱስ ትምህርት እየሰማ እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለው ወይም ሽርሽር የሚሄድ አእምሮ አልነበረም። አእምሮአቸው በመስማትም ሆነ በማየት ተጠምዶ ነበር።
ፍቅር የሚያስገድድ ሆኖ ሲያገኘው ኢየሱስ እሺ ባይ ይሆን ነበር
6. ምክንያታዊ ወይም እሺ ባይ መሆን ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆነው መቼ ነው?
6 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምክንያታዊነት ሲናገር የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ በተደጋጋሚ ይህ ቃል እሺ ባይ መሆን ማለት እንደሆነ ያሳያል። አንድ ሰው ለሠራው ስሕተት በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገ ሌላ ነገር ካለ አምላካዊ ጥበብ እሺ ባይ ትሆናለች። አንዳንድ ጊዜ ምክንያታዊ ወይም እሺ ባዮች መሆን አለብን። ሽማግሌዎች ፍቅር በሚያስገድድበት ጊዜና የንስሐው ፍሬ በቂ መሠረት ሆኖ ሲገኝ ውሳኔን ለማላላት ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:3፤ ያዕቆብ 3:17) ኢየሱስ ምሕረትና ርኅራኄ አስገዳጅ በሚሆኑበት ጊዜ አጠቃላይ ከሆኑ ደንቦች ወጣ ያሉ ነገሮችን በማድረግ ግሩም የእሺ ባይነት ምሳሌዎችን ትቷል።
7. ኢየሱስ እሺ ባይ መሆኑን ያሳየባቸው አንዳንድ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
7 ኢየሱስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ቢክደውም እንኳ ኢየሱስ ዓይንህን ላፈር አላለውም። ጴጥሮስ ለፈጸመው ስሕተት በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገ ሌላም ነገር ነበር፤ ኢየሱስም ይህን ግምት ውስጥ እንዳስገባው ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 10:33፤ ሉቃስ 22:54–62) ብዙ ደም ይፈሳት የነበረችው የረከሰችው ሴትም ከሕዝቡ ጋር በመቀላቀል የሙሴን ሕግ በጣሰች ጊዜ ለፈጸመችው ስሕተት በከፊል ምክንያት የሚሆን ነገር ነበራት። ኢየሱስ እሷንም ቢሆን አልኮነናትም። ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ተረድቶላት ነበር። (ማርቆስ 1:40–42፤ 5:25–34፤ በተጨማሪም ሉቃስ 5:12, 13ን ተመልከት።) ኢየሱስ ሐዋርያት እርሱ መሲሕ ነው እያሉ እንዳይናገሩ አሳስቧቸው ነበር፤ ሆኖም በውኃው ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት መሲሕ መሆኑን ሲነግራት ከዚህ ደንብ ጋር ሙጭጭ አለማለቱን አሳይቷል። (ማቴዎስ 16:20፤ ዮሐንስ 4:25, 26) በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ፍቅር፣ ምሕረትና ርኅራኄ ግትር አለመሆንን ተገቢ አድርገውታል።—ያዕቆብ 2:13
8. ጻፎችና ፈሪሳውያን ደንቦችን ላላ ያደርጉ የነበረው መቼ ነበር? የማያላሉትስ መቼ ነበር?
8 እሺ ባይነት የሚባል ነገር የማያውቁት ጻፎችና ፈሪሳውያን ግን ከዚህ የተለዩ ነበሩ። ለራሳቸው ሲሆን ከብቶቻቸውን ውኃ ለማጠጣት የሰንበት ወጋቸውን ያፈርሱ ነበር። ወይም ደግሞ ከብታቸው አሊያም ልጃቸው ጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅ ከጉድጓዱ ለማውጣት ሲሉ የሰንበትን ሕግ ያፈርሱ ነበር። ሆኖም ተራውን ሕዝብ ውልፍት አያደርጉትም ነበር! “እነርሱ ግን [ብቃቶቹን] በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።” (ማቴዎስ 23:4፤ ሉቃስ 14:5) ኢየሱስ ሰዎችን ከአብዛኛዎቹ ደንቦች አስበልጦ ይመለከታቸው ነበር፤ ፈሪሳውያን ግን ደንቦችን ከሰዎች አስበልጠው ይመለከቱ ነበር።
“የትእዛዝ ልጅ” መሆን
9, 10. የኢየሱስ ወላጆች ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላ ኢየሱስን ያገኙት የት ነው? የኢየሱስ አጠያየቅ ምን ያዘለው ቁም ነገር አለ?
9 አንዳንዶች ኢየሱስ በልጅነቱ ካሳለፋቸው ነገሮች መካከል ተዘግቦ የምናገኘው በአንድ ወቅት የተከናወነውን ነገር ብቻ ነው የሚል ቅሬታ ያሰማሉ። ሆኖም ብዙዎች ያ ክንውን የያዘውን ታላቅ ትርጉም ሳይገነዘቡት ይቀራሉ። ይህ ክንውን በሉቃስ 2:46, 47 ላይ ተዘግቦልናል፦ “ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ።” በኪትል የተዘጋጀው ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት “ሲጠይቃቸውም” ለሚለው የገባው የግሪክኛ ቃል በዚህ አገባቡ ያለው ትርጉም አንድ ልጅ ለማወቅ ያለውን ጉጉት ብቻ የሚያመለክት አለመሆኑን ይገልጻል። ቃሉ የፍርድ ምርመራ ለማድረግና አንድን ጉዳይ መርምሮ ለማግኘት የሚቀርቡትን ጥያቄዎች፣ መስቀለኛ ጥያቄዎችንና አልፎ ተርፎም በማርቆስና 10:2ና በ12:18–23 ላይ ያሉትን የመሰሉ “ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ያቀርቧቸው የነበሩትን መሠሪ የምርመራ ጥያቄዎችም” ሊያመለክት ይችላል።
10 ይኸው መዝገበ ቃላት እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ከዚህኛው የቃሉ አገባብ አንጻር [ሉቃስ] 2:46 ልጁ ለማወቅ ካለው ጉጉት የተነሣ ያነሣው ጥያቄ መሆኑን እምብዛም አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ግቡን የመታ ክርክር ማድረጉን የሚያመለክት ነው . . . ሊባል ይቻላል። [ቁጥር] 47 ግቡን የመታ ክርክር አድርጓል ከሚለው ሐሳብ ጋር በደንብ ይስማማል።”a የሮዘርሃም ትርጉም ቁጥር 47ን እሰጥ አገባ እንደተካሄደበት ድራማ አድርጎ አቅርቦታል፦ “ሲናገር የሰሙት ሁሉ በማስተዋሉና በመልሶቹ ተደንቀው ይህስ እንዴት ያለው ጉድ ነው አሉ።” በሮበርትሰን የተዘጋጀው ወርድ ፒክቸርስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ በጣም ተገርመው ነበር ሲባል “ዓይኖቻቸው እስኪፈጡ ድረስ በመገረም ይህስ እንዴት ያለው ጉድ ነው” ብለው ነበር ማለት ነው ይላል።
11. ማርያምና ዮሴፍ ባዩትና በሰሙት ነገር ምን ስሜት ተሰማቸው? አንድ ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪስ ምን ሐሳብ ሰጠ?
11 በመጨረሻ የኢየሱስ ወላጆች ወደ ትዕይንቱ መድረክ ሲመጡ “ተገረሙ።” (ሉቃስ 2:48) ሮበርትሰን እዚህ ቦታ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል በዚህ አገባቡ “መምታት፣ ገፍትሮ ማስወጣት” ማለት ነው ብለዋል። አክለውም ዮሴፍና ማርያም የሰሙትና ያዩት ነገር “ጭንቅላታቸውን መቷቸው ነበር” ብለዋል። ኢየሱስ ገና በዚህ ዕድሜው ድንቅ መምህር ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል። በቤተ መቅደሱ ውስጥ በተከናወነው በዚህ ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ የኪትል መጣጥፍ “ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ በመጨረሻ እጃቸውን የሚሰጡበትን ግጭት ገና ከልጅነቱ ቆስቁሶታል” ብሏል።
12. ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ያደረገው ውይይት ምን ልዩ ባሕርይ ነበረው?
12 ደግሞም እጃቸውን ሰጥተዋል! ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ፈሪሳውያንን “ከዚያን ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው” የሚደፍር እስኪጠፋ ድረስ ድል የነሣቸው ይህን በመሰለው አጠያየቅ ነው። (ማቴዎስ 22:41–46) ሰዱቃውያንም ልክ እንደዚሁ በትንሣኤ ጥያቄ አፋቸውን ይዘዋል፤ “ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም።” (ሉቃስ 20:27–40) ጻፎችም ከዚህ የተሻለ ዕጣ አልገጠማቸውም። ከእነርሱ መካከል አንዱ አንድ ጥያቄ አንሥቶ ከኢየሱስ ጋር ከተወያዩ በኋላ ኢየሱስን “ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።”—ማርቆስ 12:28–34
13. በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተከናወነውን ነገር በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ትርጉም እንዲኖረው ያደረገው ምንድን ነው? ይህስ ሌላ ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?
13 ኢየሱስ በልጅነቱ ካሳለፋቸው ነገሮች መካከል እርሱና በቤተ መቅደሱ የሚገኙ መምህራን ያካሄዱት ይህ ውይይት ብቻ ተመርጦ ለታሪክ የበቃው ለምንድን ነው? ይህ ወቅት በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ስለነበረ ነው። 12 ዓመት ገደማ ሲሆነው አይሁዶች “የትእዛዝ ልጅ” ብለው የሚጠሩት ማለትም ሕግጋቱን ሙሉ በሙሉ ማክበር የሚጠበቅበት ልጅ ሆኖ ነበር። ማርያም ኢየሱስን በእሱ ምክንያት እሷና ዮሴፍ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስትነግረው የመለሰላት መልስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተወለደበትን ሁኔታና ወደፊት መሲሕ እንደሚሆን ተገንዝቦ እንደነበረ ይጠቁማል። አባቱ አምላክ መሆኑን በማያሻማ መንገድ መናገሩ ይህን የሚያሳይ ነው፦ “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተዘገቡት የመጀመሪያዎቹ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው። ይሖዋ እርሱን ወደ ምድር የላከበትን ዓላማ እንዳወቀ ይጠቁማሉ። በመሆኑም ይህ አጭር የታሪኩ ምዕራፍ ትልቅ ትርጉም ካዘሉት ክንውኖች አንዱ ነው።—ሉቃስ 2:48, 49
ኢየሱስ ልጆችን ይወዳቸዋል፤ ስሜታቸውንም ይረዳላቸዋል
14. ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ጊዜ በቤተ መቅደሱ ስላደረገው ነገር የሚናገረው ታሪክ ወጣቶች ምን ምን አስደሳች ነጥቦችን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል?
14 ይህ ዘገባ በተለይ የወጣቶችን ስሜት በጣም የሚቀሰቅስ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ ወደ ጉልምስና እያደገ በነበረበት ጊዜ ምን ያህል በትጋት ያጠና እንደነበረ ያሳያል። በቤተ መቅደሱ ይገኙ የነበሩት ረቢዎች ይህ የ12 ዓመት ዕድሜ ያለው “የትእዛዝ ልጅ” በነበረው ጥበብ በጣም ተደንቀዋል። ሆኖም ኢየሱስ በዚህም ወቅት ከዮሴፍ ጋር በአናጢ ሱቅ ውስጥ እየሠራ ነበር፤ ለዮሴፍም ሆነ ለማርያም “ይታዘዝላቸውም ነበር።” “በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።”—ሉቃስ 2:51, 52
15. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ወጣቶችን ይደግፋቸው የነበረው እንዴት ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ ላሉት ወጣቶች ምን ትርጉም አለው?
15 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ወጣቶችን በጣም ይደግፋቸው ነበር፦ “የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፣ ተቆጥተው፦ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም፦ እሰማለሁ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።” (ማቴዎስ 21:15, 16፤ መዝሙር 8:2) ልክ እንደዚሁም ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ፍጹም አቋማቸውን የሚጠብቁትንና ለይሖዋ ምስጋና የሚያቀርቡትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ይደግፋቸዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ይህን ለማድረግ ሕይወታቸውን እስከ መሠዋት ደርሰዋል!
16. (ሀ) ኢየሱስ በመካከላቸው አንድን ሕፃን በማቆም ሐዋርያቱን ምን አስተማራቸው? (ለ) ኢየሱስ ለልጆች የሚሆን ጊዜ የዋጀው በየትኛው አንገብጋቢ የሕይወቱ ክፍል ላይ እያለም ነበር?
16 ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማንኛው ታላቅ እንደሚሆን በተከራከሩ ጊዜ ኢየሱስ ለ12ቱ እንዲህ አላቸው፦ “ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው። ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው አቅፎም፦ እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።” (ማርቆስ 9:35–37) ከዚህም በላይ ዘግናኝ መከራ ለመቀበልና የሞትን ጽዋ ለመጠጣት ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ባቀናበት ወቅት ልጆችን ለማነጋገር ጊዜ ዋጅቶ ነበር፦ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና” አለ። ከዚያም “አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።”—ማርቆስ 10:13–16
17. ኢየሱስ የልጆችን ስሜት መረዳት የማይቸግረው ለምንድን ነው? ልጆችስ እርሱን በተመለከተ ምን ነገር ማስታወስ አለባቸው?
17 ልጅ ሆኖ በአዋቂዎች መካከል መኖር ምን እንደሚመስል ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ከአዋቂዎች ጋር ኖሯል፤ ከእነርሱ ጋር ሠርቷል፤ ለእነርሱ መገዛት ምን ማለት እንደሆነ በራሱ ሕይወት አይቶታል፤ እንዲሁም ደስ የሚያሰኘውንና የመተማመን መንፈስ የሚሰጠውን በእነርሱ የመወደድንም ስሜት ቀምሷል። ልጆች ሆይ፣ ይህን ሁሉ ያሳለፈው ኢየሱስ ወዳጃችሁ ነው። ለእናንተ ሲል ሞቷል፤ ትእዛዛቱን ካከበራችሁ ለዘላለም ትኖራላችሁ።—ዮሐንስ 15:13, 14
18. በተለይ ውጥረት ወይም አደገኛ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ የትኛውን አስደሳች ሐሳብ ወደ አእምሮአችን ማምጣት ይኖርብናል?
18 ኢየሱስ ያዘዘውን መፈጸም የምናስበውን ያህል ከባድ አይደለም። ወጣቶች ሆይ፣ በማቴዎስ 11:28–30 ላይ እንደምናነበው ኢየሱስ ከእናንተም ሆነ ከማንም ሰው ጎን ነው፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ [ወይም “ቀንበሬን ከእኔ ጋር ተሸከሙ፤” የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ] ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” እስቲ አስበው፣ ይሖዋን እያገለገልክ በሕይወት ጎዳና ስትጓዝ ኢየሱስ ቀንበሩን ልዝብ ሸክሙንም ቀሊል በማድረግ ከጎንህ አብሮ እየተጓዘ ነው። ይህ ሁላችንንም የሚያስፈነድቅ ሐሳብ ነው!
19. ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን የማስተማሪያ መንገዶች በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች በየጊዜው መለስ ብለን ልናጤናቸው እንችላለን?
19 ኢየሱስ ያስተማረባቸውን ጥቂት መንገዶች ብቻ መለስ ብለን ከቃኘን በኋላ እኛም የምናስተምርበት መንገድ ልክ የእሱ ዓይነት ሆኖ አግኝተነው ይሆን? አካላዊ ሕመም ያለባቸውን ወይም መንፈሳዊ ጠኔ የያዛቸውን ሰዎች ስንመለከት ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶን ባለን አቅማችን ሁሉ እነርሱን ለመርዳት እንነሣሳለንን? ሌሎችን ስናስተምር የአምላክን ቃል ነው ወይስ እንደ ፈሪሳውያን የራሳችንን ሐሳብ ነው የምናስተምረው? የመንፈሳዊ እውነቶችን እውቀት ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስተላለፍ፣ በሰዎች አእምሮ ጓዳ ውስጥ ለማስቀመጥና ለመቅረጽ እንዲሁም ማራኪ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን በአካባቢያችን በየዕለቱ የሚከናወኑ ነገሮች በንቃት እንከታተላለንን? በአንዳንድ ሁኔታዎች የተነሣ ፍቅርና ምሕረት በተወሰኑ መመሪያዎች አጠቃቀም ረገድ እሺ ባይነትን በማሳየት ይበልጥ ተገቢ በሆነ መንገድ ሊገለጹ በሚችሉበት ጊዜ ደንቦቹን የሙጥኝ ከማለት እንታቀባለንን? ልጆችንስ? ልክ ኢየሱስ ያሳያቸውን ዓይነት አሳቢነትና ፍቅራዊ ደግነት እናሳያቸዋለንን? ልጆቻችሁ ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ጊዜ ያጠና በነበረበት መንገድ እንዲያጠኑ ታበረታቷቸዋላችሁን? ልክ እንደ ኢየሱስ የጸና አቋም ትወስዳላችሁን? ንስሐ የሚገቡትን ሰዎች ዶሮ ጫጩቶቿን እንደምትሰበስብ ሁለት እጃችሁን ዘርግታችሁ ለመቀበል ዝግጁዎች ናችሁን?—ማቴዎስ 23:37
20. አምላክን ስናገለግል በምን አስደሳች ሐሳብ ራሳችንን ልናጽናና እንችላለን?
20 ልክ ኢየሱስ ባስተማረበት መንገድ ለማስተማር ባለ አቅማችን ሁሉ የምንፍጨረጨር ከሆነ ‘ቀንበሩን ከእርሱ ጋር እንድንሸከም’ እንደሚያደርገን ምንም አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 11:28–30
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ከእርሱ በዕድሜ ይበልጡ ለነበሩት በተለይም ሁለት ጠጉር ላበቀሉት ሰዎችና ለካህናቱ ተገቢውን አክብሮት አሳይቷቸዋል ብለን የምናምንበት በቂ ምክንያት አለን።—ከዘሌዋውያን 19:32ና ከሥራ 23:2–5 ጋር አወዳድር።
ታስታውሳለህን?
◻ ኢየሱስን ብዙ ሰዎች የተከተሉት ለምን ነበር?
◻ አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ በአንዳንድ ደንቦች ረገድ ላላ ለማለት እሺ ባይነትን ያሳየው ለምን ነበር?
◻ ኢየሱስ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ከቤተ መቅደሱ አስተማሪዎች ጋር ካደረገው ውይይት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
◻ ኢየሱስ ከልጆች ጋር ከነበረው ግንኙነት ምን ትምህርቶች መቅሰም እንችላለን?